6. አላህ ብቸኛ ረዳት ወይስ ሌሎች ረዳቶችም አሉ?
ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡
አላህ ብቸኛ ረዳት፡–
ሱራ 9፡116 “አላህ የሰማያትና የምድር ንግስና የርሱ ብቻ ነው፡፡ ህያው ያደርጋል ይገድላልም፤ ለናንተም ከርሱ በቀር ጠባቂም ረዳትም የላችሁም”
ሌሎች ረዳቶችም አሉ፡–
ሱራ 5፡55 “ረዳታችሁ አላህና መልክተኛው እነዚያም ያመኑት ብቻ ናቸው…”
መልስ
“እረዳት” ተብሎ የተቀመጠው ቃል “ወሊይ” وَلِىّ ወይም “ነሲር” نَصِير ሲሆን የአላህ እረዳትነት በመጥቀም ሆነ ከጉዳት በማዳን፣ በማሞት ሆነ ሕያው በማድረግ፤ ለሰናይ ሥራ በመሸለምና ለእኩይ ሥራ በመቅጣት ነው። በዚህ ስሌት አላህ ብቻውን እረዳት ነው። ከእርሱ ሌላ እረዳት የለም፦
4፥123 ነገሩ በምኞታችሁና በመጽሐፉ ሰዎች ምኞት አይደለም፡፡ *መጥፎን የሚሠራ ሰው በእርሱ ይቀጣል፡፡ ለእርሱም ከአላህ ሌላ ጠባቂንም ረዳትንም አያገኝም*፡፡
4፥145 *መናፍቃን በእርግጥ ከእሳት በታችኛው አዘቅት ውስጥ ናቸው፡፡ ለእነርሱም ረዳትን አታገኝላቸውም*፡፡
4፥173 *እነዚያማ ያመኑት መልካሞችንም የሠሩት ምንዳዎቻቸውን ይሞላላቸዋል፡፡ ከችሮታውም ይጨምርላቸዋል፡፡ እነዚያን የተጠየፉትንና የኮሩትንማ አሳማሚን ቅጣት ይቀጣቸዋል፡፡ ከአላህም ሌላ ለእነርሱ ዝምድንና ረዳትን አያገኙም*፡፡
2፥107 አላህ የሰማያትና የምድር ንግሥና ለእርሱ ብቻ መኾኑን አታውቅምን? *ለእናንተም ከአላህ ሌላ ዘመድና ረዳት ምንም የላችሁም*።
9፥116 አላህ የሰማያትና የምድር ንግስና የእርሱ ብቻ ነው፡፡ *ሕያው ያደርጋል፤ ይገድላልም፡፡ ለእናንተም ከእርሱ በቀር ጠባቂም ረዳትም የላችሁም*፡፡
የወሊይ ብዙ ቁጥር “አውሊያ” أَوْلِيَاءَ ሲሆን ሰዎች እንደ አላህ ይረዱናል ብለው የሚይዟቸው እረዳቶች ብዙ ናቸው፤ ለምሳሌ የሚጠነቁሉና የሚያስጠነቁሉ ሰዎች ከአላህ ሌላ ይጠቅመኛል ይጎዳኛል ብሎ ሰይጣናትን ከአላህ ሌላ ረዳቶች አድርገው ይዘዋል፦
7፥30 ከፊሉን ወደ ቅን መንገድ መራ፡፡ ከፊሎቹም በእነርሱ ላይ ጥመት ተረጋግጦባቸዋል፡፡ *እነርሱ ሰይጣናትን ከአላህ ሌላ ረዳቶች አድርገው ይዘዋልና*፡፡ እነርሱም ቅኑን መንገድ የተመራን ነን ብለው ያስባሉ፡፡
ሰዎች በተጨማሪም ወደ ነቢያትንና መላእክትን ዱዓ በማድረግ ሲለማመኑ ከአላህ ሌላ ረዳቶች አድርገው ይዘዋል፦
18፥102 እነዚያ የካዱት *ባሮቼን ከእኔ ሌላ አማልክት አድርገው መያዛቸውን የማያስቆጣኝ አድርገው አሰቡን?* እኛ ገሀነምን ለከሓዲዎች መስተንግዶ አዘጋጅተናል፡፡
17፥56 *«እነዚያን ከእርሱ ሌላ የምትሏቸውን ጥሩ፡፡ ከእናንተም ላይ ጉዳትን ማስወገድን ወደ ሌላ ማዞርንም አይችሉም»* በላቸው፡፤
ሙሽሪኮች ጣዖቶቻቸውን ከአላህ ሌላ ይጠቅሙናል ይጎዱናል ብለው በማለት እረዳቶች አድርገው ይዘዋል፦
13፥16 «የሰማያትና የምድር ጌታ ማን ነው» በላቸው፡፡ «አላህ ነው» በል፡፡ *«ለነፍሶቻቸው ጥቅምንም ጉዳትንም የማይችሉን ረዳቶች ከእርሱ ሌላ ያዛችሁን»* በላቸው፡፡
29፥41 *የእነዚያ ከአላህ ሌላ ረዳቶችን የያዙ ሰዎች ምሳሌ ቤትን እንደ ሠራች ሸረሪት ብጤ ነው፡፡ ከቤቶችም ሁሉ በጣም ደካማው የሸረሪት ቤት ነው፡፡ ቢያውቁ ኖሮ አማልክት አድርገው አይግገዟቸውም ነበር*፡፡
ይህንን ያደረጉበት መረዳትንም በመከጀል፣ መከበሪያ እንዲኾኑዋቸው፣ መቃረቢያ ይኾኑ ዘንድ ከአላህ ሌላ አማልክት አድርገው ያዙ፦
36፥74 *መረዳትንም በመከጀል* ከአላህ ሌላ አማልክትን ያዙ፡፡
46፥28 *እነዚያም መቃረቢያ ይኾኑ ዘንድ ከአላህ ሌላ አማልክት አድርገው የያዙዋቸው አይረዷቸውም ኖሯልን?* በእርግጥ ከእነርሱ ራቁ፡፡ ይህም ውሸታቸውና በልማድ ይቀጥፉት የነበሩት ነው፡፡
19፥81 *ከአላህም ሌላ አማልክትን ለእነርሱ መከበሪያ እንዲኾኑዋቸው ያዙ*፡፡
“አሊሀህ” آلِهَةٌ ማለትም “አማልክት” የሚለው ቃል “አውሊያ” أَوْلِيَاءَ በሚለው ተለዋዋጭ ቃል”interchange” ሆኖ መጥቷል፦
42፥6 *እነዚያም ከእርሱ ሌላ ረዳቶችን የያዙ*፤ አላህ በእነርሱ ላይ ተጠባባቂ ነው፡፡ አንተም በእነርሱ ላይ ኀላፊ አይደለህም፡፡
25፥3 *ከሓዲዎች ከእርሱም ሌላ ምንንም የማይፈጥሩን፣ እነርሱም የሚፈጠሩን፣ ለነፍሶቻቸውም ጉዳትን ለመከላከል ጥቅምንም ለማምጣት የማይችሉን ሞትንና ሕይወትንም መቀስቀስንም የማይችሉን፣ አማልክት ያዙ*፡፡
21፥24 ይልቁንም *ከእርሱ ሌላ አማልክትን ያዙን?* «ማስረጃችሁን አምጡ፡፡
21፥21 *ይልቁንም ከምድር የኾኑን እነርሱ ሙታንን የሚያስነሱን አማልክት ያዙን?* የለም፡፡
ስለዚህ “ወሊይ” وَلِىّ የሚለው “ኢላህ” إِلَٰه ማለትም “አምላክ” በሚለው ከመጣ ከአላህ በቀር መፍጠር፣ ማሞት፣ ሕያው ማድረግ የሚችል እረዳት የለም ማለት ነው፦
42፥9 *ከእርሱ ሌላ እረዳቶችን ያዙን? እረዳቶች አይደሉም፡፡ አላህም እረዳት እርሱ ብቻ ነው፡፡ እርሱም ሙታንን ሕያው ያደርጋል፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው*፡፡
7፥3 ከጌታችሁ ወደ እናንተ የተወረደውን ተከተሉ፡፡ *ከአላህም ሌላ ረዳቶችን አትከተሉ*፡፡ ጥቂትን ብቻ ትገሰጻላችሁ፡፡
“ምእምንና ምእምናትም ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው” የተባሉበት አላህ በተባለበት ስሌትና ቀመር ሳይሆን አላህ እና መልእክተኛው ባስቀመጡት ሑክም በመልካም በማዘዝና ከመጥፎ በመከልከል ነው፦
9፥71 *ምእምንና ምእምናትም ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው፡፡ በደግ ነገር ያዛሉ፤ ከክፉም ይከለክላሉ*፡፡ ሶላትንም ይሰግዳሉ፡፡ ዘካንም ይሰጣሉ፡፡ *አላህንና መልክተኛውንም ይታዘዛሉ*፡፡ እነዚያን አላህ በእርግጥ ያዝንላቸዋል፡፡ አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና፡፡
3፥104 *ከእናንተም ወደ በጎ ነገር የሚጠሩ በመልካም ሥራም የሚያዙ ከክፉ ነገርም የሚከለክሉ ሕዝቦች ይኑሩ*፡፡ እነዚያም እነሱ የሚድኑ ናቸው፡፡
እሩቅ ሳንሄድ በቤተሰብ ደረጃ ወንድም ለወንድሙ እረዳት ይሆናል እኮ፤ ለምሳሌ ሙሳ ወንድሙን ሃሩንን እረዳት እንዲሆንለት አላህ ለምሎ ነበር፤ አላህም ልመናውን ሰምቶ እረዳት አደረገለት፦
28፥34 «ወንድሜም ሃሩን እርሱ ምላሱ ከእኔ የተባ ነው፡፡ እውነተኛነቴንም የሚያረጋግጥልኝ *እረዳት* ኾኖ ከእኔ ጋር ላከው፡፡ እኔ ሊያስተባብሉኝ እፈራለሁና፡፡»
30፥29 «ከቤተሰቦቼም ለእኔ *እረዳትን* አድርግልኝ፡፡
25፥35 በእርግጥም ለሙሳ መጽሐፍን ሰጠነው፡፡ ከእርሱም ጋር ወንድሙን ሃሩንን *እረዳት* አደረግንለት፡፡
እሺ ወገናችን ሐተታህ መቋጫ ያለው አይመስልም፡፡ ነገርን ማንዛዛት የጥሩ ሙግት ምልክት አይደለም፤ ጥቅስ ማንጋጋትም አንባቢን ከማሰልቸት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ያንተን ነጥብ ስንጨምቀው አላህ በነፍሳችን ጉዳይ ብቸኛ ረዳት ወይንም ዋሊ እንደሆነና ከነፍስ ጉዳይ ውጪ ባሉት ነገሮች ነቢያት፣ አማኞችና ሌሎች ፍጥረታት የሰው ረዳቶች (አውሊያ) ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው፡፡ ቁርኣን ሱራ 18፡102 ላይ ሰዎችን ከወቀሰባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የአላህን ባርያዎች ረዳቶቻቸው አድርገው በመያዛቸው ነው፡፡
ጉዳዩ እንደርሱ ከሆነ ሱራ 5፡55 ላይ “ረዳታችሁ አላህና መልክተኛው እነዚያም ያመኑት ብቻ ናቸው…” ስለሚል አላህ ከፍጥረቱ ጋር ተዳብሎ ረዳት ሆኖ መቅረቡ ጥያቄን ያጭራል፡፡ አላህ ረዳት የተባለው ፍጥረታት በተባሉት መንገድ ካልሆነ ስለምን ከፍጥረት ጋር ተደብሎ “ረዳታችሁ” (ዋሊዩኩም) ተብሎ ቀረበ? የረዳትነት መደቡ ከፍጥረት ጋር የሚመደብ ከሆነስ ሱራ 9፡116 ላይ ለምን ብቸኛ ረዳት ተባለ?
አላህ በነፍሳችን ጉዳይ ብቸኛ ረዳት ከሆነ በሐዲሳት መሠረት በመጨረሻው ዘመን ሙስሊሞች ከአላህ እንዲያማልዷቸው ነቢያትን እርዳታ እንደሚጠይቁ ስለምን ተነገረ? ሙሐመድ በአላህና በሙስሊሞች መካከል ገብቶ በምልጃው ነፍሳቸውን ከገሃነም እንደሚያተርፍስ ስለምን ተነገረ? ሌሎች ለሙሐመድ የተሰጡትን መብቶችና በሙስሊሞች ደህንነት ውስጥ የሚጫወታቸውን ቁልፍ ሚናዎች መዘርዘር ይቻላል (Sahih Al-Bukhari, Volume 2, Book 24, Number 553)፡፡
ከ99ኙ የአላህ ስሞች መካከል “አል-ዋሊ” የሚለው አንዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከነዚህ ስሞች መካከል አንዱን እንኳ ለፍጥረታት መስጠት ደግሞ ሺርክ እንደሆነ እስልምና ያስተምራል፡፡ እንደርሱ ከሆነ ሱራ 5፡55 ላይ አላህ ከፍጥረቱ ጋር ተቆጥሮ “ረዳታችሁ” (ዋሊዩኩም) መባሉና በረዳትነት ከፍጥረታት ጋር መሻረኩ ሺርክ አይሆንምን? ሙስሊሞች ይህንን ቃል የሚፈቱበትን መንገድ ስንመለከት መጠርያው ለፍጥረታት ለምን እንደማይገባ እንገነዘባለን፡፡ ለምሳሌ ያህል ይህ እስላማዊ ዌብሳይት እንዲህ ሲል ይፈታዋል፡-
From the root w-l-y which has the following classical Arabic connotations:
to be near, close, nearby
to be a friend, helper, supporter
to defend, guard (lit. friendly dealing)
to be in charge, to turn one toward something
to be the master, owner, lord
ምንጭ፡- https://wahiduddin.net/words/99_pages/walee_55.htm
ደምቆ የተጻፈውን ልብ በሉ፡፡ “የበላይ ገዢ፣ ባለቤት፣ ጌታ” የሚሉ ትርጉሞች እንዳለው ይናገራል፡፡ ቃሉ ይህንን ትርጉም የሚሸከም ከሆነ ይህ ማዕርግ ተገቢው የሆነለት ፍጥረት ማን ነው?
አላህ በረዳትነት ከፍጥረታት ጋር መዳበሉ ሳያንሰው ከፍጥረታት መካከል ረዳቶች እንዳሉት ቁርኣን ይናገራል፡-
“ዒሳ ከነርሱ ክህደት በተሰማው ጊዜ፡- ወደ አላህ (ተጨምረው) ረዳቶቼ እነማናቸው? አለ፤ ሐዋርያት፡- እኛ የአላህ ረዳቶች ነን በአላህ አምነናል እኛም ትክክለኛ ታዛዦች መኾናችንን መስክር አሉ፡፡” (ሱራ 3፡52)
በዚህ ቦታ “ረዳቶች” ለሚለው የገባው የአረብኛ ቃል “አንሷሪ” የሚል ቢሆንም “ዋሊ” ከሚለው እምብዛም የተለየ ትርጉም የለውም፡፡ እናም የእስልምናው አላህ በረዳትነት ከፍጥረት መደብ ጋር ከመቆጠርም አልፎ ከፍጥረት መካከል ረዳት አስፈልጎታል፡፡ ይህ ሁሉ ውስብስብ ጥያቄዎችን ይፈጥራል፡፡
ይህ አልገባ ካላችሁ ከራሳችሁ ባይብል አንድ ናሙና እናሳያችሁ፤ ፈጣሪ፦ “ከእኔ በቀር ሌላ አማላክ የለም” እያለ ይናገራል፦
ዘዳግም 32፥39 አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥ *ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ*፤
ኢዩኤል 2፥27 እኔም አምላካችሁ ያህዌህ እንደ ሆንሁ፥ እኔም በእስራኤል መካከል እንዳለሁ፥ *ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቃላችሁ*፤ ሕዝቤም ለዘላለም አያፍርም።
ኢሳይያስ 44:6 የእስራኤል ንጉሥ ያህዌህ፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ ያህዌህ እንዲህ ይላል። እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ *ከእኔ ሌላም አምላክ የለም*።
አዎን እግዚአብሔር አምላክ ብቸኛ እውነተኛ አምላክ ነው፡፡ ያሕዌ በሚለው የተፀውዖ ስሙም ይታወቃል፡፡
ነገር ግን መላእክት፣ ነብያት፣ የእስራኤልን ፈራጆች አምላኮች ተብለዋል፦
መዝሙር 138:1 አቤቱ፥ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፥ የአፌን ነገር ሰምተኸኛልና፤ *“በአማልክትም”כֵּאלֹהִ֔ים ፊት እዘምርልሃለሁ*።
መዝሙር 82:1 እግዚአብሔር *በአማልክት ማኅበር ቆመ*፥
መዝሙር 82:6 እኔ ግን፦ *አማልክት ናችሁ*፥ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ፤
ዘጸአት 21:5 ባሪያውም። ጌታዬን ሚስቴን ልጅቼንም እወድዳለሁ፥ አርነት አልወጣም ብሎ ቢናገር፥ ጌታው *ወደ “አማልክትን”כֵּאלֹהִ֔ים ይውሰደው*፥
ዘጸአት 22:8 ሌባውም ባይገኝ ባለቤቱ *ወደ “አማልክትን”כֵּאלֹהִ֔ים ይቅረብ*፥ እጁንም በባልንጀራው ከብት ላይ እንዳልዘረጋ ይማል።
ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም፤ መላእክት፣ ነብያት፣ የእስራኤልን ፈራጆች አምላኮች መባላቸው የፈጣሪ አፈ-ቀላጤና ቃል አቀባይ ስለሆኑ የእነርሱም አምላክነት ስልጣንና ሹመትን እንጂ መመለክን አያመለክትም። ፈጣሪ አምላክ የተባለበት እነርሱ አምላኮች በተባሉበት ሒሳብ አይደለም ከተባለ እንግዲያውስ አላህም እረዳት የተባለው ምእመናን ለምእመናን እረዳቶች በተባሉበት ሒሳብ አይደለም ነው። በሰፈሩት ቁና መሰፈር “double standard” ይሉሃል እንደዚህ ነው።
በነገርህ ላይ “Double Standard” በተለያዩ ሁለት ዓይነት ቁናዎች መስፈር ማለት እንጂ በሰፈሩት ቁና መሰፈር ማለት አይደለም፡፡ ለማንኛውም ያሕዌ ከሚለው የእግዚአብሔር የተፀውዖ ስም በተጻራሪ ኤሎሂም የሚለው የወል ስም እውነተኛውን አምላክ፣ ሐሰተኛ አማልክትን፣ የሰው ፈራጆችንና መላእክትን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ እንደርሱ ሲሆን አውዱ ግልፅ ስለሚያደርግ ምንም የሚያምታታ ነገር የለውም፡፡ ቁርኣን ግን አላህ ብቸኛ ረዳት (ዋሊ) ነው ካለ በኋላ አላህን ከፍጥረት ጋር በመቁጠር ረዳት (ዋሊ) ይለዋል፤ ለሌላ ፍጥረት መስጠት ይቅርታ የሌለው ኃጢአት እንደሆነ የተነገረውንም አል-ዋሊ የተሰኘውን ስሙን ከፍጥረት ጋር ሲጋራ ይታያል (ሱራ 5፡55 )፤ በነፍስ ጉዳይ ረዳት እንደማይሆኑ የተነገሩት ነቢያትም በመጨረሻው ቀን ሙስሊሞች እርዳታቸውን እንደሚለምኑ ተነግሮናል (Sahih Al-Bukhari, Volume 2, Book 24, Number 553)፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ ብቸኛ ረዳት የተባለው አላህ እራሱ ረዳቶች (አንሷር) እንዳሉት መነገሩ ነው (ሱራ 3፡52)፡፡ ስለዚህ ጥያቄያችን ተገቢ ነው ብለን እናምናለን፡፡
እነዚህን ግጭቶች ስንዘረዝር ዓላማ አድርገን የተነሳነውን ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡ እርሱም ሙስሊሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያነሱትን ጥያቄ የቁርኣንን አስቸጋሪ ክፍሎች ለመረዳት በሚሞክሩት መንገድ እንዲረዱት ማገዝ ነው፡፡ ስለዚህ ሙስሊም ወገኖች በተደጋጋሚ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያነሱትን ከላይ የሚገኘውን ጥያቄ አንስተህ ቁርኣንን በተረዳኸው መንገድ መረዳት እንደሚቻልና ችግር እንደሌለበት በመግለፅህ ደስ ብሎናል፡፡ እናም ዓላማችን ግቡን መቷል፡፡