7. የመላእክት ስግደት ለማን ነው?
ማሳሰብያ፡- በሰማያዊ የተጻፈው የኛ ሲሆን በጥቁር የተጻፈው የእርሱ ነው፡፡
ለአላህ ብቻ፡–
ሱራ 7፡206 “እነዚያ እጌታህ ዘንድ ያሉት መላዕክት እርሱን ከመገዛት አይኮሩም ያወድሱታልም ለርሱ ብቻ ይሰግዳሉ፡፡”
ለአደም ሰግደዋል፡–
ሱራ 2፡34 “ለመላዕክት ለአደም ስገዱ ባልን ጊዜ አስታውስ ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር እምቢ አለ ኮራም ከከሐዲዎቹም ሆነ፡፡”
መልስ
የሰው ልጆች ሆነ ማንኛውም ነጻ ፈቃድ ያለው ፍጡር በውደታ ለአላህ የሚታዘዘው የውደታ ስግደት ይባላል፤ ይህም ስግደት “ሡጁዱል ዒባዳ” سُّجُود العبادة ማለትም “የአምልኮ ስግደት” ይባላል፦
53:62 ለአላህ “ስገዱ” وَاعْبُدُو “አምልኩትም” وَاعْبُدُو ።
22:77 እላንተ ያመናችሁ ስዎች ሆይ በስግደታችሁ አጎንብሱ፣ “በግንባራችሁም ተደፉ” وَاسْجُدُو፣ ጌታችሁንም “አምልኩ” وَاعْبُدُو ፤ በጎንም ነገር ሥሩ፤ ልትድኑ ይከጃልላችኃልና።
41፥37 ሌሊትና ቀንም ፀሐይና ጨረቃም ከምልክቶቹ ናቸው፡፡ ለፀሐይና ለጨረቃ “አትስገዱ”፡፡ ለእዚያም ለፈጠራቸው አላህ “ስገዱ” وَاسْجُدُو ፡፡ እርሱን ብቻ “የምታመልኩ” تَعْبُدُونَ እንደ ኾናችሁ ለሌላ አትስገዱ፡፡
7፥206 እነዚያ እጌታህ ዘንድ ያሉት መላእክት እርሱን “ከማምለክ” عِبَادَتِهِۦ አይኮሩም፡፡ ያወድሱታልም፡፡ “ለእርሱም ብቻ ይሰግዳሉ” وَيُسَبِّحُونَهُۥ ።
53፥62 ለአላህም ስገዱ አምልኩም
ስግደት ከአምልኮ ጋር ከተያያዘ ያ ስግደት በኒያ “የአምልኮ ስግደት” ይሆናል፤ መላእክት “ለአላህ ብቻ ይሰግዳሉ” የተባለው ሡጁድ “ሡጁዱል ዒባዳ” سُّجُود العبادة ነው፤ ሌላው ሡጁድ ደግሞ “ሡጁዱ አተሒያ” سُّجُود التحيه ማለትም “የአክብሮት ስግደት” ነው፤ ይህ ስግደት በጥንት ባህል በሰላምታ እጅ መንሳት፣ ማጎንበስ እና መደፋትም ሲኖረው ማክበርን ያመለክታል፤ ለምሳሌ መላእክት ለአደም ሰግደው ነበር፦
7:11በእርግጥ ፈጠርናችሁ፤ ከዚያም ቀረጽናችሁ፤ ከዚያም ለመላእክቶች ለአደም “ስገዱ” اسْجُدُو አልን፤ ወዲያውም “ሰገዱ” فَسَجَدُو ፤ ኢብሊስ ሲቀር ከሰጋጆቹ አልሆነም። አላህ “ባዘዝኩህ” ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ? አለው፤ እኔ ከእርሱ የበለጥኩ ነኝ፤ ከእሳት ፈጠርከኝ፤ እርሱን ግን ከጭቃ ፈጠርከው አለ።
መቼም መላእክት ለአደም አክብሮትን እንጂ አምልኮትን እንዳልሰጡት እሙንና ቅቡል ነው፤
ምነው የዩሱፍ ወንድሞችና ወላጆች ለዩሱፍ ሰግደውለት የለ እንዴ አመለኩት ማለት ነውን? ወይስ አከበሩት?፦
12:4 ዩሱፍ ለአባቱ፦ አባቴ ሆይ! እኔ ዐሥራ አንድ ክዋክብትን ፀሐይንና ጨረቃን በሕልሜ አየሁ፤ ለእኔ “ሰጋጆች” سَاجِدِينَ ሆነው አየኋቸው ባለ ጊዜ አስታውስ ።
12:100 ወላጆቹንም በዙፋኑ ላይ አወጣቸው፤ ለእርሱም “ሰጋጆች” سُجَّد ሆነው ወረዱለት ፤ አባቴም ሆይ ይህ ፊት ያየኋት ሕልሜ ፍች ነው፤ ጌታዬ በእርግጥ እውነት አደረጋት፤
“ቂያም” قيام በሶላት ላይ “መቆም” ሲሆን የአምልኮ ክፍል ነው፤ ነገር ግን “መቆም” ሁሉ አምልኮ አይደለም፤ ምክንያቱም ሰው ለስራ ይቆማልና፣ “ሩኩዕ” رُكوع በሶላት ላይ “ማጎንበስ” ሲሆን የአምልኮ ክፍል ነው፤ ነገር ግን “ማጎንበስ” ሁሉ አምልኮ አይደለም፤ ምክንያቱም እቃ ለማንሳት ማጎንበስ አለና፣ “ሱጁድ” سُّجُود በሶላት ላይ “ስግደት” ሲሆን የአምልኮ ክፍል ነው፤ ነገር ግን “ስግደት” ሁሉ አምልኮ አይደለም፤ ምክንያቱም መላእክት ለአደም የዩሱፍ ወንድሞችና ወላጆች ለዩሱፍ ሰግደዋልና። መላእክት ለአላህ የሚሰግዱት እና ለአደም የሚሰግዱት ስግደት ይለያያል፤ ለምሳሌ መልክተኛውን እና የሥልጣን ባለቤቶችን በአላህ ፈቃድ እንታዘዛለን፤ አላህ ታዘዙ ሲባል አምልኩ ማለት ሲሆን መልክተኛውን እና የሥልጣን ባለቤቶችን ታዘዙ ማለት ደግሞ አክብሩት ማለት ነው፦
4:64 ማንንም መልክተኛ በአላህ ፈቃድ “ሊታዘዙት” لِيُطَاعَ እንጅ አልላክንም።
4፥59 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን አምልኩ፡፡ መልክተኛውን እና ከእናንተም የስልጣን ባለቤቶችን ታዘዙ፡፡ يَٰ
71:3 አላህን “አምልኩት” اعْبُدُو ፣ ፍሩትም፣ “ታዘዙኝም” وَأَطِيعُونِ በማለት አስጠንቅቂ ነኝ።
48:9 በአላህ እና በመልክተኛውም ልታምኑ እና ልትረዱትም “ልታከብሩትም” አላህን በጧትና ከቀትር በኋላ ልታወሱትም::
ነገር ግን ይህ አክብሮት አቅጣጫውን ቀይሮ አምልኮ እየሆነ ስላለ ከሰላምታ ውጪ በሱጁድ ለፍጡራን ማጎብደድ፣ መተናነስ፣ ማሸርገድ ቁርኣን ሲወርድ ቆሟል፤ የአክብሮት ስግደት ከአምልኮ ስግደት ጋር እንዳይደባለቅ የተከለከለው በነብያችን ጊዜ ነው፦
ሱነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 9, ሐዲስ 1926:
አዝሃር ኢብኑ መርዋር እንዳለው፤ ሐማድ ኢብኑ ዘይድ እንዳለው፤ ከአዩብ፣ ከአል ቃሲሙል ሸይባኒይ፣ ዐብዲላህ ኢብኑ አቢ ዐውፋ እንዲህ አለ፡- ሙዓዝ ኢብኑ ጀበል ከሻም ምድር በተመለሰ ጊዜ *ለነቢዩ ሰገደ፤ እሳቸውም፦ “ሙዓዝ ሆይ! ምንድነው ይህ?” አሉት፤ እርሱም፦ “ሻም ምድር ሄጄ ነበር፤ ለኤጲስ ቆጶሳቶቻቸው እና ለጳጳሳቶቻቸው ሲሰግዱ ተመለከትኩኝ፤ ይህንን ለእርሶ ልንሰራው ተመኘሁ” አለ፤ የአላህ መልክተኛም፦ “ይህንን በፍጹም እንዳትሰሩ! እኔ ከአላህ ውጪ ስግደትን ለሰው የማዝ ብሆን ኖሮ ሴትን ለባሏ እንድትሰግድ አዛት ነበር፤ የሙሐመድ ነፍስ በእጁ በሆነው እምላለሁ፤ ሚስት የባሏን መብት እስክትወጣ ድረስ የጌታዋን የአላህ ሐቅ አትወጣምና”* አሉት፡፡
ከላይ የተቀመጠው ሙግት ሲጨመቅ ሦስት ነጥቦች ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡ 1ኛ. ስግደት የአምልኮና የአክብሮት ተብሎ ለሁለት ይከፈላል 2ኛ. በቁርኣን ውስጥ የዮሴፍ ወንድሞች ሰግደውለታል ስለዚህ የአክብሮት ስግደት አለ፡፡ 3ኛ. ስግደት ከጊዜ በኋላ ወደ አምልኮ ስለተቀየረ በነቢዩ ዘመን ተከልክሏል፡፡ አንድ በአንድ እናያቸዋለን፡፡
- በቁርኣን ስግደት የአምልኮና የአክብሮት ተብሎ ለሁለት ተከፍሏልን?
ቁርኣን በየትኛውም ቦታ በግንባር ወደ መሬት ተደፍቶ መስገድን የሚያመለክተውን ስግደት (ሱጁድ ወይም ሰጅዳህ) የአምልኮና የአክብሮት በማለት ለሁለት ከፍሎ አላቀረበም፡፡ በአንድ ወገን ሱጁድ ለአላህ ብቻ የተገባ እንደሆነና መላእክትም ለእርሱ ብቻ እንደሚሰግዱ ይናገራል፡-
“ሌሊትና ቀንም፣ ጸሐይና ጨረቃም፣ ከምልክቶቹ ናቸው፤ ለፀሐይና ለጨረቃ አትስገዱ፤ ለዚያም ለፈጠራቸው አላህ ሰገዱ፤ እርሱን ብቻ የምትግገዙ እንደሆናችሁ፣ (ለሌላ አትስገዱ)፡፡” (ሱራ 41፡37)
“እነዚያ እጌታህ ዘንድ ያሉት መላዕክት እርሱን ከመገዛት አይኮሩም ያወድሱታልም ለርሱ ብቻ ይሰግዳሉ፡፡” (ሱራ 7፡206)
በሌላ ወገን ደግሞ በአላህ ትዕዛዝ ፍጡራን ለፍጡራን ተመሳሳይ ነገር መፈፀማቸውን ይናገራል (ሱራ 2:34; 7:11-12; 15:29-33; 17:61; 18:50; 20:116; 38:72-73, 75)፡፡ ይህ ግልፅ ግጭት ነው፡፡
- በቁርኣን ውስጥ የዮሴፍ ወንድሞች ለዮሴፍ መስገዳቸው የአክብሮት ስግደት መኖሩን ያረጋግጣልን?
ቁርኣን ሱጁድ ለአላህ ብቻ እንደሆነ ከተናገረ በኋላ በሌላ ቦታ ወንድሞቹ ለዮሴፍ መስገዳቸውን መናገሩ የመላእክትን ለአዳም መስገድ የሚያጸድቅ ሳይሆን ተጨማሪ ተቃርኖ ነው፡፡ አስቀድመህ “የአክብሮት ሰጅዳህ አለ” የሚል ቅድመ ግንዛቤ ይዘህ የዮሴፍ ወንድሞች ለእርሱ መስገዳቸውን በዚያው መሠረት ተረጎምከው፡፡ ቁርኣን ሱጁድ ለአላህ ብቻ እንደሆነ አስቀድሞ ስለነገረህ በሌላ ቦታ ለሰው እንደተሰገደ መናገሩ ሌላ ግጭት እንጂ የግጭት መፍቻ አይሆንም፡፡ ይህንን የተረዱት አንዳንድ የእንግሊዘኛ ቁርኣን ተርጓሚዎች የዮሴፍ ወንድሞች ለዮሴፍ ሳይሆን ለአላህ እንደሰገዱ በሚገልፅ መንገድ ተርጉመውታል፡፡ ለምሳሌ ያህል ሼሪ አሊ የተሰኘ ተርጓሚ እንዲህ አስቀምጦታል፡-
And he raised his parents upon the throne and they all fell down prostrate BEFORE ALLAH for him …
መውላና ሙሐመድ አሊም እንዲህ ተርጉሞታል፡-
And he raised his parents on the throne, and they fall prostrate FOR HIS SAKE …
ሙሐመድ አሰድ የተሰኘ ሙስሊም ሊቅ ኢብን አባስን ዋቢ አድርጎ እንደተናገረው ዮሴፍ እናትና አባቱን በፊቱ እንዲሰግዱ ማድረጉ የማይታሰብ በመሆኑ ቤተሰቦቹ የሰገዱት ለእርሱ ሳይሆን ለአላህ ነው፡፡ (Asad, The Message of the Qur’an, የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 100 እዚህ የተፍሲር ድረገፅ ላይ ይመልከቱ https://www.altafsir.com/ViewTranslations.asp?Display=yes&SoraNo=12&Ayah=0&toAyah=0&Language=2&LanguageID=1&TranslationBook=7 )
ስለዚህ ወንድሞቹ ለዮሴፍ ሰግደዋል የምትል ከሆነ ተጨማሪ ግጭት ልትፈጥር ነው፡፡ የነዚህን ሊቃውንት ትርጓሜ ተቀብለህ ወንድሞቹ ለአላህ እንደሰገዱ ካመንክ ደግሞ ከተጨማሪ ግጭት ትተርፋለህ፤ ነገር ግን ለአክብሮት ስግደት ምሳሌ ይሆነኛል ያልከውን ብቸኛውን የቁርኣን ጥቅስ ታጣለህ፡፡ ፍጥረት ለፍጥረት መስገዱን የሚያጸድቅ መላእክት ለአዳም መስገዳቸውን ከሚገልጸው ትረካ ውጪ ያለው ብቸኛ ትረካ ይህ ነውና፡፡
- ስግደት በሙሐመድ ዘመን የተከለከለው ወደ አምልኮ ስለተቀየረ ነውን?
በየትኛውም ዘመን ሰዎች ስግደትን ሌላውን ፍጡር ለማምለክም ሆነ ፈጣሪያቸውን ለማምለክ ሲጠቀሙበት እንደነበር ስለሚታወቅ ይህ ትርጉም አይሰጥም፡፡ ከሙሐመድ ዘመን በፊት ሰዎች ለፍጡራን በመስገድ ያመልኳቸው አልነበረምን? ታድያ የአክብሮት ስግደት ወደ አምልኮ ተለወጠ እንዴት ይባላል? ሰዎች ስግደትን ፍጡራንን ለማምለክ በመጠቀማቸው ምክንያት ለፍጡራን ስግደት መከልከል ከነበረበት ከመጀመርያውኑ መከልከል ነበረበት፡፡ “አክብሮት አቅጣጫውን ቀይሮ አምልኮ እየሆነ ስላለ ከሰላምታ ውጪ በሱጁድ ለፍጡራን ማጎብደድ … ቁርኣን ሲወርድ ቆሟል” ብሎ ማለት ትርጉም አልባ ነው፡፡ ሰዎች ከጥንት ጀምሮ በሱጁድ ፍጥረታትን ሲያመልኩ ነበር፣ ዛሬም ያንኑ ያደርጋሉ፡፡ በሙሐመድ ዘመን የተፈጠረ የተለየ ነገር አልነበረም፡፡
ሙሐመድ “እኔ ከአላህ ውጪ ስግደትን ለሰው የማዝ ብሆን ኖሮ ሴትን ለባሏ እንድትሰግድ አዛት ነበር” ብሎ የተናገረውን ሐዲስ በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡
- አንተ እንዳልከው ቁርኣን የአክብሮት ስግደትን ፈቅዶ ከሆነ በቁርኣን ውስጥ የሚገኘው የአላህ ፈቃድ መሻር (“ሻ” ጠብቃ ትነበብ) ካለበት በራሱ በአላህ እንጂ በሙሐመድ ትዕዛዝ መሻር አልነበረበትም፡፡ ይህ ሙሐመድን ከአላህ ቃል በላይ ያደርገዋል፡፡ አላህ በቁርኣን የፈቀደውን ሙሐመድ በሐዲስ እንዴት ይሽራል?
- ፍጡር ለፍጡር እንዳይሰግድ በሙሐመድ ዘመን ከተከለከለ ለሙሐመድ እፅዋት፣ እንስሳትና ግዑዛን ፍጥረታትም ጭምር ይሰግዱ እንደነበር በሐዲሳት መዘገቡ እንዴት ይታያል? እነዚህ ፍጥረታት ከሰገዱ ሰዎች እንዳይሰግዱ ምን ይከለክላቸዋል? (Hadith of al-Tirmidhi, Number 963– ALIM CD-ROM Version)
- ሌላ የሐዲሱ ዘገባ ቅጂ እንዲህ ይላል፡- “Had it been permissible that a person may prostrate himself before another, I would have ordered that a wife should prostrate herself before her husband” (Hadith of al-Tirmidhi, Number 110- ALIM CD-ROM Version እንዲሁም Ibn Hibbaan 4162)፡፡ በዚህ ሐዲስ መሠረት ሙሐመድ የተናገረው “አንድ ሰው ለሌላው እንዲሰግድ ተፈቅዶ ቢሆን ኖሮ…” በማለት ነው፡፡ ስለዚህ ቀድሞውኑ አልተፈቀደም ነበር ማለት ነው፡፡ ይህም አንዱ ፍጥረት ለሌላው መስገድ እንደሌለበት የሚናገሩትን የቁርኣን ጥቅሶች በማረጋገጠ ግጭቱን ይበልጥ ያጠነክራል፡፡
ስናጠቃልል በቁርኣን ስግደት “የአምልኮና የአክብሮት” ተብሎ ለሁለት መከፈሉን የሚናገር ምንም ነገር የለም፡፡ በቁርኣን ይቅርና በሐዲስ እንኳ ስግደት እንዲህ ተብሎ አልተከፈለም፡፡ በእስልምና ለፍጥረት አጎንብሶ መስገድ ከአምልኮ የሚቆጠርና የተከለከለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቁርኣንም ሆነ በሐዲስ የተረጋገጠ ነው፡፡ በቁርኣን ውስጥ የሚገኙት ስግደቶች ከሞላ ጎደል ለአላህ የተነገሩ ሲሆን አላህ ለአዳም እንዲሰግዱ ያዘዘበት (2:34; 7:11-12; 15:29-33; 17:61; 18:50; 20:116; 38:72-73, 75)፣ ለዮሴፍ የተሰገደበትና (12:4, 100) የንግሥተ ሳብ ሕዝቦች ለፀሐይ ይሰግዱ እንደነበር የተነገረበት (27:24-25) በቁርኣን ውስጥ የሚገኙ አጋጣሚዎች ናቸው፡፡ የንግሥተ ሳባ ሕዝቦች ጣዖታውያን በመሆናቸው ትረካው ከቁጥር አይገባም፡፡ የዮሴፍ ታሪክም ቢሆን እንዴት መተርጎም እንዳለበት በሙስሊም ሊቃውንት መካከል ስምምነት የለም፡፡ ይህ ደግሞ አላህ ፍጡር ለፍጡር እንዲሰግድ ያዘዘበት ብቸኛ አጋጣሚ መላእክት ለአዳም እንዲሰግዱ ያዘዘበት ትረካ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ይህንን ትረካ የቁርኣን ደራሲ ከአይሁድ ታልሙድ ላይ በግርድፉ በመገልበጥ ከአጠቃላይ እስላማዊ አስተምሕሮ ጋር የሚጋጭ ትምሕርት ፈጥሯል፡፡ እናም ሙስሊም ወገኖቻችን በእስላማዊ አስተምሕሮ ውስጥ በግልፅ ያልተነገረና በቁርኣን ውስጥ የሌለ የስግደት ዓይነት፣ ማለትም “የአክብሮት ስግደት” በመፍጠር ይህንን ግጭት ለማስታረቅ ተገድደዋል፡፡
በቀጣይ ይህ ወገናችን ጉዳዩን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ በማዞር አንዳንድ ጥያቄዎችን ይጠይቃል፡፡ እስኪ እንየው፡-
ወደ ባይብል ስንገባ “ስግደት” የሚለው ቃል በዕብራይስጥ “ሻቻህ” שָׁחָה ሲሆን በግሪክ ደግሞ “ፕሮስካኒኦ” προσκυνέω ይባላል፤ ይህም ለተለያየ ምንነት ሆነ ማንነት በኒያ”intention” የሚቀርብ አምልኮን”Adoration” ወይም አክብሮትን”prostration” ነው ለማመልከት በባይብል ተጠቅሞበታል፤ በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውም ተብሏል፦
ስግደት በዕብራይስጥ “ሻቻህ” ሳይሆን “ሻኻህ” ነው የሚባለው፡፡ በእንግሊዘኛ ትራንስሊትሬት ሲደረግ Shachah ተብሎ ተጽፎ ስላየኸው “ሻቻህ” ብለህ አሳስተህ እንዳነበብከው ግልፅ ነው፡፡ በግሪኩም ቢሆን ትክክለኛው አነባበብ “ፕሮስኩኔኦ” እንጂ “ፕሮስካኒኦ” አይደለም፡፡ እብራይስጥም ሆነ ግሪክ ማንበብ አትችልም፡፡ ነገር ግን በጽሑፎችህ ውስጥ እብራይስጥና ግሪክ እየጠቀስክ አጉል ትንታኔ ውስጥ ስትገባ የተመለከተህ ሙስሊም ወገንህ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመርያ ቋንቋዎች ሊቅ አድርጎ ሊያስብህ ይችላል፡፡ እንዲህ ያለ አጉል Pseudo Scholar መሆን ቀርቶብህ በአቅምህ ልክ ብትናገር ምን አለበት? እውነት እልሃለሁ ይህንን የምናገርህ በዘለፋ መንፈስ ሳይሆን ከቅንነት በመነጨ ልባዊ ምክር ነው፡፡ ምክር መስማት ደግሞ ጥቅሙ ለራስ ነው፡፡
ማቴዎስ 4፥10 ያን ጊዜ ኢየሱስ፦ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን *”ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ”* ተብሎ ተጽፎአልና አለው።
በዚህ ጥቅስ ውስጥ “ስገድ” የሚለው “ፕሮስኩኔኦ” ሲሆን ሰዎች ለሌሎች ሰዎች ያላቸውን አክብሮት ለማሳየት ይሰግዳሉ፤ ይህ ዓይነቱ ስግደት ለጣዖታት እንጂ ለሰዎች አልተከለከለም፡፡ በጥቅሱ ውስጥ ልዩ (Exclusive) የተደረገው “አምልክ” የሚለው ቃል መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ እርሱ ደግሞ “ላትሬኦ” የሚል ሲሆን ከእግዚአብሔር ውጪ ለየትኛውም ፍጥረት መስጠት የተከለከለ ነው፡፡
ዘዳግም 5፥8-9 በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፤ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤ ለሚወድዱኝ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኛና *”አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውም*”።
ለጣዖታት የአክብሮት ስግደትም ሆነ ማንኛውም የአምልኮ ተግባር ተከልክሏል፡፡ ለሰው ግን የአክብሮት ስግደት አልተከለከለም፡፡ አብርሃም፣ ዳዊትና ሌሎች ታላላቅ ሰዎች ያንኑ አድርገዋል፡፡
ራዕይ 19፥10 *”ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ”*። እርሱም፦ እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ *”ለእግዚአብሔር ስገድ”*፤ …አለኝ።
መላእክትና ሰዎች እንደተሰገደላቸው የሚናገሩ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ያሉ ሲሆን ጥቂት፣ ምናልባትም በአዲስ ኪዳን ከሁለት ያልበለጡ ቦታዎች ላይ ግን የተሰገደላቸው ሰዎችና መላእክት ስግደትን ሳይቀበሉ ቀርተዋል፡፡ ይህም ከትህትና አንፃር “አይገባንም” በማለት ስላሰቡ እንጂ “ፕሮስኩኔኦ” ለፍጡር የተከለከለ በመሆኑ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል አንተ ቆርጠህ ያስቀረኸው ክፍል መልአኩ ለምን ስግደቱን እንዳልተቀበለ እንዲህ ይናገራል፡- “…ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ…” መልአኩ ከዮሐንስ ጋር በአንድ ደረጃ ላይ እንዳለ ይገልጻል፡፡ ዮሐንስ እንዳይሰግድ የከለከለውም ከዚያ አንፃር ነው፡፡ ነገር ግን መሥዋዕትን ማቅረብን የመሳሰሉ አምልኳዊ ተግባራት በተደረጉ ጊዜ ቅዱሳን ሰዎች በምን ዓይነት ሁኔታ ምላሽ እንደሰጡ ከተከታዩ ጥቅስ መረዳት ይቻላል፡-
በከተማውም ፊት ቤተ መቅደስ ያለው የድያ ካህን ኮርማዎችንና የአበባን አክሊሎች ወደ ደጃፍ አምጥቶ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ሊሠዋላቸው ወደደ። ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፥ እንዲህም አሉ፦ እናንተ ሰዎች፥ ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፥ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን። (ሐዋ. 14፡13-15)
እስኪ ይህንን ሁኔታ ሐዋርያው ጴጥሮ ቆርኖሌዎስ በሰገደለት ጊዜ ከሰጠው ምላሽ ጋር አነፃፅሩ፡-
ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተገናኝቶ ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት። ጴጥሮስ ግን፦ ተነሣ፤ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ ብሎ አስነሣው። (ሐዋ. 10፡25-26)
በዚህ ቦታ ላይ ጴጥሮስ በትህትና መንፈስ ሲናገር የምንመለከት ሲሆን ቆርኖሌዎስ ከእግሩ ስር ወድቆ አክብሮት በመስጠቱ እምብዛም አልተረበሸም፡፡ ነገር ግን ጳውሎስና በርናባስ ሰዎች እንደ አማልክት ቆጥረው መሥዋዕት ሊያቀርቡላቸው ሲሉ እጅግ ደነገጡ፣ ልብሳቸውን ቀደዱ፣ ሕዝቡንም ከዚያ ተግባር ለማስቆም ሮጡ፣ በፍርሃትና በድንጋጤ ውስጥ ሆነውም ሕዝቡን መክረው ያንን ተግባር አስቆሙ፡፡ ይህም የሆነው መሥዋዕት እግዚአብሔርን የማምለኪያ መንገድ በመሆኑና ለሰው ተገቢ ባለመሆኑ ነው፡፡
ለማንም ለምን “አትስገድ” ከተባለ ለምንድን ነው ሰዎች ለሰዎች የሰገዱት?፦
የአክብሮት ስግደት ለጣዖት ነው የተከለከለው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተከለከለው ሰዎችን ማምለክ እንጂ አክብሮትን ለማሳየት በሰዎች ፊት መደፋት አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ክርስቲያኖች እርስ በርስ ይቅርታ ለመጠያየቅና ሰዎችን ለማስታረቅ በሰዎች እግር ላይ ሲደፉ የሚታየው፡፡ እኔ ራሴ የበደልኳቸውን ሰዎች ይቅርታ ለመጠየቅ ከአንዴም ሁለቴ ወድቄ እግር ስሜያለሁ፡፡ ተጣልቶ ለሁለት የተከፈለ ጉባኤን ለማስታረቅ በሕዝቡ ፊት በግንባሬ ተደፍቼ አውቃለሁ፡፡ እንዲህ ያለው ስግደት በመጽሐፍ ቅዱስ አልተከለከለም፤ ለጣዖት ካልሆነ በስተቀር፡፡ ይህ ማለት ግን በአፀደ ነፍስ ላሉት ቅዱሳን ሰዎች ወይንም በአካል ላልተገለጡ መላእክት መስገድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ማለት አይደለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደዚያ ያደረገ ሰው የለም፡፡ ለቅዱሳንና ለመላእክት ምስል መስገድ የተፈቀደበትም ቦታ የለም፡፡
ዘፍጥረት 23:7 አብርሃምም ተነሣ፥ ለምድሩ ሕዝብም፥ *”ለኬጢ ልጆች ሰገደ”*።
ዘፍጥረት 27፥29 አሕዛብ ይገዙልህ ሕዝብም *”ይስገዱልህ”*፤ ለወንድሞችህ ጌታ ሁን፥ *”የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ”*፤
ዘፍጥረት 37:9 ደግሞም ሌላ ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፥ እንዲህም አለ። እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን ዓለምሁ፤ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክብትም *”ሲሰግዱልኝ”* አየሁ።
ዘፍጥረት 42:6 ዮሴፍም በምድር ላይ ገዥ ነበረ፥ እርሱም ለምድር ሕዝብ ሁሉ ይሸጥ ነበር፤ የዮሴፍም ወንድሞች በመጡ ጊዜ በምድር ላይ *”በግምባራቸው ሰገዱለት”*።
ዘፍጥረት 43:26 ዮሴፍም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ በእጃቸው ያለውን እጅ መንሻ በቤት ውስጥ አቀረቡለት፥ *”ወደ ምድርም ወድቀው ሰገዱለት”*።
ዘፍጥረት 43:28 እነርሱም አሉት። ባሪያህ አባታችን ደኅና ነው፤ ገና በሕይወት አለ። *”አጐንብሰውም ሰገዱለት”*።
1ዜና.29:20፤ ዳዊትም ጉባኤውን ሁሉ። አምላካችሁን እግዚአብሔርን ባርኩ አላቸው። ጉባኤውም ሁሉ የአባታቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ባረኩ፥ ራሳቸውንም አዘንብለው ለእግዚአብሔር እና *”ለንጉሡ ሰገዱ”*።
በግሪክ ፕሮስኩኔኦ ወይንም በእብራይስጥ ሻኻህ ለሰዎች አልተከለከለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሰዎች በጥብቅ የተከለከሉት በአረማይክ “ፔላኽ” በግሪክ ደግሞ “ላትሬኦ” የተሰኙት የአምልኮ ተግባራት ናቸው፡፡
አንዳንድ ቂል ሰዎች፦ “ሰዎች ናቸው የሰገዱት እንጂ ስገዱ አልተባሉም” ብለው ውሃ የማያነሳና የማይቋጥር ስሁት ሙግት ያቀርባሉ፤ ለመሆኑ ኢየሱስ ሲመጣ ኢአማንያንን መጥተው በአማንያን እግር ፊት ይሰግዱ ዘንድ ማድረጉ ስህተት ነውን?፦
ራእይ 3:9 እነሆ፥ አይሁድ ሳይሆኑ፦ አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ እነሆ፥ መጥተው *”በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ”* προσκυνήσουσιν ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ።
ለቂሎች መልስ መስጠቱን ተወውና ሃይማኖታቸውን ከሚያውቁት ክርስቲያኖች ጋር ተወያይ፡፡ በዚህ ቦታ “ስግደት” ተብሎ የተገለጸው “ፕሮስኩኔኦ” እንጂ “ላትሬኦ” አይደለም፡፡
ዮሐንስ ሊሰግድለት በእግሩ ፊት ሲደፋ “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ባሪያ ነኝ ለእግዚአብሔር ስገድ” ብሎት እያለ ኢየሱስ ኢአማንያንን መጥተው በአማንያን እግር ፊት ይሰግዱ ዘንድ ማድረጉ አግባብ ነው ወይ? ስንል ፦አይ መልአኩ ለዮሐንስ ያለው “የአምልኮት ስግደት” ሲሆን ኢየሱስ ያለው ደግሞ “የአክብሮት ስግደት” ነው፤ የአምልኮት ስግደት በባህርይ የአንድ አምላክ ሃቅና ገንዘብ ሲሆን የአክብሮት ስግደት ደግሞ በፀጋ ለቅዱሳን ማክበን ያመለክታል” ይሉናል፤ እንግዲያውስ የቁርአኑንም በዚህ ስሌትና ቀመር ተረዱት፤ በሰፈሩት ቁና መሰፈር ይሉሃል እንደዚህ ነው፤
በቁርኣን “ሱጁድ” ወይም “ሰጅዳህ” ለፍጡር የተከለከለና ለአላህ ብቻ የተገባ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ “ተውሒድ አል-ኢባዳ” በተሰኘው እስላማዊ አስተምሕሮ በጥብቅ ከተነገሩት መካከል አንዱ ለፍጡር መስገድ ሺርክ መሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን በቁርኣን ውስጥ አላህ መላእክት ለአዳም እንዲሰግዱ እንዳዘዘ ስለተነገረ ይህ በእስላማዊ አስተምሕሮ ውስጥ የሚገኝ ግጭት ሊሆን በቅቷል፡፡
በተጨማሪም ፍጥረታት ሁሉ ለአዳም እንደሰገዱ በአሁን ጊዜ ጥንት ከሚባሉት እደ-ክታባት አንዱ በሆነው በአሌክሳድሪየስ ኮዴክስ በሚገኘው በሮሙ ክሌመንት ማለትም በቀለሚንጦስ ተገልጿል፦
ክሌመንት 1፥41 አራዊት፣ እንስሳት ወፎች “”እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ””ወደ አዳም ተሰበሰቡ ከፊቱ ቁመው ራሳቸውን አዘነበሉ፤ *ለአዳምም ሰገዱ”*።
የቁርኣን ደራሲ ይህንን ታሪክ በደመነፍስ ስለኮረጀ በእስላማዊ አስተምሕሮ ውስጥ ግጭት ፈጥሯል፡፡ ነገር ግን ከኮዴክስ አሌክሳንድሪነስ ጋር የተገኙት የቀለሜንጦስ ጽሑፎች 1ኛ እና 2ኛ ተብለው ስለተከፈሉ በየትኛው ውስጥ ነው የሚገኘው? 1፥41 ስትልስ ምን ለማለት ፈልገህ ነው? ምክንያቱም 1ኛ ወይንም 2ኛ ቀለሜንጦስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 41 ለማለት ፈልገህ ከሆነ በ1ኛው ውስጥ የመጀመርያው ምዕራፍ 3 ቁጥሮች ብቻ ነው ያሉት፡፡ 2ኛው ውስጥ ደግሞ 8 ቁጥሮች ነው ያሉት፡፡ ከቁርኣን ጋር የሚመሳሰል ታሪክም በውጡ አላገኘንም፡፡ ልታሳየን ብትችል መልካም ነው፡፡ ተሳስተሃል ለማለት ሳይሆን ፈልገን ስላላገኘን ነው፡፡
በተጨማሪም በመቃብያን ላይ ዲያቢሎስ የወደቀበት ለአደም አልሰግድ በማለቱ እንደሆነ ተገልጿል፦
3ኛ መቃብያን 1፥6 የሚጠፉ በኔም የሚስቱ ሰዎች ፈጽመው ይበዙ ዘንድ የአዳምም ልጆች ይጠፉ ዘንድ ይህንን በተናገሩ ጊዜ እኔ ደስ ይለኛል። ለሚዋረድልኝ *”ለአዳም አልሰግድም በማለቴ እግዚአብሔር ስለአባታቸው ስለአዳም ከማዕረጌ አዋርዶኛልና”*።
የጠቀስከው ቃል የሚገኘው 1፡6 ላይ ሳይሆን 1፡15 ላይ ነው፡፡ የቁርኣንን የኩረጃ ምንጭ ስለጠቆምከን እናመሰግናለን፡፡ የታሪኩ ዝርዝር ግን ከአይሁድ የአዋልድ መጽሐፍ የተቀዳ ነው፡፡ ይህንን በተጨባጭና በማይታበል ማስረጃ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ቁርኣን የሰው ሥራ እንጂ ከሰማይ የመጣ የፈጣሪ መጽሐፍ አይደለም፡፡
“ሳያውቁ መናገር፥ ኃላ ለማፈር” ይላሉ አበው። መልሱ ኢንሻ አላህ ይቀጥላል…
በትክክል! በዚህ ምላሽ የተመለከትነው ያንተንና የቁርኣን ደራሲን ያለማወቅ ነው፡፡