ደካማ አመክንዮ የተዛባ ምንጭ – የቁርኣንን ኩረጃዎች ለማስተባበል የተደረገ ከንቱ ጥረት

ደካማ አመክንዮ የተዛባ ምንጭ

የቁርአንን ኩረጃዎች ለማስተባበል የተደረገ ከንቱ ጥረት

ተለማማጁ ሙስሊም ዳዋጋንዲስት ከነበረበት ሀይበርኔሽን ነቅቶ የማይስተባበለውን ለማስተባበል በመሞከር እንደተለመደው ግንባሩን በማመቻቸት መስመራችን ላይ ገብቶልናል፡፡ በዚህ ምላሻችን በምንመለከተው ጽሑፉ ውስጥ የቁርአንን ኩረጃ ለማድበስበስ ሞክሯል፡፡ ነገር ግን እንደተለመደው ጽሑፉ በደካማ ሎጂክና መረጃዎችን በማዛባት ላይ  የተመሠረተ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ይህ አብዱል ቁርአን ከመጽሐፍ ቅዱስ ኮርጇል የሚለው ሙግት ክርስቲያኖች በጣም የሚደጋግሙት ሙግት መሆኑን በማጋነን ከገለጸ በኋላ የሁለት ጸሐፊያንን ሐሳብ እንደ ምሳሌ በማንሳት ትችት ይሰነዝራል፡፡

በመጀመርያ የጠቀሰው ዲሰን መንዲድ በተባለ ጸሐፊ “እውነቱ ይህ ነው” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ሲሆን ጸሐፊው ቁርአን ከመጽሐፍ ቅዱስ መኮረጁን ከመግለጹ በፊት የተወሰኑ ገፆችን ቀደም ብሎ የመጽሐፍ ቅዱስና የቁርአን አስተምህሮዎች እንደሚጣረሱ ስለገለጸ ቁርአን ከመጽሐፍ ቅዱስ ኮርጇል የሚለው ሐሳቡ እርስ በርሱ ይጣረሳል የሚል ትችት ሰንዝሯል፡፡ በዚህ አብዱል አስተሳሰብ መሠረት ሁለት መጻሕፍት እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ አስተምሕሮዎችን የሚያስተላልፉ ከሆነ አንዱ ከሌላው ሊኮርጅ አይችልም፡፡ የዚህ ሎጂክ ደካማነት ማሰብ ከሚችል ሰው ሁሉ የተሰወረ ነው ብዬ ባላስብም ምላሽ ልስጠው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ቁርአንና መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የአስተምህሮ ልዩነቶች ቢኖሯቸውም የሚስማሙባቸው ጉዳዮችም አሉ፡፡ ቁርአንና መጽሐፍ ቅዱስ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ እንደማይስማሙ የተናገረ ክርስቲያን አጋጥሞኝ አያውቅም፤ ዲሰንም እንደርሱ አላለም፡፡ ስለዚህ እነዚህ የሚመሳሰሉባቸው ክፍሎች አስቀድሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙ የኩረጃ ክስ ቢቀርብ እንዴት የተኮረጁ እንዳልሆኑና እንዴት የቁርአን ኦሪጅናል ሐሳብ ተደርገው ሊወሰዱ እንደሚችሉ ማስረዳት ከሙስሊሞች ይጠበቃል፡፡ ሌላው የቁርአን ደራሲ ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችንና ትምህርቶችን በመውሰድ ለአዲሱ አስተምህሮው እንደሚመች አድርጎ ማቅረብ ይችላል፡፡ በቁርአን ውስጥ የሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች እንዲህ ያለ ተግባር የተፈጸመባቸው ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስና የቁርአን መሠረታዊ አስተምህሮዎች ስለሚጋጩ ብቻ ቁርአን ከመጽሐፍ ቅዱስ አልኮረጀም ሊባል አይችልም፡፡

ሌላው “አማን ገረመው” በተባለ ጸሐፊ “ኢስላም መለኮታዊ ሃይማኖት ነውን?” በሚል ርዕስ የተጻፈ መጽሐፍ በመጥቀስ ትችት ይሰነዝራል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ የ “ኢስላም መለኮታዊ ሃይማኖት ነውን?” መጽሐፍ ደራሲ አብዱልሃቅ ጀሚል የተባለ ሰው ነው፡፡ ክርስትናንና እስልምናን በተመለከተ “አማን ገረመው” በተባለ ሰው የተጻፈ መጽሐፍ ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህ አብዱል እንዳደረገው የአንድን ግለሰብ ስም አንስቶ መለጠፍ አግባብ አይደለም፤ አደገኛ ተግባርም ነው፡፡ ለማንኛውም ይህ አብዱል ደራሲው በመጽሐፉ ውስጥ የቁርአን ምንጭ ሰይጣን ነው የሚል ሙግት ካቀረበ በኋላ ዘግይቶ ደግሞ ቁርአን ከመጽሐፍ ቅዱስ የተቀዱ ነገሮች በውስጡ መኖራቸውን በመጥቀስ ተችቷል፡፡ “አንድ ሰው የቁርአን ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው ብሎ ከተነተነ በኋላ መልሶ ቁርአን የሰይጣን ቃል ነው ካለ በተዘዋዋሪ መጽሐፍ ቅዱስ የሰይጣን ቃል መሆኑን መስክሯል ማለት ነው” በማለትም ደካማ ድምዳሜውን ያስቀምጣል፡፡ የቁርአን ምንጭ ሰይጣን ስለመሆኑ ሙሐመድ በሒራ ዋሻ ውስጥ ከባዕድ መንፈስ ጋር በተገናኘ ጊዜ ያጋጠመውን ሁኔታና በዘመኑ ሁሉ ያሳለፈውን ልምምድ ማየት በቂ ነው፡፡ ሆኖም የቁርአን ደራሲ በሰይጣን ተመርቶ ከመጽሐፍ ቅዱስ በመኮረጅ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል በማጥመም አፈንጋጭ አስተምህሮውን አላስተላለፈበትም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ሰይጣን ጌታችንን በምድረ በዳ በፈተነበት ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል በመጥቀስ የራሱን ጠማማ መልእክት ለማስተላለፍ እንደሞከረ ማስታወስ አስፈላጊ ነው (ማቴዎስ 3፡1-11)፡፡ የሰይጣን በጣም አደገኛው ባሕርይ እውነትና ሐሰትን በመቀላቀል ሰዎችን ማታለል መቻሉ ነው፡፡ በኤደን ገነት አዳምና ሔዋንን ያሳሳታቸው እግዚአብሔር የተናገረውን በማጣመምና የራሱን ሐሳብ በመጨመር ነበር (ዘፍጥረት 3፡1-5)፡፡ ውሸት ሌጣዋን ብትመጣ ብዙ ሰው ማንነቷን ያውቃል ስለዚህ የእውነትን ካባ በመደረብ ትመጣለች፡፡ ሰይጣንም አፍጥጦና አግጥጦ ከመጣ ብዙ ሰው ማንነቱን ያውቀዋል፤ ስለዚህ የብርሃን መልአክ መስሎ ይቀርባል፡፡ ይህንን እውነታ የተረዳ ሰው “በቁርአን ውስጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ ሐሳቦች ስላሉ ከሰይጣን ሊሆን አይችልም” የሚል ሙግት አያቀርብም፡፡

በማስከተል ደግሞ ቁርአን ከመጽሐፍ ቅዱስ አልኮረጀም ለሚለው አቋሙ አመክንዮአዊና ማስረጃዊ ሙግቶችን ለማቅረብ ሞክሯል፡፡

ያቀረበው አመክንዮአዊ ሙግት “መመሳሰል ሁሌም ኩረጃ አይደለም” የሚል ነው፡፡ ለዚህ ማብራርያ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፡-

ስለቁርአን ኩረጃ የሚያነሱ ክርስቲያኖች የሚነሱበት አንድ የተሳሳተ ምንስኤ/Premise/ አለ። እሱም ቁርአን ውስጥ የሚገኙና ከመጽሀፍ ቅዱስ ጋር የሚመሳሉ ታሪካዊም ሆነ አስተምህሯዊ ምንባቦች ከመጽሀፍ ቅዱስ የተቀዱ ብቻ ናቸው የሚል ነው። የዚህ መሠረቱ መጽሀፍ ቅዱስ ቅድሚያ የነበረ መጽሀፍ ከመሆኑ አንፃር መመሳሰሎች ካሉ በኩረጃ ሊወነጀል የሚገባው የኃለኛው ነው የሚል ጥቅል ድምዳሜ ነው። ይህ ድምዳሜ ግን ሁሌም ትክክል አይሆንም። ከኔ በፊት የነበሩ ግለሰቦች የተናገሩት እውነት እኔ በዘመኔ ብደግመው ኩረጃ ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ፦ 1+1 ስንት እንደሆነ ከኔ በፊት የነበሩ ሰዎች የሚያውቁትና የገለፁት ሁኔታ ነው። ማለት ግን ዛሬ ላይ እኔ 1+1 ስንት ነው? ተብየ ብጠየቅና 2 ብየ ብመልስ ከነሱ ቀድቻለሁ ማለት አይደለም። ይህ ከሰው የማትቀዳው ዝንተ አለም የማይቀያየር እውነታ ነው። በተመሳሳይ ምንጫቸው አንድ የሆኑ ነብያት ያመጡት መልዕክት በይዘት ቢመሳሰል አንደኛው ከአንደኛው ቀድቶ ሳይሆን መሠረቱ አንድና አንድ ስለሆነ ብቻ ነው።

ስለ ቁርአን ኩረጃዎች ጥናት ያደረጉ ወገኖች “ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚመሳሰሉ ታሪካዊም ሆነ አስተምህሯዊ ምንባቦች ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የተቀዱ ናቸው” በማለት ሲናገሩ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ የቁርአን ደራሲ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን የአይሁድና የክርስቲያን አዋልድ መጻሕፍን ከመሳሰሉት ደህራይ ምንጮች የቀዳ በመሆኑ በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ የወሰዳቸው ሐሳቦች ጥቂት ናቸው፡፡ በቀጥታ የተወሰዱትም ቢሆኑ የተዛቡ በመሆናቸው ደራሲው እያነበበ ሳይሆን በሌሎች ሲነገር የሰማውን ከትውስታው እየተናገረ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይህ በዚህ መስተካከል ይኖርበታል፡፡

አብዱሉ የቁርአን ኩረጃዎችን የወል ዕውቀት በሆነው 1+1 መመሰሉ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ከሞላ ጎደል የወል ዕውቀት ሳይሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን ያነበበ፣ ሲነበብ የሰማ ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተገለበጠ ምንጭ ላይ ያገኘ ሰው ሊያውቃቸው የሚችላቸው ናቸው፡፡ የአብርሃም፣ የሙሴ፣ የኤልያስ፣ የዳዊትና የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪኮች እንደ 1+1 በተፈጥሮ ሳይሆን ከመጽሐፍ ቅዱስና ከእርሱ ላይ ከተወሰዱት ምንጮች ብቻ ሊታወቁ የሚችሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ታሪኮች በአንድ መጽሐፍ ውስጥ ተደግመው ቢገኙ ከመጽሐፍ ቅዱስ መኮረጃቸው ግልፅ ነው፡፡

የሙሐመድና የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት ምንጭ አንድ እንደሆነ የተናገረው ግልፅ ሐሰት ነው፡፡ ምንጫቸው አንድ ከሆነ ሙሐመድ ስለምን በእነርሱ የተነገሩ ታሪኮችን አዛብቶ አቀረበ? ስለምንስ የእነርሱን ትምህርት የሚጻረሩ ትምህርቶችን አስተማረ? ሙሐመድ የነቢያትን ታሪኮችና ትምህርቶች በማጣመም መሠረታዊ አስተምህሯቸውን የሚጻረር እንግዳ ትምህርት የፈጠረ የሰይጣን አገልጋይ እንጂ እውነተኛ ነቢይ አይደለም፡፡

በማስከተል ይህ አብዱል ክርስትናን በኩረጃ ለመክሰስ ይሞክራል፡፡ እንዲህ ይላል፡-

ከዚህ ጋር ተያይዞ ለክርስቲያኖች እንደ አብነት የተወሰነ ምሳሌ መጥቀስ እንችላለን። ለምሳሌ ከኦሪትም ሆነ ከወንጌላት መፃፍ በፊት ከአይሁድም ሆነ ከክርስትና እምነት በፊት የነበሩ እምነቶች ውስጥ መጽሀፍ ቅዱስ ጋር የሚመሳሰሉ አመለካከቶች አሏቸው። የጥንት ፋርሶች/Persian Religion/ ብንመለከተ በከፉ መናፍስትና በአምላክ ማንነት ዙሪያ በመጠኑም ቢሆን ከክርስትናው ጋር የሚያስማሙ አስተምህሮቶች ነበሩት። ማለት መጽሀፍ ቅዱስ ከነዚህ እምነቶች ነው ኮርጆ አስተምህሮውን የቀመመው ማለት ነው? ከዚህ በተጨማሪ የጥንት ሜሴፖታሚያ ሀይማኖት ዘንድ የሚታመነውን የጎርፍ መጥለቅለቅ ታሪክ ከመጽሀፍ ቅዱሱ የኖህ ታሪክ ጋር ይመሳሰላልና ምንጩ እሱ ነው ማለት ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስና በቁርአን መካከል ያለው መመሳሰል እንደ ዞሮአስትሪያኒዝምና ይሁዲ የክፉና የመልካም አስተምህሮ “መጠነኛ” ተብሎ ሊታለፍ የሚችል ሳይሆን ኩረጃ መሆኑ በግልፅ የሚታይ ነው፡፡ የጥፋት ውኀ ታሪክ በመላው ዓለም እጅግ የተራራቁና ሊገናኙ የማይችሉ ሊባሉ በሚችሉ ሥልጣኔዎች ውስጥ ሲነገር የኖረ መሆኑ የታሪኩን እውነተኛነት የሚያሳይ ነው፡፡ ክስተቱ የሰው ልጆች ሁሉ ታሪክ በመሆኑ የወል ዕውቀት ልንለው እንችላለን፡፡ ዝርዝሩን በተመለከተ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ የብቻው የሆኑ ትረካዎች አሉ፡፡ ይህንን ትረካ ቁርአን ከመጽሐፍ ቅዱስ በመኮረጅ ወስዶታል፡፡

በመጨረሻም ይህ አብዱል “ማስረጃዊ” ያለውን ሙግቱን ያቀርባል፡፡ የመጀመርያው የሚያቀርበው ሙግት ቁርአን ከአይሁድ ታልሙድ መጻሕፍት መቅዳቱን በተመለከተ “መጻሕፍቱ ብዙ ስለሆኑ ሙሐመድ ሊቀዳ አይችልም” የሚል ነው፡፡

በመጀመርያ ደረጃ የመጻሕፍቱ ብዛት ምንም ያህል ቢሆን በውስጣቸው የሚገኙት ተረቶች በቁርአን ውስጥ እስከተገኙ ድረስ የተኮረጁ መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ሙሐመድ ሰዎች ረድተውትም ይሁን በራሱ ጥረት ከእነዚህ መጻሕፍት የተወሰዱ ታሪኮችን በቁርአን ውስጥ እንዲካተቱ አድርጓል፡፡ መቼስ ሙስሊም ወገኖች እነዚህ ቅድመ እስልምና የነበሩት የአይሁድ ተረቶች ከሰማይ የመጡ መገለጦች ናቸው ሊሉን አይችሉም፡፡ ከነቢያት ዘመን በኋላ የተጻፉ ተረቶች በምንም መስፈርት መለኮታዊ መገለጥ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

በሁለተኛ ደረጃ እነዚህ መጻሕፍት አይሁድ እንደ ሃይማኖት መመርያ የያዟቸው ስለሆኑ ቢያንስ ከእነርሱ የተወሰዱ ታሪኮች አይሁድ ባሉበት ሁሉ መኖራቸው ጥርጥር የለውም፡፡ የሆነው ሆኖ መለኮታዊ ምንጭ የሌላቸው የቅድመ እስልምና ተረቶቹ በቁርአን ውስጥ ስለተገኙ የተኮረጁ መሆናቸውን ማስተባበል አይቻልም፡፡

በመጨረሻም በቁርአን ውስጥ የተጠቀሰው የንግሥተ ሳባ ተረት የአስቴር ታርጉም ከተሰኘ የአይሁድ አዋልድ የተወሰደ መሆኑን በተመለከተ መልስ ለመስጠት ሞክሯል፡፡ ምላሹም የአስቴር ታርጉም ከሙሐመድ በኋላ በ700 እና 800 ዓ.ም. የተዘጋጁ ናቸው የሚል ነው፡፡ ዋቢ ይሆነው ዘንድም The Jewish Encyclopedia የተሰኘ መጽሐፍ ጠቅሷል፡፡ ሙስሊም አፖሎጂስቶች ለቁርአን ኩረጃ መልስ ሲሰጡ በተደጋጋሚ የሚጠቅሱትና ለመመለስ የሚደፍሩት የአስቴርን ታርጉም በተመለከተ ነው፡፡ ነገር ግን “ይህ ምላሽ” የተሳሳተ መሆኑ ከታወቀ ሰነባብቷል፡፡ የአገራችን ኡስታዞች በመሰል ጉዳዮች ዙርያ “መልስ” ከመስጠታቸው በፊት ከዚህ ቀደም የነበረው ሙግት ምን እንደሚመስል የማጥናት ልማድ ቢኖራቸው ጥሩ ነበር፡፡

አብዱሉ እንዲሁ የኢንሳይክሎፒድያውን ስምና ገፅ ጠቀሰ እንጂ የስንት ዓመተ ምህረት ዕትም እንደሆነ አልገለጸም፡፡ ይህ በጣም አስፈላጊ ነው ምክንያቱም ኢንሳይክሎፒድያዎች ብዙ ጊዜ ስለሚሻሻሉና ስለሚከለሱ መረጃዎች እንደየ ሁኔታው ሊሻሻሉ ይችላሉና፡፡

ስለ አስቴር ታርጉም የሚናገረው ኢንሳይክሎፒድያ በ 1905 ዓ.ም. የታተመ ሲሆን ስለ አስቴር ታርጉም ጥንታዊ ኮፒ እንጂ ታርጉሙ የተዘጋጀበትን ዘመን የሚጠቅስ አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ ኢንሳክሎፒድያው በ1925 እንደገና ተሻሽሎ ሲታተም መረጃው ከመጽሐፉ ውስጥ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ በዚህ ፋንታ የአስቴር ታርጉም ቅድመ እስልምና በ500 ዓ.ም. ተጽፎ በተጠናቀቀው የኢየሩሳሌም ታልሙድ ውስጥ መጠቀሱን በመግለፅ ቅድመ እስልምና የተጻፈ መጽሐፍ መሆኑን አረጋግጧል (The Jewish Encyclopedia 1925 edition by Funk & Wagnalls Company, Vol 12, p 63)፡፡ ሁለተኛውን የአስቴር ታርጉም ወደ እንግሊዘኛ የተረጎሙት በርናርድ ግሮስፈልድ መጽሐፉ በአራተኛው ክፍለ ዘመን በተለያዩ ምንጮች ውስጥ መጠቀሱን በማውሳት በአራተኛው ክፍለ ዘመን የነበረ መጽሐፍ መሆኑን አረጋግጠዋል (The Targum of Esther (Second) (Targum Sheni) Translated by Bernard Grossfeld, 1991, Introduction)፡፡

ስለዚህ ይህ አብዱል ጊዜው ያለፈበትን የተዛባ መረጃ በመጥቀስ የቁርአንን ኩረጃ ለማስተባበል ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም፡፡ በዚህ ርዕስ ላይ በክርስቲያንና ሙስሊም ምሑራን መካከል የተደረገውን ክርክር እዚህ ጋ ጠቅ በማድረግ ማንበብ ትችላላችሁ፡፡

ይህ አብዱል ሌሎቹን የቁርአን ኩረጃዎች በተመሳሳይ መንገድ ምላሽ እንደሚሰጥ ቃል በመግባት ጽሑፉን አጠናቋል፡፡ እኛም መልካም ዕድል ብለነዋል፡፡

 

የቁርአንን ኩረጃዎች ለማስተባበል የተደረገ ከንቱ ጥረት – ዙር ሁለት

ቅዱስ ቁርአን