የቁርኣን ትንቢት? ክፍል 1

የቁርኣን ትንቢት?

ክፍል 1

ሙሐመድ እውነተኛ ነቢይ አለመሆኑን ከሚያሳዩ ማስረጃዎች መካከል አንዱ ለፍጻሜ የበቃ አንዳችም ትንቢት አለመናገሩ ነው፡፡ ነቢይ ማለት መጻዒ ነገሮችን የመተንበይ ጸጋ ያለው እንደመሆኑ ከፈጣሪ ዘንድ ተልኬያለሁ የሚል ማንኛውንም ሰው በዚህ መስፈርት መመዘን እውነተኛነቱን ለማወቅ ጥሩ መንገድ ነው፡፡ ዳሩ ግን ሙሐመድን በዚህ ሚዛን የመዘንን እንደሆን ውድቅ ሆኖ ስለሚገኝ የመስፈርቱን ወሳኝነት የተገነዘቡ ሙስሊም ሰባኪያን ለነቢይነቱ ማረጋገጫ የሚሆኑ “የተፈጸሙ” ትንቢቶችን ፍለጋ ሲደክሙ ይታያሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ መሰል ጥረቶችን ካደረጉ ሰባኪያን መካከል የአንዱን ሙግት የምንመለከት ይሆናል፡፡

ፍሬዎች ፆታ አላቸውን?

በቁርኣን ውስጥ ሙሐመድ ፍሬዎች ሁሉ ጥንድ ሆነው እንደተፈጠሩ ተናግሯል፡፡ ሙስሊሙ ሰባኪ የትንቢት ፍጻሜ በማስመሰል የጠቀሰው ጥቅስ እንዲህ ይነበባል፡-

“እርሱም ያ ምድርን የዘረጋ በእሷም ተራራዎችን እና ወንዞችን ያደረገ በውስጧም ከፍሬዎች ሁሉ ሁለት ሁለት ጥንዶችን ያደረገ ነው፡፡ ሌሊትን በቀን ይሸፍናል፡፡ በዚህም ውስጥ ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች ታምራቶች አሉ፡፡” (ሱራ 13፡3)

ሙስሊሙ ሰባኪ ይህ ጥቅስ “ትንቢታዊ” መሆኑን ሊያስረዳን የሚሞክረው እንዲህ በማለት ነው፡-

36፥36 ምድር ከምታበቅለው፣ ከራሶቻቸውም፣ ከማያውቁትም ነገር ጥንዶችን ሁሏንም የፈጠረ ጥራት ይገባው፡፡ “ከማያውቁትም ነገር ጥንዶችን” ማለት በቁርኣን መውረድ ጊዜ የዕጽዋት ጥንድነት ዐለመታወቁን ያሳያል። አምላካችን አላህ ጊዜው ሲደርስ በ 19ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች ታምራት ይሆን ዘንድ ዕፅዋት ጾታ እንዳላቸው ዐሳውቆናል። “ጋይኒ” γυνή ማለት “ሴቴ” ማለት ሲሆን ይህቺ የዕፅዋት እንቁላል ህዋስ ”gynoecious” በሥነ-ሕይወት ጥናት “ካርፔልስ”carpels” ትባላለች፥ “አንድሮ” ἀνήρ ማለት “ወንዴ” ማለት ሲሆን የዕፅዋት የዘር ህዋስ ”Androecium” በሥነ-ሕይወት ጥናት “ስቴመንስ”stamens” ይባላል። ቁርኣን ከያዛቸው መካከል “አል-ገይቡል ሙሥተቅበል”  ማለትም “መጻእያት የሩቅ ወሬ” ነው፥ ይህንን ትንቢት ከጊዜ በኋላ በእርግጥ ታውቁታላችሁ ባለን መሠረት ዛሬ በዘመናችን ዐውቀነዋል፦ 38፥88 «ትንቢቱንም ከጊዜ በኋላ በእርግጥ ታውቁታላችሁ፡፡

የሙግቱን ስሁትነት ከማስረዳታችን በፊት የዚህን ሰው አንድ ስህተት በመጠቆም እንጀምር፡፡ ይህ ሰው ራሱን ምሑር ለማስመሰል ብዙ ጊዜ የግሪክ ቃላትን ሲጠቅስ ይታያል፡፡ ይህንንም የሚያደርገው ቋንቋውን በማወቅ ሳይሆን ለጽሑፉ ክብደት በመጨመር “ምሑር” ለመሰኘት ነው፡፡ አስቂኝ የሆነው ጉዳይ ግን እንኳንስ ቋንቋውን ሊያውቅ ይቅርና ፊደላቱን እንኳ ለይቶ አለማወቁ ነው፡፡ ለዚህም ነው γυνή (ጉኔ) የሚለውን “ጋይኒ”ἀνήρ (አኔር) የሚለውን “አንድሮ” ብሎ ያነበበው፡፡ በረባው ባልረባው የማያውቁትን ቋንቋ እየጠቀሱ ከመዘላበድ ቢቀርስ? አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ የሚያውቁትን ሰዎች መጠየቅ፤ መጻሕፍትን ማመሳከር፤ ዕድል ከተገኘ ቋንቋውን መማር ይቻላል፡፡ በማያውቁት ገብቶ ምሑር ለመምሰል አጉል መወጣጠር ትርፉ ቅሌት ነው፡፡

ወደ ዋናው ጉዳይ ስንገባ ይህንን የቁርኣን ጥቅስ “የተፈጸመ ትንቢት” በማስመሰል ማቅረብ ከጅምሩ ስህተት ነው፡፡ ጥቅሱ የሙሐመድን ነቢይነት የሚያረጋግጥ ሳይሆን ተቃራኒውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ስህተቱን በሦስት ከፍለን እንመልከት፡-

1. ወንዴና ሴቴ ዕፅዋት ወይንም የዕፅዋት አበቦች እንጂ ፆታ ያለው ፍሬ የለም፡፡ እንደዚህ የሚል ነገር በየትኛውም የሳይንስ መጽሐፍ ውስጥ አይገኝም፡፡ ቁርኣን “ፍሬ” ሲል አጠቃላዩን ተክል ለማመልከት ነው ብለን ካላጠጋጋን በስተቀር ወንዴና ሴቴ የሚባል የፍሬ ዓይነት የለም፡፡ ይህ የመጀመርያው ስህተት ነው፡፡

2. በቁጥር አንድ ላይ የተጠቀሰውን ስህተት ችላ ብለን በዕፅዋት ደረጃ እናስብ ከተባለ ወንዴና ሴቴ የሆኑ ዕፅዋት በቁጥር አነስተኛ ሲሆኑ አብዛኞቹ ዕፅዋት በአበቦቻቸው ውስጥ ወንዴም ሴቴም ያላቸውና ሌሎች ደግሞ ያለ ፆታ መራባት የሚችሉ ናቸው፡፡ የቁርኣን ጸሐፊ ግን ሁሉም ፍሬዎች ጥንድ ሆነው እንደተፈጠሩ ይነግረናል፡፡ ሙስሊሙ ሰባኪ ለዚህ ምላሽ ይሆንልኛል በማለት ተከታዩን ሐሳብ አቅርቧል፡-

ኩል” ማለትም “ሁሉ” የሚለው ቃል ፍጹማዊ “Absolute” ሆኖ ሲመጣ “ሙጥለቅ” ሲባል፥ በአንጻራዊ “Relative” ሆኖ ሲመጣ ደግሞ “ቀሪብ”  ይባላል፥ እዚህ አንቀጽ ላይ “ኩል” ቀሪብ ሆኖ የምናውቀው “ሁሉ” በሚለው ገላጭ ቅጽል መነሻ ላይ “ሚን” ማለትም “ከ” የሚል መስተዋድድ መኖሩ ነው። “ከ”ፍሬዎች ሁሉ” ማለት እና “ፍሬዎች ሁሉ” ማለት ሁለት ለየቅል ትርጉም አላቸው፥ ከፍራፍሬዎች መካከል ጥንድ ያልሆኑ በከፊል መኖራቸው ይህንኑ ያሳያል።

ሙስሊሙ ሰባኪ “ሁሉ” የሚለው ቃል ትርጉሙ ምን እንደሆነ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ “ከፍሬዎች ሁሉ” ማለት “ፍሬ ከተባለ ነገር ሁሉ” ማለት እንጂ “የተወሰኑ ፍሬዎች” ማለት አይደለም፡፡ “ሁሉ” የሚል ጠቅላይ ቃል እስከገባ ድረስ “ከ” የሚል መስተዋድድ በዚህ አውድ ለውጥ አያመጣም፡፡ “ከፍሬዎች ሁሉ” ማለት “ከሁሉም ፍሬዎች” ማለት ነው፡፡ ሰባኪው ከተናገረው በተጻራሪ የተለያዩ የእንግሊዘኛ ትርጉሞችን ስንመለከት ሁሉም ፍሬዎች ጥንድ ተደርገው እንደተፈጠሩ በሚያመለክት መንገድ ተርጉመውታል፡፡

and fruit of every kind He made in pairs, two and two (Yusuf Ali)

and of all fruits He placed therein two spouses (male and female). (Pickthall)

and of fruits of every kind HE made therein two sexes. (Sher Ali)

and from all of the fruits He made therein two mates; (Saheeh International)

and created thereon two sexes of every [kind of] plant; (Muhammad Asad)

ከላይ የተጠቀሱት ትርጉሞች ሁሉ እንደሚያመለክቱት የቁርኣን ደራሲ ከፍሬዎች መካከል ስለተወሰኑት ሳይሆን ስለ ፍሬዎች ሁሉ እየተናገረ ነው፡፡ ቀደም ሲል እንዳልነው ፆታ ያለው ፍሬ አለመኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ “ፍሬ” ሲል አጠቃላዩን ተክል ለማመልከት የገባ ነው ቢባል እንኳ ሁሉም ተከሎች ጥንድ ፆታ ያላቸው ባለመሆናቸው ጥቅሱ ስህተት ነው፡፡

3. ሙስሊሙ ሰባኪ ጥንድ ዕፅዋት መኖራቸው በሙሐመድ ዘመን የማይታወቅ በማስመሰል ቢናገርም ሃቁ እንደርሱ አይደለም፡፡ እውነት ነው በጽሑፍ በሰፈሩት መረጃዎች መሠረት ዕፅዋት ፆታ እንዳላቸው የታወቀው በቅርብ ጊዜ ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ቴምርና ፓፓያ ያሉ ዕፅዋት ጥንድ ተደርገው ካልተተከሉ በስተቀር ምርት አለመስጠታቸው ከጥንትም ያለ የተፈጥሮ እውነታ በመሆኑ ምናልባት በሙሐመድ ዘመን የነበሩ ሰዎች ሚስጥሩን አያውቁት ይሆናል እንጂ ጥንድ መሆናቸውን አለማወቅ የሚችሉበት ምንም ዓይነት ተዓምር የለም፡፡ ሙሐመድ በአረብያ በብዛት የሚመረተውን ቴምር በመመልከት ዕፅዋት ሁሉ ተመሳሳይ ተፈጥሯዊ ባሕርይ እንዳላቸው በመደምደም ይህንንም ስህተት የአምላክ መገለጥ በማስመሰል በመናገር ሐሰተኝነቱን ግልፅ አድርጓል፡፡ ሙስሊም ሰባኪያን ግን “ምንተስኖት” በሆነው ምላሳቸው ሃቁን በማጣመም እውነትን ሐሰት ሐሰትን ደግሞ እውነት ለማድረግ ይፍጨረጨራሉ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ማስተዋልን ይስጣቸው፡፡ አሜን፡፡

የቁርኣን ትንቢት?