የቁርኣን ትንቢት? ክፍል 2

የቁርኣን ትንቢት?

ክፍል 2

ፈጠራ የማይሰለቸው የሙስሊም ሰባኪያን ብዕር ሙሐመድን ነቢይ ለማሰኘት የቁርኣን ጥቅሶችን በመጠምዘዝ አዳዲስ “ትንቢቶችን” መፍጠሩን ቀጥሏል፡፡ አንድ ሰለምቴ ነኝ ባይ ዳዋጋንዲስት በማሕበራዊ የመገናኛ ብዙኀን ላይ እየተዘዋወረ በሚገኝ ጽሑፉ ቁርኣን ስለ ዘመናዊ መጓጓዣዎች አስቀድሞ ትንቢታዊ ቃል አስቀምጧል ይለናል፡፡ ይህንን “ትንቢት” ከዚህ ቀደም አቡ ሃይደር የተሰኘ ሌላ ዳዋጋንዲስት ጠቅሶት የነበረ ሲሆን በወቅቱ ብዙዎች ተሳልቀውበት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ “ትንቢቱ” እንደሚከተለው ይነበባል፡-

ሱራ 16፡8 “ፈረሶችንም፣ በቅሎዎችንም፣ አህዮችንም ልትቀመጡዋቸውና ልታጌጡባቸው ፈጠረላችሁ፡፡ የማታውቁትንም ድንቅ ነገር ይፈጥራል፡፡”

ከዚህ ጥቅስ በመነሳት የሚያቀርቡት ሙግት የመጓጓዣ እንስሳትን ከጠቀሰ በኋላ “የማታውቁትንም ድንቅ ነገር ይፈጥራል” ማለቱ እንደ መኪና፣ ባቡር፣ ባለሞተር መርከብና አውሮፕላን ያሉ መጓጓዣዎችን እንደሚፈጥር ያመለክታል የሚል ነው፡፡ እነዚህ ዘመናዊ መጓጓዣዎች በሙሐመድ ዘመን ስላልነበሩና ሙሐመድ ስለነዚህ ጉዳዮች ማወቅ የሚችልበት መንገድ ስላልነበረ ነቢይነቱን የሚያረጋግጥ ትንቢት ነው ይላሉ፡፡

በግልፅ እንደሚታየው ጥቅሱ ስለ አላህ ፍጥረት እንጂ ስለ ሰዎች ፈጠራ እየተናገረ አይደለም፡፡ ስለ ገዛ ፍጥረቱና ሌሎች ፍጥረታትንም እንደሚፈጥር እየተናገረ ባለበት ሁኔታ የሰዎች ፈጠራ የሆኑትን ዘመናዊ መጓጓዣዎችን የተመለከተ ነው ብሎ ማለት ትርጉም አይሰጥም፡፡ አላህ ስለ ሰዎች ፈጠራ መናገር ቢፈልግ ኖሮ እንደ ፈረስ፣ በቅሎና አህያ ያሉትን ሕያዋን ፍጥረታት ብቻ ሳይሆን በሙሐመድ ዘመን የነበሩትን እንደ መርከብ፣ ጀልባ፣ ሠረገላ፣ በሰዎች የሚጎተት ጋሪና የመሳሰሉትን መጓጓዣዎች ቀላቅሎ በመጥቀስ እነርሱን የሚመስሉ ሌሎችን እንደሚፈጥር በተናገረ ነበር፡፡ ሁሉንም ፍጥረታት የፈጠረውና ለሰው ልጆችም የመፍጠር ችሎታን ያጎናፀፈው ሕያው አምላክ በመሆኑ ምክንያት የሁሉም ፈጠራ ባለቤት እርሱ መሆኑን ብንቀበልም ነገር ግን እርሱ ራሱ በቀጥታ ስለፈጠራቸው ሕያዋን ፍጥረታት እየተናገረ ባለበት አውድ የሰው እጅ ሥራዎች ስለሆኑት ግዑዛን ማሽኖች እየተናገረ ነው ማለት የማይመስል ነው፡፡ ደግሞ እውነተኛው አምላክ ስለ ዘመናዊ መጓጓዣዎች ትንቢታዊ ቃል መስጠት ከፈለገ እንዲህ ባለ በተድበሰበሰ መንገድ ስለምን ይናገራል? ግልፅ በሆነ ቋንቋ እኮ መናገር ይችላል፡፡ እርሱ ሁሉን አዋቂ አምላክ አይደለምን?

የሚገርመው ነገር ሙስሊም ሰባኪያን ከላይ ላነሳነው መቃወሚያ ምላሽ አለን ይላሉ፡፡ ምላሻቸውም አላህ በሌላ ቦታ ላይ የኖኅን መርከብ እርሱ እንደፈጠረ ስለተናገረ ሌሎች ሰው ሠራሽ ዘመናዊ መጓጓዣዎችንም ፈጥሯል የሚል ነው፡፡ የሚጠቅሱት ጥቅስ እንዲህ ይነበባል፡-

ሱራ 36፡41 “እኛም የቀድሞ ትውልዳቸውን በተሞላች መርከብ ውስጥ የጫን መኾናችን ለእነርሱ ምልክት ነው፡፡ ከመሰሉም በእርሱ የሚሳፈሩበትን ለእነርሱ ፈጠርንላቸው፡፡”

በዚህ ጥቅስ ውስጥ አላህ እየተናገረ ያለው ሙስሊም ዳዋጋንዲስቶች እንደሚሉት የኖኅን መርከብ መፍጠሩን ሳይሆን መርከቡን የሚመስል ሌላ ነገር መፍጠሩን ነው፡፡ ይህ አላህ የፈጠረው መርከብ የሚመስል ነገር ምንድነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሹ ኢብን ከሢር ኢብን አባስን ጠቅሶ በተናገረው መሠረት “የበረሃ መርከብ” የተባለው ግመል ነው፡-

“(And We have created for them of the like thereunto, on which they ride.) Al-`Awfi said, narrating from Ibn `Abbas, may Allah be pleased with him, “This means the camel, for it is the ship of the land on which they carry goods and on which they ride…”

“(ከመሰሉም በእርሱ የሚሳፈሩበትን ለእነርሱ ፈጠርንላቸው፡፡) አል ዓውፊ ከኢብን አባስ የሰማውን እንዲህ ሲል አውርቷል፡- “ይህ ማለት ግመል ነው፤ ዕቃ የሚጭኑበትና የሚሳፈሩበት የየብስ መርከብ ነውና…” Tafseer Ibn Kathir, https://quranx.com/tafsirs/36.41

ሌሎች ሙፈሲሮች ደግሞ ከኖኅ መርከብ ጋር የሚመሳሰሉ ሌሎች መርከቦችን የተመለከተ ሊሆን እንደሚችል አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል፡፡  ነገር ግን “ወኸለቅነ” (ፈጠርን[ላቸው]) የሚለው የአረብኛ ቃል በአላፊ ጊዜ የተቀመጠ እንጂ የወደፊት ፍጥረትን የሚያሳይ ባለመሆኑ በቦታው የተመለከተው ፍጥረት ግመል ነው የሚለው የኢብን አባስ አመለካከት ይበልጥ አሳማኝ ነው፡፡ ስለዚህ አላህ የሰው ልጆች የሠሯቸው ግዑዛን መጓጓዣዎች እንደ እንስሳት ሁሉ የእርሱ ፍጥረታት መሆናቸውን በግልፅ የተናገረበት ቦታ በቁርኣን ውስጥ የለም፡፡

ስናጠቃልል ሱራ 16፡8 ላይ አላህ ሕያዋን ፍጥረታትን ከጠቀሰ በኋላ “የማታውቁትንም ድንቅ ነገር ይፈጥራል” ማለቱ የመፍጠር ችሎታ የእርሱ መሆኑን ለመግለፅ እንጂ ሙስሊም ሰባኪያን እንደሚሉት የአየር መጓጓዣ አውሮፕላን፣ ጀት፣ ሔሊኮፕተር፥ የየብስ መጓጓዣ መኪና፣ ባቡር፥ የባሕር መጓጓዣ ባለ ሞተር መርከብ ወዘተ. የመሳሰሉትን የሰው እጅ ሥራዎች እንደሚፈጥርልን እየተናገረ አይደለም፡፡ ሙስሊም ወገኖች የክርስቲያኖችና የአይሁዶች ፈጠራዎች የሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እየቆጠሩ “ቁርአናችን ተናግሮ ነበር! አል-ሐምዱሊሏህ! አላህ ወክበር!” እያሉ ዘመናቸውንና የእነርሱን ከንቱ ዲስኩር የማይቀበሉትን ወገኖች ከሚፈጁ እግዚአብሔር የሰጣቸውን አእምሮ ተጠቅመው እንደ ክርስቲያኖችና አይሁዶች ለሰው ልጆች መሻሻል የረባ ሳይንሳዊ አስተዋፅዖ ቢያበረክቱ የተሻለ ነው የሚል አስተያየት አለኝ፡፡



መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አየር ትራንስፖርት የተናገረው ትንቢት

ሙስሊም ወገኖቻችን ትንቢት ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንዲያውቁ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ምሳሌ እናሳያቸው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት 700 ዓመታትን ቀድሞ የኖረው ነቢዩ ኢሳይያስ እስራኤላውያን ከመላው ዓለም ወደ ምድራቸው ስለመመለሳቸው በተነበየበት ክፍል በምን ዓይነት መጓጓዣዎች እንደሚመለሱ ሲናገር እንዲህ ይላል፡፡ (ትንቢቱ የተፈጸመና ሊፈጸም ያለ ገፅታ እንዳለው ልብ ይሏል)፡-

“ዓይኖችሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሙአቸዋል። በዚያን ጊዜ የባሕሩ በረከት ወደ አንቺ ስለሚመለስ፥ የአሕዛብም ብልጥግና ወደ አንቺ ስለሚመጣ፥ አይተሽ ደስ ይልሻል፥ ልብሽም ይደነቃል ይሰፋማል። የግመሎች ብዛት፥ የምድያምና የጌፌር ግመሎች፥ ይሸፍኑሻል ሁሉ ከሳባ ይመጣሉ፥ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ። የቄዳር መንጎች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ የነባዮትም አውራ በጎች ያገለግሉሻል እኔን ደስ ሊያሰኙ በመሠዊያዬ ላይ ይወጣሉ፥ የክብሬንም ቤት አከብራለሁ። ርግቦች ወደ ቤታቸው እንደሚበርሩ፥ እነዚህ እንደ ደመና የሚበርሩ እነማን ናቸው? እርሱ አክብሮሻልና ለአምላክሽ ለእግዚአብሔር ስምና ለእስራኤል ቅዱስ ልጆችሽን ከሩቅ ከእነርሱ ጋርም ብራቸውንና ወርቃቸውን ያመጡ ዘንድ ደሴቶች የተርሴስ መርከቦችም አስቀድመው ይጠባበቁኛል።” (ኢሳይያስ 60፡4-9)

በዚህ ትንቢት ውስጥ እንደተመለከተው የተበተኑት አይሁዳውያን በየብስና በባሕር ብቻ ሳይሆን በአየርም ጭምር ወደ ምድራቸው ይመለሳሉ፡፡ እስራኤላውያን ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ወደ ተፈናቀሉባት ምድር እንደሚመለሱ የተነገረው ትንቢት በሃያኛው ክፍለ ዘመን ወደ ፍጻሜ መምጣቱ አስደናቂ ሆኖ አውሮፕላን ባልተሠራበት ዘመን ሰዎች በአየር ላይ እየበረሩ ወደ ምድራቸው እንደሚመለሱ ነቢዩ ኢሳይያስ መናገሩ ደግሞ ትንቢቱን ይበልጥ አስደማሚ ያደርገዋል፡፡ ነቢዩ ርግቦች ወደ ቤታቸው እንደሚበርሩ፥ እነዚህ እንደ ደመና የሚበርሩ እነማን ናቸው?” ብሎ በመደነቅ ሲናገር የርግብ ቅርፅ ያላቸው ነገር ግን ክንፎቻቸውን ሳያርገበግቡ እንደ ደመና ወደፊት የሚበሩ አውሮፕላኖችን በመንፈሱ እንደተመለከተ ግልፅ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ሙስሊም ሰባኪያን በቁርኣን ላይ እንደሚፈፅሙት ጥምዘዛና ቆርጦ መቀጠል የማያስፈልገው ግልፅ ትንቢት ነው፡፡ ውድ ሙስሊም ወገኖች፤ ትንቢት ማለት እንዲህ ነው! መለኮታዊ ሽታ ከሌለው የሰው ፈጠራ ከሆነው ከቁርኣን ውስጥ ትንቢት ለማግኘት ስትቆፍሩ፣ ስትቆርጡና ስትቀጥሉ ዕድሜያችሁን ከምታባክኑ እውነተኛ መለኮታዊ ቃል ወደ ሆነው ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ትመለሱ ዘንድ ጥሪ እናቀርብላችኋለን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ይርዳችሁ!

የቁርኣን ትንቢት?