የቁርኣን ትንቢት? ቁርኣን ስለ አተም ክፍልፋዮች ይናገራልን?

የቁርኣን ትንቢት?

ቁርኣን ስለ አተም ክፍልፋዮች ይናገራልን?

ሙስሊም ዳዋጋንዲስቶች በቁርኣን ውስጥ ተተንብየዋል በማለት ከሚያቀርቧቸው ሳይንሳዊ እውነታዎች መካከል አንዱ አተሞችን የተመለከተ ነው፡፡ ቁርኣን ስለ አተም ብቻ ሳይሆን በአተም ውስጥ ስለሚገኙት እንደ ኤሌክትሮን፣ ኒውትሮንና ፕሩቶንን ስለመሳሰሉት ጥቃቅን ክፍልፋዮች ተናግሯል ይላሉ፡፡ ከሙሐመድ ዘመን በብዙ ክፍለ ዘመናት ቀድመው የኖሩት ግሪኮች ስለ አተም አስቀድመው ስላስተማሩ አተምን የተመለከተ ጥቅስ በቁርኣን ውስጥ አለ ቢባል እንኳ አስቀድሞ የተነገረን ዕውቀት ከመድገም የዘለለ ባለመሆኑ ከትንቢት የሚቆጠር አይሆንም፡፡ በማስከተል እንደምንመለከተው ሙስሊም ሰባኪያን ከሚነዙት የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በተጻራሪ ቁርኣን ስለ አተምም ሆነ በውስጡ ስለሚገኙት ክፍልፋዮች ምንም የሚናገረው ነገር የለም፡፡ አንድ ሙስሊም ሰባኪ እንዲህ ሲል ጽፏል፡-

“ዘራህ” ذَرَّة የሚለው ቃል “ደቂቅ” ንዑስ” “ኢምንት” “ብናኝ”Atom” ማለት ሲሆን ጥቃቅን ነገር ነው፦

99፥7 የብናኝ ክብደት ያክልም መልካምን የሠራ ሰው ያገኘዋል፡፡

99፥8 “የብናኝ ክብደት ያክልም ክፉን የሠራ ሰው ያገኘዋል”፡፡ 

“ብናኝ” ለሚለው የገባው ቃል “ዘራህ” ذَرَّة መሆኑ አንባቢ ልብ ይለዋል። ዐረቦች ከጥቃቅን ፍጥረት አነስተኛ የሚሉት “ጉንዳን” ነበር። ነገር ግን ቁርኣኑ “ጉንዳን” ለሚለው ቃል የሚጠቀመው “ዘራህ” ذَرَّة ሳይሆን “ነምል” نَّمْل ነው፦

27፥18 በጉንዳንም ሸለቆ በመጡ ጊዜ አንዲት ጉንዳን «እናንተ ጉንዳኖች ሆይ! ወደ መኖሪያዎቻችሁ  ግቡ፡፡ ሱለይማንና ሰራዊቱ እነርሱ የማያውቁ ሲኾኑ አይሰባብሩዋችሁ» አለች፡፡

ሲቀጥል “ጉንዳን” በሰማያትና በምድር ውስጥ አይገኝም። ብናኝ”Atom” ግን በሰማያትና በምድር ውስጥ አለ፦

34፥3 እነዚያ የካዱትም «ሰዓቲቱ አትመጣብንም» አሉ፡፡ በላቸው «አይደለም፤ ሩቁን ሁሉ ዐዋቂ በኾነው ጌታዬ እምላለሁ፡፡ በእርግጥ ትመጣባችኋለች፡፡ “የብናኝ ክብደት ያክል እንኳ በሰማያትና በምድር ውስጥ ከእርሱ አይርቅም፡፡ ከይህ ያነሰም ኾነ የበለጠ የለም በግልጹ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበ ቢኾን እንጅ፡፡»

እዚህ አንቀጽ ላይ በግልጹ መጽሐፍ በተጠበቀው ሰሌዳ ውስጥ ከብናኝ ያነሰም ኾነ የተለቀ ፍጥረት የተመዘገበ መሆኑን ፍትንትውና ቁልጭ አርጎ ያሳያል። “ዛሊከ” ذَٰلِكَ ማለትም “ይህ” የሚለው አመልካች ተውላጠ-ስም “ዘራህ” ذَرَّة የሚለውን ስም ተክቶ የመጣ ነው፥ ከአተም ያነሰ በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለ ነገር ኤሌክትሮን፣ ፕሮቶን፣ ኒውትሮን ነው…

በአማርኛ “የብናኝ ክብደት” ተብሎ የተተረጎመው በአረብኛ “ሚሥቀለ ዘረቲን” የሚል ሲሆን በቁርኣን ውስጥ ስድስት ጊዜ ተጠቅሷል (ሱራ 4፡40፣ 10፡61፣ 34፡3፣ 33፡22፣ 99፡7፣ 99፡8)፤ ቀጥተኛ ትርጉሙም ይህ ሙስሊም ሰባኪ ለመካድ ከሞከረው በተጻራሪ “የጉንዳን ክብደት” ማለት ነው፡፡ ይህም ከዕውቁ የሌን አረቢክ ሌግዚከን ጀምሮ የአረብኛ መዝገበ ቃላት ያስቀመጡት ትርጉም ሲሆን የተለያዩ የእንግሊዘኛ የቁርኣን ተርጓሚዎችም በዚሁ መንገድ አስቀምጠዋል፡፡

ምንጭ፡- http://www.studyquran.net/LaneLexicon/Volume3/00000123.pdf

ከመዝገበ ቃላቱ ከተወሰደው ከላይ በሚገኘው ምስል ላይ በግልፅ እንደሚታየው “ዘረህ” የሚለው የአረብኛ ቃል ተቀዳሚና ቀጥተኛ ትርጉም “ጉንዳን” የሚል ነው፡፡ ቃሉን “ጉንዳን” በማለት የተረጎሙት የእንግሊዘኛ የቁርኣን ትርጉሞች የሚከተሉት ናቸው፡-

Lo! Allah wrongeth not even of the weight of an ant; and if there is a good deed, He will double it and will give (the doer) from His presence an immense reward. S. 4:40 Pickthall

Surely God shall not wrong so much as the weight of an ant; and if it be a good deed He will double it, and give from Himself a mighty wage. S. 4:40 Arberry

Surely! Allah wrongs not even of the weight of an atom (or a small ant) but if there is any good (done), He doubles it, and gives from Him a great reward. S. 4:40 Al-Hilali & Khan

Thou art not upon any occupation, neither recitest thou any Koran of it, nor do you any work, without that We are witnesses over you when you press on it; and not so much as the weight of an ant in earth or heaven escapes from thy Lord, neither is aught smaller than that, or greater, but in a Manifest Book. S. 10:61 Arberry

The unbelievers say, the hour [of judgement] will not come unto us. Answer, yea, by my Lord, it will surely come unto you; [it is he] who knoweth the hidden secret: The weight of an ant, either in heaven or in earth, is not absent from him, nor any thing lesser than this or greater, but [the same is written] in the perspicuous book [of his decrees]; S. 34:3 Sale

“የጉንዳን ክብደት” የሚለው በአረብኛ ዘይቤያዊ ንግግር ሲሆን ክብደቱ ኢምንት የሆነን ነገር ወይንም ብናኝን ለማመልከት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ ጥቅሱን “አተም” በማለት የተረጎሙ ሙስሊም ተርጓሚዎች ቢኖሩም የቃሉ ቀጥተኛ ትርጉም አተምን አያመለክትም፡፡ “አተም” ተብሎ ሊተረጎም ቢችል እንኳ ፅንሰ ሐሳቡ የአተምን ሳይንሳዊ ትንታኔ አይሸከምም፡፡ ሙስሊም ሰባኪያን የግድ አተምን የሚያመለክት የአረብኛ ቃል ቢያደርጉትም “አተም” የሚለው ቃልም ሆነ የተወሰነ ሳይንሳዊ ገፅታው ከእስልምና ዘመን ከብዙ ክፍለ ዘመናት በፊት የግሪክ ፈላስፎች የጠቀሱትና ትንታኔ የሰጡበት ጉዳይ በመሆኑ የቁርአኑን ጥቅስ ሳይንሳዊ ተዓምር የሚያደርገው ምንም ነገር የለም፡፡

ጥንታውያን ሙስሊሞች የግሪክ ጽሑፎችን ወደ አረብኛ በሚተረጉሙበት ወቅት “አቶሞስ” የሚለው የግሪክ ቃል ሲያጋጥማቸው በቁርኣን ውስጥ የሚገኘውን “ሚሥቀለ ዘረቲን” የሚለውን ቃል ከመጠቀም ይልቅ “ነጠላ ባሕርይ” የሚል ትርጉም ያለውን  “አል-ጀውሐር አል-ፈርድ” (الجوهر الفرد) የሚል ቃል እንደመረጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ “ሚሥቀለ ዘረቲን” የሚለውን ሐረግ አተምን ለማመልከት መጠቀም የተጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ (በጽሑፉ መቋጫ የተሰጡትን አስፈንጣሪዎች ይመልከቱ)

ሙስሊሙ ሰባኪ ከላይ የሚገኘውን የቁርኣን ጥቅስ ጫፍ በመያዝ እንዲህ የሚል ትንታኔ ያስነብበናል፡-

እዚህ አንቀጽ ላይ በግልጹ መጽሐፍ በተጠበቀው ሰሌዳ ውስጥ ከብናኝ ያነሰም ኾነ የተለቀ ፍጥረት የተመዘገበ መሆኑን ፍትንትውና ቁልጭ አርጎ ያሳያል። “ዛሊከ” ذَٰلِكَ ማለትም “ይህ” የሚለው አመልካች ተውላጠ-ስም “ዘራህ” ذَرَّة የሚለውን ስም ተክቶ የመጣ ነው፥ ከአተም ያነሰ በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለ ነገር ኤሌክትሮን፣ ፕሮቶን፣ ኒውትሮን ነው። ከአተም ያነሰ ነገር አለ ተብሎ ስለማይታመን “አቶም” ወይም  “አተም” የሚለው  ቃል እራሱ “አቶሞስ” ἄτομον ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙ “የማይከፋፈል”indivisible” ማለት ነው። አቶም ሁሉም ቁስ የተገነባበት መሰረታዊ ንዑስ ነው፥ እስከ አስራ ዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ከአቶም ወደ ታች ፍጥረት አለ ተብሎ አይታመንም ነበር። የፊዚክስ ምሁር ጆን ዳልተን እንኳን አቶም በውስጡ ፍጥረት አለው ብሎ አያምንም ነበር፥ ነገር ግን እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በ 1897 ድኅረ-ልደት ላይ ጆን ቶምሶን፣ በ 1911 ድኅረ-ልደት ላይ ኤርነስት ራዘርፎርድ ወዘተ ከአተም ያነሱ የቁስ መጠን ክፍፍሎች“particle” አግኝተው ገለጡ። እነዚህም፦ ኤሌክትሮን፣ ፕሮቶን፣ ኒውትሮን፣ ፈርሚኦን፣ ሌፕቶን፣ ቦሶን፣ ፎቶን፣ ዲላቶን፣ ሳክሲኦን፣ አክሲኦን የመሳሰሉት ናቸው። በተለይ ኤሌክትሮን፣ ፕሮቶን እና ኒውትሮን በሁሉም ቁስ ላይ የሚገኙ ከአቶም በታች የሚገኙ ናቸው። እስከ 1897 ድኅረ-ልደት ድረስ ከአተም ወደ ታች ፍጥረት የለም ተብሎ ቢታመንም፣ አላህ ግን በቁርኣን ከአቶም በታች ያሉት ፍጥረቶች በእውቀቱ መዝገብ ላይ ተጽፎ እንዳለ ነግሮናል።

በነገራችን ላይ ἄτομον የሚለው የግሪክ ቃል “አቶሞን” እንጂ ጸሐፊው እንዳስቀመጠው “አቶሞስ” ተብሎ አይነበብም፡፡ ይህ ሙስሊም ሰባኪ የግሪክ ቋንቋ ዕውቀት ያለው በማስመሰል ራሱን ማቅረብ የሚያዘወትር ቢሆንም በሌሎች ጽሑፎቹ ውስጥ እንደተለመደው የእንግሊዘኛውን ትራንስሊትሬሽን እንኳ በትክክል ማስቀመጥ ባለመቻሉ ስህተት ሠርቷል፡፡ አተምን በተመለከተ የነበረው ትወራ የማይከፋፈል የመጨረሻው ቁስ እንደሆነ በደፈናው የተናገረውም ስህተት ነው፡፡ እንደ ፕሌቶና አርስቶትል ያሉ ዕውቅ ፈላስፎች የአተምን መኖር ከነ ጭራሹ አልተቀበሉም ነበር፡፡ ዲሞክራተስን የመሳሰሉት ትወራውን የሚደግፉ ፈላስፎች የማይከፋፈል የመጨረሻው ቁስ እንደሆነ ቢናገሩም በ 50 ዓ.ዓ. አካባቢ የኖረው ሌክሬቲየስ የአተምን መከፋፈል ያምን ነበር፡፡ (Philosophy of Science: An Historical Anthology. edited by Timothy McGrew & et.al; p. 69)፡፡ ስለዚህ ቁርኣን የአተምን መከፋፈል ጠቅሷል ከተባለ ከእርሱ በፊት ያልተነገረ አዲስ ሐሳብ ያነሳ በማስመሰል መናገር ስህተት ነው፡፡ አተም ሊከፋፈል መቻሉን ሌክሬቲየስ አስቀድሞ ተናግሯልና፡፡

እስኪ የቁርአኑን ጥቅስ ደግመን እናንብብና ሚዛኑን ባልሳተ ኅሊና እንፍረድ፡፡ ለመሆኑ በአተም ውስጥ ስለሚገኙት ቅንጣቶች እየተናገረ ነውን?

“እነዚያ የካዱትም «ሰዓቲቱ አትመጣብንም» አሉ፡፡ በላቸው «አይደለም፤ ሩቁን ሁሉ ዐዋቂ በኾነው ጌታዬ እምላለሁ፡፡ በእርግጥ ትመጣባችኋለች፡፡ የብናኝ ክብደት ያክል እንኳ በሰማያትና በምድር ውስጥ ከእርሱ አይርቅም፡፡ ከይህ ያነሰም ኾነ የበለጠ የለም በግልጹ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበ ቢኾን እንጅ፡፡»” (ሱራ 34፡3)

በዚህ ጥቅስ ውስጥ “በግልጹ መጽሐፍ የተመዘገበ” የተባለው ምን እንደሆነ ለማወቅ አንድ ጥቅስ ጨምረን እናንብብ፡-

“(ሙሐመድ ሆይ!) በማንኛውም ነገር ላይ አትሆንም፣ ከርሱም ከቁርኣን አታነብም፣ ማንኛውንም ሥራ (አንተም ሰዎቹም) አትሠሩም በገባችሁበት ጊዜ በናንተ ላይ ተጠባባቂዎች ብንሆን እንጂ፡፡ በምድርም ሆነ በሰማይ የብናኝ ክብደት ያክል ከጌታህ (ዕውቀት) አይርቅም፡፡ ከዚያም ያነሰ የተለቀም የለም፤ በግልጹ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈ ቢሆን እንጂ፡፡” (ሱራ 10፡61)

“በግልጹ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈ” የተባለው የሰዎች መልካምና ክፉ ሥራ ነው፡፡ እነዚህ ጥቅሶች ከብናኝ የበለጠም ሆነ ያነሰ ማንኛውም የሰዎች መልካምም ሆነ ክፉ ሥራ በአላህ ዘንድ እንደተመዘገበ ነው የሚነግሩን፡፡ ከብናኝ (በሙስሊም ሰባኪያን መሠረት ከአተም) የበለጠም ሆነ ያነሰ የተባሉት የሰዎች መልካምና ክፉ ሥራዎች እንጂ በአተም ውስጥ የሚገኙ እንደ ኤሌክትሮንና ፕሩቶን ያሉ ቅንጣቶች አይደሉም፡፡ ጥቅሱ ስለ ሰዎች ሥራ የሚናገር መሆኑን ኢብን አባስ በተፍሲሩ ይናገራል፡-

(Those who disbelieve) the disbelievers of Mecca: Abu Jahl and his host (say: The Hour will never come unto us. Say) to them, O Muhammad: (Nay, by my Lord) Allah swore by Himself, (but it is coming) the Hour is coming (unto you surely. (He is) the Knower of the Unseen) He knows what is hidden from people. (Not an atom’s weight) not even a small red ant, (or less than that or greater, escapes Him) is hidden from Allah (in the heavens or in the earth) as regard the works of the servants, (but it is in a clear Record) in the Guarded Tablet well preserved. (ምንጭ)

ሙሐመድ እየተናገረ የነበረው በሰው ዕይታ ትንሽ ሊባል ከሚችለው ከብናኝ (በቀጥተኛ ትርጉሙ ከጉንዳን) ክብደት ያነሰ የሠዎች ደግና ክፉ ሥራ በአላህ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ እንደሚገኝ ሲሆን እንዲህ ያለ ንግግር መናገር ሳይንሳዊ ዕውቀትን እንደማይጠይቅ ግልፅ ነው፡፡ ብናኝ የምታክል ሐሳብ ከቁርኣን ይዞ የአውሮፓውያን ግኝቶችን እየዘረዘሩ በቁርኣን ውስጥ አስቀድመው እንደተተነበዩ መናገር በእውነቱ ከሆነ አእምሮ ያላቸው ሙስሊሞች ሁሉ ሊያፍሩበት የሚገባ ተግባር ነው፡፡ በሙሐመድ ዘመን የነበሩት አረቦች ከፍጥረት አነስተኛ የሚሉትን የጉንዳንን ክብደት በመጥቀስ ፈጣሪ ከዚያ ያነሰ ክብደት ያለውን ነገር እንደሚያውቅ ከሚናገር ጥቅስ ውስጥ ይህንን ሁሉ ሳይንሳዊ ትንታኔ ማውጣት ከብናኝ ውስጥ ተራራ የሚያክል አለት የማውጣት ያህል ቅጥፈት ነው፡፡ አሳማኝ አይደለም፡፡ ኅሊናው የሚሠራ ሰው የሚገዛው ሐሳብ አይደለም፡፡ ሙስሊም ዳዋጋንዲስቶች ከላይ በሚገኘው ሁኔታ ጥቅሶችን አለ ቅጥ በመለጠጥ ከሚፈጥሯቸው የሐሰት ተዓምራት በተረፈ በቁርኣን ውስጥ ለተዓምርነት የሚበቃ አንዳችም ሳይንሳዊ ቅድመ ዕውቀትም ሆነ ትንቢት የለም፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ በሌሎች ወገኖች ተሰጡ ሰፊ ምላሾችን ለማንበብ እዚህ ጋ እና እዚህ ጋ ጠቅ ያድርጉ፡፡

 

የቁርኣን ትንቢት?

ቅዱስ ቁርኣን