የቁርኣን ታሪካዊ ስህተቶች

የቁርኣን ታሪካዊ ስህተቶች


በሙስሊሞች እምነት መሠረት ቁርኣን ተንዚል (ከላይ የወረደ መገለጥ) እንጂ ታሪክ አይደለም፡፡ ሙስሊሞች ቁርኣን ከታሪክ ያለፈ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ይህ ማለት ግን ከታሪክ ጋር የሚገናኝ ምንም ዓይነት ሐሳብ በውስጡ አይገኝም ማለት አይደለም፡፡ የኖኅና የጥፋት ውሃ ታሪክ፤ የአብረሃም ታሪክ፤ የሙሴና የእስራኤላውያን ታሪክ ወዘተ. በውስጡ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ታሪኮች ተጽፈው የሚገኙት ቅደም ተከላቸው በተጠበቀ ኹኔታ በታሪካዊ ዘገባ መሠረት አይደለም፡፡ በቁርኣን ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን ታሪክ-ጠቀስ ዘገባዎች ስንመለከት በየትኛውም መመዘኛ ሚዛን የማይደፉ ኁልቁ መሣፍርት የሌላቸው ሐሳቦችን የሸከፉና ከተረጋገጡ የታሪክ እውነታዎች ጋር የሚጣረሱ ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡ አንባቢያን እግዚአብሔር የሰጣቸውን የማመዛዘን ችሎታ ተጠቅመው የቀረቡትን ነጥቦች እንዲመዝኑ በትህትና እየጠየቅን፣ የሚከተሉትን ጥቂት ምሳሌዎች እናቀርባለን፡-

  1. ሳምራዊ በሙሴ ዘመን?

ሱራ 20፡85 “(አላህ) እኛም ከአንተ በኋላ ሰዎችህን ፈትተን ሳምራዊውም አሳሳታቸው አለው፡፡ ሙሳም ወደ ሰዎቹ የተቆጣ ያዘነ ኾኖ ተመለሠ፡፡

ታሪክ እንደሚናገረው የእስራኤል መንግሥት በ930 ዓ.ዓ. ለሁለት ተከፍሎ ነበር፡፡ የሰሜኑ መንግሥት “እስራኤል” በመባል ሲጠራ የደቡብ መንግሥት ደግሞ “ይሁዳ” ይባል ነበር፡፡ የሰሜኑ መንግሥት ሕዝብ ከ722-705 ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በአሦር ንጉሥ በሳርጎን አካዲያን ተማርኮ ተወስዶ ነበር፡፡ በአርኪዎሎጂ የተገኙ መዛግብት እንደሚያስረዱት 27,290 የሚያክሉ የዋና ከተማዋ የሰማርያ ነዋሪዎች በምርኮ ወደ አሦር (Assyria) ፈልሰዋል፡፡ ነገር ግን በዚሁ ጊዜ በሰማርያና በአካባቢዋ ጥቂት ሰዎች ከምርኮ ተርፈው ቀሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች ከሌላ ቦታ ከመጡ ሰፋሪዎች ጋር በመጋባታቸውና በመደባለቃቸው ሳብያ ሃይማኖታቸውና ባሕላቸው ከሌላው ጋር የተቀየጠ ኾነ፡፡ በዚህ ምክንያትም በተቀሩት አይሁድ ዘንድ የተገለሉ ኾኑ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ በዋና ከተማዋ በሰማሪያ ስም “ሳምራዊያን” ተብለው መጠራት የጀመሩት፡፡ (www.jewishencyclopedia.com/articles/13059-samaritans ይመልከቱ፡፡) ቁርኣን እንደሚለው በሙሴ ዘመን የወርቁን ጥጃ ሠርተው ያመልኩ ዘንድ ያሳሳታቸው ሳምራዊ ነው፡፡ ሳምራዊ በመባል መጠራት የመጣው ከምርኮው ዘመን በኋላ እንደሆነና ሙሴ ደግሞ ከዚህ ዘመን በብዙ መቶ ዓመታት ቀድሞ የኖረ መኾኑ ሊካድ የማይችል ሃቅ ነው፡፡ ታዲያ ሳምራዊ በሙሴ ዘመን ከየት ተገኘ? ሙስሊም ሰባኪያን የትኛውን የታሪክ ምንጭ በመጥቀስ ይኾን ይህንን የመጽሐፋቸውን ስህተት የሚያስተባብሉት?

ለዚህ ታሪካዊ ስህተት በአንድ ሙስሊም የተሰጠውን ምላሽና የኛን ግምገማ ለማንበብ እዚህ ጋ ጠቅ ያድርጉ፡፡

  1. አይሁድ ዑዘይር (ዕዝራ) የአላህ ልጅ ነው አሉ?

ሱራ 9፡30 አይሁድ ዑዘይር የአላህ ልጅ ነው አለች፤ ክርስቲያኖችም አልመሲህ የአላህ ልጅ ነው አሉ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሚታወቀው ዕዝራ ካህንና የሕግ መምህር ሲኾን ከነህምያ ጋር በመተባበር ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ኢየሩሳሌምን እንደገና ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም በስሙ “መጽሐፈ ዕዝራ” በመባል የሚታወቅ አንድ መጽሐፍ ጽፏል፡፡ በአይሁድ ሕግና ልማድ መሠረት ክርስቲያኖች ጌታ ኢየሱስን “የእግዚአብሔር ልጅ” በሚሉት አጠራር ዓይነት አንድን ሰው “የእግዚአብሔር ልጅ” በማለት መጥራት እንደ ክህደት ይቆጠራል፡፡ የጌታ ኢየሱስንም የእግዚአብሔር ልጅነት ለመቀበል የተቸገሩበት አንዱ ምክንያት ይህ ቢኾንም ብሉይ ኪዳን ግን መሲሁ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በግልፅ ያውጃል (መዝሙር 2፡7፣ ሆሴዕ 11፡1 ከማቴዎስ 2.15 ጋር ያነጻጽሩ)፡፡ አይሁድ ዕዝራን ከሌላው ሕዝበ እግዚአብሔር በመነጠል ልዩ በኾነ መንገድ “የእግዚአብሔር ልጅ” ብለው እንደጠሩት የሚጠቁም ምንም ዓይነት የታሪክ ፍንጭ የለም፡፡ በዚህ ተግባር የቁርኣን ክስ አይሁድን ሁሉ በጅምላ እንጂ ከአይሁድ መካከል አንዳንዶቹን ብቻ ባለመኾኑ ምናልባት በአረቢያ ይኖሩ ከነበሩት አይሁድ መካከል ጥቂቶቹ ዕዝራ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ያምኑ ይሆናል የሚል ግምት የሚያስኬድ አይሆንም፡፡ ለምሳሌ ያህል እኔ የማውቃቸው መጠጥ የሚጠጡና የሚሰክሩ የተወሰኑ ሙስሊሞች አሉ፡፡ እነዚህን ጥቂት ሰዎች ብቻ በመመልከት “ሙስሊሞች ጠጪዎችና ሰካራሞች ናቸው” ብዬ ሙስሊሙን ሕብረተሰብ በጅምላ በመንቀፍ መጽሐፍ ብጽፍ ትልቅ ስህተት አይሆንምን? ያለጥርጥር ይህ ዓይነቱ የጅምላ ክስ እውቀት የጎደለውና አግባብነት የሌለው ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ጥቂት ሰዎች መላውን የእስልምና እምነት ተከታይ ሕዝብ የሚወክሉ አይደሉምና፡፡ በሙሐመድ ዘመን ዕዝራ የአላህ ልጅ እንደኾነ የሚያምኑ ጥቂት አይሁድ በአረቢያ ነበሩ ብለን ብንቀበል እንኳ (ይህንን የሚጠቁም ማስረጃ አለመኖሩ ይሰመርበት) እነዚህን ጥቂት ሰዎች ብቻ በመመልከት አይሁድ “ዕዝራ የአላህ ልጅ ነው” ብለው እንደሚያምኑ በመናገርና በመጻፍ የአይሁድን ሕዝብ በጅምላ መንቀፍ ከባድ ስም ማጥፋት ነው፡፡ ዳሩ ግን ከአይሁድ መካከል አንዱ እንኳ ዕዝራን የአላህ ልጅ ብሎ መጥራቱን የሚጠቁም ታሪካዊ ዘገባ ባለመኖሩ ይህ የቁርኣን ጥቅስ ታሪክንና የአይሁድን ሃይማኖት ትምህርት ያላገናዘበ ነው፡፡ እናም በግልፅ የሚታይ ታሪክንና ሃይማኖታዊ እውነታዎችን ያፈረሰ ስህተት አለበት፡፡

  1. ሩቁ መስጊድ?

ሱራ 17፡1 ባርያውን ከተከበረው መስጊድ ወደዚያ ዙርያውን ወደባረክነው ወደ ሩቁ መስጊድ በሌሊት ውስጥ ያስሄደው (ጌታ) ጥራት ይገባው፤ ከታምራታችን ልናሳየው (አስሄድነው) እነሆ እርሱ (አላህ) ሰሚው ተመልካቺው ነው፡፡

ይህ ጥቅስ በራሱ ‘ያ ባሪያ ማነው?’ ‘ሩቁ መስጊድ የት ነው?’ ‘ያ ባርያ በምንና እንዴት ወደዚያ ሄደ?’ ‘ሄዶስ ምን ሠራ?’ ወዘተ. ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ አይሰጠንም፡፡ ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘተ የምንችለው የተለያዩ ተፍሲሮችንና ሐዲሳትን እንዲሁም የሙሐመድን ግለ ታሪኮች በመመልክት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሁሉንም ነገር በውስጡ አሟልቶ እንደያዘና ግልፅ እንደሆነ በሙስሊሞች ዘንድ የሚታመንበት ቁርኣን በራሱ ምሉዕ አለመሆኑን የሚገልጥና ራሱን ችሎ በመቆም ለጥያቄዎቻችን መልስ የመስጠት ብቃት እንደሌለው የሚያሳይ ነው፡፡

እንግዲህ ብዙ ሙስሊም መጽሐፍት እንደሚናገሩት ከላይ የተቀመጠው ጥቅስ የሚያመለክተው ሙሐመድ በሌሊት ወደ ኢየሩሳሌም “የተጓዘበትን” አፈ ታሪክ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሙሐመድ ቡራቅ በተባለ ባለ ክንፍ በቅሎ መሳይ እንስሳ ከመካ ተነስቶ ኢየሩሳሌም ወደነበረው ቤተመቅደስ እንደተጓዘና በመሰላል ወደ ሰማያት በመውጣት እንደወረደ ያስነብቡናል፡፡ (Abdullah Yusuf Ali, the Qur’an Commentary pp. 691-693 እንዲሁም እስልምናና የታላቁ ነቢይ የሙሐመድ ታሪክ በሐጂ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ ገፅ 62-64 ይመልከቱ፡፡)

በዚህ አፈ ታሪክ ውስጥ ሩቁ መስጊድ የተባለው የሰለሞን ቤተመቅደስ (አሁን የአል-አቅሳ መስጊድ ያለበት) ነው፡፡ ነገር ግን ሙሐመድ ወደዚያ ስፍራ ኼደ በተባለበት በዚያ ጊዜ የሰለሞን ቤተመቅደስ ከፈረሰ ብዙ ክፍለ ዘመናት አልፈዋል፡፡ ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ተሠርቶ በሄሮድስ የታደሰው ቤተመቅደስም ቢኾን ጥጦስ (Titus) በተባለ ሮማዊ ጄነራል በ 70 ዓ.ም. ፈርሷል፡፡ በዚያ ስፍራ ላይ እስከዛሬ ድረስ ቆሞ የሚታየው የአል-አቅሳ መስጊድም ቢኾን ከሙሐመድ ሞት በኋላ ብዙ አመታት ዘግይቶ በኻሊፋ አብድ አል-ማሊክ የተሠራ ስለኾነ በሙሐመድ ዘመን ምንም ዓይነት መስጊድም ኾነ ቤተመቅደስ በቦታው ላይ አልነበረም፡፡ ታድያ ቁርኣንና ሙስሊም ጸሐፍት ሙሐመድ ወደ ሩቁ መስጊድ ኼደ የሚሉን ይህንን እውነታ እንዴት ቢመለከቱት ነው?

  1. ስለ ሰለሞን ተረት ተረት ወይንስ እውነተኛ ታሪክ?

በቁርኣን መሠረት ሰለሞን:-

  • ነፋስ ይታዘዝለት ነበር፡፡ (ሱራ 21፡81)
  • ሰይጣናት ሉልን ያወጡለት ነበር፤ ሥራም ይሠሩለት ነበር፡፡ ሱራ 21፡82)
  • የወፍ ቋንቋ ይችል ነበር፡፡ (ሱራ 27፡16) አልፎ ተርፎም ከዝናብ ወፍ ጋር ይነጋገር ነበር (ሱራ 27፡20-28)
  • ሠራዊቱ ከጋኔን፣ ከሰውና ከወፎች የተዋቀረ ነበር (ሱራ 27፡17)
  • ጉንዳን ስትናገር መስማት ይችል ነበር (ሱራ 27፡18-19)
  • የንግሥተ ሳባን ዙፋን ከጋኔን ኃይለኛው ሰርቆ አምጥቶለታል (ሱራ 27፡38-40)
  • ጋኔኖች ምኩራቦችን፣ ምስሎችን፣ ገንዳዎችንና ድስቶችን ይሠሩለት ነበር (ሱራ 34፡12-13፣ 38፡36-37)

የሰለሞንን አሟሟት በተመለከተ ቁርኣን 34፡14 ላይ እንዲህ ይላል፡-

በእርሱም ላይ ሞትን በፈፀምንበት ጊዜ መሞቱን በትሩን የምትበላ ተንቀሳቃሽ ምስጥ እንጂ ሌላ አላመለከታቸውም፡፡ በወደቀ ጊዜም ጋኔኖች ሩቅን ሚስጢር የሚያውቁ በሆነ ኖሮ በአዋራጅ ስቃይ ውስጥ የማይቆዩ እንደነበሩ ተረዱ፡፡

እዚህ ጋር ልብ በሉ እንግዲህ ሰለሞን በትሩ ላይ ተደግፎ ቆሞ ለእርሱ ይሠሩ የነበሩትን ጋኔኖች ሲቆጣጠር ሳለ ድንገት በቆመበት ሞተ፡፡ ጋኔኖቹ እርሱ እየተመለከታቸው በሕይወት ያለ መስሏቸው ይሠራሉ፡፡ ነገር ግን አንዲት ምስጥ የተደገፈበትን በትር በላችና ወደቀ፡፡ በዚህ ጊዜ ጋኔኖቹ የእርሱን መሞት ተረዱ፡፡ ቁርኣንና ሙስሊም ምሁራን የሚነግሩን ይህንን ነው፡፡ ለመሆኑ የት አገር ነው ንጉሥ በቆመበት ስፍራ እስኪሞትና ምስጥ የተደገፈበትን በትር በልታ እስክትጨርስ ድረስ ብቻውን የሚኾነው? ሰለሞን ከሞተ በኋላ የመሬት ስበት ሕግ በርሱ ላይ ስለማይሠራ ይሆን ደርቆ የቆመው?

በዚህ የሰለሞን ታሪክ ውስጥ ልክ እንደሰው የሚታዩና በሁለት እግሮቻቸው ቆመው የሚሄዱ ጋኔኖችን፤ የሚናገሩ ወፎችንና የሚናገሩ ጉንዳኖች እናገኛለን፡፡ ለመሆኑ ከመቼ ወዲህ ነው ወፎችና ጉንዳኖች ልክ እንደሰው እንዲያውም የወደፊቱን አውቀው መናገር የጀመሩት? ከወፎች መካከል በቀቀን (Parrot) ከብዙ ልምምድ በኋላ የሰውን ንግግር አስመስላ መናገር እንደምትችል ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ትርጉሙን አውቃ ሳይሆን በደመነፍስ የምትፈፅመው ነገር ነው፡፡ ቁርኣን ባስቀመጠው በሰለሞን ታሪክ ውስጥ ደግሞ እንደሚናገር የተነገረን የዝናብ ወፍ ነው፡፡ ጉንደኖችም መረጃም የሚለዋወጡት ሰዎች አይተውም ኾነ ሰምተው ሊረዱት በሚችሉት መንገድ አይደለም፡፡ ቁርኣን ግን እንዲህ ይላል፡-

“በጉንዳንም ሸለቆ በመጡ ጊዜ አንዲት ጉንዳን «እናንተ ጉንዳኖች ሆይ! ወደ መኖሪያዎቻችሁ ግቡ፡፡ ሱለይማንና ሠራዊቱ እነርሱ የማያውቁ ሲኾኑ አይሰባብሩዋችሁ» አለች፡፡” (ሱራ 27፡18)

የሚገርመው ነገር በቁርኣን ውስጥ እንደተናገረች የተጠቀሰችው ጉንዳን፡-

  • የሰለሞንን ስም አውቃለች
  • ሰለሞን ሠራዊት እንዳሉት አውቃለች
  • የሰለሞን ሠራዊት ወደዚያ ስፍራ እንደሚመጡ አውቃለች
  • የሰለሞን ሠራዊት ሳያውቁ ከረጋገጧቸው ጉንዳኖቹን እንደሚሰባብሯቸው አውቃለች
  • ይህንን ኹሉ መረጃ ደግሞ በማቀናበር ልክ እንደ ሰዎች ውስብስብ የኾነን ዓረፍተ ነገር ሠርታ መናገር ችላለች

ውድ አንባቢያን “ለፈጣሪ የሚሳነው ነገር የለም” በሚል ሽፋን እንዲህ ዓይነት ተረቶች ተቀባይነት ማግኘት ይገባቸዋልን? ይህ የሰለሞን ታሪክ ከእውነተኛ ታሪክ ይልቅ በተረታ ተረቶች ውስጥ የሚነገር ዓይነት የአስማትና የምትሃት ዓለም ይመስላል፡፡

ሙስሊም ወገኖቻችን ሰለሞን ነቢይ እንደኾነ ያምናሉ፡፡ በብዙዎቹ እምነት መሠረትም ነቢያት ከኃጢአት ነጻ ናቸው፡፡ ቁርኣን ይህንን “የሰለሞን” ተግባር ያጸድቃል፡፡ ክርስቲያኖች ግን ከአጋንንትና ከሰይጣናት ጋር ተባብሮ የሚሠራ ነቢይ አያውቁም፡፡ እንዲህ ከአጋንንትና ከሰይጣናት ጋር የሚሠራ ሰው ሊሆን የሚችለው ጠንቋይና አስማተኛ እንጂ ነቢይ አይደለም፡፡ እውነተኛ  ነቢይ የተባለ ሰው እንዲህ ዓይነት ተግባር ሲፈፅም ከተገኘ የነቢይነት ፀጋው ከርሱ ላይ ተወስዶ የሰይጣን ወዳጅ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የሰለሞን ፍፃሜ እንደ ጅማሬው ያማረ ባይሆንም ነገር ግን ከጌታ አምላክ ጋር ተስማምቶ በኖረበት ዘመን በቁርኣን ውስጥ በተጠቀሰው ዓይነት ሁኔታ ከአጋንንትና ከሰይጣናት ጋር ተባብሮ የኖረበት ጊዜ አልነበረም፡፡ አባቱ ዳዊት በገና በሚደረድርበት ጊዜ ክፉ መንፈስ ከሳዖል ይርቅ እንደነበር ተጽፏል (1ሳሙኤል 16.14-23)፡፡ የእግዚአብሔር ነቢያት ባሕርይም ይኸው ነው፡፡ ሙስሊም መገኖቻችን ሰለሞን ነቢይ ሆኖ ሳለ ከአጋንንቶችና ከሰይጣናት የተዋቀረ ሠራዊት አለቃ ሆኖ ይኖር አንደነበረ የሚናገረውን የቁርኣን ቃል ክርስቲያኖች እንደ ፈጣሪ ቃል ባለመቀበላቸው ምክንያት ቅር ሊላቸው አይገባም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ሰለሞንን በተመለከተ የሚከተለውን ቃል ይናገራል፡-

1ነገሥት 4.29-34፡- እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው። የሰሎሞንም ጥበብ በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብጽ ጥበብ ሁሉ በለጠ። ከሰውም ሁሉ ይልቅ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታንና ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ከደራልም ይልቅ ጥበበኛ ነበረ። በዙሪያውም ባሉ አሕዛብ ሁሉ ዝናው ወጣ። እርሱም ሦስት ሺህ ምሳሌዎች ተናገረ፤ መኃልዩም ሺህ አምስት ነበረ። ስለ ዛፍም ከሊባኖስ ዝግባ ጀምሮ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው እስከ ሂሶጵ ድረስ ይናገር ነበር፤ ደግሞም ስለ አውሬዎችና ስለ ወፎች ሰለተንቀሳቃሾችና ስለ ዓሣዎች ይናገር ነበር። ከአሕዛብም ሁሉ፥ ጥበቡንም ሰምተው ከነበሩ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ሰዎች ይመጡ ነበር።

ከሁለቱ ታሪኮች የትኛው ትክክለኛና አሳማኝ እንደኾነ አንባቢያን ለመለየት ይቸገራሉ ብለን አናምንም፡፡ በቁርአኑ የሰለሞን ታሪክ ላይ ሊነሱ የሚችሉ ብዙ ጥያቄዎች ቢኖሩም ነገር ግን ከጊዜና ከቦታ አንፃር ታልፈዋል፡፡ አንባቢያን ግን በጥልቀት በመመርመር ሊመዝኑት ይችላሉ፡፡

  1. የፀሐይ መውጫና መግቢያ መድረስ የቻለ ሰው?

ዙልቀርናይን የተባለ ልዩ የሆነ ሰው ወደ ፀሐይ መግቢያ ቦታ ደርሶ ጥቁር ጭቃ ባላት ምንጭ ውስጥ ስትጠልቅ እንዳገኛትና እዚያ የሚገኙ ሰዎችን በኃይል እንደገዛቸው እንዲሁም ወደ ፀሐይ መውጫ ቦታ ደርሶ እዚያ አካባቢ የሚገኙ ሰዎች ከሙቀቷ የሚጠለሉበት ነገር እንደሌላቸው እንደተመለከተ ቁርኣን ይነግረናል፡-

ሱራ 18፡81-90 “ከዙልቀርነይንም ይጠይቁሃል፡፡ «በእናንተ ላይ ከእርሱ ወሬን አነባለሁ፤» በላቸው፡፡ እኛ ለእርሱ በምድር አስመቸነው፡፡ ከነገሩም ሁሉ (መዳረሻ) መንገድን ሰጠነው፡፡ መንገድንም (ወደ ምዕራብ) ተከተለ፡፡ ወደ ፀሐይ መግቢያም በደረሰ ጊዜ ጥቁር ጭቃ ባላት ምንጭ ውስጥ ስትጠልቅ አገኛት፡፡ ባጠገቧም ሕዝቦችን አገኘ፡፡ «ዙልቀርነይን ሆይ! ወይም (በመግደል) ትቀጣለህ ወይም በእነርሱ መልካም ነገርን (መማረክን) ትሠራለህ» አልነው … ከዚያም መንገድን (ወደ ምሥራቅ) ቀጠለ፡፡ ወደ ፀሐይ መውጫ በደረሰም ጊዜ ለእነሱ ከበታችዋ መከለያን ባላደረግንላቸው ሕዝቦች ላይ ስትወጣ አገኛት፡፡”

በተጨማሪም ይህ ታላቅ ተፈጥሮ የነበረው ሰው (super human) ከብረት ቁርጥራጮች ትልቅ ግድብ በመሥራት ነሃስ አቅልጦ በማፍሰስ እንደሸፈነውና ይህ ግድብ ግዙፍ ከመኾኑ የተነሳ በሁለት ተራሮች መካከል የሚገኝን ክፍተት መድፈን ችሎ እንደነበር እናነባለን፡፡ ቁርኣን የዚህን ግድብ ጠቀሜታ ሲያብራራ እጁጅ እና ማእጁጅ (ጎግ እና ማጎግ) የተባሉ አመፀኛ ህዝቦች ጥፋት እንዳያስከትሉ ለመከላከል እንደሆነና ይህም ግድብ በፍርድ ቀን እንደሚፈርስ ይናገራል ሱራ (18፡93-96)፡፡

ለመሆኑ ዙልቀርናይን ማነው? ዙልቀርናይን የሚለው ስም ትርጉሙ “ባለሁለት ቀንድ” ማለት እንደሆነ የአማርኛው ቁርኣን ግርጌ ማስታወሻ ገፅ 206 ላይ ይናገራል፡፡ አንዳንድ ሙስሊም ምሁራን ይህንን ሰው ታላቁ እስክንድር (Alexander the Great) እንደኾነ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን እስክንድር ጣዖት አምላኪ መሆኑ በታሪክ ስለሚታወቅና በተፃራሪው ደግሞ ቁርኣን ውስጥ የተጠቀሰው ሰው በአላህ አጥብቆ እንደሚያምን የተገለፀ በመኾኑ ይህ ማብራርያ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡

ዙልቀርናይን እንደሠራው የተነገረን ግድብ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ የሚቆይ ከኾነ አሁንም አለ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሙስሊም ወገኖቻችን ይህ ግድብ የት አገር እንደሚገኝ ሊነግሩን ይችላሉን? በተጨማሪም ዙልቀርናይን በእርግጠኝነት ማን እንደሆነና የተባለውም ሰው ታላቁን የብረት ግድብ መሥራቱን ታሪካዊ ማስረጃ በመጥቀስ ሊያብራሩልን ይችላሉን? መቼም እንዲህ ዓይነት ታላቅ ሥራ የሠራ ሰው በምድር ላይ ኖሮ ከኾነ ከታሪክ ሊሰወር አይችልም፡፡ እርሱ የሠራው ማንም ሊያልፈው የማይችለው ታላቅ ግድብ በዚህች ኘላኔት ላይ የሚገኝ ከኾነ የት እንዳለ መታወቁ አይቀርም፡፡

  1. ዲርሃም በዮሴፍ ዘመን?

ዮሴፍ ወደ ግብፅ የተሸጠበትን ዋጋ በተመለከተ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-

“በርካሽ ዋጋም በሚቆጠሩ ዲርሃሞች ሸጡት፡፡ በእርሱም ከቸልተኞቹ ነበሩ፡፡” (ሱራ 12፡20)

“And they sold him for a reduced price – a few dirhams”

ችግሩ በዮሴፍ ዘመን ዲርሃም የተሰኘ የመገበያያ ገንዘብ አለመኖሩ ብቻ አይደለም፡፡ በዮሴፍ ዘመን ሰዎች በሳንቲም መገበያየት አለመጀመራቸውም ጭምር እንጂ! በታሪክ ምሑራን መሠረት ሰዎች በሳንቲም መገበያየት የጀመሩት በ600 ዓ.ዓ. ገደማ ሲሆን ዮሴፍ ደግሞ የኖረው በ1700 ዓ.ዓ. ገደማ ነው (The Origin of Electrum Coinage by Robert W. Wallace, a professor at Northwestern University, in American Journal of Archaeology, July 1987)፡፡ ታድያ የመገበያያ ገንዘብ ባልተፈጠረበት ዘመን ዲርሃም የተሰኘ ገንዘብ ከየት መጣ? ችግሩን ይበልጥ ውስብስብ የሚያደርገው ደግሞ ይህ የታሪክ ተፋልሶ (anachronism) ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በሰማይ በሚገኝ ሰሌዳ ላይ ተጽፎ እንደነበረ በሙስሊሞች ዘንድ መታመኑ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ዮሴፍ የተሸጠበትን ዋጋ በግልፅ ከማስቀመጡም በላይ በዘመኑ የነበረውን መገበያያ (የብር ቁርጥራጭ pieces of silver) ጠቅሷል፡፡ ቁርኣን ግን በሰባተኛው ክፍለ ዘመን የሚታወቀውን የመገበያያ ሳንቲም ነው የጠቀሰው፡፡

  1. ስቅለት (Crucifixion) በዮሴፍ ዘመን?

ከዮሴፍ ጋር ወህኒ ቤት የነበሩት ሁለቱ ሰዎች ሕልማቸውን ከነገሩት በኋላ ዮሴፍ እንዲህ ማለቱ ተነግሯል፡-

«የወህኒ ቤት ጓደኞቼ ሆይ! አንደኛችሁማ ጌታውን (ንጉሡን) ጠጅ ያጠጣል፡፡ ሌላውማ ይሰቀላል፡፡ ከራሱም በራሪ (አሞራ) ትበላለች፡፡ ያ ፍቹን የምትጠይቁት ነገር ተፈጸመ፤» (አላቸው)፡፡ (ሱራ 12፡41)

“…but as for the other, he will be crucified”

ስቅለት (Crucifixion በአረብኛ ሰለበ) በዚያን ዘመን በምድረ ግብፅ የወንጀለኛ መቅጫ እንደነበረ የሚያሳይ ምንም ዓይነት ታሪካዊም ሆነ የአርኮዎሎጂ ማስረጃ የለም፡፡ በምሑራን የተደረጉት ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ስቅለት የተጀመረው በ6ኛው ክፍለ ዘመን ቅድመ ክርስቶስ ሲሆን ዮሴፍ ከኖረበት ዘመን ጋር ቢያንስ የ1000 ዓመታት ልዩነት አለው፡፡ (Britannica: Encyclopedia of World Religions; p. 270) ለዚህ ታሪካዊ ስህተት በአንድ ሙስሊም የተሰጠውን ምላሽና የኛን ግምገማ ለማንበብ እዚህ ጋ ጠቅ ያድርጉ፡፡

  1. የግብፅ ግብርና በዝናብ ላይ የተመሠረተ ነበር?

ዮሴፍ ከፈታው ህልም ጋር የሚገናኝ ሌላ የታሪክ ተፋልሶ አለ፡፡ ዮሴፍ የንጉሡን ህልም ሲፈታ ድርቅ እንደሚሆንና ከድርቁ በኋላ ዝናብ የሚዘንብበትና ሰዎች በዝናቡ የሚያመርቱበት ዘመን እንሚመጣ ይገልፃል፡፡ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-

«ከዚያም ከእነዚያ በኋላ ሰዎቹ በርሱ የሚዘነቡበት በርሱም (ወይንን) የሚጨምቁበት ዓመት ይመጣል፡፡» (ሱራ 12፡49)

Then will come after that a year in which the people will be given rain and in which they will press [olives and grapes].

በዚህ ጥቅስ ውስጥ የሚገኘው ስህተት ለማንኛውም የጂኦግራፊ ተማሪ ግልፅ ነው፡፡ ግብፃውያን በዝናብ ላይ ጥገኛ እንደነበሩ ወይም ዝናብ ተጠቅመው ያመርቱ እንደነበር የሚገልፅ የታሪክም ሆነ የአርኪዎሎጂ ማስረጃ የለም፡፡ የግብፅ ህልውና የተመሠረተው በአባይ ወንዝ ላይ እንጂ በዝናብ ላይ አልነበረም፡፡ የቁርኣን ደራሲ የግብፅን ጂኦግራፊ የማያውቅ ሰው መኾኑ ግልፅ ነው፡፡

ማጠቃለያ

ከላይ የተጠቀሱት ስምንት ታሪካዊ ስህተቶች በቁርኣን ውስጥ ከሚገኙ እጅግ በርካታ ታሪካዊ ስህተቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እውነተኛ የፈጣሪ መገለጦች መዋሸትና መሳሳት ከማያውቁት ከሃያሉ ፈጣሪ ዘንድ የሚመጡ በመኾናቸው ምክንያት እንዲህ ያሉ ስህተቶች በውስጣቸው ሊገኙ አይችሉም፡፡ ቁርኣን እውነተኛ የፈጣሪ ቃል ቢኾን ኖሮ ስህተት ባልተገኘበት ነበር፡፡ ውድ ሙስሊም ወገኖቻችን፤ አንድ መጽሐፍ ከፈጣሪ ዘንድ እንደመጣ ስለተናገረና ከፈጣሪ አንደበት የወጣ ንግግር በሚመስል መንገድ ስለተጻፈ ብቻ እውነተኛ የፈጣሪ ቃል ሊኾን እንደማይችል እንደምትስማሙ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ቁርኣን የፈጣሪን ንግግር በመላበስ የተጻፈ ጽሑፍ ቢኾንም ደራሲው ሥጋ ለባሽ በመኾኑ በእንዲህ ያሉ ስህተቶች የተሞላ ጽሑፍ ኾኖ ተገኝቷል፡፡ እነዚህ ስህተቶች ደግሞ ቁርኣን የአፅናፈ ዓለም ፈጣሪ ከኾነው እውነተኛው አምላክ ዘንድ እንዳልመጣ የሚያሳዩ የማንቂያ ምልክቶች ናቸው፡፡ ጌታ እግዚአብሔር የልብ ዓይኖቻችሁን በመክፈት እውነተኛ ቃለ እግዚአብሔር ወደ ኾነው ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ትመለሱ ዘንድ ይርዳችሁ፡፡

 

ቅዱስ ቁርኣን