የደህንነትን ማረጋገጫ መረዳት (ክፍል 2)

ለተጠራጣሪዎች መድኃኒት

መግቢያ

ከአሜሪካ ወደ አውሮፓ በመርከብ ጉዞ ስለጀመረ አንድ ሰው ሰምቼ ነበር፡፡ ይህ ሰው ለቲኬት ብቻ የሚበቃ ገንዘብ ያዘጋጀ ሲሆን በመርከቢቱ ሬስቱራንት ላይ ምግብ ገዝቶ የሚመገብበት ገንዘብ አልነበረውም፡፡ ስለዚህ የራሱን ጥቂት ምግብ በማዘጋጀት ሰዎች በደስታ ከሚመገቡበት የመርከቢቱ ሬስቱራንት ራሱን አራቀ፡፡

ከቀናት በኋላ የያዘው ምግብ አለቀበት፡፡ ከእርሱ ጋር ተጓዥ የነበረ አንድ ሰው ቀረብ ብሎ “ወዳጄ ሬስቱራንቱ ውስጥ አብረኸን ስትመገብ አላይህም፤ ካላስቸገርኩህ ምክንያቱን ልትነግረኝ ትችላለህ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ለቲኬቱ እንጂ ለምግቡ የሚከፍለው ገንዘብ እንደሌለው ገለጸለት፡፡ ከዚያም ያ ሰው መልሶ “ምን ነካህ ወዳጄ? ምግቡ እኮ ከትኬቱ ጋር አብሮ የመጣ ነው!” ብሎ መለሰለት፡፡ (1)

በሚያሳዝን ሁኔታ ብዙ ክርስቲያኖች ልክ እንደዚህ ሰው ናቸው፡፡ ሁሉም ነገር ወደሰማይ ከሚወስደው ትኬት ጋር አብሮ እንደመጣላቸው ወደማመን ብስለት አያድጉም፡፡ ራሳቸው ባዘጋጁት ድርቆሽ ላይ ጥገኛ በመሆን እግዚአብሔር ከደህንነታቸው ጋር እንደተሰጣቸው የተናገረውን ድግስ ሳይታደሙ ይቀራሉ፡፡

እስኪ ዛሬ በድግሱ ውስጥ የሚገኙትን ጥቂት ነገሮችና ተጠራጣሪዎች ድግሱን እንዳይታደሙ የሚያደርጓቸውን አንዳንድ ነገሮች መመልከት እንጀምር፡፡

የአሁን አዋጅ

ደህንነት ከሞት በኋላ ስላለ ሕይወት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የዘላለምን ሕይወት ከብዙ ጥቅሞቹ ጋር አሁን እዚሁ አግኝተናል፡፡ ጥቂቶቹ እነሆ፡-

ይቅርታ – አንዳንድ ክርስቲያኖች ባለፈው ጊዜ በፈጸሙት ኃጢአት ምክንያት ውስጣቸው እየተወቀሰ ወደ መኝታቸው ይሄዳሉ፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዕይታ ምስራቅ ከምዕራብ የራቀውን ያህል ኃጢአታቸው ከእነርሱ ርቋል፡፡ በምንም መንገድ ውስጣችን ሊከሰስ አይገባም! በናዚ የማሰቃያ ካምፕ ውስጥ የነበረችው ካሪ ቴን ቡም እንደተናገረችው “ኃጢአታችንን ስንናዘዝ እግዚአብሔር ለዘላለም እንዲጠፋ ወደ ባሕር ይወረውረዋል፡፡ ከቃሉ ጥቅስ መጥቀስ ባልችልም እግዚአብሔር ‹እዚህ ቦታ አሣ ማጥመድ አይፈቀድም!› የሚል ምልክት እንዳስቀመጠበት አምናለሁ፡፡” (2)

“በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት፡፡” (ኤፌ. 1፡7)

አዲስ ፍጥረት – አንዳንድ ሰዎች “ሕይወቴን እንዲህ አድርጌ ስላበለሻሸሁት ከታች መጀመር ያስፈልገኛል” ይላሉ፡፡ ለዚህ ነው እግዚአብሔር አሮጌውን ሕይወታችንን ከእንደገና ከማስተካከል ያለፈ ሥራ የሠራልን፡፡ በቤተሰቡ ውስጥ እንደገና እንድንወለድ በማድረግ አዲስ ሕይወት አስጀምሮናል፡፡ እንደ አዲስ ፍጥረት ከእግዚአብሔር ጋር አዲስ ሕብረት ጀምረናል፡፡ በዚያ ሕብረት ውስጥ የመኖር ፍላጎትም ተሰጥቶናል፡፡

“ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል፡፡” (2ቆሮ. 5፡17)

መንፈስ ቅዱስ – እግዚአብሔር ካዳነን በኋላ የተቀረውን ሕይወታችንን በራሳችን እንድንኖር ለብቻችን አልተወንም፡፡ ስንድን መንፈስ ቅዱስ ወደኛ በመምጣት በውስጣችን መኖር ጀምሯል፡፡ ስኬታማ ክርስቲያናዊ ሕይወትም እንድንኖር ያስችለናል፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ክርስቲያናዊ ሕይወት ከባድ አይደለም፤ ነገር ግን ሊኖሩት ፈፅሞ የማይቻል ነው! በራሳችን ኃይል ልንኖረው አንችልም፡፡  ስኬታማ ክርስቲያኖች ክርስቲያናዊውን ሕይወት መኖር እንዲችሉ በመንፈስ ቅዱስ ላይ መደገፍን ይማራሉ፡፡

“ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡” (ሐዋ. 2፡38)

የወደፊት ተስፋዎች

ከዓመታት በፊት ከአንድ ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋች ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ አንብቤ ነበር፡፡ ሪኮርድ ያስመዘገበ፣ ግሩም ችሎታ የነበረው፣ ደጋፊዎች ለማምለክ የሚፈተኑበት ዓይነት ተጫዋች ነበር፡፡ በእግር ኳስ ሜዳ ውስጥ ከፍተኛ በራስ መተማመን የነበረው ይህ ተጫዋች በሕይወቱ ትልቅ ጉዳይ ላይ መተማመን አልነበረውም፡፡ ጋዜጠኛው ይህ ተጫዋች ምን እንደሚያስፈራው ጠየቀው፡፡ ወደ ሜዳ ሲገባ ተቀናቃኞቹን የሚያስፈራ ተጫዋች ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን ምለሽ መስማት በጣም ያጓጓል፡፡ እንዲህ ሲል ነበር ምላሹን የሰጠው፡- “መሞትና ወደ ሲዖል መሄድ፡፡ ነገር ግን የምሄድ አይመስለኝም ምክንያቱም ጥሩ ሰው ሆኜ ኖሬያለሁና፡፡”

ይህ ሰው በሙያው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ነገር ግን የዘላለም መኖርያው የት እንደሆነ በእርግጠኝነት ማወቅ ስላልቻለ ውስጡ ሰላም አላገኘም፡፡ ብዙ ሰዎች የዘላለም መኖርያቸውን ማወቅ የሚችሉ እንኳ አይመስላቸውም፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በግልፅ ይናገራል፡-

“ዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ፡፡” (1ዮሐ. 5፡13)

ማወቅ እንጂ ተስፋ ማድረግ ወይም ምናልባት ይሆናል ብሎ ማሰብ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ስለ መጨረሻ መድረሻችን እርግጠኞች እንድንሆንና ሰላም እንዲኖረን ይፈልጋል፡፡ በሰማዩ ቤታችን ከእርሱ ጋር ለዘላለም ለመኖር ዝግጁዎች ልንሆን ይገባናል!

እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ የሚከተሉትን ተስፋዎች ሰጥቶናል፡-

ከእግዚአብሔር ቁጣ እናመልጣለን፡- እግዚአብሔር ፍትሃዊ አምላክ በመሆኑ የኃጢአት ቅጣት መከፈል አለበት፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ምክንያት ኢየሱስ የኃጢአትን ቅጣት በሙሉ በራሱ ላይ ወሰደ፡፡

“ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን፡፡” (ሮሜ 5፡9)

በክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ከሞት መነሳት፡- የሞቱትም ሆኑ በሕይወት ያሉት አማኞች ክርስቶስ ሲመለስ አዲስ የከበረ አካል ይለብሳሉ፡፡ ምድራዊው አካሌ በታመመና በተጎዳ ቁጥር ስለ ሰማያዊው አካሌ እያሰብኩ ደስ እሰኛለሁ!

“የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው። በመበስበስ ይዘራል፥ ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፥ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ፡፡” (1ቆሮ. 15፡42-44)

የዘላለም ሕይወት ይኖረናል፡- ሁሉም አማኞች ለዘላለም ከክርስቶስ ጋር እንደሚኖሩ ተስፋ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኘን ለማወቅ ጊዜ መጠበቅ የለብንም፡፡ አሁን እንኳ አግኝተነዋል!

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡” (ዮሐ. 3፡16)

ጥርጣሬን መቅረፍ

እግዚአብሔር ከቁጣው እንድናመልጥ፣ አዲስ ሰማያዊ አካል እንደምናገኝና ለዘላለም ከእርሱ ጋር እድንኖር ቃል ከገባልን ለምንድነው አንዳንድ ክርስቲያኖች ከጥርጣሬ ጋር የሚታገሉት? እናንተ ከጥርጣሬ ጋር ባትታገሉም እንኳ ይህ ችግር ያለባቸው ሰዎች ሊያጋጥሟችሁ ይችላሉ፡፡ እሰኪ አንዳንድ የጥርጣሬ ምክንያቶችን እንመልከት፡፡

  1. “እግዚአብሔር ያለፈውን ኃጢአቴን ይቅር ይለኛል ብሎ ማመን ከባድ ነው፡፡”

እስኪ የዚህን ታላቅ ኃጢአተኛ ሰው ምስክርነት ስሙ፡-

…አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን፥ ይህን አደረገልኝ፤ ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምህረትን አገኘሁ፥ የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ካሉ ከእምነትና ከፍቅር ጋር አብልጦ በዛ፡፡ ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ፤ ስለዚህ ግን፥ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ፥ ምህረትን አገኘሁ፡፡

ይህንን ማን እንደጻፈው ታውቃለህ? እግዚአብሔር አብዛኞቹን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ለመጻፍ የተጠቀመበት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነው (1ጢሞ. 1፡13-16)፡፡ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ምን ይመስል እንደነበር ታውቃለህ? የኢየሱስን መሲህነት ክዶ ነበር፡፡ በጣም ነውጠኛ ሰው ከመሆኑ የተነሳ በታላቅ ቁጣ ቤተ ክርስቲያንን አሳዷል፣ ክርስቲያኖችን አሳስሯል፣ እንዲገረፉና እንዲገደሉ አድርጓል (1ጢሞ. 1፡13፣ ሐዋ. 7፡58፣ 8፡1፣ 9፡1-5፣ 22፡4-7፣ 19-20፣ 26፡9-11)፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስ እግዚአብሔር እርሱን ይቅር ካለው ይቅር የማይለው ሰው ሊኖር እንደማይችል ሊነግራችሁ ይወዳል፡፡ ምንም ብታደርጉ ይህንን አስታውሱ፡-

“የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል፡፡” (1ዮሐ 1፡7)

ከስንት ኃጢአት? “ከኃጢአት ሁሉ፡፡” የዕፅ ሱሰኛና የዝሙት ኃጢአት የፈፀምን እንኳ ብንሆን? “ከኃጢአት ሁሉ፡፡” ክርስቲያን የገደልን እንኳ ብንሆን? “ከኃጢአት ሁሉ፡፡”

  1. “እውነቱን ለመናገር ስለ እግዚአብሔር ብዙም ግድ የለኝም፡፡”

አቤሴሎም የሃይስኩል ተማሪ እያለ ክርስቶስን ለመቀበል የንስሐ ጸሎት ጸልዮ ነበር፡፡ በወር አንድ ሁለት ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ብቅ ቢልም በዕለት ተዕለት ኑሮው ለእግዚአብሔር ያን ያህል ትኩረት አይሰጥም፡፡ ንግዱን እንዴት መምራት እንዳለበት፣ ልጆቹን እንዴት ማሳደግ እንዳለበትና ሚስቱን እንዴት መያዝ እንዳለበት ለማወቅ እንኳ መጽሐፍ ቅዱሱን ገልጦ አያነብም፡፡ ሕይወቱ በየቀኑ አብሯቸው ከሚሠራቸው ክርስቲያን ካልሆኑ ሰዎች የተለየ አይደለም፡፡ ስለ መዳኑ ጥርጣሬ ቢኖረውም የሃይስኩል ተማሪ ሳለ በጸለየው የንስሐ ጸሎት ይተማመናል፡፡

አቤሴሎም የፈሩትን የሚያረጋጉ ጥቅሶችን ማንበብ እንዳለበት ሁሉ የተረጋጉትንም የሚያስፈሩ ጥቅሶችን ማንበብ ይኖርበታል፡፡ አቤሴሎም መፍራት አለበት፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስነውን ጥቅስ ታስታውሳላችሁ?

“የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ፡፡” (1ዮሐ. 5፡13)

ዮሐንስ ማረጋገጫ እንዲሆኗቸው የጻፈላቸው እነዚህ ነገሮች ምንድናቸው? የዮሐንስ መልዕክት ሁለት ዓይነት ሕይወቶችን ይጠቅሳል፤ የዘላለም ሕይወት ያላቸውና የሌላቸው ሰዎች ሕይወቶች፡፡ የያንዳንዱን ሕይወት ባሕርይ ተመልከቱ፡-

እውነተኛ ክርስቲያኖች የመዳናቸውን ማስረጃዎች በሚከተሉት መንገዶች ማሳየት አለባቸው፡-

መታዘዝ (1ዮሐ. 2፡3-4)

“ትእዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን፡፡ አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም፡፡”

እምነት (1ዮሐ. 5፡1)

“ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል፡፡”

ፍቅር

ፍቅር ለእግዚአብሔር (1ዮሐ. 5፡1-2)

“ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል፡፡ እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን፡፡”

ፍቅር ለእግዚአብሔር ሕዝብ (1ዮሐ. 3፡14-15)

“እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል፡፡ ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ፡፡”

አንዳንዶቻችን ይህንን ዝርዝር በማየት ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፡፡ ማናችንም እምነት፣ ፍቅርና መታዘዝን ሁል ጊዜ 100% አሟልተን አንገኝም፡፡ ይህ ማለት ክርስቲያኖች አይደለንም ማለት ነውን? በፍፁም! ዮሐንስ መልዕክቱን በጻፈበት የግሪክ ቋንቋ ተላምዶ መኖርን የሚያሳይ ቃል ተጠቅሟል፡፡ ዮሐንስ 1፡8 ስለ ፍፅምና እያወራን እንዳልሆነ ግልፅ ያደርጋል፡፡

“ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም፡፡”

አንዳንድ ሰዎች ስሜታቸው በጣም ስስ ከመሆኑ የተነሳ በጸሎት በእግዚአብሔር ፊት የሚያሳልፉበትን ጊዜ ከዘለሉ መዳናቸውን ይጠራጠራሉ፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት መፈለግህና ካልተገናኘህ ቅር መሰኘትህ በራሱ መንፈስ ቅዱስ በሕይወትህ ውስጥ እየሠራ መሆኑን ያሳያል፡፡

ክርስቶስን ስንቀበል በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ለውጥ ተደርጓል፡፡ ውሳኔዎችን ሁሉ “እኔ እኔ እኔ” ብለን በራሳችን ላይ አተኩረን ከማድረግ ይልቅ ሌሎችን ስለመውደድና ለእግዚአብሔር ስለመኖር እናስባለን፡፡

በ1ዮሐንስ መሠረት ማረጋገጫዬ ያረፈው በሃይማኖታዊ ሥርኣት ወቅት በሚሰማኝ ስሜት ላይ ሳይሆን አሁንና እዚህ አጠቃላዩ ሕይወቴ በሚይዘው አቅጣጫ ላይ ነው፡፡

አሁን በኢየሱስ ታምናለህን? አሁን ኢየሱስን እየተከተልክ ነውን? በክርስቶስ ያሉትን ወንድሞችህንና እህቶችህን አሁን ትወዳቸዋለህን? ራስህን ከመከተል ይልቅ እግዚአብሔርን እየተከተልክ ነውን? በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ክርስቲያን ነህ፤ የዘላለም ሕይወት አለህ፡፡

ማስጠንቀቂያ! የኑሮ ዘይቤያችን ለደህንነታችን ምልክት ቢሆንም የደህንነታችን ምክንያት ወይም ጠባቂ አይደለም፡፡ ደህንነታችን በእምነት በሆነ ጸጋ እንጂ እኛ ሠርተን ያገኘነው አይደለም (ኤፌ. 2፡8-9)፡፡

  1. “ደህንነቴን ለመጠበቅ በጣም ደካማ በመሆኔ እፈራለሁ፡፡”

ላንተ የምሥራች አለኝ! መጀመርያ በእግዚአብሔር ዘንድ የዘላለም ሕይወት እንዳለህ ለማወቅ እስከ ዕለተ ሞትህ ድረስ መጠበቅ የለብህም፡፡ የዘላለምን ሕይወት አግኝተሃል፡፡

“የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ፡፡” (1ዮሐ. 5፡13)

እስኪ አስበው፡፡ የዘላለም ሕይወትህን የምታጣ ከሆነ ሲጀመር የዘላለም ሕይወት አይደለም! እንደማታገኘው የምትፈራውን የዘላለምን ሕይወት አግኝተኸዋል፤ በእጅህ ነው!

ሁለተኛ እግዚአብሔር እንደሚጠብቅህ ተስፋን ሰጥቷል፡፡ ደህንነታችን በኛ የመጠበቅ ችሎታ ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ችሎታና የመጠበቅ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ኢየሱስ እንዲህ አለ፡-

“ከሰጠኝም ሁሉ አንድን ስንኳ እንዳላጠፋ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው እንጂ የላከኝ የአብ ፈቃድ ይህ ነው፡፡ ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ፡፡” (1ዮሐ. 6፡39-40)

“በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም፡፡ የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም፡፡ እኔና አብ አንድ ነን፡፡” (ዮሐ. 10፡27-30)

እነዚህ ጥቅሶች በኢየሱስና በእግዚአብሔር አብ እጆች ውስጥ አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ መያዛችንን በግልፅ ይስላሉ፡፡ ያ ምስል ከአእምሮህ እንዲጠፋ አትፍቀድ፡፡ እንወድቃለን እርሱም ደግሞ ይጥለናል ብለን በእግዚአብሔር እጆች ላይ ተንጠልጥለን እየተፍጨረጨርን የምንኖር ሰዎች አይደለንም፡፡ የእርሱ ሃያል እጅ አጥብቆ ስለያዘን ምንም ነገር ከእጁ ፈልቅቆ ሊያወጣን አይችልም፡፡ የኛ ደህንነት አጥብቆ የያዘንን የእግዚአብሔርን እጅ ያህል አስተማማኝና ጠንካራ ነው፡፡

ማስታወሻዎች

  • Found in Bill Bright’s Transferable Concepts (Campus Crusade for Christ). Worded by Steve Miller.
  • Corrie ten Boom with Jamie Buckingham, Tramp for the Lord (Fort Washington, PA: CLC Publications, 1974), 53.