ሳምራዊ ወይንስ ዘንበሪ? ቁርኣንን ከታሪካዊ ቅጥፈቱ ለመታደግ የተደረገ ከንቱ ጥረት

ሳምራዊ ወይንስ ዘንበሪ?

ቁርኣንን ከታሪካዊ ቅጥፈቱ ለመታደግ የተደረገ ከንቱ ጥረት

በቁርኣን ውስጥ ለቁጥር የሚያታክቱ ታሪካዊ ስህተቶች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ሳምራዊ በሙሴ ዘመን እንደነበር የሚናገረው አንዱ ሲሆን ሙስሊም ወገኖች ይህንን ታሪካዊ ቅጥፈት ለማስተባበል የተለያዩ ጥረቶችን አድርገዋል፡፡ ነገር ግን የረባ ሙግት በማቅረብ ቁርኣንን ከዚህ ስህተት መታደግ የቻለ አንድም ሙስሊም የለም፡፡ በዚህ መጣጥፍ ይህንን ቅጥፈት ለማስተባበል ያልተሳኩ ጥረቶችን ካደረጉ ሙስሊም ሰባኪያን መካከል የአንዱን እንመለከታለን፡፡ ይህንን ጽሑፍ ለመልስ የመረጥንበት ምክንያት የረባ ሙግት ስላገኘንበት ሳይሆን በፌስ ቡክ፣ በቴሌግራም፣ በተለያዩ ጦማሮችና በሌሎች መድረኮች ብዙ ሙስሊም ወገኖች ሲቀባበሉት በማየታችን ምክንያት ነው፡፡ አንባቢያንም ሙስሊም ሰባኪያን እንዴት ባለ ማምታታት ሕዝባቸውን እንደሚያጭበረብሩ መታዘብ ይችሉ ዘንድ የሚያግዝ ጥሩ ማሳያ እንደሆነ እንገምታለን፡፡ ጸሐፊው እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-

ሣሚሪይ

20:85 አላህም እኛም ከአንተ በኋላ ሰዎችህን በእርግጥ ፈትተን፤ ሳምራዊውም አሳሳታቸው አለው። قَالَ فَإِنَّا قَدْ فَتَنَّا قَوْمَكَ مِن بَعْدِكَ وَأَضَلَّهُمُ السَّامِرِيُّ

“ሣሚሪይ” سَّامِرِىّ በሙሳ ዘመን ለእስራኢል ልጆች በእሳት አቅልጦ ወይፈን የሰራላቸው ሰው ነው፦

20:85 አላህም እኛም ከአንተ በኋላ ሰዎችህን በእርግጥ ፈትተን፤ ሳምራዊውም አሳሳታቸው አለው። قَالَ فَإِنَّا قَدْ فَتَنَّا قَوْمَكَ مِن بَعْدِكَ وَأَضَلَّهُمُ السَّامِرِيُّ

20:87 ቀጠሮህን በፈቃዳችን አልጣስንም፤ ግን እኛ ከሕዝቦቹ ጌጥ፣ ሸክሞችን ተጫን በእሳት ላይ ጣልናትም፤ ሳምራዊውም እንደዚሁ ጣለ አሉት። قَالُوا مَا أَخْلَفْنَا مَوْعِدَكَ بِمَلْكِنَا وَلَـٰكِنَّا حُمِّلْنَا أَوْزَارًا مِّن زِينَةِ الْقَوْمِ فَقَذَفْنَاهَا فَكَذَٰلِكَ أَلْقَى السَّامِرِيُّ

20:95 ሙሳ ሳምራዊው ሆይ ነገርህም ምንድነው? አለ። قَالَ فَمَا خَطْبُكَ يَا سَامِرِيُّ

ይህ ሰው አንድ በጣም ወሳኝ እውነት እያድበሰበሰ ነው፡፡ ይኸውም “ሳምራዊው” ተብሎ የተረጎመው በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ እርሱ እንዳለው “ሣሚሪይ” ሳይሆን “አስ-ሳሚሪዩ” السَّامِرِيُّ መባሉ ነው፡፡ በዐረብኛ “አል-“ በእንግሊዘኛ “The” የሚል የተወሰነ መስተአምር በአንድ ቃል ላይ ሲጨመርና ያ ቃል አንድን ሰው ለማመልከት ጥቅም ላይ ሲውል ዜግነቱን፣ ጎሣውን፣ አገሩን፣ ሙያውን ወዘተ. የሚያመለክት እንጂ የግለሰቡ የተጸውዖ ስም ሊሆን አይችልም፡፡ ለምሳሌ ያህል የአንድ ሰው ስም መገርሣ ቢሆን በየትኛውም ቋንቋ “መገርሣ” ይባላል እንጂ የተወሰነ መስተአምር ታክሎበት ለምሳሌ በእንግሊዘኛ The Megersa ወይም በዐረብኛ “አል-መገርሣ” አይባልም፡፡ ይህ “መገርሣ” የሆነውን ስም በአማርኛ “መገርሣዊው” ብሎ እንደመጥራት ነው፡፡ ሰውየው ከየት ወገን እንደሆነ የሚያመለክተውን ቃል “ሣሚሪይ” ብሎ በዐረብኛው ባልተባለ ቃል በመለወጥ የተጸውዖ ስም ማስመሰል ተዓማኒነትን ማጉደል ነው፡፡ ዕውቁ ሙስሊም ሊቅ አል-ባይደዊ የሳምራዊውን ማንነት ሲያብራራ እንደተናገረው የሰውየው ስም ሙሳ ኢብን ዘፋር ሲሆን ሳምራውያን ከተሰኙ ሕዝቦች ወገን ነበር (Thomas Patrick Hughes, Dictionary of Islam, p. 564)፡፡ ሳምራውያን የተሰኙ ሕዝቦች ከሰባተኛው ክፍለ ዘመን ቅ.ክ. በፊት እንዳልነበሩ የተረጋገጠ በመሆኑ ምክንያት የቁርኣን ደራሲ የታሪክ ስህተት ፈፅሟል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚቀርብ የትኛውም ሙግት ዋጋ ባይኖረውም ሙስሊሙ አፖሎጂስት የሚለውን እንስማ፡-

እሱም የሰራላቸው አንድ ወይፈን የሆነ ጥጃ ነው፦

20፥88 ለእነሱም አካል የኾነ ጥጃን ለእርሱ መጓጎር ያለውን አወጣላቸው፡፡ ተከታዮቹ «ይህ አምላካችሁ የሙሳም አምላክ ነው ግን ረሳው» አሉም፡፡

7፥148 የሙሳም ሕዝቦች ከእርሱ መኼድ በኋላ ከጌጦቻቸው ወይፈንን አካልን ለእርሱ ማግሳት ያለውን አምላክ አድርገው ያዙ፡፡ እርሱ የማያናግራቸው መንገድንም የማይመራቸው መኾኑን አይመለከቱምን? አምላክ አድርገው ያዙት፡፡ በዳዮችም ኾኑ፡፡

ይህን ትረካ በመጠኑም ቢሆን ከፔንታተች ጋር ይመሳሰላል፦

የወርቁ ጥጃ ማግሳቱን በተመለከተ ቁርኣን የተናገረው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኝ ሲሆን ከአይሁድ አዋልድ የተቀዳ ተረት ነው፡፡ ይህም ቁርኣን ሰው ሰራሽ መጽሐፍ እንጂ መለኮታዊ መገለጥ ላለመሆኑ አንዱ ማስረጃ ነው፡፡

ዘጸአት 32፥7-8 ያህዌህም ሙሴን፦ ከግብፅ ምድር ያወጣኸው ሕዝብህ ኃጢአት ሠርተዋልና ሂድ፥ ውረድ። ካዘዝኋቸው መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ምስል ለራሳቸው አደረጉ፥ ሰገዱለትም፥ ሠዉለትም፤፦ እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አሉ ሲል ተናገረው።

ዘጸአት 32፥20 የሠሩትንም ጥጃ ወስዶ በእሳት አቀለጠው፥ እንደ ትቢያም እስኪሆን ድረስ ፈጨው፥ በውኃውም ላይ በተነው፥ ለእስራኤልም ልጆች አጠጣው።

እዚህ ጋር የተሰራው ጥጃ አንድ ጥጃ እንደሆነ ይናገራል፤ ሰሪውም አሮን ነው ብሎ ያስቀምጣል፤ “ሣሚሪይ” سَّامِرِىّ በዕብራይስጥ “ሳንበርይ” זִמְרִי በአማርኛ “ዘንበሪ” የተባለው ሰው ነው፦

ዘኍልቍ 25፥14 ከምድያማዊቱም ጋር የተገደለው የእስራኤላዊው ሰው ስም ዘንበሪ ነበረ፤

ይህ ሆኖ ሳለ ሚሽነሪዎች ሁለት የተለያዩ ታሪኮችን በማታታት ቁርኣን የታሪክ ግድፈት እንዳለበት ለማሳየት ሲያምታቱ ይገኛሉ። “ሳንበርይ” זִמְרִי ማለትም “ዘንበሪ” የተባለውን ስም “ሰማሪይ” שומרון‎ ማለትም “ሰማሪያ” ጋር ደባልቀው ቁርኣን፦ “በሙሳ ዘመን ጥጃ ሰራ የሚለው ግለሰብ የሰማሪያ ሰዎችን ነው” ብለው ለመጠምዘዝ ይሞክራሉ፤

ይህ ሰው በርካታ ቅጥፈቶችን ፈፅሟል፡፡ זִמְרִי በዕብራይስጥ “ዝምሪ” እንጂ “ሳንበርይ” ተብሎ አይነበብም፡፡ “ዘንበሪ” የሚለው የአማርኛ አጠራር ይበልጥ ለቃሉ የቀረበ ነው፡፡ በዕብራይስጡ ቃል ውስጥ “ሰ” ድምፅ ያለው ፊደል በማይታይበት ሁኔታ זִמְרִי (ዝምሪ) የሚለውን ቃል “ሳንበርይ” ብሎ ትራንስሊትሬት ማድረግ በእጅጉ አስቂኝ ነው፡፡ ሙስሊሙ አፖሎጂስት በዕውቀት ሳይሆን በግምት ማውራቱ ግልፅ ነው፡፡ שומרון (ሸምሮን) የሚለውንም ቃል “ሰማሪይ” ብሎ ትራንስሊትሬት ማድረጉ ሌላ ጽርፈት ነው፡፡ ሳምራዊ “ሰማሪተስ” ከሚለው የግሪክ አጠራር የመጣ ሲሆን ዐረብኛውም ከግሪኩ የተገኘ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ዕውቁ የአረብኛ ቋንቋ ሊቅ ኢብን መንዙር “በሊሳን አል-ዐረብ” ዲክሽነሪው “ሳምራዊ” የሚለውን “አስ-ሳሚርዩ” በሚል ከቁርኣን ጋር ተመሳሳይ በሆነ ቃል ገልጿል፡፡ ተከታዩ የዐረብኛ መዝገበ ቃላት ድረገፅ ኢብን መንዙርን ጨምሮ ከአሥር በላይ የዐረብኛ ቋንቋ ሊቃውንት በተመሳሳይ መንገድ ማስቀመጣቸውን ያሳያል፡፡ http://arabiclexicon.hawramani.com/%D8%B3%D9%85%D8%B1/ ሙስሊም ሰባኪያን እንዲህ ለቅሌት ከሚዳረጉ የመጽሐፍ ቅዱስን የመጀመርያ ቋንቋዎች መጥቀስ ቢቀርባቸው ይሻላል፡፡

ዘኍልቍ 25፡14 ላይ የተጠቀሰው ዘንበሪ (በዕብራይስጥ ዝምሪ) የወርቁን ጥጃ መሥራቱን የሚናገር ምንም ነገር በሌለበትና የስያሜ መመሳሰል ይቅርና መቀራረብ እንኳ በሌለበት ሁኔታ የቁርአኑ ሳምራዊ እርሱ እንደሆነ መናገር ባዶ ግምት ከመሆኑም በላይ ዐይን ያወጣ ውሸት ነው፡፡ ቃሉ በግልፅ እንደሚናገረው ዘንበሪ ከሚድያማዊት ሴት ጋር ዝሙት በመፈፀሙ ምክንያት የተገደለ እስራኤላዊ እንጂ የወርቁን ጥጃ የሠራ ሰው አይደለም፡፡

ሙስሊሙ አፖሎጂስት ለገዛ ቁርአኑ እንኳ ታማኝ አይደለም፡፡ በቁርኣን የተባለው አስ-ሳሚሪዩን እንጂ “ሣሚሪይ” አይደለም፡፡ ማናችንም ብንሆን ከስህተት የፀዳን አይደለም፤ ነገር ግን እንዲህ ግልፅ ቅጥፈት መፈፀም ከአንድ በፈጣሪ መኖር ከሚያምን ሰው የሚጠበቅ አይደለም!

የሙስሊሙን አፖሎጂስት ሙግት ውኀ በልቶታል ነገር ግን “መልሴን ቆረጡብኝ” እንዳይል የተቀረውን እንስማ፡-

በ 930 BC በአስሩ ነገድ ይኖር የነበረው ዘንበሪ የተባለው ንጉሥ ሳምርም ከሚባል ሰው በሁለት መክሊት ብር የሰማርያን ተራራ ገዛ፤ በተራራውም ላይ ሠራ፥ የሠራውንም ከተማ በተራራው ባለቤት በሳምር ስም ሰማርያ ብሎ ጠራው፦

1ኛ ነገሥት 16፥24 ከሳምርም በሁለት መክሊት ብር የሰማርያን ተራራ ገዛ፤ በተራራውም ላይ ሠራ፥ የሠራውንም ከተማ በተራራው ባለቤት በሳምር ስም ሰማርያ ብሎ ጠራው።

ከዚያ በኃላ ያሉ ሕዝቦች “ሳምራውያን” ሲባሉ ወንዱ “ሳምራዊ” ሴቷ “ሳምራዊት” ይባላሉ፦

ሉቃስ10፥33 አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፥

ሉቃስ 17፥16 እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ።

ዮሐንስ 4፥9 ስለዚህ ሳምራዊቲቱ፦ አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ? አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና።

ዮሐንስ 8፥48 አይሁድ መልሰው፦ ሳምራዊ እንደ ሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ በማለታችን እኛ መልካም እንል የለምን? አሉት።

ይህንን እሳቤ ከያዝን ሳምራውያን ከጊዜ በኃላ የአስሩ ነገዶች መጠሪያ ሆነ፤ ሳምራውያን ቀልጠው የተሠሩትንም የሁለቱን እንቦሶች ምስሎች አደረጉ፥ የማምለኪያ ዐፀድንም ተከሉ፥ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገዱ፥ በኣልንም አመለኩ፤ የሰሯቸው አማልክት ብዙ ናቸው፦

2 ነገሥት 17፥16 የአምላካቸውንም የያህዌን ትእዛዝ ሁሉ ተዉ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም የሁለቱን እንቦሶች ምስሎች አደረጉ፥ የማምለኪያ ዐፀድንም ተከሉ፥ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገዱ፥ በኣልንም አመለኩ።

2 ነገሥት 17፥29 በየሕዝባቸውም አምላካቸውን አደረጉ፥ ሰምራውያንም በሠሩት በኮረብታው መስገጃዎች ሕዝቡ ሁሉ በሚኖሩበት ከተሞቻቸው አኖሩአቸው።

አንዳንድ ሙስሊም አፖሎጂስቶች ሳምራውያን የተሰኙ ሕዝቦች በሙሴ ዘመን ነበሩ በሚል ያለ ማስረጃ በድርቅና ሲከራከሩ ታይተዋል፡፡ ነገር ግን አንተ ራስህ በትክክል እንዳስቀመጥከው ሳምራውያን የተሰኙ ሕዝቦች ከሙሴ ዘመን በኋላ የመጡ ናቸው፡፡

ታዲያ ይህ ታሪክ በየትኛው ቀመርና ስሌት ነው ከቁርኣን ጋር የሚመሳሰለው? ሲጀመር ከመነሻው “ሳንበርይ” זִמְרִי የተባለውን ስም እና “ሰማሪይ” שומרון‎ የተባለው ስም አንድ ነውን? ሲቀጥል በሙሳ ጊዜ የነበረው ሳንበርይ አንድ ግለሰብ ሲሆን ከይሁዳ ንጉሥ ከአሳ በኃላ አማልክት የሰሩት ሳምራውያን ደግሞ ሕዝብ ናቸው፤ ሲሠልስ ቁርኣን ልክ እንደ ዘጸአት በሙሴ ጊዜ ተሰራ የሚለን አንድ ጥጃ ነው፤ ነገር ግን በተቃራኒው ሳምራውያን የሰሩት የሁለቱን እንቦሶች ምስሎች ናቸው።

ሁሉም ነጥቦችህ ቀደም ሲል መልስ አግኝተዋል፡፡ זִמְרִי የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ዝምሪ” እንጂ “ሳንበርይ” ተብሎ አይነበብም፡፡ שומרון የሚለውም “ሸምሮን” ተብሎ እንጂ “ሰማርይ” ተብሎ አይነበብም፡፡ “ሳምራዊ” የሚለው የአማርኛ አጠራርም ሆነ “አስ-ሳሚርዩ” የሚለው የአረብኛ አጠራር “ሰማሪተስ” ከሚለው የግሪክ አጠራር የተገኙ መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ የታወቁት የአረብኛ መዝገበ ቃላትም “ሳምራዊ” ለሚለው አቻ “አል-ሳሚርዩ” የሚለውን በቁርኣን ውስጥ የሚገኘውን ቃል ያስቀምጣሉ፡፡ የቁርኣን ደራሲ 2 ነገሥት 17፡16 ላይ በሰማርያ የተሠሩትን የወርቅ ጥጃዎች በሙሴ ዘመን ከተሠራው ጋር የማምታታቱ ሁኔታው ከፍተኛ ቢሆንም በሙሴ ዘመን ያልነበረውን ሳምራዊ ወደ ሙሴ ዘመን መውሰዱ ሊታበል የማይችል ሃቅ ነው፡፡ እናም ከሰማይ እንደወረደ በተነገረለት ቁርኣን ውስጥ እንዲህ ያለ ታሪካዊ ቅጥፈት መገኘቱ መጽሐፉ የፈጣሪ ቃል ሳይሆን የሙሐመድ ፈጠራ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ይህ ታሪካዊ ቅጥፈትም አንተንና መሰሎችህን የእስላም ጠበቆች እንቅልፍ መንሳቱን ይቀጥላል፤ ለእውነት እጅ እስካልሰጣችሁ ድረስ!

 

የቁርኣን ታሪካዊ ስህተቶች