ሁለተኛው አጽናኝ ሙሐመድ አይደለም! ለሙስሊም ሰባኪያን ቅጥፈት የተሰጠ መልስ

ሁለተኛው አጽናኝ ሙሐመድ አይደለም!

ለሙስሊም ሰባኪያን ቅጥፈት የተሰጠ መልስ

ሰለምቴ ነኝ ባዩ ኡስታዝ ሙሐመድን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማስገባት ትግል ላደረገበት አንድ ጽሑፍ መልስ እንድንሰጥ ከተወሰኑ ክርስቲያኖች ዘንድ ጥያቄ ቀርቦልን በማሕበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ በነበረን የቀጥታ ስርጭት መልስ ሰጥተናል፡፡ ምላሻችን ለዘላቂ ማጣቀሻነት እንዲሆን በጽሑፍ ማስቀመጥ አስፈላጊ በመሆኑ በድምፅ ያቀረብነውን ምላሽ በመጭመቅ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡ የድምፅ ምላሻችን ብዙ ነጥቦችን ያካተተ በበቂ ማብራርያ የተደገፈ በመሆኑ ርዕሱን በበለጠ ስፋትና ጥልቀት ማጥናት የሚፈልጉ ወገኖች አግኝተው ያደምጡ ዘንድ እናበረታታለን፡፡

ሙስሊሙ ሰባኪ እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-

አብዱል

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

61፥6 የመርየም ልጅ ዒሳም፡- «የእስራኤል ልጆች ሆይ! እኔ ከተውራት በፊቴ ያለውን የማረጋግጥ እና ”ከእኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድ በኾነው የማበስር” ስኾን ወደ እናንተ የተላክሁ የአላህ መልክተኛ ነኝ» ባለ ጊዜ አስታውስ፡፡ በግልጽ ተዓምራቶች በመጣቸውም ጊዜ «ይህ ግልጽ ድግምት ነው» አሉ፡፡

መልስ

ጥቅሱ የሙሐመድ ፈጠራ እንጂ ተጨባጭ ማስረጃ ያለው አይደለም፡፡ ኢየሱስ ይህንን የተናገረበት ቦታ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ አይገኝም፡፡ የኢየሱስ ተልዕኮ የሰው ልጆችን ከኃጢአት ማዳን እንጂ ከእርሱ በኋላ ስለሚመጣ ብዙ የስነ ምግባር ጉድለቶችን ሲያሳይ ስለነበረ ሐሰተኛ ነቢይ መናገር አይደለም፡፡

አብዱል

መግቢያ

የመጽሐፉም ባለቤቶች ክርስቲያኖች እና አይሁዳውያን ከአላህ የወረደውን እውነት ከሰው ንግግር ቃል ቀላቅለዋል፤ በተጨማሪም ከአላህ የወረደውን እውነት ደብቀዋል፦

3፥71 የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! እውነቱን በውሸት ለምን ትቀላቅላላችሁ ”እውነቱንም እናንተ የምታውቁ ስትኾኑ ለምን ትደብቃላችሁ”?

መልስ

ቁርኣን በጽሑፍ የሚገኙት ቶራህ እና ወንጌል መበረዛቸውን በአንድም ቦታ አይናገርም፡፡ ሙሐመድ በሐዲስ መጻሕፍት ውስጥ አንድም ጊዜ ቶራህና ወንጌል መበረዛቸውን የተናገረበት ቦታ የለም፡፡  ይልቅ ቁርኣንና ሐዲስ የቀደሙት መጻሕፍት በሙሐመድ ዘመን ተጠብቀው መቆየታቸውንና ወደፊትም በዚያ ሁኔታ እንደሚቀጥሉ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡

http://www.ewnetlehulu.net/am/ask-those-who-read-the-book/

http://www.ewnetlehulu.net/am/the-holy-bible/tawrat-injil/

http://www.ewnetlehulu.net/am/the-holy-bible/islamic_dilemma/

አብዱል

 በ 397 AD የተደረገው የካርቴጅ ጉባኤ ብዙ የወንጌል ቅሪት አፓክራፋ ብሎ ቀንሷል፤ “አፓክራፋ” ማለት “አፓክራፎስ” ἀπόκρυφος ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን “ድብቅ” “ስውር” ማለት ነው፦

5፥15 የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! ”ከመጽሐፉ ትሸሽጉት ከነበራችሁት ነገር ብዙውን ለእናንተ የሚገልጽ ከብዙውም የሚተው” ሲኾን መልክተኛችን በእርግጥ መጣላችሁ፡፡ ከአላህ ዘንድ ብርሃንና ገላጭ መጽሐፍ በእርግጥ መጣላችሁ፡፡

መልስ

ይህ ጸሐፊ የግሪክ ቃላትን በጠቀሰ ቁጥር ስህተት መሥራት ያዘወትራል፡፡ ἀπόκρυφος የሚለው ቃል አፖክሩፎስ ተብሎ እንጂ  “አፓክራፎስ” ተብሎ አይነበብም፡፡ የአፖክሪፋ ወንጌላት ከሁለተኛው ክፍለ ዘመን በኋላ የተጻፉ እንጂ ከክርስቶስና ከሐዋርያቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አይደሉም፡፡ ይህ በሊቃውንቱ ዓለም የታወቀና የተረጋገጠ ሃቅ በመሆኑ ምንም የሚያከራክር ነገር የለውም፡፡ የአፖክሪፋ መጻሕፍትን ትክክለኛ ወንጌላት እንደሆኑ የሚናገር ሰው ስለ ጉዳዩ ምንም ዕውቀት የሌለው ሰው አለበለዚያም የአንባቢያኑን አለማወቅ ተገን አድርጎ ሐሰተኛ መረጃ የሚያስተላልፍ ቀጣፊ ነው፡፡ መጻሕፍቱ አፖክሪፋ (ድብቅ/ስውር) የተባሉበት ምክንያት ምንጫቸው ወይም መነሻቸው የማይታወቅና አጠራጣሪ በመሆኑ እንጂ ክርስቲያኖች ስለሚደብቋቸው አይደለም፡፡ ብዙ የአፖክሪፋ መጻሕፍት እስከዚህ ዘመን ድረስ ዘልቀዋል፤ ብዙዎቹም በቀደምት አበው ምላሽና ማብራርያ የተሰጠባቸው በመሆኑ ይዘታቸው ይታወቃል፡፡ የቁርኣን ደራሲ ከእነዚህ የኋለኞቹ ዘመናት ተረቶች ከሆኑት መጻሕፍት የተቀዱ ብዙ ታሪኮችን በቁርኣን ውስጥ ቢያካትትም በብዙ አጋጣሚዎች ትምህርቶቻቸው ከቁርኣን ጋር ይጋጫሉ፡፡ ስለዚህ ሱራ 5፡15 ስለ አፖክሪፋ መጻሕፍት ነው የሚናገረው ከተባለ እነዚህ የአፖክሪፋ መጻሕፍት እስልምና የሚቃወማቸውን እንደ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ፣ የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነትና መለኮት ስለመሆኑ የሚናገሩ በመሆናቸው እንዲሁም ሙሐመድንና ትምህርቱን ፈፅሞ የማያውቁ በመሆናቸው ቁርኣን ስህተት ሊሆን ነው፡፡ ጥቅሱ እየተናገረ ያለው በአራተኛው ክፍለ ዘመን ሐሰተኛ መጻሕፍት መሆናቸው ስለተነገረው የአፖክሪፋ መጻሕፍት ሳይሆን በሙሐመድ ዘመን በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ ስለሚገኘው ቅዱስ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ደግሞ ዛሬ በእጃችን ከሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ የተለየ አለመሆኑ የታወቀ ነው፡፡

አብዱል

2፥146 እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ወንዶች ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ ያውቁታል፡፡ ከእነሱም የተለዩ ክፍሎች እነርሱ የሚያወቁ ሲኾኑ ”እውነቱን በእርግጥ ይደብቃሉ” ፡፡

ከ+ተደበቁት ዋናው አጀንዳ ወንዶች ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ  የምስራቹን የምስራች ያሰኘው ኢየሱስ ስለ ነብያችን”ﷺ” መምጣት ያበሰረውን የሚያወቁ ሲኾኑ ይህንን እውነቱን በእርግጥ ይደብቃሉ፤ አላህ ኢንጅል የሚለው ስለ ነብያችን”ﷺ” መምጣት የሚተነብየውን ወንጌል እንደሆነ ቅቡልና እሙን ነው፦

61፥6 የመርየም ልጅ ዒሳም፡- «የእስራኤል ልጆች ሆይ! እኔ ከተውራት በፊቴ ያለውን የማረጋግጥ እና ”ከእኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድ በኾነው የማበስር” ስኾን ወደ እናንተ የተላክሁ የአላህ መልክተኛ ነኝ» ባለ ጊዜ አስታውስ፡፡ በግልጽ ተዓምራቶች በመጣቸውም ጊዜ «ይህ ግልጽ ድግምት ነው» አሉ፡፡

መልስ

በቁርኣን ውስጥ ኢንጂል የተባለው መጽሐፍ በዘመኑ በክርስቲያኖች እጅ እንደነበረ ቁርኣን ይመሰክራል፡፡ በዚያ ዘመን የነበረው ወንጌል በአራቱ ጸሐፍት የተጻፈው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ስለዚህ የቁርኣን ደራሲ ወንጌል በዘመኑ በነበሩት ክርስቲያኖች እጅ የሚገኝ መጽሐፍ መሆኑን ከመሰከረ በኋላ በወንጌሉ ውስጥ የሌለ ስለ ሙሐመድ የተተነበየ ትንቢት አለ ማለቱ ስለ መጽሐፉ ይዘት የማያውቅ መሆኑን ከማሳየት የዘለለ ትርጉም የለውም፡፡

አብዱል

ከእኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድ በኾነው የማበስር ስኾን ወደ እናንተ የተላክሁ የአላህ መልክተኛ ነኝ”

ይህ ቃል በአራቱ ወንጌላት የለም ማለት ኢየሱስ አልተናገረውም ማለት አይደለም፤ ምክንያቱንም ኢየሱስ ተናግሮ በአራቱ ወንጌል ላይ ያልሰፈሩ ሃረጎች ስላሉ፤ ለምሳሌ፦

1ዮሐንስ 1፥5 ከእርሱ የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። “እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም” የምትል ይህች ናት።

ኢየሱስ፦ “”እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም”” ብሎ ተናግሮ ነበር፤ ዮሐንስም፦ “ከእርሱ(ከኢየሱስ) የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት ይህች ናት” ብሎናል፤ ግን ይህ ከኢየሱስ የሰሙት መልእክት በአራቱ ወንጌላት የለም ማለት ኢየሱስ አልተናገረውም ማለት አይደለም፤ በተጨማሪ በተመሳሳይ መልኩ ኢየሱስ፦ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” ብሎ ተናግሮ ነበር፤ ይህ ቃል አራቱ ወንጌል ላይ የለም፦

የሐዋርያት ሥራ 20:35 እንዲሁ እየደከማችሁ ድውዮችን ልትረዱና እርሱ ራሱ። “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ።

መልስ

መላው አዲስ ኪዳን ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት፣ ትምህርትና ሥራ የሚናገር ሆኖ ሳለ የኢየሱስን ንግግር በአራቱ ወንጌላት የገደበው ማን ነው? በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገራቸውን ቃላት የዘገቡልን ወገኖች በዘመኑ ከእርሱ ጋር የነበሩት የዓይን ምስክሮችና ከዓይን ምስክሮች ጋር አብረው ያገለገሉት የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ይህ ሃቅ ከክርስቶስ በኋላ ስድስት ክፍለ ዘመናትን ዘግይቶ የኖረ፣ በባዕድ መንፈስ ተመርቶ ባዕድ ትምህርት ያስተማረ ግለሰብ ክርስቶስ ስለ እርሱ እንደተነበየ በማስመሰል በክርስቶስ አንደበት ላይ ያኖረውን የሐሰት ቃል ለማጽደቅ ሊውል አይችልም፡፡  ሙሐመድ ከክርስቶስና ከሐዋርያቱ ትምህርት ጋር የሚጋጩ አስተምህሮዎችን ያስተማረ ሰው ሆኖ ሳለ ክርስቶስ ስለ እርሱ አዎንታዊ ትንቢት የሚናገርበት ምንም ዓይነት ተዓምር ሊኖር አይችልም፡፡

አብዱል

ይህንን በወፍ በረር ለመግቢያ ያክል ካየን በአራቱ ወንጌላት ቅሪት ላይም ስለ ነብያችን”ﷺ” መምጣት ኢየሱስ ትንቢት ተናግሮ እንደነበር በሰከነና በሰላ መረዳት እስቲ እናስተንትን፦

ዮሐንስ 14:15-16 ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ “አጽናኝ” Παράκλητον ይሰጣችኋል፤”

 

ነጥብ አንድ

አጽናኝ”

አጽናኝ” ተብሎ የተቀመጠው የግሪኩ ቃል “ፓራቅሊጦስ” Παράκλητον ሲሆን ኢየሱስ “ሌላ” ማለቱ “ተጨማሪ” ማለቱ ነው፤ ለምሳሌ “ሌላ አስተማሪ” ይመጣል ብል፤ ሌላው ሁለተኛ አስተማሪ ከመምጣቱ በፊት ፊተኛ አስተማሪ እንዳለ ያመለክታል፤ በተመሳሳይ “ሌላ አጽናኝ” የሚለው ቃል  ፊተኛው አጽናኝ እንዳለ ያሳያል፤ ታዲያ የመጀመሪያው አጽናኝ ማን ነው? ስንል መልሱ ኢየሱስ ነው፦

1ዮሐንስ 2:1 ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ “አጽናኝ” παράκλητον አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ በ 33 AD ከወረደ ከ 57 አመት በኋላ በ 90 AD አጽናኝ ተብሏል፣ አያችሁ እስከ 90 AD ድረስ ኢየሱስ አጽናኝ እንደነበረ ካየን እስከ 90 AD ጊዜ ድረስ ሌላው አጽናኝ አልመጣም ማለት ነው፡፡

መልስ

Παράκλητον (ፓራክሌቶን) የሚለው የግሪክ ቃል አፅናኝ፣ አጋዥ፣ አበረታታች፣ ጠበቃ፣ ወዘተ. የሚሉ ትርጉሞች አሉት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን “ሌላ ፓራክሌቶን” ብሎ ሲል እርሱም ፓራክሌቶን መሆኑን እያመለከተ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ 90 ዓ.ም. ላይ በ 1ዮሐንስ መልእክት ፓራክሌቶን ተብሎ መጠራቱ ሌላ ፓራክሌቶን የሆነው መንፈስ ቅዱስ አለመምጣቱን የሚያሳየው በየትኛው ሎጂክ ነው? መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ ኢየሱስ ፓራክሌቶን መሆኑ እንደሚቀር ተናግሯል እንዴ? በእርግጥ 1ዮሐንስ 2፡1 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ የኛ ፓራክሌቶን (በዚህ አውድ ጠበቃ) ሆኖ እንደሚኖር እየተናገረ ነው፡፡

ይህ ሙስሊም ጸሐፊ ቆርጦ ያስቀረውን ወሳኝ ክፍል ጨምረን ጥቅሱን ደግመን እናንብብና ስለ ሙሐመድ ይናገር እንደሆን እንመልከት፡-

“ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።” (ዮሐንስ 14፡15-17)

ኢየሱስ ቃሉን ሲናገር የነበረው ለሐዋርያቱ ነው፡፡ አፅናኙም ይመጣል እያለ ያለው ወደ ሐዋርያቱ ነው፡፡ ለመሆኑ ሙሐመድ መች ነው የመጣው? ሐዋርያቱ ካለፉ ከ 6 ክፍለ ዘመናት በኋላ! ስለዚህ እንዴት ሆኖ ነው ወደ ሐዋርያቱ በመምጣት ለዘላለም ከእነርሱ ጋር የሚኖረው? አፅናኙ ዓለም የማያየውና የማያውቀው የእውነት መንፈስ ተብሏል፡፡ ለመሆኑ ሙሐመድ ዓለም ያላየውና ያላወቀው መንፈስ ነበረን? በፍፁም! በታሪክ የታወቀ ግዘፍ አካል የነበረው ሰብዓዊ ፍጡር እንጂ መንፈስ አልነበረም፡፡ ለመሆኑ ሙሐመድ በሐዋርያት ዘንድና በውስጣቸው ኖሯልን? እንዴት ሆኖ? ኢየሱስ ይመጣል ያለው አፅናኝ ከሐዋርያት ጋር አብሮ የሚኖርና በውስጣቸው የሚሆን መንፈስ እንጂ የሚዳሰስ አካል ያለው ሥጋ ለባሽ አይደለም፡፡ ስለዚህ አፅናኙ ሙሐመድ ነው የሚለው የሙስሊም ሰባኪያን ብሒል ከእውነት የራቀ ነው፡፡

አብዱል

ግን እውን ኢየሱስ ግሪክ ተናጋሪ ነበርን? አይ አረማይክ ተናጋሪ ነበር ይሉናል፤ ታዲያ “ሌላ አጽናኝ” ይሰጣችኋል” ነው ያለው ወይስ “ሌላ ነብይ” ይሰጣችኋል” ነው ያለው? ይህ የደበቁት እውነት እንገልጠዋለን፦

የሐዋርያት ሥራ 4:36 ትውልዱም የቆጵሮስ ሰው የነበረ አንድ ሌዋዊ ዮሴፍ የሚሉት ነበረ፥ እርሱም በሐዋርያት “በርናባስ” ተባለ ትርጓሜውም የመጽናናት ልጅ ነው፤

ልብ አድርጉ “በርናባስ”  בר נביא የአረማይክ ቃል ነው፤  የሁለት ቃላት ውቅር ነው፤ “ባር-ነቢያ” בר נביא ሲሆን “የነብይ ልጅ” ማለት ነው፤ “ባር” בר ማለት “ልጅ” ማለት ሲሆን “ነብያ” נביא ማለት ደግሞ “ነብይ” ማለት ነው፤ ግን ግሪኩ ላይ ሲተረጎም “ሃይኦ ፓራክሌቶስ” υἱός παρακλήσεως ማለትም “የመጽናናት ወይም የአጽናኝ ልጅ” አሉት፤ ይህንን ያነሳሁበት ቃሉ እየለወጡ እንዴት እውነቱን እንደሚደብቁ ለማሳየት ነው፤  ስለዚህ  “ፓራቅሊጦስ” Παράκλητον ተብሎ የተቀመጠው ቃል “ነብያ” נביא ማለት ከሆነ ኢየሱስ በአረማይክ “ሌላ ነብይ ይሰጣችኋል” ብሎ ነው የተናገረው ማለት ነው፤ ይህ ነብይ ማን ነው? ምሁራን፦ “አንድ አፅናኝ የሚያፅናናው በትንቢት ነው” ይሉናል፦

1ቆሮንቶስ 14:3 “ትንቢት” የሚናገር ግን ለማነጽና ለመምከር “ለማጽናናትም” ለሰው “ይናገራል።”

መልስ

የቃላት ስህተቶቹን በማረም እንጀምር፡፡ አንደኛ בר נביא የሚለው ቃል “ባር ነቢ” እንጂ “ባር ነቢያ” ተብሎ አይነበብም፡፡ በግሪክ Βαρνάβας (በርናባስ) ተብሎ የተነበበው ቃል መነሻው አረማይክ ቢሆንም አነባበቡ የግሪክ ነው፡፡ ሁለተኛ υἱός παρακλήσεως የሚለው “ሁዮስ ፓራክሌሴዎስ” ተብሎ እንጂ “ሃይኦ ፓራክሌቶስ” ተብሎ አይነበብም፡፡ ይህ ሰው ማንበብ እንኳ በማይችለው ቋንቋ ኤክስፐርት ለመምሰል ከሚጥር አስፈላጊ መሣርያዎችን በትክክል መጠቀም ቢለማመድ ጥሩ ነበር፡፡

“በርናባስ” የሚለው ቃል መነሻው የትኛው የአረማይክ ቃል እንደሆነ በምሑራን መካከል ስምምነት የለም፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት “ነባ” ወይም “ትንቢት” ከሚለው የእብራይስጥና የአረማይክ ቃላት ጋር የተያያዘ እንደሆነና የትንቢት አገልግሎት ማፅናናትና መምከር (Comforting and Exhortation) በመሆኑ (1ቆሮንቶስ 14:3) ከዚያ አንፃር “የመፅናናት ወይም የምክር ልጅ” (ሁዮስ ፓራክሌሴዎስ) ተብሎ እንደተተረጎመ ይናገራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በር-ኔቦ (የኔቦ ልጅ) ከሚል የመጣ መሆኑን ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ነገር ግን ኔቦ የአረማውያን ጣዖት በመሆኑ ሐዋርያት ይህንን ስያሜ ሊሰጡ አይችሉም በሚል መነሻ ይህ ግምት ተቀባይነት አላገኘም (C. K. Barrett. A Critical and Exegetical Commentary on the Acts of the Apostles; Vol. 1, p. 259) ፡፡ “በርነዋሃ” (የመፅናናት ልጅ) የሚል ሌላ የአረማይክ ቃል የጠቆሙ ሊቃውንትም ይገኛሉ (F.F. Bruce. The acts of the Apostles፡ the Greek Text with Introduction and Commentary; p. 160)፡፡ ሌሎች ደግሞ “በርነሃማህ” የሚል ተመሳሳይ ትርጉም ያለው ቃል ጠቁመዋል፡፡ http://www.jewishencyclopedia.com/articles/2533-barnabas-joses ስለዚህ ይህ ሙስሊም ጸሐፊ ሊቃውንት ባልተስማሙበት ሁኔታ ቃሉን እንዲህ ማለት ነው በማለት አንዱን ግምት ብቻ ይዞ የቅዱሳት መጻሕፍት ጸሐፊዎችን ቃሉን ለውጠዋል ብሎ መክሰሱ ተቀባይነት የለውም፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አረማይክ ተናጋሪ እንደነበረ ሊቃውንት ይስማሙበታል፡፡ ነገር ግን ትንቢቱ የሚገኝበት የዮሐንስ ወንጌል መጀመርያ በግሪክ ቋንቋ ነው የተጻፈው፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ የኢየሱስን ንግግር ለውጧል የሚያስብል ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፡፡ Παράκλητον ከሚለው ቃል የተለየ ሌላ ቃል በየትኛውም የእጅ ጽሑፍ ውስጥ አይደገኝም፡፡ ቁርኣን ደግሞ ስለ ሙሐመድ የተነገረው ትንቢት በዘመኑ በነበሩት አይሁድና ክርስቲያኖች እጅ በሚገኙት መጻሕፍት ውስጥ እንደሚገኝ ነው የተናገረው፡-

“ለነዚያ ያንን እነሱ ዘንድ በተውራትና በኢንጂል ተጽፎ የሚያገኙትን የማይጽፍና የማያነብ ነብይ የሆነውን መልክተኛ የሚከተሉ ለሆኑት…” (ሱራ 7፡157)

በዘመኑ በነበሩት ክርስቲያኖች እጅ የነበረው ተውራት በእብራይስጥ የተጻፈና ወንጌል ደግሞ በግሪክ የተጻፈ ነው፡፡ በግሪክ የተጻፈው ወንጌል ደግሞ ስለ መንፈስ ቅዱስ እንጂ ስለ ነቢይ አይናገርም፡፡ ስለዚህ ሙሐመድ በግሪክ በተጻፈው በዘመኑ በነበረው ወንጌል ውስጥ ስለ እርሱ እንደተተነበየ በእርግጠኝነት መናገሩ የኢየሱስ ንግግር ተቀይሯል የሚለውን የሙስሊሙን ጸሐፊ ሙግት ውድቅ ያደርጋል፡፡ በግሪክ ወንጌል ውስጥ ሙሐመድ አለመጠቀሱ ደግሞ ሙሐመድ ስለ ወንጌል ይዘት ዕውቀት እንዳልነበረው ያሳያል፡፡

አብዱል

አዎ የሚመጣው ነብይ ግን ልክ እንደ ኢየሱስ ከላከው እየሰማ መጪውን ክስተት የሚናገር እንጂ ከራሱ ምንም አይናገርም፦

ዮሐንስ 16:13 እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ “የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል” እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።”

መልስ

ጥቅሱ ስለ መንፈስ እንጂ ስለ ሥጋ ለባሽ አይናገርም፡፡ የሚመጣው አካል በግልፅ “የእውነት መንፈስ” ተብሎ ሳለ ሥጋ ለባሹን ሙሐመድን በቦታው የተካኸው ምን ያህል ብትታወር ነው?

አብዱል

መቼም ሁለተኛ ነብይ መንፈስ ቅዱስ ነው ካላችሁን እስቲ መንፈስ ቅዱስ ከኢየሱስ በተለየ መልኩ አዲስ ያስተማረው ትምህርቱ የት ይገኛል?

መልስ

በክፍሉ ውስጥ ስለ መንፈስ ቅዱስ እንጂ ስለ ነቢይ የሚናገር አንዳች ነገር የለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከኢየሱስ የተለየ አዲስ ትምህት ያስተምራልም አልተባለም፡፡ ይልቅ መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ ኢየሱስ የተናገረውን ለሐዋርያቱ እንደሚያሳስብ ተነግሯል፡- “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።” (ዮሐንስ 14፡26)

አብዱል

ነጥብ ሁለት

ሌላ”

ሌላ” የሚለው ገላጭ ደግሞ “አሎን” ἄλλον ነው፣ “አሎን” ተመሳሳይ ባህርይ ያለውን ምንነት ለማመልከት የሚውል ገላጭ ነው፣ ለምሳሌ፦

ማቴዎስ 5:39 ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሌላውን ἄλλην ደግሞ አዙርለት፤

 ቀኝ ጉንጭ ከግራ ጉንጭ እንደሚመሳሰል ሁሉ ሁለተኛ አጽናኝም ከመጀመሪያ አጽናኝ ጋር ይመሳሰላል፣ ሁለተኛ አጽናኝ ምን እንደሆነና ማን እንደሆነ ለመረዳት የመጀመሪያውን አጽናኝ በቅጡ መረዳት ግድ ይላል፦

መልስ

“አሎን” የሚለው የግሪክ ቃል በአማርኛ “ሌላ” ከሚለው ቃል የተለየ ትርጉም የለውም፡፡ ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ ተከታዩን ማስጠንቀቂያ በሰጠበት ክፍል ይህንን ቃል ተጠቅሟል፡- “የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ (ἄλλον Ἰησοῦν) ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ” (2ቆሮንቶስ 11፡4)፡፡ በዚህ ክፍል የቃሉ አገባብ ሐሰተኞች የሚሰብኩት ከእውነተኛ ኢየሱስ የተለየ ሌላ ኢየሱስ ለማለት እንጂ ሌላ ሁለተኛ ኢየሱስ ለማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ቃሉ እንደ አማርኛው ቃል ሁሉ አንድ ዓይነትነትን፣ ተመሳሳይነትን ወይም ተፃራሪነት ሊያመለክት ይችላል፡፡ ቃሉ በተለያየ መልክ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን የግሪክ መዝገበ ቃላት other, another (of more than two), different በማለት ይተረጉመዋል https://biblehub.com/greek/243.htm ፡፡ በርግጥ ኢየሱስና መንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ ማንነቶች በመሆናቸው የባሕርይ ልዩነት የላቸውም። መንፈስ ቅዱስም ኢየሱስ የጀመረውን ሥራ ነው በሐዋርያቱ ውስጥ የቀጠለው። ስለዚህ ቃሉን ሙስሊሙ ሰባኪ ባስቀመጠው መልኩ ብንወስደው ለሙግቱ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም።

አብዱል

@የመጀመሪያው አጽናኝ ከላከው ሰምቶ የሚናገር ሰው ነው፦

ዮሐንስ 8:40 ነገር ግን አሁን ከእግዚእብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኋችሁን “ሰው” ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፤

@የመጀመሪያው አጽናኝ ፈጣሪ ያናገረው ነብይ ነው፦

ማርቆስ 6:4 ኢየሱስም። “ነቢይ” ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው።

@የመጀመሪያው አጽናኝ ከላከው መልእክት የተቀበለ መልዕተኛ ነው፦

ዮሐንስ 8:26 ዳሩ ግን “የላከኝ እውነተኛ ነው እኔም ከእርሱ የሰማሁትን ይህን ለዓለም እናገራለሁ” አላቸው።

ዮሐንስ 12:49 እኔ “ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ”።

ሹፍ እንግዲህ የመጀመሪያው አጽናኝ ከፈጣሪ ሰምቶ የሚናገር ሰው፣ ነብይ፣ መልዕተኛና ትእዛዝን የተቀበለ ነው እንጂ ከራሱ የሚናገር አይደለም፣ ሁለተኛውም አጽናኝ ከፈጣሪ ሰምቶ የሚናገር እንጂ ከራሱ የሚናገር አይደለም፦

ዮሐንስ 16፥12-15 የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፦ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ።

መልስ

የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ከአብ ዘንድ ተልኮ ወደ ዓለም በመምጣት ሰው ሆኖ በምድር ላይ የአብን ዓላማ ፈፅሟል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ከሰማይ የሚመጣው ልክ እንደ ኢየሱስ ሁሉ የአብን ሐሳብ ለመፈፀም ነው፡፡ አንድ የአገራችን የነገረ መለኮት ሊቅ እንዳስቀመጡት “በመሢህነቱ ፍጹም ጠባቂ ታላቅ ነቢይና ዓይነተኛ ሊቀ ካህናት ዘለዓለማዊም ንጉሣችን የሆነ በአንዲት ተዋሕዶ ሕላዌ የሚሰገድለት ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው” (መሠረት ስብሐት ለአብ፣ ስምዓ ጽድቅ ብሔራዊ፣ በጥንታውያን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መምህራን ፍለጋ፣ 1991፣ ገፅ 71)፡፡ መንፈስ ቅዱስ እንደ ኢየሱስ ሥጋ ሆኖ (incarnated) የነቢይነት አገልግሎት ባይፈፅምም በሰዎች ውስጥ አድሮ ነቢያት ያደርጋቸዋል፤ ትንቢትንም ያናግራቸዋል፡፡ የትንቢት ምንጭ ራሱ መንፈስ ቅዱስ በመሆኑ የኢየሱስ የምድር ላይ አገልግሎትና የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት በዚህ ረገድ ምንም ልዩነት የለውም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ በእርሱና በሚመጣው አፅናኝ መካከል ያሉትን ተከታዮቹን ወሳኝ መመሳሰሎች ግልፅ በማድረጉ ሙሐመድ በዚህ ክፍል ምንም ዓይነት ቦታ የለውም፡፡

የመጀመርያው አፅናኝ የሆነው ኢየሱስ የአብን ፈቃድ ሊፈፅም ከሰማይ ተልኳል፡-

“ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና፡፡” (ዮሐንስ 6፡38)

ሁለተኛው አፅናኝ የሆነው መንፈስ ቅዱስ የአብን ፈቃድ ሊፈፅም ከሰማይ ተልኳል፡-

“…ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፦ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ።” (ዮሐንስ 16፡13-15)

“እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።” (ዮሐንስ 16፡7)

የመጀመርያው አፅናኝ ከአብ የወጣ (Proceed) ነው፡-

“ኢየሱስ አብ ኹሉን በእጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ…” (ዮሐ. 13፡3)፡፡

“እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና” (16፡27-28)፡፡

“ኢየሱስም አላቸው፦ እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና” (8፡42)፡፡

“ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ” (16፡28)፡፡

“ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ” (17፡8)፡፡

ሁለተኛው አፅናኝ ከአብ የሚወጣ ነው፡-

“ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፡፡” (ዮሐንስ 15፡26)

ሙሐመድ ከሰማይ አልተላከም፤ ከአብም ወጥቶ ወደ ዓለም አልመጣም፡፡ ይህንን ሃቅ ችላ ብሎ ትንቢቱን ለእርሱ ማድረግ ትልቅ ድፍረት ነው፡፡

አብዱል

ሁለተኛው አጽናኝ ኢየሱስ ያልተናገራቸውንና ኢየሱስ ተናግሮ ያስተማራቸውን የአምላክ አንድነት ትምህርት ከፈጣሪ ሰምቶ የሚያስተላልፍ እራሱን የቻለ ቅዋሜ-ማንነት ያለው ነው፣ ይህንን ለማሳየት ከራሱ himself” የሚለው ድርብ ተውላጠ-ስም” Reflexive pronoun” ይጠቀማል፤ ኢየሱስም ለራሱ ሲጠቀም ከራሴ my self” የሚለውን አጠቃቀም ያመሳስለዋል፣ ይህም የመጀመሪያው አጽናኝ ሰው፣ ነብይ፣ መልዕተኛ ሆኖ ከፈጣሪ ሰምቶ የሚያስተላልፍ ከሆነ ሁለተኛውም አጽናኝ በተመሳሳይ መልኩ ከፈጣሪ ሰምቶ የሚያስተላልፍ ሰው፣ ነብይ እና መልዕተኛ ነው።  

መልስ

ጌታችን ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን ማንነትን በሚያመለክት ተውላጠ ስም መጥቀሱ መንፈስ ቅዱስ ማንነት ያለው አካል መሆኑን የሚያሳይ እንጂ ሰው መሆኑን የሚያሳይ አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ማንነትን በሚያመለክት ተውለጣ ስም ስለተጠቀሰ የግድ ሥጋ ለባሽ መሆን አለበት ከተባለ በቁርኣን ውስጥ አላህና መላእክት በተመሳሳይ መንገድ ስለተገለጹ የግድ ሥጋ ለባሾች መሆን አለባቸው ማለት ነው፡፡ ይህ የጸሐፊውን የማሰብ አቅም የሚያስገመግም ደካማ ሙግት ነው፡፡

አብዱል

ከዚህ ነብይ በኃላ ሌላ ነብይ ስለማይመጣ ለዘላለም ከእኛ ጋር በነብይነቱ ይኖራል፤

መልስ

የጸሐፊውን ቅጥፈት ለማስተዋል ጥቅሱን ማንበብ ብቻ በቂ ነው፡-

“አሁን ግን ወደ ላከኝ እሄዳለሁ ከእናንተም፦ ወዴት ትሄዳለህ? ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። ነገር ግን ይህን ስለ ተናገርኋችሁ ኀዘን በልባችሁ ሞልቶአል። እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።” (ዮሐ. 16፡5-7)

የአፅናኙ አብሮነት እውን እንጂ ምናብ አይደለም፡፡ ኢየሱስ የአፅናኙን መምጣት ከእርሱ መሄድ ጋር በማነፃፀር ነው ያቀረበው፡፡ የመምጣቱን ተስፋ እየሰጠ የነበረው ደግሞ ለሐዋርያት ነበር፡፡ ሙሐመድ እንዴት ሆኖ ነው ከእርሱ ቀድመው ከስድስት ክፍለ ዘመናት በፊት ወደሞቱት ሐዋርያት መጥቶ ከእነርሱ ጋር ለዘላለም ሊኖር የሚችለው?

አብዱል

ክርስቲያኖች ይህንን ሁለተኛ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ ነው ሲሉ ከአውዱ ጋር ይጣላሉ፦

ዮሐንስ 16፤7 እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። “እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና”፤

መልስ

ይህ ሙስሊም ጸሐፊ ስለ አውድ ምንም አያውቅም፡፡ የጠቀሰውን ጥቅስ እንኳ አሟልቶ ባልጠቀሰበት ሁኔታ ክርስቲያኖች አውድ አይጠብቁም የሚል ክስ ማቅረቡ አስገራሚ ነው፡፡ ሙግቱን በሙሉ የሚያፈርሰውን የመጨረሻውን ዓረፍተ ነገር ከጥቅሱ ውስጥ አጉድሎ ነው የጠቀሰው፡-

“እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል፡፡ እኔ ባልሄድ አፅናኙ ወደ እናንተአይመጣምና፡፡ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ” (ዮሐ. 16፡7)፡፡

አፅናኙን ወደ ሐዋርያቱ የሚልከው ራሱ ኢየሱስ ነው፡፡ ሙስሊሞች ሙሐመድ በኢየሱስ እንደተላከ ያምናሉን? አፅናኙ ሙሐመድ ነው ከተባለ ተከታዩ አመክንዮአዊ ድምዳሜ አይቀሬ ነው፦

  • ሙሐመድን የላከው አላህ ነው።
  • ሙሐመድ አፅናኙ ነው።
  • አፅናኙን የላከው ኢየሱስ ነው።
  • ስለዚህ አፅናኙ ሙሐመድን የላከው አላህ ኢየሱስ ራሱ ነው።

ሙስሊሙ ሰባኪ ጥቅሱን ለምን ቆርጦ እንደጠቀሰ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ አውዱ በግልፅ አፅናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ውጪ ሌላ ማንም ሊሆን እንደማይችልም ይናገራል፡፡ እስኪ እነዚህን አባባሎች አንብቡና ለህሊናችሁ ፍረዱ፡-

“እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለሆነ ሊቀበለው የማይችለው የእውነት መንፈስ ነው፡፡ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውስጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቁታላቸሁ” (ዮሐ. 14፡17)፡፡

“አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አፅናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔምየነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል” (ዮሐ. 14፡26)፡፡

ለመሆኑ እነዚህ አባባሎች ለሥጋ ለባሽ ሊነገሩ የሚችሉ ናቸውን? በሰባተኛው ክፍለ ዘመን የኖረውን ብዙ የሥነ ምግባር ጉድለቶችን ሲያሳይ የነበረውን ሙሐመድን ሊያመለክቱ የሚችሉበት ዕድልስ ይኖራልን? ፍርዱን ለህሊናችሁ ትተናል፡፡

አብዱል

ሁለተኛው አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ እንዳልሆነ ጥልልና ጥንፍፍ ባለ መልኩ መረዳ ግድ ይላል፣ ኢየሱስ ስለ ሁለተኛው አጽናኝ የተናገረው ከማረጉ ማለትም ወደ ፈጣሪ ሳይሄድ ነው፣ ታዲያ ኢየሱስ ሳያርግ ሁለተኛው አጽናኝ እንደማይመጣ ተናግሮ እያለ ከማረጉ በፊትና ስለ ሁለተኛው አጽናኝ ከተናገረ በኋላ መንፈስ ቅዱስ መጥቷል፦

ዮሐንስ 20:22 ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና። መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።

መልስ

“ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና። መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።” የሚለው አነባበብ ስርዓተ ነጥቦቹን ካለማስተዋል የመነጨ የተሳሳተ ንባብ ነው፡፡ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፡- “ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና፦ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው።”

ጥቅሱ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ” ብሎ እንዳላቸው እንጂ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን እንደተቀበሉ የተዘገበ ዘገባ አይደለም፡፡ ጸሐፊው “ተቀበሉ” በሚለው ውስጥ “በ”ን በማላላት ማንበብ ሲኖርበት አጥብቆ በማንበብ ስህተት ሠርቷል፡፡ አማርኛው ይበልጥ ግልፅ እንዲሆን በአዲሱ መደበኛ ትርጉም እናንብበው፡-

‹‹ኢየሱስም እንደ ገና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እኔን እንደ ላከኝ፣ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው። ይህን ካለ በኋላም፣ እፍ አለባቸውና እንዲህ አላቸው፤ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ የሰዎችን ኀጢአት ይቅር ብትሉ፣ ኀጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል፤ ኀጢአታቸውን ይቅር ባትሉ ግን፣ ይቅር አይባልላቸውም።”›› (ዮሐ. 20፡21-23 አ.መ.ት)

ስለዚህ ኢየሱስ እፍ ካለባቸው በኋላ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ እንደነገራቸው እንጂ በዚያው ቅፅበት መንፈስ ቅዱስን እንደተቀበሉ የሚገልፅ ዘገባ አይደለም፡፡ ኢየሱስ እፍ በማለት የመንፈስ ቅዱስ ሰጪ እርሱ መሆኑን ተምሳሌታዊ በሆነ ሁኔታ በመግለፅ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ነግሯቸዋል፡፡ ሐዋርያቱ በዚያው ቅፅበት መንፈስ ቅዱስን ስለመቀበላቸው በጥቅሱ ውስጥ የተባለ ነገር የለም፡፡ ይልቅ መንፈስ ቅዱስን የመቀበል ክስተት ወደፊት የሚፈፀም መሆኑን በሌላ ቦታ እንዲህ ሲል ነግሯቸዋል፡-

“እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ።” (ሉቃስ 24፡49)

“ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው። ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፥ ነገር ግን፦ ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ።” (ሐዋ. 1፡3-5)

ሌሎች ሙስሊም ጸሐፊያን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ከዚያ ቀደም በምድር ላይ መኖሩን በመጥቀስ (የብሉይ ኪዳን ነቢያትና የኢየሱስን አገልግሎት በመጥቀስ) አስቀድሞ ስለነበረ ድጋሜ ሊመጣ አይችልም የሚል ሙግት ያቀርባሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስ መለኮት በመሆኑ በሁሉም ቦታ ይገኛል፡፡ የኢየሱስም አገልግሎት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነበር፡፡ ስለዚህ ለሐዋርያቱ የሰጠው ተስፋ መንፈስ ቅዱስ በኃይል ወደ እነርሱ በመምጣት ልዩ የሆነ መለኮታዊ ሥልጣን በማስታጠቅ ወንጌልን እንዲሰብኩ እንደሚያስችላቸው የሚያመለክት እንጂ ከዚያ ቀደም አለመኖሩን የሚያሳይ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል ጌታችን ኢየሱስ መንግሥተ ሰማያት በሰዎች መካከል መሆኗን አስተምሯል፤ ነገር ግን ደግሞ ገና የምትመጣ መሆኗንም አስተምሯል፡፡ ለሐዋርያቱ “መንግሥትህ ትምጣ” ብለው እንዲጸልዩ ነግሯቸዋል (ማቴዎስ 6፡10)፤ ነገር ግን ደግሞ በሌላ ቦታ የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣቷን ተናግሯል (ሉቃስ 17፡20-21)፡፡ ይህ ማለት መንግሥተ ሰማያት አሁናዊና መፃዒ ገፅታዎች አሏት ማለት ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ መንፈስ ቅዱስ መለኮት በመሆኑ ምን ጊዜም ከሐዋርያቱ ጋር የነበረ ቢሆንም ሊጠቀምባቸውና ሥራውን ሊሠራ በውስጣቸውም ሊኖር በታላቅ ክብር ወደ እነርሱ የመጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 2)፡፡

አብዱል

ሁለተኛው አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ ነው የሚለውን ብዥታ በህዝብ ላይ የጣሉት ሰዎች ናቸው፦

ዮሐንስ 14:26 አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።

መንፈስ ቅዱስ የሆነው የሚለው ቃል በፓፒረስ 75 ላይ፣ በፓፒረስ 22 ላይ፣ በፓፒረስ 52 ላይ፣ በፓፒረስ 90 ላይና ቤአፍሬማይ እደ-ክታብ”manuscript” ላይ የሉም፣ በተለይ በ 107-130 AD በተዘጋጁ ፓፒረሶች ላይ መንፈስ ቅዱስ የሆነው የሚለው ቃል አለመኖሩና ከዛ በኋላ ባሉት ላይ የመጨመሩ ጉዳይ የብርዘት ውጤቶች ናቸው፤ የመጀመሪያ መቶ ክፍለ-ዘመን የኢየሱስ ተከታዮች የሚባሉት የዮሐንስ ማህበረሰብ ሁለተኛው አጽናኝ ነብይ ነው ብለው ይጠብቁ ነበር፤ ነገር ግን ይህን እሳቤ ወደ መንፈስ ቅዱስ ያሸጋገሩት ሰዎች ናቸው፣ በዚህ ጥናት ዙርያ ዋቢ መጽሐፍትን ይመልከቱ፦

1. Cambridge History of Christianity, 6: Johannine Christianity, 2006

2. The Early Christian Community: From Diversity to Unity to Orthodoxy, lecture delivered February 25, 2000

3. Bart D Ehrman, 2002. Lost Christianities: Christian Scriptures and the Battles over Authentication.

መልስ

ይህ ጸሐፊ እነዚህን ምንጮች ዝም ብሎ ጠቀሰ እንጂ አንዳቸውንም ገፅ ጠቅሶ እንዳላስቀመጠ ወይም አንድ መስመር እንኳ ቃል በቃል እንዳልጠቀሰ ልብ በሉ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ቅጥፈት እየፈፀመ መሆኑ ነው፡፡ እርሱ በጠቀሳቸው ምንጮች ውስጥ የርሱን ሐሳብ የሚደግፍ ምንም ነገር የለም፡፡ ቁጥር 1 እና ቁጥር 3 ላይ የሚገኙት መጻሕፍት ሲሆኑ ቁጥር 2 ላይ የሚገኘው በኢንተርኔት ላይ የሚገኝ ጽሑፍ ነው፡፡ ጽሑፉን በቀጣዩ አድራሻ ገብታችሁ እስኪ ተመልከቱ፡፡ እንኳንስ በዮሐንስ ወንጌል የእጅ ጽሑፎች ውስጥ “መንፈስ ቅዱስ” የሚለው ጭማሪ መሆኑን ሊናገር ይቅርና ስለ ዮሐንስ ወንጌል የእጅ ጽሑፎች ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡ https://web.archive.net/web/20060901094259/https://minerva.wells.edu/whatsnew/wnspch25.htm

የመጀመርያ መታወቅ ያለበት ነገር በ 107-130 መካከል የተጻፈ ለዚህ ዘመን የበቃ የዮሐንስ ወንጌል ከፓፒረስ 52 ውጪ ሌላ የእጅ ጽሑፍ አለመኖሩ ነው፡፡ በጣም ጥንታዊ የሚባለው የዮሐንስ ወንጌል የእጅ ጽሑፍ ፓፒረስ 52 የሚባለው ሲሆን የዮሐንስ ወንጌል 18፡31-33 እና 18፡37-38 ብቻ የያዘ ዕድሜው በ114-138 ዓ.ም. መካከል እንደሆነ የተረጋገጠ ትንሽዬ ቁርጥራጭ ነው፡፡ ይህ ሙስሊም “በ 107-130 AD በተዘጋጁ ፓፒረሶች ላይ መንፈስ ቅዱስ የሆነው የሚለው ቃል አለመኖሩና ከዛ በኋላ ባሉት ላይ የመጨመሩ ጉዳይ የብርዘት ውጤቶች ናቸው” ብሎ መጻፉ ስለ አዲስ ኪዳን የእጅ ጽሑፎች ምንም ዕውቀት እንደሌለው ያሳያል፡፡

ይህ ሙስሊም በጣም እየዋሸ ነው፡፡ ፓፒረስ 75 የሚባለው የሉቃስ ወንጌልና የዮሐንስ ወንጌልን ግማሽ ክፍሎችን የያዘ የአዲስ ኪዳን ቁርጥራጭ ሲሆን ዮሐንስ 14፡26 ላይ “መንፈስ ቅዱስ” የሚል አለው፡፡ ፓፒረስ 22 የዮሐንስ ወንጌል 15፡25-16:2 እና ቁጥር 21-32 ብቻ ያሉት በዘመን ብዛት የተቆራረጠ ትንሽዬ ቁርጥራጭ ነው፡፡ ፓፒረስ 52 የዮሐንስ ወንጌል 18፡31-33 እና 18፡37-38 ብቻ ያሉት የእጅ መዳፍ የሚያክል ቁርጥራጭ ነው፡፡ ፓፒረስ 90 እንደዚሁ የዮሐንስ ወንጌል 18፡36-19፡7 ብቻ ያሉት በጣም አነስተኛ ቁርጥራጭ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ የእጅ ጽሑፎች “መንፈስ ቅዱስ” የሚል አለመኖሩን ለማሳየት ሊጠቀሱ የሚችሉ አይደለም፡፡ ኮዴክስ ኤፍራይሚም ቢሆን በዘመን ብዛት ከውስጡ የተቆራረጡ ብዙ ገፆች አሉት፡፡ ከዮሐንስ 14፡7 ጀምሮ ሁለት ቅጠሎች ከውስጡ ተበጣጥሰው የጠፉ ሲሆን በመካከል ያለውን ክፍል በመዝለል ከዮሐንስ 16፡21 ጀምሮ ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ የእጅ ጽሑፉ የተሟላ ባልሆነበት ሁኔታ “መንፈስ ቅዱስ” የሚለው ከውስጡ እንደጎደለ መናገር ማሰብ የሚችል አእምሮ ካለው ሰው የሚጠበቅ አይደለም፡፡

ስናጠቃልል ለሙስሊም ወገኖቻችን ማስተላለፍ የምንፈልገው መልእክት ቢኖር ሙሐመድን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማግኘት መሞከር “ላም ባልዋለበት…” ዓይነት ከንቱ ልፋት ነው የሚል ነው፡፡ ሙሐመድ በአስተምህሮም ሆነ በስነ ምግባር ከመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት ተርታ ሊሰለፍ የማይችል ልዩ የሆነ ትምህርት ያስተዋወቀ፣ ስለ ሌላ አምላክ ያስተማረና በባዕድ መንፈስ ቁጥጥር ስር የኖረ ሐሰተኛ ነቢይ እንጂ እውነተኛ ነቢይ አይደለም፡፡ የእርሱን ከንቱ ተረት ተቀብሎ ክርስቶስ ጌታችን ስለ መንፈስ ቅዱስ የተናገረውን ለእርሱ መስጠት ትልቅ ድፍረት ነው፡፡

ስለሙሐመድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተተንብዮአልን?

የሙሐመድ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ?

ሙሐመድ በኢሳያስ 29፡12?

ሙሐመድ