ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነው! እስልምናስ? – የመጽሐፍ ሒስና ግምገማ

ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነው!

እስልምናስ?

የመጽሐፍ ሒስ

ርዕስ – ንቁ! ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነውን?

ደራሲ – ሰልማን ኮከብ

የታተመበት ዘመን – 2010

አሳታሚ – አልተገለፀም

የገፅ ብዛት – 270

መግቢያ

የዘመናችን ሙስሊም ሰባኪያን በተሳሳቱ መረጃዎች የታጨቁ መጻሕፍትን በማሳተም እየተናደ የሚገኘውን የሃይማኖታቸውን ቅጥር ለመጠገንና ክርስቲያኖችን ግራ ለማጋባት ታጥቀው የተነሱ ይመስላሉ፡፡ በተለይም ውሉደ ኢንተርኔት የሆኑት የማሕበራዊ ሚድያ ታዋቂነት ከዕውቀት ጋር የተምታታባቸው አንዳንድ ጥራዝ ነጠቆች የሚያሳትሟቸው መጻሕፍት ለዚህ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ የተለያዩ ርካሽ ስልቶችን ተጠቅሞ በማሕበራዊ ሚድያ ዕውቅናን ማትረፍ ሲበዛ ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን የማሕበራዊ ሚድያ ዕውቅና ከንባብና ከትምሕርት ከሚገኘው ዕውቀት ጋር መምታታት የለበትም፡፡ መጽሐፍ ማሳተም ብዙ መማርና ማንበብን፣ ብሎም በልምድ የዳበረ ብስለትን ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ወገኖች ከሚመጥናቸው የማሕበራዊ ሚድያ መድረክ በመውጣት የሕትመቱን ዓለም ሲቀላቀሉ ለዚያ በሚያበቃ ዕውቀትና ብስለት ሳይሆን በቁንፅል ዕውቀትና በስሜታዊነት በመሆኑ መደበኛውን የክርስቲያን-ሙስሊም ውይይት ለጊዜውም ቢሆን ቢያደፈርሱትም በዘላቂነት ግን ራሳቸውንም ሆነ እንወክለዋለን የሚሉትን ሃይማኖት ለአደጋ ያጋልጣሉ፡፡ የችኩልነታቸውም ውጤት ዘግይቶም ይሁን በረጅም ጊዜ ሒደት ዋጋን ያስከፍላቸዋል፡፡ ሰልማን ኮከብን የመሳሰሉ ያልታደሉ ችኩሎች ደግሞ ፈጥነው የክርስቲያን ዐቃቤያነ እምነት ጥርስ ውስጥ ስለሚገቡ ውርደታቸውና ውድቀታቸው ይፈጥናል፡፡

የሰልማን መጽሐፍ ከኢንተርኔት የተለቃቀሙ የሐሰተኛ መረጃዎች ጥርቅም እንጂ የምሑራዊ ጥናት ውጤት እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ “ንቁ!” የሚለው የመጽሐፉ ርዕስ በራሱ በየወሩ ከሚታተመው የይሖዋ ምስክሮች መጽሔት የተኮረጀ ነው፡፡ ደራሲው ስለ እስልምናም ሆነ ስለ ክርስትና የረባ ዕውቀት የሌለው ምሑር መሳይ (Pseudo-Scholar) እንጂ እውነተኛ ምሑር አለመሆኑም ገሃድ ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት የመጽሐፉን የመጀመርያዎቹን ጥቂት ገፆች ብቻ መመልከት በቂ ነው፡፡ ታድያ መልስ መስጠት ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፤ ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቶቹ ሦስት ናቸው፡፡

1) መጽሐፉ ስለ እምነታቸው የጠለቀ ዕውቀት የሌላቸውን ክርስቲያን ወገኖች ግራ ሊያጋባ ስለሚችል መልስ እንድሰጥ ከአንዳንድ ክርስቲያን ወገኖች ተደጋጋሚ ማሳሰብያ ስለደረሰኝ፡፡

2) ሙስሊም ወገኖች ሰባኪዎቻቸው እንዴት አድርገው እንደሚያጭበረብሯቸው እንዲገነዘቡ ለመርዳት መጽሐፉ ጥሩ ማሳያ በመሆኑ፡፡

3) እንዲህ ያሉ የፕሮፓጋንዳ መጻሕፍትን ለማሳተም እየተጣደፉ የሚገኙትን ወገኖች ተመሳሳይ ቅሌት ውስጥ እንዳይገቡ ለማስጠንቀቅ፤ የሚሉት ናቸው፡፡

እያንዳንዱን የመጽሐፉን ገፅ እየፈተሹ መልስ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ስለታየኝ ይህ ምላሽ ጊዜ መውሰዱና መርዘሙ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ በተለያዩ ክፍሎች በመከፋፈል ወደ ፊት በተከታታይ መልስ መስጠቴን እቀጥላለሁ፡፡ ብዙ የተሳሳቱ መረጃዎችን በጥቂት ዓረፍተ ነገሮች ማስተላለፍ ቢቻልም ስህተቶቹን ማብራራትና ማረም ብዙ ጊዜና ገፅ ማባከንን እንደሚጠይቅ ማስታወስም አስፈላጊ ነው፡፡ አበው “አንድ ሞኝ ያሠረውን አሥር ብልሆች አይፈቱትም” ብለው መተረታቸው ያለ ምክንያት አይደለምና፡፡ ስለዚህ የሚወጡትን ጽሑፎች ጨርሳችሁ ታነቧቸውና ቀጣይ ክፍሎችን በትዕግስት ትጠባበቁ ዘንድ እጠይቃለሁ፡፡

ማሳሰቢያ፡ ከደራሲው መጽሐፍ በተወሰዱ ቀጥተኛ ጥቅሶች ውስጥ የሚገኙት የፊደልና ሌሎች ግድፈቶች የደራሲው እንጂ የእኔ አይደሉም፡፡ በኢታሊክስ የፊደል አጣጣል ያስቀመጥኩት እኔ ነኝ፡፡

ምዕራፍ አንድ

መጽሐፍ ቅዱስን ማን ጻፈው?

ደራሲው ርዕሱ ጥንቃቄን የሚሻ መሆኑን በመግለፅ ሐተታውን ቢጀምርም (ገፅ 10) ዳሩ ግን መረጃዎችን በማሳከርና የገዛ ራሱን ምናባዊ ፈጠራዎች በማከል የወረደባቸው የድምዳሜ ቁልቁለቶች ከግምት ውስጥ ሲገቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይቅርና የጥንቃቄን ትርጉም ማወቁ በራሱ አጠራጣሪ ነው፡፡

ገና በሁለተኛው አንቀፅ “መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ታሪክ ፀሐፊያን አይገመገምም የሚል የመሸፈኛ ዘዴ አለ” በማለት ሐሰተኛ ክስ በማቅረብ ይጀምራል (ገፅ 10)፡፡ ላለፉት 200 ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስ መደበኛ የጥናት ዘዴዎችን በመጠቀም ሲጠናና ሲገመገም እንደነበር ስለሚታወቅ ይህ አባባል ቅጥፈት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘትና ታሪካዊ አመጣጥ በክርስቲያኖችም ሆነ ክርስቲያን ባልሆኑት ሊቃውንት ሲመረመር ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያጠና የተከለከለ ወይንም ደግሞ የጥናቱን ውጤት ይፋ በማድረጉ ምክንያት በክርስቲያኖች አካላዊ ጥቃት የደረሰበት ሊቅ በዚህ ዘመን የለም፡፡ በታላላቅ የነገረ መለኮት ትምሕርት ቤቶቻችን ውስጥ የሚሰጡት ትምሕርቶች የክርስቲያንና ክርስቲያን ያልሆኑ ሊቃውንትን የጥናት ውጤቶች ያገናዘቡ መሆናቸው ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ እምነታቸውን የሚያውቁ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ የሚወጡ የጥናት ውጤቶችን የሚቀበሉትም ሆነ የማይቀበሉት በምክንያት እንጂ በጭፍን እምነት አይደለም፡፡ በዚህ ዘመን ክርስቲያን ባልሆኑት ሊቃውንት ላይ ያለን ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች ጥንታውያን ዓለማውያን ጽሑፎችን ለመመዘን ሁለት ዓይነት መመዘኛዎችን (double standard) ለምን ይጠቀማሉ? የሚል እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ለምን ያጠኑታል? የሚል አይደለም፡፡  ዕውቅ የአዲስ ኪዳን ሊቅ የነበሩት ኤፍ ኤፍ ብሩስ እንዲህ ብለዋል፡-

“ለአዲስ ኪዳናችን  ያለው ማስረጃ ማንም ሰው እርግጠኛነታቸውን አጠያያቂ ለማድረግ ከማያልማቸው ከብዙ ጥንታውያን ጽሑፎች እጅግ በጣም ይልቃል፡፡ አዲስ ኪዳን የዓለማውያን ጽሑፎች ስብስብ ቢሆን ኖሮ ተዓማኒነቱ ከምንም ዓይነት ጥርጣሬ በጸዳ ሁኔታ ተቀባይነት ባገኘ ነበር፡፡ … ቅዱሳት መጻሕፍትን የሃይማኖት መጻሕፍት በመሆናቸው ብቻ በጥርጣሬ የሚያዩዋቸውና ከሌሎች ዓለማዊ ወይንም የአረማውያን ጽሑፎች ይልቅ ለንደነዚህ ዓይነት ሥራዎች ብዙ ማስረጃዎችን የሚጠይቁ ሰዎች አሉ፡፡ ከታሪክ ተመራማሪ ዕይታ አኳያ ለሁለቱም አንድ ዓይነት መስፈርት ጥቅም ላይ መዋል አለበት…”[1]

የአዲስ ኪዳን የእጅ ጽሑፎች በብዛትና ለኦሪጅናሎቹ ባላቸው የዘመን ቅርበት ከዓለማውያን ጽሑፎች ምን ያህል የላቁ መሆናቸውን በዝርዝር ካስረዱ በኋላ ብሩስ እንዲህ ይላሉ፡-

“ማንኛውም ምሑር የሄሮዱተስ ወይንም ደግሞ የቱሳይዲደስ ሥራዎች ከመጀመርዎቹ ጽሑፎች 1,300 ዓመታት ያህል የዘገዩ በመሆናቸው ምክንያት ተዓማኒነታቸው ጥርጣሬ ውስጥ መግባቱን መስማት አይፈልግም፡፡”[2]

ስለዚህ ክርስቲያኖች አንዳንድ የዓለማውያን ሊቃውንትን ድምዳሜዎች የማንቀበልበት ምክንያት በአባይ ሚዛን በመጠቀማቸው ምክንያት እንጂ ደራሲው እንዳለው “መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ታሪክ ጸሐፊያን አይገመገምም” ከሚል ምክንያት በመነሳት አይደለም፡፡ ይልቅ ደራሲው እስላማዊውን አመለካከት በክርስትና ላይ ለመጫን እየሞከረ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ከዓለም ሃይማኖታት መካከል የእስልምናን ያህል ግምገማና ሒስን የሚፈራ ሃይማኖት የለም! በዚህ ዘመን የቁርኣንን ተዓማኒነት አጠያያቂ ያደረጉ ሊቃውንት እስከ ግድያ የሚደርስ ጥቃት ሲደርስባቸው ማየታችን ለዚህ እማኝ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ረሺድ ኸሊፋ የተሰኘ የቁርኣን ተርጓሚ ሱራ 9፡128-129 ላይ የሚገኙት ሁለት አንቀፆች ሙሐመድ ከሞቱ ከዓመታት በኋላ በኡሥማን ዘመን በቁርኣን ላይ የተጨመሩ መሆናቸውን በመግለፅ ከራሱ ቅጂ ውስጥ አስወግዷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በአክራሪ ሙስሊሞች ተገድሏል፡፡[3] ገርድ ሩዲጀር ፑዊን የተሰኘ ጀርመናዊ የአረብኛ ቋንቋ ሊቅ “የሰነዓ የእጅ ጽሑፎች” ተብለው በሚታወቁት የቁርኣን ጽሑፎች ላይ ጥናትና ምርምር እንዲያደርግ በየመን መንግሥት ጥሪ ተደርጎለት የነበረ ሲሆን ቁርኣን የተለዋወጠ መጽሐፍ መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ማግኘት ሲጀምር የየመን መንግሥት ሥራውን አስቁሞታል፡፡ ጽሑፎቹንም ድጋሜ እንዳያገኛቸው እገዳ ጥሎበታል፡፡ ዶ/ር ፑዊን ጽሑፎቹን ቀደም ሲል በፎቶ ፊልም ወስዷቸው ስለነበር ወደ አገሩ በመመለስ ጥናቱን ቀጥሏል፡፡ የጥናቱን ውጤት በመጽሐፍ አንደሚያሳትም ማሳወቁ በሙስሊሞች ዘንድ ቁጣና ተቃውሞን ሊያስነሳ እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት መኖሩን ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡[4]

ብሉይ ኪዳን

ኦሪት

ዘፍጥረት፣ ዘጸአት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኁልቁና ዘዳግም

ከጥንት ጀምሮ በነበረው የአይሁድም ሆነ የክርስቲያኖች አመለካከት መሠረት የአምስቱ ብሔረ ኦሪት (ፔንታቱክ) ጸሐፊ ሙሴ ነው፡፡ ይህ አመለካከት በብዙ ጥንታውያን አይሁድ ጸሐፍት እንዲሁም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በሐዋርያቱ ድጋፍ ተችሮታል (ማቴ. 8፡4፣ ማር. 12፡26፣ ሉቃ. 24፡44፣ ዮሐ 7፡19፣ ሐ.ሥ. 28፡23፣ 1ቆሮ 9፡9፣ ዕብ. 9፡19-20)፡፡

ከቅርብ ዘመናት ወዲህ ለዘብተኛ ሊቃውንት የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ አምስቱ መጻሕፍት በሙሴ እንዳልተጻፉና ዘግይተው እንደተጻፉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ለዚህ በዋናነት የተጠቀሙት ዶክሜንተሪ ሃይፖቴሲስ (Documentary Hypothesis) የተሰኘውን የጥናት ስልት ነው፡፡ ደራሲውም በመጽሐፉ ውስጥ ይህንኑ አመለካከት አንጸባርቋል፡፡ እንዲህ ይላል፡-

የብሉይ ኪዳን ለዘብተኛም ሆነ ፅንፈኛ ምሁራን በጥናታቸው እንደሚያትቱት ኦሪት ለሙሴ የተሰጠው ከክ.በ በ1312 ዓመት ሲሆን እነዚህ አምስቱ መጽሐፍት ግን የተዘጋጁት ከ600-400 ከክ.በ ነው፡፡ ዶክሜንተርይ ሃይፖቴሲስ (DH) እንዳስቀመጠው መጽሐፍቱ ከ500-950 ከክ.በ በደቡቡ የይሁዳ መንግስት፣ በሰሜኑ የእስራኤል መንግስት፣ በኢየሩሳሌም በተሃድሶ ዘመን እና በካህናት በባቢሎን ምርኮ ጊዜ የተዘጋጁ አራት ምንጮችን መሰረት አድርገው የተጻፉ ናቸው፡፡ (ገፅ 12)

ደራሲው ዶክሜንተሪ ሃይፖቴሲስ ምን እንደሆነ ባለማብራራቱ ምክንያት ስለ ጉዳዩ ያለው ግንዛቤ ምን ያህል እንደሆነ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም በቂ ዕውቀት እንደሌለው ከአገላለጹ በመነሳት መገመት ይቻላል፡፡ ለጻፈው ሐሳብ ምንጭ አለመጥቀሱና ዘመንን በማዛባት ማቅረቡ (500-950 ከክ.በ የሚባል የዘመን አቆጣጠር ስለሌለ) ግድ የለሽነቱ ግልፅ ነው፡፡ ርዕሱ “ጥንቃቄን የሚሻ” እንደሆነ በመግለፅ ከጀመረ በኋላ እንዲህ ያለ የጥንቃቄ ጉድለት ማሳየቱ በራስ ከመተማመኑ ጋር የሚመጣጠን ዕውቀት እንደሌለው ያሳያል፡፡ በራስ መተማመን ከዕውቀት ጋር ካልተመጣጠነ ደግሞ ከንቱ ተዓብዮ ይሆናል፡፡

ዶክሜንተሪ ሃይፖቴሲስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይዘትና የአጻጻፍ ስልቶች በመነሳት የደራሲያኑን ማንነት እንዲሁም የተጻፉበትን ዘመን ለመገመት የሚሞክር የጥናት ዘዴ ሲሆን ለዚህ የጥናት ስልት ፈር ቀዳጅ በመባል የሚታወቀው ጀርመናዊው ሊቅ ጁሊየስ ወልሃውሰን ነው (1844-1918 ዓ.ም.)፡፡ የዚህ መላ ምት ዋና ትኩረት የኦሪትን ተዓምራዊ ይዘትና የሙሴን ጸሐፊነት ማጣጣል ሲሆን መሠረቱም የእስራኤላውያን የአሓዳዊነት እምነት በዝግመተ ለውጥ ከመድብለ አማልክታዊነት ወደ አሓዳዊነት ያደገ ነው የሚል ነው፡፡ በወልሃውሰን ግምት መሠረት አምስቱ ብሔረ ኦሪት አራት ምንጮች ያሏቸው ሲሆን ያሕዌያዊ፣ ኤሎሂማዊ፣ ዘዳግማዊና ካህናዊ (Jehovist, Elohist, Deuteronomist, Priestly) በማለት ሰይሟቸዋል፡፡ በአጭሩ J-E-D-P በመባል የሚታወቁ ሲሆን እንደየ ቅደም ተከተላቸው የዘጠነኛው፣ የስምንተኛው፣ የስድስተኛውና የአምስተኛው ዓ.ዓ. (ቅድመ ክርስቶስ) ምንጮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምቱን አስቀምጧል፡፡[5]

ክርስቲያኖች ይህንን መላምት ለምንድነው የማይቀበሉት?

  1. መላምቱ በታሪክና በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ውድቅ ነው፡፡ ቀደም ሲል እንዳልነው የጥንት አይሁድ፣ ለምሳሌ ያህል የአንደኛው ክፍለ ዘመን ሊቃውንት የነበሩት ፋይሎና ጆሲፈስ (ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን) የአምስቱ ብሔረ ኦሪት ጸሐፊ ሙሴ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም መጻሕፍቱ በሙሴ የተጻፉ መሆናቸውን ይመሰክራል፡፡ ከአምስቱ መጻሕፍት አራቱ፣ ማለትም ዘጸአት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኁልቁና ዘዳግም በሙሴ የተጻፉ መሆናቸውን መጻሕፍቱ ራሳቸው ይመሰክራሉ (ዘጸ. 24፡4፣ ሌዋ. 1፡1፣ 4፡1፣ 5፡14፣ ዘኁ. 1፡1፣ 33፣2፣ ዘዳ. 1፡1፣ 4፡44፣ 29፡1)፡፡ መጽሐፈ ኢያሱን ጨምሮ ሌሎች የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትም ይህንኑ ምስክርነት ያረጋግጣሉ ( ኢያ. 1፡7፣ መሳ. 3፡4፣ 1ነገ. 2፡3፣ 2ነገ 14፡6፣ ዕዝ. 3፡2፣ ነህ. 1፡7፣ መዝ. 103፡7፣ ዳን. 9፡11፣ ሚል. 4፡4)፡፡ ቀደም ሲል እንዳልነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ ከእነዚህ መጻሕፍት ከመጥቀሳቸውም ባለፈ በሙሴ የተጻፉ ስለመሆናቸው ተናግረዋል (ማቴ. 4፡7-10፣ 8፡4፣ ማር. 7፡10፣ 12፡26፣ ሉቃ. 20፡28፣ 24፡44፣ ዮሐ. 7፡19፣ ሐ.ሥ. 3፡22፣ 28፡23፣ ሮሜ 10፡19፣ 1ቆሮ 9፡9፣ ዕብ. 9፡19-20)፡፡ ስለዚህ የታሪክና የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነቶች መላ ምቱን ውድቅ ያደርጉታል፤ ተዓማኒነታቸውንም ለመጠራጠር የሚያበቃ ምክንያት የለም፡፡
  2. J-E-D-P የጽሑፍም ሆነ የአርኪዎሎጂ ድጋፍ የሌለው መላ ምት ነው፡፡ አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት በተለያዩ ዘመናትና በተለያዩ ቦታዎች የተጻፉ መሆናቸውን የሚያሳይ ምንም ዓይነት የጽሑፍም ሆነ የአርኪዎሎጂ ማስረጃ የለም፡፡
  3. ጁሊየስ ወልሃውሰን የእስራኤላውያን የአሓዳዊነት እምነት በዝግመተ ለውጥ ከመድብለ አማልክታዊነት ወደ አሓዳዊነት ያደገ ነው ብሎ ያስቀመጠውን የመላምቱን መነሻ ውድቅ የሚያደርጉ የአርኪዎሎጂ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ስለዚህ የአሓዳዊነት ይዘት ያላቸው መጻሕፍት በሙሴ ዘመን ሊኖሩ እንደማይችሉ መናገር ከአርኪዎሎጂ ማስረጃ ጋር መላተም ነው፡፡[6]
  4. የመላምቱ “ማስረጃ” እንደሆነ የተነገረው በመጻሕፍቱ ውስጥ የሚገኘው የአጻጻፍ ልዩነት በቀላሉ ሊብራራ የሚችልና ውኀ የማይቋጥር ነው፡፡ የመላምቱ ፈር ቀዳጅ የነበረው ወልሃውሰን “ከያሕዌያዊ ምንጭ የተገኙ” ብሎ የፈረጃቸው ክፍሎች “ኤሎሂም” ከሚለው ይልቅ “ያሕዌ” የሚለውን የእግዚአብሔርን የተፀውዖ ስም የሚጠቀሙ ሲሆን “ከኤሎሂማዊ ምንጭ የተገኙ” ያላቸው ደግሞ “ኤሎሂም” የሚለውን የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ዘፍጥረት 1 ኤሎሂምን የሚጠቀም ሲሆን 2 ደግሞ ያሕዌን ይጠቀማል፡፡ እንዲህ እያለ የመጽሐፉን የተለያዩ ክፍሎች “ከያሕዌያዊና ከኤሎሂማዊ ምንጮች የተገኙ” በማለት ከፋፍሏቸዋል፡፡ ነገር ግን ሁለቱ ስሞች ያላቸውን አገባብ ስንመለከት ኤሎሂም የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት፣ ያሕዌ ደግሞ እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ሕብረት ማድረጉንና የሰዎች አምላክ መሆኑን በሚያሳዩ ክፍሎች ውስጥ ጥቅም ላይ ውለው እንመለከታለን፡፡ ስለዚህ ሙሴ ሁለቱን ስሞች በተለያየ አገባብ መጠቀሙ የተለያዩ መልእክቶችን ከማስተላለፍ አንፃር በዓላማ ያደረገው እንጂ ተቺዎች እንደሚሉት እነዚያ ክፍሎች ከተለያዩ ምንጮች ስለተቀዱ አይደለም፡፡ “ያሕዌ” በተጠቀሰባቸው የዘፍጥረት አብዛኞቹ ክፍሎች ውስጥ “ኤሎሂም” የሚለው ተደራቢ ሆኖ “ያሕዌ-ኤሎሂም” ተብሎ ተጠቅሶ መገኘቱም የትወራውን መሠረተ ቢስነት የሚያረጋግጥ ሌላ ማስረጃ ነው፡፡ ካህናዊ ሕግጋትና ሌሎች ሕግጋት ልዩነት ስላላቸው የአጻጻፍ ልዩነቶቹን መነሻ በማድረግ “ካህናዊና ዘዳግማዊ ምንጮች” ብሎ ያስቀመጠው ግምትም የሚያስኬድ አይደለም፡፡ እጅግ ደካማ ነው፡፡

ሙስሊሞች ይህንን መላ ምት መቀበላቸው ምን ችግር ያስከትላል?

  1. ከቁርኣንና ከሐዲስ መጻሕፍት ጋር ይጋጫል፡፡ የሙሴ ተውራት በሙሐመድ ዘመን በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ እንደነበረ ቁርኣንና እስላማዊ ሐዲሳት[7] ይመሰክራሉ (ቁርኣን 2፡40-41፣ 2፡89፣ 2፡91፣ 2፡101፣ 10፡94፣ 7፡169፣ 2፡44፣ 2፡113፣ 2፡121፣ 3፡93፣ 3፡113፣ 5፡66፣ 5፡68፣ 5፡43-44፣ 5፡65፣ 2፡4)፡፡ በታሪክ የታወቀው ተውራት (ቶራህ) የዶክሜንተሪ ሃይፖቴሲስ አቀንቃኞች እየተቿቸው የሚገኙት የአምስቱ መጻሕፍት ስብስብ በመሆኑ ሙስሊሞች ይህንን መላምት ከተቀበሉ የገዛ እምነታቸውን ውድቅ አደረጉ ማለት ነው፡፡
  2. የመላምቱ ዋልታና ማገር “የእስራኤላውያን አሓዳዊነት በዝግመተ ለውጥ ከመድብለ አማልክታዊነት የተገኘ በመሆኑ የሙሴን ያህል ዕድሜ የለውም” የሚል ነው፡፡[8] ነገር ግን ከአብርሃም ጀምሮ፣ ልጁ ይስሓቅና የይስሐቅ ልጅ ያዕቆብ እንዲሁም ከእርሱ የተገኙት አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች አንዱን አምላክ ያመልኩ እንደነበር ሙስሊሞች  ስለሚያምኑ ሊያስኬዳቸው አይችልም፡፡ መላምቱን መቀበል አብረሃምና ነገዶቹ አንዱን አምላክ አያውቁትም ማለት ይሆናልና፡፡
  3. የመላምቱ ዋና ዓላማ እግዚአብሔር አምላክ በሙሴ በኩል የሠራቸውን ተዓምራትና እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ያደረጉትን ጉዞ ማጣጣል በመሆኑ ሙስሊሞች ይህንን መላምት ከተቀበሉ እነዚህን እውነታዎች ሊክዱ ነው፡፡ እነዚህን እውነታዎች መካድ ደግሞ ቁርኣንን መካድ ነው (ቁርኣን 28፡30-32፣ 26፡61-68)፡፡
  4. አንድ ሰው የቁርኣንንም ክፍሎች በዚህ መንገድ ከፋፍሎ ተመሳሳይ መላምት መፍጠር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ረብ የሚለው የፈጣሪ ስም በ 11 የቁርኣን ሱራዎች ውስጥ አይገኝም (24፣ 48፣ 49፣ 58፣ 61፣ 62፣ 77፣ 88፣ 95፣ 104፣ 112)፡፡ እንዲሁም አላህ የሚለው ስም በ 18 ሱራዎች ውስጥ አይገኝም (54፣ 55፣ 56፣ 68፣ 75፣ 78፣ 83፣ 89፣ 92፣ 93፣ 94፣ 99፣ 100፣ 105፣ 106፣ 108፣ 113፣ 114)፡፡ ስለዚህ ረብ ያልተጠቀሰባቸውን፣ አላህ ያልተጠቀሰባቸውን እንዲሁም ረብና አላህ ተቀላቅለው የተጠቀሱባቸውን ሱራዎች ይዘን ከሦስት የተለያዩ ምንጮች የተቀዱ ናቸው ልንል እንችላለን፡፡ ዶክሜንተሪ ሃይፖቴሲስ ማለት በአጭሩ ይህ ነው፡፡ ሙስሊም ወገኖች ቁርኣንን በተመለከተ እንዲህ ያለውን ግምታዊ አመለካከት የማይቀበሉ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን ፈጥነው ተቀብለው የሚያስተጋቡበት ምክንያት ምንድነው?

እዚሁ ገፅ ላይ ደራሲው አንድ ከእውነት የራቀ ነገር ጽፏል፡፡ እንዲህ ይለናል፡-

አይሁዶች በ90 (እ.ኤ.አ) በጀሚኒያ ጉባኤ በፅሑፍ ያልሰፈረውንና በትውፊት የተላለፈ ኦሪት የተባሉትን አስወጥተው አምስቱ መጽሐፍት ብቻ ያስቀሩ ሲሆን ሌሎቹን ‹‹አፖክሪፋ›› ወይንም ‹‹ድብቅ ኦሪት›› ብለው እንደሸሸጓቸው በታሪክ ተፅፎ እናገኛለን፡፡ (ገፅ 12)

በየትኛው ታሪክ ነው የተጻፈው? ምንጭ አልጠቀሰም፡፡ ምንጭ ያለመጥቀሱ ምክንያቱ እርሱ ከተናገረው ውስጥ ማስረጃ ያለው ብቸኛው ብሂል የጀምኒያ ጉባኤ ተደርጓል የሚለው ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ማስረጃ አልባ የግል ፈጠራው ነው፡፡

የትኞቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በቀኖናነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ እንደነበሩ ለይቶ ዕውቅናን ለመስጠት በ90 ዓ.ም. ዮሐናን ቤን ዛካይ በተባለ ረቢ መሪነት ጥቂት የአይሁድ ሊቃውንት በጀምኒያ እንደተሰበሰቡ የታሪክ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ የዚህ ጉባኤ ዋና ትኩረት መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞንና መጽሐፈ መክብብ ቀኖናዊ ናቸው ወይንስ አይደሉም? የሚል የነበረ ሲሆን ሁለቱን መጻሕፍት ጨምሮ ሰላሳ ዘጠኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ብቸኛ እስትንፋሰ መለኮት መሆናቸውን ተስማምተዋል፡፡ ይህ ጉባኤ በቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና ላይ ለውጥ ለማድረግ የተሰበሰበ ባለመሆኑ የሆነ ነገር እንዳስወጡና እንደጨመሩ በማስመሰል መናገር በእጅጉ የተሳሳተ ነው፡፡ ያንን ለማድረግ የሚያስችል በቂ የሊቃውንት ውክልናም እንዳልነበረው የታሪክ ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል፡፡[9]

“በጽሑፍ ያልሰፈረውንና በትውፊት የተላለፈ ኦሪት የተባሉትን አስወጥተው” የሚለው የደራሲው አባባል ትርጉም አልባ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ቀደም ሲል ለነበሩት መጻሕፍት ዕውቅናን ለመስጠት ከተሰበሰቡ ያልተጻፈውን እንዴት አስወጡ ይባላል? ትርጉም አይሰጥም!

በዚህ ዘመን የሚገኘው ረቢያዊ ይሁዲ ከሙሴ ኦሪት በተጨማሪ ተልሙድ፣ ሚሽናህ፣ ጌመራ፣ ወዘተ. በተሰኙ የሕግጋት ስብስቦች ላይ የተመሠረተ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ እነዚህ ሕግጋት በአፈ ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ እንደኖሩ የሚነገር ሲሆን ከሁለተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በጽሑፍ ሰፍረዋል፡፡ በረቢያዊ ይሁዲ አመለካከት መሠረት እግዚአብሔር ለሙሴ የተጻፉና ያልተጻፉ ሕግጋትን የሰጠው ሲሆን ይህ አመለካከት ማስረጃ የሌለው አፈታሪክ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስና ሐዋርያቱም እነዚህን የአይሁድ የፈጠራ ሕግጋትና ታሪኮች ተቃውመዋል (ማር. 7፡8፣ 1ጢሞ. 1፡3-4፣ ቲቶ 1፡13-14)፡፡ ደራሲው እነዚህ አፈ ታሪካዊ ሕግጋት ቀኖናዊ አለመሆናቸው ትክክል መስሎ ካልታየው በጽሑፍ ሰፍረው ለዚህ ትውልድ ስለበቁ አንብቦ የራሱን ፍርድ መስጠት ይችላል፡፡ በአጠቃላይ እርባና የሌላቸው የሰው ፈጠራዎች ናቸው፡፡ ዳሩ ግን የቁርኣን ደራሲ ብዙ ታሪኮችንና ትምሕርቶችን ከእነዚህ መጻሕፍት መኮረጁ በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡[10]

ደራሲው ‹‹አፖክሪፋ›› ወይንም ‹‹ድብቅ ኦሪት›› በማለት በጉባኤው የተሸሸጉ መጻሕፍት መኖራቸውን መናገሩ ሌላ እብለት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚናገራቸው ነቢያት ባልነበሩበት ዘመን የተጻፉ ከጀምኒያ ጉባኤ በፊትም ሆነ በኋላ በአይሁድ ዘንድ ተቀባይነትን ያላገኙ መጻሕፍት መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ዛሬ በኦርቶዶክስና በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ዲዩትሮካኖኒካል (ተጨማሪ ቀኖና) የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸው ከቀኖና የተቆጠሩት በመሆናቸው “ተሸሸጉ” የሚለው ክስ መሠረተ ቢስ ነው፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በአንዳንድ የአይሁድ ቡድኖች ዘንድ ጥቅም ላይ ከመዋል በዘለለ ከጀምኒያ ጉባኤ በፊት የቀኖናነት ደረጃ እንደተሰጣቸው የሚጠቁም ማስረጃ ባለመኖሩ የቀኖናነት ደረጃን ያጡት በጉባኤው ውሳኔ እንደሆነ በማስመሰል መናገር የታሪክ ዕውቀት እጥረት ነው፡፡ “አፖክሪፋ” ወይም “ስውር” የሚለው ስያሜም ከጉባኤው ከሦስት ክፍለ ዘመናት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ላቲን ቋንቋ በተረጎመው በቅዱስ ጀሮም የተሰየመ እንጂ በጀምኒያ ተሰብሳቢዎች የተሰጠ ስያሜ ባለመሆኑ ደራሲው “‹‹አፖክሪፋ›› ወይንም ‹‹ድብቅ ኦሪት›› ብለው ሸሸጓቸው” ብሎ መጻፉ የረባ ጥናት አለማድረጉን የሚያሳይ ቅጥፈት ነው፡፡[11]

የኋለኞቹ ዘመናት ማብራርያዎች በመጻሕፍቱ ውስጥ መገኘታቸው በሙሴ እንዳልተጻፉ ያረጋግጣሉን?

አምስቱ ብሔረ ኦሪት በሙሴ የተጻፉ መሆናቸው በአይሁድና በክርስቲያኖች ዘንድ በፅኑ ቢታመንም ከሙሴ በኋላ የነበሩ ሰዎች አልፎ አልፎ ማብራርያ መስጠታቸውና አንዳንድ ቃላትን ለዘመናቸው አንባቢያን በሚገባ መንገድ መጻፋቸው ይታመናል፡፡[12] ለዘብተኛ ምሑራን ይህንን እውነታ መጻሕፍቱ በሙሴ ላለመጻፋቸውና ከሙሴ ህልፈት በኋላ ዘግይተው ስለመጻፋቸው እንደ ማስረጃ ጠቅሰው ይናገራሉ፡፡ የመጽሐፉ ደራሲም ይህንን ስሁት ድምዳሜ ያረጋግጥልኛል ያላቸውን የተወሰኑ ጥቅሶች አቅርቧል (ገፅ 12-15)፡፡ ዳሩ ግን መጽሐፍቱን ይገለብጡ የነበሩ ሰዎች ከኋለኞች የታሪክ ዘመናት ጋር በማመሳከር ማብራርያዎችን ማከላቸው መሠረታዊው ጽሑፍ በሙሴ እንዳልተዘጋጀ አያረጋግጥም፡፡ ይህም በዘመነ ነቢያት የተፈፀመ መሆኑና በጌታችን በኢየሱስና በሐዋርያቱ መፅደቁ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የተፈፀመ ሰናይ ተግባር መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ባይሆን ኖሮ ቅዱሳን ነቢያት እንዲሁም ጌታ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ከመጻሕፍቱ ጠቅሰው ከማስተማር ይልቅ ይህንን ተግባር በተቃወሙና ትክክል አለመሆኑን በነገሩን ነበር፡፡ የሙሴን አሟሟትና መቀበር የሚጠቅሰውን የዘዳግም መዝጊያንም በዚሁ መንገድ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

የበኩረ ጽሑፎች መጥፋት

ደራሲው እንዲህ ሲል የቅጥፈት ዲስኩሩን ይቀጥላል፡፡ (መልስ ለመስጠት እንዲያመች ዓረፍተ ነገሮቹን በቁጥር ከፋፍለናቸዋል)፡-

1የኦሪትን ህልውና ስናይ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ኦሪት የሙሴ ነው ከመባሉ ውጭ በፅሁፍ ያስተላለፈውን ስረ-መሰረት አናገኝም፡፡  2እሱ ይቅርና አምስቱ መጽሐፍት መሰረት አድርገው የተነሱበት አራቱ ምንጮችም የሉም፡፡ 3እንደዚሁ የዕብራይስጥ ቀዳማይ እደ-ክታብም (manuscript) እናገኝም፡፡ 4ዛሬ ላይ ቀዳማይ እደ-ክታብ ተብሎ የተመዘገበው በ280 (እ.ኤ.አ) የእስክንድርያ 70 የአይሁድ ሊቃውንት አምስቱ መጽሐፍትን ከዕብራይስጥ ወደ ኮይኔ ግሪክ የተረጎሙት ነው፡፡ 5ወደ ግሪከኛ የተረጎሙበት ዕብራይስጡ መጽሐፍ ግን የለም፡፡ 6ሌሎች ሰማሪያን፣ ማሶሬቲክ የሚባሉት የሙት ባህር ጥቅል እደ-ክታቦችም ከግሪኩ ትርጉም በኋላ የመጡ ናቸው፡፡ 7ጥንታዊ ትርጉሞች የሚባሉት የላቲን፣ የስላቮኒክ፣ የሶርያ፣ የጆርዲያ፣ የአርመንያ፣ የግብጽ የመሳሰሉት ጥንታዊ ኦሪቶችም እንዲሁ የግሪኩን ትርጉም መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡

8በአጠቃላይ ኦሪት ከታሪካዊ ማስረጃዎችና ከራሱ ከመጽሐፉ ምስክርነት ከሙሴ ህልፈት ከዘመናት በኋላ ማንነታቸው በማይታወቁ ሰዎች የተፃፈና በጊዜ ሂደት እየተጨመረና እየተቀነሰ የመጣ መጽሐፍ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ (ገፅ 16)፡፡

በነዚህ ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ የታጨቀው የቅጥፈት ብዛት የማይታመን ነው፡፡ የመጀመርያው ዓረፍተ ነገር የሞኝ ጥያቄ ነው፡፡ ከ3300 ዓመታት በፊት የተጻፉ መጻሕፍት እስከ ዛሬ ድረስ ለምን አልኖሩም? ብሎ የሚጠይቅ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ሰው የለም፡፡ ጥንታውያን ጽሑፎች በጊዜ ሒደት በስብሰው አሊያም በሌላ ምክንያት መጥፋታቸው የማይቀር የተፈጥሮ ሒደት በመሆኑ ለዘብተኛም ሆኑ አጥባቂ ሊቃውንት እንዲህ ያለውን መመዘኛ አይጠቀሙም፡፡ ቁርኣንን ጨምሮ ከጥንታዊ መጻሕፍት መካከል በኩረ ጽሑፉ ለዚህ ዘመን የበቃ አንድም መጽሐፍ የለም፡፡

ሁለተኛው ዓረፍተ ነገር ደግሞ የግምታዊ ምንጮችን ህልውና ከእውናዊ ምንጮች ህልውና ጋር ያስተካከለ በመሆኑ ምላሽ እንኳ የሚያሻው አይደለም፡፡ “አራቱ ምንጮች” የተባሉት ከዶክሜንተሪ ሃይፖቴሲስ በመነሳት የቀረቡ ግምታዊ ምንጮች እንጂ ተጨባጭ ማስረጃ ያላቸው አይደሉም፡፡ ሲጀመር “አራቱ ምንጮች” በጽሑፍ የነበሩ ስለመሆናቸው የሃይፖቴሲሱ አቀንቃኞች እንኳ ደምድመው አላስቀመጡም፡፡

ሦስተኛው ዓረፍተነገር ፍፁም ቅጥፈት ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት የተጻፉትን ጨምሮ ብዙ ቀዳሚያን የዕብራይስጥ የእጅ ጽሑፎች ይገኛሉ፡፡ ደራሲው ቀዳሚያን የእጅ ጽሑፎች (Early Manuscripts) እና በኩረ ጽሑፍ (Original Manuscript) የተምታቱበት ይመስላል፡፡ ይህም ለርዕሱ እንግዳ መሆኑን አመላካች ነው፡፡

አራተኛውና አምስተኛው ዓረፍተ ነገሮች የመረጃ መዛባትና ቅጥፈት አለባቸው፡፡ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም በመባል የሚታወቀው የብሉይ ኪዳን የግሪክ ትርጉም ብሔረ ኦሪት ቅድመ ክርስቶስ 285-246 ዓ.ዓ መካከል በግብፅ እስክንድርያ የተዘጋጀ ሲሆን የሊቃውንቱ ብዛት 72 እንደነበርና ከያንዳንዱ ነገደ እስራኤል ስድስት ስድስት ሊቃውንት እንደተውጣጡ በታሪክ ተጽፏል፡፡ ሌሎች መጻሕፍት ግን በተለያዩ ዘመናት በተለያዩ ተርጓሚዎች ወደ ግሪክ ተተርጉመዋል፡፡ [13] ደራሲው ግን የመጽሐፉ ስያሜ ከሊቃውንቱ ቁጥር ጋር ስለተምታታበት የሊቃውንቱን ቁጥር 70 ያደረገ ሲሆን ዘመኑን ደግሞ “በ280 (እ.አ.አ)” በማለት አስቀምጦታል፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት የሚገኘው ዘመን ሲጠቀስ “እ.አ.አ” (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር) ብሎ መጥቀስ የተለመደ ባለመሆኑ ደራሲው ዘመኑን ሲጠቅስ ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሚገኘውን ዘመን እያሰበ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ “እ.አ.አ” ብሎ በጠቀሰባቸው ቦታዎች በሙሉ ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሚገኙትን ዘመናት ለማመልከት በመሆኑ (ለምሳሌ ገፅ 12፣ 46፣ 166) የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም የተዘጋጀው ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደሆነ ማሰቡን እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ ምን ያህል የዕውቀት እጥረት እንዳለበት የሚያሳይ ነው፡፡

ደራሲው ቅጥፈቱን በስድስተኛው ዓረፍተ ነገር ውስጥም አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የማሶሬት ቅጂ የሚባለው ከ7ው እስከ 9ው ክ.ዘ (ዓ.ም) መካከል የተገለበጠ የዕብራይስጥ ብሉይ ኪዳን ቅጂ በመሆኑ ደራሲው እንደቀጠፈው የሙት ባሕር ጥቅልል አይደለም፡፡[14] የሳምራውያን ፔንታቱክ የተወሰኑ ቁርጥራጮች ግን ከሙት ባሕር ጥቅልሎች ጋር ተገኝተዋል፡፡ እነዚህ የእጅ ጽሑፎች ከሰብዓ ሊቃናት ትርጉም በኋላ የተገለበጡ መሆናቸው የዕብራይስጡን ብሉይ ኪዳን በዕድሜ ከሰብዓ ሊቃናት ትርጉም አያሳንስም፤ ምክያቱም የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ምንጭ የእነዚህ ቅጂዎች እናት የሆነው የእብራይስጡ ቅጂ ነውና፡፡

በሰባተኛው ዓረፍተ ነገር ላይ ከዘረዘራቸው የተለያዩ ቋንቋዎች ትርጉሞች መካከል የዕብራይስጡን የእጅ ጽሑፎች መሠረት ያደረጉ መኖራቸውን ከታሪክ ማየት ስለሚቻል ደራሲው በማስረጃ ሳይሆን በደመ ነፍስ እየተናገረ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህም የላቲን፣ የሦርያና የጆርጅያ ትርጉሞች ናቸው፡፡ ቅዱስ ጀሮም ብሉይ ኪዳንን ወደ ላቲን ሲተረጉም የግሪኩን ትርጉም ቢያመሳክርም በቀጥታ የዕብራይስጡን እንደተጠቀመ ታሪክ ይናገራል፡፡[15] ይህንን ሃቅ ከጀሮም ጋር በአንድ ዘመን የኖረው ቅዱስ አውግስጢኖስ ተናግሯል፤ በቀጥታ ከዕብራይስጥ መተርጎሙን “የእግዚአብሔር ከተማ” በሚል ርዕስ በጻፈው ዝነኛ መጽሐፉ ውስጥ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡[16] በተመሳሳይ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን የተዘጋጀው ፐሺታ የተሰኘው የሦርያ ቋንቋ ትርጉም በቀጥታ ከዕብራይስጡ እንደተተረጎመ የታወቀ ነው፡፡[17] የጆርጅያ ትርጉምና የዕብራይስጥ ጽሑፍ ጎን ለጎን የተቀመጡበት በ11ኛው ክ.ዘ. የተጻፈ የእጅ ጽሑፍ በመገኘቱ ምክንያት የጆርጅያ ትርጉምም ከዕብራይስጡ የተዘጋጀ እንደሆነ ማወቅ ተችሏል፡፡[18]

ቅጥፈት የማይሰለቸው ደራሲ “ኦሪት … ከሙሴ ህልፈት ከዘመናት በኋላ ማንነታቸው በማይታወቁ ሰዎች የተፃፈና በጊዜ ሂደት እየተጨመረና እየተቀነሰ የመጣ መጽሐፍ መሆኑ ተረጋግጧል” ይለናል፡፡ በእንዲህ ዓይነት የተዛባና ያልተጣራ መረጃ የታጨቀ መጽሐፍ ጽፎ እውነተኛና ሕያው በሆነው ቃለ እግዚአብሔር ላይ በድፍረት መናገር በእውነቱ ከሆነ እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡

ንቁ! ሙስሊም ሰባኪያን ሐሰተኞች ናቸው፡፡

ይቀጥላል…

 


[1] Bruce, FF. The New Testament Documents, Are They Reliable?, 1959, pp. 7-9

[2] Ibid.

[3] http://masjidtusco.net/quran/appendices/appendix24.html

[4] https://www.theguardian.com/education/2000/aug/08/highereducation.theguardian

[5] Norman Geislere: Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 1391

[6] Ibid., 1392

[7] Sunan Abu Dawud, Book 38 (Kitab al Hudud, i.e. Prescribed Punishments), Number 4434

[8] Geisler, pp. 1390-91

[9] Lee Martin McDonald, James A. Sanders, Editors: The Canon Debate; Jack P. Lewis, Jainnia Revisited, 2002, p. 161

[10] Rev. W. ST Clair Tisdall. The Sources of Islam  ሙሉ መጽሐፍ ያንብቡ፡፡

[11] Encyclopedia Brittanica:

https://www.britannica.com/topic/apocrypha

[12] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 1972፣ ገፅ 189

[13] Encyclopedia Britannica:

https://www.britannica.com/topic/Septuagint

[14] Herschel Shanks. Understanding the Dead Sea Scrolls; (1st ed.), 1992), Random House. p. 336

[15] Worth Jr, Roland H. Bible Translations: A History Through Source Documents. pp. 29–30

[16] City of God edited and abridged by Vernon J. Bourke 1958

[17] Sebastian P. Brock. The Bible in the Syriac Tradition St. Ephrem Ecumenical Research Institute, 1988. P. 13:

[18] Filling Some Gaps: Notes on the History of Genetian Bible Translation, p. 50: 


 

ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነው! እስልምናስ?

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ