ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነው! እስልምናስ? – የመጽሐፍ ሒስና ግምገማ

ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነው!

እስልምናስ?

የመጽሐፍ ሒስና ግምገማ – ክፍል 2

ርዕስ – ንቁ! ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነውን?

ደራሲ – ሰልማን ኮከብ

የታተመበት ዘመን – 2010

አሳታሚ – አልተገለፀም

የገፅ ብዛት – 270

ግምገማችንን ካቆምንበት እንቀጥላለን፡፡ ያለፈውን ክፍል ያላነበባችሁ ወገኖች እዚህ ጋ በመንካት ታነቡ ዘንድ እናበረታታችኋለን፡፡ ደራሲው በጥቂት ገፆች ውስጥ ለቁጥር የሚያታክቱ ስህተቶችንና ቅጥፈቶችን መፈፀሙን በቀደመው ክፍል ተመልክተናል፡፡ እነሆ “ምሑሩ” የስህተትና የቅጥፈት ዙሩን አክርሯልና ለባሰው ነገር ተዘጋጁ!

ማሳሰቢያ፡ ከደራሲው መጽሐፍ በተወሰዱ ቀጥተኛ ጥቅሶች ውስጥ የሚገኙት የፊደልና ሌሎች ግድፈቶች የደራሲው እንጂ የእኔ አይደሉም፡፡ በኢታሊክስ የፊደል አጣጣል ያስቀመጥኩት እኔ ነኝ፡፡

መጽሐፈ ኢያሱ

ደራሲው መጽሐፈ ኢያሱን በተመለከተ የለዘብተኛ ሊቃውንትን ግምት ያስተጋባል፡፡ ነገር ግን ከግምቱ በስተጀርባ የሚገኘውን እስልምናንም ጭምር ውድቅ የሚያደርገውን ቅድመ ግንዛቤ አልተረዳም፡፡ እንዲህ ብሎ ይጀምራል፡-

“በተለምዶ መጽሐፉ በኢያሱ ልጅ እንደተፃፈ የሚነገር ሲሆን በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ግን ከኢያሱ በኋላ 600 ዓመታትን ቆይቶ እንደተፃፈ ይስማሙበታል፡፡ ኢያሱ የኖረው በ1300 (ከክ.በ) እንደሆነ የሚገመት ቢሆንም መጽሐፉ ከ3-5ኛው ክ/ዘ በተፃፈው የአይሁዶች የባቢሎን ታልሙድ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡” (ገፅ 16-17)

በአይሁድና በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የምናገኘው የተለመደው አመለካከት ጸሐፊው ኢያሱ ነው የሚል መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ደራሲ ግን በተለምዶ መጽሐፉ በኢያሱ ልጅ እንደተጻፈ እንደሚነገር በመግለፅ ፍፁም ተሰምቶ የማይታወቅ የግል ፈጠራውን ጽፏል፡፡ ኢያሱ መጽሐፍ የጻፈ ልጅ ሊኖረው ይቅርና ልጅ መውለዱን እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም፡፡ ልጅ መውለድ ይቅርና ጋብቻ መፈጸሙ እንኳ በግልፅ የተጻፈበት ቦታ የለም፡፡ ደራሲው ርዕሱ ጥንቃቄን የሚሻ መሆኑን በመግለፅ ትችቱን ቢጀምርም ከልክ ያለፈ ግድየለሽነቱን እየታዘብን ነው፡፡

ስለ ባቢሎናውያን ታልሙድ የጠቀሰው ምን ለማለት ፈልጎ እንደሆነ ግልፅ አይደለም፡፡ ኢያሱ በ13ኛው ዓ.ዓ. ኖሮ ከነበረ መጽሐፉ ከ3-5 ዓ.ም. መካከል በተጻፉት የአይሁድ ታልሙድ ውስጥ መካተቱ ችግሩ ምንድነው?

በማስከተል እንዲህ ብሎ ጽፏል፡-

“የፕሮቴስታንት ንቅናቄ መስራች ጆን ካልቪን (1509-1564) እና ቶማስ ሆቤስ (1588-1679) መጽሐፉ ከኢያሱ ህልፈት በኋላ ባልታወቀ ሰው የተፃፈ ስለመሆኑ የደረሱበትን ጥናት አሳውቀዋል፡፡” Albert De Pury, Thomas Romer, Jean-Daniel Macchi, (2000) “Israel Constructs its History”. pp.26-30

“የጀርመን የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪ ማርቲን ኖት (1943) በበኩላቸው መጽሐፈ ኢያሱ በባቢሎን ምርኮ ዘመን (600 ከክ.በ) በአንድ ፀሐፊ የተሰበሰበና እርምት የተደረገበት ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡ መጽሐፈ ኢያሱ በአብዛኛው እውነተኛ ታሪክ ሳይሆን የተለያዩ ዘመናት ክስተቶችን አንድ ላይ በመጠቅለል በኢያሱ የብዕር ስም የተፃፈ ስለመሆኑ የዘመናችን ምሁራን ደርሰውበታል፡፡” Gordon McConville, Stephen Williams, (2000), “Joshua” pp.4 (ገፅ 16-17)

የካልቪንን አቋም በተመለከተ ለአባባሉ በዋቢነት በጠቀሰው ምንጭ ውስጥ የተባለውና እርሱ የገለፀበት መንገድ ከፍተኛ ልዩነት አላቸው፡፡ ካልቪን መጽሐፈ ኢያሱ ከኢያሱ ህልፈት በኋላ ባልታወቀ ሰው እንደተጻፈ አልተናገረም፡፡ ይልቅ የአይሁድ ታልሙድ የመጽሐፉ መዝጊያ በኢያሱ ዘመን በኖረው በአሮን ልጅ በካህኑ አልዓዛር እንደተጻፈ ስለሚናገር ከዚያ በመነሳት የመጽሐፉ ይዘት በመሠረታዊነት በአልዓዛር መዘጋጀቱን እንደሚያምን ተናግሯል፡፡ ደራሲው የጠቀሰው መጽሐፍም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡[1] ምንጭ ጠቅሶ በምንጩ ውስጥ ባልተባለ የግል ፈጠራ አንባቢን ማሳሳት ጸያፍ ድርጊት ነው፡፡ የካልቪን ጽሑፍ በሕትመትም ሆነ ኦንላይን ስለሚገኝ አንብቦ ሃቁን ማወቅ ይቻላል፡፡[2]

ደራሲው በጎርደን ማክቪልና እስቴፈን ዊልያምስ የተጻፈውን መጽሐፍ በወጉ አንብቦት ቢሆን ኖሮ እንደ ሙስሊምነቱ “ማስረጃ” ብሎ ባልጠቀሰው ነበር፡፡ ምሑራኑ መጽሐፈ ኢያሱ በኢያሱ ዘመን እንዳልተጻፈ አጥብቀው የሚሟገቱበት ምክንያት እስራኤላውያን በሒደት ከመድብለ አማልክታዊነት አንዱን አምላክ ወደ ማምለክ የመጡ ከነዓናውያን እንጂ በግብፅ በባርነት የነበሩና ነፃ የወጡ ሕዝቦች አልነበሩም ከሚል ቅድመ ግንዛቤ በመነሳት መሆኑ ደራሲው በጠቀሰው በዚያው ገፅ ላይ ተጽፏል፡፡[3] ይህ ደግሞ እውነት ከሆነ እስራኤላውያን በግብፅ በባርነት እንደኖሩና ነፃ እንደወጡ፣ አሓዳዊነታቸውም ከአብርሃም ዘመን ተያይዞ የመጣ እንደሆነ የሚያረጋግጠው ቁርአን ሐሰት ሊሆን ነው! መጽሐፍ ቅዱስን ውድቅ ለማድረግ ካላቸው ጥድፊያ የተነሳ ቁርአንን ገደል መክተት የሙስሊም ሰባኪያን ሁሉ አባዜ ነው፡፡ (ቁርአን 7፡103-136፣ 28፡30-32፣ 26፡61-68)፡፡

እንዲህ ሲል ትችቱን ይቀጥላል፡-

“ለአብነት ኢያሱ በመጽሐፉ ምዕራፍ 10፡3 እና 11፡1 ላይ የአሶርና የለኪሶን ከተማዎች እንዳቃጠላቸውና በውስጣቸው ያለውን ሁሉ እንዳጠፋ የሚተርክልን ሲሆንነገር ግን የታሪክ አጥኚዎች እነዚህ ከተማዎች የፈረሱት ከኢያሱ በኋላ እንደሆነ ይስማማሉ፡፡” James Maxwell Miller and John Haralson Hayes, (1986) “A History of Ancient Israel and Judah”, pp.71-72 (ገፅ 17)

ደራሲው የጠቀሰውን ምንጭ በትክክል አላነበበም፡፡ ማክስዌልና ሄይስ በኢያሱ እንደተወረሩ መጽሐፍ ቅዱስ የጠቀሳቸው አንዳንድ ከተሞች ወረራ እንደተፈፀመባቸው የሚገልፅ የአርኪዎሎጂ ማስረጃ አለመገኘቱን እየተናገሩ መሆናቸው እውነት ነው፡፡ ዳሩ ግን አሶርና ለኪሶን በተመለከተ የተናገሩት ተቃራኒውን ነው! እናንብበው፡-

The sites where artifactual remains indicate city destructions at the end of the Late Bronze Age, with a few exceptions (Lachish, Hazor), are not the ones that the biblical account associates with the conquest under Joshua.[4]

ትርጉም፡ “በኋለኛው የመዳብ ዘመን ውድመት እንደደረሰባቸው በእደ-ጥበባት ውጤቶች የተጠቆሙት ከተሞች ከጥቂቶች (ለኪሶ፣ አሶር) በስተቀር የመጽሐፍ ቅዱስ ትረካ ከኢያሱ ወረራ ጋር ያገናቸው አይደሉም፡፡”

ኋለኛው የመዳብ ዘመን (Late Bronze Age) የሚባለው ከ1500-1200 ዓ.ዓ. መካከል የሚገኘው ዘመን ሲሆን ሙሴና ኢያሱ የኖሩት በነዚህ ዘመናት መካከል እንደሆነ ይገመታል፡፡ በማክስዌልና ሄይስ መሠረት በአርኪዎሎጂ ከተገኙት የእደ-ጥበባት ውጤቶች መረዳት እንደተቻለው በነዚህ ዘመናት መካከል የወደሙት የከነዓን ከተሞች ኢያሱ እንደወረራቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የተነገሩት አይደሉም፤ ነገር ግን ይህ ጉዳይ አሶርና ለኪሶን አይመለከትም! ምክንያቱም እነዚህ ሁለት ከተሞች በዘመነ ኢያሱ መፈራረሳቸው በአርኪዎሎጂ ተረጋግጧልና! ደራሲያኑ ስለ ሌሎች ከተሞች የተናገሩት ከቅርብ ዘመናት ግኝቶች ጋር የሚስማማ ባይሆንም ስለ ሁለቱ ከተሞች የተናገሩት ግን ትክክል ነው፡፡

አሶርና ለኪሶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጻፈው መሠረት በዘመነ ኢያሱ ውድመት እንደደረሰባቸው የሚያሳዩ የአርኪዎሎጂ ማስረጃዎች እንዳሉ ከሌሎች ምንጮች መረዳት ይቻላል፡፡ በዚያን ዘመን አሶር ሁለት ጊዜ[5]፣ ለኪሶ ደግሞ አንድ ጊዜ[6] በወረራ እንደፈረሱ ከአርኪዎሎጂ ማስረጃዎች ማወቅ ተችሏል፡፡ ደራሲው የእንግሊዘኛ ችግር ኖሮበት ይሁን ወይንም ደግሞ እያወቀ ለማምታታት ምክንያቱ ባይታወቅም ነጭ ውሸት ሲዋሽ እጅ ከፍንጅ ተይዟል፡፡ እንዲህ ካለው ቅሌት ይሰውረን ከማለት ውጪ ሌላ ምን ይባላል?

ደራሲው ይቀጥላል፡-

‹‹ኬብሮን›› የተባለችውን ከተማ ስናይ ደግሞ በኢያ 15፡13 ላይ ኢያሱ ለካሌብ እንዳወረሰውና ከዚያም ተጨማሪ ከተሞችን እንደያዘ ይተርካል፡፡ ነገር ግን ይህ ታሪክ ተመሳሳይ በሆነ ቃል በመሳ 1፡10-20 የተፃፈ ሲሆን በቁጥር 1፡1 ላይ ኢያሱ ከሞተ በኋላ የካሌብ ወንድም ይሁዳ ኬብሮንን ዘምቶባት ከያዛት በኋላ ለካሌብ እንደሰጠው ይነግረናል፡፡

እንዲሁ ካሌብ በኢያሱ ዘመን (ኢያ 15፡15-19) የዳቤርን ከተማ እንደያዛት የተገለፀ ሲሆን ነገርግን ይቺ ከተማ በካሌብ እጅ የገባችው ከኢያሱ ሞት በኋላ መሆኑን በመሳ 1፡11-15 ላይ ተተርኳል፡፡ (ገፅ 17)

ኢያሱ 15፡13-15 ላይ የሚገኘው ታሪክ ካሌብ ኬብሮንንና ዳቤርን እንዴት አድርጎ እንደያዘ የሚናገር ጠቅለል ያለ ዘገባ እንጂ እያንዳንዱ ነገር ኢያሱ በሕይወት እያለ እንደተፈፀመ አይናገርም፡፡ ኢያሱ ኬብሮንን ለካሌብ ርስት እንድትሆን ሰጣት፤ ካሌብም ኬብሮንንና በአቅራብያዋ የምትገኘዋን ዳቤርን ያዘ፡፡ መቼ? በመጽሐፈ ኢያሱ ላይ አልተነገረም፡፡ የዚህን ታሪክ ዝርዝር ዘገባ የምናገኘው መሳፍንት 1፡1-36 ላይ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከኢያሱ ሞት በኋላ እግዚአብሔር በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት በይሁዳ ነገድ ፊታውራሪነት ኬብሮንን ጨምሮ በከነዓን ከተሞች ውስጥ በነበሩት ሕዝቦች ላይ ውጊያ ከተደረገ በኋላ አስቀድሞ በተወሰነው ክፍፍል መሠረት እያንዳንዱ የየድርሻውን ወስዷል፡፡ በኢያሱ ዘመን የተደረገው ውጊያ ዋና ዋና ጠላቶችን የማስወገድ እንጂ የመጨረሻ ፍልሚያ አልነበረም (ኢያ. 13፡1-13)፡፡ በይሁዳ ፊታውራሪነት የተደረገውም ጦርነት ቢሆን ርስቶቹን የማስከፈት እንጂ ጠላትን ሙሉ በሙሉ ያፀዳ ዘመቻ አልነበረም፡፡ ለምሳሌ ያህል ካሌብ ወደ ኬብሮን ከገባ በኋላ ሦስቱን የኤናቅ ልጆች ማስወጣት አስፈልጎታል (መሳ. 1፡20)፡፡ ዳቤርንም ለመያዝ የካሌብ ታናሽ ወንድም ልጅ መፋለም አስፈልጎታል (መሳ. 1፡11-13)፡፡ ስለዚህ የኢያሱና የመሣፍንት ዘገባዎች የተጋጩት በደራሲው ምናብ ውስጥ ብቻ ነው፡፡

ደራሲው ይሁዳን “የካሌብ ወንድም” ማለቱ ስህተት ነው፡፡ ካሌብ ይሁዳ የተባለ ወንድም እንደነበረው አልተጻፈም፡፡ ይልቅ ካሌብ በነገደ ይሁዳ ውስጥ የተቆጠረ የአንድ ቤተሰብ አባት እንጂ የይሁዳ ወንድም አልነበረም (ዘኁ. 13፡6)፡፡ ሰውየው በያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ስህተት ለመሥራት አስቦ፣ ተጨንቆና ተጠቦ የሚሳሳት ነው የሚመስለው፡፡ አይ ጥንቃቄ!

ደራሲው ይቀጥላል፡-

የዳን ከተማ ታሪክንም ስናይ በኢያ 19፡47 ላይ የዳን ልጆች የሚኖሩበት ዳርቻ ስላልበቃቸው ተጨማሪ ቦታ ፍለጋ ከሌሼም ጋር እንደተዋጉና ከተማዋን ሲይዙ በአባታቸው ስም ዳን ብለው እንደጠሯት ይጠቅሳል፡፡ መጽሐፈ መሳፍንት 18፡27-29ደግሞ የዳን ከተማ ከኢያሱ ህልፈት በኋላ እስራኤላውያን ያለ ንጉስ በነበሩበት ዘመን ስለመያዟ ይገልፃል፡፡

‹‹ሔርማ›› የተባለችውን ከተማ ታሪክ ስናይ እስራኤላውያን ከኢያሱ ሞት በኋላ በመሳፍንት ዘመን ‹‹ይሁዳም ከወንድሙ ከስምዖን ጋር ሄደ፥ በጽፋት የተቀመጡትንም ከነዓናውያንን መቱ፥ ፈጽመውም አጠፉአት። የከተማይቱንም ስም ሔርማ ብለው ጠሩአት።›› (መሳ 1፡17) በማለት ሔርማ ስሟን ያገኘችው ከኢያሱ በኋላ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ነገርግን በመጽሐፈ ኢያሱ12፡14፣ 15፡31፣ 19፡4ላይ ‹‹ሔርማ›› በስም ተጠቅሳ እናገኛለን፡፡ ይህም መጽሐፉ ከኢያሱ ህልፈት በኋላ ዘግይቶ የተዘጋጀ ስለመሆኑ ፍንጭ ይሰጠናል፡፡ (ገፅ 17-18)

የዳን ነገድ ሌሼምን እንደ ያዘ የሚያወሳው ታሪክ በኢያሱ ላይ ጠቅለል ባለ ሁኔታ የተቀመጠ ሲሆን በመሣፍንት ውስጥ ግን በዝርዝር ተዘግቧል፡፡ በኢያሱ ላይ የታሪክ ዘመን ስላልተጠቀሰ በሁለቱ ዘገባዎች መካከል የዘመን ግጭት የለም፡፡

የኢያሱን ጸሐፊነት በተመለከተ የአይሁድ ታልሙድ ምስክርነቱን የሚሰጥ ሲሆን የመጨረሻዎቹ ክፍሎች ደግሞ በአሮን ልጅ በአልዓዛር እንደተጻፉ ተነግሯል፡፡[7] በክፍል አንድ ምላሻችን የሙሴን መጻሕፍት በተመለከተ እንዳልነው ሁሉ መጽሐፉን ይገለብጡ የነበሩ ሰዎች ከኋለኞች የታሪክ ዘመናት ጋር በማመሳከር ማብራርያዎችን ማከላቸው መሠረታዊው ጽሑፍ በኢያሱ እንዳልተዘጋጀ አያሳይም፡፡ ይህም በዘመነ ነቢያት የተፈፀመ መሆኑ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የተፈፀመ ሰናይ ተግባር መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ባይሆን ኖሮ ቅዱሳን ነቢያት እንዲሁም ጌታ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ይህንን ተግባር በተቃወሙና ትክክል አለመሆኑን በነገሩን ነበር፡፡

የኢያሱን ጸሐፊነት በተመለከተ መጽሐፉ በተወሰነ ደረጃ ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ ያህል 24፡25-26 ላይ እንዲህ ተብሏል፡-

“በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ በሴኬምም ሥርዓትና ፍርድ አደረገላቸው። ኢያሱም ይህን ቃል ሁሉ በእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ጻፈ ታላቁንም ድንጋይ ወስዶ በእግዚአብሔር መቅደስ አጠገብ ከነበረችው ከአድባሩ ዛፍ በታች አቆመው።”

ደራሲው ትችቱን ይቀጥላል፡-

“ኬጥያውያንን በተመለከተ ኢያሱ በመጽሐፉ መግቢያ (1፡4) እግዚአብሔር በእሱ በኩል እስራኤላውያንን ‹‹ከምድረ በዳው ከዚያም ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ የኬጢያውያን ምድር ሁሉ እስከ ፀሐይ መግቢያ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ዳርቻችሁ ይሆናል።›› በማለት ቃል እንደገባላቸው ተነግሯል፡፡ ይሁን እንጅ ከኢያሱ በኋላ ደቡብ ምዕራብ ሶርያ በቱርካዊው ጦረኛ ሱፒሉሊማስ እስከተያዘችበት ጊዜ ድረስ የኬጥያውያን ንጉስ እንዳልነበረ የታሪክ አጥኚዎች አረጋግጠዋል፡፡ በተጨማሪም በዘዳግም 11፡24 ላይ ‹‹ከምድረበዳ ከሊባኖስም ከታላቁም ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ባህር ድረስ ዳርቻችሁ ሆናል፡፡›› ተብሎ የተገለፀው በዘመኑ ኬጥያውያን ንጉስ እንዳልነበራቸው ማሳያ ተደርጎ ቀርቦበታልም፡፡” (ገፅ 18)

የሙስሊም ሰባኪያን የቅጥፈት ውድድር ቢኖር ኖሮ ይህ ደራሲ ያለጥርጥር ዋንጫውን ይበላ ነበር፡፡ ተመልከቱ! ይህ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት ከሚያረጋግጡ አስደናቂ ግኝቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በ19ው ክ.ዘ. አጋማሽ ላይ የአርኪዎሎጂ ግኝቶች ማረጋገጫ እስኪሰጡ ድረስ ስለ ኬጥያውያን የሚታወቀው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈው ብቻና ብቻ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ ብዙ የታሪክ ሊቃውንት መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት መሆኑንና ኬጥያውያን የተሰኙ ሕዝቦች በምድር ላይ እንዳልነበሩ፣ አሉ ከተባሉም ከይሁዳ መንግሥት ጋር ሊነፃፀር የሚችል ኃይል ያልነበራቸው ደካማ ሕዝቦች እንደነበሩ ያምኑ ነበር፡፡ ነገር ግን በተከታታይ የተገኙት የአርኪዎሎጂ ማስረጃዎች እንዳረጋገጡት ኬጢያውያን ከግብፅና ከአሦር መንግሥታት ጋር ሊነፃፀር የሚችል ግዛተ መንግሥት መሥርተው ይኖሩ የነበሩ ኃያል ሕዝቦች እንደነበሩ ተረጋገጠ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ነቃፊዎችም እጃቸውን በአፋቸው ላይ ጫኑ! እነዚህን አስደናቂ ግኝቶች በተመለከተ ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ አርችባልድ ሴይስ ከግኝቶቹ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በመጽሐፉ ውስጥ በዝርዝር ጽፏል፡፡[8]

ደራሲው የጠቀሰው ሱፒሉሊዩማስ ወይንም ሹፒሉሊዩማሽ የተሰኘው ንጉሥ የመጀመርያው የኬጢያውያን ንጉሥ አልነበረም፡፡ የኬጢያውያን ግዛተ መንግሥት ከአብርሃም ዘመን እንኳ የሚቀድም ሲሆን ብዙ ነገሥታት ተፈራርቀዋል፡፡ የነገሥታቱን ዝርዝር ማየት የሚፈልግ ሰው ከታች በተሰጠው የፒኪፒድያ ገፅ ላይ በመግባት ማየት ይችላል፡፡[9] ስለዚህ እስከ ሱፒሉሊዩማስ ድረስ ኬጥያውያን ንጉሥ አልነበራቸውም የሚለው አባባል ዐይን ያወጣ ቅጥፈት ነው! ሱፒሉሊዩማስ የነገሠበት ዘመን በራሱ ከኢያሱ ዘመን ጋር ስለሚገጣጠም ሙግቱ ገለባ ነው፡፡[10]

ግብረ ገባዊ ተቃውሞ

ደራሲው በመጽሐፈ ኢያሱ ታሪካዊነት ላይ ብቻ ሳይሆን በግብረ ገባዊነቱም ላይ ጥያቄን ያነሳል፡፡ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በማድላት ከእስራኤል ዘር ውጪ ያለው በሙሉ እንዲጠፋ ያዘዘ በማስመሰል ትችቱን ይሰነዝራል፡፡ ጠላቶቻችንን ስለመውደድ ከሚናገረው የአዲስ ኪዳን ግብረ ገብነት ጋር እንደሚጋጭም ይናገራል፡፡ (ገፅ 18-19)፡፡ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ከነዓናውያን እንዲጠፉ ያዘዘው ለእስራኤል ስላደላ ሳይሆን ክፋታቸው እጅግ በመብዛቱ ምክንያት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ የከነዓናውያን የፍርድ ፅዋ እስኪሞላ ድረስ እስራኤላውያን በግብፅ ባርነት ለአራት ክፍለ ዘመናት ተሠቃይተዋል፡-

“አብራምንም አለው፦ ዘርህ ለእርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኞች እንዲሆኑ በእርግጥ እወቅ፤ ባሪያዎች አድርገውም አራት መቶ ዓመት ያስጨንቋቸዋል። ደግሞም በባርነት በሚገዙአቸው ሕዝብ ላይ እኔ እፈርዳለሁ፤ ከዚያም በኋላ በብዙ ከብት ይወጣሉ። አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ በመልካም ሽምግልና ትቀበራለህ። በአራተኛው ትውልድ ግን ወደዚህ ይመለሳሉ፤ የአሞራውያን ኃጢአት ገና አልተፈጸመምና።” (ዘፍ. 15፡13-16)

ከነዓናውያን ህፃናትን ለጣዖት መሠዋትንና ከቤተሰብ አባላት ጋር አልፎም ከእንስሳት ጋር ወሲብ መፈፀምን የመሳሰሉ ብዙ ፀያፍ ተግባራትን ይፈፅሙ እንደነበር የአርኪዎሎጂ ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እንዲህ ያለውን ተግባር በመፈፀም ምድሪቱን ስላረከሱና እግዚአብሔርን ስላስቆጡ ከምድሪቱ ይወገዱ ዘንድ የእግዚአብሔር ፍርድ ተላለፈባቸው፡፡ እግዚአብሔር በኖኅና በሎጥ ዘመናት ተመሳሳይ ፍርድ በኃጢአተኞች ላይ አስተላልፏል፡፡ ልዩነቱ በኖኅና በሎጥ ዘመናት እግዚአብሔር ተፈጥሮን መጠቀሙና በኢያሱ ዘመን ደግሞ እስራኤላውያንን መጠቀሙ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለእስራኤላውያን ማስጠንቀቂያም ጭምር ሲሆን ተመሳሳይ ተግባር ከፈፀሙ ተመሳሳይ ዕጣ እንደሚገጥማቸው እግዚአብሔር አስቀድሞ አስጠንቅቋቸዋል (ዘሌ. 26፡14-46፣ ዘዳ. 28፡15-68)፡፡ ከነዓናውያንም ከምድሪቱ ላይ የተወገዱት በኃጢአታቸው ምክንያት እንጂ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ስላደላ አለመሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይናገራል፡-

“አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ ካወጣቸው በኋላ፦ ስለ ጽድቄ እወርሳት ዘንድ ወደዚች ምድር እግዚአብሔር አገባኝ ስትል በልብህ አትናገር፤ እነዚህን አሕዛብ ስለ ኃጢአታቸው እግዚአብሔር ከፊትህ ያወጣቸዋል። ምድራቸውን ትወርሳት ዘንድ የምትገባው ስለ ጽድቅህና ስለ ልብህ ቅንነት አይደለም፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ በሚያጠፋቸው በእነዚያ አሕዛብ ኃጢአት ምክንያትና ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውን ቃል ይፈጽም ዘንድ ነው።” (ዘዳ. 9፡4-5)

እስራኤላውያንም ተመሳሳይ ኃጢአት ውስጥ በገቡ ጊዜ ጌታ እግዚአብሔር በዙርያው የነበሩ መንግሥታትን በመጠቀም ከምድሪቱ ላይ እንዳስወገዳቸው ቅዱስ ቃሉ ይናገራል፡፡ (2ነገ. 17፣ 25)፡፡

ይህ የእግዚአብሔር ፍርድ ከአዲስ ኪዳን የግብረ ገብነት መመርያ ጋር መምታታት የለበት፡፡ የከነዓናውያን መጥፋት እግዚአብሔር በኃጢአተኞች ላይ የፈረደው ፍርድ ነው፡፡ ጠላቶቻችንን ስለመውደድ በአዲስ ኪዳን የተነገረው ደግሞ ለክርስቲያኖች የተሰጠ የሕይወት መመርያ ነው፡፡

ንቁ! ሙስሊም ሰባኪያን ሐሰተኞች ናቸው፡፡

ይቀጥላል…


[1] Albert de Pury, Thomas Römer, Jean-Daniel Macchi. Israel Constructs its History: Deuteronomistic Historiography in Recent Research; Journal for the Study of the Old Testament Supplement Series 306, Sheffield Academic Press, 200, p. 29

[2] http://www.documenta-catholica.eu/d_1509-1564-%20Calvin,%20John%20-%20Commentary%20on%20Joshua%20-%20EN.pdf

[3] Gordon McConville and Stephen Williams. Joshua: The Two Horizons New Testament Commentary;  Eerdmans Publishing Company, 2010, p. 4

[4] J. Maxwell Miller and John H. Hayes. A History of Ancient Israel and Judah; Westminster Press; 1st edition, 1986, p. 71

[5] David M. Howard, Jr. and Michael A. Grisanti. Giving the Sense: Understanding and Using Old Testament Historical Texts; Grand Rapids: Kregal, 2003, pp. 256-82

[6] Adrian Curtis. Oxford Bible Atlas; 4th Edition, Oxford University Press 2007, p. 118.

[7] አዲሱ መደበኛ ትርጉም፣ የመጽሐፈ ኢያሱ መግቢያ፣ ገፅ 289 ይመልከቱ፡፡፡

[8] Archibald Henry. The Hittites: the story of a fnetotten Empire; 1890. ሙሉ መጽሐፉ ኦንላይን ይገኛል https://archive.net/details/hittitesstoryoff00saycuoft

[9] https://en.wikipedia.net/wiki/List_of_Hittite_kings

[10] Encyclopedia Britannica: https://www.britannica.com/biography/Suppiluliumas-I


ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነው! እስልምናስ?

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ