ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነው! እስልምናስ? የመጽሐፍ ሒስና ግምገማ – ክፍል 4

ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነው!

እስልምናስ?

የመጽሐፍ ሒስና ግምገማ – ክፍል 4

ርዕስ – ንቁ! ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነውን?

ደራሲ – ሰልማን ኮከብ

የታተመበት ዘመን – 2010

አሳታሚ – አልተገለፀም

የገፅ ብዛት – 270

ባለፉት ጽሑፎቻችን ለሰልማን መጽሐፍ እስከ ገፅ 21 ድረስ ምላሽ መስጠታችን ይታወሳል፡፡ ካቆምንበት እንቀጥላለን፡፡

ጸሐፊው እስከ ገፅ 44 ድረስ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን በተመለከተ የጻፈ ሲሆን አብዛኞቹ መረጃዎቹ ቀለል ባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛዎች ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ለጀማሪዎች እንጂ ጥልቅ ዕውቀት ለሚፈልጉ ሰዎች የሚመጥኑ አይደሉም፡፡ አጠቃላይ ድምዳሜውም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጸሐፊያን ማንነት አይታወቅም የሚል ሲሆን አሉታዊ መረጃዎቹን በጥናት ላይ የተመሠረተ ለማስመሰል የተወሰኑ ምንጮችን ለመጥቀስ ሞክሯል፡፡

የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጸሐፊያንን ማንነት በተመለከተ የአይሁድ ትውፊትና ጥንታውያን ጽሑፎች በዝርዝር የሚነግሩን ሲሆን ዘመንኛ ለዘብተኛ ሊቃውንት ግን ብዙዎቹን እንደማይቀበሉ የታወቀ ነው፡፡ የእያንዳንዱን መጽሐፍ ጸሐፊ ማንነት በተመለከተ ከነዚህ ጥንታውያን መረጃዎች ጋር በመስማማት ጥሩ ሙግት ማቅረብ ቢቻልም እንደ ክርስቲያኖች የዕውቀት ፍላጎታችንን ከመሙላት በዘለለ አሳሳቢ ጉዳይ ባለመሆኑ ብሉይ ኪዳን ቃለ እግዚአብሔር መሆኑን ለማረጋገጥ እንደዚያ ያለ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባት አያስፈልገንም፡፡ ቀደም ባሉት ክፍሎች እንደገለፅነው ጌታችን ኢየሱስና ሐዋርያቱ ጠቅላላው ብሉይ ኪዳን ቃለ እግዚአብሔር መሆኑን ስላስተማሩ እነርሱ የሰጡን ማረጋገጫ ብሉይ ኪዳንን እንደ ቃለ እግዚአብሔር ለመቀበል ከበቂ በላይ ነው፡፡ ሙስሊሞችም ቢሆኑ የገዛ ቁርአናቸውና ሐዲሶቻቸው ሙሐመድ ብሉይ ኪዳን መለኮታዊ ቃል መሆኑን እንዳስተማረ ስለሚመሰክሩ በነቢያቸው ሥልጣንና እውነተኛነት የሚያምኑ ከሆነ እንደ ክርስቲያኖች ሁሉ ጉዳዩ ሊያሳስባቸው ባልተገባ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ሙሐመድ ለመጽሐፍ ቅዱስ ሃቀኝነት ምስክርነቱን ከሰጠ በኋላ መልሶ ደግሞ ተጻራሪ ትምሕርቶችን ስላስተማረ ሙስሊም ወገኖች የመጽሐፍ ቅዱስን ሃቀኝነት በመቀበልና የሙሐመድን ተጻራሪ ትምሕርቶች በመቀበል መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን መቀበል ተጻራሪ የሙሐመድ ትምሕርቶችን መካድ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን አለመቀበል ደግሞ ሙሐመድ የሰጠውን ምስክርነት መካድ ነው (ሱራ 2፡40-41፣ 2፡89፣ 2፡91፣ 2፡101፣ 10፡94፣ 7፡169፣ 2፡44፣ 2፡113፣ 2፡121፣ 3፡93፣ 3፡113፣ 5፡66፣ 5፡68፣ 5፡43-44፣ 5፡65፣ 2፡4)፡፡ በዚህ አጣብቂኝ መካከል ሙስሊም ሆኖ መገኘት በእጅጉ ከባድ ነው፡፡

ለተጨማሪ መረጃ ተከታዮቹን ጽሑፎች ያንብቡ፡-

—–

ይህ ጸሐፊ የዜና መዋዕል መጻሕፍት ከሌሎች የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጋር ይጋጫሉ የሚል ትችት ሰንዝሯል (ገፅ 26-28)፡፡ ነገር ግን የእርሱ የመረዳት አቅም እንጂ በጠቀሳቸው ክፍሎች ውስጥ ምንም ዓይነት ግጭት የለም፡፡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች እንመልከት፡-

ሳኦልም እግዚአብሔርን ጠየቀ [በእብራይስጥ ሸዓል]፤ እግዚአብሔርም በሕልም ወይም በኡሪም ወይም በነቢያት አልመለሰለትም። (1ሳሙ. 28፡6)

ይህ ጥቅስ ከተከታዩ ጋር ይጋጫል ይለናል፡-

እንዲሁ ሳኦል በእግዚአብሔር ላይ ስላደረገው ኃጢአት፥ የእግዚአብሔርንም ቃል ስላልጠበቀ ሞተ። ደግሞም መናፍስት ጠሪ ስለ ጠየቀ [በእብራይስጥ ሸዓል] እግዚአብሔርንም ስላልጠየቀ [በእብራይስጥ ደራሽ]፥ ስለዚህ ገደለው፥ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት አሳለፈው። (1ዜና 10፡13-14)

የመጀመርያው ጥቅስ ሳኦል እግዚብሔርን እንደጠየቀና እንዳልመለሰለት ይናገራል፤ ሁለተኛው ጥቅስ ግን እንዳልጠየቀ ይናገራል ስለዚህ ግጭት ነው ይለናል፡፡ ወደ ዋናው የእብራይስጥ ጽሑፍ ኼደን ስንመለከት በመጀመርያው ጥቅስ ውስጥ “መጠየቅ” ለሚለው “ሸዓል” የሚል ቃል የገባ ሲሆን “መጠየቅ፣ ማማከር፣ መለመን” ወዘተ. የሚሉ ተቀዳሚ ትርጉሞች አሉት፡፡ እንዲሁም በሁለተኛው ጥቅስ ውስጥ ቁጥር 13 ላይ መናፍስት ጠሪ ስለ ጠየቀ” ለሚለው “ሸዓል” የሚል ተመሳሳይ ቃል ገብቷል፡፡ ነገር ግን ቁጥር 14 ላይ እግዚአብሔርንም ስላልጠየቀ” ለሚለው “ደራሽ”  የሚል ቃል ነው የገባው፡፡ ተቀዳሚ ትርጉሙም “መከተል፣ መፈለግ፣ ማምለክ” የሚል ነው፡፡ አንድ ሰው እግዚአብሔርን መጠየቅ ቢችልም እግዚአብሔር አምላክ ሰው ስለጠየቀ ብቻ ሳይሆን እንደ ፈቃዱ ስለሚመልስ “እግዚአብሔር አልመለሰልኝም” ብሎ በማኩረፍ ወደ ጠንቋይ መሄድ የለበትም፡፡ ስለዚህ የመጀመርያው ጥቅስ ሳኦል እግዚአብሔርን እንደጠየቀና መልስ እንዳላገኘ ይነግረናል፡፡ ሁለተኛው ጥቅስ ደግሞ ሳኦል እግዚአብሔርን መከተልና ማምለክ ማቆሙን ይነግረናል፡፡ በሁለቱ መካከል ግጭት የለም፡፡

ንጉሥ ዳዊት የገደለውን ሠራዊት ብዛት በተመለከተ ግጭት አለ ይለናል፡-

ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት መቶ ሰረገለኞች አርባ ሺህም ፈረሰኞች ገደለ፤ የሠራዊቱንም አለቃ ሶባክን መታ፥ እርሱም በዚያ ሞተ። (2ሳሙ. 10፡18)

ይህ ጥቅስ ከተከታዩ ጋር ይጋጫል ይለናል፡-

ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት ሺህ ሰረገለኞች፥ አርባ ሺህም እግረኞች ገደለ፥ የሠራዊቱንም አለቃ ሾፋክን ገደለ። (1ዜና 19፡18)

ይህንን ልዩነት አንዳንድ ሊቃውን የእጅ ጽሑፉን የገለበጡ ሰዎች የግልበጣ ስህተት እንደሆነ ቢናገሩም ይህንን የማይቀበሉና የአረዳድ ችግር ብቻ እንደሆነ የሚናገሩ ሌሎች ደግሞ አሉ፡፡ በዚህም መሠረት 2ሳሙ. 10፡18 ላይ የተዘገበው የሰረገሎች ብዛት ሲሆን 1ዜና 19፡18 ላይ የተዘገበው የሰረገለኞች ብዛት ነው፡፡ የኪንግ ጀምስ ትርጉም የመጀመርያውን “and David slew the men of seven hundred chariots” (ዳዊት የሰባት መቶ ሰረገላዎችን ሰዎች ገደለ) በማለት ያስቀመጠ ሲሆን ሁለተኛውን ጥቅስ “David slew of the Syrians seven thousand men which fought in chariots” (ዳዊትም ከሶርያውያን በሰረገሎች የሚዋጉ ሰባት ሺህ ሰዎችን ገደለ) በማለት ያስቀምጣል፡፡ በዚህ መሠረት 2ሳሙ. 10፡18 በሰባት መቶ ሰረገሎች ላይ ስለተቀመጡ ተዋጊዎች የሚናገር ሲሆን 1ዜና 19፡18 ደግሞ የተዋጊዎቹ ብዛት ሰባት ሺህ መሆኑን ይነግረናል፤ ስለዚህ ግጭት የለም፡፡

እግረኞቹንና ፈረሰኞቹን በተመለከተ እነዚህ እንደ እግረኛም እንደ ፈረሰኛም የመዋጋት ስልጠናና ድርሻ ስለነበራቸው አንዱ ጸሐፊ እግረኞች ሲላቸው ሌላው ደግሞ ፈረሰኞች ብሏቸዋል፡፡ ውጊያው ለተወሰኑ ቀናት የተደረገ በመሆኑ እነዚህ ወታደሮች አመቺ ሲሆን በፈረስ አመቺ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ በእግር ቢዋጉና እግረኛ ወይንም ፈረሰኛ ተብለው ቢጠሩ ምንም ችግር የለውም፡፡ ይህ የዘጋቢዎቹ ምርጫ ነው የሚሆነው፡፡

ለማንኛውም የግልበጣ ስህተት ነው ቢባል እንኳ ሙስሊም ወገኖች እንዲህ ያሉ ከዋና አስተምሕሮዎች ጋር ያልተያያዙ ጥቃቅን ጉዳዮችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እያወጡ ከሚተቹ ቁርአናቸውን ቢመረምሩና ቢያርሙ ያዋጣቸዋል ባይ ነን፡፡ ሊቃውንቶቻቸው ለመደበቅ ቢሞክሩም በቁርአን የእጅ ጽሑፎች ውስጥ በቅርቡ የተገኙት ከ 4000 በላይ ሆን ተብለው የተደረጉት ለውጦች (intentional changes) ለዓለም ሕዝብ ይፋ ሆነዋልና፡፡ ይህንን አስመልክቶ ዶ/ር ዳንኤል አለን ብሩቤከር የተሰኙ የቁርአን ጽሑፎች ሊቅ Corrections in Early Quran Manuscripts: Twenty Examples በሚል ርዕስ የጻፉትን መጽሐፍ ማንበብ በቂ ነው፡፡ እኚህ ሊቅ በጥናት ካገኟቸው 4000 ልዩነቶች መካከል ሃያዎቹን በናሙናነት በመጽሐፍ ያሳተሙ ሲሆን ሌሎቹንም በተከታታይ ለንባብ እንደሚያበቁ ይጠበቃል፡፡

ደራሲው በንጉሥ አሳ ዘመን የነበረውን የሰላም ሁኔታ በተመለከተ ግጭት መኖሩን ይነግረናል፡-

በአሳና በእስራኤል ንጉሥ በባኦስ መካከል በዘመናቸው ሁሉ ሰልፍ ነበረ። (1ነገ. 15፡16)

ይህ ጥቅስ ከተከታዩ ጋር ይጋጫል ይለናል፡-

አብያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም አሳ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። በእርሱም ዘመን ምድሪቱ አሥር ዓመት ያህል ዐረፈች። (2ዜና 14፡1)

በሁለቱ ጥቅሶች መካከል ይገኛል ያለውን ግጭት በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል፡- “መጽሐፈ ነገስት እንደሚነግረን ደግሞ በይሁዳ ንጉስ አሳና በእስራኤል ንጉስ ባኦስ መካከል ጦርነት የነበረ ሲሆን መጽሐፈ ዜና ግን ንጉስ አሳ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ምንም ጦርነት አልነበረም ይላል፡፡” (ገፅ 27)

ለመሆኑ በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ “አሳ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ምንም ጦርነት አልነበረም” የተባለው የቱ ጋር ነው? አሳ ሥልጣን ላይ የቆየው ለ 41 ዓመታት ያህል የነበረ ሲሆን (2ዜና 16፡13) ጸሐፊው በጠቀሰው 2ዜና 14፡1 ላይ ምድሪቱ አሥር ዓመት ያህል እንዳረፈች እንጂ አርባ አንዱንም ዓመታት ምንም ዓይነት ጦርነት እንዳልነበረ አልተጻፈም፡፡ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት እንደሚናገሩት “በዘመናቸው ሁሉ ሰልፍ ነበረ”  መባሉ ለሁለት በመከፈላቸው ምክንያት በመካከላቸው የተፈጠረውን የጠላትነት ስሜት ለማመልከት እንጂ የጦር ሜዳ ፍልምያ መኖሩን ለማመልከት አይደለም፡፡ (አ.መ.ት. ገፅ 507 ይመልከቱ)፡፡

በመጨረሻም ኢዮሳፍጥና አምልኮተ ጣዖትን በተመለከተ ግጭት መኖሩን ይነግረናል፡-

“በአባቱም በአሳ መንገድ ሁሉ ሄደ፥ ከእርሱም ፈቀቅ አላለም፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቅን አደረገ፤ ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉትን መስገጃዎች አላራቀም፤ ሕዝቡ ገና በኮረብቶቹ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር።” (1ነገ. 22፡43)

ይጋጫል የሚለን ከተከታዩ ጥቅስ ጋር ነው፡-

“ልቡም በእግዚአብሔር መንገድ ከፍ ከፍ አለ፤ የኮረብታውን መስገጃዎችና የማምለኪያ ዐፀዱንም ከይሁዳ አስወገደ።” (2ዜና 17፡5)

የመጀመርያው ጥቅስ የኢዮሳፍጥን ታሪክ ጠቅለል ባለ ሁኔታ የሚያስቀምጥ ሲሆን ሁለተኛው ጥቅስ ደግሞ የኢዮሳፍጥን ጅማሬ የሚያመለክት ነው፡፡ ኢዮሳፍጥ በንግሥናው መጀመርያ ላይ አምልኮተ ጣዖትን ከይሁዳ ምድር ማስወገድ ችሎ ነበር፡፡ ወደ ንግሥናው ፍጻሜ አካባቢ ጣዖት አምላኪ ከነበረው አካዝ ከተሰኘው የእስራኤል ንጉሥ ጋር ወዳጅነት ስለመሠረተ የመጀመርያው አቋሙ መላላቱ አልቀረም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡-

“ከዚህም በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሥራው እጅግ ክፉ ከሆነ ከእስራኤል ንጉሥ ከአካዝያስ ጋር ተባበረ። ወደ ተርሴስም የሚሄዱትን መርከቦች ያሠሩ ዘንድ አንድ ሆኑ መርከቦቹንም በዔጽዮንጋብር አሠሩ። የመሪሳም ሰው የዶዳያ ልጅ አልዓዛር፦ ከአካዝያስ ጋር ተባብረሃልና እግዚአብሔር ሥራህን አፍርሶታል ብሎ በኢዮሣፍጥ ላይ ትንቢት ተናገረ። መርከቦቹም ተሰበሩ፥ ወደ ተርሴስም ይሄዱ ዘንድ አልቻሉም።” (1ዜና 20፡35-37)

ከጥቅሱ እንደምንረዳው የኢዮሳፍጥ ፍጻሜ እንደ ጅማሬው አልሆነም፡፡ በሕይወቱ መጨረሻ ላይ ከክፉ ንጉሥ ጋር ስለተወዳጀ አቋሙ መላላቱ ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ ቀደም ሲል ያጠፋው አምልኮተ ጣዖት መልሶ ማንሰራራቱ አያስገርምም፡፡

ጸሐፊው ከላይ የሚገኙትን “ግጭቶች” ከጠቀሰ በኋላ “መጽሐፉ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እውነታ ላይ ትልቅ ጥያቄ ከሚያስነሱት ትረካዎች መካከል አንዱ ሊሆን ችሏል” በማለት ይደመድማል (ገፅ 28)፡፡ መቼስ እነዚህን “ግጭቶች” መርጦ ያቀረበው ከሌሎቹ የተሻሉ ጠንካራ ሙግቶች እንደሆኑ ስላሰበ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ከላይ እንዳየነው በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ በመሆናቸው ከእንዲህ ያሉ ችግሮች በመነሳት የአንድን መጽሐፍ ተዓማኒነት የሚጠራጠር አእምሮ ያለው ሰው ሊኖር አይችልም፡፡

—–

ገፅ 30 ላይ ስንሄድ ጸሐፊው በመጽሐፈ አስቴር ውስጥ የተዛቡ ታሪኮች አሉ ይለናል፤ ለአብነትም ተከታዩን ጥቅስ ይጠቅሳል፡-

“አንድ አይሁዳዊ የቂስ ልጅ የሰሜኢ ልጅ የኢያዕር ልጅ መርዶክዮስ የሚባል ብንያማዊ በሱሳ ግንብ ነበረ። እርሱም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረካቸው ከይሁዳ ንጉሥ ከኢኮንያን ጋር ከተማረኩት ምርኮኞች ጋር ከኢየሩሳሌም የተማረከ ነበረ።” (አስ. 2፡5-6)

ሙግቱ መርዶክዮስ በናቡከደነፆር ዘመን ከተማረከ እስከ አርጤክስስ ዘመን በሕይወት ሊኖር አይችልም የሚል ነው፡፡ የመጀመርያው መታወቅ ያለበት እውነታ መርዶክዮስ የተባለ የንጉሥ ባለሟል መጽሐፍ ቅዱሳችን በተናገረው ዘመን በፋርስ ምድር በሱሳ ቤተመንግሥት ይኖር እንደነበር በአርኪዎሎጂ መረጋገጡ ነው (አ.መ.ት. ገፅ 721 ይመልከቱ)፡፡ ስለዚህ የመርዶክዮስን ማንነትና በተባለው ዘመን በተባለው ቦታ መኖሩን በተመለከተ ጥያቄ ባለመኖሩ ከዚህ ጥቅስ በመነሳት ልናነሳ የምንችለው ጥያቄ የመርዶክዮስን ዕድሜ በተመለከተ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ መርዶክዮስ በናቡከደነፆር ዘመን ከተማረከና እስከ አርጤክስስ ዘመን ከኖረ ዕድሜው ከመቶ ዓመት በላይ ስለሚሆን ወላጆቹ ተማርከው በምርኮ ምድር የተወለደ ሰው መሆኑን ብንገምት ይበልጥ ትክክል እንሆናለን፡፡ አንዳንድ የእንግሊዘኛ ትርጉሞችን ስንመለከት የተማረከው የመርዶክዮስ አባት ቂስ መሆኑን በሚያመለክት መንገድ ተርጉመውታል፡፡ ለናሙናነት ሁለቱን እንጠቅሳለን፡-

GOD’S WORD Translation

Kish had been taken captive from Jerusalem together with the others who had gone into exile along with Judah’s King Jehoiakin, whom King Nebuchadnezzar of Babylon had carried away.

New Living Translation

His family had been among those who, with King Jehoiachin of Judah, had been exiled from Jerusalem to Babylon by King Nebuchadnezzar.

ብዙዎቹ የእንግሊዘኛ ትርጉሞች ደግሞ የተማረከው መርዶክዮስ ይሁን ቂስ ግልፅ ባልሆነ መንገድ ተርጉመውታል፡፡ ይህም የእብራይስጡ ንባብ አሻሚ መሆኑን ያሳያል፡፡ ስለዚህ እብራይስጡን በሁለቱም መንገዶች መተርጎም ይቻላል፡፡ ሆኖም የአማርኛውን ትርጉም እንዳለ ብንቀበል በምርኮ ወይንም በስደት ምድር የተወለዱትን ሰዎች በዚህ መንገድ መግለፅ የተለመደ በመሆኑ ምንም ችግር አይፈጥርም፡፡ ለምሳሌ ያህል በኢትዮጵያ ውስጥ ከሱዳን ስደተኞች የተወለዱትን ወገኖች “በደርግ ዘመን ከሱዳን ተሰድደው የመጡ ስደተኞች” ብንል በኢትዮጵያ ውስጥ መወለዳቸውን እየካድን አይደለም፡፡ ከሱዳን ጋር ያላቸውን ቁርኝት እየገለፅን ብቻ ነው፡፡ ሌላው በዚያን ዘመን የነበሩ ሰዎች ረጃጅም ዕድሜ ይኖሩ እንደነበር ስለሚታወቅ መርዶክዮስ ያንን ያህል ዕድሜ መኖሩ ፈፅሞ የማይታሰብ ተደርጎ ሊወሰድም አይገባውም፡፡ እንኳንስ በዚያን ዘመን ይቅርና በዚህ ዘመን እንኳ ሰዎች በጥሩ ጤንነት ከመቶ ዓመት በላይ ሲኖሩ እያየንም አይደል? ያም ሆነ ይህ እንዲህ አሻሚ ከሆኑ ሐሳቦች በመነሳት አንድን ታሪክ በስህተትነት መፈረጅ ፅንፍ የረገጠ ሒስ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

በማስከተልም ጸሐፊው በመጽሐፉ ግብረ ገብነት ላይ ጥያቄን ያነሳል፡፡ እንዲህ ይላል፡-

“አጨራረሱ ላይ አይሁዳውያን ግድያ እንዲፈፀምባቸው ካደሙባቸው ሰዎች ባለፈ ህፃናትንና ሴቶችን ጨምሮ ከ73 ሺ ህዝብ በላይ በበቀል እንደገደሉ ይተርካል…” (ገፅ 31)፡፡

ይህንን ብሎ ዘዳግም 24፡16 ላይ “አባቶች ስለ ልጆች አይገደሉ፥ ልጆችም ስለ አባቶች አይገደሉ…” ከሚለው ጥቅስ ጋር እንደሚጻረር ይነግረናል፡፡ ማስረጃ ይሆነኛል በማለትም ተከታዮቹን ጥቅሶች ከመጽሐፉ ይጠቅሳል፡-

በዚያም ደብዳቤ በከተሞቹ ሁሉ የሚኖሩት አይሁድ እንዲሰበሰቡ፥ ለሕይወታቸውም እንዲቆሙ፥ በጥል የሚነሡባቸውን የሕዝቡንና የአገሩን ሠራዊት ሁሉ ከሕፃናቶቻቸውና ከሴቶቻቸው ጋር እንዲያጠፉና እንዲገድሉ እንዲደመስሱም፥ ምርኮአቸውንም እንዲዘርፉ ንጉሡ ፈቀደላቸው። (አስ. 8፡11)

የቀሩትም በንጉሡ አገር ያሉ አይሁድ ተሰብስበው ለሕይወታቸው ቆሙ፥ ከጠላቶቻቸውም ዐረፉ፤ ከሚጠሉአቸውም ሰባ አምስት ሺህ ገደሉ፤ ነገር ግን ወደ ብዝበዛው እጃቸውን አልዘረጉም። (አስ. 9፡16)

የመጀመርያው ጥቅስ ንጉሥ አርጤክስስ አይሁድ ከጠላቶቻቸው ራሳቸውን እንዲከላከሉ እንደፈቀደላቸው የሚገልፅ ነው፡፡ በዚህ ቦታ የተገለጸው የንጉሡ ፈቃድ እንጂ የአይሁድ ተግባር አይደለም፡፡ በሁለተኛው ጥቅስ መሠረት አይሁድ ተሰብስበው ራሳቸውን ስለመከላከላቸውና ጠላቶቻቸውን ስለ መግደላቸው እንጂ ሴቶችና ህፃናትን ስለ መግደላቸው ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡ ንጉሡ የፈቀደላቸውን ምርኮ እንኳ አልወሰዱም፡፡ ስለዚህ ጸሐፊው “አይሁዳውያን … ህፃናትንና ሴቶችን ጨምሮ ከ73 ሺ ህዝብ በላይ በበቀል እንደገደሉ ይተርካል…” በማለት የጻፈው የንጉሡን ፈቃድና የአይሁድን ተግባር በማምታታት የፈጠረው ታሪክ እንጂ እንደዚያ የሚል ነገር የለም፡፡

ጸሐፊው ዝም ብሎ ከገዛ ምናቡ እየፈለሰፈ የሚጽፍ እንጂ መጽሐፉን አንብቦ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ መጽሐፈ አስቴርን ያነበበ ሰው አይሁድ ራስን በመከላከል ጦርነት ውስጥ እንደነበሩና በማጥቃት ጦርነት ውስጥ እንዳልነበሩ በቀላሉ ይገነዘባል፡፡ ሐማ አይሁድ እንዲገደሉ ያወጣው ትዕዛዝ በንጉሡ ማሕተም የተደገፈ ስለነበርና የንጉሡ ማሕተም የታተመበት ትዕዛዝ ደግሞ ሊሻር ስለማይችል የነበረው ብቸኛ አማራጭ አይሁድ ራሳቸውን እንዲከላከሉ ሌላ ትዕዛዝ ማውጣት ነበር (አስ. 8፡8-17)፡፡ በዚህም መሠረት አይሁድ ራሳቸውን ለመከላከል ወደ አንድ ቦታ ተከማችተው ሊያጠቋቸው የመጡትን ሰዎች ገደሉ እንጂ የማጥቃት ጦርነት ላይ አልነበሩም፡፡ በዚህ ሁኔታ በሴቶችና በህፃናት ላይ ጭፍጨፋ ሊፈፀም መቻሉ የማይመስል ነው፡፡ ስለዚህ ጸሐፊው የገዛ ፈጠራውን እያስነበበን ነው፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ ፅንፍ የረገጠ ትችት የሚሰነዝረው ይህ ሙስሊም ጸሐፊ ቁርአን በአስቴር ዘመን የኖረውን ሐማን በዘጸአቱ ፈርዖን ዘመን የኖረ በማስመሰል መናገሩን ሲያውቅ ምን ይል ይሆን (ሱራ 28:6፣ 8፣ 38፣ 29:39፣ 40:24፣ 36)? እንዲህ ያለ የታሪክ ግድፈት የሸከፈ መጽሐፍ ታቅፎ የሌላውን መተቸት ለትዝብት ይዳርጋል፡፡

—–

መጽሐፈ ኢዮብን በተመለከተ ስለ ተጻፈበት ዘመን በሊቃውንት መካከል የሚገኘውን አለመግባባት የገለጸ ሲሆን “ኢዮብ በመቼ ዘመን እንደኖረና ዖፅ የተባለው አገሩም የት አካባቢ እንደሆነ አይታወቅም” በማለት የተሳሳተ መረጃ ያስተላልፋል (ገፅ 31)፡፡ ኢዮብ በሁለተኛው ሺህ ቅ.ክ. መጨረሻ አካባቢ እንደኖረ በሊቃውንት መካከል ስምምነት ያለ ሲሆን ዖፅ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የሚገኝ በደቡብ ኤዶምን በሰሜን ደግሞ አራምን የሚያጠቃልል ምድር መሆኑ ይታወቃል (አ.መ.ት. ገፅ 731-735)፡፡ የጸሐፊው ትችት ኢዮብ በእስልምና ተቀባይነት ያለው ነቢይ መሆኑን የዘነጋ ነው፡፡ ስለ ኢዮብ ያለን መረጃ አናሳ መሆኑ ከችግር የሚቆጠርና መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተች ከሆነ ሙስሊሞችም በኢዮብ (አዩብ) ስለሚያምኑ ችግሩን መጋፈጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ኢዮብ የአብርሃም ዘር እንዳልሆነ በሊቃውንት መካከል ስምምነት ያለ ከመሆኑ አንጻር የቁርአን ጸሐፊ ኢዮብን ከአብርሃም ዘሮች መካከል አንዱ መሆኑን መግለጹ ሙስሊሞች እንዲፈቱት የሚጠበቅባቸው ሌላው ችግር ነው (ሱራ 6:84-86)፡፡

—-

ጸሐፊው በመጽሐፈ መዝሙርና በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ የሰነዘረው ትችት እንደነ አሳፍ፣ ሙሴ፣ ሐጌና ዘካርያስ ያሉ ቅዱሳን ሰዎች የጻፏቸው ሐሳቦች በመጻሕፍቱ ውስጥ ስለሚገኙ “የሌሎች ሰዎች እጅ ገብቶባቸዋል” የሚል ነው (ገፅ 32)፡፡ ይህ እስላማዊውን የብረዛ ክስ ለማረጋገጥ ያለመ ይመስላል፡፡ ሲጀመር እነዚህ መጻሕፍት የዳዊትና የሰለሞንን ጽሑፎች ብቻ እንደያዙ የተናገረ የለም፡፡ በመሐመድ ዘመንም ሆነ በየትኛውም ዘመን መጻሕፍቱ የሚታወቁት በዚህ ይዘታቸው ነው፡፡ የሙሴና የሌሎች ነቢያት መዝሙራት በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ መገኘታቸው “የሌሎች ሰዎች እጅ ገብቶበታል” አያስብልም፡፡ ሙስሊም ሰባኪያን ካላዋቂነታቸው የተነሳ የሚናገሩት መሰል ንግግር ቦታ የሚሰጠው አይደለም፡፡

—-

ገፅ 33 ላይ ስንሄድ ጸሐፊው መጽሐፈ መክብብ ሁሉም ነገር ከንቱ እንደሆነ ስለሚናገር ሰዎች አዲስ ነገር እንዳይፈልጉ ተስፋ ያስቆርጣል የሚል ትችት ይሰነዝራል፡፡ እንዲህ ያለ ትችት መሰንዘሩ ጸሐፊው መጽሐፈ መክብብን በትክክል አለመረዳቱን ያሳያል፡፡ በርግጥ መጽሐፈ መክብብ የጥበብ መጽሐፍ በመሆኑ በአስተውሎት ያልተመለከተው ሰው ለእንዲህ ያለ ስሁት ድምዳሜ መዳረጉ የሚጠበቅ ነው፡፡ በአጠቃላይ የመጽሐፈ መክብብ ጸሐፊ “ሕይወት ያለ እግዚአብሔር ከንቱ መሆኗን” ይገልጻል፡፡ እግዚአብሔር ባይኖርና የሰው ሕይወት በሞት የሚደመደም ቢሆን ኖሮ ሁሉም ነገር ከንቱና ትርጉም አልባ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ስለዚህ አቶ ሰልማን የሰነዘረው ትችት መጽሐፉን አንብቦ ካለመረዳት የመነጨ ነው፡፡

ሌላው አስገራሚ ነገር መክብብ እርስ በራሱ እንደሚጋጭ ለማሳየት መሞከሩ ነው፡፡ ይህም የመጽሐፉን ባሕርይ ካለማወቅ የመነጨ ሌላ ስህተት ነው፡፡ መክብብ የሰው ልጆች ሕይወትን በተመለከተ የሚያነሷቸውን መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚያነሳ መጽሐፍ ነው፡፡ ጸሐፊው ለማጋጨት የሞከራቸው ሁለቱ ጥቅሶች ለዚህ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ከጸሐፊው አንደበት እንስማ፡-

በተጨማሪም መክብብ ከብሉይ ኪዳንም ሆነ ከራሱ ንግግሮች ጋር የሚጋጩ ሃሳቦችን የምናገኝበት ሲሆን በምዕ 4፡2 ላይ “እኔም እስከ ዛሬ በሕይወት ካሉት ይልቅ በቀድሞ ዘመን የሞቱትን አመሰገንሁ” በማለት ሞት ከህይወት እንደሚሻል ሲገልፅ በአንፃሩ በምዕ 9፡4 ላይ “ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና ሰው ከሕያዋን ሁሉ ጋር በአንድነት ቢኖር ተስፋ አለው” በማለት ህይወት ከሞት እንደሚሻል ይናገራል፡፡ (ገፅ 33)

የመጀመርያውን ጥቅስ አውድ ስንመለከት መክብብ ከሕይወት ሞት እንደሚመረጥ የተናገረው “በምድር ላይ የሚፈፀሙትን የግፍ ሥራዎች አለማየት ይሻላል” በሚል መንፈስ ነው፡፡ አውዱን እናንብበው፡-

“እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፥ የተገፉት ሰዎች እንባ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፥ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም። እኔም እስከ ዛሬ በሕይወት ካሉት ይልቅ በቀድሞ ዘመን የሞቱትን አመሰገንሁ፤ ከእነዚህም ከሁለቱ ይልቅ ገና ያልተወለደው ከፀሐይም በታች የሚደረገውን ግፍ ያላየው ይሻላል።” (መክብብ 4፡1-3)

በምድር ላይ የሚፈፀመውን ግፍ ተመልክቶ በመፈጠሩ የማያዝን ሰው ይኖር ይሆን? መክብብ እየነገረን ያለው ዕለት ዕለት የምንጋፈጠውን ይህንን ስሜት ነው፡፡ በምድር ላይ ብዙ ግፍ አለ፡፡ ለዚህች ከንቱ ዓለም ሲል ወንድም ወንድሙን ሲገድል፣ ገዢዎች ድኾችን ሲጨቁኑ፣ የንፁሃን ደም በከንቱ ሲፈስስ አይቶ እንዲህ ካለው ስሜት ጋር የማይታገል የለም፡፡ ኾኖም ውስጥ ውስጡን ሕይወትን እንወዳታለን፤ ካለመፈጠር መፈጠር የተሻለ እንደሆነ እናምናለን፤ ከመሞትም መኖርን እንመርጣለን፤ “ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላል” እንላለን (መክብብ 9፡4)፡፡ የመክብብ መጽሐፍ ይህንን የሕይወት መንታ ገፅታ ማሳየቱን በግጭትነት መፈረጅ አስተውሎት ካለው ሰው የሚጠበቅ አይደለም፡፡

የመክብብን ጸሐፊ ማንነት በተመለከተ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ “ሰባኪው” ተብሎ በመጠራቱ ምክንያት “ሰለሞን የሰባኪነት ባሕርይ ያልነበረው” በመሆኑ ምክንያት ሰለሞን ሊሆን አይችልም ይለናል፡፡ “የዳዊት ልጅ” መባሉንም ኢየሱስን ጨምሮ ሌሎች ወገኖች “የዳዊት ልጅ” በመባላቸው ምክንያት ሰለሞን ስለመሆኑ ማረጋገጫ እንደማይሆን ይነግረናል (ገፅ 34)፡፡ ሆኖም ጸሐፊው በመጽሐፉ ውስጥ ብዙ ምሳሌዎችን የተናገረ ጥበበኛ (12፡9)፣ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ነገሥታት ሁሉ ይልቅ ባለጠጋ (2፡9-10) እንዲሁም ሺ ሴቶችን የሚያውቅ (7፡28) እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህ ሁሉ መግለጫ ከሰለሞን ውጪ ሌላ ማንን ሊያመለክት ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰለሞን ጥበብ እንዲህ ይላል፡-

እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው። የሰሎሞንም ጥበብ በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብጽ ጥበብ ሁሉ በለጠ። ከሰውም ሁሉ ይልቅ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታንና ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ከደራልም ይልቅ ጥበበኛ ነበረ። በዙሪያውም ባሉ አሕዛብ ሁሉ ዝናው ወጣ። እርሱም ሦስት ሺህ ምሳሌዎች ተናገረ፤ መኃልዩም ሺህ አምስት ነበረ። ስለ ዛፍም ከሊባኖስ ዝግባ ጀምሮ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው እስከ ሂሶጵ ድረስ ይናገር ነበር፤ ደግሞም ስለ አውሬዎችና ስለ ወፎች ሰለተንቀሳቃሾችና ስለ ዓሣዎች ይናገር ነበር። ከአሕዛብም ሁሉ፥ ጥበቡንም ሰምተው ከነበሩ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ሰዎች ይመጡ ነበር። (1ነገ. 4፡29-34)

ይህንን ሁሉ ጥበብ የተሞላ ሰው “የሰባኪነት ባሕርይ አልነበረውም” እንዴት ይባላል? ሰባኪ (በእብራይስጥ ቆኸለት) ማለት አስተማሪ ማለት ነው፡፡ እና ሰለሞን ጥበቡን አላስተማረም እያልከን ነው? ወደው አይስቁ አሉ!

—–

መኃልየ መኃልይን በተመለከተ የተለመደውን እስላማዊ ትችት ይሰነዝራል፡፡ እርሱም የፍቅር ግጥም የአምላክ ቃል አካል ሊሆን አይችልም የሚል ነው (ገፅ 34)፡፡ የሚገርመው ነገር በብዙ ሙስሊም ሰባኪያን እምነት መሠረት ሙሐመድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስም ተጠቅሶ የሚገኘው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ ዲዳት፣ ዛኪር፣ ሻቢርና የመሳሰሉት ሙስሊም ፕሮፓጋንዲስቶች በመጽሐፉ ውስጥ “ነቢያችን በስም ተጠቅሷል” ብለው ሽንጣጨውን ገትረው ይከራከራሉ፡፡ እነዚህ ፕሮፓጋንዲስቶች እንደሚሉት ምዕራፍ 5፡16 ላይ ሙሽራይቱ “አፉ እጅግ ጣፋጭ ነው፥ እርሱም ፈጽሞ ያማረ ነው…” በማለት የምትገልጸው ሙሐመድን ነው፡፡ መልሰው ደግሞ “መጽሐፉ የፍቅር ግጥም በመሆኑ መንፈሳዊ አይደለም” ይላሉ፡፡ ግራ የገባቸው ጉዶች!

እግዚአብሔር በምድር ላይ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው በረከቶች መካከል በባልና በሚስት መካከል ከሚገኝ የፍቅር ግንኙነት የበለጠ አስደሳችና ቅዱስ የሆነ ነገር ይኖር ይሆን? በመጽሐፉ ውስጥ የሴት ተረከዝ፣ ዳሌና ጡት መጠቀሱ የፈጣሪ ቃል እንዳይሆን ካደረገው ቁርአን ሙስሊም ወንዶች በገነት ውስጥ ልቅ ወሲብ እንደሚፈፅሙ በተናገረባቸው ክፍሎች ሴቶቹን “ነጫጭ ዓይናማዎች፣ ጡተ ጉቻማዎች፣ ሰውም ጂኒም ያልገሠሣቸው፣ ወዘተ.” እያለ መግለፁ እንዴት ይታያል?

78፡30-33 “ለጥንቁቆቹ መዳኛ ስፍራ አልላቸው፡፡ አትክልቶችና ወይኖችም፡፡ እኩያዎች የኾኑ ጡተ ጉቻማዎችም፡፡ የተሞሉ ብርጭቆዎችም፡፡”

44፡51-54 “ጥንቁቆቹ በእርግጥ በጸጥተኛ መኖሪያ ውስጥ ናቸው፡፡ በአትክልቶችና በምንጮች ውስጥ ናቸው፡፡ ፊት ለፊት የተቅጣጩ ሆነው ከስስ ሐርና ከወፍራም ሐር ይለብሳሉ፡፡ (ነገሩ) እንደዚሁ ነው፤ ዓይናማዎች የኾኑን ነጫጭ ሴቶችም እናጠናዳቸዋለን፡፡”

56፡34-36 “ከፍ በተደረጉ ምንጣፎችም (ሴቶችም መካከል)፡፡ እኛ አዲስ ፍጥረት አድርገን (ለእነርሱ) ፈጠርናቸው፡፡ ለባሎቻቸው ተሽሞርሟሪዎች እኩያዎች (አደረግናቸው)፡፡ ለቀኝ ጓዶች (አዘጋጀናቸው)፡፡”

55፡74-76 “ከነሱ በፊት፥ ሰውም ጃንም አልገሠሣቸውም። ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ? በሚያረገርጉ አረንጓዴ ምንጣፎችና በሚያማምሩ ስጋጃዎች ላይ የተደላደሉ ሲሆኑ (ይቀመጣሉ)።”

በተጨማሪም በሐዲስ መጻሕፍት ውስጥ አንድ ሙስሊም የመቶ ወንዶች ጉልበት እንደሚኖረውና በማይበርድ የፍትወት ስሜት ውስጥ እንደሚኖር ጨዋነት በጎደለው መንገድ ተነግሯል፡፡ (Mishkat Al-Masabih: vol. 3, p. 1200; At-Tirmizi, vol. 2, p. 138)

እስልምና የተቀደሰውን ማርከሱና የረከሰውን መቀደሱ ለምን ይሆን?

—–

ደራሲው በነቢያት መጻሕፍት ላይም ያልተገራ ትችቱን ሰንዝሯል፡፡ ከሁሉም አስገራሚው በኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ የሰነዘረው የመጀመርያው ትችት ነው፡፡ በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ከባቢሎን ምርኮ በኋላ የተከሰቱ ክስተቶች ስለተጠቀሱ ሁለተኛው የመጽሐፉ ክፍል ከባቢሎን ምርኮ በኋላ በሌላ ሰው የተጻፈ መሆኑን ግምት መኖሩን ይነግረናል (ገፅ 35)፡፡ ደራሲው ልዕለ ተፈጥሯዊ ጉዳዮችን የሚክዱትን የለዘብተኛ ሊቃውንት አስተያየቶች በግርድፉ በመገልበጡ ምክንያት ኢሳይያስ ነቢይ የመሆኑን እውነታ ከስሌቱ ውጪ አድርጓል፡፡ ነቢይ የወደፊቱን አውቆ የሚናገር የእግዚአብሔር አገልጋይ ስለመሆኑ ለአንድ ሙስሊም ነጋሪ አያስፈልገውም፡፡ ኢሳይያስ ስለ ባቢሎን ምርኮና በምርኮው ዘመን እንዲሁም ከምርኮው በኋላ ስለሚከሰቱ ጉዳዮች አስቀድሞ የተነበየ ነቢይ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (2ነገሥት 20፡14-18)፡፡ ለዘብተኛ ሊቃውንት ልዕለ ተፈጥሯዊ ጉዳዮችን ስለሚክዱ እንዲህ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን የሚያብራሩት ከክስተቶቹ በኋላ የተጻፉ በማስመሰል ነው፡፡ በልዕለ ተፈጥሯዊ ትንቢቶች የሚያምኑት ሙስሊም ወገኖች ከዚህ ስሁት ቅድመ ግንዛቤ የመነጨውን የክህደት አመለካከት ማቀንቀናቸው አስገራሚ ነው፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር ብዙ ሙስሊም ሰባኪያን ሙሐመድ በኢሳይያስ 42 ላይ እንደተተነበየ ማስተማራቸው ነው፡፡ ትርጓሜያቸው ስህተት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እንዲህ ያለ እምነት ለመያዝ ኢሳይያስ እውነተኛ ነቢይ መሆኑን ማመን ግድ ይላል፡፡ ስለዚህ ስለ ነቢያቸው መተንበይ ከቻለ ስለ ባቢሎን ምርኮ መተንበይ የማይችልበት ምክንያት ምን ይሆን? አባይ ሚዛን የሐሳውያን አርማ ነው፡፡

በመጽሐፉ ላይ የሰነዘረው ሁለተኛው ትችት “በቁምራን የተገኘው የኢሳይያስ ጥቅልል አሁን ካለው የኢሳይያስ መጽሐፍ ጋር ሰፊ የሆነ ልዩነት ያሳያል” የሚል ነው (ገፅ 35)፡፡ ነገር ግን እርሱ በተሳሳተ መንገድ የተረዳው ከሁሉም አነጋጋሪ ስለሆነው የኢሳይያስ ጥቅልል የተሰጠውን መረጃ ሲሆን ይህንን በተመለከተ G. L. Archer የተሰኘ ዕውቅ ሊቅ እንደጻፈው የኢሳይያስ 95% ያህል የሚሆነው ቃል በቃል ከማሶሬቱ ቅጂ ጋር አንድ ሲሆን ከልዩነት የተፈረጀው 5% መልእክቱን የማይለውጥ እዚህ ግባ የማይባል የብዕር ወለምታና የአጻጻፍ ልዩነት ነው፡፡ እንዲህ ነው ያለው፡- “the two copies of Isaiah discovered in Qumran Cave 1 proved to be word for word identical with our standard Hebrew Bible in more than 95 percent of the text. The 5 percent of variation consisted chiefly of obvious slips of the pen and variations in spelling” (G. L. Archer, Jr., A Survey of Old Testament Introduction, p. 19)

በ 1000 ዓመታት ውስጥ በብዕር ወለምታና በአጻጻፍ ልዩነት ምክንያት የተፈጠረው “ልዩነት” ሁሉ ተደማምሮ የመጽሐፉ 5% ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቁርአንም ሆነ በማንኛውም ጥንታዊ መጽሐፍ የእጅ ጽሑፍ ውስጥ ሊገኝ የሚችል ነው፡፡ መሠረታዊ ልዩነት የሚያስከትልና የመጽሐፉን ተዓማኒነት የሚሸረሽር ምንም ነገር የለም፡፡

——-

ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ዳንኤልና የመሳሰሉትን ነቢያት የተለመደውን የለዘብተኛ ሊቃውንት ቅድመ ግንዛቤ በመጠቀም ለማጣጣል ጥረት አድርጓል (ገፅ 36-44)፡፡ ቀደም ሲል እንዳልነው ለዘብተኛ ሊቃውንት ልዕለ ተፈጥሯዊ ጉዳዮችን ስለማይቀበሉ የኋለኛው ዘመን ክስተቶችን በትንቢት መልኩ የሚያስቀምጡ የነቢያት መጻሕፍት የግድ ከክስተቶቹ በኋላ የተጻፉ መሆን አለባቸው የሚል ቅድመ ግንዛቤ ይዘው ይከራከራሉ፡፡ ከነቢያቱ ዘመን ጋር የሚሄዱትን ሐሳቦች በነቢያቱ ዘመን እንደተጻፉ የሚቀበሉ ሲሆን ትንቢታዊ ይዘት ያላቸውንና የወደፊቱን ዘመን የሚያመለክቱትን ከክስተቶቹ በኋላ እንደተጻፉ በማስመሰል ይናገራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ትችት ካቀረቡባቸው ነቢያት መካከል ዳንኤል ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ዳንኤል ከናቡ ከደነፆር ዘመን ጀምሮ ስለ ፋርሳውያን፣ ግሪካውያንና ሮማውያን ዘመናት አስገራሚና ዝርዝር ትንቢቶችን መናገሩ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች የዳንኤል መጽሐፍ በስድስተኛው ክ.ዘ ተጽፎ እንደነበረ ከተቀበሉ የእግዚአብሔርን መኖርና ልዕለ ተፈጥሯዊ ትንቢቶችን ለመቀበል ሊገደዱ ነው፡፡ ስለዚህ የክህደት አስተሳሰባቸውን ለማጽደቅ ያገኙት ብቸኛ መፍትሄ መጽሐፉ ከክስተቶቹ በኋላ በሁለተኛው ክ.ዘ ቅድመ ክርስቶስ እንደተጻፈ መገመት ነው፡፡ ሆኖም ክርስቶስን የተመለከቱና በአንደኛው ክፍለ ዘመን ፍፃሜን ያገኙ ሌሎች ትንቢቶች በመጽሐፉ ውስጥ ስለሚገኙ እነዚህ ወገኖች አሁንም ችግር ውስጥ ናቸው (ዳን. 9)፡፡

ሙስሊም ሰባኪያን ለእልምናም ጭምር ጠላት የሆነውን የክህደት አስተሳሰብ ተውሰው መጽሐፍ ቅዱስን ሲተቹ ማየት በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ ይህ ደራሲ ገፅ 37 ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል፡-

“…በመጽሐፉ ውስጥ ከእርሱ በኋላ ስለተከሰቱ የ400 ዓመታት ታሪክ ተጽፎ መገኘቱ የመጽሐፉ ደራሲ ዳንኤል እንዳልሆነ ምሑራኑን አስማምቷል፡፡”

ምሑራኑን ያስማማው “እንዲህ ያለ ዝርዝር ትንቢት መናገር አይቻልም” የሚለው የእግዚአብሔርን ችሎታ የመካድና በነቢያት ያለማመን አመለካከት ነው፡፡ አንድ በነቢያት አምናለሁ የሚል ሙስሊም እንዲህ ያለውን አመለካከት ማቀንቀኑ በተናጋ መሠረት ላይ መቆሙን አመላካች ነው፡፡ በርግጥ ሰልማንን የመሰለ በነገረ መለኮት የረባ ሥልጠና የሌለው የኩረጃ ደራሲ ይህንን ቅድመ ግንዛቤ ከነ አካቴው መረዳት መቻሉም የማይመስል ነው፡፡

የዳንኤል መጽሐፍ በሰብዓ ሊቃናት በሁለተኛው ክ.ዘ ቅድመ ክርስቶስ ወደ ግሪክ ቋንቋ ተተርጉሟል፤ በዚያው ክፍለ ዘመን የተገለበጡ ጽሑፎች በቁምራን ዋሻዎች ውስጥ ተገኝተዋል፤ ዮሴፍ ወልደ ኮርዮንን የመሳሰሉት አይሁድ ጸሐፍት ለትክክለኛነቱ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፤ ጌታችን ኢየሱስም ጠቅሶታል (ማቴ. 24፡15)፡፡ ከተቃዋሚዎች ግምት በተጻራሪ ለትክክለኛነቱ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል (Geisler, Encyclopedia of Christian Apologetics, pp. 327-328; አ.መ.ት ገፅ 1295 ይመልከቱ)፡፡

ሌላው ይህ ደራሲ በቁምራን የተገኙት ቀዳሚያን ጽሑፎች ከኋለኞቹ ጽሑፎች ጋር መሠረታዊ ልዩነትን እንደሚያሳዩ በተደጋጋሚ ይናገራል ፡፡ የምሑራንን ጽሑፎች ያገላበጥን እንደሆን የቁምራን ጽሑፎች ከኋለኞቹ ዘመናት ጋር ያላቸው ልዩነት በግልበጣ ወቅት ሊከሰቱ ከሚችሉ የብዕር ወለምታዎችና የአጻጻፍ ልዩነቶች እንዲሁም የጥቂት ቃላት ልዩነቶች በዘለለ መጻሕፍቱን መሠረታዊ በሆነ መንገድ ሊለውጥ የሚችል ምንም ነገር እንዳልተገኘና ይልቁኑ እነዚህ ግኝቶች ለብሉይ ኪዳን ተዓማኒነት የሚሰጡት ማረጋገጫ እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በዘርፉ ከፍተኛ ዕውቀት ካላቸው ሊቃውንት መካከል ሚለር በሮውስ አንዱ ናቸው፡፡ በኚህ ሊቅ መሠረት በአንድ ሺህ ዓመታት ውስጥ በጽሑፎቹ ውስጥ የታየው ለውጥ እዚህ ግባ የማይባል መሆኑ አስደናቂ ነው፡፡ ይህም የማሶሬቱን ቅጂ ተዓማኒነት የሚያረጋግጥ ዋነኛ ማስረጃ ነው (M. Burrows, The Dead Sea Scrolls, p. 304)፡፡ ተመሳሳይ ምስክርነት የሰጡ በርካታ ሊቃውንትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

——

ማጠቃለያ

ሙስሊም ሰባኪያን ብሉይ ኪዳንን ሲተቹ ከግምት ውስጥ የማያስገቡት አንድ እውነታ ቢኖር አይሁድ በምን ያህል ጥንቃቄና አክብሮት ቃለ እግዚአብሔርን ጠብቀው እንዳቆዩልን ነው፡፡ የአይሁድ ሕዝብ ቅዱሳት መጻሕፍትን በታላቅ ፍርሃትና አክብሮት በጥንቃቄ ይዘው እንዳቆዩ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ የጥንቃቄያቸውን ብዛት ለመረዳትና ለማድነቅ እስኪ ተከታዮቹን እውነታዎች ከግምት ውስጥ አግቡ፡-

  • የጽሑፍ ሥራው ከመጀመሩ በፊት በእድሜ የሁሉ ታላቅ የሆነ ረቢ ተነስቶ በመቆም አንድ ፊደል እንኳ መቀነስ ወይንም ደግሞ መጨመር ለጥፋት እንደሚዳርጋቸው ጸሐፍቱን ያስጠነቅቃል፡፡
  • ጸሐፍቱ ሥራቸውን እየሠሩ ሳሉ ንጉሥ እንኳ ቢገባ ስህተት ላለመሥራት የጀመሩትን ገፅ እስኪጨርሱ ድረስ ቀና ብለው ማናገር እንደ ሌለባቸው ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል፡፡
  • ብሉይ ኪዳን የሚጻፍበት ብራና ከንፁህ እንስሳት ቆዳ በአይሁዳዊ እጅ ብቻ መዘጋጀት አለበት፡፡
  • እያንዳንዱ ወርድ ከ 48 በታች እና ከ 60 በላይ መስመሮች ሊኖሩት አይገባም፡፡
  • ቀለሙ ጥቁር ብቻ መሆን አለበት፣ በተለየ ሁኔታም ይዘጋጃል፡፡
  • ከትውስታ የሚጻፍ ምንም ዓይነት ቃል ወይንም ፊደል መኖር የለበትም፡፡ ጸሐፊው ተኣማኒ የሆነ ኮፒ ከፊት ለፊቱ ማስቀመጥ አለበት፣ ከመጻፉ በፊትም ከፍ ባለ ድምፅ በትክክል ሊያነበው ይገባል፡፡
  • ጸሐፊው ከመጻፉ በፊት አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ መጻፍያውን መወልወል አለበት፡፡
  • ጸሐፊው ያሕዌ የሚለውን ስመ እግዚአብሔር ከመጻፉ በፊት መላ ሰውነቱን መታጠብ አለበት፡፡
  • ጸሐፊው ያሕዌ የሚለውን ስመ እግዚአብሔርን ለመጻፍ አዲስ ብዕር ይጠቀማል፡፡ ያሕዌ የሚለውን ስም የጻፈበትን ብዕር ሌላ ቃል ለመጻፍ አይጠቀምበትም፡፡
  • በአንድ ገፅ ላይ የሚፈጠር አንድ ስህተት ገፁን በሙሉ ያበላሸዋል፡፡ በአንድ ገፅ ላይ ሦስት ስህተቶች ከተገኙ ብራናው በሙሉ ከጥቅም ውጪ ይሆናል፡፡
  • እያንዳንዱ ቃልና እያንዳንዱ ፊደል ተቆጥሮ ተመዝግቧል፡፡ (Paul Roost, Proofs that the Bible is the word of almighty God, Book 147, pp. 30, Evangelical Bible College of Western Australia)

የብሉይ ኪዳን ጥበቃ እንዲህ ያለ ታሪክ ያለው ሆኖ ሳለ ሙስሊም ሰባኪያን ከአዋልድ መጻሕፍትና ከአረብ አፈታሪኮች የተቃረመውን ቁርአናቸውን ከስህተቱ ለመታደግ በከንቱ ይለፋሉ፡፡

ንቁ! ሙስሊም ሰባኪያን ሐሰተኞች ናቸው!

ይቀጥላል…

—-

ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነውእስልምናስ?

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ