ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነው! እስልምናስ? የመጽሐፍ ሒስና ግምገማ – ክፍል 5

ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነው!

እስልምናስ?

የመጽሐፍ ሒስና ግምገማ – ክፍል 5

ርዕስ – ንቁ! ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነውን?

ደራሲ – ሰልማን ኮከብ

የታተመበት ዘመን – 2010

አሳታሚ – አልተገለፀም

የገፅ ብዛት – 270

ለሰልማን የፕሮፓጋንዳ መጽሐፍ ምላሻችንን ካቆምንበት እንቀጥላለን፡፡ ጸሐፊው የተለመዱትን የሙስሊም ሰባኪያን ማስረጃ አልባና የተዛቡ መረጃዎች ያስነብበናል፡፡

መጻሕፍትን የማቃጠል ታሪክ ያለው ክርስትና ወይንስ እስልምና?

የአዲስ ኪዳንን መጻሕፍት አሰባሰብና የቀኖና ሒደት በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል፡-

“…ከኒቂያ ጉባኤ (325) በፊት በአሁኑ መጽሐፍ ቅዱስ ያልተካተቱ በርካታ ወንጌላትና መልዕክቶች እንደነበሩና ሊቃውንቱ ባካሄዷቸው ተከታታይ ስብሰባዎች 27ቱ ብቻ በቀኖናነት አፅድቀው ሌሎቹ እንዲቃጠሉ እንዳደረጉ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ ከጠፉት ውስጥም የሔርማስ እረኛ፣ የቶማስ ወንጌል፣ የጴጥሮስ ወንጌል፣ የበርናባስ ወንጌል ሌሎችም ይገኙበታል፡፡” (ገፅ 45)

ለዚህ ሁሉ ውንጀላው አንዳችም ማስረጃ አለመጥቀሱን ልብ በሉ፡፡ የዚህም ምክንያቱ ይህ ታሪክ ፈጠራ እንጂ እውነተኛ ታሪክ ባለመሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ውንጀላዎችን በመሰል እስላማዊ የፕሮፓጋንዳ መጽሐፍት ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በክርስትና ወዳጆችም ሆነ ባላንጣዎች በተጻፉ ምሑራዊ ምንጮች ውስጥ ማግኘት አይቻልም፡፡ በጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን ታሪክ መጻሕፍትን የማቃጠል ተግባር መፈፀሙን የሚያመለክት ምንም ዓይነት ታሪካዊ ማስረጃ የለም፡፡ ይልቅ ቁርአንንም ሆነ ሌሎች መጻሕፍትን የማቃጠል ታሪክ ያለው እስልምና ነው፡፡

ከላይ ጸሐፊው “ጠፉ” ካላቸው መጻሕፍት መካከል የሔርማሱ እረኛ፣ የቶማስ ወንጌል እና የበርናባስ ወንጌል አሁንም ይገኛሉ፡፡ የሔርማሱ እረኛ ተጠብቆ ለዚህ ዘመን እንዲበቃ ያደረጉት ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ የክርስትናን አስተምህሮ የሚቃወም ነገር ባይኖርም ሐዋርያዊ ሥልጣን የሌለው የኋለኛው ዘመን ሥራ በመሆኑ ከቀኖና ውጪ ሆኗል፡፡

የቶማስ ወንጌል በኖስቲሳውያን የተዘጋጀ የአፖክሪፋ ጽሑፍ ሲሆን ሐዋርያዊ መሠረት የለውም፡፡ የመጽሐፉ ይዘት ከሞላ ጎደል በ1945 ዓ.ም. በግብጽ ተገኝቷል፡፡ ይህንን መጽሐፍ አንዳንድ ለዘብተኛ ሊቃውንት ከኢየሱስ ዘመን ጋር ሊገናኝ እንደሚችል ገምተው የነበረ ቢሆንም በሁለተኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ የተጻፈ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ የሙስሊሞች ተወዳጅ የክርስትና ተቃዋሚ የሆነው ባርት ኤህርማን መጽሐፉ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ የተጻፈ መሆኑ ጥርጥር እንደሌለው ተናግሯል (Bart D. Ehrman. Lost Scriptures፡ Books that Did Not Make it into the New Testament; Oxford University Press, 2003, p. 20)፡፡ የሚገርመው ነገር በቁርአን ውስጥ የሚገኘው ኢየሱስ በህፃንነቱ ከጭቃ ወፍ ሠርቶ ስለማብረሩ የሚናገረው ታሪክ ከዚህ ወንጌል ላይ የተወሰደ መሆኑ ነው (The New Testament Apocrypha, vol. 1, rev. ed. by W. Schneemelcher, trans. R. McL. Wilson, Westminster / John Knox, 1991, p. 444)፡፡

የበርናባስ ወንጌል በመካከለኛው ዘመን በአንድ ሙስሊም የተጻፈ የፈጠራ ጽሑፍ ሲሆን የመጀመርያ ቋንቋው ጣልያንኛ ነው፡፡ በዚህ ዘመን አንዳንድ ዕውቀት አጠር ሙስሊሞች ካልሆኑ በስተቀር ዕውቀት ያላቸው ሙስሊሞች እንኳ ትክክለኛ መጽሐፍ መሆኑን አይቀበሉም፡፡

የጴጥሮስ ወንጌልን የመሳሰሉ በሁለተኛው ክፍለ ዘመንና ከዚያ በኋላ የተጻፉ ከቀኖና ውጪ የተደረጉ ሌሎች መጻሕፍት በኑፋቄ ቡድኖች የተዘጋጁ በመሆናቸው ትምህርቶቹ ሲከስሙ ተንከባካቢ በማጣታቸው ምክንያት አብረው ጠፍተዋል፡፡ የአንዳንዶቹ ቁርጥራጮች በቅርብ ዘመናት የተገኙ ሲሆኑ እነዚህ መጻሕፍት በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ወይንም በሐዋርያት እጅ እንደተጻፉ የሚያምን ለዘብተኛም ሆነ አጥባቂ ምሑር የለም፡፡ ይህንን ደግሞ ሰልማን ራሱ በዚህ መጽሐፉ ገፅ 51 ላይ ጽፎታል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ሐዋርያዊ ምንጭ የሌላቸው መጻሕፍት መጥፋታቸውም ሆነ ከቀኖና ውጪ መደረጋቸው በክርስትና ላይ ጥያቄን ሊያስነሳ አይችልም፡፡

የማርቆስ ወንጌል

ቁርአን ሙሐመድን ከሚያውቀው በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ማርቆስን ያውቀዋል!

 በማስከተል የማርቆስን ወንጌል በተመለከተ እንዲህ የሚል ትችት ይሰነዝራል፡-

“… የማርቆስ ስም በአራቱም ወንጌላት አልተጠቀሰም፡፡ የአባቱ ስምና ዜግነቱም አይታወቅም፡፡ ዘመናዊ የታሪክ አጥኚዎች ማርቆስ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንዳልነበረና በተለምዶ የጴጥሮስ ተማሪ እንደሆነ የሚነገረውም ማስረጃ የሌለው እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡” (ገፅ 45)

የተወሰነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከፍሎ የእገሌ ስም እዚያ ውስጥ አልተጠቀሰም ማለት ምን የሚሉት ሙግት ነው? የማርቆስ ስም በሐዋርያት ሥራና በሦስት መልእክታት ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ ትክክለኛ መረጃ ለማስተላለፍ ብቁ መሆኑን ለማመልከት ይህ በቂ አይደለምን? ለመሆኑ የሙሐመድ ስም ከቁርአን ሱራዎች በስንቱ ውስጥ ነው ተጠቅሶ የምናገኘው? የሙሐመድ አባትና እናት ስም በቁርአን ውስጥ ተጠቅሶ ይገኝ ይሆን? ከሚስቶቹ የማን ስም ነው የተጠቀሰው? ከልጆቹ መካከልስ የነማን ስም ተጠቅሷል? ቁርአንን ሲጽፉለት ከነበሩት ጸሐፊዎቹ መካከል በስም ተጠቅሶ የምናገኘው ማንን ነው? ሙስሊም ሰባኪያን ለገዛ ሃይማኖታቸው የማይጠቀሟቸውን መስፈርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መጫን ልማዳቸው ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፈልን በመነሳት ስለ ማርቆስ ተከታዮቹን መረጃዎች እናገኛለን፡-

  • የማርቆስ ሌላኛው ስም ዮሐንስ ነው (ሐዋ. 12፡25)፡፡
  • የሐዋርያት ወዳጅ የሆነችው የኢየሩሳሌሟ ማርያም ልጅ ነው (ሐዋ. 12፡12)፡፡
  • ክርስቲያኖች በቤታቸው ለጸሎት ይሰበሰቡ ነበር (ሐዋ. 12፡12)፡፡
  • የበርናባስ የወንድሙ ልጅ ነው (ሐዋ. ቆላ. 4፡10-11)፡፡
  • ጳውሎስና ወዳጁ በርናባስ ለስብከተ ወንጌል በወጡበት ወቅት ረዳት በመሆን ከአንፆኪያ ወደ ትንሹ ኢስያ አብሯቸው ተጉዞ ነበር (ሐዋ. 13፡5፣ 15፡37-38)፡፡
  • ነገር ግን ሥራውን ሳይፈፅም በመመለሱ ምክንያት ጳውሎስ ተቀይሞት ነበር (ሐዋ. 15፡37-38)፡፡
  • ከጳውሎስ ከተለየ በኋላ በርናባስ ከአንፆኪያ ወደ ቆጵሮስ ይዞት ሄዶ ነበር (ሐዋ. ሐዋ. 15፡39)፡፡
  • ኋላ ላይ ስለተስማሙ በአገልግሎት እንዲረዳው ጳውሎስ ወደ ሮም ጠርቶታል (2ጢሞ. 4፡11)፡፡
  • ጳውሎስ በሮም በእስር ላይ በነበረባቸው ጊዜያት አብረውት ከነበሩት የቅርብ ወዳጆቹ መካከል አንዱ ማርቆስ ነበር (ፊልሞ. 1፡24))፡፡
  • የሐዋርያው ጴጥሮስ መንፈሳዊ ልጅ ነበር (1ጴጥ. 5፡13)፡፡

ማርቆስ በስም ዘጠኝ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ ሲሆን የሙሐመድ ስም ግን በቁርአን ውስጥ የተጠቀሰው አራት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ቁርአን ሙሐመድን ከሚያውቀው በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ማርቆስን ያውቀዋል!

ማርቆስ የጴጥሮስ ተማሪ እንደነበርና ወንጌሉን ከእርሱ ሰምቶ እንደተጻፈ በ115 ዓ.ም. የተነገረ ከፓፒያስ የተገኘ መረጃ ኢዮስቢዮስ (375 ዓ.ም.) በጻፈው ጽሑፍ ውስጥ ተጠብቋል፡፡ ይህ መረጃ በቀዳሚነት የተላለፈው ከሐዋርያው ዮሐንስ ሲሆን፤ ማርቆስ የጴጥሮስ አስተርጓሚ የነበረ መሆኑን፤ መረጃዎቹን ሳይጨምርና ሳይቀንስ ያለ አንዳች ስህተት በታላቅ ጥንቃቄ መጻፉን መስክሯል (ሜሪል ሲ. ቴኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት፣ ገፅ 239)፡፡ ሰልማን ያለ በቂ ጥናት የግል ፈጠራውን እያስነበበን ነው፡፡

ወንጌሉ መች ነው የተጻፈው?

በማስከተል ደግሞ እንዲህ ይለናል፡-

“መጽሐፉ በመጠኑ አነስተኛ ሲሆን የኢየሱስን የልደት ታሪክ አይዘግብም፡፡ ወንጌሉ በግሪክኛ መጻፉ የአይሁድን ባሕል የተከተለ አለመሆኑ ምናልባት በስደት ሶርያ የሚኖር በደሙ አይሁዳዊ የሆነ ሰው ጽፎት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ወንጌሉ እ.ኤ.አ ከ80-100 ባለው ዘመን እንደተጻፈ ሲገመት በ250 (3ኛው ክ.ዘ) የተጻፉ ቅጂዎች ናቸው ተብለው ከተገኙ ጥቂት ገፆች በቀር የመጀመርያው ወንጌልም ሆነ የቅጂ ቅጂው ጠፍቷል፡፡” (ገፅ 45-46)

በዚህ ዘመን የሚገኙት አጥባቂ ሊቃውንት ተመሳሳዮቹ ወንጌላት ከ70 ዓ.ም. በፊት እንደተጻፉ የሚናገሩ ሲሆን ከለዘብተኛ ምሑራን መካከል የሚበዙቱ አራቱንም ወንጌላት ከ95 ዓ.ም. በፊት ያደርጓቸዋል፡፡ በለዘብተኛነታቸውና ክርስትናን በመቃወም የሚታወቁት የአዲስ ኪዳን ምሑር ባርት ኤህርማን እንኳ ማርቆስን 70 ዓ.ም. ገደማ፣ ማቴዎስንና ሉቃስን 80-85 ዓ.ም. ገደማ፣ ዮሐንስን ደግሞ 95 ዓ.ም. ገደማ ያስቀምጣሉ፡፡ (Bart D. Ehrman. Jesus, interrupted : Revealing the Hidden Contradictions in the Bible (and Why We Don’t Know About Them); New York, HarperOne, 2009, pp. 144-145) የክርስትና ተቃዋሚ የነበሩት ኤ. ቲ. ሮቢንሰን የተሰኙ ዕውቅ ለዘብተኛ ምሑር እንዲያውም ማቴዎስን ከ40-60፣ ማርቆስን ከ45-60፣ ሉቃስን ከ57-60፣ ዮሐንስን ከ40-60 ዓ.ም. ባሉት መካከል አስቀምጠዋል፡፡ (Norman Geislere: Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 389)፡፡ የለዘብተኞችን አቋም በማቀንቀን የሚታወቀው ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ ደግሞ የማርቆስ ወንጌል ከ70 ዓ.ም. በፊት የተጻፈ መሆኑን ይናገራል፡፡ https://www.britannica.com/topic/Gospel-According-to-Mark ስለዚህ ከ80-100 የሚለው ግምት ማስረጃ የለውም፡፡ ወንጌሉ በሮም እንደተጻፈ በሊቃውንት ዘንድ አጠቃላይ ስምምነት ያለ በመሆኑ በሶርያ የተጻፈው ነው የሚለው የጥቂቶች አመለካከት ነው፡፡ (ያለፈውን ምንጭ ይመልከቱ፡፡)

የዋናው ጽሑፍ መጥፋት?

ሙስሊም ሰባኪያን የቁርአናቸው የመጀመርያ ጽሑፎች ሆነ ተብለው እንዲወድሙ መደረጋቸውን በሚያውቁበት ሁኔታ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የመጀመርያዎቹ ጽሑፎች መጥፋት ማውራት ማዘውተራቸው በእውነቱ ግራ የሚገባ ነገር ነው፡፡ የመጀመርያው ቅጂ አለመኖሩ አንድን መጽሐፍ ተዓማኒ እንዳይሆን የሚያደርገው ከሆነ በቀዳሚነት ለጥርጣሬ የሚዳረገው ቁርአን እራሱ ነው፡፡ የዚህም ምክንያቱ እንደ ሌሎቹ መጻሕፍት የተፈጥሮ ሒደት ሰለባ ሆኖ ከመጥፋት ይልቅ ሆነ ተብሎ በሙስሊም መሪዎች ተሰብስቦ እንዲወድም በመደረጉ ነው፡፡ የሆነ ምስጢር ለመደበቅ የተደረገ አንዳች ሸፍጥ ባይኖር ኖሮ የፈጣሪ ቃል እንደሆነ የሚያምኑትን መጽሐፍ ሰብስቦ የማቃጠል ዘመቻ ባላደረጉ ነበር፡፡

የአዲስ ኪዳንን ቀዳሚያን ጽሑፎች በተመለከተ ተቃዋሚዎች የማቃጠል ዘመቻዎችን ከማድረጋቸው ውጪ በመጽሐፉ ባለቤቶች ሆነ ተብለው እንዲጠፉ አልተደረጉም፡፡ ይልቅ እንደ ማንኛውም መጽሐፍ በጊዜ ርዝማኔ የተፈጥሮ ሒደት ሰለባ ሆነዋል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ዕድሜ ያለው የመጀመርያው ጽሑፍ ተጠብቆ ለዚህ ዘመን የበቃ አንድም መጽሐፍ የለም፡፡ ምሑራን የአንድን ጥንታዊ መጽሐፍ ተዓማኒነት ለማረጋገጥ ነፃ በሆነ መንገድ የተገለበጡትን ኮፒዎች ብዛት፣ ጥራትና በመካከላቸው የሚገኘውን ስምምነት ይገመግማሉ እንጂ የመጀመርያው ጽሑፍ የግድ መገኘት አለበት አይሉም፡፡ እንደርሱ ዓይነት መመዘኛ ቢጠቀሙ ኖሮ ከጥንት መጻሕፍት መካከል አንዱም ተዓማኒ ባልሆነ ነበር፡፡ አዲስ ኪዳን በእጅ ጽሑፎች ሥልጣን በዓለም ታሪክ ከታዩት መጻሕፍት ሁሉ የላቀ ደረጃ ስላለው በትክክል ተላልፎ ለኛ ዘመን በመብቃቱ ላይ አንዳች ጥርጣሬ ሊኖር አይችልም፡፡

ቀዳሚያን የእጅ ጽሑፎች

ሰልማን ከተናገረው በተጻራሪ ከ250 ዓ.ም. በፊት የተጻፉ የማርቆስ ወንጌል ቁርጥራጮች ተገኝተዋል፡፡ የመጀመርያውና የሊቃውንትን ትኩረት የሳበው ጆሴ ኦክላሃን የተሰኙ እስፔናዊ ፓሌኦግራፈር የማርቆስ፣ ሐዋርያት ሥራ፣ ሮሜ፣ 1ጢሞቴዎስ፣ 2ጴጥሮስ እና ያዕቆብ መልዕክት ክፍሎችን በተወሰኑ ቁርጥራጮች ላይ ማግኘታቸው ሲሆን የማርቆስ ወንጌል ከኢየሱስ ሞት በኋላ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በጽሑፍ ለመስፈሩ እማኝ ነው፡፡ (Geisler፡ Ensyclopedia of Christian Apologetics, pp. 188)፡፡ የማርቆስን ጨምሮ አራቱን ወንጌላትና የሐዋርያት ሥራን የያዘው p45 Chester Beatty I በመባል የሚታወቀው የእጅ ጽሑፍ 100-150 ዓ.ም. መካከል የተጻፈ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ https://www.biblequery.net/mkmss.html ስለዚህ ደራሲው ከ250 ዓ.ም. በፊት የተጻፉ የማርቆስ ወንጌል የእጅ ጽሑፎች የሌሉ በማስመሰል መናገሩ ቅጥፈት ነው፡፡

ያልተፈጸመ ትንቢት ወይንስ የንበብ ችግር?

በማስከተል ጸሐፊው እንዲህ ይላል፡-

“ማርቆስ የኢየሱስን ዳግም መምጣትና የእግዚአብሔርን መንግስት ምስረታ ትኩረት ሰጥቶ የተረከው ሲሆን ከወንጌሉ ውስጥ እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን፡፡

“እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ስትመጣ እስኪያዩ ድረስ፥ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ አላቸው።” (ማር. 9፡1)

ነገር ግን ማርቆስ ኢየሱስ በቅርቡ እንደሚመጣ ይተንብይ እንጅ የሚመጣበት ጊዜ ለሁለት ሺህ ዘመናት ተራዝሟል፡፡ ‹‹እስኪመጣ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ›› የተባሉትም ሰዎች ሞተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የማርቆስ ትንቢት ‹‹ያልተሳካ›› ተብሏል፡፡ (ገፅ 46)

ሙስሊም ሰባኪያን የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅሶች ከአውድ ገንጥለው በመጥቀስ የታወቁ ናቸው፡፡ ጥቅሱ የመጨረሻውን ዘመን ምፅዓት ሳይሆን የክርስቶስን መለኮታዊ ክብር መገለጥ የሚያመለክት እንደሆነ የተሟላውን አውድ በማንበብ መረዳት ይቻላል፡፡ ጸሐፊው ቆርጦ ያስቀረውን ቀጣዩን ክፍል ካነበብን ጌታ የተናገረው ከስድስት ቀናት በኋላ መፈፀሙን እናስተውላለን፡-

“እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ስትመጣ እስኪያዩ ድረስ፥ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ አላቸው። ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ልብሱም አንጸባረቀ፤ አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ። ኤልያስና ሙሴም ታዩአቸው፥ ከኢየሱስም ጋር ይነጋገሩ ነበር። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን፦ መምህር ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው። እጅግ ስለ ፈሩ የሚለውን አያውቅም ነበር። ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፥ ከደመናውም፦ የምወደው ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ድንገትም ዞረው ሲመለከቱ ከእነርሱ ጋር ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራውም ሲወርዱ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው። ቃሉንም ይዘው፦ ከሙታን መነሣት ምንድር ነው? እያሉ እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ።” (ማር. 9፡1-10)

2ጴጥሮስ 1፡16-18 ላይ የተጻፈው ቃልም ይህንኑ የሚረጋግጥ ነው፡-

“የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ። ከገናናው ክብር በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን፡፡”

ሐዋርያው ጴጥሮስ “የጌታችን ኃይልና መምጣት” በማለት የገለጸው ከስድስት ቀናት በኋላ የተፈጸመውን የተራራውን ክብር ነበር፡፡ በተጨማሪም ይህ ትንቢት በበዓለ ሃምሳ እለት የክርስቶስ መንግስት በምድር ላይ በሚታይ ሁኔታ መመሥረቱን የሚመለክትም ሊሆን ይችላል (የሐዋርያት ሥራ 2፣ 22፡16-18)፡፡ ስለዚህ ጸሐፊው አውዱን ሳያገናዝብ የሰነዘረው ትችት ቦታ የሚሰጠው አይደለም፡፡

ሰልማን በክርስቶስ ከድንግል መወለድ ያምናልን?

በማስከተል እንዲህ የሚል ፈገግ የሚያስብል ነገር ጽፏል፡-

“ማርቆስ ከሌሎቹ ወንጌላት ቀደም ብሎ እንደተጻፈ ከመታመኑ አንጻር እንደ ማቴዎስና ሉቃስ ኢየሱስ ከማርያም በተዓምር ስለመወለዱ ምንም ነገር አለመጻፉ ምንጫቸው ላይ ጥያቄ እንዲኖር አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኢየሱስን የዘር ሐረግ አለመቁጠሩ ለየት እንዲል አድርጎታል፡፡” (ገፅ 46)

ማቴዎስና ሉቃስ የኢየሱስን ከማርያም በተዓምር መወለድ መዘገባቸው ምንጫቸው ላይ ጥያቄ እንዲኖር የሚያደርገው በምን ሒሳብ ነው? ማርቆስ ኢየሱስ በተዓምር ከድንግል የመወለዱን ታሪክ አለመጻፉ ታሪኩን በጻፉት በማቴዎስና በሉቃስ ምንጭ ላይ ጥያቄ እንዲኖር የሚያደርግ ከሆነ ተቀራራቢ ታሪክ በሚያስነብበው በቁርአን ላይስ ጥያቄ አይፈጥርምን? እንደ ክርስቲያኖች ሁሉ የኢየሱስን በተዓምር ከድንግል መወለድ የሚያምን ሙስሊም ተመሳሳይ ትረካዎችን የሚያስነብቡ መጻሕፍትን ለማጣጣል እንዲህ ያለ ሙግት እንዴት ይጠቀማል? አስገራሚ ነው!

የማርቆስ መዝጊያ

ባጠቃላይ ጸሐፊው የማርቆስ ወንጌልን በተመለከተ አንስቶታል ብዬ የምለው ትኩረት የሚሻ ነጥብ የመጽሐፉን መዝጊያ በተመለከተ ነው (ገፅ 48-49)፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ማርቆስ 16፡9-20 ድረስ የሚገኘውን ክፍል ተዓማኒነት በተመለከተ ወጥ አቋም እንደሌላቸው የታወቀ ነው፡፡ ገሚሶቹ በአብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ ስለተካተተ ተዓማኒ እንደሆነ ሲናገሩ የተቀሩት ደግሞ ይህንን ክፍል ላለመቀበል ተከታዮቹን ምክንያቶች ያቀርባሉ፡-

  • እነዚህ ቁጥሮች ቀዳሚና ይበልጥ ተዓማኒ በሆኑት የግሪክ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ አይገኙም፡፡ በተጨማሪም በቀደመው ላቲን፣ ሢርያክ፣ አርመንያና ኢትዮጵያ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ አይገኙም፡፡
  • ቀለሜንጦስ፣ ኦሪጎንና ኢዮስቢዮስን የመሳሰሉት ብዙ የጥንት አባቶች እነዚህን ቁጥሮች አያውቋቸውም፡፡ ጀሮም ከሞላ ጎደል በእርሱ ዘመን በነበሩት በሁሉም የግሪክ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ አለመገኘቱን አስታውቋል፡፡
  • ይህንን ክፍል የሚያጠቃልሉት ብዙ የእጅ ጽሑፎች አጠራጣሪ መኾኑን ለማሳየት ምልክት ያደርጉበታል፡፡
  • በአንዳንድ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ ሌላ አጠር ያለ የማርቆስ ወንጌል መዝጊያ ይገኛል፡፡
  • አንዳንዶች ደግሞ አጻጻፉና የሰዋሰው ይዘቱ ከተቀረው የማርቆስ ወንጌል ጋር እንደማይመሳሰል ይናገራሉ፡፡ (Norman L. Geisler & Thomas Howe. When Critics Ask: A Popular Hand Book on Bible Difficulties, Victor Books, p. 321-322)

ይህ ክፍል በኦሪጅናል የማርቆስ ወንጌል ውስጥ መገኘት አለመገኘቱ አጠያያቂ እንደሆነ ቢቀጥልም ነገር ግን የያዘው እውነት ከተቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር የሚስማማ ነው፡፡ ስለዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢወጣ ምንም የሚጎድል ትምሕርት የለም፡፡ ያዘለው ትምሕርት በሌሎች ክፍሎች እንደመገኘቱ ደግሞ ባለበት ቦታ ቢቆይ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምሕርት ላይ የሚጨምረው ነገር የለም፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የተጠቀሱት በልሳን የመናገር ስጦታ፣ የጥምቀት ሥርዓትና በእባብ መርዝ ያለመጎዳት ተዓምር በሌሎች ክፍሎች ላይ ተጠቅሰዋል (ሐዋ. 2፡1-21፣ 10፡44-48፣ 19፡1-7፣ 28፡3-5)፡፡ ስለዚህ ምንም የተለወጠ መልእክት ባለመኖሩ ይህ ክፍል የመጽሐፍ ቅዱስ አካል ሆኖ መቆጠር አለመቆጠሩ የእስልምናን የብረዛ ክስ አያረጋግጥም፡፡

የማቴዎስ ወንጌል

የማቴዎስን ወንጌል በተመለከተ እንዲህ ብሏል፡-

“የወንጌሉ ጸሐፊ ደቀ መዝሙሩ ቀራጩ ማቴዎስ እንደሆነ በቤተክርስቲያን ቢነገርም ማስረጃ አልተገኘም፡፡ በጊዜው የኢየሱስ ተከታዮች የአረማይክ ቋንቋ ተናጋሪዎች መሆናቸውና በግሪክኛ የቋንቋ ዘዬ የሐዋርያት ሥራ መባሉ ላይ ተጨማሪ ጥያቄ ፈጥሯል፡፡ ዘመናዊ የታሪክ አጥኚዎች ቀደምት የብራና ጽሑፎችን በምንጭነት በመጠቀም ወንጌሉ ከ125-150 ዓ.ል በአንድ ያልታወቀ ስደተኛ አይሁዳዊ ይገመታል ይላሉ፡፡ በተጨማሪም ከማርቆስ ወንጌል በርካታ ትርክቶችን በማጣቀሻነት መጠቀሙ ይታወቃል፡፡” (ገፅ 49)

ከላይ የሚገኙት ዐረፍተ ነገሮች ከሞላ ጎደል ሐሰት ናቸው፡፡ ወንጌሉ በማቴዎስ የተጻፈ መሆኑ በጥንት ቤተክርስቲያን አበው የተረጋገጠ ሃቅ ነው፡፡ ለዚህም የሚሆኑ በርካታ ማስረጃዎች ይገኛሉ፡፡ በማቴዎስ ጸሐፊነት ዙርያ በቤተክርስቲያን አበው መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የሌለ ሲሆን የቤተክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊያን ወንጌሉን ማቴዎስ እንደጻፈው አረጋግጠዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል 100 ዓ.ም. አካባቢ ፓፒያስ ወንጌሉ በማቴዎስ የተጻፈ መኾኑን ተናግሯል፡፡ 150 ዓ.ም. አካባቢ ኢሬኔዎስ ተመሳሳይ ምስክርነት ሰጥቷል፡፡ ዕውቅ የአዲስ ኪዳን ሊቅ የሆኑት ሜሪል ሲ. ቴኒ ማስረጃዎችን በሙሉ ካጤኑ በኋላ “የማቴዎስ ጸሐፊነት የሚያከራክር አይደለም” በማለት ደምድመዋል፡፡ (ሜሪል ሲ. ቴኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት፣ ገፅ 217-218)

ሰልማን ራሱ ለነዚህ መረጃዎቹ ዋቢ ያደረገው Baker Exegetical Commentary on The New Testament በሚል ርዕስ ዴቪድ ቲዩነር በተባለ ምሑር የተጻፈ መጽሐፍ ሲሆን ደራሲው ገፅ 11 ላይ የወንጌሉን ጸሐፊ ማንነት በተመለከተ የተለያዩ ምሑራንን አስቱያየቶች ከጠቀሰ በኋላ ወንጌላት ከመጀመርያው ጀምሮ የጸሐፊያናቸውን ስሞች ይዘው እንደነበር ድምዳሜውን አስቀምጧል (David L. Tuner. Baker Exegetical Commentary on The New Testament; Baker Academic, Grand Rapids, 2008, p. 11)፡፡ በተጨማሪም ጥንታውያን የማቴዎስ ወንጌል ብራናዎች ስሙን ይዘው መገኘታቸውን ማስረጃ ጠቅሷል (Ibid., p. 12)፡፡ ወንጌሉ በማቴዎስ የተጻፈ መሆኑን የመሰከሩትን ጥንታውያን አበው ስም ዘርዝሯል (Ibid., p. 12)፡፡ ሰልማን የጠቀሰውን መጽሐፍ ገልጦ ቢያነብ ኖሮ ከተሳሳተ ድምዳሜ በዳነ ነበር፡፡ ዳሩ ግን የሆነ ቦታ ስሙን ስላየ ብቻ ጠቀሰ እንጂ ገልጦ ስላላነበበ እንዲህ ያለ የተዛባ መረጃ በማስተላለፍ ራሱን ለትዝብት ዳርጓል፡፡

መች ተጻፈ? የሰልማን የተጭበረበረ የምንጭ አጠቃቀስ

የተጻፈበትን ዘመን በተመለከተ ሰልማን ከ125-150 ዓ.ም. መካከል እንደሆነ በመግለፅ የዴቪድ ቲዩነርን መጽሐፍ በዋቢነት ቢጠቅስም እርሱ በጠቀሰው ገፅ 6-7 ላይ እንዲህ የሚል ነገር አልተጻፈው፡፡ የሰልማን መረጃ ባጠቃላይ በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኝ አይደለም፡፡ እንዲያውም ቲዩነር ወንጌሉ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በኢግናጢዮስ፣ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ ደግሞ ዲዳኬ በተባለ ጽሑፍ መጠቀሱን ዋቢ በማድረግ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን የተጻፈ መሆኑን ማስረጃ አቅርቧል፡፡ ከዚህም በመነሳት ወንጌሉ ቢያንስ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን መገባደጃ አካባቢ የተጻፈ መሆኑ ጥርጥር እንደሌለው ተናግሯል (Ibid., p. 13)፡፡ ለዘብተኛ ሊቃውን ትንቢቶችን ስለማይቀበሉ ኢየሩሳሌም በ70 ዓ.ም. መፍረሷን ከሚናገረው በወንጌሉ ውስጥ ከሚገኘው የጌታ ትንቢት በመነሳት ከኢየሩሳሌም መፍረስ በኋላ በ80 ወይንም 90 ዓ.ም. እንደ ተጻፈ ቢናገሩም ይህንን የማይቀበሉና ከ70 ዓ.ም. በፊት የተጻፈ መሆኑን የሚናገሩ ብዙ ሊቃውንት መኖራቸውን ጠቅሷል፡፡ የነዚህንም ሊቃውንት ስም ዝርዝር አስቀምጧል (Ibid., p. 14)፡፡ ሰልማን የመጽሐፍ ስምና ገፅ በመጥቀስ ጭራሽ በመጽሐፉ ውስጥ ያልተባለ መረጃ ማስነበቡ አሳፋሪ ተግባር ነው፡፡

የሉቃስ ወንጌል

በማስከተል እንዲህ ሲል ጽፏል፡-

“ሉቃስ የወንጌሉና የሐዋርያት ስራ ጸሐፊ እንደሆነ የሚነገር ሲነገር ነገርግን በሁለቱም መጽሐፍት ስሙ ተጠቅሶ አናገኘውም፡፡ ፀሐፊው በኢየሱስ የህይወት ዘመን እንዳልነበረም በመግቢያው ላይ ያትታል፡፡ ወንጌሉን የፃፈው ቴዎፍሎስ ለሚባል ወዳጁ ሲሆን የቴዎፍሎስም ይሁን የሉቃስ ማንነት ሊታወቅ አልቻለም፡፡ በተለምዶ ሉቃስ የጳውሎስ የግል ሀኪም እንደነበረ ቢነገርም ማስረጃ የለውም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በገፅ 15 ላይ እንዳሰፈረው ሉቃስ የግሪክ ስም በመሆኑ በግሪኩ ዓለም የኖረና ከአህዛብ ወገን እንደነበረ ሊያመለክት ይችላል ሲል ይገልፃል፡፡ ዘመኑም ከ90-110 ዓ.ል. እንደሆነ ይገመታል፡፡ በሉቃስ ወንጌል ሁሉንም የማርቆስ ትርክት የምናገኛቸው ሲሆን ወንጌሉና የሐዋርያት ስራ የአዲስ ኪዳንን 27% ይሸፍናሉ፡፡ ይህ ማለት ማንነቱ የማይታወቅ ሰው 1/4ኛውን የአዲስ ኪዳን ክፍል ፅፏል ማለት ነው፡፡” (ገፅ 49-50)

ይህ ሐተታ እውነትን ከሐሰት የቀላቀለ ነው፡፡ የሉቃስ ስም በወንጌሉና በሐዋርያት ሥራ ውስጥ አለመጠቀሱ እውነት ነው፡፡ ጌታችን በምድር ላይ ሳለ ደቀ መዝሙር አለመሆኑ እንዲሁም የወንጌሉና የሐዋርያት ሥራ ተደራሲ የነበረው የቴዎፍሎስ ማንነት አለመታወቁም እውነት ነው፡፡ ነገር ግን “የሉቃስ ማንነት ሊታወቅ አልቻለም” የሚለው አባባል መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ በሚያውቅ ሰው የሚነገር አይደለም፡፡ የሉቃስን ማንነት በተመለከተ በአዲስ ኪዳን ውስጥም ሆነ ከአዲስ ኪዳን ውጪ መረጃዎችን እናገኛለን፡፡ የሐዋርያው ጳውሎስ ወዳጅና በሙያው ኀኪም እንደነበር ተጽፏል (ፊልሞና 1፡24፣ ቆላስይስ 4፡14)፡፡ አንዳንድ ምሑራን ከዚህ በመነሳት የሐዋርያው ጳውሎስ የግል ኃኪም ሊሆን እንደሚችል ቢገምቱም ኃኪም መሆኑ እንጂ የጳውሎስ የግል ኃኪም መሆኑ አልተገለጸም፡፡ “እኛ ክፍሎች” (We Sections) ተብለው የሚታወቁት የሐዋርያት ሥራ ክፍሎች ሉቃስ በፊልጵስዩስ ከተማ ይኖር እንደነበር፣ ከጳውሎስ ጋር አብሮ ወደ ኢየሩሳሌም መኼዱንና ወደ ሮም አብሮት መጓዙን ያስረዳሉ (16፡10-17፣ 2O፡5-I5፣ 21፡1-18፣ 27፡1-28፡16)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ 4፡10-14 ላይ አርስጦኮስ፣ ዮስጦስና ማርቆስ “ከተገረዙት ወገን” አብረውት የሚያገለግሉ ብቸኛ ወንድሞች መኾናቸውን ከገለፀ በኋላ ኤጳፍራ፣ ሉቃስና ዴማስን መጥቀሱ ሉቃስ አይሁዳዊ ላለመኾኑ እንደ ማስረጃ ይጠቀሳል፡፡

ቅዱስ ሉቃስ መጻሕፍቱን ያዘጋጀው ሐዋርያት በሕይወት ሳሉ ነበር

አሁን በእጃችን የሚገኘው ቀዳሚ የሆነው የሉቃስ ወንጌል የእጅ ጽሑፍ (180-200 ዓ.ም.) የሉቃስን ስም ይዟል፡፡ (Robert H. Gundry. A Survey of the New Testament, 3rd Edition, The Paternoster Press, Carlise UK, 1994, p. 89) “የሙራቶራ ቀኖና” በመባል የሚታወቀው በ170 ዓ.ም. አካባቢ የተጻፈው ጽሑፍና የቤተክርስቲያን አባት የሆነው የኤሬኔዎስ ጽሑፍ (180 ዓ.ም.) የወንጌሉ ጸሐፊ ሉቃስ መኾኑን ያረጋግጣሉ፡፡ (Raymond E. Brown. An Introduction to the New Testament; Anchor Bible, 1st Edition, 1997, P. 267)

የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት መቼ እንደተጻፉ ለማወቅ የተለያዩ ውጭያዊና ውስጣዊ መረጃዎችን ይጠቀማሉ፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሉቃስ ወንጌል ሁለተኛ ክፍል መኾኑ የሚታወቅ ሲሆን ዝርዝር ታሪካዊ ክስተቶችን በማካተቱ ምክንያት መቼ እንደተጻፈ ለማወቅ የሚያስችሉ በቂ መረጃዎችን ይሰጣል፡፡ ኮሊን ሒመር የተሰኙ የሮም ታሪክ ሊቅ የሐዋርያት ሥራ በ61 እና 62 ዓ.ም መካከል የተጻፈ መኾኑን የሚያሳዩ 17 ምክንያቶችን ዘርዝረዋል፡፡ ወንጌሉ ደግሞ ቀደም ሲል የተጻፈ በመኾኑ (ሉቃ. 1፡1 እና የሐዋርያት ሥራ 1፡1 ያነፃፅሩ) ቢያንስ ከ61 ዓ.ም. በፊት እንደተጻፈ መናገር ይቻላል፡፡ (Norman Geisler. Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 5-6)

ቅዱስ ሉቃስ በዓለማውያን የታሪክ አጥኚዎች ሳይቀር የተመሰከረለት ተዓማኒ ጸሐፊ ነው

ሰር ዊልያም ራምሰይ የተባሉ እንግሊዛዊ የታሪክ ምሑር የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ተዓማኒነት እንደሌላቸው የሚያምኑ ሰው ነበሩ፡፡ በተለይም ደግሞ የሉቃስ ጽሑፍ የሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሁለተኛው ክፍለ ዘመን ሥራ እንደሆነ አጥብቀው ያምኑ ነበር፡፡ ነገር ግን እኚህ ምሑር በትንሹ ኢስያ (Asia Minor) ውስጥ የተለያዩ የሥነ ቁፋሮ ግኝቶችን ሲመረምሩ ሳሉ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው የሚገኙ ብዙ ነገሮች እውነት መሆናቸውን የሚያረጋግጡ የትየለሌ ማስረጃዎችን አገኙ፡፡ እኚህ ምሑር ሉቃስ መጽሐፉን የጻፈው በመጀመርያው ምዕተ ዓመት (ሐዋርያት በነበሩበት ዘመን) መኾኑን ብቻ ሳይኾን ሉቃስ ከታላላቅ  የታሪክ ጸሐፊያን መካከል መመደብ እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በተዓማኒነት ረገድ ከሉቃስ የላቀ ሰነድ ሊኖር እንደማይችል ድምዳሜያቸውን አስቀምጠዋል፡፡ (Sir William Ramsay. Saint Paul: the Traveller and the Roman Citizen, New York, G. P. Putnam’s Sons, 1896)

[Dr. Ramsey stated: “Luke is a historian of the first rank; not merely are his statements of fact trustworthy … this author should be placed along with the very greatest of historians.”] Ramsey further said: “Luke is unsurpassed in respects of its trustworthiness.” (Josh McDowell. The Best of Josh Mcdowell: A Ready Defense, pp. 108-109)

የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ቃለ እግዚአብሔር መሆኑ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ተመስክሮለታል

በተጨማሪም የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች ጽሑፉን እንደ እግዚአብሔር ቃል በመቀበል መስክረውለታል፡፡ ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ ሙሴ የጻፈውንና ሉቃስ የጻፈውን አንድ ላይ አጣምሮ በማስቀመጥ ሁለቱም መጻሕፍት እኩል ቅዱሳት መጻሕፍት መሆናቸውን አረጋግጧል!

“መጽሐፍ፦ የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፥ ደግሞ፦ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል ይላልና፡፡” 1ጢሞቴዎስ 5፡18፡፡

“የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” የሚለው ዘዳግም 25፡4 ላይ የሚገኝ ሲሆን “ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል” የሚለው ደግሞ ሉቃስ 10፡7 ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የሚያሳየን የሐዋርያት ዘመን ከማለፉ በፊት ቢያንስ የሉቃስ ወንጌል ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እኩል ተቀባይነት ማግኘቱን ነው፡፡ ሐዋርያው እንደ ዘዳግም ሁሉ የሉቃስ ወንጌልን በስም አለመጥቀሱ በወቅቱ የሉቃስ ወንጌል በክርስቲያኑ ማሕበረሰብ መካከል በሚገባ የሚታወቅ እንደነበረ ያሳያል፡፡ ስለዚህ የሉቃስ ወንጌል የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እራሱ አረጋግጧል ማለት ነው! (አዲሱ መደበኛ ትርጉም 1ጢሞቴዎስ 5፡18 የግርጌ ማጥኛ ገፅ 1844 ይመልከቱ፡፡)

የዮሐንስ ወንጌል

በማስከተል እንዲህ ሲል ጽፏል፡-

“የዘብዴዎስ ልጅ ዮሐንስ በወንጌሉ ውስጥ ‹‹ተወዳጁ ደቀ መዝሙር›› በሚል ቅፅል ስም የተጠራ ሲሆን ነገርግን ራሱን ‹‹ተወዳጁ ደቀ መዝሙር›› እያለ መጥራቱ ፀሐፊው ዮሐንስ ስለመሆኑ አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡ የዮሐንስ ወንጌል በበርካታ ታሪኮቹና በአፃፃፍ ስልቱ ከሌሎቹ ልዩ ነው፡፡ በዮሐንስና በሌሎቹ ወንጌላት መካከል ስላለው የታሪክ ልዩነት የፃፉት ሜሪል ሲ. ቴኒ የተባሉት በኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን የኮሙኒኬሽን ስነ ፅሑፍ መምሪያ ገፅ 281 ላይ ‹‹በዮሐንስ ወንጌልና በሌሎቹ ሶስት ወንጌላት መካከል በግልፅ የሚታይ ልዩነት በመኖሩ የወንጌሉ ተዓማኒነት አጠያያቂ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል›› ብለዋል፡፡” (ገፅ 50)

የመጀመርያ ነገር ዮሐንስ ራሱን “ተወዳጁ ደቀ መዝሙር” በሚል ቅፅል ስም አልጠራም፤ ነገር ግን “ኢየሱስ ይወደው የነበረ” በማለት ነው፡፡ ራስን “ተወዳጅ” በማለት በመጥራትና “እገሌ ይወደኛል” በማለት በመጥራት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ የመጀመርያው ራስን ማሞካሸት ሲሆን ሁለተኛው ግን የሃቅ ንግግር (Statement of Fact) ነው፡፡ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ ራሱን መግለፁ ጸሐፊው እርሱ አለመሆኑን አያመለክትም፡፡ በሦስተኛ ወገን ራስን ማመልከትም በጸሐፊያን ዘንድ የተለመደ በመሆኑ ጸሐፊው ዮሐንስ ላለመሆኑ ማስረጃ አይሆንም፡፡

ሰልማን የቴኒን ሐሳብ ቆርጦ በመጥቀስ ምሑሩ ለማለት ያልፈለጉትን አስብሏቸዋል፡፡ የአዲስ ኪዳን ሊቅ የሆኑት ዶ/ር ቴኒ የተለያዩ ምሑራን የሚሰነዝሯቸውን አስተያየቶች ባገናዘበ መልኩ ከላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ ቢያሰፍሩም ነገር ግን የዮሐንስ ወንጌል ተዓማኒ መኾኑንና በዮሐንስ በራሱ የተጻፈ መኾኑን በተመለከተ የደረሱበትን ድምዳሜ እንዲህ አስቀምጠዋል፡፡

“አራተኛው ወንጌል የተጻፈው በሐዋርያው ዮሐንስ ሳይሆን ስሙ ዮሐንስ ተብሎ በሚጠራ አንድ ማንነቱ የማይታወቅ ሰው ነው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ መሠረት የለሽ ነው፡፡ ከኢራንየስ ዘመን ጀምሮ የነበሩ የቤተክርስቲያን አበው እንደመሰከሩት የዚህ ወንጌል ጸሐፊ ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው፡፡ የእስክንድርያው ቀለሜንጦስ (190 ዓ.ም.)፣ ኦሪጎን (220 ዓ.ም.)፣ ሂጶሊጦስ (225 ዓ.ም.)፣ ጠርጡሊያኖስ (200 ዓ.ም.) የሙራቶራውያን ጽሑፍ (170 ዓ.ም.) በአንድነት የሚስማሙት የዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ የዘብዴዎስ ልጅ ዮሐንስ መኾኑን ነው፡፡” (ሜሪል ሲ.ቲኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት፣ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስታን የኮሚዩኒኬሽንና ስነ ጹሑፍ መምሪያ፣ ገጽ 282)

በተጨማሪም ዶ/ር ቴኒ የወንጌሉ ጸሐፊ የኢየሱስ ደቀመዝሙር የነበረ መኾኑን የሚያሳዩ አራት ማስረጃዎችን ከወንጌሉ ይዘት በመነሳት አስቀምጠዋል፡፡ የወንጌሉ ጸሐፊ ዮሐንስ ስለመኾኑ ፅኑ እምነት መኖሩንም አበክረው ይናገራሉ፡፡ (ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 282-283)

የጠፉ “ወንጌላት”

ሰልማን እንዲህ ሲል የተለመደውንና ማስረጃ አልባው እስላማዊ ፕሮፓጋንዳ ይነዛል፡-

“ከላይ በመግቢያው ላይ እንደጠቆምነው የባዛንታየኑ ንጉስ ቆስጠንጢኖስ በ325 ዓ.ል.የኒቂያን ጉባኤ ከማካሄዱ በፊት ከአራቱ ውጭ በርካታ አይነት ወንጌሎች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ነገርግን ቆስጠንጢኖስ ለአገዛዙ ይመቸው ዘንድ ከየአገራቱ ጳጳሳትን በመጥራት ተመሳሳይ የሆኑትን አራቱን ወንጌላት ብቻ በማፅደቅ ሌሎቹ እንዲቃጠሉ እንዳደረገ በታሪክ ተዘግቧል፡፡ ከእነዚህ ከጠፉት ወንጌሎች መካከል ጥቂቶቹን ለአብንነት እንይ…” (ገፅ 51)

በየትኛው ታሪክ ውስጥ? ማስረጃ የለም! በእንቶ ፈንቶ ጉዳዮች የተለያዩ የእንግሊዘኛ መጻሕፍትን በመጥቀስ ብዙ ገፆችን ያሳለፈው ሰልማን ይህንን ማስረጃ የሚሻ ትልቅ ጉዳይ ሲናገር ግን አንዳችም ምንጭ መጥቀስ አልቻለም፡፡ የዚህ ምክንያቱ አንድና አንድ ነው፡፡ ቀደም ሲል እንዳልነው መሰል ተረቶች ሙስሊም ፕሮፓጋንዲስቶችና ቢጤዎቻቸው በሚጽፏቸው እንዲህ ያሉ መጻሕፍት ውስጥ እንጂ በምሑራዊ ምንጭ ውስጥ ሊገኙ አይችሉም፡፡ በኒቅያ ጉባኤ ላይ የመጻሕፍ ምርጫ መደረግ ይቅርና ርዕሱ እንኳ ስለመነሳቱ ቅንጣት ታክል የታሪክ ማስረጃ የለም፡፡ አለ የሚል ሙስሊም ካለ ፊት ለፊት ይውጣና ማስረጃውን ያቅርብ! የጥንት ክርስቲያኖች መጻሕፍትን የማቃጠል ታሪክ አልነበራቸውም! ቁርአናቸውንና ሌሎች መጻሕፍትን የማቃጠል ታሪክ ያላቸው ሙስሊሞች እንጂ ክርስቲያኖች አይደሉም! እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ሙስሊም ሰባኪያን የተወቀሰ ህሊና (Guilty Conscious) ስላላቸው እስልምና የሚሸማቀቅበትን ታሪክ በክርስትና ላይ ለማላከክ ይጥራሉ፡፡

ይህንን ዐይን ያወጣ ቅጥፈት ካስነበበን በኋላ የቶማስ ወንጌል፣ የጴጥሮስ ወንጌል፣ የይሁዳ ወንጌልና የማርያም ወንጌል የተባሉትን በመጥቀስ እያንዳንዳቸው ከሁለተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኋላ የተጻፉ መሆናቸውን ገልጿል (ገፅ 51)፡፡ መጻሕፍቱ በሐዋርያት ዘመን ሳይሆን ሐዋርያት ካለፉ ከብዙ ዘመናት በኋላ የተጻፉ መሆናቸው በራሱ ሐሰተኛ መጻሕፍት መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ ሰልማን በዚህ ቦታ በክርስትና ላይ ለማቅረብ የፈለገው ሙግት ምን እንደሆነ ግልፅ አይደለም፡፡ ይልቅ የቁርአን ደራሲ እነዚህን ከመሳሰሉ የኋለኛው ዘመን ሥራዎች ላይ የተወሰዱ የተለያዩ ሐሳቦችን “ከሰማይ ወረደ” በተባለው ቁርአን ውስጥ ማካተቱ የሐሳዊነቱ ማረጋገጫ ነው፡፡ ቁርአንና ኖስቲሳውያን የሚለውን ጽሑፍ ያንብቡ፡፡

የበርናባስ “ወንጌል”

በመጨረሻም “የበርናባስ ወንጌል” የተባለውን መጽሐፍ የጠቀሰ ሲሆን እንዲህ ብሏል፡-

“ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው በርናባስ እንደፃፈው ይነገራል፡፡ ወንጌሉ የኢየሱስን ተልዕኮ በተመለከተ ከአራቱ ወንጌላት የሚለይ ትምህርት የያዘ ሲሆን ከኢስላም አስተምህሮት ጋር የሚስማማ ነው፡፡ የጳውሎስን ስብከት ውድቅ በማድረግ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ሳይሆን ነቢይ እንደሆነ ሲገልፅ ሙሐመድ (ዐሰወ) የፈጣሪ መልዕክተኛ መሆናቸውን በስም ይጠቅሳል፡፡ በጳውሎስና በበርናባስ መካከልም ብዙ ጥልና ክርክር እንደነበረም በሐዋ 15፡2 ላይ ተገልጿል፡፡” (ገፅ 51-52)

ሰልማን ንባብን ከመለማመድ አልፎ መጽሐፍ ለመጻፍ ያልበቃ ሰው መሆኑ ይህ አባባሉ በጥሩ ሁኔታ ያሳያል፡፡ ሲጀመር በርናባስ እንደ ጳውሎስ ሁሉ ቤተክርስቲያን ከተመሠረተች በኋላ የሐዋርያነትን ሹመት የተቀበለ አገልጋይ እንጂ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል አንዱ አልነበረም (የሐዋርያት ሥራ 4:36-37)፡፡ የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ስም ዝርዝር የሚታወቅ ሲሆን “በርናባስ” የሚል ስም የለበትም፡፡ ሲቀጥል ብዙ ጥልና ክርክር የተከሰተው በጳውሎስና በበርናባስ መካከል ሳይሆን አማኞ እንዲገረዙ ሲያስገድዱ በነበሩት ወገኖችና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል ነበር፡፡ እናንብበው፡-

“አንዳንዶችም ከይሁዳ ወረዱና፦ እንደ ሙሴ ሥርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም ብለው ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር። በእነርሱና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል ብዙ ጥልና ክርክር በሆነ ጊዜ፥ ስለዚህ ክርክር ጳውሎስና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያት ወደ ሽማግሌዎችም ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ዘንድ ተቈረጠ።” (የሐዋርያት ሥራ 15፡1-2)

ጳውሎስና በርናባስ አንድ ላይ ሆነው ከይሁዳ ከመጡት የግዝረት መምህራን ጋር ክርክር ውስጥ ገቡ፡፡ ታሪኩ ይቀጥልና ይህ ጉዳይ ለኢየሩሳሌም ጉባኤ መሰብሰብ ምክንያት እንደሆነ ይነግረናል፡፡ በጉባኤው ላይ የጳውሎስና የበርናባስ አቋም ጸድቆ የግዝረት መምህራኑ ውድቅ ከሆነ በኋላ ወደ አንፆኪያ ተመልሰው አብረው ማገልገል ቀጠሉ፡-

“ጳውሎስና በርናባስም ከሌሎች ከብዙ ሰዎች ጋር ደግሞ የጌታን ቃል እያስተማሩና ወንጌልን እየሰበኩ በአንጾኪያ ይቀመጡ ነበር።” (የሐዋርያት ሥራ 15፡35)

በጳውሎስና በበርናባስ መካከል መለያየት የተፈጠረው ከዚህ በኋላ ሲሆን ከአስተምህሮ አለመጣጣም ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም፡፡ ልዩነት የተፈጠረው ማርቆስ ከእነርሱ ጋር ወደ አገልግሎት በመሄድ አለመሄዱ ጉዳይ ነበር፡-

“ከጥቂት ቀንም በኋላ ጳውሎስ በርናባስን፦ ተመልሰን የጌታን ቃል በተናገርንበት በየከተማው ሁሉ ወንድሞችን እንጐብኛቸው፥ እንዴት እንዳሉም እንወቅ አለው። በርናባስም ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስን ደግሞ ከእነርሱ ጋር ይወስድ ዘንድ አሰበ፤ ጳውሎስ ግን ይህን ከእነርሱ ጋር ሊወስድ አልፈቀደም፥ ከእነርሱ ዘንድ ከጵንፍልያ ተለይቶ ነበርና፥ ወደ ሥራም ከእነርሱ ጋር አልመጣም ነበርና። ስለዚህም እርስ በርሳቸው እስኪለያዩ ድረስ መከፋፋት ሆነ፥ በርናባስም ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ። ጳውሎስ ግን ሲላስን መረጠ፥ ወንድሞችም ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ከሰጡት በኋላ ወጣ፡፡” (የሐዋርያት ሥራ 15፡36-40)

የበርናባስ የእህቱ ልጅ የነበረው ማርቆስ በወሳኝ ሰዓት ጥሏቸው ስለተመለሰ ጳውሎስ በማርቆስ መተማመን አልቻለም፡፡ በርናባስ ግን የእህቱ ልጅ በመሆኑ ምክንያት ማርቆስን ትቶ መሄድ አልፈለገም፡፡ ስለዚህ በሁለቱ መካከል መለያየት ስለተፈጠረ አብረው መጓዝ ተሳናቸው፡፡ ይህ ከአስተምህሮ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም፡፡ ኋላ ላይ ጳውሎስና ማርቆስ ተስማምተው አብረው ማገልገላቸውን ቀጥለዋል (2ጢሞ. 4፡11፣ ፊል. 1፡24)፡፡ በሌላ ጊዜ ጳውሎስ ስለ በርናባስ አገልግሎት በጥሩ ሁኔታ ተናግሯል (1ቆሮ. 9፡6-12)፡፡

“የበርናባስ ወንጌል” ዕውቀት አጠር በሆኑ ሙስሊሞች ዘንድ እንደ ትክክለኛ ወንጌል ቢታይም ትክክለኛ ወንጌል መሆኑን የሚቀበል ምሑር የለም፡፡ ዕውቀት ያላቸው ሙስሊሞች እንኳ እንደ ትክክለኛ መጽሐፍ አይቀበሉትም፡፡ የኢስላም ኢንሳይክሎፒድያ እንዲህ ይላል፡-

“የበርናባስን ወንጌል በተመለከተ የመካከለኛው ዘመን ፈጠራ መሆኑ የሚያከራክር አይደለም … በመካከለኛው ዘመን ብቻ የሚታወቁ ብዙ ሐሳቦችን ያለ ቦታቸው አስገብቷል… በአጻጻፉ የበሃኡላህ መጽሐፍ ቁርአንን ለመምሰል እንደሚሞክረው ሁሉ ወንጌላትን ለመምሰል የሚሞክር ከሁለት ያጣ ጽሑፍ ነው፡፡” (Cyril Glassé, “Barnabas, Gospel of.” The Concise Encyclopedia of Islam, 2013, p. 90)

የበርናባስ ወንጌል በመካከለኛው ዘመን የተጻፈ ሐሰተኛ ድርሳን ስለመሆኑ በርካታ ውስጣዊና ውጭያዊ ማረጋገጫዎች አሉ፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ብቻ ሳይሆን ከቁርአንም ጋር የሚጋጭ ሃይማኖታቸውን የሚያውቁ ሙስሊሞች ሊያፍሩበት የሚገባ መጽሐፍ ነው፡፡ ለበለጠ መረጃ ተከታዩን ጽሑፍ ያንብቡ፡፡ የበርናባስ ወንጌል እውነተኛ ወንጌል ነውን?

የበርናባስ ወንጌል ቁርአንንም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ጠንቅቆ ባላወቀ ሰለምቴ በመካከለኛው ዘመን የተጻፈ የተጭበረበረ ድርሳን ሲሆን በብዙ ሊቃውንት ድምዳሜ መሠረት ጸሐፊው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥልጣን ባለማግኘቱ ምክንያት የተበሳጨ ሰው ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ የተሳሳተ መነሻ ያላቸው ወገኖች የቀድሞ ሃይማኖታቸውን የጎዱና አዲሱን ሃይማኖታቸውን የጠቀሙ መስሏቸው የሚጽፏቸው ጽሑፎች ሊጠቅሙት ያሰቡትን ሃይማኖት የሚጎዳ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ እንደ “የበርናባስ ወንጌል” ደራሲ ሁሉ የኛውም ሰልማን በተሳሳተ መነሻ ከክርስትና ወጥቶ እስልምናን በመቀበል ክርስትናን የጎዳና እስልምናን የጠቀመ መስሎት ያለ በቂ ዕውቀት መጽሐፍ ጻፈ፤ ሌሎች ሙስሊም ሰባኪያንም አራገቡለት፡፡ ምላሻችንን ካነበበ በኋላ ግን ይህ የተሳሳተ ውሳኔ በራሱና በእስልምና ላይ እያደረሰ ያለው ኪሳራ ከትርፉ ጋር የማይመጣጠን መሆኑ እንደሚገለጥለት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ንቁ! ሙስሊም ሰባኪያን ሐሰተኞች ናቸው!

ይቀጥላል…


ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነውእስልምናስ?

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ