ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነው! እስልምናስ? የመጽሐፍ ሒስ – ክፍል 6

ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነው! እስልምናስ?

የመጽሐፍ ሒስ – ክፍል 6

ርዕስ – ንቁ! ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነውን?

ደራሲ – ሰልማን ኮከብ

የታተመበት ዘመን – 2010

አሳታሚ – አልተገለፀም

የገፅ ብዛት – 270

 

ለሰልማን የፕሮፓጋንዳ መጽሐፍ ምላሻችንን ካቆምንበት እንቀጥላለን፡፡

መልዕክታት

የሁሉም ጸሐፍት ማንነት አይታወቅም?

አቶ ሰልማን መልዕክታትን በተመለከተ እንዲህ ይለናል፡-

“እንደ ጥቅል ስናየው የሁሉም መልዕክት ፀሐፊዎች ማንነት በግልፅ አይታወቅም፡፡ አብዛኛዎቹን መልዕክቶች ፃፈ የተባለው ጳውሎስም በመጽሐፍቱ መግቢያ ስሙ ከመጠቀሱ ውጭ ትክክለኛ የጳውሎስ ስራዎች ይሁኑ ወይንም በብዕር ስን የተፃፉ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡” (ገፅ 52)

የአዲስ ኪዳንን ጸሐፊያን ማንነት በተመለከተ በክርስቲያንም ሆነ በለዘብተኛ ሊቃውንት የተጻፉ በርካታ መጻሕፍትን አንብቤያለሁ ነገር ግን በድፍረት እንዲህ ብሎ የጻፈ ወይንም የተናገረ አንድም ጸሐፊ አላየሁም፡፡ ክርስትናን በመተቸት ከሚታወቁት የዘመናችን የአዲስ ኪዳን ምሑራን መካከል አንዱና ሙስሊሞች ደጋግመው የሚጠቅሱት ባርት ኤህርማን እንኳ ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክታት መካከል ስድስቱን ማለትም ሮሜ፣ 1ቆሮንቶስ፣ 2ቆሮንቶስ፣ ገላቲያ፣ ፊልጵስዩስ፣ 1ተሰሎንቄ እና ፊልሞና በጳውሎስ የተጻፉ መሆናቸው የማያጠራጥር (Undisputed Pauline Epistles) በማለት መድቧቸዋል፡፡ (Bart D. Ehrman, The New Testament:  Historical Introduction; Second Edition, Oxford University Press, 200, p. 262) የሰልማን አባባል በለዘብተኛ ምሑራን ዘንድ እንኳ ተቀባይነት የሌለው ያላዋቂ ንግግር ነው፡፡

በማስከተል እንዲህ ሲል ጽፏል፡-

“ይሁን እንጅ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ዕብራውያንን ጨምሮ 7 መልዕክቶች በይዘታቸውና በአፃፃፍ ስልታቸው ከሌሎቹ የጳውሎስ ስራዎች ጋር የማይዛመዱ በመሆናቸው የጳውሎስ ተማሪዎች ፅፈዋቸው ሊሆን እንደሚችል መላምት አለ፡፡” (ገፅ 52)

ቀደም ሲል የሁሉም መልዕክታት ጸሐፊያን ማንነት በግልፅ አለመታወቁን የገለጸ ሲሆን አሁን ደግሞ የጳውሎስ ጽሑፎች መኖራቸውን ተቀብሎ ሰባቱን መልዕክታት ከእነርሱ ጋር በማነጻጸር ይናገራል፡፡ ሰልማን በቀደመው አባባሉ እንደገለጸው “የሁሉም መልዕክታት ጸሐፊዎች ማንነት በግልፅ የማይታወቅ” ከሆነ “7 መልዕክቶች በይዘታቸውና በአጻጻፍ ስልታቸው ከሌሎቹ የጳውሎስ ሥራዎች ጋር የማይዛመዱ በመሆናቸው” የሚለው አባባል ትርጉም አይሰጥም፡፡ ለዘብተኛ ምሑራን ስድስቱ መልዕክታት በጳውሎስ የተጻፉ መሆናቸውን ስለተቀበሉ ነው እንዲህ ያሉ ንግግሮችን የሚጠቀሙት፡፡ ነገር ግን ሰልማን ገና ከጅምሩ የሁሉም መልዕክታት ጸሐፊያን ማንነት በግልፅ እንደማይታወቅ ስለደመደመ “ከሌሎቹ የጳውሎስ ሥራዎች ጋር የማይዛመዱ” የሚለውን አባባል መጠቀሙ ዝም ብሎ ወደ አእምሮው የመጣውን ሐሳብ ከመጻፍ በዘለለ በማስተዋል ሆኖ ሲጽፍ እንዳልነበር ያመለክታል፡፡

የተለያዩ መልዕክታትን በማነጻጸር የጸሐፊያንን ማንነት በጥርጣሬ የሚያየው አመለካከት የቅርፅ ሕየሳ (Form Criticism) ላይ የተመሠረተ ሲሆን በአሥራ ዘጠነኛው ክ.ዘ በለዘብተኛ ሊቃውንት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተግባራዊ የተደረገ ዘዴ ነው፡፡ ሆኖም ከዕብራውያን መልዕክት በተረፈ ሌሎቹ መልዕክታት በጳውሎስ የተጻፉ መሆናቸውን በግልፅ ይናገራሉ፡፡ ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ጀምረው የነበሩት አበው መልዕክታቱ የጳውሎስ መሆናቸውን በማረጋገጥ ጽፈዋል፡፡ በየትኞቹም አብያተ ክርስቲያናት ቀኖናነታቸው አጠራጣሪ ሆኖ አያውቅም፡፡ ይህ ሁሉ ማስረጃ ባለበት ሁኔታ ለዘብተኛ ሊቃውንት ሥነ ጽሑፋዊ ይዘታቸውን በመመልከት በጳውሎስ የተጻፉ አለመሆናቸውን ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ሆኖም የአንድ ሰው ጽሑፍ ሥነ ጽሑፋዊ ቅርፅ እንደየ ጽሑፉ ዓይነት፣ ዓላማና የተጻፈበት ዘመን ሊለያይ መቻሉ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ምን መምሰል እንዳለበት የሚናገሩትን የቲቶና የጢሞቴዎስ መልዕክታት ነገረ መለኮታዊ አስተምሕሮን ለመተንተን ከተጻፉት የሮሜና የገላቲያ መልዕክታት ጋር በማነጻጸር ስላልተመሳሰሉ በአንድ ሰው እንዳልተጻፉ መናገር አሳማኝ አይደለም፡፡

ሳይማር አስተማሪ የሆነው ጳውሎስ ወይስ ሙሐመድ?

ጸሐፊው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከአሳዳጅነት ወደ ቤተክርስቲያን መሥራችነት የተለወጠበትን ታሪክ በአጭሩ ከነገረን በኋላ ገና ከመለወጡ በቅፅበት የወንጌል ሰባኪ መሆኑን በተመለከተ ቅሬታ የገባው በሚያስመስል አኳኋን ይናገራል፡፡ “ሳይማር እንዴት ሰባኪ ሆነ” የሚል ጥያቄ ማንሳት እንደፈለገ ግልፅ ነው (ገፅ 53)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ብሉይ ኪዳንን ጠንቅቆ የተማረ ሊቅ ነበር፡፡ ሲያስተምርም ያሕዌ እግዚአብሔር ለቅዱሳን ነቢያት የሰጠውን ብሉይ ኪዳንን በስፋት እየጠቀሰና እየተነተነ ነበር፡፡ ይልቅ “ሳይማር እንዴት ሰባኪ ሆነ” የሚለው ጥያቄ በስማ በለው የሰማቸውን የአፖክሪፋ ታሪኮች ከእውነተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ጋር እያማታ ሲሰብክ የኖረውን ሙሐመድን የሚመለከት ነው፡፡

እንዲህ ሲልም ይቋጫል፡-

“ይህንን የጳውሎስ የመገለጥ ታሪክ የሚነግረን የሐዋርያት ስራ ፀሐፊ ደግሞ ሉቃስ እንደሆነ ቀደም ብለን የጠቀስነው ሲሆን ከሉቃስ ማንነት አለመታወቅ ጋር ይህ ለህሊና የሚጎረብጥ የጳውሎስ መገለጥ ሲጨመርበት ታሪኩ ምን ያህል አጠራጣሪ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡” (ገፅ 53)

የሉቃስን ማንነት በተመለከተ ሰልማን ለቀጠፈው ቅጥፈት ባለፈው ክፍል መልስ የሰጠን በመሆኑ ራሳችንን መድገም አያሻንም፡፡ ነገር ግን አንድ ሙስሊም የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን መለኮታዊ መገለጥ “ለኅሊና የሚጎረብጥ” በሚል አባባል ሲገልፅ ከመስማት በላይ በዚህች ምድር ላይ አስቂኝ ነገር የለም፡፡ የሙሐመድን የሒራ ዋሻ መገለጥ መለኮታዊ አድርጎ የተቀበለ ሰው በየትኛው ኅሊናው መገለጥን መመዘን እንደሚችል ማሰብ ያዳግታል፡፡ ሙሐመድ መገለጡ ኅሊናውን ስለጎረበጠው መሰለኝ በዋሻው ውስጥ ተገልጦለት አፍኖ ያስጨነቀው አካል ሰይጣን መሆኑን ያሰበው፡-

ተከታዮቹ እስላማዊ ምንጮች ሙሐመድ በዋሻው ውስጥ ከገጠመው ነገር የተነሳ ያደረበትን ፍርሃት ይናገራሉ፡-

ሲራ ኢብን ሳድ ቅጽ 1፣ ክፍል 1.45.4

ኸድጃ ሆይ ብርሃን አይቻልሁ ድምጽም ሰምቻለሁ እና ጠንቋይ እንዳልሆን ፈራሁ አሉ፡፡…

ሙስናድ አሕመድ ቢን ሐንባሊ ቅጽ 3፣ ቁጥር 2845

ነቢዩ ለኸድጃ እንዲህ አሏት፡- “ብርሃን አይቻለሁ ድምጽም ሰምቻለሁ፤ ምናልባት ውስጤ በጂን ቁጥጥር ውስጥ ሥር ተይዞ እንዳይሆን ፈራሁ አሏት፡፡…”

ሲራ ኢብን ሳድ ቅጽ 1, ክፍል 1.45.3

ኸድጃ ሆይ…በአላህ ጣኦትና ጠንቋይ እንደምጠላ ምንም ነገር አልጠላም፤ እናም እኔው ራሴው ጠንቋይ እንዳልሆን ፈራሁ አሉ፡፡

ለበለጠ መረጃ ሙሐመድ አብድ ወረሱል አል-ሸይጧን! ሙሐመድና አጋንንታዊ ልምምዶቹ በሚል ርዕስ የተጻፈውን ጽሑፍ ያንብቡ፡፡

የክርስቶስና የጳውሎስ ትምሕርቶች ይጋጫሉን?

በመቀጠል ደግሞ የክርስቶስ ትምሕርትና የሐዋርያው ጳውሎስ ትምሕርት እንደሚጋጩ ይነግረናል (ገፅ 54)፡፡ ለማጋጨት የሞከረው ተከታዮቹን ጥቅሶች ነው፡-

“እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።” (ማቴ. 5፡17)

ይጋጫል የሚለን ከተከታዮቹ ጥቅሶች ጋር ነው፡-

“ጽድቅስ በሕግ በኩል ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።” (ገላ. 2፡21)

“በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል፡፡” (ቆላ. 2፡14)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ቆላስይስ 2፡14 ላይ እየተናገረ ያለው ስለ ሕግ ሳይሆን ሕጉ ስለሚያስከትለው ቅጣት ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ሕግ ቅጣት በክርስቶስ ተሽሮልናል፡፡ ነገር ግን ሕጉ በክርስቶስ ስለተፈጸመ የሕጉ አሠራርና ጥቅም አዲስ ትርጉም አገኘ እንጂ ሕጉ በራሱ አልተሻረም፡፡ የብሉይ ኪዳንን ሕግ በተመለከተ በሌላ ቦታ ላይ እንዲህ ብሏል፡-

“እንግዲህ ሕግን በእምነት እንሽራለንን? አይደለም፤ ሕግን እናጸናለን እንጂ።” (ሮሜ 3፡31)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአንድም ቦታ ላይ የሙሴ ሕግ እንደተሻረ አላስተማረም፡፡ ነገር ግን የሕጉ ጠቀሜታ ምን እንደሆነ ነው ያብራራው፡፡

ከአውደ ንባቡ እንደሚታየው ጌታችን ኢየሱስ እየተናገረ ያለው ሕግን በመጠበቅ ወደ መንግሥተ ሰማያት ስለመግባት ሳይኾን ሕግን በመጠበቅ በመንግሥተ ሰማያት ውስጥ ስለሚገኝ ደረጃ ነው፡፡ ጌታችን ለሰው ልጆች ኃጢአት ቤዛ በመኾን እንደሚሞት በተደጋጋሚ ተናግሯል (ማቴዎስ 20፡28፣ 26፡28፣ 14፡24፣ ማርቆስ 10/፡45፣ ዮሐንስ 3፡14-15፣ 10፡11፣ 15፡30)፡፡ የሰው ልጅ ሕግን በመጠበቅ መንግሥተ ሰማያት መግባት ቢችል ኖሮ የእግዚአብሔር ልጅ ስለ ኃጢአታችን መሞት ባላስፈለገው ነበር፡፡ ዳሩ ግን ሕግን በመጠበቅ ማንም መዳን ስላልቻለ ክርስቶስ በኛ ፋንታ ሕግን በመጠበቅ ዕዳችንን ከፈለልን፡፡ ይህ ማለት ግን ሕጉ ተሽሯል ወይንም ምንም ፋይዳ የለውም ማለት አይደለም፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ይጠብቃሉ፡፡ ትዕዛዛቱን የሚጠብቁት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ሳይኾን የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች ስለሆኑ ነው፡፡ ሕግን መጠበቅ የደህንነት መገለጫ እንጂ የደህንነት ማግኛ መንገድ አይደለም፡፡ እውነተኛ እምነት በሥራ የሚገለጥ እንጂ በቃል ብቻ የሚሆን ባለመኾኑ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንደዳነ የሚናገር ነገር ግን በእርሱ ትዕዛዝ የማይኖር ሰው ሲጀመር አላመነም፡፡  ከነፍስ የተለየ አካል የሞተ እንደሆነ ኹሉ ከሥራ የተለየ እምነትም የሞተ ነውና (ያዕቆብ 2፡26)፡፡ የመዳን መገለጫ በእግዚአብሔር ሕግጋት መኖር በመሆኑ በክርስቶስ እንዳመነ የሚናገር ነገር ግን በቀድሞ ክፉ ኑሮው የሚመላለስ ሰው በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ቦታ እንደሌለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በስፋት አስተምሯል (1ቆሮ. 6፡9-10፣ ኤፌሶን 2፡8-10)፡፡

በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መሠረት ክርስቲያኖች ሕግን ማፅናት እንጂ መሻር አይገባቸውም (ሮሜ 3፡31)፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ከኃጢአት ርቀው የሚኖሩት እንደሆኑም አፅንዖት ሰጥቷል (ሮሜ 8፡1-23)፡፡ ስለዚህ የእርሱንና የክርስቶስን ትምሕርት ማጋጨት መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ ከሚያውቅ ሰው የሚጠበቅ አይደለም፡፡

ጳውሎስ ስለ ሴቶች

በማስከተል ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሴቶች ያስተማረውን በመጥቀስ እንዲህ ይላል፡-

ሴትን በተመለከተ ጳውሎስ የማንቋሸሽ ባህሪ የሚታይበት ሲሆን ወደ 1ኛ ጢሞ 2:11-12 በላከው መልዕክት፡- “ሴት በነገር ሁሉ እየተገዛች በዝግታ ትማር፤ ሴት ግን በዝግታ ትኑር እንጂ ልታስተምር ወይም በወንድ ላይ ልትሰለጥን አልፈቅድም” የሚል አቋሙን አንፀባርቋል፡፡ (ገፅ 54)

ለመሆኑ ማንቋሸሽ ማለት ምን ማለት ነው? ይህንን ጥቅስ በመጥቀስ ሴትን የሚያንቋሽሽ ነው የሚል አስተያየት ከአንድ ሙስሊም ማስማት በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ ይህ ሰው ተከታዮቹን እስላማዊ ትምህርቶች ቢመለከት ሴትን ልጅ ማንቋሸሽ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በትክክል ይገባዋል፡-

  • ሴቶች ለባሎቻቸው እርሻ ስለሆኑ በፈለጉበት ሁኔታ “ሊደርሷቸው” ይችላሉ፡- ሱራ 2፡223
  • ባሎች ሚስቶቻቸውን በመምታት መቅጣት ይችላሉ፡- ሱራ 4፡34
  • የአንድ ወንድ ምስክርነት ከሁለት ሴቶች ምስክርነት ጋር እኩል ነው፡- ሱራ 2፡282
  • በገነት ውስጥ ለሙስሊም ወንዶች የስሜት ማርኪያ እንዲሆኑ የተፈጠሩ ሴት ፍጥረታት ይገኛሉ፡- ሱራ 78፡30-33፣ 44፡51-54፣ 56፡34-36
  • ሴት የነካ ወንድ ልክ እንደሰከረ ሰው፣ እንደታመመ ሰው እና ከዓይነ ምድር እንደመጣ ሰው ሁሉ ታጥቦ ከርክሰቱ ካልነፃ መጸለይ አይችልም፡- ሱራ 4፡43
  • ዕድሜያቸው ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱትን ሴቶች ማግባት ይቻላል፡- ሱራ 65፡4
  • ሴቶች ለባሎቻቸው እንደ ባርያ ናቸው፡- (Sunan Abu Dawud2 no.2922, p.827)
  • የገሃነም አብዛኞቹ ነዋሪዎች ሴቶች ናቸው፡- (Sahih Al-Bukhari1 no.301 p.181. See also Sahih Muslim vol.2 book 4 no.1982,1983 p.432)
  • ሴት መሪ መሆን አትችልም፡- (Sahih Al-Bukhari vol.9 no.219 p.170-171)
  • ሙሐመድ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች ሕፃን አግብቷል፡- (Bukhari: vol. 5, bk. 58, no. 236)
  • ሙሐመድ የሴት ግርዛትን አፅድቋል፡- (Sunan Abu-Dawud: bk. 41, no. 5251. “Reliance of the Traveller – A Classic Manual of Islamic Sacred Law” የተሰኘ በአልአዝሃር ዩኒቨርሲቲ አፅዳቂነት የታተመ የሸሪኣ ሕግ መጽሐፍ ገፅ 59 ላይ የሴት ልጅ ግርዛት በእስልምና ግዴታ (Obligatory) መሆኑን ይገልፃል፡፡)
  • ጸሎት በሴት፣ በአህያና በጥቁር ውሻ ምክንያት ይቋረጣል፡- (Sahih Muslim, Book 004, Number 1032)

ወገኖቼ ሴትን ልጅ ማንቋሸሽ ማለት ይሄ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሴቶች ያለውን አመለካከት ለማወቅ ተከታዮቹን ጥቅሶች ማንበብ በቂ ነው፡-

“አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና፡፡” (ገላቲያ 3፡28)፡፡

“ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፥ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ፡፡ ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፥ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፥ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ፡፡” (1ቆሮንቶስ 7፡3-5)፡፡

“ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ፡፡ እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል፡፡ የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል፡፡ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡ ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ፡፡ ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፥ ሚስቱም ባልዋን ትፍራ፡፡” (ኤፌሶን 5፡25-33)፡፡

“ባሎች ሆይ፥ ሚስቶቻችሁን ውደዱ መራራም አትሁኑባቸው፡፡” (ቆላስይስ 3፡19)፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሴቶች ያለው አመለካከት ይህንን ይመስላል፡፡ የሴቶችንም አገልግሎት እንደማይቃወም ለማወቅ አብረውት ሲያገለግሉ የነበሩ ሴቶችን እየጠቀሰ እንደጻፈ ማስታወስ ያስፈልጋል (ሮሜ 16፡1፣ 7)፡፡ ሴት ነቢያት ራሶቻቸውን ተሸፍነው በቤተክርስቲያን ውስጥ ማገልገል እንደሚችሉም አስተምሯል (1ቆሮ. 11፡5)፡፡ ጸሐፊው በጠቀሰው ጥቅስ ላይ ሴቶች በጉባኤ ዝም እንዲሉ ወይም በወንዶች ላይ እንዳይሰለጥኑ መመርያ የሰጠው በወቅቱ ከነበረው ችግር አንጻር መሆኑን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይስማሙበታል፡፡ ለመሆኑ በእስልምና ሴት ልጅ በወንድ ላይ እንድትሰለጥን ወይም በመስጊድ ውስጥ እንድታስተምር ተፈቅዶላታልን?

ጳውሎስና ጋብቻ

በማስከተል ደግሞ ጳውሎስ ጋብቻን በተመለከተ የተናገራቸውን ሐሳቦች ይተቻል፡፡ እንዲህ ይላል፡-

በብሉይ ኪዳን “ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ፥ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ይቀበላል፡፡” (ምሳ 18፡22) እንዲሁም “ቤትና ባለጠግነት ከአባቶች ዘንድ ይወረሳሉ፤ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት፡፡” (ምሳ 9፡14) የሚለውን ወደ ጎን ጥሎ “ስለ ጻፋችሁልኝስ ነገር፥ ከሴት ጋር አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው፡፡” (1ቆሮ 7፡1) “እንዲሁም ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ ያላገባም የተሻለ አደረገ፡፡” (1ቆሮ 7፡38) በማለት አለማግባት የተሻለ እንደሆነና ካገባችሁ ደግሞ ደናግሎችን ብትመርጡ መልካም ነው ሲል መክሯል፡፡ (ገፅ 54-55)

ምሳሌ 9፡14 ያለው 19፡14 በሚል ይታረም፡፡ እነዚህን ጥቅሶች ከማብራራታችን በፊት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጋብቻ ያስተማረውን እስኪ እንመልከት፡፡

በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ትምሕርት መሠረት ጋብቻ መልካም ነው፡-

“መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል፡፡” (ዕብ. 13፡4)

ጋብቻን የሚከለክሉ ሰዎች የአጋንንት መንፈስ ያደረባቸው ውሸተኞች እንደሆኑ ጽፏል፡-

“መንፈስ ግን በግልጥ፦ በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፤ በገዛ ሕሊናቸው እንደሚቃጠሉ ደንዝዘው፥ እነዚህ ውሸተኞች መጋባትን ይከለክላሉ፥ አምነውም እውነትን የሚያውቁ ከምስጋና ጋር ይቀበሉ ዘንድ እግዚአብሔር ከፈጠረው መብል እንዲርቁ ያዝዛሉ፡፡” (1ጢሞ. 4፡1-3)

ከሴቶች ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል በጠቀስናቸው ጥቅሶች ውስጥ እንደሚታየው ሐዋርያው ጋብቻን ማበረታታት ብቻ ሳይሆን ባልና ሚስት እንዴት በፍቅር መኖር እንዳለባቸውም አስተምሯል፡፡ ጋብቻንም በክርስቶስና በቤተክርስቲያን መካከል ባለው ግንኙነትና አንድነት መስሏል፡- “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡ ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ፡፡” (ኤፌ. 5፡31-32)

እውነታው እንዲህ ከሆነ ታድያ “ከሴት ጋር አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው” ስለ ምን አለ? ይህንን ጥቅስ ጠቅሰው ትችት የሚሰነዝሩ ሰዎች ጥቅሱ ሲጀምር “ስለ ጻፋችሁልኝስ ነገር…” በማለት መሆኑን ይዘነጋሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው በቆሮንቶስ የነበሩ ወገኖች በወቅቱ የተቸገሩበት ለጋብቻ እንቅፋት የሆነ በጥቅሱ ውስጥ ያልተገለጸ ጉዳይ መኖሩን ነው፡፡ ሐዋርያው ከዚህ አንጻር ከጋብቻ መቆጠብ መልካም እንደሆነ ቢገልፅም ከገጠማቸው ችግር በላይ ጋብቻን አስገዳጅ የሚያደርግ ጉዳይ መኖሩን እንዲህ ሲል ያስረዳቸዋል፡-

“ስለ ጻፋችሁልኝስ ነገር፥ ከሴት ጋር አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት፡፡ ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፥ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ፡፡ ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፥ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፥ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ፡፡ ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፥ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ሁኑ፡፡” (1ቆሮ. 7፡1-5)

ከአውዱ እንደምንገነዘበው ሐዋርያው ከወቅቱ ችግር አንጻር መታቀብ መልካም ቢሆንም ከዝሙት ኃጢአት ለመራቅ እያንዳንዱ ሰው ማግባት እንደሚያስፈልገው ያስገነዝባል፡፡ ወደ ኋላ ላይ ሐዋርያው የቆሮንቶስ ወጣቶች ባያገቡ የተሻለ እንደሆነ ሲመክር ቢታይም በወቅቱ በተከሰተ በግልፅ ባልተጻፈ አንድ ችግር ምክንያት ነው፡- “እንግዲህ ስለ አሁኑ ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው” (1ቆሮ. 7፡26)፡፡ አንዳንዶች ይህ ችግር በወቅቱ የነበረው የበረታው ስደት ወይንም ልቅ የነበረው የቆሮንቶስ ከተማ የዝሙት ርኩሰት ሊሆን እንሚችል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ የሆነው ሆኖ ጳውሎስ ያቀረበው ምክር በወቅቱ ከነበረው ችግር አንጻር እንጂ ስለ ጋብቻ ያለው አቋም፡- “ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት” የሚል ነው (1ቆሮ. 7፡2)፡፡

ለጋብቻ ድንግል መምረጥን በተመከተ ምንም የሚያከራክር ነገር የለውም፡፡ ማንም እንደሚስማማበት አንድ ሰው ድንግል ቢያገባ ተመራጭ ነው፡፡ ሆኖም ጸሐፊው በዚህ ቦታ በተሳሳተ መንገድ እንደተረጎመው ሐዋርያው ለጋብቻ ድንግልን ስለመምረጥ እየተናገረ አይደለም፡፡ ሐዋርያው በወቅቱ ከነበረው ችግር አንጻር ደናግላን በድንግልናቸው ቢጸኑ መልካም እንደሆነ ከተናገረ በኋላ በዚያ ሁኔታ ለመፅናት ግዴታ እንደሌለባቸውና ማግባት እንደሚችሉ እየተናገረ እንጂ ድንግል መርጠው እንዲያገቡ ምክር እየለገሰ አይደለም፡-

“ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ፡፡ ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ግድ የለበትም፥ የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል፤ ድንግልናውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና፥ መልካም አደረገ፡፡ እንዲሁም ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ ያላገባም የተሻለ አደረገ፡፡” (1ቆሮ. 7፡36-38)

ከአውዱ ግልፅ ሆኖ እንደሚታየው ጸሐፊው የተናገረው ዓይነት ትርጉም ያለው ሐሳብ በቦታው ላይ የለም፡፡ ሐዋርያው በዚህ ቦታ ድንግልን ማግባት ተመራጭ መሆኑን ለመግለፅ ይህን ቢል ኖሮ “ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ” ካለ በኋላ “ያላገባም የተሻለ አደረገ” ለምን አለ? ነገር ግን ምክሩ መጥፎ ይመስል ይህንን ትችት የሰነዘረው ጸሐፊው ሙሐመድ ድንግል ያልሆነችን ሴት ያገባ ወንድ የገሰጸበትና ለጋብቻ ድንግል መምረጥ እንደነበረበት የተናገረበት ሐዲስ መኖሩን ያውቅ ይሆን?

Narrated Jabir bin ‘Abdullah:

When I got married, Allah’s Apostle said to me, “What type of lady have you married?” I replied, “I have married a matron.” He said, “Why, don’t you have a liking for the virgins AND FOR FONDLING THEM?” Jabir also said: Allah’s Apostle said, “Why didn’t you marry a young girl so that you might play with her and she with you?” (Sahih Al-Bukhari, Volume 7, Book 62, Number 17)

ባገባሁ ጊዜ የአላህ መልእክተኛ እንዲህ አሉኝ፡- “ምን ዓይነት ሴት ነው ያገባኸው?” እኔም “ጠና ያለች ሴት ነው ያገባሁት” አልኳቸው፡፡ እንዲህ አሉኝ “ለምንድነው ደናግላልን እና እነርሱን ማሻሸት ያልወደድከው?” በተጨማሪም ጃቢር እንደተናገረው የአላህ መልእክተኛ እንዲህ አሉ፡- “አንተም ከእርሷ ጋር እርሷም ከአንተ ጋር እንድትጫወቱ ለምን ትንሽ ልጃገረድ አላገባህም?” ይህ ሐዲስ በሌሎች ብዙ ቦታዎች ተዘግቧል፡-  (Sahih Al-Bukhari, Volume 3, Book 38, Number 504; Sahih Al-Bukhari, Volume 7, Book 62, Number 16)

ሙስሊም ሰባኪያን የገዛ ሃይማኖታቸውን ጉድ ሸሽገው በሌላው ላይ መዋሸት ልማዳቸው ነው፡፡

የጳውሎስ አሟሟት

ጸሐፊው የሐዋርያው ጳውሎስን አሟሟት በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል፡-

የጳውሎስን መጨረሻ በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈ ነገር የማናገኝ ሲሆን በታሪክ በሮም አገር እንደተሰቀለ ይነገራል፡፡ (ገፅ 55)

ጉድ! በየትኛው ታሪክ ነው እንደዚያ ተብሎ የተጻፈው? የቤተክርስቲያን ታሪክ እንደሚናገረው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሮም ከተማ አንገቱን ተሰይፎ በሰማዕትነት እንዳለፈ እንጂ እንደተሰቀለ የሚናገር ታሪክ የለም፡፡ በስቅላት ሰማዕት የሆነው ሐዋርያው ጴጥሮስ ነው፡፡ የሐዋርያው ጳውሎስ አሟሟት በቅዱስ ኢግናጢዮስ፣ ዲዮሲንዮስ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ኢዮስቢዮስ፣ ጀሮምና በመሳሰሉት አበው ጽሑፎች ውስጥ በስፋት ተዘግቧል፡፡ የዚህ መጽሐፍ ደራሲ እንዲህ ካሉ ቀላል መረጃዎች ጀምሮ በርካታ ስህተቶችን ሠርቷል፡፡ ባጠቃላይ በመጽሐፉ ውስጥ ሊታመን የሚችል መረጃ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡

ንቁ! ሙስሊም ሰባኪያን ሐሰተኞች ናቸው!

ይቀጥላል…


ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነውእስልምናስ?

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ