ውርደት የናፈቀው አብዱል ግሪክ ይጠቅሳል! የሰልማን ኮከብ “ግሪክ”

ውርደት የናፈቀው አብዱል ግሪክ ይጠቅሳል!

የሰልማን ኮከብ “ግሪክ”

ሰሞኑን “ንቁ! ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነውን?” በሚል ርዕስ በሰልማን ኮከብ ለተጻፈው የፕሮፓጋንዳ መጽሐፍ መልስ እየሰጠን መሆናችን ይታወሳል፡፡ ለመጽሐፉ ገፅ በገፅ የምንሰጠውን ምላሽ የምንቀጥል ቢሆንም ዛሬ ግን የተወሰኑ ገፆችን ወደፊት በማለፍ የሰልማንን የዕውቀት ደረጃና መረጃን የማጣራት አቅም በጥሩ ሁኔታ የሚያሳይ አንድ ነገር ልናስነብባችሁ ወደድን፡፡ ከታች የሚገኘው ፎቶግራፍ ከመጽሐፉ ገፅ 143 ላይ የተወሰደ ሲሆን ቅጥፈት የማይሰለቸው “ሰለምቴ ነኝ” ባዩ ደራሲ ጥራዝ ነጠቅነቱ ፍንትው ብሎ የታየበት ነው፡፡



ሰልማን በዚህ ገፅ ላይ የጠቀሳቸው “የግሪክ” ቃላት በሙሉ ስህተት ናቸው፡፡

“ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” በሚለው ውስጥ “እግዚአብሔር” ለሚለው የገባው ቃል “ሆንትዮስ” ሳይሆን ቶን ቴዎን (τὸν Θεόν) ነው፡፡ ኧረ ለመሆኑ “ሆንትዮስ” ማለት ምን ማለት ነው? እንዲህ የሚል ቃል ጭራሽ በግሪክ ቋንቋ ውስጥ የለም! “ሆ ቴዎስ” ለማለት ፈልጎ ይሆን? በዚህ ቦታ የተጠቀሰው ቃል እርሱ አይደለም፡፡

በድጋሜ “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” በሚለው ውስጥ የተጠቀሰው ቃል “ሆንትዮስ” ሳይሆን “ቴዎስ” (Θεὸς) ነው፡፡

καὶ Θεὸς ἦν ὁ Λόγος (ካይ ቴዎስ ኤን ሆ ሎጎስ) የሚለውን ሐረግ “ቃልም የእግዚአብሔር ሰው ነበረ” ብሎ የተረጎመ አንድም እደግመዋለሁ አንድም የግሪክ ቋንቋ ሊቅ የለም! የሌለና ያልተባለን የግል ፈጠራ በመጽሐፍ ማሳተም ከነውርም ነውር ነው፡፡

በመጨረሻው አንቀፅ ውስጥ የጠቀሰው ቶንትዮስ የሚለው ቃል በክፍሉ ውስጥ ካለመኖርም አልፎ  በግሪክ ቋንቋ ውስጥ የለም፡፡

——————————————–

ከላይ የሚገኘውን አጭር ምላሽ ካዘጋጀሁ በኋላ አስተያየቱን እንዲሰጠኝ ለአንድ ግሪክኛን እያጠና ለሚገኝ ወዳጄ (ዶ/ር) አሳየሁት፡፡ እርሱም ተከታዩን ምሑራዊ ትንታኔ ላከልኝ፡፡

የሰልማን ስህተቶች ከግሪክ ሰዋሰውና ሥነ-ልሳን አኳያ

የሰልማን ስህተቶች ከሁለት ነገሮች የመነጩ ናቸው፡-

  1. ግሪኩን ከማጥናት ይልቅ መኮረጅ (ኩረጃውንም አልቻለበትም እንጂ)
  2. የግሪክን ሥነ-ልሳንና መሠረታዊ ሰዋሰዋዊ አወቃቀርን አለማወቅ (በነገራችን ላይ ጭራሹንም አያውቀውም፡፡)

በግሪክ ቋንቋ ውስጥ cases የሚባሉ፣ ቃላት በዓረፍተ ነገር ውስጥ ያላቸውን ሙያ ወይም ሚና የሚነግሩን አወቃቀሮች አሉ። ዋና ዋናዎቹ አራት ናቸው። (ተጨማሪ አምስተኛ case ያለ ቢሆንም ለአሁኑ ርዕሳችን ብዙም ጠቃሚ ባለመሆኑ አንመለከተውም።)

  1. ኖሚኔቲቭ ኬስ
  2. አኩሴቲቭ ኬስ 
  3. ጄኔቲቭ ኬስ
  4. ዴቲቭ ኬስ
  5. ቮኬቲቭ ኬስ

ኖሚኔቲቭ ማለት አንድ ዓረፍተ ነገር ውስጥ የድርጊቱ ፈፃሚ ሲሆን አኩሴቲቭ ደግሞ ተፈፃሚ ነው። Subject እና Object እንደማለት ነው። በግሪክ ቋንቋ ውስጥ የምንለያቸው በአጻጻፋቸው ሲሆን ሊቃውንት declension ይሉታል። በዚህ ሁኔታ በተለይ አጨራረሳቸውን ማየት ወሳኝ ነው። 

ለዚህ አብዱል ማሳወቅ የምፈልጋት አንዲት ሕግ አለች። አንድን ቃል የሚገልፅ አርቲክል (the በእንግሊዝኛ) በሙያው፣ በፆታና በብዛት ከቃሉ ጋር መስማማት አለበት። ካልሆነ ግን ትርጉም አልባ ነው የሚሆነው፡፡ ይህንን ካልን ዘንዳ የሰልማንን ስህተቶች እንመልከት፡፡

የሰልማን ስህተቶች፡-

  1. ሆንትዮስ – ሲጀመር ሆንትዮስ የሚባል ቃል የለም። የስነ-ልሳን ችግር በመሆኑ “ሆ ቴዎስ” ብለን እናስተካክለው። ብናስተካክለው እራሱ “ቃልም እግዚአብሔር ነበር”  በሚለው ውስጥ “ሆ ቴዎስ” የለም። Θεος ην ο λογος  (ቴዎስ ኤን ሆ ሎጎስ) ነው የሚለው። ሆ ቴዎስ እዚህ ውስጥ አይገኝም።
  2. እርሱ “ቶንትዮስ” ብሎ ያስቀመጠው “ቶን ቴዎስ” (τον θεος)  የሚባል የግሪክ ቋንቋ አወቃቀር ውስጥ የለም። ምክኒያቱም “ቶን” (the) አኩሴቲቭ ሲሆን “ቴዎስ” (God) ደግሞ “ኖሚኔቲቭ ነው።  ሁለቱ አልተስማሙም። “ቶን” ካልን ግዴታ “ቴዎን” ማለት ይኖርብናል እንጂ “ቴዎስ” አንልም። ሰልማን የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለን ነገር ነው የጻፈው። አርፎ እንዲማር የሚነግረው መካሪ ቢኖረው ጥሩ ነበር፡፡
  3. በመጨረሻም καὶ Θεὸς ἦν ὁ Λόγος (ካይ ቴዎስ ኤን ሆ ሎጎስ) የሚለውን ሐረግ “ቃልም የእግዚአብሔር ሰው ነበረ” ብሎ ተርጉሞታል፡፡ ነገር ግን “ቃልም የእግዚአብሔር ሰው ነበረ” ለማለት “Ο ανθρωπος του θεου” (ሆ አንትሮፖስ ቶ ቴው) ተብሎ ነበር መጻፍ የነበረበት፡፡ የሰልማን ትርጓሜ ቅጥፈት በሚለው ቃል የማይገለፅ ፍፁም ቅጥፈት ነው፡፡

—————————

የግሪክ ቋንቋ አጥኚውን ወዳጄን እያመሰገንኩ የማጠቃለያ ሐሳብ ልስጥ፡፡

ሙስሊም ሰባኪያን “ግሪኩ እንዲህ ይላል” “እብራይስጡ እንዲህ ይላል” እያሉ በጠቀሱ ቁጥር እንዲህ ያሉ ስህተቶችን መፍጠራቸው አስገራሚ ነው፡፡ የአዲስ ኪዳንን ግሪክ እያንዳንዱን ቃል የሚያብራሩ መጻሕፍትና ድረገፆች የትየለሌ ናቸው፡፡ አንድ ሰው መጽሐፍን የሚያክል ነገር ለመጻፍ ብዕሩን ሲያነሳ ቢያንስ ወሳኝ ነጥቦችን ለማመሳከር እንዴት መጻሕፍትን አያገላብጥም? ለኔ ትልቁ ችግር የሚመስለኝ ኩረጃ ነው፡፡ አሕመድ ዲዳት “ቶንቴዎስ” ብሎ የሌለ ግሪክ ፈጥሮ ስለጻፈ ከእርሱ በኋላ የሚገኙት ሙስሊም ሰባኪያን በሙሉ ላለፉት 40ና 50 ዓመታት ተመሳሳይ ስህተት እየደጋገሙ ነው፡፡ የሙስሊም ሰባኪያን የመረጃ ቅብብሎሽ ከላይ ወደ ታች እንጂ ወደ ጎን በመመልከት የመረጃዎችን ሐቀኝነት ለመፈተሽ የሚፈቅድ አይመስልም፡፡ ቁርአንና የሐዲስ መጻሕፍት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡበትን የመረጃ አስተላለፍ (ኢስናድ) ስንመለከት ዋናው ነጥብ “መረጃዎቹ ምን ያህል ሃቀኛ ናቸው?” የሚል ሳይሆን “እነማን ተናገሩት?” የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የመረጃው ሃቀኝነት በግለሰቦቹ ስብዕና ላይ መቶ በመቶ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አደገኛ ሚዛን ነው፡፡ አሕመድ ዲዳትን የመሳሰሉ ሁለት ፀጉር ያበቀሉ ወገኖች “ቶንቴዎስ” የሚል የሌለ ግሪክ ፈጥረው ትውልድን ሊያሳስቱ ይችላሉ፡፡ ዛኪር ናይክን የመሳሰሉ ታዋቂ ሰባኪያን በ5 ደቂቃ ውስጥ 25 ስህተቶችን በመናገር የዋሁን ሕዝብ ሊያጭበረብሩ ይችላሉ፡፡

ውድ ሙስሊሞች፤ እስከ መቼ ድረስ በምታምኗቸው የገዛ ሰባኪዎቻችሁ ትጭበረበራላችሁ? እስከ መቼስ ለገንዘብ እንጂ ለእውነት ግድ በሌላቸው የመጻሕፍት ነጋዴዎች ትታለላላችሁ? ጌታ እግዚአብሔር የልብ ዐይኖቻችሁን በመክፈት እንዲህ ካሉ ተኩላዎች ይታደጋችሁ ዘንድ ጸሎታችን ነው፡፡

አቶ ሰልማን በዚህ ጽሑፍ ከተጋለጠ በኋላ ለማስተባበል ሞክሯል፡፡ በፒ ዲ ኤፍ የተዘጋጀውን ጽሑፍ በማውረድ ይህንን ጉድ የሚያሰኝ ቅሌት ይመልከቱ፡- “አውቄ ነው እንጂ አውቀው ነበር” – የሰልማን ቅጥፈትና ቅሌት


 


የአሕመድ ዲዳት የግሪክ ቋንቋ ቅጥፈቶች

የዶ/ር ዛኪር ናይክ 25 ስህተቶች በ5 ደቂቃ ውስጥ

ለሰልማን መጽሐፍ ምላሽ

 

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ