የግራንቪል ሻርፕ ሕግና የሙስሊም ኡስታዞች ቅጥፈት – የክርስቶስን አምላክነት ለማስተባበል የተደረገ ከንቱ ጥረት

የግራንቪል ሻርፕ ሕግና የሙስሊም ኡስታዞች ቅጥፈት

የክርስቶስን አምላክነት ለማስተባበል የተደረገ ከንቱ ጥረት

“ሰለምቴ ነኝ” ባዩ ሙስሊም ሰባኪ ቲቶ 2፡13 ላይ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት የተነገረውን ቃል ለማስተባበል ለጻፈው ጽሑፍ የሰጠነውን ምላሽ እንደገና ለመሞገት አዲስ ጽሑፍ ጽፏል፡፡ የቀደመውን ምላሻችንን ለማንበብ እዚህ ጋ ጠቅ ያድርጉ፡፡ በእውነቱ ከሆነ ቀደም ሲል የሰጠነው ምላሽ ከበቂ በላይ በመሆኑ ሌላ ዙር የሚያስጽፍ የቀረ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ይህ ሰው ግን በየዋኀን ሙስሊሞች ዘንድ ራሱን እንደ ምሑር በመሳል አርቴፊሻል ስብዕና ስለገነባ ይህንን በሐሰት የተገነባ ስብዕና ከመፈረካከስ ለመታደግ ቀቢፀ ተስፋዊ መንፈራገጥ ውስጥ የገባ ይመስላል፡፡ በማስከተል እንደምንመለከተው ይህ ሙስሊም ዳዋጋንዲስት[1] የመጽሐፍ ቅዱስን ቋንቋና ክርስቲያናዊውን አስተምህሮም ፈፅሞ አያቀውቅም፡፡ እንዲሁ በደመነፍስ ይጽፋል እንጂ የአዲስ ኪዳን ግሪክ ምሑር የነበረው የግራንቪል ሻርፕ አቋም ምን እንደሆነ አንብቦ አልተረዳም፡፡ በዚህ መጣጥፍ የዚህን ሰው ሙግት እንፈትሻለን፤ ዳግመኛ ሊያንሰራራ በማይችልበት ሁኔታም ወደ ተገቢ ቦታውም እንመልሰዋለን፡፡

እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-

አብዱል

ታላቁ አምላክ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፥ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

42፥4 በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የእርሱ ነው፡፡ እርሱም የበላዩ ታላቁ ነው፡፡

በክርስትና ስልታዊ ሥነ-መለኮት”systematic theology” ውስጥ “ኢየሱስ አምላክ ነው” ብለው ድምዳሜ ላይ ያደረሳቸው የጳውሎስ ንግግር ነው። “ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ አምላክነት ተናግሯል” ይላሉ። እዚህ ድምዳሜ ላይ አደረሰን ከሚሏቸው አናቅጽ መካከል አንዱን አንቀጽ ዳሰሳ”servey” እናደርጋለን፥ የማቀርበው ሙግት አዲሱ ዓለም ዐቀፍ ትርጉምን”NIV” ታሳቢ ያደረገ ነው፦

ቲቶ 2፥13 የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንን ክብር እና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ እየጠበቅን”። while we wait for the blessed hope the appearing of the glory of our great God and Savior, Jesus Christ, (New International Version)

ግሪኩ፦ προσδεχόμενοι τὴν μακαρίαν ἐλπίδα καὶ ἐπιφάνειαν τῆς δόξης τοῦ μεγάλου Θεοῦ καὶ Σωτῆρος ἡμῶν Χριστοῦ Ἰησοῦ,

መልስ

የክርስቶስ አምላክነት በጳውሎስ ብቻ የተነገረ ሳይሆ ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ጀምሮ እስከ አዲስ ኪዳን መጻሕፍት ድረስ በስፋት የተነገረ አንኳር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ነው፡፡ ጉዳዩን አጥብበህ ወደ ሐዋርያው ጳውሎስና ወደ አንድ ጥቅስ መውሰድህ ተቀባይነት የለውም፡፡

ለሙግትህ NIV የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መምረጥህ በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ NIV ይህንን ጥቅስ የኢየሱስን አምላክነት በማያሻማ መንገድ በሚገልፅ ሁኔታ መተርጎሙን ልብ አለማለትህ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ዕውቀት እጥረት እንዳለብህ ያሳብቃል፡፡ “our great God and Savior, Jesus Christ” በሚለው ውስጥ “great God and Savior” ካለ በኋላ ኮማ (,) አስቀምጦ “Jesus Christ” ማለቱ ሁለቱም ማዕርጋት ኢየሱስን የተመለከቱ መሆናቸውን ለማሳወቅ መሆኑ መሠረታዊ የእንግሊዘኛ ቋነቋ ዕውቀት ካለው ሰው ሁሉ የተሰወረ አይደለም፡፡ ከሁለቱ ቃላት በኋላ የኮማ ምልክት ባይኖር ኖሮ ትርጉሙ በመጠኑ አሻሚ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን ኮማ መግባቱ አሻሚነቱን በማስወገድ ሁለቱም ማዕርጋት ለኢየሱስ የተሰጡ መሆናቸውን ያረጋግጣል፡፡ በተጨማሪም የ NIV ተርጓሚዎች በግርጌ ማጥኛ እንዲህ የሚል ማብራርያ ሰጥተዋል፡- “… the NIV rendering better represents the Greek construction and is an explicit testimony to the deity of Christ.” ይህንን ወደ አማርኛ ስንመልሰው፡- “የ ኤን አይ ቪ ትርጓሜ የግሪኩን አወቃቀር በተሻለ ሁኔታ የሚወክል ሲሆን ለክርስቶስ አምላክነት ግልፅ የሆነ ምስክርነት ነው” የሚል ነው፡፡

አብዱል

እዚህ አንቀጽ “ቴስ ዶክስ ቴዩ መጋላዩ ቴኦዩ” τῆς δόξης τοῦ μεγάλου Θεοῦ ማለት “የታላቁን የአምላካችንን ክብር”the glory of our great God” ማለት ነው፥ ጳውሎስ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት፦ “የታላቁ አምላክ ክብር እና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ የተባረከውን ተስፋችን ነው” የሚል ነው።

መልስ

የግሪክ ቋንቋ ዕውቀት በትክክል ፊደላቱን ከመለየት ቢጀምርም አንተ ግን ፊደላቱን የመለየት ደረጃ ላይ እንኳ አልደረስክም፡፡ ቀጥታ ከእንግሊዘኛ ትራንስሊትሬሽን የወሰድክ ሲሆን ማንበብ ስለማትችል በትክክል ማስቀመጥ አልቻልክም፡፡ τῆς δόξης τοῦ μεγάλου θεοῦ የሚለው አንተ አወናግረህ እንደጻፍከው ሳይሆን “ቴስ ዶክሴስ ቶው ሜጋሎው ቴው” ተብሎ ነው የሚነበበው፡፡ አንድ ፊደል እንኳ ለይተህ በማታውቅበት ሁኔታ እንዲህ ያለ ድፍረት በእውነቱ እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡

በጠቀስከው የእንግሊዘኛ ትርጓሜ “the glory of our great God and Savior, Jesus Christ” ይላል እንጂ “the glory of our great God” የሚለው ለብቻው ተነጥሎ የቆመ አይደለም፡፡ ያንተ ስህተት τοῦ μεγάλου Θεοῦ “ታላቁ አምላክ” የሚለው καὶ “እና” በሚል መስተጻምር Σωτῆρος “መድኃኒታችን” ከሚለው ጋር ተያይዞ ሳለ “ክብር” የሚለውን ቃል “ታላቁ አምላክ” በሚለው መወሰንህ ነው፡፡ ይህ የሌለና ተሰምቶ የማይታወቅ የግል ትርጓሜህ ነው፡፡ ልክ በተጻፈው መሠረት “the glory of our great God and Savior, Jesus Christ” ብለህ አንብበህ የተሟላውን ትርጉም ትሰጣለህ እንጂ ቆራርጦ በመነጣጠል የተለየ ትርጉም መፍጠር ዓይን ያወጣ ማጭበርበር ነው፡፡ አሟልተህ ካነበብክ ትክክለኛው ትርጓሜ በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ እንደሚታየው “የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን” የሚለው ነው፡፡

የክርስቶስን ፍጹም አምላክነት የማይቀበሉ የይሖዋ ምስክሮች እንኳ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በተሰኘው የተቀጣጠፈ ትርጉማቸው እንዲህ በማለት ነው ያስቀመጡት፡- “while we wait for the happy hope and glorious manifestation of the great God and of [the] Savior of us, Christ Jesus” በዚህ ትርጉም “of the great God and of [the] Savior of us” በሚለው ውስጥ ሁለተኛ ላይ ደመቅ የተደረገው  “of [the]” የሚለው በግሪክ ቋንቋ የማይገኝ ሲሆን የክርስቶስን አምላክነት ለማድበስበስ ሌላ ትርጉም እንዲኖረው ሆነ ተብሎ የተደረገ ጭማሬ ነው፡፡ በአማርኛ ደግሞ እንዲህ ሲሉ ነው የተረጎሙት፡-

“በዚህ ሁኔታ አስደሳች የሆነውን ተስፋ እንዲሁም የታላቁን አምላክና የአዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን በክብር መገለጥ እንጠባበቃለን” (አዓት)

ይህ ትርጓሜ ከግሪክ ሰዋሰው አንፃር ስህተት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እግዚአብሔር አብና ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ይገለጣሉ የሚለው የጥቅሱ ምልከታ በዳግም ምፅዓት አብ አይመጣም ከሚለው የይሖዋ ምስክሮች አስተምህሮ ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ ቢሆንም ግን አንተ NIV’ን በመቀንጨብ የተለየ ትርጉም ለመፍጠር እንዳደረከው “የታላቁን የአምላካችንን ክብር”  “the glory of our great God” በማለት በመነጣጠል አልተረጎሙም፡፡

አብዱል

የታላቁ አምላክ የአብ ክብር በተለያየ ጊዜ ለእስራኤላውያን ይገለጥ ነበር፦

ዘሌዋውያን 9፥6 የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጥላችኋል”።

ዘሌዋውያን 9፥23 “የእግዚአብሔርም ክብር ለሕዝቡ ሁሉ ተገለጠ”።

ዘኍልቍ 14፥10  “የእግዚአብሔርም ክብር ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ተገለጠ”።

ኢየሱስ መለኮታዊ ኃይል ተሰጥቶት የሚሠራው ሥራ የእግዚአብሔር ክብር መገለጥ ነው፦

ኢሳይያስ 40፥5 የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል”።

ዮሐንስ 11፥40 ኢየሱስ፦ ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን? አላት።

መልስ

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር አብ ክብር ብቻ ሳይሆን ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም ክብር ይናገራል፡-

“ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን፡፡” (ዮሐንስ 1፡14)

“ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ፡፡” (ዮሐንስ 2፡11)

“አሁንም፥ አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ” (ዮሐንስ 17፡5)

“ከዚያ ብርሃንም ክብር የተነሣ ማየት ባይሆንልኝ ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች እጄን ይዘው እየመሩኝ ወደ ደማስቆ ደረስሁ፡፡” (የሐዋርያት ሥራ 22፡11) ሐዋርያው ጳውሎስ ጌታ ኢየሱስ በደማስቆ መንገድ ላይ ከተገለጠለት በኋላ የተናገረው፡፡

“አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፡፡” (1ቆሮንቶስ 2፡8)

“ወንድሞቼ ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ፡፡” (ያዕቆብ 2፡1)

ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር አብ ክብር ብቻ ሳይሆን ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብርም ይናገራል፡፡

አብዱል

እዚህ ድረስ ከተግባባን ኢየሱስ የሚመጣው በታላቁ አምላክ በአብ ክብር ነው፦

ማቴዎስ 16፥27 “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና”።

“በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና” የሚለው ኃይለ-ቃል ይሰመርበት። የእግዚአብሔር ክብር እና ኢየሱስ ደግሞ “ካይ” καὶ ማለትም “እና” በሚል መስተጻምር ተለይተዋል፦

ሐዋርያት ሥራ 7፥55 የእግዚአብሔርን ክብር “እና” καὶ ኢየሱስን በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየ”። (New International Version)

ራእይ 21፥23 ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት “እና” καὶ መብራትዋ በጉ ስለ ሆነ”። (New International Version)

ጳውሎስ በፍጹም “ታላቁ አምላክ ይገለጣል” አላለም። ባይሆን የታላቁ አምላክ ክብር እና ኢየሱስ እንደሚገለጡ መናገሩ ቢሆን እንጂ።

መልስ

የአብ ክብር የወልድ ነው፤ የወልድም ክብር የአብ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነ በአባቱ ክብር ይመጣል፤ አምላክ ስለሆነ ደግሞ በገዛ ክብሩ ይመጣል፡፡ ጌታችን ምፅዓቱ በራሱና በአባቱ ክብር እንደሆነ ሌላ ቦታ ላይ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡-

“…የሰው ልጅ በክብሩ በአባቱና በቅዱሳን መላእክቱ ክብርም ሲመጣ…” (ሉቃስ 9፡26)

“…when he shall come in his own glory, and in his Father’s, and of the holy angels”

“በቅዱሳን መላእክቱ ክብር” የተባለው በመላእክት አጀብ መምጣቱን ለማመልከት ነው፡፡

ስለዚህ አንድን ሐሳብ በትክክል ለመረዳት አጠቃላዩን መረጃ ማገናዘብ እንጂ አንተ እንዳደረከው ከፊል ሐሳብ መጥቀስ ለስህተት ይዳርጋል፡፡

አብዱል

የግሪክ ሰዋስው ግራንቪል ሻርፕ አንደኛው ላይ የተቀመጠው ሕግ ፦ “ሁለት ስሞች ተመሳሳይ ሙያ ካላቸው፣ ሁለቱም ስሞች “እና” በሚል መስተጻምር ከተያያዙ፣ ከመጀመሪያው ስም ላይ ውስን መስተአምር ከተጠቀመ እና ሁለተኛ ስም ላይ ካልተጠቀመ ሁለቱም ስሞች አንድን ማንነትን የሚያሳዩ ነው” If two nouns of the same case and the two nouns are connected by the word “and,” and the first noun has the article while the second does not, both nouns are referring to the same person”

ዋቢ መጽሐፍ ይመልከቱ፦

Wallace, Daniel B. (1996). Greek Grammar Beyond the Basics: An Exegetical Syntax of New Testament Greek. Grand Rapids. Page 270-290.

በዚህ ሕግ ከሔድን ውኃ የማይቋጥር ሙግት ነው፦

ኤፌሶን 2፥20 “በሐዋርያት “እና” በነቢያት” መሠረት ላይ ታንጻችኋል። ἐποικοδομηθέντες ἐπὶ τῷ θεμελίῳ τῶν ἀποστόλων καὶ προφητῶν

እዚህ አንቀጽ ላይ “አፓስቶሎን” ἀποστόλων ማለትም “ሐዋርያት” ከሚል ስም በፊት “ቶን” τῶν የሚል ውስን መስተአምር ይጠቀማል፣ “ፕሮፌቶን” προφητῶν ማለትም “ነቢያት” በሚለው ስም ግን ውስን መስተአምር አይጠቀምም፣ ሁለቱም ስሞች “እና” በሚል መስተጻምር ተያይዘዋል፣ ሁለት ስሞች ተመሳሳይ ተሳቢ ሙያ አላቸው። ግን ሐዋርያት እና ነቢያት ተመሳሳይ ማንነት አልነበሩም፦

1 ቆሮንቶስ 12፥28 እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን.. አድርጎአል።

መልስ

የጠቀስካቸው ስመ-ጥር የዘመናችን የአዲስ ኪዳን ግሪክ ሊቅ የሆኑት ዶ/ር ዳንኤል ዋላስ የግራንቪል ሻርፕን ሕግጋት በጥልቀት ያጠኑ ሰው ናቸው፡፡ እኚህ ሊቅ አንደኛውን ሕግ በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በሌሎች ጥንታውያን የግሪክ ጽሑፎች ላይ ጥልቅ ምርምሮች ካደረጉ በኋላ የሻርፕን ሐሳብ በማብራራት እንዲህ አስቀምጠውታል፡-

“በዋናው የግሪክ አወቃቀር (ትርጉም ባልሆነ ግሪክ) “ካይ” በሚል መስተጻምር የተያያዙ ሁለት ስሞች አንድ መስተኣምር ከፊታቸው ከገባ እና ሁለቱም ባሕርይ ገላጮች (1) በሰዋሰውም ሆነ በቃል ደረጃ ነጠላ ከሆኑ (2) ማንነታዊ ከሆኑ (ህልውና ያላቸውን አካላት አመልካች ከሆኑ) እና (3) የወል ስሞች ከሆኑ (የተጸውዖ ስሞች ወይንም ቅደም ተከተላዊ ካልሆኑ) አንድን አካል ያመለክታሉ፡፡ https://bible.net/article/sharp-redivivus-reexamination-granville-sharp-rule

ስለዚህ ቀደም ሲል የጠቀስካቸው ጥቅሶች ሕጉን የሚያሟሉ ባለመሆናቸው ሙግትህን ሊደግፉ አይችሉም፡፡ ለበለጠ መረጃ ይህንን ጽሑፍ ተመልከት፡- http://www.ewnetlehulu.net/am/sharp-1/

አብዱል

ይህ አላዋጣ ያላቸው ሥላሴአውያን ግራንቪል ሻርፕ በራሱ መጣጥፍ ላይ ባላስቀመጠው መስፈርት፦ “የሻርፐስ ሕግ ማንነት ለሌለው፣ ለብዜት ስም፣ ለተጸውዖ ስም አይሠራም” ብለው አረፉት።

መልስ

ጉድ! ለመሆኑ የሻርፕን መጽሐፍ አንብበሃል? ለነገሩ ሻርፕ መጽሐፍ መጻፉን እንኳ የምታውቅ አትመስልም፤ ለዚህም ነው “ግራንቪል ሻርፕ በራሱ መጣጥፍ ላይ ባላስቀመጠው” ብለህ የጻፍከው፡፡ ወዳጄ እነዚህ ልዩ አጋጣሚዎች (Exceptions) በራሱ በሻርፕ ተለይተው የተቀመጡ ሲሆን በመጽሐፉ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አንተ የምታውቀው “የሻርፕ የመጀመርያው ሕግ” ተብሎ በተለያዩ ወገኖች የሚጠቀሰውን አጭር ገለጻ ነው፡፡ ነገር ግን መጽሐፉን ብታነብ ኖሮ ሻርፕ ሕጉን ሲያብራራ “ሕጉ የማይሠራባቸው” በማለት ሁለቱን ነጥቦች እንዳስቀመጠና አንዱ ልዩ አጋጣሚ ደግሞ ሕጉን ሲያትት የገለጸ መሆኑን ትመለከት ነበር፡፡ ይህንን ሕግ የተለያዩ ወገኖች በተለያየ አገላለፅ ቢያስቀምጡትም ሻርፕ በመጽሐፉ ውስጥ የጻፈው ቀጥተኛ ጽሑፍ እንዲህ የሚል ነው፡-

When the copulative και connects two nouns of the same case, [viz. nouns (either substantive or adjective, or participles) of personal description, respecting office, dignity, affinity, or connexion, and attributes, properties, or qualities, good or ill], if the article ὁ, or any of its cases, precedes the first of the said nouns or participles, and is not repeated before the second noun or participle, the latter always relates to the same person that is expressed or described by the first noun or participle: i.e. it denotes a farther description of the first-named person. (Granville Sharp; Remarks on the Uses of the Definitive Article in the Greek Text of the New Testament, Containing Many New Proofs of the Divinity of Christ, from Passages Which Are Wrongly Translated in the Common English Version; 3rd Edition, 1803, p. 3)

ከላይ የሚገኘው ሻርፕ ቃል በቃል ከጻፈው የተወሰደ ሲሆን ደምቆ የተጻፈው (…of personal description…) የሚለው ሕጉ ማንነት ያለው አካልን የተመለከተ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ሕጉ ለብዜትና ለተፀውዖ ስሞች እንደማይሠራ ደግሞ ስለ ሕጉ ማብራርያ በሰጠበት ክፍል በመጽሐፉ ገፅ 6 ላይ እንዲህ በማለት ነው ያስቀመጠው፡-

….EXCEPT the nouns be proper names, or in the plural number; in which cases there are many exceptions… (Ibid. p. 6)

ስለዚህ ሕጉ ማንነት አልባ (impersonal)፣ የተፀውዖ ስሞችን (proper names) እንዲሁም ብዙ ቁጥርን (plural number) የተመለከተ እንዳልሆነ ሻርፕ በግልፅ በመጽሐፉ ውስጥ ጽፏል፡፡ “ይህ አላዋጣ ያላቸው ሥላሴአውያን ግራንቪል ሻርፕ በራሱ መጣጥፍ ላይ ባላስቀመጠው መስፈርት፦ “የሻርፐስ ሕግ ማንነት ለሌለው፣ ለብዜት ስም፣ ለተጸውዖ ስም አይሠራም” ብለው አረፉት” ብለህ ማለትህ ከቁንፅል ንባብ ተነስተህ ብዙ የምታወራ እንጂ ዕውቀት ያለህ ሰው አለመሆንህን የሚያሳይ ነው፤ እናም ካንተና ከመሰሎችህ ጋር መነጋገር ጊዜ ማጥፋት ነው፡፡

አብዱል

እሺ በነጠላ ስም እንሞግት፦

ኤፌሶን 5፥5 ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስ “እና” በአምላክ መንግሥት ርስት የለውም።

እዚህ አንቀጽ አንቀጽ ላይ “ክርስቶዩ” Χριστοῦ ማለትም “ክርስቶስ” ከሚል ስም በፊት “ቶዩ” τοῦ የሚል ውስን መስተአምር ይጠቀማል፣ “ቴኦዩ” Θεοῦ ማለትም “አምላክ” በሚለው ስም ግን ውስን መስተአምር አይጠቀምም፣ ሁለቱም ስሞች “እና” በሚል መስተጻምር ተያይዘዋል፣ ሁለት ስሞች ተመሳሳይ አገናዛቢ ሙያ አላቸው። ግን ክርስቶስ የተባለው ወልድ እና አምላክ የተባለው አብ ተመሳሳይ ማንነት አልነበሩም። “የክርስቶስ ራስ አምላክ ነው” “ክርስቶስ ለአምላክ ለአባቱ መንግሥትን አሳልፎ ይሰጣል” “ክርስቶስ ለአምላክ ራሱን አሳልፎ ሰጠ” የሚሉ ሐረጋት መኖራቸውን አትዘንጋ፦ 1ኛ ቆሮንቶስ 11፥3 1ኛ ቆሮንቶስ 15፥23-24 ኤፌሶን 5፥2።

ሙግቱን እቀጥል፦

2ኛ ጢሞቴዎስ 4፥1 በአምላክ እና በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት”። τοῦ Θεοῦ καὶ Χριστοῦ Ἰησοῦ,

እዚህ አንቀጽ አንቀጽ ላይ “ቴኦዩ” Θεοῦ ማለትም “አምላክ” ከሚል ስም በፊት “ቶዩ” τοῦ የሚል ውስን መስተአምር ይጠቀማል፣ “ክርስቶዩ” Χριστοῦ ማለትም “ክርስቶስ” በሚለው ስም ግን ውስን መስተአምር አይጠቀምም፣ ሁለቱም ስሞች “እና” በሚል መስተጻምር ተያይዘዋል፣ ሁለት ስሞች ተመሳሳይ አገናዛቢ ሙያ አላቸው። ግን አምላክ የተባለው አብ እና ክርስቶስ የተባለው ወልድ ተመሳሳይ ማንነት አልነበሩም።

በቁና ሰፍረን ብዙ ናሙና ማቅረን ይቻል ነበር፥ ቅሉ ግን አንባቢን ማሰልቸት ነው ብለን ትተነዋል።

መልስ

ኤፌሶን 5፡5 እና 2ጢሞቴዎስ 4፡1 ግራንቪል ሻርፕ በሕጉ መሠረት የክርስቶስን አምላክነት እንደሚያሳዩ ከጠቀሳቸው ስምንት ጥቅሶች መካከል ናቸው (Ibid. pp. 106-110)፡፡ ሕጉን አጥንተህና የሻርፕን ጽሑፍ አንብበህ ቢሆን ኖሮ እዚህ ስህተት ላይ ባልወደቅህ ነበር፡፡ የአዲስ ኪዳን ግሪክ ሊቃውንት ግን በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የሻርፕን አቋም አከራካሪ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ θεοῦ (ቴው – አምላክ) “የወል ስም” ሊሆን ቢችልም Χριστοῦ (ክሪስቶው) የሚለው በአዲስ ኪዳን መልእክታት ውስጥ እንደ ጌታችን የተፀውዖ ስም አገልግሎት ላይ የዋለ ይመስላል የሚል ነው፡፡ የሆነው ሆኖ በሻርፕ አቋምም ሆኖ በሌሎች የአዲስ ኪዳን ግሪክ ሊቃውንት መሠረት ያንተን አቋም የሚደግፍ ነገር የለም፡፡ የሻርፕን አቋም ተቀብለህ ጥቅሱ የክርስቶስን አምላክነት እንደሚያሳይ ብትስማማ ወይንም “ክርስቶስ” እንደ ተፀውዖ ስም ሊቆጠር ይችላል የሚለውን የአዲስ ኪዳን ግሪክ ሊቃውንት ብትቀበል በሁለቱም ትርጓሜ አቋምህ ውድቅ ነው፡፡

አብዱል

እሺ ሙግቱን ጠበብ አርገነው ሻርፐስ ሕግ ትክክል ነው ብለን በግናንቪል ሻርፕ ሕግ ኢየሱስ እራሱ የታላቁ አምላክ ክብር ነው” ቢባል እንኳን አሁንም አያጣላንም፥ ምክንያቱም ወንድ እራሱ የእግዚአብሔር ክብር ተብሏልና፦

1ኛ ቆሮንቶስ 11፥7 “ወንድ የእግዚአብሔር ምሳሌ እና ክብር ስለ ሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም”።

ወንድ “የእግዚአብሔር ክብር ነው” ማለት እና “እግዚአብሔር ነው” ማለት በይዘትና በአይነት፥ በመንስኤና በውጤት ሁለት የተለያየ ለየቅል ትርጉም እንዳለው ሁሉ ኢየሱስ “የታላቁ አምላክ ክብር ነው” ማለት እና “ታላቁ አምላክ ነው” ማለት በይዘትና በአይነት፥ በመንስኤና በውጤት ሁለት የተለያየ ለየቅል ትርጉም ነው።

መልስ

የሻርፕ ሕግ ትክክል ከሆነ “ታላቁ አምላካችንና መድኃኒታችን” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው፡፡ ታላቁ አምላክ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር እንደሚገለጥ እንጂ “ኢየሱስ የታላቁ አምላክ ክብር ነው” ተብሎ ሊተረጎም የሚችል ዓረፍተ ነገር በቦታው ላይ የለም፡፡ ምንድነው የምታወራው? ሻርፕ እየነገረህ ያለው እኮ ታላቁ አምላክ የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህ “ወንድ የእግዚአብሔር ክብር” ስለመሆኑ የጠቀስከው ጥቅስ በዚህ አውድ ሊጠቀስ የሚችል አይደለም፡፡

አብዱል

የቲቶ ጸሐፊ ጳውሎስ እዛው ዐውድ ላይ አብ አምላክ፥ ወልድን መድኃኒት በማለት “እና” በሚል መስተጻምር ለይቶ አስቀምጧቸዋል፦

ቲቶ 1፥4 ከአምላካችን Θεοῦ ከአብ “እና” καὶ   ከመድኃኒታችን ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና ምሕረት ሰላምም ይሁን።

እዚህ አንቀጽ ላይ “ቴኦዩ” Θεοῦ አገናዛቢ ዘርፍ ሲሆን ልክ እንደ ቲቶ 2፥13 “አምላካች” ተብሎ ሲነበብ አብ አምላክ ወልድ መድኃኒት መሆኑን ያሳያል።

መልስ

ይህ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም አንዱ ቦታ ላይ አብ መለኮት መሆኑን ተናግሮ ሌላ ቦታ ላይ ወልድም መለኮት መሆኑን ከተናገረ ሐዋርያው ጳውሎስ በሁለቱም የሥላሴ አካላት መለኮትነት ማመኑን ያሳያል፡፡ በቀደመው ምላሻችን ላይ እንዳስቀመጥነው፡-

“አብ አምላክ ስለተባለ ኢየሱስ አምላክ አይደለም እንዲሁም ኢየሱስ መድኃኒት ስለተባለ አብ መድኃኒት አይደለም” የሚል እሳቤ አመክንዮአዊ መሠረት የለውም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እግዚአብሔር አብን “መድኃኒታችን” በማለት የገለጸባቸው ጥቅሶች በዚሁ በቲቶ መልእክትና በጢሞቴዎስ መልእክት ውስጥ ይገኛሉ፡-

“በዘመኑም ጊዜ፥ መድኃኒታችን እግዚአብሔር…” (ቲቶ 1፡3)

“…ስለ መድኃኒታችን ስለ እግዚአብሔር የሚሆነውን ትምህርት…” (ቲቶ 2፡9)

“…የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና…” (ቲቶ 3፡4)

“መድኃኒታችን እግዚአብሔር ተስፋችንም ኢየሱስ ክርስቶስ…” (1ጢሞ. 1፡1)

ስለዚህ ባንተ ሙግት መሠረት ከቲቶ መልእክት አንጻር “አምላክ” አብ፣ “መድኃኒታችን” ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሆነ ሐዋርያው “መድኃኒታችን እግዚአብሔር” ብሎ የተናገረባቸው ቦታዎች ላይ “እግዚአብሔር” የተባለው አብ ነው ወይንስ ኢየሱስ? አብ ነው የምትል ከሆነ “አምላክ” የሚለውን ቃል በአብ “መድኃኒት” የሚለውን ደግሞ በኢየሱስ የወሰንከው ከምን ተነስተህ ነው? ካንተ ሙግት በተጻራሪ ሐዋርያው ጳውሎስ አብን “አምላክ” እንዳለው ሁሉ ኢየሱስንም “አምላክ” ብሎታል፤ ኢየሱስን “መድኃኒት” እንዳለው ሁሉ አብንም “መድኃኒት” ብሎታል፡፡ ሙግትህ ውኀ የሚያነሳ አይደለም፡፡

አብዱል

ጳውሎስ ገማልያ እግር ስር ተቀምጦ ይማር የነበረ እስራኤላዊ ሰው ነበር፥ እስራኤላውያን ደግሞ አምላካችን የሚሉት የኢየሱስን አባት ታላቁን አምላክ ነው፦

ዮሐንስ 8፥54 እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው”።

መዝሙር 77፥13 እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው?

መዝሙር 86፥10 አቤቱ፥ ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነህና፥ “አንተም ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህና።

መዝሙረኛው አንድ ነጠላ ማንነት “አንተ” ብሎ በነጠላ ተውላጠ-ስም ከመጠቀሙ ባሻገር ያንን ነጠላ ማንነት “አንተም ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህ” ይለዋል። እውነት ነው፥ እስራኤላውያን አምላካችን የሚሉት ያህዌህ ነው፥ ያህዌህ ብቻውን ታላቅ አምላክ ነው፦

ነህምያ 8፥6 ዕዝራም ታላቁን አምላክ ያህዌህን ባረከ”።

መዝሙር 95፥3 ያህዌህ ታላቅ አምላክ ነውና”።

መልስ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በገማልያል እግር ስር ተቀምጦ የተማረ የይሁዲ እምነት ተከታይ ቢሆንም ክርስትናን ተቀብሎ ሐዋርያ ሆኗል፡፡ ስለዚህ የይሁዲ ሃይማኖት ተከታይ ሆኖ እስከ መጨረሻው የኖረ ይመስል የቀድሞ ሃይማኖቱን መጥቀስ ፋይዳ የለውም፡፡ ክርስትና ከይሁዲ የቀጠለ አዲስ መገለጥ ነው፡፡ አይሁድ በነጠላ ማንነት የሚያውቁት ያሕዌ ኤሎሂም በሦት አካላት የሚኖር አንድ መለኮት መሆኑ ይፋ ሆኗል፡፡ በዘመነ ነቢያትና በክርስቶስ መምጣት መካከል ባሉት ዘመናት እግዚአብሔር በነጠላ አካል ያልተገደበ አምላክ መሆኑን የሚናገሩ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን በማገናዘብ ወደ ሥላሴ አስተምህሮ የቀረበ አቋም የነበራቸው አይሁድ ሊቃውንት እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ የእግዚአብሔር ሥላሴነት በመጨረሻው መለኮታዊ ቃል በአዲስ ኪዳን ይበልጥ ግልፅ ሆኗል፡፡

በብሉይ ኪዳን ስለ ያሕዌ የተነገሩ ብዙ ጥቅሶች በአዲስ ኪዳን ስለ ኢየሱስ መነገራቸውን ያስተዋለ ሰው የተሟላውን መለኮታዊ መገለጥ ሙሉ ምስል ያገኛል፡፡ ማስረጃዎቹን በዚህ ጽሑፍ አሰባስበናል፡- http://www.ewnetlehulu.net/am/who-is-jesus/jesus-is-yahweh/

ዳዊትን የመሳሰሉት ቅዱሳን ነቢያት የመሲሁን አምላክነት አስቀድመው ተናግረዋል፡-

“አሕዛብ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ መንግሥታትም ለእግዚአብሔር (ያሕዌ) ይገዙ ዘንድ … አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል፤ አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም።” (መዝሙር 102፡22-25)

ይህ ጥቅስ መሲሁን የተመለከተ ስለመሆኑ በአዲስ ኪዳን ተጽፏል፡-

“ስለ ልጁ ግን፦ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው፡፡ … ደግሞ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል።” (ዕብራውያን 1፡8)

በዚህ ጥቅስ ውዳሴ የቀረበለት ያሕዌ አምላክ ሰው ሆኖ ወደ ምድር መጥቷል፡፡ የገዛ ወገኖቹ እስራኤላውያን ግን ከጥቂቶች በስተቀር አላወቁትም፤ በቅዱሳን ነቢያት አስቀድሞ እንደተነገረው ለብሶት በመጣው ሥጋ አንገላቱት፣ ሰቀሉት፣ ወጉት፣ ገደሉት፡፡ ሥቃዩና ሞቱ ግን ለሰው ልጆች ኃጢአት ማስተሰርያ መሥዋዕት ሆነ፡፡ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ያረገው ይህ ያሕዌ አንድ ቀን ተመልሶ ይመጣል፡፡ ተመልሶ ከመምጣቱ በፊት ግን አንድ ነገር ይሆናል፤ እስራኤላውያን ማንነቱን አውቀው ተጸጽተው ያለቅሳሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ከክርስቶስ ልደት በፊት 400 ዓመታትን ቀድሞ የኖረው ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡-

“በዳዊት ቤትና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የርኅራኄና የልመና መንፈስ አፈሳለሁ፤ ወደ ወጉኝ ወደ እኔም ይመለከታሉ፤ እነርሱም ለአንድያ ልጅ እንደሚለቀስ ያለቅሱለታል፤ ለበኵር ልጅ ምርር ተብሎ እንደሚለቀስም አምርረው ያለቅሱለታል።” (ዘካርያስ 12፡10) (አ.መ.ት.)

ሙስሊሙ ወገኔ ሆይ፤ የመሲሁን ትክክለኛ ማንነት ማወቅ ትፈልጋለህን? ተመልሶ ሲመጣስ አብረኸው መኖር ትፈልጋለህን? ክብሩን የሚያንኳስሱ፤ ለዝናና ለገንዘብ ሲሉ የሚጽፉ እንዲህ ያሉ ሐሰተኛ ኡስታዞችን መከተል አቁም፡፡ ዛሬውኑ ቅዱስ ቃሉን አንብበህ ጌትነቱን አምነህ ተቀበል፤ የሚገባውንም ክብር ስጠው! እግዚአብሔር አምላክ የልብ ዓይኖችህን ከፍቶልህ ወደ ልጁ ብርሃን ይመራህ ዘንድ የዘወትር ጸሎቴ ነው፡፡



[1] “ዳዋጋንዲስት” የሚለው ቃል “ዳዕዋ” (እስልምናን ለማስፋፋት የሚደረግ ስብከት) እና “ፕሮፓጋንዲስት” (አንድን አስተሳሰብ በሌሎች ውስጥ ለማስረፅ ፕሮፓጋንዳ የሚነዛ ሰው) ከሚሉት ሁለት ቃላት ወንድማችን ሳም ሸሙን ያዋቀረው ቃል ሲሆን ለሙስሊም ሰባኪያን ተገቢ መጠርያ ነው፡፡

 

ታላቁ አምላክና የግራንቪል ሻርፕ ሕግ

መሲሁ ኢየሱስ