ጦጢት ተወገረች!
የማይታመን የሐዲስ ተረት
እስላማዊ ሐዲሳት እንደ ቁርኣን ሁሉ ከእውነት የራቁ ብዙ አስገራሚ አፈ ታሪኮችን በውስጣቸው የያዙ መጻሕፍት ናቸው፡፡ እነዚህን አፈ ታሪኮች በአስተውሎት የተመለከተ ሰው መጻሕፍቱ ስለ ሙሐመድ የሚሰጡትን ምስክርነቶች በተመለከተ ለጥርጣሬ መዳረጉ የማይቀር ነው፡፡ ለዛሬ በዚህች አጭር ጽሑፍ የምንመለከተው ዓምር ቢን ማዕሙና የተሰኘ የሙሐመድ የቅርብ ተከታይ ከእስልምና ዘመን በፊት እንዳጋጠመው የተናገረውን ታሪክ የተመለከተ ነው፡፡ ልብ በሉ፤ ተናጋሪው ከሙሐመድ ሰሓባዎች መካከል አንዱ ሲሆን ከእስልምና ዘመን በፊት የገጠመውን ትክክለኛ ገጠመኝ ነው የሚያወጋው፡፡ እንዲህ ይላል፡-
Narrated ‘Amr bin Maimun:
During the pre-Islamic period of ignorance I saw a she-monkey surrounded by a number of monkeys. They were all stoning it, because it had committed illegal sexual intercourse. I too, stoned it along with them. (Sahih al-Bukhari, Volume 5, Book 58, Number 188)
“ዓምር ቢን ማዕሙና እንደተናገረው፡-
‹‹ከእስልምና በፊት በነበረው ያለማወቅ ዘመን አንዲት ሴት ጦጣ በብዙ ጦጣዎች ተከባ አየኋት፡፡ ሕገ ወጥ የወሲብ ግንኙነት በመፈፀሟ ምክንያት በድንጋይ ሲወግሯት ነበር፡፡ እኔም አብሬያቸው ወገርኳት፡፡››” (ሳሂህ አል-ቡኻሪ፣ ቅፅ 5፣ መጽሐፍ 58፣ ቁጥር 188)
ይህንን የተናገረው ከሙሐመድ ተከታዮች መካከል አንዱ ሲሆን ተዓማኒ ሐዲስ ተደርጎ በአል-ቡኻሪ ስብስብ ውስጥ ተካቷል፡፡ ጥቂት ጥያቄዎች ስለዚህ ሐዲስ፡-
1. ይህ የሙሐመድ ተከታይ ጦጢት ስለፈፀመችው ኃጢአት ሊያውቅ የቻለው እንዴት ነው? ጦጣዎቹን ጠይቆ ወይንስ ወንጀሉን ስትፈፅም ተከታትሎ አይቷት? አይቷትስ ቢሆን ወንዱ ጦጣ ሕጋዊ ባሏ እንዳልሆነ በምን መንገድ አወቀ?
2. ወንዱ ጦጣ የት ገባ? ሮጦ አምልጦ ይሆን?
3. በእንስሳት ዓለም በተለይም በጦጣዎች ዘንድ እንዲህ ያለ ልማድ ስለመኖሩ ሙስሊሞች ማስረጃ ሊያቀርቡልን ይችላሉ?
አሁን ወደ ቁም ነገሩ፡፡ ይህ ሐዲስ አፈ ታሪክ መሆኑ ምንም ጥርጥ የለውም፡፡ ነገር ግን እንደ ተዓማኒ ታሪክ ተቆጥሮ ከቁርኣን ቀጥሎ ትልቅ ደረጃ በተሰጠው የሐዲስ ስብስብ ውስጥ ሰፍሯል፡፡ እንዲህ ያሉ ታሪኮችን እንደ እውነተኛ ታሪክ የሚቆጥሩ ሰዎች የአስተሳሰብ ደረጃቸው በጣም ዝቅተኛ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ምናልባት በሰባተኛው ክፍለ ዘመን በአረብ በረሃ ውስጥ ለኖረ ቤድዊን ትርጉም ይሰጥ ይሆናል፤ በሰለጠነው ዓለም ለሚኖር ሰው ግን ትርጉም አልባ ተረት ነው፡፡ ሙሐመድ እውነተኛ ነቢይ መሆኑን እንዳረጋገጡ የነገሩን ሰዎች መሰል ታሪኮችን ከእውነት የሚቆጥሩ ወገኖች መሆናቸው ደግሞ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ሙሐመድን በቅርበት የሚያውቁት እነዚያ የዓይን እማኞች መሰል ታሪኮችን እንደ እውነተኛ ታሪክ የሚቀበሉ ከሆነ ስለ ሙሐመድ የሰጧቸውን መስክርነቶች ለመጠራጠር በቂ ምክንያት አለን፡፡
መልስ ብሎ ዝም!
——————————
አምር ቢን ማዕሙና የተባለ የሙሐመድ ሰሐባ ከእስልምና ዘመን በፊት አንዲት ጦጣ ዝሙት በመፈጸሟ ምክንያት ሌሎች ጦጣዎች ሲወግሯት ተመልክቶ እርሱም አብሯቸው እንደወገራት የተናገረበትን ሐዲስ ጠቅሰን ጥያቄ ማንሳታችን ይታወሳል። ይህንን ያነበበ አንድ አብዱል “መልስ” ብሎ የለጠፈውን “እውን ነቢዩ ጨካኝና ዝንጀሮ ወጋሪ ነበሩን?” በሚል ርዕስ የተጻፈ ጽሑፍ አንብበናል። ጸሐፊው የኦርቶዶክ መምህራንን ሲሳደብ ይታያል። ለዚህ ሥርኣት አልበኝነቱ መልስ መስጠቱን እናቆየውና የነገሩን አስኳል እንመልከት። ባጠቃላይ በጽሑፉ ውስጥ የኛን ሙግት የሚጠቅስ ምንም ነገር የለም።
1. ጦጢትን የወገራት ሙሐመድ ነው የሚል ነገር እኛ በጻፍነው ጽሑፍ ውስጥ የሌለ ቢሆንም ጸሐፊው “ሙሐመድ ነው ብለዋል!” በሚል መነሻ ልክ እንደተቆጣ ዝንጀሮ ያገኛውን ሰው ሁሉ ሲቧጭርና መንደሩን ሲያመሰቃቅል ይታያል። ይህ ጽሑፍ ከ 3 ዓመታት በፊት የተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል። መቼስ መልሶ የለጠፈው ሰው የኛን ጽሑፍ ታሳቢ በማድረግ መሆኑ ግልጽ ነውና እኛ “ሙሐመድ ነው” ያልንበትን ቦታ እንዲያሳየን እንጠይቀዋለን። አለማንበብ “የነቢዩ” ሱና ቢሆንም ትዝብት ላይ ላለመውደቅ በተቻለ መጠን ማንበብ ጥሩ ነው።
2. እንዳየነው የጽሑፉ ርዕስ “እውን ነቢዩ ጨካኝና ዝንጀሮ ወጋሪ ነበሩን?” ይላል። ኋላ ላይም ሙሐመድ “የተላከበትን” ዓላማ ሲገልጽ “ከዚህ ሰይጣናዊ ተግባር ሊያወጣቸው” እንደሆነ ይገልጻል። ስለዚህ ዝንጀሮ መውገር ሰይጣናዊ ተግባር ከሆነ ሙሐመድ ሰውን የሚያክል ክቡር ፍጥረት ያለ በቂ ምክንያት ሲገድልና ሲያስገድል የኖረ፣ እራሱም ዝሙተኛ ሆኖ ሳለ ሌሎችን ሲወግር የነበረ በመሆኑ ይህንን ድርጊቱን ምን ልትለው ነው? ዝንጀሮ መውገርን “ሰይጣናዊ” ስላልከው ሌላ የከፋ ቃል ፈልግለት። ደግሞም እንስሳትን ያለ በቂ ምክንያት መግደል ትክክል ካልሆነ ሙሐመድ ጥቁር ውሾችን፣ እባቦችንና እንሽላሊቶችን ያለ ምንም ምክንያት እንዲገድሉ ሙስሊሞችን ማዘዙን እንዴት ትመለከተዋለህ? እንዲያውም እንሽላሊትን በአንድ፣ በሁለት ወይንም በሦስት ምት የገደለ ሰው እንደየደረጃው ከአላህ ዘንድ ምንዳ እንደሚጠብቀው ተናግሯል። (Muslim, Book 026, Number 5562; Muslim Book 026, Number 5564; Sunan of Abu Dawud Book 41, Number 5229; Bukhari 4.526)
3. ይህንን ድርጊት የጥንቶቹም ሆኑ የዘመኑ ሙስሊም ሊቃውንት ዝሙት የሰሩትን ሰዎች መውገር አስፈላጊ መሆኑን ለማሳየት ሲጠቅሱት ኖረዋል። ሐዲሱም ቢሆን በእስልምና የታረመ የተሳሳተ ተግባር እንደሆነ አይገልጽም። “ከዚህ ሰይጣናዊ ተግባር ሊያወጣቸው” ያልከው ምን ማስረጃ ይዘህ ነው?
4. የኛ ሙግት ታሪኩ ሲጀመር ተረት እንጂ እውነት ባለመሆኑ “በተዓማኒ” ሐዲስ ውስጥ መካተቱ በሙሐመድ አጠቃላይ ታሪክ ላይ ጥያቄን ያስነሳል የሚል ነው። እንዲህ ያሉ ተረታ ተረቶችን ከእውነት የሚቆጥሩ ሰዎች ትክክለኛ ታሪክ ማስተላለፍ ይችላሉ ብሎ ማለት ዘበት ነው። ለዚህ ሙግት ምላሽ እንደሌለህ ስለምታውቅ ነው Strawman fallacy የሸከፈ ኮተት የለጠፍከው። መልስ መስጠት ካልቻሉ ዝም ማለት አንድ ነገር ነው። እንዲህ ያለ አርቲ ቡርቲ ከየትም አምጥቶ መለጠፍ ግን አንባቢን መናቅ ነው። ኧረ ወገናችን፤ አንባቢዎችህን የሚመጥን ነገር ጻፍ አለበለዚያ ደግሞ ለአቅመ ማስተማር እስክትበቃ ድረስ ጊዜ ወስደህ ተማር።