ኢየሱስ በመጨረሻው ቀን መንግሥትን ለአብ ማስረከቡና ለአብ መገዛቱ ንግሥናው በጊዜ የተገደበ መሆኑን አያሳይምን?

ኢየሱስ በመጨረሻው ቀን መንግሥትን ለአብ ማስረከቡና ለአብ መገዛቱ ንግሥናው በጊዜ የተገደበ መሆኑን አያሳይምን?


መጽሐፍ ቅዱስ ላይ «ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፡ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፡ መጀመሪያ በኩራት የሆነው ክርስቶስ ከዚያም በኋላ እርሱ ሲመጣ የክርስቶስ የሆኑት፡፡ ከዚያም ግዛትን ሥልጣንና ኃይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግስትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ ያን ጊዜ ፍፃሜ ይሆናል፡፡ ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስኪያደርግ ድረስ ሊነገሥ ይገባዋልና፡፡» (1ኛ ቆሮንቶስ 15:22-24) እንዲሁም «ሁሉ ከተገዛለት በኋላ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል» ይላል፡፡ (1ኛ ቆሮንቶስ 15:28) (የ1980 አትም) ኢየሱስ ሥልጣን እንደ ተሰጠው ተናግሯል፡፡ ግን ይህ ጥቅስ በሚገርም መልኩ ስልጣኑን እንደሚያስረክብ ይገልፃል፡፡ ታዲያ ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ ከስልጣን የሚወርድ ከሆነ ምኑ ላይ ነው የእርሱ አምላክነት? ኢየሱስ ከስልጣኑ ወርዶ ለአምላኩ የሚገዛ ከሆነ ምኑን አምላክ ሆነ? ክርስቲያኖች አሻፈረን አሉ እንጂ ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለም አምላኩን ሲገዛ አልነበረም? ኢየሱስ የሚነግሠው በጥቅሱ “ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስኪያደርግ ድረስ ሊነግስ ይገባዋል፡፡” በማለት እንደተገለፀው ከሆነ የእርሱ “ንግስና” በጊዜ የተገደበ ነው፡፡ አምላክ ግን ከዘለዓለም እሰከ ዘለዓለም ንጉስ ነው፡፡ ስልጣንን ለማንም አያስረክብም፡፡ ኢየሱስ ግን “መንግስትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክበው፡ ያን ጊዜ ፍፃሜ ይሆናል፡፡” ተብሎ እንደተገለፀው ስልጣኑን ያስረክበዋል፡፡ ታዲያ ኢየሱስን አምላክ ልንለው እንዴት ይቻለናል? ጥቅሱ እግዚአብሔርን ነው እንጂ “እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን” ያለው ኢየሱስን አይደለም፡፡ አልያም “አንድ እግዚአብሔር የሚሆኑት አብ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን” አላለም፡፡ ታዲያ እንዴት ኢየሱስ አምላክ ሊባል ይችላል?

በአዲስ ኪዳን ውስጥ አውዱ ግልፅ እስካላደረገ ድረስ “እግዚአብሔር” ተብሎ ሲጠቀስ አብን ለማመልከት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ጥቅስ ውስጥ “እግዚአብሔር” የተባለው አብ ነው፡፡

በሥላሴ አስተምህሮ መሠረት ልጅ ለአባት እንደሚገዛ ሁሉ ወልድም ፈቅዶ ለአብ ይገዛል፡፡፡ ነገር ግን አባትና ልጅ እንደ ሰው ያላቸው እሴት (Value) እኩል እንደሆነ ሁሉ አብና ወልድም እኩል ናቸው፡፡ ወልድ በአምላካዊ ባሕርዩ ከአብ ያነሰ አይደለም፡፡ አብም በአምላካዊ ባሕርዩ ከወልድ የበለጠ አይደለም፡፡ ስለ ሥላሴ አካላት እኩልነት ስንናገር በመለኮታዊ ባሕርይ ማለታችን እንጂ በግብር (በሥራ ድርሻቸው Function) ማለታችን አይደለም፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ወልድ ለአብ መገዛቱን መናገሩ የሥላሴን አስተምህሮ የሚያፀና እንጂ የሚፃረር አይደለም፡፡ ሌላው መረሳት የሌለበት ጉዳይ የኢየሱስ ፍፁም ሰው መሆን ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ሲያርግ ፍፁም ሰው የሆነውን ደግሞም ከሙታን የተነሳውንና የከበረውን ሥጋውን በመተው አይደለም፡፡ ይህ ማለት ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው ሆኖ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሁኔታ ለአብ እንደሚገዛ ለመነገሩ እንደ ተጨማሪ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

1ኛ ቆሮንቶስ 15፡28 ላይ የኢየሱስን ለአብ መገዛት ለማመልከት ጥቅም ላይ የዋለው ቃል “ሁፖታጊሰታይ” የሚል ሲሆን ደረጃን እንጂ ባሕርይን የሚያመለክት አይደለም፡፡ ይህ የግሪክ ቃል የሚነበብበት ድምፀት ወልድ ተገዶ ወይም ትዕዛዝ ተሰጥቶት ሳይሆን በፍቃደኝነት ራሱን በራሱ ለአብ እንደሚያስገዛ ያሳያል፡፡ በዚህም መሠረት በመለኮታዊ ሥልጣኑ ከአብ የተካከለው ወልድ ወዶና ፈቅዶ ለአባቱ ይታዘዛል ማለት ነው። ይህ ትሑት ባሕርዩን የሚያሳይ እንጂ በሥልጣን ከአብ ማነሱን የሚያመለክት አይደለም። በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ የግሪክ ቋንቋ ሊቅ የሰጡትን ሐተታ በግርጌ ማስታወሻው ላይ ይመልከቱ፡፡[1]

ኢየሱስ ከሥልጣን የሚወርድበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ንግሥናውስ ይሻር ይሆን? የዚህን ጥቅስ ትክክለኛ ትርጉም ከማስቀመጣችን በፊት እስኪ መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን ዘለዓለማዊ ንግሥና በተመለከተ ምን እንደሚል እንይ፡-

እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም” (ሉቃስ 132-33)፡፡

በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት፡፡ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው ግዛቱም የማያልፍ የዘለዓለም ግዛት ነው መንግሥቱም የማይጠፋ ነው” (ዳንኤል 713-14 ከማርቆስ 1461-62 ጋር ያነፃፅሩ)፡፡

ስለ ልጁ ግን፦ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘለዓለም ድረስ ይኖራል የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው” (ዕብራውያን 18)፡፡

እንዲሁ ወደ ዘለዓለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋልና” (2ጴጥሮስ 111)፡፡

ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም፡፡ የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል” (ኢሳይያስ 96-7)፡፡

ሰባተኛው መልአክ ነፋ፤ በሰማይም፦ የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፥ ለዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ይነግሣል የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ሆኑ” (ራዕይ 1115)፡፡

ሌላ ቦታ ላይ ቅዱሳን የሚወርሱት መፃዒው መንግሥት የአብና የወልድ መሆኑ ተነግሯል፡-

ይህን እወቁ፤ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኵስ ወይም የሚመኝ እርሱም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም” (ኤፌሶን 55)፡፡

ስለዚህ መፃዒው መንግሥት የክርስቶስና የእግዚአብሔር አብ መሆኑ ከተነገረ ኢየሱስ ግዛትን ሥልጣንና ኃይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለአብ ማስረከቡ የተነገረው ለአብ መገዛቱን አፅንዖት ለመስጠት እንጂ ንግሥናው ጊዜያዊ እንደሆነ ለማመልከት አይደለም፡፡ ከዚህ ትርጓሜ በተፃራሪ መጽሐፍ ቅዱስ በሚመጣው ዓለም አብና ወልድ አንድ ዙፋን እንደሚኖራቸው ይናገራል፡-

በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን [ነጠላ] የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ፡፡ በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፥ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ፡፡ ከእንግዲህም ወዲህ መርገም ከቶ አይሆንም፡፡ የእግዚአብሔርና የበጉም ዙፋን [ነጠላ] በእርስዋ ውስጥ ይሆናል፥ ባሪያዎቹም ያመልኩታል፥ ፊቱንም ያያሉ፡፡” (ራዕይ 221-7)፡፡

ጠያቂው ከሰጠው ትርጓሜ በተጻራሪ “ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስኪያደርግ ድረስ ሊነግስ ይገባዋል” መባሉ ንግሥናው ጊዜያዊ መሆኑን አያመለክትም፡፡ ለምሳሌ ያህል እስኪ የሚከተሉትን ጥቅሶች ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፡-

እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና” (ዘፍጥረት 2815)፡፡ ከዚያ በኋላ ይተወዋል ማለት ነው?

የሳኦልም ልጅ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም” (1ሳሙኤል 623)፡፡ ከዚያ በኋላ መውለድ ትችላለች ማለት ነው?

እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ” (ማቴዎስ 518)፡፡ ከተፈፀመ በኋላ ያልፋል ማለት ነው?

እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴዎስ 2820)፡፡ ከዚያ በኋላ ይለያቸዋል ማለት ነው?

እግዚአብሔርም ለአብርሃም የማለለት የተስፋው ዘመን ሲቀርብ፥ ዮሴፍን የማያውቀው ሌላ ንጉሥ በግብፅ ላይ እስኪነሣ ድረስ፥ ሕዝቡ እየተጨመሩ በግብፅ በዙ” (የሐዋርያት ሥራ 717-18)፡፡ ከዚያ በኋላ መብዛት አቆሙ ማለት ነው?

እንዲህ ዓይነት አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቁርአንም ውስጥ ይገኛል፤ ለምሳሌ፡-

አላህም ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ ዒሳ ሆይ! እኔ ወሳጂህ ወደ እኔም አንሺህ ነኝ፡፡ ከነዚያም ከካዱት ሰዎች አጥሪህ ነኝ እነዚያንም የተከተሉህን እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ ከነዚያ ከካዱት በላይ አድራጊ ነኝ፡፡ ከዚያም መመለሻችሁ ወደእኔ ነው፡፡” (ሱራ 355)፡፡ ከዚያ በኋላ የበታቾች ይሆናሉ ማለት ነው?

እርግማኔም እስከ ፍርዱ ቀን ድረስ ባንተ ላይ ይኹን” (ሱራ 3837)፡፡ ከፍርዱ ቀን በኋላ የአላህ እርግማን ከሰይጣን ላይ ይነሳል ማለት ነው?

ስለዚህ “እንዲህ እስኪሆን ድረስ” የሚል ሐረግ ስለገባ ብቻ ድርጊቱ የሆነ ጊዜ ላይ ያቆማል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የተባለው ነገር እስኪፈፀም ድረስ ድርጊቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው የሚገልፅ የተለመደ አባባል ነው፡፡ ስለ ኢየሱስ ንግሥና የተነገረውንም በዚሁ መልኩ መረዳት ያስፈልጋል፡፡


[1] The translation of the verb as “the Son Himself also will be subjected to the One” is very misleading. It is taken as a passive, whereas the exegesis demands that it should be taken as a middle voice which means that the Lord Jesus Christ at the completion of His mediatorial work subjects Himself to the One who had subjected all things unto Him. It is a voluntary act and not a compulsory subjugation of one person of the Trinity to the other. This is not something which took place while the Lord Jesus was the God-Man on earth, but it is something that will take place in the future when all people will be made subject unto Christ, and then He will finally subject Himself with the finished work of redemption before God the Father. (Spiros Zodhiates, New American Hebrew-Greek Key Word Study Bible, 1990, p. 1530)


 

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ

መሲሁ ኢየሱስ