የክርስቶስ ትንሣኤና የከፊል ሞት እሳቤ

የክርስቶስ ትንኤና የከፊል ሞት እሳቤ

በወንድም ትንሣኤ


ታሪክን ተጠቅመን በቀላሉ ማረጋገጥ ከምንችላቸው የክርስትና አስተምህሮዎች መካከል አንዱ የክርስቶስ ትንሣኤ ነው። በታሪክ ተመራማሪዎች ዘንድ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደፈጸማቸው ጥርጥር የሌለባቸውን እውነታዎችን ብቻ ብንወስድና ብንመዝን ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ ለመደምደም የሚከለክለን አንዳችም ምክንያት አይኖርም። ከነዚህ እውነታዎች ውስጥ የክርስቶስ መሰቀል፣ መቀበር፣ በሦስተኛው ቀን የመቃብሩ ባዶ ሆኖ መገኘትና ብዙ ተከታዮቹ እንዳዩት መዘገባቸው ይጠቀሳሉ።

ትንሣኤውን የማይቀበሉ ወገኖች ታዲያ እነዚህን እውነታዎች በሌላ መንገድ ለማብራራት ከመሞከር አልቦዘኑም። ከነዚህ መንገዶች አንዱ በኢ-አማንያን ተጀምሮ በሙስሊም አቃቤ እምነታውያን ሲስተጋባ የሚስተዋለው የከፊል ሞት ወይም ራስን የመሳት እሳቤ (Swoon Theory) ነው። በዚህ እሳቤ መሠረት ከሆነ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ራሱን በመሳቱ ምክንያት (ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ የእንቅልፍ መድኃኒት ወይም ማደንዘዣ ሰጥቶት የሚሉም አሉ) የሞተ የመሰላቸው ሮማውያን ቢቀብሩትም ከእንቅልፉ ነቅቶ ለሐዋርያቱ ተገልጦ በመታየቱ ከሞት ተነስቷል የሚለው ትምህርት ሊስፋፋ ችሏል።

እንደ ዛኪር ናይክ እና አሕመድ ዲዳት ያሉ እውቅ ሙስሊም ሰባኪያን ጭምር ይህንኑ እሳቤ በማስተገባት ይታወቃሉ።[1][2]

ይህ አመለካከት ግን ካለን ታሪካዊና ስነ-አካላዊ ማስረጃ ጋር ፈጽሞ የማይስማማ ነው። ኤድዋርድ፣ ጋቤል እና ሆስመር የተባሉ ሦስት ዕውቅ የጤና ባለሙያዎች በጥምር ባሳተሙት ጽሑፍ በዘመኑ ከስቅለት በፊት ይደረግ ስለነበረው የግርፋት ሂደት የሚከተለውን ይላሉ-

“…የተለመዱት መግረፊያዎች አጭር ጅራፍና በተወሰነ እርቀት የብረት ወይም የአጥንት ቁርጥራጮች የታሰረባቸው ቁመታቸው የተለያዩ የሆኑ የቆዳ መቆንጠጫዎች ነበሩ። የሚሰቀለው ሰው ልብሱን ይገፈፍና ቀጥ ያለ እንጨት ላይ ይታሰራል፤ ጀርባው፣ እግሩና መቀመጫው ይገረፋሉ። የግርፋቱ አላማ ሰውየውን ለሞት ትንሽ እስኪቀረው ድረስ ማድከም ነው፤ የሮም ወታደሮች በሙሉ ኃይላቸው የሰውየውን ጀርባ በሚመቱበት ሰዓት የብረት ቁራጮቹ ሰውነቱ ላይ ጥልቅ ቁስል እንዲፈጠር ያደርጋሉ። አጥንቶቹም ቆዳውን በስተው በመጥለቅ ከባድ ጉዳት ያደርሳሉ።…” [3]

ይህ እንግዲህ አንድ የሚሰቀል ሰው ከመሰቀሉ በፊት የሚፈፀምበት የማዘጋጃ ግርፊያ ብቻ ነው። አንድ ሰው ይህንን መሰል ግርፋት ተገርፎ በሕይወት ቢተርፍ እንኳን ለወዳጆቹ ተገልጦ ከሞት ተነስቻለው ብሎ ሊያስተምር ይቅርና ምሑራኑ እንደሚሉት “ቢያንስ ለአንድ ወር ያህል መራመድ አይችልም” [4]

 ክርስቶስ እስከ ስቅለቱ ፍጻሜ ድረስ በሕይወት ነበረ ቢባል እንኳን በወንጌላት እንደምናገኘው ሮማውያን ወንጀለኞቹ እንደሞቱ ለማረጋገጥ ሲሉ የሰዎቹን ጭን መስበር አልያም ጎናቸውን በጦር መውጋት ያዘወትሩ ነበር። ይህንን ከወንጌላት ውጪ ማርከስ ቁንጥሊያኖስ የተባለው የአንደኛ ክፍለዘመን የሮም ጸሐፊ ዘግቦት ይገኛል።[5] ስለዚህ የክርስቶስ መሰቀል በራሱ የአተነፋፈስ ስርአቱ ላይ ከባድ ችግር ስለሚያስከትል በጦር መወጋቱ መሞቱን ፈጽሞ እንዳረጋገጠው መደምደም እንችላለን።

ከላይ ያየናቸው ሦስት ምሁራንም ይህንኑ በመደገፍ እንዲህ ይላሉ፦

“የናዝሬቱ ኢየሱስ የሮምና የአይሁድ የፍርድ ሂደትን አልፏል፣ ተገርፏል፣ ተሰቅሏልም። ግርፊያው በቆዳው ላይ ስንጥቅጥቆችንና በዛ ያለ የደም ፍሰትን አስከትሏል። መስቀሉን እስከ ጎሎጎታ መሸከም አለመቻሉን አይተን መረዳት እንደምንችለው ግርፋቱ ልቡ ወደ ሰውነቱ ክፍሎች ደም መርጨት እንዳይችልና፣ ድካም እንዲሰማው አድርጎታል። የስቅለቱ ቦታ ላይ ሲደርስ እጆቹ ተቸንክረዋል፤ እንጨቱን ካቆሙት በኋላ ደግሞ እግሩንም ቸንክረውታል። የስቅለት ዋነኛ ዓላማ ትክክለኛ አተነፋፈስን መከልከል ነው፤ በዚህም ምክንያት ኢየሱስ በትንፋሽ እጥረትና በደም ፍሰት ሊሞት ችሏል። የኢየሱስ ሞት ወታደሩ ጎኑ ላይ ባስገባው ጦር እርግጥ ሆኗል፤ ያለን ታሪካዊ መረጃ በዘመናዊው የኅክምና ትምህርት ሲተነተን ኢየሱስ ከመስቀል ሲወርድ ሞቶ እንደነበር ያሳያል።”[6]

ይኸው ጥናት ኢየሱስ (Most probably) በጦር ከመወጋቱ በፊትም ሞቶ እንደነበርና ማንኛውም አይነት የከፊል ሞት እሳቤ ከዘመናዊ የኅክምና ሳይንስ ጋር ፈጽሞ ሊስማማ እንደማይችል ይደመድማል።[7]

የዚህን እሳቤ ደካማነት የሚያረጋግጠው ሌላው ነጥብ እሳቤው የተፈጠረበትን አላማ በቅጡ ማሳካት ያልቻለ መሆኑ ነው። የዚህ እሳቤ አቀንቃኞች ይህንን ሐሳብ የሚነዙት በዋነኝነት የኢየሱስን ለሐዋርያቱ መገለጥ ለማብራራት ነው። ነገር ግን ዴቪድ ስትራውስ የተባለ የ 19 ክፍለዘመን ሊቅ እንደሚለው “አንድ ከሞት በከፊል ነቅቶ ድካምና ህመም እየተሰማው ኅክምና ሲፈልግ የነበረ ሰው ለደቀመዛሙርቱ “የሞት አሸናፊና የሕይወት ልዑል” እንደሆነ ሊያሳምናቸው ይችላል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ አይቻልም”[8]

በተጨማሪም መቃብሩን ይጠብቁ የነበሩትን ሮማውያን መርሳት የለብንም። ፖሊቢየስ የተባለ የታሪክ ጸሐፊ በጥበቃ ሰዓት ጥፋት ስላጠፉ ወታደሮች እንዲህ ይላል-

“ግዴታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ ወታደሮች ‘ፉስታሪየም’ የተባለውን በድንጋይ የመወገር ቅጣት ይቀጡ ነበር። ከዚህ ድብደባ እንደምንም በሕይወት ቢተርፉ እንኳን ወደ ሀገራቸውም ሆነ ቤታቸው የመመለስ ምንም ተስፋ የላቸውም።”[9] ወታደሮቹ ላይ ከባድ ቅጣት ይጣል እንደነበረ ከወንጌላትም መረዳት ይቻላል (ማቴዎስ 28:14 ስራ 16:27)። ስለዚህ ለሮም ወታደሮች በስቅለትና ግርፋት አልፎ በቅጡ መራመድ እንኳን የማይችል ሰው ቋጥኝ አንከባልሎ ሲያመልጥ ተቀምጦ መመልከት ሕይወት ላይ መቆመር ነው የሚሆነው።

ስናጠቃልል ይህ እሳቤ ሦስቱን የታሪክ እውነታዎች (የክርስቶስ መቀበር፣ በሦስተኛው ቀን ባዶ መቃብር ትቶ መነሳትና ለሐዋርያቱ መገለጥ) ከማረጋገጥ ባለፈ ትንሣኤው ላይ አንዳች ጥርጣሬ የሚጭር አይደለም።


[1] https://youtu.be/jICKPV5BJKQ

[2] Ahmed Deedat, Crucifixion or Crucifiction , Chapter 16.

[3] The American Medical Association, On the physical death of Jesus Christ, page 255.

[4] Fredrick Zugibe, The Crucifixion of Jesus a forensic inquiry, page 161.

[5] Marcus Quintilian , Declarationes Maiores , 6:9.

[6] The American Medical Association, On the physical death of Jesus Christ, page 255.

[7] Ibid.

[8] David Strauss, The Life of Jesus for the people, Volume 1 page 412.

[9] Polybius, The Histories, Volume 6 pages 36-37.


መሲሁ ኢየሱስ