ተመሳሳዮቹ ወንጌላት ተጻራሪ ወይስ ተሰባጣሪ?

ተመሳሳዮቹ ወንጌላት ተጻራሪ ወይስ ተሰባጣሪ?


ዊኪፔድያን ከመሳሰሉት የለዘብተኛ ሥነመለኮት ምሑራን የሐሳብ መድረኮች ከሆኑት ክፍት ምንጮች (Open Sources) መረጃዎችን በመቃረም በሚታወቅ ሙስሊም ሰባኪ የተጻፈ ጽሑፍ በማሕበራዊ ሚድያዎች ሲዘዋወር ተመልክተናል፡፡ የጽሑፉ ይዘት ለመልስ የሚመጥን ባይሆንም ብዙ ሙስሊም ወገኖቻችን እንደ ጥሩ የሙግት ሐሳብ በመቁጠር ሲቀባበሉት በመታዘባችን መልስ ልንሰጠው ወደድን፡፡ ሙስሊሙ ሰባኪ “መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟል” የሚለውን በታሪክም ሆነ በቀደምት እስላማዊ ምንጮች ተቀባይነት  የሌለውን የዘመናችን ሙስሊሞች መሠረተ ቢስ እምነት እንደሚደግፍ ያመነውን አንድ የቁርኣን ጥቅስ በመጥቀስ ይጀምራል፡፡

አብዱል

2፡79 ለእነዚያም መጽሐፉን በእጆቻቸው ለሚጽፉ እና ከዚያም በእርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «ይህ ከአላህ ዘንድ ነው» ለሚሉ ወዮላቸው፡፡ ለነርሱም ከዚያ እጆቻቸው ከጻፉት ወዮላቸው፡፡ ለነሱም ከዚያ ከሚያፈሩት ኃጢኣት ወዮላቸው፡፡

መልስ

ሙስሊም ሰባኪያን መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ሳይሆን ቁርአናቸውንም እንደሚያጣምሙ ይህ ጥቅስ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ጥቅስ መጽሐፍ ቅዱስን የተመለከተ አለመሆኑን ለማወቅ የተሟላውን የጥቅሱን አውድ ያገናዘበ ማብራርያ መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ! በሚል ርዕስ ባዘጋጀነው ጽሑፍ ውስጥ ያገኛሉ፡፡ ገጹን ወደ ታች በመሳብ የመጨረሻውን ክፍል ይመልከቱ፡፡

አብዱል

ኢየሱስ በዐረማይክ ዘዬ ተናግሮት የነበረው ቀዳማይ ወንጌል ጥናት በነጠላ “ሎጂኦን” λόγιον በብዜት “ሎጂያ” λόγια ይባላል። ይህም በቃል”oral” ሲተላለፍ የነበረ ወንጌል ነበር። ሐዋርያቱም ለተማሪዎቻቸው በቃል ሲያስተላልፉ ኢየሱስ ያስተማረውን ወንጌል ብቻ ሳይሆን ያሳለፈውን የሕይወት ታሪክ፣ የሠራውን ታምር እና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ያደርጋቸው የነበሩት ሙግቶችን ጨምረው አስተላልፈዋል። እነዚህም ተማሪዎች ከተለያየ ምንጭ ሲሰበስቡት የነበረው ስብስብ የሚያጠናው ጥናት “አንቶሎጂ” ἀνθολογία ይባላል።

መልስ

በመጀመርያ ደረጃ λόγιον የሚለው ቃል “ሎጊዮን” እንጂ “ሎጂኦን” ተብሎ አይነበብም፡፡ λόγια የሚለውም ቃል “ሎጊያ” እንጂ “ሎጂያ” ተብሎ አይነበብም፡፡ ἀνθολογία የሚለውም ቃል “አንቶሎጊያ” እንጂ “አንቶሎጂ” ተብሎ አይነበብም፡፡ በግሪክ ቋንቋ ውስጥ “ጀ” ድምፅ ያለው ፊደል የለም፡፡ γ (ጋማ) ፊደል የ “ገ” ድምፅ ነው ያለው፡፡ ይህ ጸሐፊ የግሪክ ቋንቋ ፊደላትን እንኳ መለየት ስለማይችል በእንግሊዝኛ ትራንስሊትሬት የተደረገውን በመመልከት በግሪክ ቋንቋ በማይታወቅ ድምፀት ሲያነበው እንታዘባለን፡፡ ጉዳዩን “ትውፊት” በሚል አገርኛ ቃል መግለፅ ሲቻል በማያውቀው ቋንቋ ውስጥ ገብቶ አጉል መዘላበድ ለምን እንዳስፈለገው በእውነቱ ግራ ይገባል፡፡ ቋንቋውን የሚያውቅ መስሎ በአንባቢያን ፊት በመቅረብ ደረጃውን ለማላቅ ፈልጎ ከሆነ አሳፋሪ ተግባር ነው፡፡ የእንግሊዝኛውን ትራንስሊትሬሽን እንኳ በትክክል ማንበብ ሳይችሉ ያልሆኑትን ሆኖ ለመታየት መሞከር ትርፉ ቅሌት ነው፡፡

አብዱል

“ሲኖፕቲክ”Synoptic” የሚለው የኢንግሊሹ ቃል “ሲኖፕቲከስ” συνοπτικός ከሚለው ከግሪኩ ቃል የተወሰደ ሲሆን “ተመሳሳይ” ወይም “ተከታታይ” ማለት ነው። የማርቆስ፣ የማቴዎስ እና የሉቃስ ወንጌል ከዮሐንስ ወንጌል በተለየ መልኩ ታሪካቸው፣ ይዘታቸው እና ቅድመ ተከተላቸው መመሳሰል ስላላቸው “ሲኖፕቲክ ወንጌል” ይባላሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ የተለያየ ንድፈ-አሳብ”theory” አሉ፤ እነዚህም፦ የማቲያን ተቀዳሚነት፣ የማርካን ተቀዳሚነት፣ የሉካን ተቀዳሚነት እና “Q” ምንጭ ናቸው።

መልስ

ሙስሊሙ ጸሐፊ አንዱንም የግሪክ ቃል አስተካክሎ መጻፈፍ አልቻለም፡፡ συνοπτικός የሚለው ቃል “ሲኖፕቲከስ” ሳይሆን “ሱኖፕቲኮስ” ተብሎ ነው የሚነበበው፡፡ ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ በብዙ መልኩ መመሳሰል ስላላቸው “ተመሳሳዮቹ ወንጌላት” (Synoptic Gospels) በመባል ይታወቃሉ፡፡

አብዱል

± የማቲያን ተቀዳሚነት የሚባለው የአውግስቲን ንድፈ-አሳብ መሰረት ያደረገ ቅድሚያ የዘገበው ማቴዎስ ነው የሚል ንድፈ-አሳብ ነው፥ ይህም “ኤም” M ምንጭ ይባላል፤ “M” የሚለው “ማቴዎስ ምንጭ”source” ማለት ነው።

± የማርካን ተቀዳሚነት የሚባለው የአዩስቲን ፋረር ንድፈ-አሳብ መሰረት ያደረገ ቅድሚያ የዘገበው ማርቆስ ነው የሚል ንድፈ-አሳብ ነው።

± የሉቃን ተቀዳሚነት የሚባለው የሮበት ንድፈ-አሳብ መሰረት ያደረገ ቅድሚያ የዘገበው ሉቃስ ነው የሚል ንድፈ-አሳብ ነው፥ ይህም “ኤል” L ምንጭ ይባላል፤ “L” የሚለው “ሉቃስ ምንጭ”source” ማለት ነው።

± ማቴዎስ እና ሉቃስ ከማርቆስ እና ከሌላ ምንጭ ወስደዋል የሚለው ንድፈ-አሳብ “ኪው” Q ምንጭ ይባላል፤ “Q” የሚለው “ኪዌል” Quelle ከሚል ከጀርማኒክ ቃል የመጣ ሲሆን “ምንጭ” ማለት ነው።

አብላጫውን የአዲስ ኪዳን ዐበይት ለዘብተኛ ምሁራን ሆነ ጽንፈኛ ምሁራን ማርቆስ የማቴዎስ እና የሉቃስ ወንጌል ምንጭ እንደሆነ ይስማማሉ።

መልስ

ሙስሊሙ ጸሐፊ በሚያወራው ጉዳይ ዙርያ የረባ ዕውቀት እንደሌለው የቃላት አጠቃቀሙ ያሳብቃል፡፡ ብዙ የለዘብተኛ ሥነ መለኮት ሊቃውንትና የተወሰኑ አጥባቂዎች የማርቆስ ወንጌል ለማቴዎስና ለሉቃስ በምንጭነት እንዳገለገለ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ በማርቆስ ውስጥ የማይገኙና የማቴዎስና የሉቃስ የጋራ ያልሆኑ መረጃዎች ደግሞ M እና L በማለት ከሰየሟቸው ንድፈ ሐሳባዊ ምንጮች ተገኝተው ይሆናል ይላሉ፡፡ ይህ አመለካከት በወንጌላት ተዓማኒነት ላይ ምንም ዓይነት ችግር የማይፈጥር ቢሆንም ግምት ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

ሌላ ከአራቱ ወንጌላት የሚቀድም የኢየሱስ ትምህርቶች ስብስብ የሆነ፤ ነገር ግን ታሪኩንና ተዓምራቱን ያላካተተ Q የተሰኘ ንድፈ ሐሳባዊ ሰነድ ይኖር ይሆናል የሚልም ግምት አለ፡፡ Q – “Quelle” የሚለው የጀርመንኛ ቃል የመጀመርያ ፊደል ሲሆን “ምንጭ” የሚል ትርጉም አለው፡፡ ይህ ትወራ መጀመርያ የቀረበው ፍሬድሪክ ሽሌይማከር (Friedrich Schleiermacher (1768–1834)) በተሰኘ ጀርመናዊ ምሑር ሲሆን ይህ ሰው “የዘመናዊው ለዘብተኛነት አባት” በመባል ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ይህ ትወራ ከተጠነሰሰበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በታላላቅ የነገረ መለኮት ምሑራን ተቃውሞ ደርሶበታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንድና አንድ ነው፤ Q የተባለ ሰነድም ሆነ እርሱን የሚመስል ነገር ስለመኖሩ ሊጠቀስ የሚችል ቅንጣት ታክል የታሪክ ማስረጃ የለም! ይህንን ትወራ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እያቀነቀነ የሚገኘው Jesus Seminar የተሰኘው ህልውናው ለማክተም ጫፍ ላይ የደረሰ የለዘብተኞች ማሕበር ነው፡፡ (Geislere: Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 1126)

አብዱል

ማርቆስ ከ 66-70 ዓመተ-ልደት”AD” ሲጽፍ ከእርሱ በኃላ የማቴዎስ ጸሐፊ ከ 80-90 ዓመተ-ልደት”AD” እንዲሁ ሉቃስ ከ 80-110 ዓመተ-ልደት”AD” እንደጻፉ ይገመታል።

ማቴዎስ ለዕብራውያን በ 50 ዓመተ-ልደት”AD” አካባቢ በዕብራይስጥ ቋንቋ ደብዳቤ ጽፎላቸው ነበር፥ ይህ ደብዳቤ ሲጠፋ አንድ ማንነቱ በውል የማታወቅ ሰው በማቴዎስ ስም የማርቆስን ወንጌል ምንጭ አድርጎ 80-90 ዓመተ-ልደት”AD” የማቴዎስን ወንጌል ጽፋል።

ይህ የማቴዎስ ወንጌል ጸሐፊ ከማርቆስ ወንጌል ላይ እየወሰደ ቢጽፍም በማርቆስ ላይ የሚጨምረም፣ የሚቀንሰው እና የሚለውጠው ቃላት አለ። ይህንን ነጥብ በነጥብ እንመልከት፦

መልስ

በዚህ ዘመን የሚገኙት አጥባቂ ሊቃውንት ተመሳሳዮቹ ወንጌላት ከ70 ዓ.ም. በፊት እንደተጻፉ የሚናገሩ ሲሆን ከለዘብተኛ ምሑራን መካከል የሚበዙቱ አራቱንም ወንጌላት ከ95 ዓ.ም. በፊት ያደርጓቸዋል፡፡ በለዘብተኛነታቸውና ክርስትናን በመቃወም የሚታወቁት የአዲስ ኪዳን ምሑር ባርት ኤህርማን እንኳ ማርቆስን 70 ዓ.ም. ገደማ፣ ማቴዎስንና ሉቃስን 80-85 ዓ.ም. ገደማ፣ ዮሐንስን ደግሞ 95 ዓ.ም. ገደማ ያስቀምጣሉ፡፡ (Bart D. Ehrman. Jesus, interrupted : Revealing the Hidden Contradictions in the Bible (and Why We Don’t Know About Them); New York, HarperOne, 2009, pp. 144-145)

ለዘብተኛ ምሑራን በወንጌላት ውስጥ የሚገኙ የክርስቶስ ትንቢቶች ከክስተቶቹ በኋላ እንደተጻፉ ስለሚያምኑ ወንጌላት ዘግይተው የተጻፉ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ግምታቸው ልዕለ ተፈጥሯዊ ትንቢቶችን ከመካድ የመነጨ እንጂ በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ የተደገፈ አይደለም፡፡ ይህንን ባለማወቅ ሙስሊም ወገኖቻችን ዋቢ አድርገው ሲጠቅሷቸው እንታዘባለን፡፡ ክርስትናን የማጣጣል እኩይ ፍላጎት ያላቸው ሰባኪያኖቻቸውም ወንጌላትን ከሐዋርያት ዘመን ውጪ የሚያደርጉ ፅንፍ የረገጡ ለዘብተኛ አመለካከቶችን ያቀነቅናሉ፡፡

ልዕለ ተፈጥሯዊ ትንቢቶችን የሚክደውን አመለካከታቸውን በወንጌላት ላይ ከመጫን ተቆጥበው በሚዛናዊነት የተመራመሩ አንዳንድ ለዘብተኛ ምሑራን ወንጌላት በዘመነ ሐዋርያት የተጻፉ ስለመሆናቸው አሳማኝ ሙግቶችን አቅርበዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል የክርስትና ተቃዋሚ የነበሩት ኤ ቲ ሮቢንሰን የተሰኙ ዕውቅ ለዘብተኛ ምሑር ማቴዎስን ከ40-60፣ ማርቆስን ከ45-60፣ ሉቃስን ከ57-60፣ ዮሐንስን ከ40-60 ዓ.ም. ባሉት መካከል አስቀምጠዋል፡፡ (Norman Geislere: Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 389)

አብዱል

ነጥብ አንድ

“መጨመር”

“መሢሕ” مَسِيح የሚለው የዐረቢኛ ቃል፣ “መሢሐ” מָשִׁ֫יחַ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል፣ “ክርስቶስ” Χριστός የሚለው የግሪክ ኮይኔ ቃል ትርጉማቸው ተመሳሳይ ሲሆን “የተቀባ” ወይም “ቅቡዕ” ማለት ነው፥ ኢየሱስ አይሁዳውያን የሚጠብቁት መሢሕ ስለሆነ “መሲሕ” የሚለው ቃል ቁርኣን ውስጥ በዘጠኝ አንቀፆች 11 ጊዜ ተጠቅሷል። ኢየሱስ እርሱ ማን እንደሆነ ለሐዋርያቱ ሲጠይቅ ጴጥሮስ የመለሰው መልስ፦ “አንተ ክርስቶስ ነህ” ብሎ ነው፦

ማርቆስ 8፥29 እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፦ “አንተ ክርስቶስ ነህ” ብሎ መለሰለት።

ነገር ግን የማቴዎስ ጸሐፊ የማርቆስን ዘገባ ምንጭ አድርጎ፦ “የሕያው እግዚአብሔር ልጅ” ብሎ ጨምሮበታል፦

ማቴዎስ 16፥16 ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፦ አንተ ክርስቶስ “የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” አለ።

መልስ

מָשִׁ֫יחַ የሚለው ቃል “መሺያኽ” እንጂ “መሢሐ” ተብሎ አይነበብም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋዎችን ብቻ ሳይሆን በእንግሊዝኛ የተቀመጡ አጻጻፎችን ማንበብ የማይችል ነገር ግን የጥንታውያን ቋንቋዎች ሊቅ መስሎ ለመታየት የሚፍጨረጨር ሙስሊም ሰባኪ ነው የገጠመን፡፡

የወንጌላቱ ዘገባዎች ተሰባጣሪ እንጂ ተጻራሪ አይደሉም፡፡ አሳሳቢ ሊሆን የሚገባው በማቴዎስ ውስጥ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ በማርቆስ ውስጥ ባይባል ነበር፡፡ ማቴዎስ የተሟላውን የጴጥሮስን ንግግር የዘገበ ሲሆን ማርቆስ ደግሞ ከፊሉን ነው የዘገበው፡፡ የማርቆስ ወንጌል መክፈቻና መዝጊያ ላይ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ተነግሯል፤ ይህም የወንጌሉ ዋና ነጥብ መሆኑን አመላካች ነው (ማርቆስ 1፡1፣ 15፡39)፡፡ በዚህ ጸሐፊ ሙግት መሠረት ከሄድን የማርቆስ ወንጌል ገና በመጀመርያው ቁጥር “የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል” በማለት ስለሚጀምርና ማቴዎስ ደግሞ “የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ” በማለት ስለሚጀምር ከማቴዎስ ይልቅ ማርቆስ ለኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት ትኩረት ሰጥቷል ልንል ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የፈለገውን መርጦ ያልተረጋገጡ የምሑራን ግምቶችን በመጠቀም የሚፈልገውን ድምዳሜ ማስቀመጥ ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ግን አጠቃላይ መረጃዎችን በማመሳከር የድምዳሜውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ መቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከሄድን ማርቆስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በተደጋጋሚ ከመግለጹ አንጻር የሙስሊሙ ጸሐፊ ሙግት ውድቅ ነው፡፡

አብዱል

ነጥብ ሁለት

“መቀነስ”

የአንድ አምላክ አስተምህሮት የሙሴም ሆነ የኢየሱስ ቀዳማይ መርሕ ነው። “እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው” የሚለው እንዳስተማረ ማርቆስ ዘግቧል፦

ማርቆስ 12፥29-30 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፦ “እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው”፥ አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ፡ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።

ነገር ግን የማቴዎስ ጸሐፊ የማርቆስን ዘገባ ምንጭ አድርጎ፦ “እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው” የሚለውን መርሕ ቀንሶታል፦

ማቴዎስ 22፥36-37 መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።

መልስ

ከላይ የሚገኘው ማስረጃ ማቴዎስ ማርቆስን በምንጭነት ተጠቅሟል የሚለውን መላ ምት አጠራጣሪ የሚያደርግ እንጂ ማቴዎስ መቀነሱን የሚያመለክት አይደለም፡፡ አንድ ሰው ይህንን ቀንሷል ይህንን ደግሞ ጨምሯል ተብሎ ሊነቀፍ የሚችለው ያንን ለማደረግ የሚያበቃ ግልፅ ወይም ስውር አጀንዳ ሲኖረው ነው፡፡ ማርቆስ በእግዚአብሔር አንድነት የሚያምነውን ያህል በእግዚአብሔር አንድነት የሚያምነው ማቴዎስ ምን አጀንዳ ኖሮት ነው ስለ እግዚአብሔር አንድነት የሚናገረውን ሐሳብ ሊቀንስ የሚችለው? ማቴዎስም ሆነ ማርቆስ ስለ ጉዳዩ ከነበራቸው መረጃ በመነሳት ዘግበዋል፤ አከተመ፡፡ በማርቆስ ዘገባ ውስጥ በማቴዎስ ውስጥ ያልተጠቀሰ ተጨማሪ መረጃ እናገኛለን፡፡ የሁለቱ ዘገባዎች ተሰባጣሪና ተደጋጋፊ እንጂ እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ አይደሉም፡፡ በግምታዊ መላ ምት ላይ ተመሥርቶ ከዚህ ሁኔታ ውስጥ አዲስ ታሪክ ለማውጣት መሞከር ተቀባይነት የለውም፡፡

አብዱል

ነጥብ ሦስት

“መለወጥ”

አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ሮጦ ተንበረከከለትና፦ “ቸር መምህር ሆይ”፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፦ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም” አለው፦

ማርቆስ 10፥17-18 እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና፦ “ቸር መምህር ሆይ”፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፦ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም”።

ነገር ግን የማቴዎስ ጸሐፊ የማርቆስን ዘገባ ምንጭ አድርጎ፦ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም” የሚለውን “ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው” በማለት ለውጦታል፦

ማቴዎስ 19፥16-17 እነሆም፥ አንድ ሰው ቀርቦ፦ መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ? አለው። እርሱም፦ “ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው”፤ ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ” አለው።

“ትለኛለህ” እና “ትጠይቀኛለህ” ሁለት የተለያየ ቃላትና ትርጉም ያላቸው ሐረግ ናቸው፤ “መልካም የሆነ ነገር” እና “አንዱ እግዚአብሔር” ሁለት የተለያዩ ምነቶች ናቸው። ነገር ሁሉ ፍጡር ነው፤ እግዚአብሔር የነገር ሁሉ ፈጣሪ ነው።

መልስ

ወንጌላት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአረማይክ ቋንቋ የተናገረው ንግግር የግሪክ ትርጉሞች በመሆናቸው ምክንያት የወንጌላት ጸሐፊዎች የተለያዩ የግሪክ ቃላትን ቢጠቀሙ አያስገርምም፡፡ እንደ እስልምና ድርቅ ያለ (Mechanical) የመገለጥ ፅንሰ ሐሳብ አመለካከት ካልተከተልን በስተቀር የተለያዩ ሰዎች ንግግሮችን ከአንዱ ቋንቋ ወደ ሌላው ቋንቋ ሲተረጉሙ ሙሉ በሙሉ በአንድ መንገድ ብቻ እንዲተረጉሙ መጠበቅ የማይቻል ነው፡፡ ማርቆስ ሰፊ ትርጉም ያለውን “ሌጌይስ” የሚል ቃል የተጠቀመ ሲሆን ማቴዎስ ደግሞ “ኤሮታስ” የሚል ጠበብ ያለ ትርጉም ያለውን ቃል ተጠቅሟል፡፡ ነገር ግን ማቴዎስ የተጠቀመው “ኤሮታስ” የሚለው ቃል በትርጉም ደረጃ ማርቆስ በተጠቀመው “ሌጌይስ” በሚለው ቃል ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ሁለቱም ትክክል ናቸው፡፡ “መጠየቅ” የሚለው “ሌጌይስ” የሚለው ቃል ከሚያጠቃልላቸው ትርጉሞች መካከል አንዱ ነው፡፡ ሁለቱ ጸሐፍት የተለያዩ ቃላትን የመጠቀማቸው ጉዳይ ማቴዎስ ማርቆስን በምንጭነት ተጠቅሟል የሚለውን ግምት ጥያቄ ላይ የሚጥል አጋጣሚ እንጂ ማቴዎስ የሆነ ነገር መለወጡን የሚያሳይ አይደለም፡፡

አብዱል

ማርቆስ ሐዋርያት ኢየሱስን፦ “መምህር ሆይ” ብለው እንደጠሩት ይናገራል፦

ማርቆስ 9፥5 ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን “መምህር ሆይ”፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው።

ማርቆስ 4፥38 እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ አንቅተውም፦ “መምህር ሆይ”፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት።

ነገር ግን የማቴዎስ ጸሐፊ የማርቆስን ዘገባ ምንጭ አድርጎ በአንድ አንቀጽ፣ በአንድ ጊዜና ክስተት “መምህር ሆይ” የሚለውን “ጌታ ሆይ” በማለት ለውጦታል፦

ማቴዎስ 17፥4 ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ”፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ።

ማቴዎስ 8፥24-25 እነሆም፥ ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ በባሕር ታላቅ መናወጥ ሆነ፤ እርሱ ግን ተኝቶ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፦ “ጌታ ሆይ”፥ አድነን፥ ጠፋን እያሉ አስነሡት።

“ጌታ” ማለት እና “መምህር” ማለት ሁለት ለየቅ ቃላት ናቸው።

መልስ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው በአራማይክ ቋንቋ የመሆኑን እውነታ ከግንዛቤ ውስጥ ስናስገባ የዚህን ልዩነት መነሻ በቀላሉ መረዳት እንችላለን፡፡ “ረብ” የሚለው የአረማይክ ቃል በእብራይስጥ “ረቭ” በአረብኛ ደግም “ረብ” ከሚለው ጋር አንድ ሲሆን ትርጓሜው “ጌታ፣ የበላይ፣ መምህር” ማለት ነው፡፡ በአረብኛው “ረብ” የሚለው ቃል የሰው ጌታንም ሆነ (ሱራ 12:23) ፈጣሪን ሊያመለክት እንደሚችል ሁሉ የአረማይኩም እንደዚያው ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በአረይማይክ ቋንቋ በተጻፉት የብሉይ ኪዳን ክፍሎች ውስጥ እግዚአብሔር አምላክ “ረብ” ተብሏል፡-

“ወደ ይሁዳ አገር ወደ ታላቁም አምላክ (ረበ ኤላሃ) ቤት እንደ ሄድን ንጉሡ ይወቅ፤ እርሱም በትልቅ ድንጋይ ተሠራ፥ በቅጥሩም ውስጥ እንጨት ተደረገ፥ ያም ሥራ በትጋት ይሠራል፥ በእጃቸውም ይከናወናል።” (ዕዝራ 5፡8)

“ድንጋዩም እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ ብረቱንና ናሱን ሸክላውንና ብሩን ወርቁንም ሲፈጨው እንዳየህ፥ እንዲሁ ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ታላቁ አምላክ (ረብ ኤላህ) ለንጉሡ አስታውቆታል፤ ሕልሙም እውነተኛ ፍቺውም የታመነ ነው።” (ዳንኤል 2፡45)

ወንጌላዊው ማርቆስ 9፡5 ላይ “ረቢ” የሚለውን የአረማይክ ቃል ወደ ግሪክ ሳይተረጉም እንዳለ ያስቀመጠ ሲሆን 4፡38 ላይ ደግሞ “ዲዳስከሎስ” የሚል ቃል ተጠቅሟል፤ ትርጓሜውም “አዋቂ፣ መምህር፣ የበላይ (Master)” ማለት ነው፡፡ ማቴዎስ ደግሞ “ረቢ” የሚለውን ቃል “ኩርዮስ” ወደሚል የግሪክ ቃል የተረጎመ ሲሆን “ጌታ፣ የበላይ” የሚሉ ትርጉሞች አሉት፡፡ ኩሪዮስ የሚለው ቃል እንደየአውዱ አምላክነትንም ሆነ ሰብዓዊ ጌትነትን ሊያመለክት ይችላል፡፡ ሐዋርያት የጌታችንን አምላክነት እየተረዱ ሲመጡ “ጌታ” የሚለውን ቃል አምላክነቱን በሚያመለክት ሁኔታ መጠቀም መጀመራቸውን አዲስ ኪዳንን ስናጠና መገንዘብ እንችላለን፡፡ ጌታችን ራሱ ደግሞ ጌትነቱ የፍጡር አለመሆኑንና አምላክነቱን እንደሚያሳይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ገልጿል (ማር. 2፡28፣ ማቴ. 22፡41-45)፡፡ “ረቢ” የሚለውንም ቃል ከእርሱ ውጪ ለሌላ ለማንም እንዳይጠቀሙ ሐዋርያቱን አዟቸዋል፡- “እናንተ ግን፦ መምህር (ረቢ) ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ  አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ።” (ማቴ. 23፡8)

ልዩነቱ የወንጌላቱ ጸሐፊያን አረማይኩን ወደ ግሪክ ለማምጣት የተለያዩ ቃላትን በመምረጣቸው ምክንያት የተፈጠረ እንጂ የሐሳብ ልዩነት እንደሌለ መገንዘብ ይቻላል፡፡ አሁንም ይህ አጋጣሚ ማቴዎስ ማርቆስን በምንጭነት እንደተጠቀመ መላ ምት ያስቀመጡ ወገኖች ግምታቸውን ጥያቄ ላይ የሚጥል ከመሆን የዘለለ ትርጉም ያለው አይደለም፡፡

አብዱል

ማርቆስ ኢየሱስ፦ “የአምላክን ፈቃድ” ብሎ እንደተናገረ ይናገራል፦

ማርቆስ 3፥35 “የአምላክን ፈቃድ” የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ ነው እኅቴም እናቴም አለ።

ነገር ግን የማቴዎስ ጸሐፊ የማርቆስን ዘገባ ምንጭ አድርጎ በአንድ አንቀጽ፣ በአንድ ጊዜና ክስተት “የአምላክን ፈቃድ” የሚለውን “የአባቴን ፈቃድ” በማለት ለውጦታል፦

ማቴዎስ 12፥50 በሰማያት ያለውን “የአባቴን ፈቃድ” የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና አለ።

“አምላክ” ማለት እና “አባት” ማለት ሁለት ለየቅል ቃላት ናቸው።

እንግዲህ እኛ ሙሥሊሞች እነዚህን በማርቆስ ላይ የተጨመሩትንና የተለወጡትን፦ ኢየሱስን “የአምላክ ልጅ” እና “ጌታ” ፈጣሪን ደግሞ “አባት” የሚሉትን ቃላትና እሳቤ ሳንቀበል ማርቆስ ባስቀመጠው፦ ኢየሱስን “መሢሕ” እና “መምህር” እንዲሂ ፈጣሪን “አምላክ” ብለን ብንቀበል በእውነት የሐዋርያት ሥረ-መሠረት ቅሪት ተቀበልን ማለት ነው።

መልስ

ማርቆስ “ቴዎስ” ብሎ የጠቀሰውም ሆነ ማቴዎስ “ፓትሮስ” ብሎ የገለጸው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት የሆነውን እግዚአብሔር አብን ነው፡፡ ማርቆስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በተደጋጋሚ ስለገለጸ አንድ ሙስሊም በምን ተዓምር የማርቆስን ወንጌል ለእስላማዊ የክህደት አስተምህሮ ማስረጃ አድርጎ ሊጠቀም እንደሚችል ማሰብ ያዳገታል፡፡

  • ማርቆስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ያወጀው ገና ከጅምሩ ነው፡- “የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ።” (1፡1)፡፡
  • እዚያው ምዕራፍ 1፡10-11 ላይ እግዚአብሔር አብ ኢየሱስን “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል” ብሎ ከሰማይ እንደተናገረው ዘግቧል፡፡
  • ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ምዕራፍ 3፡11 ላይ “ርኵሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ በፊቱ ተደፍተው፦ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ ጮኹ” በማለት ዘግቧል፡፡
  • ምዕራፍ 5፡7 ላይ እንዲሁ አንድ ክፉ መንፈስ ያደረበት ሰው ማንነቱን አውቆ “በታላቅ ድምፅም እየጮኸ፦ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ” እንዳለ ዘግቧል፡፡ ሰዎች ማንነቱን ባያውቁትም እንኳ እርኩሳን መናፍስት ማንነቱን በማወቅ በፊቱ ሲንቀጠቀጡ እንመለከታለን፡፡
  • ከዚያ ቀጥሎ ምዕራፍ 9፡7 ላይ “ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፥ ከደመናውም፦ የምወደው ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ” በማለት የእግዚአብሔር አብን ምስክርነት ጽፎልናል፡፡

ተመሳሳይ በርካታ ዘገባዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለዚህ የማርቆስ አዘጋገብ ከማቴዎስ የተለየባቸውን የተወሰኑ አጋጣሚዎች ጠቅሶ የማርቆስ ወንጌል እስልምናን የሚደግፍ በማስመሰል ማቅረብ የከፋ እብለት ነው፡፡

አብዱል

ሲቀጥል አንደኛው ከሌላው ወሰደ ከተባለ መንፈስ ቅዱስ ምንም ድርሻ ስለሌለው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት አልጻፉትም።

መልስ

በመጀመርያ ደረጃ ማቴዎስ ከማርቆስ ወስዷል የሚለው የምሑራን ማላምት እንጂ የተረጋገጠ እውነታ አይደለም፡፡  ማቴዎስ ከማርቆስ ላለመውሰዱ ማረጋገጫ ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችን ይህ ሙስሊም ሰባኪ እንዳደረገው “ተጨምሯል፣ ተቀንሷል፣ ተለውጧል” በማለት ውኀ የማይቋጥር ሰበብ አስባብ እየሰጡ ስለ የትኛውም መጽሐፍ በዘፈቀደ መናገር ይቻላል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ መቻል ነው፡፡ ሌላው አንድ ጸሐፊ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፈ ሌላ ምንጭ መጠቀም አይችልም የሚል እሳቤ አመክንዮአዊም ክርስቲያናዊም አለመሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት መጻፍ ሌላ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፈ ምንጭ መጠቀምን ይከለክላል የሚለውን እሳቤ ሙስሊሙ ሰባኪ ከየት እንዳመጣ ግልፅ አይደለም፡፡ ክርስትና እንዲህ አያስተምርም፡፡ ቅዱሳን ሰዎች ከእነርሱ በፊት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉ ምንጮችን እየጠቀሱ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ይናገራሉ፣ ይጽፋሉ፡፡

አብዱል

ከዚህ ሁሉ የሚያጅበው ምሁራን አራቱ ወንጌላት ውስጥ ያልተካተቱ የኢየሱስ ንግግር እንዳሉ መቀበላቸው ነው፤ ይህ እሳቤ በነጠላ “አግራፎን” αγραφον በብዜት “አግራፋ” αγραφα ይባላል፥ የአሌክሳንድሪያ ክሌመንት፣ ጀስቲን ማርቲን፣ ኦሪገን ወዘተ ኢየሱስ ተናገረ ብለው የተናገሯቸው በቁና ንግግሮች አራቱ ወንጌላት ውስጥ ያልተካተቱ አሉ። ለናሙና ያክል ባይብል ውስጥም ማየት ይቻላል፦

1ኛ ዮሐንስ 1፥5 ከእርሱ የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። ”እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም” የምትል ይህች ናት።

የሐዋርያት ሥራ 20:35 እንዲሁ እየደከማችሁ ድውዮችን ልትረዱና እርሱ ራሱ። ”ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ።

ኢየሱስ፦ “እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም” ብሎ ተናግሮ ነበር፤ ዮሐንስም፦ “ከእርሱ(ከኢየሱስ) የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት ይህች ናት” ብሎናል፤ ግን ይህ ከኢየሱስ የሰሙት መልእክት በአራቱ ወንጌላት የለም ማለት ኢየሱስ አልተናገረውም ማለት አይደለም፤ በተጨማሪ በተመሳሳይ መልኩ ኢየሱስ፦ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” ብሎ ተናግሮ ነበር፤ ይህ ቃል አራቱ ወንጌል ላይ የለም ማለት ኢየሱስ አልተናገረውም ማለት አይደለም። ይህ ከላይ እንደተጠቀሰው “አግራፎን” ወይም “አግራፋ” ይባላል።

መልስ

ወንጌላት ጊዜና ቦታን በማገናዘብ የክርስቶስን ትምህርት ሁሉ ሊወክሉ የሚችሉ ንግግሮቹንና አንኳር አንኳር ሥራዎቹን የያዙ መጻሕፍት እንጂ ክርስቶስ በሦስት ዓመት ተኩል ውስጥ የተናገራቸውን ንግግሮችና ያደረጋቸውን ተዓምራት ሁሉ ጠቅልለው የያዙ መጻሕፍት አይደሉም፡፡ እንዲህ ያለ ይዘት ያለው መጽሐፍ እንኳንስ በዘመነ ጥቅልል ብራና ይቅርና በዚህ ዘመን እንኳ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ ይህንን እውነታ እንዲህ በማለት ገልጿል፡- “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” (ዮሐ. 21፡25)፡፡

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገራቸውን ቃላት የዘገቡልን ወገኖች በዘመኑ ከእርሱ ጋር የነበሩት የዓይን ምስክሮች እና ከዓይን ምስክሮች ጋር አብረው ያገለገሉት የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ የኢየሱስ ንግግሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እስከተጠቀሱ ድረስ በአራቱ ወንጌላት ውስጥ ብቻ እንዲሰፍሩ የሚያስገድድ ምን ሁኔታ አለ? የሙስሊሙ ጸሐፊ ሙግት ከምክንያታዊነት በእጅጉ የራቀ ነው!

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሚገኘውን ዓይነት የለዘብተኛ ምሑራን ሙግቶች መጠቀም እስልምናን እንዴት ውድቅ እንደሚያደርግ ለማወቅ ይህንን ጽሑፍ ያንብቡ፡- ዶክሜንተሪ ሃይፖቴሲስ እና የሙስሊም ሰባኪያን ስህተት

መጽሐፍ ቅዱስ