ስቅለት በዮሴፍ ዘመን?
ቁርኣንን ከታሪካዊ ቅጥፈቱ ለመታደግ የተደረገ ያልተሳካ ጥረት
በዮሴፍ ዘመን ሰዎች በስቅለት መቀጣታቸውን በተመለከተ ቁርኣን የፈፀመውን የታሪክ ቅጥፈት ለማስተባበል አብዱሎች እየተራወጡ ይገኛሉ (ሱራ 12፡41)፡፡ ሰለምቴ ነኝ ባዩ ኡስታዝ እንደተለመደው እጅ እጅ በሚለው የአጻጻፍ ስልቱ ባዘጋጀው ጽሑፉ ቁርኣንን ለመታደግ ረጅም ትግል አድርጓል፡፡ ነገር ግን የሙግቱን ነጥብ ፈፅሞ አልተረዳም፡፡ ስለ ምን እየተወራ እንዳለ እንኳ ያወቀ አይመስልም፡፡ ይህ ርዕስ ከኛ በፊት የነበሩት ክርስቲያንና ሙስሊም ሊቃውንት ሰፊ ክርክር አድርገውበት ሙስሊሞቹ ተስፋ ቆርጠው የተውት ርዕስ በመሆኑ የአገራችን ኡስታዞች “መልስ” ብለው ከመጻፋቸው በፊት ከዚህ ቀደም ምን ተባለ? ብለው የመጠየቅ ልምድ ቢኖራቸው መልካም ነበር፡፡
ኡስታዙ በቁርኣን ላይ ለሰነዘርኩት ሒስ ምላሽ በሚል በጽሑፉ ውስጥ ሁለት ሙግቶችን ነው ያቀረበው፡-
በመጀመርያ ስቅለት በዮሴፍ ዘመን ተግባራዊ ይደረግ እንደነበር የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ አለመኖሩንና ከዮሴፍ ዘመን በጣም ዘግይቶ የተጀመረ ልማድ መሆኑን ካመነ በኋላ ፈርዖናውያን ወንጀለኛን በስቅላት እንደሚቀጡ የሚያሳይ ታሪካዊም ሆነ ሥነ-ቁፋሮአዊ መረጃ አለመገኘቱ ክስተቱን ውሸት እንደማያደርገው ሊያስረዳን ሞክሯል፡፡ ያቀረበው ሰበብም የታሪክ ተማራማሪዎች ያልደረሱበት አላህ ብቻ የሚያውቀው ምስጢራዊ ክስተት ሊኖር ይችላል የሚል ነው፡፡ ይህ የግብፃውያንን ማንነት ካለማወቅ የመነጨ ስህተት ነው፡፡ ግብፃውያን ታሪካቸውንና አኗኗራቸውን በዝርዝር በጽሑፍና በምስል በማስቀረት ይታወቃሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የተለያዩ የአገዳደል ዓይነቶችን መዝግበው ያቆዩ ሲሆን የመስቀል ስቅላት አልተጠቀሰም፡፡ በግብፃውያን አለመጠቀሱ ብቻ ሳይሆን እስከ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ቅድመ ክርስቶስ ድረስ ስቅለት መፈጸሙን የሚያሳይ ምንም ዓይነት የጽሑፍም ሆነ የአርኪዎሎጂ ማስረጃ የለም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የሰጠው “ማስረጃ” መጽሐፍ ቅዱስ በዮሴፍና በሙሴ ዘመን ስቅለት መኖሩን ይናገራል የሚል ነው፡፡ ለዚህ ነው የሙግቱን ነጥብ ፈፅሞ አልተረዳም ያልኩት፡፡ እኔ እያወራሁ ያለሁት በእንጨት ላይ አንጠልጥሎ ስለመግደል (hanging) ወይም የጥንት ግብፃውያን እንደሚያደርጉት ረጅም እንጨት በሰውነት ውስጥ አሳልፎ በመውጋት ስለማንጠልጠል (impalement) አይደለም፡፡ እኔ እያወራሁ ያለሁት የስቅለት ዓይነት በቁርኣን ውስጥ አሻሚ ባልሆነ ሁኔታ በግልፅ ስለተቀመጠው የስቅለት ዓይነት ማለትም በመስቀል ላይ ሰዎችን ሰቅሎ ስለመግደል (Crucifixion) ነው፡፡ በሱራ 12፡41 ላይ ዮሴፍ ህልም ሲፈታ فَيُصْلَبُ “ፈዩስለቡ” (ይሰቀላል) በማለት ይናገራል፡፡ በተጨማሪም ሱራ 7፡124 ላይ ፈርዖን لَأُصَلِّبَنَّكُمْ “ለኡሰሊበነኩም” (በእርግጥ እሰቅላችኋለሁ) በማለት ይናገራል፡፡ ይህም በግንድ ላይ መንጠልጠልን ሳይሆን በመስቀል (በአረብኛ “ሰሊብ”፣ በእንግሊዝኛ “Cross”) ላይ መሰቀልን የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ ይህ ልማድ ደግሞ ከስድስተኛው ክፍለ ዘመን ቅድመ ክርስቶስ በፊት ስለመኖሩ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም፡፡ ለዚህ ነው የቁርኣን ደራሲ ተሳስቷል ያልኩት፡፡
ኡስታዙ ይህንን ነጥብ ባለመረዳቱ ምክንያት የመስቀል ስቅለትንና መንጠልጠልን ሊያምታታ ችሏል፡፡ ቁርኣንን ከታሪካዊ ቅጥፈቱ ለመታደግ ጥረት ሲያደርግ ሳለ እግረ መንገዱን እንደ ልማዱ እሱ ራሱ ሌላ ታሪካዊ ቅጥፈት ሲፈፅም ማየት ደግሞ አስቂኝ ጉዳይ ነው፡፡ “[በ]ታሪክ[ም] ሆነ [በ]ሥነ-ቁፋሮ ወንጀለኛ[ን] በስቅላት [ስለመቅጣት] ያለው መረጃ በ 559 ቅድመ-ልደት በፋርሳዊያን ጊዜ ነው…” በማለት ከተናዘዘ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መንጠልጠል የተነገሩትን ጥቅሶች በመጥቀስ ሁሉንም ዓይነት ስቅለት አንድ አድርጓል፡፡ (ፊደላትን በዚህ [] ምልክት ውስጥ ያስገባሁት የተወናገረውን አጻጻፉን ለማስተካከል መሆኑን ልብ በሉ፡፡) ነገር ግን በታሪክ ተመራማሪዎች መሠረት እስከ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ቅ.ክ. የታሪክም ሆነ የስነ ቁፋሮ ማስረጃ የሌለው ሁሉም ዓይነት ስቅለት ሳይሆን ቁርኣን በስህተት ወደ ዮሴፍና ሙሴ ዘመን የወሰደው የመስቀል ስቅለት (Crucifixion) ነው፡፡ ሌላው የስቅለት ዓይነት በግብፅ ውስጥም ጭምር ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር ከበቂ በላይ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ነገር ግን መሳሳት የማይሰለቸው ኡስታዝ የቁርኣንን ስህተት ለመሸፈን ሲሞክር ራሱ ስህተት ፈጽሟል፤ “የቆጡን አወርድ ብላ…” እንዲሉ (A.J. Van Loon. Law and Order in Ancient Egypt: The Development of Criminal Justice from the Pharaonic New Kingdom until the Roman Dominate; Leiden University, 2014, p. 19)፡፡
በነገራችን ላይ ስቅለት (Crucifixion) በዕብራይስጥ ቋንቋ “ትስሊባ” ሲሆን “ተስሊብ” ከሚለው የአረብኛ ቃል ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት 40፡22፣ 41፡13፣ ዘዳግም 21፡22-23 እና 2ሳሙኤል 21፡12 ላይ በዮሴፍ፣ በሙሴና በዳዊት ዘመን ስቅለትን ሲጠቅስ የተጠቀመው ቃል “ታላህ” የሚል መንጠልጠልን የሚያመለክት ቃል ነው፡፡