1979 – ዓለም አቀፋዊው ሽብርና ሦስቱ ክስተቶች

1979 – ዓለም አቀፋዊው ሽብርና ሦስቱ ክስተቶች

በብዙዎች ግንዛቤ የዓለም አቀፋዊው ጂሃድ ጅማሮ ተደርጎ የሚታሰበው መስከረም 11/ 2001 በአሜሪካ ላይ የተፈፀመው ጥቃት ነው፡፡ ነገር ግን ጥቃቱ የዓለም አቀፋዊው ጂሃድ ውጤት እንጂ ጅማሬ አልነበረም፡፡ ማርክ እስቴይን በተሰኘ ጸሐፊ አባባል “መስከረም 11 ሁሉም ነገር የተለወጠበት ዕለት ሳይሆን ነገሮች ምን ያህል እንደተለወጡ ይፋ የወጣበት ዕለት ነበር፡፡”[1] በዘመናዊው ጂሃድ ታሪክ ከዚያ ይልቅ ልዩ ትርጉም ያለው 1979 ዓ.ም. ነው፡፡ ያ ዓመት ሽብርተኝነት ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ያደረጉ ተከታዮቹ ሦስት ታሪካዊ ኹነቶች የተፈፀሙበት ዓመት ነበር፡፡

የኢራን አብዮት

እስላማዊው አብዮት ከመነሳቱ በፊት ኢራን የአሜሪካ ወዳጅ በነበረው የፓህላቪ ቤተሰብ ትመራ ነበር፡፡ በፈረንሳይ አገር ውስጥ በስደት ላይ የነበሩት አያቶላህ ኾሜይኒ መልዕክቶቻቸውን በካሴት በማሰራጨት ያፋፋሙት አብዮት ተሳክቶ የቀደመው ሥርኣት ከወደቀ በኋላ ወደ አገራቸው በመመለስ በሪፈረንደም እስላማዊ መንግሥት መሠረቱ፡፡ በሺኣ እስልምና ትርጓሜ ላይ የተመሠረተ የሸሪኣ ሕግም የእስላማዊቷ አገር ላዕላይ ሕግ ሆኖ ፀደቀ፡፡ በዚያው ዓመት ሚያዝያ 4 በቁጣ የተሞሉ የኾሜይኒ ወጣት ደጋፊዎች “ታላቋ ሰይጣን” በማለት የሚጠሯትን የአሜሪካን ኤምባሲ በመውረር ስድሳ ስድስት ዜጎቿን አገቱ፡፡ አሜሪካ የታገቱባትን ዜጎች በማስለቀቅ ላይ ከማተኮር የዘለለ በኢራን ውስጥ ሲከናወን የነበረውን ጉዳይ መረዳት ተስኗት ነበር ወይም “በምን ያመጣል” ስሕተት ማተኮር አልፈለገችም ነበር፡፡ አዛውንቱ ኾሜይኒ የመሠረቱት ሥርኣት ጠንካራ ለነበረው የፓህላቪ ቤተሰብ አመራር አማራጭ በመሆን ይዘልቃል የሚል ግምት ስላልነበራትም ሊሆን ይችላል ጉዳዩን በቸልታ ተመለከተችው፤ ነገር ግን ያ ግምት ፍፁም የተሳሳተ ነበር፡፡

የኢራኑ እስላማዊ አብዮት በዚህ ዘመን እስላማዊ መንግሥት ማቋቋም እንደሚቻልና ምዕራባውያን አይደፈሬ አለመሆናቸውን በማረጋገጥ ለብዙ ጂሃዳውያን የመነቃቃት ምክንያት ሆኗል፡፡[2]

የመካ ከበባ

የቴህራኑ የአሜሪካ ኤምባሲ በተወረረ በአሥራ ሁለተኛው ቀን ሳዑዲ አረብያ ውስጥ አንድ ያልታሰበና ያልተጠበቀ ክስተት ተፈፀመ፡፡ ሦስት መቶ የሚሆኑ ሙስሊም ታጣቂዎች ታላቁን የመካ መስጊድ ተቆጣጠሩት፡፡ የታጣቂዎቹ መሪ ሲጠበቅ የነበረው መሐዲ እርሱ መሆኑን በማወጅ ዓለምን አስደመመ፡፡ እነዚህ ታጣቂዎች እንደ ምዕራባውያን አሻንጉሊት የሚቆጥሩትን የሳዑድን ቤተሰብ ጨምሮ ከአመለካከታቸው ጋር የማይስማሙትን ሙስሊሞች በሙሉ በከሃዲነት የሚፈርጁ የተክፊሪ[3] አመለካከት አራማጆች ነበሩ፡፡ ትግላቸው መጀመርያ ከእውነተኛው መንገድ ካፈነገጡት ሙስሊሞች ጋር እንደሆነና ሙስሊም ካልሆኑት ጋር የሚደረገው ፍልሚያ የመጀመርያው ተልዕኮ ከተሳካ በኋላ እንደሚቀጥል ያምኑ ነበር፡፡ ታጣቂዎቹ መደበኛ ሥልጠና ያልነበራቸውና ቀላል መሣርያዎችን የታጠቁ ቢሆኑም በማይታመን ሁኔታ ለሁለት ሳምንታት ያህል መስጊዱን ተቆጣጥረውት ከቆዩ በኋላ በፈረንሳይ ኮማንዶዎች እርዳታ አብዛኞቻቸው ተገድለው የተቀሩት በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

የሳዑዲ አረብያ የስለላ መረብ ከታጣቂዎቹ በስተጀርባ የነበሩትን ሰዎች ማንነት ካጣራ በኋላ የደረሰበት ነገር ለንጉሥ ሳዑድ ቤተሰብ በእጅጉ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ግለሰቦቹ ቁልፍ በሆኑ ኡላማዎች (የሃይማኖት ሊቃውንት) ድጋፍ የተቸራቸውና ሊቃውንቱ ለሳዑዲ ገዢዎች የነበራቸውን ጥላቻ በተግባር የገለፁ ግለሰቦች ነበሩ፡፡ የጥላቻው መሠረት ደግሞ በገዢዎቹ ዳተኝነት ሕዝበ ሙስሊሙ እምነቱን በትክክል መተግበር ስለተሳነው ከሃዲያን የሆኑት የምዕራባውያን የበታች ሆኗል የሚል ነበር፡፡ አብዱል ወሃብ ከሳዑዲ ንጉሣውያን ቤተሰቦች ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን እንደገና ታድሶ ምዕራባውያን በአረብ ባሕረ ሰላጤ ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ለመቀልበስ ጊዜው እንደሆነ አምነዋል፡፡

ከበባው ካከተመ በኋላ የሳዑዲ የስለላ መረብ በምርመራ የደረሰባቸውን ሊቃውንት አንገታቸውን ከመቅላት ይልቅ ንጉሡ ወደ ቤተ መንግሥት በመጋበዝ አጓጊ የሆነ የድርድር ነጥብ አቀረቡላቸው፡፡ ሊቃውንቱ በእስላም ምድርና በሙስሊሞች ላይ ጂሃድ መፈጸም ፍጹም ሐራም ወይም የተጠላ መሆኑን በማወጅ ዳግመኛ ለሳዑዲ መንግሥትና ለሳዑድ ቤተሰብ ስጋት መሆኑ እንዲቀር ለማድረግ፤ በምትኩ ደግሞ “በከሃዲያን” አገራትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚፈፀመው ጂሃድ ንጉሣዊ ቤተሰቡ ድጋፍ ለማድረግ ከስምምነት ተደረሰ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከነዳጅ የሚገኘውን ከፍተኛ ገቢ በመጠቀም አክራሪ እስልምናን በዓለም ዙርያ ለማስፋፋት በሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲሁም አሸባሪዎችን በመርዳት ረገድ ሳዑዲ አረብያ ግንባር ቀደም ሚና መጫወቷን ቀጥላለች፡፡[4]

የአፍጋኒስታን በሶቪዬት ሕብረት መወረር

የሶቪዬት ሕብረት ወዳጅ የነበረው የአፍጋኒስታን ሶሻሊስት መንግሥት በአገር በቀል ፅንፈኞች ይደርስበት የነበረውን ጥቃት መቋቋም ተስኖት ለመውደቅ ጫፍ ላይ በመድረሱ ምክንያት የውጪ ድጋፍ አስፈልጎት ነበር፡፡ በሕብረቱና በአፍጋኒስታን መንግሥት መካከል ከዚያ ቀደም በተፈረመው ስምምነት መሠረት ታህሳስ 24/ 1979 የሶቪየት ወታደሮች ወደ አፍጋኒስታን በመግባት በታጣቂዎች ላይ ጥቃቶችን መፈፀም ጀመሩ፡፡ ይህ ጦርነት ከጥቂት ጊዜ በኋላ የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ባላንጣዎች በሆኑት በራሽያና በአሜሪካ መካከል ወደሚደረግ ጦርነት ተሸጋገረ፡፡ ራሽያ በቀጥታ ውጊያው ውስጥ የገባች ስትሆን አሜሪካ ደግሞ አገር በቀሎቹን ሙጃሂዲኖች በመርዳት የራሽያን ዓላማ ለማክሸፍ ጥረቷን ተያያዘች፡፡ ሙጃሂዲኖች ከአሜሪካና ከሳዑዲ አረብያ በሚጎርፈው ከሚፈለገው በላይ በሆነ ድጋፍ በመደራጀታቸው ምክንያት ለዓለም አቀፋዊው የሽብር ንቅናቄ ተግባራዊ መሠረት የተጣለው በዚያን ወቅት ነበር፡፡ የአፍጋኒስታን ጦርነት የነበረውን አንድምታ በተመለከተ የቢንላደን የበላይና የአልቃኢዳ ትክክለኛ መስራች የነበረው አብዱላህ አዛም የሚከተለውን ጽፎ ነበር፡-

“አንዳንዶች ዓለም እንደጠፋችና ይህ ኡማ በሰማዕታት ጥማት እንዳረረ ተሰምቷቸው ነበር፡፡ ስለዚህ አላህ በምድረ አፍጋኒስታን ጂሃድን በማፈንዳት ከተለያዩ የሙስሊም አገራት ወጣቶች ጂሃድና ሰማዕትነትን ፍለጋ እንዲጎርፉ አደረገ…”[5]

አብዱላህ አዛም፣ ቢንላደንና ጥቂት አረብ ጓዶቻቸው በአፍጋኒስታን ውስጥ የተደረገውን ጦርነት ወደ ዓለም አቀፋዊ የጂሃድ ንቅናቄ ለወጡት፡፡ አዛም ጂሃዳዊ ስልቶችን የመንደፍ ዕውቀት የነበረው ሲሆን ቢንላደን ደግሞ ገንዘብ ነበረው፡፡[6]

እነዚህ ሦስቱ ክስተቶች የዘመናዊው እስላማዊ ሽብርተኝነት መሠረቶች ምን እንደሆኑ በግልፅ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ የኢራን አብዮት እስላማዊው አገዛዝ በዚህ ዘመን ሊተገበር የሚችል መሆኑን እንዲሁም የነፃውን ዓለም ተግዳሮት የመቋቋም አቅም እንዳለው በማሳየት ለጂሃዳውያን ወኔና ሰጥቷቸዋል፤ ሞዴልም ሆኗቸዋል፡፡ የመካ ከበባ ክስተት የሳዑዲ አረብያ መንግሥት ሽብርተኝነትን እንዲደግፍ በማሳመን የገንዘብና የአስተምህሮ ምንጭ እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ የአፍጋኒስታን ጦርነት ደግሞ  ለመደራጀትና ለመሰልጠን ምቹ የሆነ ከባቢን በመፍጠር ወደ ተግባራዊ እርምጃ እንዲገቡ ረድቷቸዋል፡፡ ከሽብርተኝነት ጋር በሚደረገው ፍልሚያ እነዚህን ሦስትዮሽ መሠረቶች ሳያፈርሱ ድልን ማሰብ የህልም እንጀራ የመብላት ያህል ነው፡፡ እስላማዊ ሽብርን ድል ለመንሳት እንደ ሞዴል የሚያየውን የወኔ መሠረቱን መደምሰስ፣ የአስተምህሮና የገንዘብ ምንጩን መድፈን እንዲሁም የርቢ መስኩን ምቹ እንዳይሆን ማድረግ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው፡፡

——————

[1] Mark Steyn. America Alone: the End of the World as We know it; p. XI, 2006.

[2] Sebastian Gorka. Defeating Jihad: the Winnable War;  pp. 81-82

[3] ተክፊሪ ሌሎች ሙስሊሞችን በከሃዲነት የሚፈርጅ የሱኒ ሙስሊም መጠርያ ነው፡፡

[4] Ibid., pp. 83-84

[5] Ibid., 85

[6] Ibid., pp. 84-86

እስልምናና ሽብርተኝነት