የአክራሪ እስልምና ሁለቱ የማደናገርያ ጥቅሶች

የአክራሪ እስልምና ሁለቱ የማደናገርያ ጥቅሶች

የአክራሪ እስልምና ትክክለኛ ገፅታ ገሃድ እየወጣ ባለበት በዚህ ወቅት ብዙ ወገኖች አልቃኢዳና አይሲስን የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖች እስላማዊ አለመሆናቸውንና እስልምና የሰላም ሃይማኖት መሆኑን እየሰበኩ ይገኛሉ፡፡ እስልምና የሰላም ሃይማኖት መሆኑንም ለማሳየት ከቁርኣን ውስጥ የተወሰኑ ጥቅሶችን ከታሪካዊና ምንባባዊ አውዳቸው ውጪ በመጥቀስ ሊያሳምኑን ይሞክራሉ፡፡ አሳዛኙ ነገር ብዙ ሰዎች በነዚህ ከንቱ ስብከቶች ተታልለው የአክራሪ እስልምናን ፀረ ሰላም መሆን መጠራጠራቸው ነው፡፡ አንዳንድ ወገኖች የእስልምናን ሰላማዊነት ለማስረዳት በተደጋጋሚ የሚጠቅሷቸው ሁለት ጥቅሶች አሉ፡፡ የመጀመርያው ሱራ 2፡256 ላይ የሚገኘው ነው

“በሃይማኖት ማስገደድ የለም፡፡ ቅኑ መንገድ ከጠማማው በእርግጥ ተገለጠ፡፡”

ይህ ጥቅስ ቁርኣንን የማያነበውንና የእስልምናን ታሪክና አስተምህሮ በወጉ የማያውቀውን ህዝብ ለማደናገር በእጅጉ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ነገር ግን የቁርኣን ሐታቾች እንደሚናገሩት ይህ ጥቅስ ጊዜው አልፎበታል፡፡ እስልምና “ናሲክ ወል መንሱክ” የተሰኘ አስተምህሮ አለው፡፡ “ናሲክ ወል መንሱክ” ሻሪና ተሸሪ የሚል ትርጉም ያለው የአረብኛ ሐረግ ሲሆን በዚህ አስተምህሮ መሠረት ሁለት እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ የቁርኣን ጥቅሶች ቢኖሩ የኋለኛው የፊተኛውን ይሽረዋል፡፡ ይህንን በተመለከተ ኢብን ከሢር የተሰኘ ትልቅ ተቀባይነት ያለው የሱኒ ሐታች የጥቅሱን ትክክለኛ ትርጉም፤ ማለትም ሰዎች እምነታቸውን እንዲቀይሩ ማስገደድ አስፈላጊ አለመሆኑን እንደሚናገር ካብራራ በኋላ እንዲህ ይላል፡-

“… ነገር ግን ይህ ጥቅስ በውጊያ ጥቅሶች ተሽሯል፤ ስለዚህ ሁሉም የዓለም ህዝቦች ወደ እስልምና እንዲመጡ ጥሪ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ማናቸውም ሰዎች ያንን ለማድረግ ፍቃደኛ የማይሆኑ ከሆነ ወይም ጂዝያን ለመክፈል እምቢ የሚሉ ከሆነ እስኪገደሉ ድረስ ውጊያ ሊደረግባቸው ይገባል…”[1]

ሌሎች ብዙ ሙስሊም ሐታቾች ይህ ጥቅስ በኋለኞቹ መገለጦች መሻሩን ይገልፃሉ፡፡ ስለዚህ ጥቅሱ “ካፊሮችን” ከማደናገር የዘለለ ጥቅም የለውም፡፡

ሙስሊሞች እስልምና የሰላም ሃይማኖት መሆኑን ለማሳየት የሚጠቅሱት ሌላው ጥቅስ ሱራ 5፡32 ላይ የሚገኘው “ያለ ነፍስ (መግደል) ወይም በምድር ላይ ያለማጥፋት (ካልሆነ በስተቀር) ነፍስን የገደለ ሰው ሰዎቹን ሁሉ እንደገደለ ነው፤ ሕያው ያደረጋትም ሰው ሰዎቹን ሁሉ ሕያው እንዳደረገ ነው” የሚለው ነው፡፡ ነገር ግን ሙስሊሞች ይህንን ጥቅስ ከአውድ ውጪ ነው የሚጠቅሱት፡፡ ሙሉ አውዱ እንዲህ ይላል፡-

“በዚህ ምክንያት በእስራኤል ልጆች ላይ እነሆ ያለ ነፍስ (መግደል) ወይም በምድር ላይ ያለማጥፋት (ካልሆነ በስተቀር) ነፍስን የገደለ ሰው ሰዎቹን ሁሉ እንደገደለ ነው፤ ሕያው ያደረጋትም ሰው ሰዎቹን ሁሉ ሕያው እንዳደረገ ነው ማለትን ጻፍን፡፡ መልክተኞቻችንም በግልጽ ተዓምራት በእርግጥ መጡዋቸው፡፡ ከዚያም ከዚህ በኋላ ከእነሱ ብዙዎቹ በምድር ላይ ወሰንን አላፊዎች ናቸው፡፡”

የቁርኣን ጸሐፊ ይህንን ሐሳብ የቀዳው ከአይሁድ የታልሙድ መጽሐፍ ላይ ነው፡፡ ጥቅሱ የሚናገረው ይህ ትዕዛዝ የተሰጠው ለእስራኤላውያን መሆኑን ነው፡፡ ለሙስሊሞች ደግሞ ምን ዓይነት ትዕዛዝ እንደተሰጠ ቀጣዩ አንቀፅ ይናገራል፡-

የእነዚያ አላህንና መልክተኛውን የሚዋጉ በምድርም ላይ ለማጥፋት የሚተጉ ሰዎች ቅጣት መገደል ወይም መሰቀል ወይም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን በማፈራረቅ መቆረጥ ወይም ከአገር መባረር ነው፡፡ ይህ በነሱ በቅርቢቱ ዓለም ውርደት ነው፡፡ በመጨረሻይቱም ለእነርሱ ከባድ ቅጣት አላቸው፡፡” ሱራ 5፡35

ቀደም ሲል የተጠቀሰው በጎ ትዕዛዝ የተሰጠው ለእስራኤላውያን ሲሆን በማስከተል የተቀመጠው የጭካኔ ትዕዛዝ ደግሞ ለሙስሊሞች የተሰጠ መሆኑን እናያለን፡፡ ነገር ግን ሙስሊም ወገኖች ጥቅሱን ሲጠቅሱ ለእስራኤላውያን የተሰጠ ትዕዛዝ መሆኑን የሚያመለክተውን ቀዳማይ ክፍልና ለሙስሊሞች የተሰጠውን ትዕዛዝ የያዘውን ተከታይ ክፍል ቆርጠው በመተው “ነፍስን የገደለ ሰው ሰዎቹን ሁሉ እንደገደለ ነው፤ ሕያው ያደረጋትም ሰው ሰዎቹን ሁሉ ሕያው እንዳደረገ ነው” የሚለውን ብቻ በማንበብ ያወናብዳሉ፡፡

 አላህንና መልክተኛውን መዋጋት ማለት በእስላማዊ አተረጓጎም መሠረት ማንኛውንም ቁርኣንንና እስላማዊ ህግጋትን መፃረር እንዲሁም የሙሐመድን ነቢይነት አለመቀበል ማለት ነው፡፡ “በምድር ላይ ማጥፋት” ደግሞ ለሙስሊም ማህበረሰብ እንቅፋት የሚሆን ማንኛውንም ነገር ማድረግን ያመለክታል፡፡ ይህም ደግሞ ወንጌልን መስበክን ያጠቃልላል፡፡ ስለዚህ “ሂዱና ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” የሚለውን የጌታን ትዕዛዝ በሸሪኣ ህግ በሚተዳደር የሙስሊም ማህበረሰብ መካከል የምትተገብሩ ከሆነ በሸሪኣ ህግ መሰረት ቅጣቱ በጥቅሱ ውስጥ የተዘረዘረው ነው፡፡

“ጅብ እስኪይዝ ያነክሳል” እንደሚለው የአገራችን ብሒል አክራሪ እስልምናም እነዚህን የመሳሰሉ ጥቅሶችን በመጠቃቀስ ምቹ ጊዜ እስኪመጣለት ድረስ ይሸነግላል፡፡ የበላይ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ግን ትክክለኛ ገፅታውን ያሳያል፡፡ በመታረድና ለእርሱ በመገዛት መካከል ያስመርጣል፡፡ ሦስተኛ ምርጫ የለም፡፡

——————

[1] Tafsir of Ibn Kathir, Al-Firdous Ltd., London, 1999: First Edition, Part 3, pp. 37-38

 

እስልምናና ሽብርተኝነት