የቁርኣን ኢ-ምክንያታዊ ትምህርት (“ሃይማኖትም ሁሉ ለአላህ እስኪሆን ድረስ ተጋደሉዋቸው”)

የቁርኣን ኢ-ምክንያታዊ ትምህርት

“ሃይማኖትም ሁሉ ለአላህ እስኪሆን ድረስ ተጋደሉዋቸው”

ከመስከረም አስራ አንዱ የሽብር ጥቃት ወዲህ በዓለማችን ላይ የሚገኙ ብዙ ሙስሊም ዐቃቤ-እምነታውያን እስልምና የሰላም ሃይማኖት መሆኑን በመስበክ ስራ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች በፈጣን ንግግሮቻቸውና ባማሩት ቃላታቸው የእስልምናን ሰላማዊነት ለዓለም ለማስረዳት እየደከሙ ቢገኙም እነርሱ ከሚናገሩት በተፃራሪ እስልምና የሰላም ሃይማኖት አለመሆኑን ጆሮ ያለው የሚሰማ ዓይን ያለው የሚያይ ሰው ሁሉ የሚስማማበት እውነታ ነው፡፡ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እንደምንከታተለው በዓለማችን ላይ በእስላማዊ ቡድኖች አማካይነት ብዙ ግድያዎችና አሳቃቂ ጭካኔዎች ሙስሊም ባልሆኑ ሰዎች ላይ ይፈጸማሉ፡፡ አንድ ሃይማኖት መመዘን ያለበት ከሚያስተምረው ትምህርት አንጻር እንጂ የሃይማኖቱ ተከታዮች ነን የሚሉ ሰዎች በሚፈጽሙት ተግባር መሆን እንደሌለበት እሙንና ቅቡል ነው፡፡ ነገር ግን በነዚህ እስላማዊ ቡድኖች አማካይነት ሙስሊም ባልሆኑ ሰዎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ብዙ የሽብር ተግባራት እስልምና ራሱ ከሚያስተምራቸው መሰረታዊ የሆኑ ትምህርቶች የተነሳ መሆኑን ማንኛውም ቁራኣንንና ሌሎች የእስልምና መጽሐፍትን ያነበበ ሰው ሁሉ የሚያውቀው እውነታ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ባለው አጭር ጽሑፍ ውስጥ እስልምና ተከታዮችን ለማፍራት ወታደራዊ ኃይል መጠቀሙና በእምነቱ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ምርጫዎቻቸውን እንዳይከተሉ በሰይፍ ማገቱ ትክክል አለመሆኑን ስነ-አመክንዮን በመጠቀም እንገልጣለን፡፡

“በሃይማኖት ማስገደድ የለም!” ቁርኣን 2፡256

ይህ የቁርኣን ጥቅስ ሰዎች የፈለጉትን እምነት ይከተሉ ዘንድ ነፃ ፈቃዳቸውን የሚያከብር መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ዛሬ ብዙ ሙስሊም ዐቃቤ-እምነታውያን ይህንን ጥቅስ በተደጋጋሚ በመጥቀስ እስልምና የሰው ልጆችን የሃይማኖት ነፃነት የሚያከብር የሰላም ሃይማኖት እንደሆነ አጥብቀው ይከራከራሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ጥቅስ ከአያሌ የቁርኣን ጥቅሶች ብሎም ከእስልምናና ከሙሐመድ ታሪክ ጋር የሚጋጭ መሆኑን ሊሸፍኑ የሚችሉበት ምንም አይነት ዘዴ የላቸውም፡፡ ሌሎች የቁርኣን ጥቅሶች እንዲህ በማለት ይህንን ሀሳብ ያፈርሳሉ፡-

ሱራ 8፡39 “እውከትም እስከማትገኝ ሃይማኖትም ሁሉ ለአላህ እስኪሆን ድረስ ተጋደሉዋቸው፤ ቢከለከሉም አላህ የሚሰሩትን በሙሉ ተመልካች ነው፡፡”

ሱራ 9፡123 “እላንተ ያመናችሁ ሆይ! እነዚያን በዙሪያችሁ ያሉትን ከሓዲዎች ተዋጉ፤ ከናንተም ብርታትን ያግኙ፤ አላህም ከሚጠነቀቁት ጋር መሆኑን እወቁ፡፡”

ሱራ 9፡73 “አንተ ነቢዩ ሆይ ከሓዲዎችንና መናፍቃንን ታገል፤ በነሱም ላይ ጨክን፤ መኖሪያቸውም ገሃነም ናት መመለሻቸውም ከፋች፡፡”

ሱራ 9፡5 “የተከበሩ ወሮች ባለቁ ጊዜ አጋሪዎችን ባገኛችሁባቸው ስፍራ ግደሏችው፣ ያዟቸውም፣ ክበቧቸውም፤ ለነሱም(መጠባበቅ) በየመንገዱ ተቀመጡ፤ ቢፀፀቱም ሶላትንም ደንቡን ጠብቀው ቢሰግዱ ግዴታ ምፅዋትንም ቢሰጡ መንገዳቸውን ልቀቁላቸው፤ አላህ መሀሪ አዛኝ ነውና፡፡’’

ሱራ 9፡29 “ከነዚያ መጽሐፍን ከተሰጡት ሰዎች እነዚያን በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑትን አላህና መልዕክተኛዉን (ሙሐመድን) እርም ያደረጉትንም እርም የሚያደርጉትንና እውነትኛውን ሃይማኖት የማይቀበሉትን እነርሱ የተዋረዱ ሆነው ግብርን በእጆቻቸው እስከሚያመጡ ድረስ ተዋጉዋቸው፡፡”

ሙስሊሞች ከቁርኣን ቀጥሎ ትልቅ ስፍራ በሚሰጡት መጽሐፍ በሳሂህ አልቡኻሪ ውስጥ ሙሐመድ እንዲህ የሚል ጠንካራ ትዕዛዝ ለተከታዮቹ ማስተላለፉ ተነግሯል፦

“ማንኛውንም እስልምናን ትቶ ወደኋላ የሚመለስ ሰው ግደሉት!” (ሳሂህ አል-ቡኻሪ መጽሐፍ 52 ሐዲስ 260)

እዚያው ሳሂህ አልቡኻሪ ውስጥ እንዲህ የሚል ሌላ አስገራሚ ዘገባ እናገኛለን

“ኢብን ዑመር እንደዘገበው የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ብለዋል፤ ‘ሰዎች ከአላህ በስተቀር ሊመልክ የሚገባው እንደሌለ እና ሙሐመድ ደግሞ የእርሱ መልዕክተኛ መሆኑን እስኪመሰክሩ ድረስ እንዲሁም ሰላትን ደንቡን ጠብቀው እስኪሰግዱ ድረስ እና ግዴታ ምጽዋትን እስኪሰጡ ድረስ እንድዋጋቸው (በአላህ) ታዝዣለሁ፤ ይህንን ካደረጉ በእስልምና ህግ ከተደነገገው በስተቀር ህይወታቸውንና ንብረታቸውን ከእኔ ይታደጋሉ፣ ድርሻቸውም በአላህ ይቆጠርላቸዋል፡፡’” (ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅጽ1 መጽሐፍ 2 ሐዲስ 24)

እንግዲህ በእነዚህና እነዚህን በመሳሰሉት ሌሎች እጅግ በጣም ብዙ የሰይፍ ጥቅሶች ሳቢያ እስልምና ወታደራዊ ሀይል ተጠቅሞ ተከታየቹን በማብዛትና የሌሎች እምነቶች እንቅስቃሴዎችን በሰይፍ በመግታት ረገድ ወደር የለሽ ሃይማኖት ሆኗል፡፡ ከእስልምና ታሪክ እንደምንረዳውና ዛሬ በዙርያችን እንደምንታዘበው “በሃይማኖት ማስገደድ የለም” የሚለው የቁርኣን ቃል አፍኣዊ ብቻ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ አንድን የራሱ የሆነ ነጻ ፈቃድ ያለውንና ማሰብ የሚችል አዕምሮ ያለውን ሰው በማስገደድ የኛን ሃይማኖት እንዲከተል ማድረግ በየትኛውም ሚዛን ተቀባይነት የለውም፡፡ እስልምና ትክክል ሆነም አልሆነም የማይከተሉትንና ከሃይማኖቱ የሚወጡትን ሰዎች ይገደሉ ዘንድ ማዘዙ ኢ-ምክንያታዊ ነው፡፡

እስኪ እስልምና ትክክለኛ ሃይማኖት ነው እንበልና ይህንን ድርጊት እንመዝን፤ ማን ያውቃል ዛሬ ሙስሊም ያልሆነ ሰው ሌላ ጊዜ እስልምና “ትክክል” መሆኑን ተድረቶ ሊሰልም ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ ሰው እስልምናን የሚመረምርበት ጊዜ ከተነፈገውና አንዴ በተነገረው ነገር ብቻ ካላመንክ ተብሎ ቢገደል ወደፊት ይህንን ሃይማኖት በደንብ አውቆ የሚሰልምበት እድል አይኖረውም ማለት ነው፡፡ ማን ያውቃል የሚገደለው ሰው ነገ ቁርኣንን በራሱ አንብቦ የእስልምና “እውነትነት” ገብቶት ጥሩ የእምነቱ ተከታይ ሊወጣው ይችላል፡፡ ምናልባት ደግሞ ዛሬ በተለያዩ ምክንያቶች ተሳስቶ እስልምናን የለቀቀ ሰው ነገ ተፀፅቶ ወደ ቀድሞ ሃይማኖቱ በመመለስ ሌሎችንም ወደ እስልምና እንዲገቡ የሚያደርግ ጠንካራ ሙስሊም ሊሆን ይችላል፡፡ ከተገደለ ግን ይህንን እድል ያጣል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እስልምና ትክክለኛ ሃይማኖት ቢሆን እንኳ የእምነቱን ጥሪ ያልተቀበሉትንና ከእምነቱ ያፈነገጡትን ሰዎች እንዲገደሉ ማዘዙ ትክክል አለመሆኑ ግልፅ ነው፡፡

እስኪ አሁን ደግሞ እስልምና ትክክለኛ ሃይማኖት አይደለም ብለን በተቃራኒው እናስብና የሚሆነውን እንመልከት፡፡ እስልምና ትክክለኛ ሃይማኖት ካልሆነና ክርስትና ወይም እንበልና ሌላ ሃይማኖት ትክክል ከሆነ ደግሞ እነዚህ የሚገደሉ ሰዎች ትክክለኛውን ሃይማኖት በመመርመር መንገዳቸውን ከማስተካከላቸው በፊት በመሞታቸው ሳቢያ በስጋቸውም በነፍሳቸውም ተጎጂዎች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ የሚገደሉት ሰዎች ደግሞ ትክክለኛ እምነት ላይ ያሉ ሰዎች ከሆኑ የንጹሃንን ደም በከንቱ ያፈሰሱት ሙስሊሞች እውነተኛ በሆነው እነዚህ ሰዎች በሚያመልኩት አምላክ ዘንድ ተጠያቂዎች ይሆናሉ፤ ፍርዱንም ይቀበላሉ፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ሳብያ እስልምና ሰዎችን ለማዳን መጣሁ እያለ ለሰዎች መጥፋት ምክንያት እየሆነ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እውተኛው አምላክ ተከታዮቹን ይጠብቃ ቸዋል እንጂ እነርሱ አይጠብቁትም፡፡ ሙስሊም ወገኖች ሆይ፤ አምላክ ኃይል አንሶት ነው ኃይማኖቴን ለመጠበቅና ለማስፋፋት ተዋጉልኝ የሚለው? መሲሁ ኢየሱስ ዛሬ ከሁለት ቢሊየን በላይ ተከታዮች ያፈራው ሠይፍ በመጠቀም ሳይሆን ፍቅር በመስጠት ነው፡፡ ፍቅር ከሠይፍ በላይ ኃይል አለው! ሠይፍ የሰው ልብ አይለውጥም፡፡ ፍቅር ግን የሰውን ሁለንተና ይለውጣል፡፡ የመሲሁ መንገድ የሠይፍ መንገድ ሳይሆን የፍቅር መንገድ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚረግሙአችሁንም መርቁ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ ስለሚያሳድዱአችሁም ፀልዩ” በማለት ያስተማረው (ማቴዎስ 5፡43)፡፡ ለዚህም ነው “ሰይፍ የሚያነሱ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደሰገባው መልስ” በማለት ጴጥሮስን የገሰፀው (ማቴዎስ 26:52)፡፡ ለዚህም ነው በመስቀል ላይ ሳለ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለት ለጠላቶቹ የማለደው (ሉቃስ 23:34)፡፡ ከዚህ የተነሳ እኛ የመሲሁ የኢየሱስን ትምህርቶች ለመከተል መርጠናል፡፡ እናንተም ምርጫችሁን ታስተካክሉ ዘንድ የፍቅርና የሰላምን ጥሪ እናቀርብላችኋለን፡፡