ውዳሴ አሕመድ ግራኝ፤ ግፈኛን የማጀገን ዘመቻ በኢትዮጵያ አክራሪያን

ውዳሴ አሕመድ ግራኝ

ግፈኛን የማጀገን ዘመቻ በኢትዮጵያ አክራሪያን

በተለምዶ አሕመድ ግራኝ ወይም በትክክለኛ ስሙ አሕመድ ኢብን ኢብራሂም አል-ጋዚ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ትልልቅ ጥፋቶችን ካደረሱ ጂሃዳውያን መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ይህ ሰው አነሳሱ ከሐረር አካባቢ ሲሆን ከሶማሌ ዘር መሆኑ በአብዛኞቹ የታሪክ ጸሐፍት ዘንድ ይታመናል፡፡ ነገር ግን የዘር ግንዱ ከአረብ ይመዘዛል የሚሉም አልጠፉም፡፡[1] ግራኝ የተነሳበት ዘመን በየአገራቱ የጂሃድ ቋያ እሳት ይንቀለቀል የነበረበትና ፖለቲካዊውም እስልምና ከመቸውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ የሙስሊም አገራትን በማስተሳሰር ለአንድ ዓላማ እንዲሰለፉ ያስቻለበት ዘመን ስለነበር ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ በነበሩትና ከሃይማኖት ይልቅ ወደ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ የበላይነት በሚያደሉት፤ እርስ በርሳቸውም በመዋጋት በሚታወቁት ሙስሊም ሱልጣኔቶች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡ እነዚህን ሱልጣኔቶች ለአንድ ዓላማ በማሰለፍ እስልምና በኢትዮጵያ ላይ ሲመኝ የነበረውን የበላይነት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ማሳካት የቻለው አሕመድ ግራኝ ነበር፡፡ የአፄ ልብነ ድንግል ደካማ የአመራር ብቃትና በክርስትና እምነቱ ላይ የነበረው የላላ አቋም እንዲሁም የፊውዳሉ ብልሹና ኀላፊነት የጎደለው ሁኔታ የጂሃድ ጦር በኢትዮጵያውያን ላይ ድልን እንዲቀዳጅ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ደግሞ በኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ የነበሩትን ሕዝቦች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ማስተማር እንደተሳናትና በጥቃቅን ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በነበሩት የአመለካከት ልዩነቶች በጎራ የመከፋፈል ሁኔታም እንደነበር የታሪክ ጸሐፍት ይናገራሉ፡፡[2] ቱርኮችና ማምሉኮችን የመሳሰሉት የውጪ የእስላም ኃይላት ለወራሪ ጂሃዳውያኑ የሚሰጡት ድጋፍም ቀላል አልነበረም፡፡ በዚያን ዘመን በአገር ውስጦቹ ላይ ብቻ ሳይሆን በውጪ አገራት በነበሩት ኢትዮጵያውያን ላይም ጭምር ጥቃቶች ይፈፀሙ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል በ1518 እና በ1522 ቱርኮች ለጸሎት ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዙ በነበሩት ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ላይ ጭፍጨፋ ፈፅመዋል፡፡[3] ይህም ደግሞ በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ላይ የተደረገው ጂሃድ ዓለም አቀፋዊ ገፅታ እንደነበረው ያሳያል፡፡

በሞቃዲሾ ለአሕመድ ግራኝ (አሕመድ ጉርዬ) የተሠሩለት የመታሰብያ ሐውልታት
የፎቶ ምንጭ Wikipedia.net

የሰሜኑ የክርስቲያን መንግሥት በጂሃዳውያን ላይ የበላይነቱን ማጣቱንና ታሪክ መቀየሩን ያመለከተው በ1529 በወርሃ መጋቢት የተደረገው የሽምብራ ኩሬ ጦርነት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ የግራኝ ጦር ከቱርክ ባስመጣቸው አዳዲስ መድፎች በመጠቀም የአፄ ልብነ ድንግልን ሠራዊት ገጠመ፡፡ በዚህ ጦርነት ላይ 200 የሚሆኑ ሥልጡን የቱርክ ወታደሮችና ብዙ የአረብ ወታደሮች ተሳትፈዋል፡፡[4] በመድፎቹ ጥቃት የተደናገጡት የንጉሡ ወታደሮችም ነፍሳቸውን ለማትረፍ መሸሽ ግድ ስለሆነባቸው የጂሃድ ጦር ወሳኝ ድል ተቀዳጀ፡፡ ከዚያ ወዲያ የአፄ ልብነ ድንግል ወታደሮች ያሉበት ቦታ ታውቆ ለጥቃት እንዳይጋለጡ በመስጋት ምግባቸውን ለማብሰል እንኳ እሳት ማንደድ አልቻሉም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥሬ ሥጋ መብላት የተጀመረው በዚያን ዘመን እንደነበር ይነገራል፡፡[5]

የመጀመርያውን ስኬት ተከትሎ የጂሃድ ጦር በድል ላይ ድልን እየደረበ እስከ ትግራይ ድረስ ዘለቀ፡፡ የትግራይ አምባዎች በቀላሉ የሚያዙ ስላልነበሩ ግራኝ አውራይ አቡይ የተሰኘ ሹሙን በመላክ ሦስት ትልልቅ መድፎችን ገዝቶ እንዲያመጣ አደረገ፡፡ ከሦስቱ መድፎች መካከል አንዱ በጣም ግዙፍ ነበር፡፡ ተኳሾቹም በመድፍ ተኩስ ጥበብ የተካኑ ከሕንድ የመጡ ቅጥረኞች ነበሩ፡፡[6] የጂሃድ ሠራዊት የአክሱም ፅዮን ማርያምን ቤተ ክርስቲያ ዘረፈ፣ አቃጠለ፡፡ ወደ ምዕራብም በመዘርጋት እስከ ኑቢያ ድረስ የነበረውን የክርስቲያን ምድር ወረረ፣ አጠፋ፣ አብያተ ክርስቲያናትንና ቅዱሳት መጻሕፍትን አቃጠለ፣ ካህናትና ምዕመናንን አረደ፣ ንዋዬ ቅዱሳትን ዘረፈ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን በግድ አሰለመ፡፡ ሁለት ሦስተኛው የክርስቲያን ግዛት በጂሃዳውያን እጅ የገባ ሲሆን በክርስቲያን ምንጮች መሠረት ዘጠና ከመቶ በላይ የሚሆነውም ሕዝብ በግድ እንዲሰልም ተደርጎ ነበር፡፡[7] በሙስሊም ምንጮች መሠረት ግን በጣት የሚቆጠሩት ብቻ ሲቀሩ ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን ሰልሞ ነበር፡፡[8]

በዚያን ዘመን የእሳት ሲሳይ ከሆኑት አብያተ ክርስቲያናት መካከል የደብረ ሊባኖስ ገዳምና የአትሮንስ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ይጠቀሳሉ፡፡ የደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳት ቤተ ክርስቲያኒቱን ከቃጠሎ ለማትረፍ አቡበከር ከቲም ለተሰኘው የግራኝ የጦር መኮንን በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚገኘውን ኃብት፣ ከብርና ከወርቅ የተሰሩትን ንዋየ ቅዱሳት ሁሉ ቢሰጡትም ቤተ ክርስቲያኒቱ ከመቃጠል አልዳነችም፡፡[9] በአትሮንስ ማርያም ላይ የተደረገውን በተመለከተ ይልማ ዴሬሳ የተሰኙት የታሪክ ጸሐፊ ተከታዩን አስፍረዋል፡-

መካነ ሥላሴን ካጠፋ በኋላ ግራኝ ወደ ሌላዋ ኃብታም ደብር ገሥግሦ አትሮንስ ማርያም የምትባለውን ታላቅ ደብር አዘርፎ አቃጠላት፡፡ ያትሮንስ ማርያም ዘረፋ ከስድስት ሰዓት እስከሚከተለው ጠዋት ድረስ ቆየ ይባላል፡፡ የግራኝ ሱማሌዎች ከመቅደሱ ግድግዳ ላይ የተለበጠውን ከፈይና የሙካሽ ጥልፍ ሥራዎች እየቀደዱ ከወሰዱ በኋላ ቁጥር የሌላቸውን የወርቅ ፅዋዎችና ሌሎችንም የንዋየ ቅዱሳት ዕቃዎች ሁሉ ዘረፉ፡፡ ከተወሰዱትም ምርኮዎች መካከል አንድ ሺህ ወቄት የሚመዝን የወርቅ ጽላትና በወርቅ ቅጠል ላይ የተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ ነው ይባላል፡፡ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በጣም የሚከብድ ስለነበረ አራት ሰዎች ሁነው ሊያነሱት አልቻሉም፡፡ ዘረፋው ከተፈጸመ በኋላ የግራኝ ሰዎች በዚህችም ደብር ላይ እሳት ለቀቁባት፡፡ ከመነኮሳቱም መካከል ቤተ ክርስቲያናቸው ስትቃጠል ባዩ ጊዜ በኀዘንና በወዮታ እየዘለሉ ከእሳቱ ውስጥ ወድቀው አብረው የተቃጠሉ ብዙዎች ነበሩ፡፡[10]

ጂሃዳውያን አንሰልምም ያሉትን ክርስቲያኖች አብዛኞቹን የገደሉ ሲሆን የተቀሩትን በነቢዩ ሙሐመድ ትዕዛዝ መሠረት ጂዝያ ያስከፍሉ ነበር፡፡[11]

በዚያን ዘመን ክርስቲያኖች እምነታቸውን ይዘው ለመቆየት ያሳዩትን ጀግንነት ሊገልፅ የሚችል አንድ ታሪክ እንጥቀስ፡-

… ሁለት ክርስቲያኖችን ይዘው ወደ ኢማሙ ሰፈር በመመለስ በፊቱ አቀረቧቸው፡፡ እርሱም “አገሪቱ በሙሉ መስለሟን እያያችሁ እስልምናን የማትቀበሉት ለምንድነው?” በማለት ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም “አይ መስለም አንፈልግም” አሉት፡፡ “ስለዚህ የምናስተላልፍባችሁ ፍርድ ራሳችሁን መቁረጥ ነው” አላቸው፡፡ እነርሱም “ይሁን” አሉት፡፡ ኢማሙም በመልሳቸው ተደነቀ፤ እንዲገደሉም አዘዘ፡፡[12]

አሕመድ ግራኝ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ምድሪቱን ሲያስጨንቅ ከቆየ በኋላ ንግሥት እሌኒ በነበራት ፖለቲካዊ ብስለት ያስመጣቻቸውንና አፄ ልብነ ድንግል አስቀይሞ የመለሳቸውን ፖርቹጋሎች እንደገና ለማስመጣት ቤርሙዴዝ የተባለ መልእክተኛ ተላከ፡፡ የእርዳታ ጥያቄውም አዎንታዊ ምላሽ በማግኘቱ 400 የሚሆኑ የፖርቹጋል ወታደሮች ከነረዳቶቻቸው ክርስቶፈር ዳጋማ[13] በተሰኘ የ25 ዓመት ወጣት የጦር አዛዥ መሪነት ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ በጂሃድ ጦር ከፍተኛ የሞራል ውድቀት ውስጥ ገብቶ የነበረውም የንጉሡ ሠራዊት ወኔው ተነሳሳ፡፡ ግራኝ የፖርቹጋሎቹን መምጣት በሰማ ጊዜ ከንጉሡ ጋር እንዳይገናኙ ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት ውጊያ የገጠማቸው ሲሆን በመጀመርያው ውጊያ በጥይት ቆስሎ ለጥቂት ከመያዝ ተርፎ ሸሽቷል፡፡[14] ነገር ግን ኋላ ላይ ተሳክቶለት ክርስቶፈር ዳጋማን በመማረክ ገድሎታል፡፡ የክርስቶፈርን አሟሟት በተመለከተ ሚጉኤል ዴ – ካስታንጓዞ የተሰኘ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት የፖርቹጋል ወታደሮች መካከል አንዱ የነበረ ሰው በስፋት ጽፏል፡፡

… ዶም ክርስቶፍ መሆኑን በትጥቁ ወዲያውኑ ስላወቁት በያዙት ጊዜ በጣም ደስ አላቸው፡፡ በመንገድም ላይ በጣም እያላገጡበትና በጣም እንዳልሆነ እያደረጉት ይዘውት ሄዱ፡፡ ከዚያ በኋላ እርሱንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን በግራኝ ፊት አቀረቧቸው፡፡ ግራኝም ከመቶ ስድሳ የሚበልጡ የፖርቱጋሎች ራስ ከድንኳኑ ፊት በእንጨት ሰክቶ ተክሎ ስለነበረ ባደረገው ድል በጣም ደስ አለው፤ ለያንዳንዱ የፖርቱጋልን ራስ ለሚቆርጥ ወታደር ዋጋ አድርጎለት ስለነበረ ይህንኑ ዋጋ ለማግኘት ሰዎቹ ከጦሩ ሜዳ ያገኟቸውን ሁሉ ይዘው ሄዱ፡፡

ዶም ክርስቶፍ ከድንኳኑ ፊት በቀረበ ጊዜ የበለጠ ጭንቀት እንዲያድርበት ለማድረግ ይህ ውሻ የፖርቱጋሎችን ራሶች ከፊቱ አስመጥቶ የማን ራሶች ናቸው? እያለ አላገጠባቸው፡፡ እነዚህ ዶም ክርስቶፍ ከነርሱ ጋር ሁኖ አገሩን ሊወስዱበት የነበሩት መሆናቸውን (በቀልድ እያመለከተ) ዶም ክርስቶፍ እንዲህ ዓይነት ነገር በማሰቡ እብደቱ እንደሚታይ እያስገነዘበ ለዚህ ድፍረቱም ትልቅ ክብር ሊያደርግለት መፍቀዱን ለመግለጥ ዶም ክርስቶፍን ልብሱን እንዲያወልቁ፣ ሁለት እጆቹን እንዲያስሩና በጭካኔ እንዲገርፉት በባርያዎቹ ጫማም ፊት ፊቱን እንዲመቱት አደረገ፡፡ ሪዙን የመብራት ክር በማድረግ ብዙ ሠም ካስቀባ በኋላ እንዲያያይዙት አደረገ፡፡ የሰደደለትንም መቀስ አስመጥቶ ምን ጊዜም ለእርሱ ስላቆየው እርሱም ሆነ ወታደሮቹ አልሰሩበትም እያለ ቅንድቡንና ሽፋሉን አስቆረጠው፡፡ ይህንን ሁሉ ካስደረገ በኋላ ለእረፍት ድንኳኖቹን ሁሉና የጦር አለቆቹን እንዲጎበኝ አዘዘ፡፡ ከዚያም ብዙ የውርደት ሥራ ተሠራበት፡፡ (ዶም ክርስቶፍም) ከክርስቲያኑ አገር መቶ ማይል ከያዘ በኋላ ለዚህ ስላበቃው እግዚአብሔርን እያመሰገነ ይህንን ሁሉ በትዕግስት ተቀበለው፡፡ የጠላትም ጭፍሮች ጊዜውን በእርሱ ካሳለፉ በኋላ ወደ ግራኝ ድንኳን መልሰው አመጡት፡፡ ይህም ራሱን ለሌሎች ለማስቆረጥ የማይበቃው ስለሆነ እርሱ በእጁ ራሱን ቆረጠው፡፡[15]

ይህ የክርስቶፈር ዳ ጋማ ታሪክ በዚህች አገር ላይ ክርስትናን ለማቆየት ምን ያህል ዋጋ እንደተከፈለ ያሳየናል፡፡

በዚህ የግራኝ አስነዋሪና ዘግናኝ ድርጊት የተበሳጩ ብዙ ቱርኮች ግራኝን በመተው ወደ መጡበት እንደተመለሱ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ለቱርኮች ከግራኝ መለየት አገሪቱ በድህነት መመታቷና የሚፈልጉትን ምርኮ ለማግኘት ተስፋ ሰጪ ሁኔታ አለመኖሩም እንደ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ ግራኝም የፖርቹጋሎችን መበታተንና የመሪያቸውን ሞት እንደ ጦርነቱ ፍፃሜ ስለቆጠረ ቱርኮች ወደ መጡበት በመመለሳቸው ቅሬታ አልነበረውም፡፡ ነግር ግን ቱርኮችን ማሰናበቱ ከባድ ስህተት ነበር፤ ዋጋም አስከፍሎታል፡፡[16]

የክርስቶፈር ዳ ጋማ ፊርማ
የፎቶ ምንጭ Wikipedia.net

ረጅሙ ታሪክ ሲቋጭ፤ የተረፉት የፖርቹጋል ወታደሮች ከንግሥት ሰብለ ወንጌልና ከልጇ ከአፄ ገላውዴዎስ ጋር ተገናኙ፡፡ የካቲት 22/ 1543 ዓ.ም. ወይና ደጋ በሚባል ቦታ በተደረገ ጦርነት 9,000 የነበረው የገላውዴዎስና የፖርቹጋሎች ሠራዊት አረቦችና ቱርኮች የተካተቱበትን 15,000 የግራኝ ሠራዊት ድል ነሳ፡፡ ግራኝም በውጊያው ላይ በአንድ የፖርቹጋል ወታደር በተተኮሰ ጥይት ከቆሰለ በኋላ አዝማች ካሊት የተባለ ሰው በሰይፍ ራሱን ቆረጠው፡፡ አገሪቱን እንደ አንበጣ አልብሷት የነበረው የጂሃድ ሠራዊት መሪው መሞቱን ባወቀ ጊዜ ወኔው ስለተሰለበ ተፍረክርኮ ከክርስቲያን ምድር ተጠራርጎ ወጣ፡፡ የግራኝ ሚስት ባቲ ድል ወንበራም ከተወሰኑ የቱርክ ወታደሮች ጋራ ከተዘረፈው ኃብት የቻለችውን ያህል በመውሰድ ወደ ሐረር ሸሽታ ከተመች፡፡[17]

ዛሬ ምን እየሆነ ነው? በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ላይ ይህንን ታላቅ ጭፍጨፋ ያደረሰው አሕመድ ግራኝ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ በሚዘጋጁ ብዙ እስላማዊ የህትመት ውጤቶች ውስጥ እንደ ጀግና እየተወደሰ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ያህል አሕመዲን ጀበል “ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የጭቆናና የትግል ታሪክ” በሚል ርዕስ በጻፈው መጽሐፉ ውስጥ “ታላቁ ወጣት ሙጃሒድ ኢማም አሕመድ በ37 ዓመቱ በፌብሩዋሪ 22/ 1443 ተሰዋ” በማለት ሙሾ ያወርድለታል፡፡[18] ሐሰን ታጁ የተሰኘ ጸሐፊም “ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጀግና” በማለት ያወድሰዋል፡፡[19] ይኸው ጸሐፊ በሌላ መጽሐፉ የግራኝን ወንጀሎች ለማስተባበል ጥረት ሲያደርግ ይታያል፡፡ የአገራችንን ታላላቅ የታሪክ ጸሐፍትንም ታሪኩን በትክክል አላቀረቡም በሚል ክፉኛ ይወርፋል፡፡[20]  ውዳሴ አሕመድ ግራኝ በግለሰቦች ብቻ ሳይሆን በመንግሥት በጀት በሚታተሙ የህትመት ውጤቶችም ውስጥ ይስተዋላሉ፡፡ ሺሃብ አድ-ዲን አሕመድ ቢን አብደልቃድር በተሰኘ የአረብ ጸሐፊ ተጽፎ በሐረሪ ክልል ጉባኤ አማካኝነት “ሐበሻን የማቅናት ዘመቻ” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ የተመለሰው ባለ ሁለት ቅፅ የግራኝ ዜና መዋዕል ለዚህ እማኝ ነው፡፡ “ፉቱሑል ሐበሽ” የሚለው የመጽሐፉ የአረብኛ ርዕስ “የሐበሻ ሽንፈት” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ላዩን ለማሳመር “ሐበሻን የማቅናት ዘመቻ” ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ይህም ጦርነቱ የተደረገው ለሐበሾች ታስቦ እንደሆነ ያስመስላል፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ሐበሾች ጠማሞች ናቸው የሚል ውስጠ ወይራዊ ስድብን ያዘለ ነው፡፡ ይህ የጂሃድ መጽሐፍ አዲሱን ትውልድ ለአመፅ ለማነሳሳት ታልሞ የተተረጎመ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሲደረግ ሀይ የሚል አካል መጥፋቱ ጂሃዳውያን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ምን ያህል እንደተሰገሰጉና ጡንቻቸው ምን ያህል እንደፈረጠመ የሚያሳይ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች በቸልታ የሚታለፉ ከሆነ ነገ መንግሥትንም ሆነ ሕዝብን ዋጋ ማስከፈላቸው የማይቀር ነው፡፡

አሕመድ ግራኝ በሙስሊሙ ሕብረተሰብ ላይ “የተጫነውን የጭቆና ቀንበር” ለመስበር እንደተዋጋ የነፃነት አርበኛ እየተቆጠረ ሲሆን ነገር ግን ከአረብና ከቱርክ ተስፋፊዎች ጋር በመመሳጠር አብያተ ክርስቲያናትን በማቃጠል፣ ቅርሶችን በማውደም፣ ንብረት በመዝረፍ፣ ምዕመናንና ካህናትን በመግደል የፈፀመው የውድመትና የእልቂት ወንጀል ችላ እየተባለ ይገኛል፡፡ የጠቡም መነሻ ክርስቲያኖች እንደሆኑ በማስመሰል እየተነገረ ይገኛል፡፡ ነገር ግን በሰሜን የነበረውን የባህር በር በመያዝ ክርስቲያኑ መፈናፈኛ እንዲያጣ ያደረጉት ሙስሊሞች ነበሩ፡፡ በደቡብ የነበረውን የባህር በር የያዘው የእስላም ኃይል ከሰሜኑ የሚያንስ ስለነበረ በዚህ የባህር በር ለመጠቀም በዚያ አካባቢ የነበሩትን እስላማዊ አንጃዎች ማስገበር አስፈላጊ ስለነበር የክርስቲያን ነገሥታት ወታደራዊ ኃይላቸውን ተጠቅመዋል፡፡ ትኩረታቸውም የባህር በርና የንግድ መስመሮችን ከሥጋት ነፃ ማድረግ እንጂ ሙስሊሞችን ማጥፋት አልነበረም፡፡ የሰሜን ነገሥታት በደቡብ ከነበሩት ሱልጣኔቶች ጋር በየጊዜው ውጊያ ቢገጥሙም ነገር ግን በግዛቶቻቸው ውስጥ የነበሩትን ሙስሊሞች በተመለከተ የተለየ ፖሊሲ ይከተሉ ነበር፡፡ አናሳ የነበሩት ሙስሊም ማሕበረሰቦች ከመንግሥታዊ ሥልጣን ቢገለሉም ነገር ግን በሙሉ ነፃነት ይንቀሳቀሱ እንደነበር የታሪክ ሃቅ ነው፡፡[21] አሕመድ ግራኝ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ላይ የፈፀመው ወረራ በአረቦችና በቱርኮች የታገዘ ክርስትናን ሙሉ በሙሉ የማጥፋትና በምትኩም እስልምናን የማስቀመጥ የጂሃድ ወረራ እንጂ ራስን የመከላከል ጦርነት አልነበረም፡፡ ያንን ዘመን የሚመኙና ለግራኝ የሚዘምሩለት የአገር ውስጦቹና የውጪዎቹ ጂሃዳውያን ቀን ቢሰጣቸውና እድል ቢያገኙ ተመሳሳይ ታሪክ ከመድገም ወደ ኋላ እንደማይሉና ክርስትናን ለማጥፋት የሚቋምጡ መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ነገር ግን ምቹ ጊዜ እስኪመጣላቸው ድረስ አጉርጠው አድብተዋል፡፡

———————————————

[1] Siegbert Uhlig. Encyclopedia Aethiopica; 2003, A-C, p. 155

[2] Merdechai Abir. Ethiopia and the Red Sea: the Rise and Secline of the Solomonic Dynasty and Muslim-European Rivalry in the Region: 1980, pp. 80-82

[3] Ibid.

[4] ይልማ ዴሬሳ፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን፤ 1959፣ ገፅ 64-65

[5] United States  Joint Publications Research Service: Translations on Sub-Saharan Africa; Issue 1767-1775, p. 62

[6] ይልማ ዴሬሳ፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ገፅ 109

[7] J. Spencer Trimingham. Islam in Ethiopia; 1952, p. 88

[8] Ibid., 87

[9] ይልማ ዴሬሳ፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ገፅ 85

[10] ዝኒ ከማሁ ገፅ 91

[11] Trimingham. Islam in Ethiopia; p. 88

[12] Ibid., 88-89

[13] ክርስቶፈር ዳ ጋማ የዝነኛው ፖርቹጋላዊ አሳሽ የቫስኮ ዳ ጋማ ልጅ ነበር፡፡

[14] Trimingham. Islam in Ethiopia; p. 89

[15] ሚጉኤል ዴ – ካስታንጓዞ፡፡ የፖርቱጋሎች ጀግንነት፤1952፣ ገፅ 68፤ በዶ/ር ሙራድ ከሚል እና በዮናስ ቦጋለ ወደ አማርኛ የተመለሰ

[16] ይልማ ዴሬሳ፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ገፅ 187-189

[17] ዝኒ ከማሁ ገፅ 93-201

[18]አሕመዲን ጀበል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች 615-1700 የጭቆናና የትግል ታሪክ፤ ቅፅ 1፣ 2003፣ ገፅ 212

[19] ሐሰን ታጁ፡፡ የሐመረ ተዋሕዶን ቅጥፈት በእስልምና እውነት፤ አልበያን ሊሚትድ፣ አንደኛ ዕትም፣ 2002፣ ገፅ 86

[20] ሐሰን ታጁ፡፡ ሰይፉን ፍለጋ፤ ከመካ እስከ ቫቲካን፤ አንደኛ ዕትም፣ 2006፣ ገፅ 332-234

[21] M. Abir. Ethiopia and the Read Sea; p. 731

 

እስልምናና ሽብርተኝነት