የዚማ ሕግና የጂዝያ ግብር – እስላማዊ የግፍ ቀንበር በአይሁድና በክርስቲያኖች ላይ

የዚማ ሕግና የጂዝያ ግብር

እስላማዊ የግፍ ቀንበር በአይሁድና በክርስቲያኖች ላይ

የኸይበር ወረራ ሙስሊሞች እስከ ዛሬ ድረስ ከአይሁድና ከክርስቲያኖች ጋር ላላቸው ግንኙነት መሠረት የጣለ የታሪክ ክስተት ነበር፡፡ መሐመድ በኸይበር ወረራ ወቅት በሕይወት የተረፉትን አይሁድ ሃይማኖታቸውን ይዘው እንዲቆዩ የፈቀዱላቸው ቢሆንም ያንን ማድረግ ይችሉ ዘንድ አንድ ቃል ኪዳን አስገብተዋቸው ነበር፡፡ ይህ ቃል ኪዳን “የዚማ ቃልኪዳን” ወይም “የመገዛት ቃልኪዳን”  በመባል ይታወቃል፡፡

“ዚማ” የሚለው ቃል “ዘማ” ከሚል የአረብኛ ግሥ የተገኘ ሲሆን “(ክፉ ጠባይን በተመለከተ) መውቀስ፣ ምስጋና መንፈግ፣ ስህተትን ፈልጎ ማግኘት፣ መገምገም፣ ማሔስ” የሚሉ ትርጉሞች አሉት፡፡ የማመስገን ተቃራኒ ነው፡፡ ዚማ ጥፋት ወይም ስህተትን ከመፈፀም የተነሳ የሚመጣ ተጠያቂነትን የሚያመለክት ሲሆን ቢፈርስ ወይም ቢጣስ ቃል ኪዳን አፍራሹን ወገን ተጠያቂ ሊያደርግ የሚችል ስምምነትን ወይም ቃል ኪዳንን ለማመልከት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡[1] ስምምነቱን የሚፈርሙ ሰዎች ደግሞ “ዚሚ” በመባል የሚታወቁ ሲሆን የገቡትን ቃል ኪዳን እስካላፈረሱ ድረስ ሕይወታቸው በሕግ ይጠበቃል፡፡ ዚሚዎች የመጀመርያ የሚገቡት ውል ለሙስሊሞች እንደ ደም ካሳ የሚቆጠር “ጂዝያ” በመባል የሚታወቅ ግብር መክፈል ነው፡፡ ይህ ግብር የሚከፈለው ሕይወትን ለማቆየት ነው፡፡ ሙስሊሞች ግብሩን የሚቀበሉት እንደ ተጎጂ አካል በመሆን ነው፡፡ ማለትም አንድ ጂሃዳዊ ክርስቲያኑን ሲገድል የገደለውን ሰው ንብረት፣ ሚስትና ልጅ የራሱ የማድረግ ዕድል ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን ካልገደለው ይህንን ጥቅም በማጣት “ተጎጂ” ስለሚሆን የጉዳት ካሳ ሊከፈለው ይገባል ማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል ጂዝያ የሚከፈለው ሙስሊሞች ከገዛ ራሳቸው ዚሚውን እንዲጠብቁት ነው፡፡[2] የሚከተለው የቁርአን ጥቅስ ስለ ጂዝያ ክፍያ የሚናገር ነው፡-

“ከእነዚያ መጽሐፍን ከተሰጡት ሰዎች [አይሁድና ክርስቲያኖችን ለማመልከት ነው] እነዚያን በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑትን፣ አላህና መልክተኛው እርም ያደረጉትንም እርም የማያደርጉትንና እውነተኛውንም ሃይማኖት የማይቀበሉትን እነርሱ የተዋረዱ ኾነው ግብርን በእጆቻቸው እስከሚሰጡ ድረስ ተዋጉዋቸው፡፡” (የንስሐ ምዕራፍ 9፡29)

መሐመድ ዚሚዎች እንዳይገደሉ አጥብቀው ከልክለዋል፡፡ ምክንያቱን ሲናገሩ ደግሞ የሙስሊሞች የገቢ ምንጭ ስለሆኑ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡[3]

በሸሪኣ ሕግ መሠረት ሴቶች፣ ድኾች፣ ህሙማንና አቅመ ደካሞች ጂዝያን እንደማይከፍሉ ቢነገርም ነገር ግን ከአርመንያ፣ ከሦርያ፣ ከሰርብያና ከአይሁድ የተገኙ ምንጮች እንደሚመሰክሩት ህፃናት፣ መበለቶች፣ ወላጅ አልባዎችና ሙታን እንኳ ሳይቀሩ ጂዝያ መክፈል ይጠበቅባቸው ነበር፡፡[4] የዚሚ ማሕበረሰቦች ከጂዝያ በተጨማሪ የሚከፍሏቸው ብዙ የግብር ዓይነቶች ነበሩ፡፡ ሙስሊሞች ለንግድ ወይም ለመጓጓዣ የሚከፍሏቸው ሌሎች ቀረጦች በሙሉ ዚሚዎች በእጥፍ እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡ በጦርነት ምክንያት የሚወጡትን ወጪዎች ለማካካስ ሙስሊም ገዢዎች የዚሚ ማሕበረሰቦች የሚበዘበዙባቸውን ስልቶች ይነድፉ ነበር፡፡ ሙስሊም ሽፍቶችና አማፅያን ደግሞ ግለሰቦችን አፍኖ በመውሰድ ወጆ (የማስለቀቂያ ክፍያ) እንዲከፈል ያስገድዱ ነበር፡፡ ብዝበዛውን መቋቋም ካለመቻላቸው የተነሳ ብዙ ክርስቲያኖች ልጆቻቸውን ለባርነት እስከመሸጥ ደርሰዋል፡፡[5]

የዚማ ቃል ኪዳን እጅግ አዋራጅና ዘግናኝ ገፅታዎች አሉት፡-

የጂዝያ አከፋፈል ሥርዓት

  • ግብር በሚከፈልበት ቀን በቆሻሻ በተሞላ ዝቅተኛ ቦታ እንዲቆሙ ይደረጋል፡፡
  • ዚሚው የመጓጓዣ እንስሳትን በመጠቀም ሳይሆን በእግሩ እየሄደ ወደ ቦታው መምጣት አለበት – አንዳንድ ምንጮች በእጁና በጉልበቱ እየዳኸ መምጣት እንዳለበት ይናገራሉ፡፡
  • ተቀባዩ በመቀመጥ እርሱ ግን በመቆም ክፍያውን መፈፀም ይኖርበታል፤ – ተቀባዩ ከእርሱ በላይ ከፍ ብሎ ይቀመጣል፡፡
  • ዚሚው ወዲያና ወዲህ ክፉኛ ይገፈታተራል፤ እንዲፈራና እንዲርበተበትም ይደረጋል፤ ይዋረዳል፡፡
  • ግብር ተቀባዩ በእጁ ላይ ጅራፍ ይይዛል፡፡
  • ዚሚው ለምን እዛ እንደተገኘ የሚያውቅ ቢሆንም እንዲከፍል ቀጭን ትዕዛዝ ይሰጠዋል፡፡
  • ድብደባ ይፈፀምበታል፡፡
  • ሊገደል እየተወሰደ እንዳለ ምርኮኛ ልብሱን በመያዝ ወይም አንገቱ ላይ ገመድ ታስሮ በመጎተት ጎሮሮው ታንቆ ወደ ፊት እንዲደፋ ይደረጋል፡፡
  • ልክ እንደሚሰየፍ ሰው ወይም እንደሚታረድ ሰው ማጅራቱ ላይ ወይም ደግሞ ጎሮሮው ላይ ይመታል (በሰይፍ የእርድ ምልክት ይደረጋል)፡፡
  • ፀጉሩን ከግንባሩ አካባቢ እንዲቆርጥ ይታዘዛል፡፡ ይህም የሚደረገው አንገቱን ከመቆረጥ መትረፉን እንዲያስታውስ ነው፡፡
  • ሌላው አንገትን የመቆረጥ ምልክት የብረት ማነቆ በአንገት ላይ ማጥለቅ ነው፡፡
  • እንደሚሰየፍ ሰው ጢሙ ተይዞ ይጎተታል፡፡
  • ራሱ ላይ ቆሻሻ ይጣልበታል፡፡
  • ሙስሊሙ ሰው የዚሚው አንገት ላይ ይቆማል፡፡
  • ክፍያውን ከፈፀመ በኋላ ከሰይፍ ማምለጡን ለማመልከት ወደ ጎን ተገፍትሮ እንዲያልፍ ይደረጋል፡፡
  • የከፈሉበትን ደረሰኝ ይዘው የማይንቀሳቀሱ ወይም የጣሉ ዚሚዎች ሕይወታቸውን ለከፍተኛ አደጋ ያጋልጣሉ፡፡

የዚሚ ግዴታዎች

  • በእስልምና ስር ባለ ግዛት ውስጥ ወደ ክርስትና ወይም ወደ ይሁዲ የሚቀየር ሙስሊም ይገደላል፡፡ ሰዎች እምነታቸውን ይዘው እንዲቆዩ ተፈቅዷል ነገር ግን ወደ እስልምና ካልሆነ በስተቀር ወደ ሌላ እምነት መቀየር ክልክል ነው፡፡
  • አንድን ሙስሊም እምነቱን እንዲቀይር ለማድረግ መሞከር በሞት ሊያስቀጣ የሚችልና የተከለከለ ተግባር ነው፡፡
  • አንድ ዚሚ እስልምናን እንዳይቀበል እንቅፋት መሆን የተከለከለ ነው፡፡
  • አንድ ሙስሊም ወንድ ክርስቲያን ወይም አይሁዳዊት ሴት ማግባት ይችላል ነገር ግን ልጆቻቸው በሸሪኣ ሕግ መሠረት ሙስሊሞች ናቸው፡፡ ያ ቤተሰብ የሙስሊም ቤተሰብ ነው፡፡ ዚሚ ከሙስሊም ሴት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ይህንን ተግባር መፈፀም እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት ያስከትላል፡፡
  • ወደ እስልምና የሚቀየር ማንኛውም ሰው በቤተሰቡ ውስጥ ልዩ የውርስ መብት ይኖረዋል – የሚሰልም ወይም የምትሰልም የትዳር አጋር በፍቺ ወቅት ልጆችን የማሳደግ ልዩ መብት ታገኛለች ወይም ያገኛል፡፡
  • ከወረራ በኋላ አዲስ አብያተ ክርስቲያናትን መገንባት የተከለከለ ነው፡፡ ያረጁትንም ማደስ የተከለከለ ነው፡፡
  • ቅዱሳት መጻሕፍቶቻቸውን በማባዛት ማሰራጨት የተከለከለ ነው፡፡
  • የዚሚ ቤቶች ከሙስሊም ቤቶች ያነሱና ዝቅ ያሉ መሆን አለባቸው፡፡ ሲወጡና ሲገቡ እንዲያጎነብሱ የቤታቸው በር ጠባብና አጭር መሆን አለበት፡፡ በጥንቷ እስፔን ውስጥ የሚገኙ አይሁድ ይኖሩባቸው የነበሩ አጫጭር ቤቶች እስከ ዛሬ ድረስ ይታያሉ፡፡
  • ዚሚዎች በተለየ ሁኔታ መልበስና ከሙስሊሞች ያነሱ አልባሳትን መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ [6]
  • እስላማዊ ስሞችን መጠቀም ክልክል ነው፡፡ ይህም በቀላሉ ተጋላጭ እንዲሆኑ የታለመ ነው፡፡
  • ዚሚ የሚቀመጥበትን ቦታና የሚሄድበትን መንገድ ለሙስሊም ሰው የመልቀቅ ግዴታ አለበት፡፡
  • ዚሚ የትህትና አቋቋም ሊኖረው ይገባል፡፡
  • ዚሚ በሙስሊም ሰው ላይ እጁን ማንሳት (መምታት) በሞት ወይንም አካልን በመቆረጥ የሚያስቀጣ በጥብቅ የተከለከለ ድርጊት ነው፡፡ በምንም ምክንያት አንድን ሙስሊም መምታት የተከለከለ ነው፡፡
  • ሙስሊሞችን መስደብ የተከለከለና በሞት የሚያስቀጣ ነው፡፡
  • ዚሚ መሳርያ ሊኖረው ወይንም ሊይዝ አይችልም፡፡ ክርስቲያኖችና አይሁድ ራሳቸውን የሚከላከሉበት ምንም መንገድ መኖር የለበትም ማለት ነው፡፡ (ዛሬ እንኳ በአንዳንድ የሙስሊም አገራት የሚኖሩ ክርስቲያኖች መሳርያ መያዝ ስለማይፈቀድላቸው የቤተ ክርስቲያን ዘበኞች ሙስሊሞች ናቸው፡፡)
  • የሙስሊም ሰው ደም ከዚሚ ሰው ደም ጋር እኩል አይደለም፡፡[7] ለምሳሌ ያህል አንድን ሙስሊም መግደል በሞት የሚያስቀጣ ቢሆንም የሸሪኣ ሕግ እንደሚናገረው ሙስሊም ያልሆነን ሰው በመግደሉ ምክንያት ማንም ሙስሊም በሞት መቀጣት የለበትም፡፡
  • ዚሚ ሌላውን ዚሚ ከገደለ በኋላ ቢሰልም ከቅጣት ሊያመልጥ ይችላል፤ ወደ እስልምና የሚቀየር ማንኛውም ሰው ከሚጠብቀው የሞት ቅጣት ያመልጣል፡፡
  • ክርስቲያኖችና አይሁድ ሕዝባዊ ሥልጣን ሊኖራቸው አይችልም፤ ወይንም በሥልጣን ከሙስሊሞች በላይ እንዲሆኑ አይፈቀድላቸውም፡፡
  • ሙስሊም ባርያ ሊኖራቸው አይችልም ወይም ከሙስሊም ባርያን መግዛት አይችሉም፡፡
  • በእስላማዊ ሸሪኣ ፍርድ ቤት ዚሚ በሙስሊም ላይ የሚሰጠው ምስክርነት ተቀባይነት የለውም፡፡
  • አንድ ሙስሊም ከፍተኛ ቅጣት በሚያስከትል ክስ አንድን ክርስቲያን ቢከስ የክርስቲያኑ ምስክርነት ራሱን ለመከላከል የሚበቃና ተቀባይነት ያለው አይደለም፡፡ አንድ ሙስሊም ወንድ ክርስቲያን ሴት ቢደፍር ቃሏ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
  • ዚሚዎች ሙስሊም ወታደሮችን የማስጠለልና የመመገብ ግዴታ አለባቸው፡፡ በስምምነቱ መሠረት ጂሃድን ሊደግፉ ይገባል፡፡
  • ዚሚዎች ከሙስሊም ጠላቶች ጋር መወዳጀት፣ እነርሱን መርዳትም ሆነ ከእነርሱ እርዳታን መቀበል የተከለከለ ነው፡፡
  • ዚሚዎች በእስልምና ቁጥጥር ስር ካለ አካባቢ ለቆ መሄድ የተከለከለ ነው፡፡
  • ዚሚዎች በአደባባይ እምነታቸውን በምንም ዓይነት መንገድ እንዲያንፀባርቁ አይፈቀድም፡፡ መስቀል ማሳየት አይችሉም፡፡ በሃይማኖታቸው መሠረት የቀብር ስርኣት መፈፀም አይችሉም፡፡ ደወል ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው መዘመርም ሆነ ማስተማር አይችሉም፡፡[8]
  • ዚሚዎች ልጆቻቸውን ስለ እስልምና ከማስተማር ተከልክለዋል፡፡ በሥርኣቱ ስር ተጨቁኖ መሠቃየት እንጂ የሥርኣቱን ምንነት ማወቅ የተከለከለ ነው፡፡
  • እስልምናን፣ መሐመድንና የዚማን ሥርኣት መተቸት በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡
  • ዚሚዎች ፈረስ እንዳይቀመጡ ተከልክለዋል ምክንያቱም በደረጃ ከሙስሊሞች በላይ ከፍ ያደርጋቸዋልና፡፡
  • አህያ እንዲቀመጡ የሚፈቀድላቸው ሲሆን እግራቸውን በማንፈራጠጥ እንስሳው ላይ መቀመጥ አይችሉም፡፡ ሁለቱም እግሮቻቸው ወደ አንድ አቅጣጫ ዞረው በጎን መቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡
  • በብዙ ቦታዎች ዚሚዎች ከሌላው እንዲለዩ በልብሳቸው ላይ የተለየ የቀለም ምልክት እንዲኖራቸው ይጠበቅባቸው ነበር፡፡
  • በብዙ ቦታዎች አንድ ዓይነት ጫማ እንዲጫሙ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡
  • በሕዝባዊ መታጠብያ ቦታዎች ከሙስሊም ተለይተው እንዲታወቁ የአንገት ማነቆዎችን ወይም ቃጭሎችን እንዲያጠልቁ ይገደዱ ነበር፡፡
  • በተለያዩ አካባቢዎች የዚሚን ማሕበረሰቦች የሚያዋርዱ የተለያዩ ተግባራት ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል የሞሮኮ አይሁድ የቆሻሻ መጣያዎችን እንዲያፀዱ፣ የሞቱ እንስሳትን እንዲያነሱና የሞት ፍርድ በተፈፀመባቸው ወንጀለኞች ጭንቅላት ላይ ጨው እንዲነሰንሱ ይገደዱ ነበር፡፡
  • ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች ርኩሶች እንደሆኑ ከሚናገረው የቁርአን ቃል በመነሳት (9፡28) በ19ው ክፍለ ዘመን በሐመዳን (ኢራን አገር) ይኖሩ የነበሩ አይሁድ በበረዶና በዝናባማ ቀን ከቤት እንዳይወጡ ይከለከሉ ነበር፡፡ ይህም የተደረገበት ምክንያት ሰውነታቸውን የነካ እርጥበት ኋላ ላይ የሙስሊሞችን እግር በመንካት እንዳያረክሳቸው በሚል ነበር፡፡

በዚህ ኢ-ሰብዓዊ ሕግ መሠረት ከዚሚ ማህበረሰብ መካከል አንድ ሰው የገባውን ቃል ኪዳን በማፍረስ አንዱን ሕግ እንኳ ተላልፎ ቢገኝ ሙስሊሞች መላውን የዚሚ ማሕበረሰብ የመቅጣትና የመግደል መብት አላቸው፡፡ በእስላማዊ አነጋገር ደማቸው ሐላል (የተፈቀደ) ይሆናል ማለት ነው፡፡ ግብሩ እጅግ አስጨናቂ ከመሆኑ የተነሳ አእምሯቸውን የሳቱ፣ መድረሻቸውን ሳያውቁ ጠፍተው በመንከራተት የሞቱ ብዙ ክርስቲያኖችና አይሁድ መኖራቸውን ታሪክ ዘግቧል፡፡[9]

የ18ው ክፍለ ዘመን ሞሮኮዋዊ ሐታች የነበረው ኢብን አጂባህ ሱራ 9፡29 ላይ አስተያየት ሲሰጥ እንዲህ አለ፡-

“ዚሚው ነፍሱን፣ መሻቱንና መልካም ዕድሎቹን ሁሉ በገዛ ፈቃዱ እንዲገድል ይታዘዛል፡፡  ከሁሉም በላይ ለሕይወት፣ ለሥልጣንና ለክብር ያለውን ፍቅር መግደል ይኖርበታል፡፡ ዚሚው የነፍሱን ጥማት መለወጥ አለበት፤ ሙሉ በሙሉ እስኪገዛ ድረስ ነፍሱን መሸከም ከምትችለው በላይ ማስጨነቅ አለበት፡፡ ከዚያ በኋላ መሸከም የማይችለው ነገር አይኖርም፡፡ ለጭቆናና ለኃይል ጥቃት ግዴለሽ ይሆናል፡፡ ድህነት እና ኃብት ለእርሱ አንድ ይሆናሉ፤ ሙገሳና ንቀት አንድ ይሆኑበታል፤ መከልከልና መስጠት አንድ ይሆኑበታል፤ ማግኘትና ማጣት አንድ ይሆኑበታል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ነገር አንድ ሲሆንበት ፍፁም በሆነ መገዛት ከእርሱ የሚፈለገውን ነገር ማቅረብ ይችላል፡፡”[10]

ኢብን ከሢር በመጽሐፉ ውስጥ እንዲህ በማለት አስፍሯል፡-

“አላህ በቁርአኑ ‹የተዋረዱ ሆነው ጂዝያን እስኪከፍሉ ድረስ ተጋደሏቸው› ብሏል፡፡ ሙስሊሞች የዚማን ሕዝቦች ማክበር ወይንም ከሙስሊሞች በላይ ከፍ ማድረግ አልተፈቀደላቸውም፤ ምክንያቱም እነርሱ ዕድለ ቢሶች፣ ቆሌያቸው የተገፈፈና ወራዶች ናቸውና፡፡ ሙስሊም የተሰኘው ዘጋቢ ከአቡ ሁራይራ ሰምቶ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- ‹አይሁድን ወይንም ክርስቲያኖችን ሰላም አትበሏቸው፤ ማናቸውንም በመንገድ ላይ ብታገኙ ወደ ጠባቡ የመንገዱ ጠርዝ ግፏቸው፡፡› ለዚህ ነው የታማኞች መሪ የነበረው ኡመር አል ከታብ (አላህ ይውደደውና) ሁላችንም የምናውቃቸውን ቅድመ ሁኔታዎቹን ክርስቲያኖች እንዲቀበሉ የጠየቀው፡፡ እነዚህም ቅድመ ሁኔታዎች ውርደታቸው፣ ቅለታቸውና እፍረታቸው ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥ ለማድረግ የታለሙ ናቸው፡፡” [11]

ይህ አስጨናቂ ሕግ አውሮፓውያን የሙስሊም አገራትን በቅኝ ገዢነት እስከያዙበት ዘመን ድረስ ቀጥሎ ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን በብዙ ሙስሊም አገራት ውስጥ በተወሰነ መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ሦርያ፣ ግብፅ ኢራንና ኢራቅን በመሳሰሉት የአረብ አገራት ውስጥ እየኖሩ የሚገኙት ክርስቲያኖችና አይሁድ እነዚህን ኢ-ሰብዓዊ ሕግጋት ተቋቁመው ያለፉ ናቸው፡፡

——————–

[1] Mark Durie. The Third Choice: Islam, Dhimmitude and Freedom; 2010, pp. 122-123

[2] Ibid., pp. 122-125

[3] Sahih al-Bukhari. The Book of al-Jizya the Stoppage of War. Vol. 4, Book 58,  No. 3166

[4] Bat Ye’or. Islam and Dhimmitude: Where Civilization Collide; 2002, p. 69

[5] Ibid., p. 71

[6] ቃዲ አሕመድ ቢን ጣሊብ (ዘጠነኛው ዓ.ም.) በአንደሉሽያ (እስፔን) አይሁዶች በትከሻው ላይ የዝንጀሮ ምልክት ያለበትና ክርስቲያኖች ደግሞ የአሳማ ምልክት ያለበትን ነጭ ልብስ እንዲለብሱ፤ እንዲሁም በበራቸው ላይ የዝንጀሮ ምልክት ያለውን ሰሌዳ እንዲለጥፉ የሚያስገድድ ትዕዛዝ ወጥቶ እንደነበር ጽፏል፡፡ Bat Ye’or. The decline of Eastern Christianity Under Islam: from Jihad to Dhimmitude; p. 340

[7] ሳዑዲ አረብያ የሁሉንም ዓይነት ሰው ዘር ደም ዋጋ የሚያሳይ ዝርዝር አላት፤ ሙስሊም ወንድ ከሁሉ የላቀ ዋጋ አለው፣ ከዚያ ሙስሊም ሴት፣ ክርስቲያን ወንድ፣ ክርስቲያን ሴት፣ አይሁድ ወንድ፣ አይሁድ ሴት፣ ሒንዱ ወንድ፣ ሒንዱ ሴት እያለ የደረጃ ምድብ ዝርዝሩ ይቀጥላል፡፡ https://en.wikipedia.net/wiki/Diyya

[8] ለዚህ ነው በ19ው ክፍለ ዘመን ተነሱትን የኢየሩሳሌምን ፎቶግራፎች ስንመለከት በአንድም ቤተ ክርስቲያን ላይ የመስቀል ምልክት ማግኘት የማይቻለው፡፡

[9] እነዚህ መረጃዎች የተወሰዱት፡- Mark Durie. The Third Choice: Islam, Dhimmitude and Freedom; pp. 131-153 እንዲሁም Bat Ye’or. Islam and Dhimmitue: Where Civilization Collide; 2002, pp. 50-110 ላይ ነው፡፡ በተጨማሪም በባት ዬኦር የተመሠረተውን www.dhimmitude.net በመጎብኘት መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል፡፡

[10] Durie. The Third Choic; p. 140-141

[11] Tafsir Ibn Kathir, vol. 4:406-7; Quoted in፡- Durie. The Third Choic; p. 142

እስልምናና ሽብርተኝነት