ሊቃውንተ ሽብር
የእስላማዊ ሽብርተኝነትን አስተሳሰብ ከዋናዎቹ ምንጮች በመቅዳት ያስተማሩና የተገበሩ፣ ትምህርቱንም ስልታዊ ይዘት ባለው መልኩ ያዋቀሩ ሊቃውንተ ሽብር ይገኛሉ፡፡ በዋናነት የሚጠቀሱት አራት ሲሆኑ የመጀመርያው በመካከለኛው ዘመን የኖረ፣ ሁለተኛው በአሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን የኖረና የተቀሩት ሁለቱ ደግሞ በሃያኛው ክፍለ ዘመን የኖሩ ናቸው፡፡
ኢብን ተይሚያ – “የወሃቢዝም አያት”
ሐራን በተባለችው የቱርክ ከተማ በ1263 ዓ.ም. የተወለደው ኢብን ተይሚያ ሞንጎሊያኖች በሦርያ ላይ ጥቃት በፈፀሙበት ዘመን (1299-1303) ተዋግቶ ነበር፡፡ የሞንጎሊያ ሙስሊሞች እውነተኛ ሙስሊሞች እንዳልሆኑና ማንም ከእነርሱ ጋር እንዳይተባበር እንዲሁም ለእነርሱ እንዳይገዛ አስተምሮ ነበር፡፡ ለነርሱ የተገዛ፣ እነርሱን የረዳ ወይንም ደግሞ ከነርሱ ጋር የተደራደረ ሰው ልክ እንደነርሱ ከሃዲ እንደሆነም በማወጅ ሙስሊሞችን በጎራ ከፍሏል፡፡ ይህ አቋሙ ተከታዮቹ ሙስሊም ያልሆኑትን ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ሙስሊሞች እንዳልሆኑ በሚያምኗቸው ሰዎች ሁሉ ላይ ጦርነትን እንዲያውጁ መንገድ ከፍቷል፡፡ ብዙ ሙስሊም ሊቃውንትን በመተቸት ጽሑፎችን የጻፈ ሲሆን ቁርኣንና ሐዲሳት በቀጥታ መተርጎም አለባቸው የሚል አቋም ነበረው፡፡ ሙስሊሞች የነቢዩን አጋሮች (የሰሃባዎችን ወይም ሰለፎችን) መንገድ እንዲከተሉና “ቅዱሳን” የተባሉ ሰዎችን መቃብሮች ከመጎብኘት እንዲታቀቡ በብርቱ አስተምሯል፡፡ ኢብን ከሢርና ኢብን ቀይም የኢብን ተይሚያ አስተምህሮ ተፅዕኖ ካሳደረባቸው ሙስሊም ሊቃውንት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡[1] የዚህ ሰው ጽሑፎችና ትምህርቶች በአብደል ወሃብ ላይ ተፅዕኖ በማሳደር ለዛሬው የወሃቢዝም ፍልስፍና ዋና ምንጭ በመሆናቸው ምክንያት “የወሃቢዝም አያት” ብለነዋል፡፡
ኢብን አብደል ወሃብ – “የወሃቢዝም አባት”
የሳዑዲ አረብያ ተወላጅ የነበረው አብደል ወሃብ (1703-1791) የወሃቢዝም (ሰለፊ) እንቅስቃሴ መስራችና ዋና ፈላስፋ ነበር፡፡ ቁልፍ አስተምህሮዎቹ “ኪታብ አል-ተውሂድ” (የአሃዳዊነት መጽሐፍ) በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ ሰፍረዋል፡፡ እንደ ኢብን ተይሚያ ሁሉ የቅዱሳን ሰዎችን መቃብሮች መጎብኘትን በጥብቅ የተቃወመ ሲሆን የቁርኣንና የሐዲስ ጽሑፎች በቀጥታ መተርጎም እንዳለባቸው ያምናል፡፡ የሸሪኣ ሕግም በጥብቅ ተፈፃሚ መሆን እንዳለበት አስተምሯል፤ ተግባራዊም አድርጓል፡፡ አብደል ወሃብ ፍልስፍናው ፖለቲካዊ ድጋፍ ከሌለው በስተቀር ዘለቄታነት እንደማይኖረው ስለተረዳ በዘመኑ ከነበሩት የሳዑዲ ገዢዎች ጋር ስምምነት በመፍጠር ትምህርቱን አስፋፍቷል፡፡ አመለካከቱንም በንጉሣዊ ቤተሰቦች ዘንድ በማስረፅ ህልውናው የተረጋገጠ እንዲሆን አድርጓል፡፡ አብደል ወሃብ የእርሱን የእስልምና ትርጓሜ የማይቀበሉ ሰዎችን ሁሉ በከሃዲነት ይፈርጃል፡፡ የእርሱ አመለካከት ዛሬ የሳዑዲ አረብያ ኦፊሴላዊ የእስልምና ቅጂ ሲሆን ወራሾቹ የሆኑት “የሼኹ ቤተሰብ” ከንጉሣዊ ቤተሰብ ጋር በመጋባት በሳዑዲ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ሰው መርዛማ አስተምህሮ ተፅዕኖ ካደረባቸው ሰዎች መካከል ኦሳማ ቢንላደን ይጠቀሳል፡፡ የአልቃኢዳና የአይኤስ አባላት የዚህ ፍልስፍና ተከታዮች ሲሆኑ በዓለም ላይ የሚገኙትን አብዛኞቹን አሸባሪዎች እየፈለፈለ የሚያወጣውም ይኸው የወሃቢዝም ፍልስፍና ነው፡፡[2] ይህ እኩይ አስተምህሮ ወደ አገራችንም በመግባት ተቻችሎ የመኖር ባሕላችንን መናድ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡
ሰይድ ቁጥብ – “የሽብርተኝነት መሐንዲስ”
ሰይድ ቁጥብ (1906-1966) ቀለም ገብ የሚባል ዓይነት ሰው ነበር፡፡ የ24 ማጻሕፍት ደራሲ ሲሆን “ማሊም ፊ አል-ጠሪቅ” (የምልክት ድንጋዮች) በሚል ርዕስ የጻፈው መጽሐፉ ከሁሉም በላይ ዝነኛ አድርጎታል፡፡ ይህም መጽሐፍ ከዚያ ወዲህ በዓለም ላይ ለተነሱት እስላማዊ የሽብር ቡድኖች ሁሉ እንደ ዋና መመርያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ በ1948 ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በመሄድ የትምህርት ሥርኣት ቀረፃ ትምህርቱን ባጠናበት ወቅት የታዘባቸውን ነገሮች “እኔ ያየኋት አሜሪካ” በሚለው መጽሐፉ ውስጥ ያሰፈረ ሲሆን በአሜሪካውያን የቴክኖሎጂ ምጥቀት መደመም ውስጥ መግባቱን ሳይሸሽግ “ቁሳዊነት የሚያጠቃውን” አመለካከታቸውንና “ምግባረ ብልሹ” የሆነውን የኑሮ ዘይቤያቸውን እንደተፀየፈ ተናግሯል፡፡ ዛሬ በብዙ ሙስሊሞች ዘንድ ለሰረፀው አሜሪካን እንደ ክፋት ሁሉ ምንጭ የመቁጠርና የመጥላት አመለካከት መሠረት የጣለው ሰይድ ቁጥብ ነው፡፡ ይህ ሰው ከእስልምና ውጪ የሚገኙትን ንፅረተ ዓለማት ሁሉ “ጀህሊያ” (ድንቁርና) በማለት ያብጠለጥላል፣ ይዘልፋል፣ ይኮንናል፤ በኃይል መወገድ እንዳለባቸውም ይናገራል፡፡ ሙሐመድና ተከታዮቻቸው መካን በመልቀቅ ወደ መዲና እንደተሰደዱት ሁሉ እውነተኛ ሙስሊሞችም “ጀህሊያን” ለቀው በመውጣት ራሳቸውን በመነጠል እንዲደራጁ አስተምሯል፡፡ ይህ አመለካከቱ ለብዙ ሽብርተኞች በቡድን መደራጀት ምክንያት ሆኗል፡፡ “ማሊም ፊ አል-ጠሪቅ” የሚለው መጽሐፉ ከታተመ በኋላ የዚህን ሰው መርዛማ አመለካከቶች አደገኛነት የተገነዘበው የግብፅ መንግሥት ነሐሴ 29/ 1966 ዓ.ም. በስቅላት እንዲቀጣ አድርጎታል፡፡ መጽሐፍቱንም አግዷቸዋል፡፡[3] ነገር ግን የግብፅ መንግሥት የወሰደው እርምጃ “ጅብ ከሄደ …” ዓይነት ስለነበር ምንም ሊፈይድ አልቻለም፡፡ መርዛማ ትምህርቶቹ በብዙ ተከታዮቹ ዘንድ ከሰረፁ በኋላ የተወሰደው እርምጃ እንዲያውም ጂሃዳውያን ቁጥብን እንደ ጀግናና እንደ ሰማዕት በመቁጠር መርሆቹን አጥብቀው እንዲይዙና መጻሕፍቱም በብዙ ወጣቶች ዘንድ የመነበብ ጉጉት እንዲፈጥሩ ከማድረግ የዘለለ ውጤት አልነበረውም፡፡ የሞት ብያኔው ከተላለፈበት በኋላ “አልሀም ዱሊላህ፤ ይህንን የሰማዕትነት ዕድል እስካገኝ ድረስ ለአሥራ አምስት ዓመታት ጂሃድ አድርጌያለሁ…” ብሎ መናገሩ የጀግና አሟሟት መሞቱን ለማመልከ በተከታዮቹ ዘንድ ይጠቀሳል፡፡[4]
አብዱላህ አዛም – “የዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት አባት”
አብዱላህ ዩሱፍ አዛም በምድረ ፍልስጥኤም የተወለደ ሲሆን የሙስሊም ወንድማማቾች ሕብረት መሥራች የሆነው የሐሰን አልባናን እንዲሁም የሰይድ ቁጥብን ሥራዎች በጥልቀት ያጠና ሰው ነበር፡፡ እስላማዊ ትምህርቶችን በሦርያና በግብፅ ውስጥ ካጠና በኋላ በሳዑዲ አረብያና በፓኪስታን ውስጥ በማስተማር አገልግሏል፡፡ በዘመኑ የነበሩትን የእስላማዊ ንቅናቄ መሪዎች ጽሑፎች በጥልቀት በማጥናት ሐሳቦቻቸውን መልክ አስይዞ ለተግባራዊ እርምጃ በሚረዳ መልኩ ወጥ የሆነ አስተምህሮ በማዋቀር በ1984 በአንድ ጥራዝ አሳትሞ ነበር፡፡ “የሙስሊም ይዞታዎችን መጠበቅ” የሚል ርዕስ ያለው ይህ መጽሐፉ ለዓለም አቀፋዊው ጂሃድ መሠረታውያን የሆኑ ተከታዮቹን ነጥቦች አካቷል፡-
- ሙስሊሞች በቅኝ ገዢዎችና ፍትሃዊ ባልሆኑ ሥርዓቶች ተዋርደዋል፡፡
- ሙስሊሞች ጂሃድን እንደ ግል ግዴታ ካልተቀበሉት እስልምና የመጨረሻው ሽንፈት ይደርስበታል፡፡
- እስልምና ከውድቀት መትረፍ የሚችለው ለአላህ ክብር ካሊፌት ሲቋቋም ብቻ ነው፡፡
አዛም በጂሃድ ራስን መሰዋትን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፡-
“ታሪክ መስመሮቹን የሚያሰምረው በደም ብቻ ነው፡፡ ክብር ማማዎቹን ሊገነባ የሚችለው በሰዎች የራስ ቅል ብቻ ነው፡፡ ሞገስና ክብር መሠረታቸውን የሚገነቡት በተቆራረጡ አካላትና በሬሳዎች ላይ ብቻ ነው፡፡”[5]
በአዛም እምነት መሠረት ለአንድ ሙስሊም ዓለም አቀፋዊውን ካሊፌት መልሶ ለማቆም ሲጋደል ከመሞት የበለጠ ክብር ሊኖር አይችልም፡፡
አብዱላህ አዛም በሙስሊሙ ዓለም ውስጥ እጅግ የተከበረ የቁርኣን ሊቅ በመሆኑ ምክንያት እርሱ ያወጣቸው ፈትዋዎች (ሃይማኖታዊ ድንጋጌዎች) በብዙ ሙስሊም ሊቃውንት ዘንድ ዕውቅና ተቸሯቸዋል፡፡ የሶቪዬት ሕብረት አፍጋኒስታንን በወረረበት ወቅት የነበረውን የሙጃሂዲኖች ንቅናቄ ወደ ዓለም አቀፋዊ ጂሃድ የለወጠው ይህ ሰው ነበር፡፡ ከበርቴ ከነበረው አባቱ ብዙ ሚሊዮን ዶላሮችን በውርስ አግኝቶ የነበረው ኦሳማ ቢንላደን በ1980ዎቹ መጀመርያ አካባቢ ብዙ ሺህ ወጣቶችን በመመልመል በፓኪስታን በኩል ወደ አፍጋኒስታን በማስረግና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ቁርአናዊ ተልዕኮውን ይወጣ በነበረበት ጊዜ ከአዛም ጋር ተወዳጅቶ ነበር፡፡ የሶቪዬት ጦር አፍጋኒስታንን ለቆ ከወጣ ከአንድ ዓመት በኋላ አብዱላህ አዛም በፓኪስታን ውስጥ ሲገደል በእርሱ የተመሠረተውን፣ ሃምሳ አምስት ሺህ የውጪ ሙጃሂድኖችን መልምሎ የነበረውን የጂሃድ ተቋም ለመምራት በወቅቱ ከቢንላደን የተሻለ ሰው አልነበረም፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይህ ተቋም አልቃኢዳ የሚል ስም በማግኘት ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮን አንግቦ እንደ አዲስ ተደራጅቷል፡፡[6]
ከላይ የተጠቀሱት አራት ሰዎች በዚህ ዘመን ለሚገኘው የጂሃድ-ወሽብር አስተሳሰብ መሠረት የጣሉ ሰዎች በመሆናቸው ምክንያት ትኩረት ሰጠናቸው እንጂ በአደገኛ ትምህርቶቻቸው የሚታወቁ እስላማውያን ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ በተለይ የአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ ውጤቶች የሆኑት ከምድረ ግብፅ የፈለቁት ጂሃዳውያን የሽብር ስልቶችን በመንደፍ ረገድ ወደር አይገኝላቸውም፡፡ የሙስሊም ወንድማማቾች መስራች የነበረው ሐሰን አል-ባና፣ የሂዝቡ አል-ታህሪር (እስላማዊ የአርነት ንቅናቄ) መስራች የነበረው ሳላህ ሴሬያ፣ የአል-ተክፊር ወል-ሂጅራ መስራች የነበረው ሹክሪ ሙስጠፋ፣ የተብሊሒ ጀመዓት መስራች የነበረው ሙሐመድ ኢልያስ አል-ካንዝላዊ፣ የአል ጂሃድና የሌሎች ሽብርተኛ ቡድኖች መንፈሳዊ መሪ የነበረውና ፕሬዚዳንት ሳዳትን ያስገደለው አሁን በአሜሪካ እስር ቤት ውስጥ የዕድሜ ልክ እስር ላይ የሚገኘው “ዓይነ ስውሩ ሼኽ” ኦማር አብደልረህማን፣ የቢን ላደን ቀኝ እጅ የነበረውና የአልቃኢዳን የመሪነት ቦታ የተረከበው አይማን አል-ዘዋሕሪ፣ የብዙ አደገኛ መጻሕፍት ደራሲ የሆነውና በመገናኛ ብዙሃን የሰላም ጭምብል በመልበስ የሚቀርበው በመጻሕፍቱ ግን የሽብርን መርዝ የሚያሰራጨው ዩሱፍ አል-ቀረዳዊ፣[7] ወዘተ. የመሳሰሉት ግለሰቦች በትምህርቶቻቸውና በጽሑፎቻቸው በሚሊዮኖች ደም የጨቀየውን፣ ሳይወድ በግድ የተዳፈነውን የሞት ማዕበል፣ የግፍ ረመጥ በመቆስቆስ የዘመናዊውን ጂሃድ ቋያ እሳት የለኮሱና እያነደዱ የሚገኙ በመሆናቸው ከአራቱ ግለሰቦች ያልተናነሰ ትኩረት ያሻቸዋል፡፡
———————-
[1] Mark Gabriel. Islam and Terrorism; p. 111
[2] Campo. Encyclopedia of Islam; pp. 324-325
[3] Mark Gabriel. Islam and Terrorism; pp.113-122
[4] Sayyid Qutb; Edited by A.B. al-Mehri. Ma’alim fi’l-tareeq (Mile Stones); 2006, p. III
[5] Sebastian Gorka. Defeating Jihad: the Winnable War; p. 88
[6] Ibid., pp. 86-94
[7] የዩሱፍ አል ቀረዳዊ ሥራዎች በብዛት ወደ አማርኛ ተተርጉመው በእስላማዊ የመጽሐፍት መሸጫ መደብሮች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የዚህ ሰው ትምህርት ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ለማወቅ “ጂሉ ነስር አል-መንሹድ” በሚል ርዕስ ተጽፎ “ድል አድራጊ መፃዒ የሙስሊም ትውልድ” ተብሎ ወደ አማርኛ የተመለሰውን መጽሐፍ ማንበብ በቂ ነው፡፡ መጽሐፉን ያነበበ ሁሉ አሁን እየታየ የሚገኘውን እንደ አሸን የፈላውን፣ በጥላቻ፣ በእብሪትና፣ በአጉል ሃይማኖታዊ ቅንኣት የተጀነነውን፣ በጂሃድ የሚያምነውን ትውልድ በግልፅ ማየት ይችላል፡፡ የዚህን ሰው መርዛማ መጻሕፍት በብዛት ወደ አማርኛ በመመለስ እያሰራጨ የሚገኘው እዚሁ በምድረ ሐበሻ እየኖረ የሚገኝ ግለሰብ ነው፡፡