ጂሃድ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ

ጂሃድ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ19ው ክፍለ ዘመን ወዲህ

የግራኝ ወረራ በወቅቱ ከፍተኛ ጉዳት ቢያደርስም ነገር ግን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሃይማኖት ስብጥር ላይ የነበረው ተፅዕኖ የተጠበቀውን ያህል አልነበረም፡፡ ከግራኝ ሽንፈት በኋላ ሙስሊም ሱልጣኔቶች የተደካሙና እንቅስቃሴያቸውም የተገደበ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ቀድሞ ይዞታዋ ተመልሳለች፡፡ ይህ በንዲህ እንዳለ ቱርክን የመሳሰሉት የውጪ ጂሃዳውያን ኢትዮጵያን በማስለም ረገድ የነበራቸው ተስፋ እንዳልተሟጠጠ ታይቷል፡፡ ቱርኮች ተሸንፈው ከአገር ከተባረሩ በኋላ በ1557 የምፅዋን ወደብ የተቆጣጠሩ ሲሆን እስከ ደብረ ዳሞ ገዳም ድረስ ዘልቀው በመምጣት በመነኮሳቱ ላይ ጭፍጨፋ እንደፈፀሙና ገዳሙንም እንዳረከሱ፤ የወቅቱ ባህረ ነጋሽ የነበረው ይስሐቅም ድል በመንሳት ከአካባቢው እንዳባረራቸው የታሪክ ድርሳናት ይዘክራሉ፡፡[1] ከግራኝ ሽንፈት በኋላ የክርስቲያኑን ምድር ከበው የነበሩት ሙስሊም ማሕበረሰቦች ተዳክመው የነበረ ሲሆን የሰሜኑ ግዛት በደቡብ በነበሩት ሕዝቦች እንቅስቃሴ ከመረበሽ በስተቀር የገጠመው ያን ያህል የጎላ ችግር አልነበረም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በአንድ አካባቢ ሕዝቦች ላይ ብቻ በማተኮር እንቅስቃሴዋ የተገደበ ባይሆን ኖሮ ዛሬ እስልምናን ተቀብለው የሚታዩትና ከሌሎች ጋር ተደባልቆ ለመኖር የማይቸገሩት ወርቃማ ባሕል ያላቸው የኦሮሞ ሕዝቦች ክርስትናን ይቀበሉ እንደነበር ትሪሚንግሃም የተሰኙት የታሪክ ሊቅ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡[2]

የግብፅ ወረራዎች

በአባይ ወንዝ ላይ ካላት ጥቅም የተነሳ ግብፅ ኢትዮጵያን የመቆጣጠርና የማስለም የረጅም ጊዜ ምኞት እንደ ነበራት ይታወቃል፡፡ በተለያዩ ዘመናት የተነሱት የግብፅ ገዢዎች ኢትዮጵያን በኃይል መቆጣጠር ቀላል እንዳማይሆንላቸው ይገባቸው ስለነበር የማስለም መርሃ ግብሩን በተለያዩ ዘዴዎች በመጠቀም ያስፈፅሙ እንደነበር ታሪክ ይናገራል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳትን ስታገኝ የነበረው በገዢዎቹ መልካም ፈቃድ ስለነበረ ከእነዚህ ጳጳሳት ጋር የተለያዩ ስምምነቶችን በማድረግ እስልምናን የማስፋፋት ሙከራዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ያህል አባ ሳዊሮስ የተሰኙ ጳጳስ (1080 ዓ.ም.) ገና ተሹመው ከመምጣታቸው ሰባት መስጊዶችን አስገንብተው የነበረ ሲሆን ይህ ድርጊታቸው የሕዝቡን ቁጣ በመቀስቀሱ ምክንያት ለእስር ተዳርገው መስጊዶቹም ፈርሰዋል፡፡[3] ነገር ግን ከግብፅ የሚመጡት ጳጳሳት እንዲህ ያለውን ድርጊት የሚፈፅሙት ወደው ሳይሆን ሙስሊም ገዢዎች በግብፅ ያለውን ሕዝበ ክርስቲያን እንደ መያዣ በመጠቀም ስለሚያስገድዷቸው ነበር፡፡ የግብፅ ሙስሊሞችም ክርስቲያን በመምሰል ወደ አገር ውስጥ የገቡባቸውና በቤተ ክርስቲያን ላይ ጉዳት ያደረሱባቸው ጊዜያትም ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ያህል አብዱን የተሰኘ ሙስሊም፣ ክርስቶዱሎስ (1047-78 ዓ.ም.) በተሰኙት ጳጳስ ዘመን በሀሰተኛ ሰነዶች ተጠቅሞ በመግባትና ተቀባይነትን በማግኘት ለጳጳሱ አገልግሎት እንቅፋት ሆኖ እንደነበር በታሪክ ሰፍሯል፡፡[4]

በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ሙሐመድ አሊ የተባለ ሰው የግብፅን በትረ ሥልጣን በመጨበጥ ግዛቱን የናይል ተፋሰስ አገራት ውስጥ ለማስፋፋት እቅድ ይዞ ተነስቶ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ሱዳንን በመያዝ በ1830  ነጭ አባይና ጥቁር አባይ በሚገናኙበት ቦታ ላይ የካርቱም ከተማን ቆረቆረ፡፡ ልጁ ኢብራሂምንም “የሂጃዝና የአቢሲኒያ አስተዳዳሪ” በማለት ከሾመ በኋላ ኢትዮጵያን የመውረር እቅዱን ለአውሮፓውያን ሸሪኮቹ ግልፅ አደረገ፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በካይሮ የብሪቲሽ ቆንስላ ጄኔራል የነበረው ሳልት እቅዱን በመቃወም አውሮፓውያን ኃይላት ለዘመናት ክርስትናዋን ጠብቃ የቆየች ብቸኛዋ አፍሪቃዊት አገር እንድትወረር እንደማይፈቅዱ ገለፀለት፡፡[5] ነገር ግን አውሮፓውያን ጥቅማቸው እስካልተነካ ድረስ ለክርስትና ግድ እንደሌላቸው በኋለኞቹ ዘመናት ግልፅ ሆኗል፡፡


ከዲቭ ኢስማኤል (ኢስማኤል ፓሻ)

ሙሐመድ አሊ በሦርያ ያደረገው ወረራ ስላልተሳካለት ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በ1838 በሱዳን በኩል ቀለበት በተባለ የድንበር መግብያ ወራሪ ሠራዊቱ ወደ አገር ውስጥ እንዲዘልቅ አድርጓል፡፡ ወረራው በጎንደር ከተማ ውስጥ ከፍተኛ ሽብርን ያስከተለ ሲሆን ጂሃዳውያኑ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን የማርከስ አስነዋሪ ተግባራትን ፈፅመዋል፡፡ ይህ ደግሞ በሕዝቡና በመሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ በደጃች ክንፉ የተመራ ሠራዊት በወኔና በቁጭት ክፉኛ በመቅጣት አባሯቸዋል፡፡ ሙሐመድ አሊ ሽንፈቱን ለመበቀል ቢፈልግም ነገር ግን ፈረንሳይና ብሪቴን ጫና ስላሳደሩበት እቅዱን ሳይፈፅም ቀርቷል፡፡[6]

ግብፅ ኢትዮጵያን የመውረር እቅዷን እንደገና በኢስማኢል ፓሻ ዘመን ለመተግበር የተንቀሳቀሰች ቢሆንም ህዳር 16/ 1875 በምዕራባውያን ቅጥረኞች እየተመራ በምፅዋ በኩል የገባው የግብፅ የጂሃድ ሠራዊት ጉንደት በተባለ ቦታ ላይ የአፄ ዮሐንስን ሠራዊት በመግጠም ሙሉ በሙሉ ተደመስሷል፡፡ የመጀመርያውን ሽንፈት ለመቀልበስ ለሁለተኛ ጊዜ መጋቢት ወር ላይ ተመልሶ የመጣውም ወረሪ የጂሃድ ሠራዊት ጉራ በተባለ ቦታ ላይ ተደመስሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ግብፅ ጦር አዝምታ ኢትዮጵያን ለማስለም የነበራት ምኞት ሊከሽፍ ችሏል፡፡[7]

የሱዳን መሐዲስቶች ጥቃት

ግብፅ ሱዳንን በመያዟ ምክንያት የመሐዲ እንቅስቃሴ ሱዳን ላይ ተነስቶ ነበር፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ዋና አላማው በእንግሊዛውያን የምትደገፈውን ግብፅን ማሸነፍ ቢሆንም አፄ ዮሐንስ በመሐዲዎች የተከበበውን የግብፅ ሠራዊት በኢትዮጵያ ግዛት በኩል ለማስወጣት ያደረጉት ስምምነት መሐዲስቶች ትኩረታቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመልሱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በወቅቱ የጎጃም ንጉሥ የነበሩት ተክለሃይማኖት በጥር ወር 1887 የመሐዲስቶች ይዞታ በነበረችው የመተማ ከተማ ላይ ጥቃት ፈፅመው ነበር፡፡  በቀጣዩ ዓመት የመሐዲስቶች ሠራዊት እስከ ጎንደር ድረስ ዘልቆ በመግባት አብያተ ክርስቲያናትን አቃጥሏል፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን ጨፍጭፏል፣ ብዙዎችንም ማርኮ ለባርነት ወስዷል፡፡ በዚህም ምክንያት መጋቢት 9 እና 10 በመተማ ላይ በተደረገው ጦርነት አፄ ዮሐንስ ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን መሐዲስቶችም ራሳቸውን በመቁረጥ ወደ ሱዳን ወስደዋል፡፡ የመሐዲስቶቹ ትኩረት ዋና ጠላታቸው ወደሆነችው ወደ ግብፅ ስለተመለሰ ኢትዮጵያን ከመውረር ታቅበዋል፡፡[8] ግብፅና ሱዳን ሙሉ በሙሉ በብሪቲሽ ቅኝ ግዛት ስር ከገቡ በኋላ በውጪ እስላማውያን  ኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰው የጂሃድ ስጋት ለጊዜውም ቢሆን ጋብ ማለቱ አልቀረም፡፡

የልጅ ኢያሱ የማስለም ሤራ

ልጅ ኢያሱ

ሌላው ለኢትዮጵያ ክርስትና በጣም አደገኛ ዘመን እንደነበረ የሚነገረው የልጅ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት ነበር፡፡ አፄ ሚኒሊክ የአልጋ ቁራኛ ከሆኑ በኋላ በ1907 የልጅ ልጃቸው የነበሩትን ልጅ ኢያሱን የአልጋ ወራሽ፤ ራስ ተሰማን ደግሞ እንደራሴ አድርገው ሹመው ነበር፡፡ በ1911 የራስ ተሰማን ሞት ተከትሎ ልጅ ኢያሱ ከእስልምና ወደ ክርስትና ከመጡት ከአባታቸው ከራስ ሚካኤል ጋር በመሆን ሥልጣናቸውን ካጠናከሩ በኋላ ወደ እስልምና እምነት ማድላት እንደጀመሩ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ትሪሚንግሃም ይናገራሉ፡፡ በጸሐፊው መሠረት ልጅ ኢያሱ ወደ ሐረር ከተማ በመሄድ እስልምናን መለማመድ ጀምረው ነበር፡፡ ክርስቲያን የነበሩትን ባለቤታቸውን ሮማን ወርቅን ገሸሽ በማድረግ ሙስሊም ሴቶችን አግብተዋል፡፡ መስጊዶችንም በድሬ ደዋና በጅጅጋ አስገንብተዋል፡፡ በዚህ ሳያበቁ ኢትዮጵያ በሃይማኖት ከቱርክ ስር መሆኗን ለማመልከት በኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ የጨረቃ ምልክትና የእስልምናን የእምነት መግለጫ (ላኢላሀ ኢለላ መሐመደን ረሱል አላህ) በማድረግ ለቱርክ ቆንስላ ጄነራል ላኩለት፡፡ ለራሳቸው ሙስሊም ባለሥልጣናትም ተመሳሳይ ባንዲራዎችን በመላክ ለጂሃድ እንደሚመሯቸው ቃል ገቡ፡፡ ከኦጋዴኑ የሶማሌ መሐዲ ሙሐመድ ኢብን አብደላህ ጋር ስምምነት በማድረግም ጠብመንጃዎችንና ጥይቶችን ላኩለት፡፡ በክርስቲያኖች ላይ ለሚያደርጉት ጂሃድ እንዲከተሏቸውም ለሶማሌዎች ጥሪ አቀረቡ፤ ወደ ጂጂጋም በመሄድ ሠራዊት መለመሉ፡፡ በመጨረሻም እቅዳቸው ግቡን ሳይመታ ከሥልጣን እንዲወርዱ ተደረገ፡፡[9]

ማሳሰብያ፡- አንዳንድ የታሪክ ተመራማሪዎች በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከተጻፉት የታሪክ መጻሕፍት በመነሳት የልጅ ኢያሱን ታሪክ ከላይ በተቀመጠው መልኩ ማየት ሚዛናዊነት እንደሚጎድለው  ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም አንባቢያን ታሪኩን ከሌላ ፅንፍ የሚያሳዩ ምንጮችን እንዲያገናዝቡ እንመክራለን፡፡

የፋሺስት ኢጣሊያ እስላማዊ ተልዕኮ

በኢጣሊያ ወረራ ወቅት በኢትዮጵያ ክርስትና ላይ የተደቀነው አደጋ ቀላል አልነበረም፡፡ ቤኒቶ ሞሶሎኒ ኢትዮጵያን ለመውረር ዝግጅት ሲያደርግ ሳለ በአገር ውስጥና በውጪ አገራት ከነበሩት ሙስሊሞች ዘንድ ድጋፍ ለማሰባሰብ የተጠቀመው ዘዴ የኢትዮጵያን ክርስትና በማዋረድ እስልምናን ከፍ እንደሚያደርግ ቃል መግባት ነበር፡፡ የሞሶሎኒን የወረራ እቅድ በመቃወም ከኢትዮጵያ ጎን የተሰለፉ አረብ ሙስሊሞች ቢኖሩም ነገር ግን ብዙዎቹ ለወራሪው ኃይል ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ ልጅ ኢያሱም ትክክለኛው የኢትዮጵያ መሪ መሆኑን በማወጅ እስላማዊውን አገዛዝ እንደሚመልስ ቃል መግባቱ በሐረር፣ በኦጋዴን፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ሙስሊሞችና በአዲስ አበባ ይኖሩ በነበሩት አረብ ነጋዴዎች ዘንድ ተቀባይነትን አስገኝቶለት እንደነበር የኢጣሊያ ምንጮች ይገልፃሉ፡፡ ከጦርነቱ በፊት አፄ ኃይለ ሥላሴ ሚያዝያ 7/ 1935 ወደ ሳዑዲ አረብያ የላኩት የልዑካን ቡድን ምንም ተስፋ ሰጪ ነገር ሳያገኝ ወደ ካይሮ አቅንቷል፡፡ በወቅቱም ንጉሥ ኢብን ሳዑድ የልዑካን ቡድኑ አባል ለነበሩት ለኢትዮጵያዊው ሙስሊም ለአሕመድ ሳሊቅ፡- “ኢትዮጵያ በሙስሊሞች ላይ የፈፀመችውን ሁሉ አውቃለሁ፤ አባ ጂፋር ከሥልጣን ወርዷል ልጆቹም ከአገር ተሰደዋል፡፡ ለክፍለ ዘመናት የኖረው የጅማ እስላማዊ መንግሥት ጠፍቷል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የረባ ሥልጣን ያለው ሙስሊም የለም፡፡ ኢትዮጵያን ልረዳት አልችልም” በማለት መናገራቸው ተመዝግቧል፡፡ ይህም ለሞሶሎኒ አስደሳች ዜና ነበር፡፡[10]

ኢትዮጵውያኑ ባዶ እጃቸውን ከሳዑዲ በተመለሱ ልክ በወሩ በልኡል ሳዑድና ሐምዛ በተባለ ኢትዮጵያን በሚጠላ ሰው የሚመራ የልዑካን ቡድን ሮም ደረሰ፡፡ ሞሶሎኒ “ትክክልኛ የእስልምና ወዳጅ እንደሆነና በክርስትና ቀንበር ስር ለሚሰቃዩት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትክክለኛ ጠባቂ” እንደሆነም ተገለፀ፡፡ ሳዑዲ የኢጣሊያና የኢትዮጵያ ጦርነት በሁለት ክርስቲያን አገራት መካከል የሚደረግ ጦርነት መሆኑን በመግለጽ ገለልተኛነትን ትመርጣለች በሚል ሰበብ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደምታቋርጥ፤ ለኢጣሊያ ወታደሮች የሚሆን ምግብ እንደምትሸጥ፤ ፀረ ኢጣሊያ የሆነን የትኛውንም ፕሮፓጋንዳ እንደምታግድ፤ በምትኩም ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ኢጣሊያ ለሳዑዲ አየር ኃይል ድጋፍ እንደምታደርግና መሣርያ በመስጠት ውለታዋን እንደምትመልስ የሚገልጽ ምስጢራዊ ስምምነት ተደረሰ፡፡ ሳዑዲ 12,000 ግመሎችን ለሞሶሎኒ ለመሸጥ በመስማማት ድጋፏን ቸራለች፡፡ በቀጣዩ ክረምት ንጉሡ ሌላ የልዑካን ቡድን ወደ ሳዑዲ ቢልኩም ነገር ግን ውጤት አልነበረውም፡፡ በ1935 ኢትዮጵያን የወረረው የሞሶሎኒ ሠራዊት ከሶማሊያ፣ ከኤርትራና ከሊብያ የተውጣጡ ቁጥራቸው ከሰባ ሺህ በላይ የሚሆኑ ሙስሊም ወታደሮችን ያካተተ ነበር፡፡[11]

ቤኒቶ ሞሶሎኒ “የእስላም ሰይፍ” የሚል መፈክር በማሰማት ራሱን የእስላም ጠባቂ አድርጎ ያወጀበት የትሪፖሊ ትዕይንት

ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረባቸው በነዚያ አምስት ዓመታት እስልምናን ለማስፋፋት ጥረት ያደረገ ሲሆን አብያተ ክርስቲያናትን አውድሟል፤ ብዙ ክርስቲያኖችንም በጥይት፣ በመድፍና በመርዝ ጋስ ጨፍጭፏል፡፡ በአርሲና በሲዳማ አካባቢ የነበሩት ሕዝቦች እንዲሰልሙ ይበረታቱ ነበር፡፡ በሦስት ግዛቶችም ላይ እስልምና ኦፊሴላዊ ሃይማኖት ሆኖ ታውጆ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ ጣሊያኖች እስላማዊ ትምህርት ቤቶችን ይደጉሙ ነበር፡፡ ሙስሊሞችም እስላማዊውን ሕግ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ይበረታቱ ነበር፡፡ የሐጅ ቢሮ እንደ አዲስ በመደራጀት ተጓዦች በብዛት እንዲሄዱ ይበረታቱ፤ ድጋፍም ይደረግላቸው ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘውን ታላቁን የአንዋር መስጊድን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ መስጊዶች በመላ አገሪቱ እንዲገነቡ ተደርጓል፡፡ ለአንዋር መስጊድ ግንባታ ሞሶሎኒ በግሉ ድጋፍ አድርጓል፡፡ የሐረር ከተማ “የቁርኣንን ብርሃንና የእስልምናን ሥልጣኔ የምታበራ” የእስልምና ቅድስት ከተማ እንደምትሆን በግራዚያኒ ቃል ተገብቶ ነበር፡፡ አረብኛ የመማርያና የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የአረብኛ መጻሕፍትና ጋዜጦች ይታተሙ ነበር፡፡ የአረብኛ ሬዲዮ ጣብያዎችም ተቋቁመው ነበር፡፡ ሁሉም ጋዜጦች አንድ የአረብኛ አምድ እንዲኖራቸው ግዴታ ሆኖ ነበር፡፡ በ1936 ግራዚያኒ የዒድ አል ፈጥር በዓል ላይ ለመጀመርያ ጊዜ መድፍ እንዲተኮስ አድርጓል፡፡ ወራሪዎቹን የተቃወሙ የኃይማኖት አባቶችና ካህናት በጅምላ ተጨፍጭፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከግብፅ ጋር የነበራት ታሪካዊ ትስስር እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ ባጠቃላይ ያ ዘመን ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጭንቅ ዘመን ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ በ1937 ሞሶሎኒ ሊብያን በጎበኘበት ወቅት ፈረስ እየጋለበ “የእስላም ሰይፍ!” የሚል መፈክር በማሰማት “በሊብያና በኢትዮጵያ ውስጥ እንደተረጋገጠው፤ ካሊፌት ከጠፋ ወዲህ የእስልምና ዋና ጠባቂ” እርሱ መሆኑን ያወጀበት ትርዒት የሞሶሎኒን እስላማዊ ፕሮፓጋንዳ ከፍታ ጫፍ ያሳየ ነበር፡፡[12] ነገር ግን ፋሺስት ኢጣሊያ በቂ ጊዜ ስላላገኘ አገሪቱን የማስለም እቅዱ ግቡን ሳይመታ ቀርቷል፡፡

የዚያድ ባሬና የሶማሊያ የሽብር ቡድኖች ሙከራ

ዚያድ ባሬ “ታላቋ ሶማሊያን” የመመሥረት እቅዱን ለማሳካት የአፄ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት ውድቀትና የአገሪቱን አለመረጋጋት ተከትሎ በ1977 በአገሪቱ ላይ ጦርነትን አውጆ ብዙ አካባቢዎችንም ተቆጣጥሮ ነበር፡፡ ነገር ግን ከስምንት ወራት እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ በኋላም ተሸንፎ ከአገሪቱ ሊወጣ ችሏል፡፡ የኢትዮጵያን ግዛቶች ቆርሶ የእስላማዊቷ ሶማሊያ አካል የማደረግ ህልሙም መና ቀርቷል፡፡ ከዚያድ ባሬ ውድቀት በኋላ በሳዑዲ አረብያ መንግሥትና ካርቱም ላይ በነበረው የአልቃኢዳ እርዳታ የተለያዩ እስላማዊ የሽብር ቡድኖች ሶማሊያ ውስጥ ተመስርተው ነበር፡፡ ከነዚህ መካከል  አል-ተክፊር ወል ሒጅራ፣ አል-ኢስላህ እና አል-ተብሊሂ ይጠቀሳሉ፡፡[13]

ዚያድ ባሬ

በዚያድ ባሬ አስተዳደር ከአገር የተሰደዱት ግለሰቦችና በኦጋዴን ውስጥ የተሸነፉት ሶማሌ ታጣቂዎች በመተባበር በሳዑዲ አረብያ ውስጥ በ1978 አል-ኢትሃድ አል-ኢስላሚ (እስላማዊ ሕብረት) የሚል የሽብር አንጃ በማቋቋም በኢትዮ-ሶማሌ ድንበር አካባቢ መንቀሳቀስ ጀምረው ነበር፡፡ ይህ የሽብር ቡድን የሶማሊያን ሽብርተኞች ከዓለም አቀፉ የሽብር መረብ ጋር አስተሳስሮ ነበር፡፡ በ1980ዎቹ ውስጥ ደግሞ የተወሰኑ የሶማሌ “ሙጃሂዲኖችን” በአፍጋኒስታን ጦርነት ውስጥ እንዲሳተፉ ልኮ ነበር፡፡ በ1984 ብዙ የሽብር ቡድኖችን አባል በማድረግ ኃይሉን ያጠናከረ ሲሆን አልቃኢዳን ለመሳሰሉት የሽብር ቡድኖች እርዳታን በመስጠት በሚታወቁት አል ሐራሚን የተባለውን የሳዑዲ አረብያ የእርዳታ ድርጅትን በመሳሰሉት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይታገዝ ነበር፡፡ በ1991 ዚያድ ባሬ ከወደቀ በኋላ ህልውናውን ይፋ በማድረግ ሼኽ ዳሂር አዌይስን መሪው አድረጎ ሾመ፤ በኢትዮጵያ ላይም ጂሃዳዊ ጥቃቶቹን መፈፀም ጀመረ፡፡ በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ላይ ብዙ ጥቃቶችን ከፈፀመ በኋላ በ1995-1996 ዓ.ም. (የዘመን አቆጣጠሮቹ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር መሆናቸው ይታወስ) በአዲስ አበባ ከተማም ውስጥ የቦምብ ጥቃቶችን ፈፀመ፡፡ እነዚህ ሁሉ የሽብር ጥቃቶች አል ሐራሚን በተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅትና በአልቃኢዳ ይደገፉ እንደነበር ይነገራል፡፡ ኋላ ላይም የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ ሶማሊያ በመግባት ብዙ የአል-ኢትሃድን ካምፖች አጥፍቷል፡፡ ሽብርተኞቹንም ድል በመንሳት በታትኗቸዋል፡፡ የተበታተኑትም ሽብርተኞች ኋላ ላይ በመሰባሰብ “የእስላማዊ ፍርድቤቶች ሕብረት” የተባለውን ድርጅት የመሠረቱ ሲሆን ይህ የሽብር ቡድን በኢትዮጵያና በአሜሪካ የሚደገፈውን የሶማሊያ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት በማስወገድ ሞቃዲሾን ተቆጣጥሮ በሸሪኣ የሚመራ መንግሥት መሥርቶ ነበር፡፡ ኦጋዴንም የአዲሱ ካሊፌት አካል እንደሆነ በማወጅም በኢትዮጵያ ላይ ጂሃድን አውጆ ነበር፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በ2006 ወደ ሶማሊያ በመግባት ዓለምን ባስደመመ ፍጥነት ድል ነስቶ በታትኖታል፡፡ የሽግግር መንግሥቱም መልሶ ቦታውን እንዲይዝ አድርጓል፡፡[14]

——————————–

[1] Trimingham. Islam in Ethiopia; p. 92

[2] Ibid., p. 114

[3] Ibid., p. 63

[4] Ibid.

[5] Ibid., pp. 114-115

[6] Ibid., pp. 115-116

[7] Ibid., pp. 120-121

[8] Ibid., p. 116-125

[9] Ibid., 130-131

[10] Erlich. Saudi Arabia & Ethiopia; pp. 39-45

[11] Ibid., p. 46-67

[12] Ibid., 67-61

[13] Ibid., p. 205

[14] Ibid., 204-207

 

እስልምናና ሽብርተኝነት