ጥንታውያን የክርስቲያን ማዕከላት ላይ የተፈፀሙ የጂሃድ ወረራዎች

ጥንታውያን የክርስቲያን ማዕከላት ላይ የተፈፀሙ የጂሃድ ወረራዎች

በሙሐመድ ዘመን በአረብያ የነበሩት ክርስቲያን ማሕበረሰቦች ቁጥራቸው አናሳ ስለነበረ እንደ አይሁድ ለአዲሱ እስላማዊ ማሕበረሰብ “ስጋት” ሊፈጥሩ የሚችሉ አልነበሩም፡፡ ነገር ግን ሙሐመድ ዙርያው በክርስቲያን ማሕበረሰቦች እንደተከበበ ያውቁ ነበር፡፡ እነዚህ አገራት እንዲሰልሙ ወደየመሪዎቻቸው ደብዳቤዎችንም ይጽፉ ነበር፡፡ የሙሐመድን ደብዳቤዎች ከተቀበሉት ክርስቲያን ነገሥታት መካከል የአክሱም ንጉሥ ይገኝበታል፡፡ በሙስሊሞች የተጻፉት ታሪኮች እንደሚናገሩት “አል-ነጃሺ” የተሰኘ የአክሱም ንጉሥ እንደ ሙስሊም የተቆጠረ ሲሆን ከእርሱ ቀጥሎ የነገሠው ንጉሥ እንዲሁ ወደ እስልምና እንዲመጣ ግብዣ የሚያቀርብ በማስፈራርያ የሚደመደም ደብዳቤ ከሙሐመድ ደርሶታል፡፡[1]

(አል-ነጃሺ የሚባል ንጉሥ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደማይታወቅና ከዚህ የፈጠራ ታሪክ በስተጀርባ የሚገኘውን የአክራሪዎች ሤራ ለማወቅ ይህንን ጽሑፍ ያንብቡ፡፡)

ከሙሐመድ ሞት በኋላ ወዲያውኑ ነበር የጂሃድ ሠራዊት የክርስቲያን አካባቢዎችን መውረር የጀመረው፡፡ በዘመኑ ዋና ዋና የሚባሉትን የክርስቲያን ማዕከላትንም በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቆጣጠር በሰይፍ ስለት አሰለመ፡፡ ደማስቆ በ635 በጂሃድ ሠራዊት እጅ ወደቀች፡፡ አንፆኪያ በ636 ተያዘች፡፡ ኢየሩሳሌም በተያዘች በሁለት ዓመታት ውስጥ ደግሞ ቂሣርያ ከረጅም ጊዜ ከበባ በኋላ በሙአዊያና በወንድሙ ለሚመራው የጂሃድ ጦር እጅ ሰጠች፡፡ በ640 በሦርያ የነበሩት ክርስቲያኖች በአረብ ሙስሊሞች ምድራቸውን ተነጠቁ፡፡ በ641 ፋርስና ግብፅ ለጂሃድ ሠራዊት እጅ ሰጡ፡፡

በቱርክ ጂሃዳውያን ወደ መስጊድነት የተቀየረው በኢስታንቡል የሚገኘው የሶፍያ ቤተ ክርስቲያን፡፡ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በዚህ መልኩ ወደ መስጊድነት ተቀይረዋል፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ወቅት ሙዚየም ሆኗል፡፡

ከ649-668 ቆጵሮስ፣ ሮዴስና ቀርጤስን የመሳሰሉት የክርስቲያኖች መኖርያ የነበሩት ደሴቶች በእስላም ጦር ተያዙ፡፡ ሙሐመድ በሞቱ በዘጠኝ ዓመታት ውስጥ በዘመኑ የሚታወቁት የክርስቲያን ማዕከላት የጂሃዳውያን ሰለባ ሆኑ፡፡ ሙስሊም ጂሃዳውያን በመካከለኛው ምስራቅና በሰሜን አፍሪቃ የነበሩትን የክርስቲያን አገራት ከተቆጣጠሩ በኋላ በቀጥታ ወደ ቁስጥንጢንያ ነበር የዘመቱት፡፡ በ668 ዓ.ም.[2] ከሦርያ የተንቀሳቀሰው የጂሃድ ጦር ከተማይቱን ለስድስት ዓመታት የከበባት ሲሆን ሳይሳካለት ተመልሷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቢዛንታውያን ይጠቀሙት የነበረ የፈላ ፈሳሽ እንደነበር ይነገራል፡፡[3] በመጨረሻም በ1453 በኦቶማን ቱርኮች እጅ ወድቃለች፡፡ ስሟም ተቀይሮ ኢስታንቡል ተብሏል፡፡ ውብ የሆነውም የሶፍያ ቤተ ክርስቲያን መስጊድ የተደረገ ሲሆን በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ ወደ ሙዚየምነት ተቀይሯል፡፡

የመስቀል ጦርነቶች (ክሩሴዶች)


ጂሃዳውያን በምስራቅ የሚገኙትን የክርስቲያን አገራት ከወረሩ በኋላ መላውን አውሮፓ በማስለም ክርስትናን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት በቀጥታ ወደ ምዕራብ ነበር የዘመቱት፡፡ በዚህም መነሻ በ711 ዓ.ም. ጣሪቅ ኢብን ዚያድ የተሰኘ ጂሃዳዊ 7,000 የሚሆን ሠራዊት በማስከተል ከሰሜን አፍሪቃ ወደ እስፔን ተሻገረ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይህ ቁጥር ወደ 12,000 በማደግ ተጠናከረ፡፡ ሮዴሪክ የተሰኘ የወቅቱ የእስፔን መሪ 25,000 ሠራዊት አስከትሎ ሊገጥመው የወጣ ቢሆንም ይህ መሪ ዊቲዛ በተባለ ንጉሥ ላይ መፈንቅለ መንግሥት በመፈፀም ወደ ሥልጣን የመጣ ስለነበረ በሕዝቡ ዘንድ የሚወደድ አልነበረም፤ ከዚህም የተነሳ የወታደሮቹ የመዋጋት ፍቃደኝነት ያን ያህል ነበር፡፡ የዊቲዛ ወንድም የነበሩት ጳጳሱ ኦፓስ ለጂሃዳውያኑ በመወገናቸው ምክንያትና ሌላውም ነገር ተደማምሮ የጂሃድ ጦር ድል ነሳ፡፡ የክርስቲያን ምድር የሆነችው እስፔንም በእስላማዊ አገዛዝ ስር ወደቀች፡፡[4]የመስቀል ጦርነቶችን ትክክለኛ መነሻና አውድ ለማወቅ ከጦርነቶቹ በፊት የተፈፀሙትን ታሪኮች ወደ ኋላ መለስ ብሎ መቃኘት ያስፈልጋል፡፡

እስልምና እስፔንን በገዛባቸው ክፍለ ዘመናት ብዙ ግፎች በክርስቲያኖች ላይ ተፈፅመዋል፡፡ በተለይ አል-ኀኪም የተሰኘ የኡመያድ ሥረወ መንግሥት ኤሚር (796-822) እጅግ ጨካኝ ሰው ነበር፡፡ ቶሌዶ በተባለ ቦታ ወደ እስልምና ተቀይረው የነበሩ ክርስቲያኖች እንኳ ከጭፍጨፋ ሊተርፉ አልቻሉም ነበር፡፡ በአንድ ቀን ወደ 5,000 የሚሆኑ ሰዎች አንገታቸውን መቀላታቸው ተዘግቧል፡፡ ይህም በእስፔን ታሪክ “የጉድጓድ ቀን” በመባል ይታወቃል፡፡ በኮርዶባ ሙስሊም ጂሃዳውያን የምግብ ዋጋ በማስወደዳቸው ምክንያት ሰላማዊ ሰልፍ የጠሩ መሪዎች እንዲሰቀሉ ተደርጓል፡፡ በበነጋው ስቅላቱን ለመቃወም የወጡ 300 ሰዎች ተሰቅለዋል፡፡ በዚያን ዘመን በመስቀል ላይ የበሰበሱ አስክሬኖችን በየመንገዱ ማየት የተለመደ ነበር፡፡ ከሮማውያን የስደት ዘመን ቀጥሎ በአውሮፓ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሰማዕታት የበዙበት እንደዚያ ያለ ዘመን አልነበረም፡፡ ፍሎራና ማርያም የተሰኙ ሁለት ሴቶች በታሪክ ሲታወሱ ከሚኖሩት የእስፔን ሰማዕታት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ካህናቱ ፐርፌክቶስና ኢሎጊዎስ እንዲሁም አሥራ አንዱ የኮርዶባ ሰማዕታትም ከብዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡[5]

የጂሃድ ጦር ወደ ኢጣሊያ በመሻገር ከ827-902 በሲሲሊ ላይ የማያቋርጥ ጥቃት ፈፅሟል፡፡ በነዚያ ዘመናት ጂሃዳውያን ለመስማት የሚዘገንን ብዙ ግፍ በክርስቲያኖች ላይ ፈፅመዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን ያረክሱ ነበር፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑን ይጨፈጭፉ፣ ያዋርዱና ንብረቱን ይዘርፉ ነበር፡፡ ኤድዋርድ ጊቦን የተባለ ጸሐፌ ታሪክ እንደዘገበው በሴሌርኖ ከበባ ጊዜ የጂሃዱ መሪ የቅዱስ ቁርባን ማስቀመጫ በሆነው በመቅደሱ ውስጥ በሚገኘው መሰዊያ ላይ መደረቢያውን በማንጠፍ በምንኩስና ይኖሩ የነበሩትን የገዳሙን ደናግላን አንድ በአንድ እያመጣ ድንግልናቸውን ይገስስ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ የመቅደሱ ጣርያ ድንገት ተደርምሶ ጭንቅላቱ ላይ በመውደቅ ዘማዊውን ጂሃዳዊ ገድሎታል፡፡[6]

ጂሃዳውያኑ የክርስቲያን ማዕከላት የነበሩትን ሮምንና ቁስጥንጢንያን ለመቆጣጠር ወደፊት ገሠገሡ፡፡ በ846 ሮም ከተማ በመግባት የቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስን አብያተ ክርስቲያናት ዘረፉ፡፡ ጳጳሱም በዓመት 25,000 የብር ሳንቲሞችን ለመክፈል ቃል ስለገቡ ወራሪዎቹ ተመለሱ፡፡ ጳጳሱ ሊዮን አራተኛ የቅዱስ ጴጥሮስን ቤተ ክርስቲያን ከጥቃት ለመከላከል “የሊዮን ግንብ” በመባል የሚታወቀውን ቅጥር አስገነቡ፡፡ ነገር ግን የሚሸነፍ የማይመስለው የጂሃድ ሠራዊት መላውን አውሮፓ ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት ቱርስ በተባለ ቦታ ላይ ተገታ፡፡ አረቦች በፈረንሳዮች እጅ የሽንፈት ፅዋቸውን ተጎነጩ፡፡ አውሮፓም ለእስልምና ከመንበርከክ ተረፈች፡፡[7]

ክሩሴዶች ወይም የመስቀል ጦርነቶች ተብለው የሚታወቁት ጦርነቶች በዚህ ሁኔታ መላውን የክርስቲያን ዓለም ለማጥፋት የተነሳውን ጂሃድ ለመቋቋም በ 1095-1291 ዓ.ም. መካከል የተደረጉ ነበሩ፡፡ በነዚያ 200 ዓመታት ውስጥ ባጠቃላይ ወደ 10 ክሩሴዱች ተደርገዋል፡፡ ጦርነቶቹን ያወጁት የፈረንሳይ ጳጳስ የነበሩት ዳግማዊ አርባን ነበሩ፡፡ አውሮፓውያን ክርስቲያኖች  በመጀመርያው ክሩሴድ እስከ መካከለኛው ምስራቅ በመዝለቅ ኢየሩሳሌምን ከሙስሊሞች እጅ የነጠቁ ሲሆን ሦርያና ፍልስጥኤምን በግዛቶች በመከፋፈል ማስተዳደር ጀምረው ነበር፡፡ ነገር ግን ኋላ ላይ ተሸንፈው ለቀው ወጥተዋል፡፡[8] 

የክሩሴድ ጦርነቶች የአውሮፓ ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ከሠራቻቸው ትልልቅ ስህተቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት ቢጠቀሱም ለጦርነቶቹ መቀስቀስ ምክንያት የሆኑት የሙስሊም ወራሪ ኃይላት እንጂ ክርስቲያኖች አለመሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ዛሬ እስልምና ተጎናዝሎ የተቀመጠባቸው የመካከለኛው ምስራቅና የሰሜን አፍሪቃ አገራት የክርስቲያን አገራት የነበሩና በእስላም ወራሪ ኃይላት ተደምስሰው የክርስትና ታሪካቸው እንዲጠፋ የተደረጉ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዛሬም ድረስ የሚታዩት ጥንታውያን የአብያተ ክርስቲያናት ፍርስራሾችና ከብዙ የግፍ ሥራዎች በእግዚአብሔር ተዓምር ተርፈው ክርስትናቸውን ጠብቀው የሚገኙት ቅሬታዎች ምስክሮች ናቸው፡፡ ሙስሊሞች እነዚህን አገራት ያሰለሙት በሰይፋቸው እንጂ በመጽሐፋቸው  ፈፅሞ አልነበረም፡፡ እስፔን ድረስ በመዝለቅ ጎሮሯቸው ላይ ሰይፉን ያስቀመጠውን ይህንን እስላማዊ የጂሃድ ወረራ ለመቋቋምና ልክ እንደ ዛሬዎቹ የአይኤስና የአልቃኢዳ አሸባሪዎች ጨካኞች በነበሩት ጂሃዳውያን እጅ ለወደቁት የመካከለኛው ምስራቅ ክርስቲያን ወንድሞቻቸው የድረሱልን ጥሪ ጩኸት ምላሽ ለመስጠት የነበራቸው አማራጭ ኃይልን መጠቀም እንደነበረ ስለተሰማቸው የአውሮፓ ክርስቲያኖች የጦርነት ዘመቻዎችን በማድረግ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን ክርስቲያኖች በዚያ የታሪክ አጋጣሚ የተፈጠረውን ስህተት ሲያስቡ ዛሬም ድረስ ይፀፀታሉ፡፡ የአውሮፓ ቤተ ክርስቲያንም በተደጋጋሚ ይቅርታ ጠይቃለች፡፡ ሙስሊም አገራት ግን አንድም ጊዜ ለይቅርታ ጥያቄው ዕውቅና ሰጥተው አያውቁም፡፡ የክርስቲያኖች የይቅርታ ጥያቄ የመነጨው ሰይፍን መጠቀም ከክርስቶስ ትምህርት ጋር የሚጣረስ መሆኑን ከማመን እንጂ እነርሱ የፈፀሙት ራስን የመከላከል የአልሞት ባይ ተጋዳይ ትንቅንቅ  ጂሃዳውያን ከ7ው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በክርስቲያኖች ላይ ከፈፀሙት በደልና ግፍ ጋር የሚነፃፀር ሆኖ አይደለም፡፡ ቢሆንም ግን ሰይፍን በሰይፍ መመለስ  የክርስቶስ ትምህርትና ኑሮ ባለመሆኑ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ተከታዩ ሕዝብ እንደዚያ ዓይነት ውድቀት ውስጥ መግባታቸው ስህተት ነበር፡፡

ክሩሴዶች እስከ ዛሬ ድረስ በምዕራብና በሙስሊም አገራት መካከል ላለው ግንኙነት ተምሳሌት ሆነው ቀጥለዋል፡፡ ሙስሊሞች በክሩሴድ ዘመን በገዛ አገሮቻቸው በሰላም ሲኖሩ እንደነበርና ያለ ምንም ምክንያት በክርስቲያኖች ወረራ እንደተፈፀመባቸው በማስመሰል ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ማለትም በክርስቲያኖችና በመሰብሰቢያ ቤቶቻቸው ላይ ለሚፈፅሟቸው ጥቃቶችም እንደ ማፅደቅያ ይጠቀሙታል፡፡

የከሸፉ ጂሃዶች

ጂሃዳውያን የክርስቲያን ማዕከላትን በመውረር የተሳካላቸውን ያህል ክሽፈቶችንም አስተናግደዋል፡፡ በተለይም የቱርስና የቪዬና ጦርነቶች ወርቃማ ዕድሎችን እንዳጡ በማሰብ በእጅጉ የሚቆጩባቸው የታሪክ አጋጣሚዎች ናቸው፡፡

የቱርስ (የፖይቲርስ) ጦርነት

ቱርስ በፈረንሳይ ውስጥ የምትገኝ ታሪካዊ ቦታ ናት፡፡ ጦርነቱ የተደረገው ከእስፔን ወደ ምዕራብ አውሮፓ በተሻገሩ አረብ ወራሪዎችና በፈረንሳይ ክርስቲያኖች መካከል ነበር፡፡ የኡመያድ ካሊፌት ጦር አብዱልረህማን አል ጋፊቅ በተሰኘ የአል-አንደሉሺያ (እስፔን) ኤሚር የተመራ ሲሆን የፈረንሳይ ሠራዊት ደግሞ ቻርልስ ማርቴል[9] በተሰኘ መኮንን ነበር፡፡ ሁለቱ ሠራዊቶች ሰኔ 10/ 732 ዓ.ም. በመግጠም እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ አድርገዋል፡፡ በዚህ ጦርነት አብዱልረህማን የተገደለ ሲሆን በእርሱ የተመራው የአረብ ወራሪ ኃይል ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት በመሸነፍ አፈግፍጓል፡፡ ከዚያ በኋላ የእስላም ጦር መላውን አውሮፓ ለማስለም ያንን በሚያህል ግዙፍ ሠራዊት ወረራ ለመፈጸም 700 ዓመታት ያህል መጠበቅ ነበረበት፡፡[10]

የቪዬና ከበባ

ከነበራት እስትራቴጂያዊ አቀማመጥ የተነሳ የኦስትሪያ ዋና ከተማ የሆነችውን ቪዬናን መያዝ የኦቶማን ቱርኮች የረጅም ጊዜ ህልም ነበር፡፡ ኦቶማኖች የሮማ ምስራቃዊ ግዛተ መንግሥት የነበረውን ቢዛንታይንን በመውረር ቁስጥንጢንያን ከያዙ በኋላ ግሪክ፣ ቡልጋርያ፣ ሩማንያና ሰርቢያን የመሳሰሉትን የምስራቅ አውሮፓ አገራት በቁጥጥራቸው ስር ማድረግ ተሳክቶላቸዋል፡፡ መላውን አውሮፓ የማስለም ህልማቸውን እውን ለማድረግ በኦስትሪያ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በመፈፀም በ1529 ቪዬናን የከበቡ ቢሆንም ሳይሳካላቸው በመቅረቱ እንደገና ተጠናክረው በመምጣት በ1683 ወረራ ፈፅመዋል፡፡ በዚህ ወረራ ወቅት በመንገዳቸው ላይ ብዙ ከተሞችንና መንደሮችን አጥፍተዋል፤ ብዙ ክርስቲያኖችንም ማርከዋል፡፡  የኦስትሪያ ንጉሥ የነበረው ሊኦፖልድ 11,000 ወታደሮችና 5,000 ፈቃደኛ ዜጎችን በማስተባበር ከተማይቱ እንዳትያዝ ቢፋለምም የእርሱ አቅም በቱርካዊው የጦር መኮንን ካራ ሙስጠፋ ፓሻ ከሚመራው 150,000 የእስላም ሠራዊት ጋር የሚመጣጠን አልነበረም፡፡ የፖላንድ ንጉሥ የነበረው ሣልሳዊ ጆን ሶቢዬስኪ 30,000 ወታደሮችን በማስከተል ባይደርስ ኖሮ የከተማይቱ መያዝ እርግጥ ነበር፡፡ ከፖላንዶች በተጨማሪ በዚህ ጦርነት ላይ 18,500 የኦስትሪያ ወታደሮች፣ 9,000 የሳክሰን ወታደሮችና 19,000 የፈረንሳይ፣ የሱዋቢያኖችና የባራቪያኖች ቅይጥ የሆኑ ወታደሮች ተሳትፈዋል፡፡ ሶቢዬስኪ ከፍተኛ ወታደራዊ ብቃቱን በመጠቀም እነዚህን ሠራዊቶች ካቀናጀ በኋላ መስከረም 12፣ 1683  በቱርኮች ላይ ጥቃት ከፈተ፡፡ 12 ሰዓታት ያህል በፈጀው በዚህ ወሳኝ ፍልሚያ የቱርኮች ኃይል ተሰበረ፡፡ ሽንፈቱን የተረዳው የእስላም ጦርም በእጁ በሚገኙት ምርኮኞች ላይ ጭፍጨፋ ከፈፀመ በኋላ ብዙ ንብረት በመጣል ሕይወቱን ለማትረፍ ሸሸ፡፡ በሽንፈታቸው ከፍተኛ ብስጭትና እፍረት ውስጥ የገቡት ቱርኮች ካራ ሙስጠፋ ፓሻን ተጠያቂ በማድረግ ጥቅምት 25፣ 1683 ቤልግሬድ ውስጥ በዘግናኝ ሁኔታ በሞት ቀጥተውታል፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ የጂሃድ ጦር በዚያ መልኩ ወረራ ለመፈፀም ዳግመኛ ወደ ምዕራብ አውሮፓ አልተመለሰም፡፡[11]

አረቦችና ቱርኮች እነዚያን ጦርነቶች ድል አድርገው ቢሆን ኖሮ መላውን የምዕራብ ዓለም የማስለም ዕድል ይኖራቸው ስለነበር አላህ በቁርኣን ውስጥ እስልምናን ከሃይማኖቶች ሁሉ የበላይ ሊያደርግ የገባው ቃል እውን በሆነ ነበር (ሱራ 9፡33)፡፡ ነገር ግን ይህ ተስፋ አሁንም ድረስ ተስፋ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

——————————

[1] ሙሐመድ ጦይብ፡፡ ኢትዮጵያና ኢስላም፣ በኢድሪስ ሙሐመድ የተተረጎመ፤ 1999፣ ገፅ  102-103

[2] ትክክለኛውን ዓመት በተመለከተ የተለያዩ ጸሐፊያን የተለያዩ ዓመታትን ያስቀምጣሉ፡፡

[3] Fregosi. Jihad; pp. 71-86

[4] Anwar Shaikh. Islam and Terrorism; 2004, pp. 167-173

[5] Fregosi. Jihad; pp. 1126-129

[6] Edward Gibbon. Decline and Fall of Roman Empire; Vol. 5, chap. 46, quoted in Paul Fregosi. Jihad in the West; 1998, p. 133

[7]. Ibid. 116-121

[8] Campo. Encyclopedia of Islam; p. 175

[9] ‹ማርቴል› ‹መዶሻ› ማለት ሲሆን በጂሃዳውያን ላይ በተቀዳጀው ድል ምክንያት የተሰጠው ቅፅል ስም ነው፡፡

[10] Encyclopedia Britannica www.britannica.com/event/Battle-of-Tours

[11] Ibid., www.britannica.com/event/Siege-of-Vienna-1683

 

እስልምናና ሽብርተኝነት