ሽብርተኝነት – የጥንቱ ጂሃድ አዲስ ገፅታ

ሽብርተኝነት – የጥንቱ ጂሃድ አዲስ ገፅታ

አሥራ ስምንተኛው ክፍለዘመን የመካከለኛው ምስራቅ ሥልጣኔ በመክሰም የምዕራባውያን ሥልጣኔ ከፍ ብሎ የታየበት ነበር፡፡ ናፖሊዮን ቦናፓርት በ1798 ሠላሳ አምስት ሺህ ወታደሮቹን ግብፅ ላይ ማሥፈሩ የኃይል ሚዛኑ መለወጡን በግልፅ ያመለከተ የታሪክ አጋጣሚ ነበር፡፡ በአሥራ ዘጠነኛውና በሃያኛው ክፍለ ዘመን የነበረው የአውሮፓውያን የመስፋፋት ፖሊሲ የዓለምን የኃይል ሚዛን ስለለወጠው የሙስሊሙ ዓለም ከገዢነት ወደ ተገዢነት ለማሽቆልቆል ተገደደ፡፡ በኦቶማን ቱርኮች በክርስቲያኖች ላይ ይደረጉ የነበሩት የማጥቃት ዘመቻዎችም ወደ ውጪ ከመሆን ይልቅ በግዛተ መንግሥቱ ውስጥ በነበሩት የክርስቲያን ማሕበረሰቦች ላይ ያነጣጠሩ ሆኑ፡፡ የኦቶማን ግዛተ መንግሥትም ከመፈራረሱ በፊት ማሳረጊያውን የብዙ ክርስቲያኖችን ደም በማፍሰስ አደረገ፡፡

ከአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ብሪቴንና ፈረንሳይን በመሳሰሉት አገራት በቱርኮች ላይ ይደረግ የነበረው ጫና እየበረታ በመምጣቱ ሳብያ የኦቶማን ቱርኮች ግዛተ መንግሥት ፈተና ውስጥ ገባ፡፡ ምዕራባውያንም በኦቶማን ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖችና አይሁድ የሚከፍሉት የጂዝያ ግብር እንዲቀር ግፊት አደረጉ፡፡ የግብሩ መቅረት ያስቆጣቸው ሙስሊሞች በየቦታው ክርስቲያኖችን ማጥቃት ተያያዙ፡፡ በተለይ በደማስቆ ክርስቲያኖች ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ እጅግ ዘግናኝ ነበር፡፡ ጭፍጨፋው የተደረገው በ1860 ዓ.ም. ሲሆን በቁጣ የተሞሉ ሙስሊሞች ስለታማ መሳርያዎችን ይዘው በመውጣት ከ7,000 – 10,000 የሚገመቱ ክርስቲያኖችን ገድለዋል፡፡ ብዙዎችንም ለስደት ዳርገዋል፡፡ የቱርክ ወታደሮችም ጨፍጫፊዎቹን በመርዳት ክርስቲያኖችን አሳልፈው ይሰጡ ነበር፡፡ በሽሽት ላይ የነበሩትንም በመያዝ ከነሕይወታቸው የእሳት ነበልባል ውስጥ ይወረውሯቸው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ አብዱል ቃድር የተሰኙ ምግባረ ሰናይ ሙስሊም በሺህዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን በቤታቸው በማስጠለል ማትረፋቸው በደግነታቸው ታሪክ ከሚያስታውሳቸው ሰዎች መካከል አንዱ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከፈረንሳይ መንግሥት የክብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት በሰብኣዊነት የሚመሩ ለጥላቻ ትምህርቶች ልባቸውን ያልሰጡ ወገኖች ባይኖሩ ኖሮ ዓለማችን ምን ትሆን ነበር? ብዙ የአውሮፓ የሚስዮናውያን ድርጅቶችም ክርስቲያን ስደተኞችን በመታደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል፡፡ በወቅቱ የተደረገውን ጭፍጨፋ ዝነኛው የኒውዮርክ ታይምስ መጽሔት በኦገስት 13/ 1860 እትሙ ላይ በስፋት ዘግቦታል፡፡[1]

የኦቶማን ኢምፓየር መዳከም ሲጀምር ለዘመናት ሲጨቆኑ የኖሩት የተለያዩ የክርስቲያን ማህበረሰቦች ነፃነታቸውን መፈለግ ጀመሩ፡፡ ነገር ግን ይህንን ጥያቄ ማንሳታቸው እየተፈረካከሰ የነበረው የእስላም ግዛተ መንግሥት ምህረት የለሽ የጂሃድ ሰይፉን እንዲያሳርፍባቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለይ በአርመናውያን ክርስቲያኖች ላይ የደረሰው ሰቆቃ መቼም ቢሆን የሚረሳ አይደለም፡፡ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋው የተደረገው በ1915 ሲሆን ከአንድ ሚሊዮን እስከ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚገመቱ ክርስቲያኖች በዘግናኝ ሁኔታ ተጨፍጭፈዋል፡፡ ወንዶቹ በጀማ የተጨፈጨፉ ሲሆን ሴቶችና ህፃናት ደግሞ በወታደሮች እየተነዱ ወደ ሦርያ በረሃ በመወሰድ እንዲበዘበዙ፣ እንዲደፈሩ፣ በረሃብ፣ በጥማትና በፀሐይ ሀሩር ተጠብሰው እንዲያልቁ ተደርጓል፡፡[2] ወታደሮቹ ክርስቲያን ሴቶችን ሲደፍሩ እንዲመለከቱ ባሎቻቸውን ያስገድዱ ከዚያም ይገድሏቸው እንደነበርና ብዙ ወጣት ሴቶችም በመስቀል ተቸንክረው መሰቀላቸውን የታሪክ ድርሳናት እማኝነታቸውን ይሰጣሉ፡፡[3]

የኦቶማን ግዛተ መንግሥት ከፈራረሰ ወዲህ ጂሃድ አዲስ መልክ እየያዘ መጣ፡፡ ከዚያ ቀደም ሙስሊም ባልሆኑት ሕዝቦች ላይ ይፈፀም የነበረው ጂሃድ በዋናነት በእስላም መንግሥታት አማካይነት ሲሆን አሁን ግን ኦፊሴላዊ በሆነ ሁኔታ በሕጋዊ መንግሥታት የሚደረጉ የጂሃድ እንቅስቃሴዎች የሚያስኬዱ አልሆኑም፡፡ ስለዚህ የእስላም መንግሥታት የሽብር ቡድኖችን በማደራጀትና በመደገፍ ከመድረክ ጀርባ ሆኖ መተወን አስፈልጓቸዋል፡፡ ዛሬ ለምዕራባውያን ሃያላን መንግሥታት እንኳ ፈተና የሆኑት በዓለም ላይ የሚገኙት የሽብር ቡድኖች ያላቸው አቅምና አደረጃጀት የግለሰቦች ስብስብ ብቻ አለመሆናቸውንና ከበስተጀርባቸው ሌላ ኃይል መኖሩን ይጠቁማል፡፡

በነቢዩ ሙሐመድና በተከታዮቻቸው የተጀመረው የጥንቱ ጂሃድ ስልቱን ቀይሮ “ሽብርተኝነት” የሚል ስም በማግኘት ብቅ ካለ ሰነባብቷል፡፡ በግብፅ የሚገኘው የአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲም ዋነኛ የፅንፈኛ ትምህርቶች መፍለቂያ መሆኑና ግብፅም የሽብርተኛ ቡድኖች የርቢ መስክ ሆና መቆየቷ ይታወቃል፡፡

—————————-

[1] The New York Times: http://www.nytimes.com/1860/08/13news/syrian-outbreak-details-damascus-massacre-foreign-intervention-syria.html

[2] Christopher J. Walker. Armenia, the Survival of Nation; 1980, pp. 200-203; Campo. Encyclopedia of Islam; pp. 62-63

[3] Shahkeh Yaylaian Setian. Humanity in the Midst of Inhumanity; Xlibris publishers,  2011, p. 170