ወሃቢዝም በኢትዮጵያ ውስጥ

ወሃቢዝም በኢትዮጵያ ውስጥ

በደርግ ውድቀት ማግስት በኢትዮጵያ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት መታወጁ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ነፃነት የለአግባብ የተጠቀሙና የጥፋት መርዛቸውን በትውልዱ መካከል ለማሰራጨት የተጉ፣ ከዚህም የተነሳ ብዙ ጥፋቶችን ያስከተሉ ቡድኖች መኖራቸው አልቀረም፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ የወሃቢዝም (ሰለፊ) ፍልስፍናን የሚከተሉ ወገኖች ይጠቀሳሉ፡፡ ዛሬ በአገሪቱ ውስጥ በብዛት ተሰራጭቶ በሕዝቦች መካከል ያለውን የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባሕል እያደፈረሰ የሚገኘው ወሃቢዝም ይህንን ነፃነት ተጠቅሞ የተስፋፋ ይሁን እንጂ እግሩን  በአገሪቱ ውስጥ ካሳረፈ ብዙ አሥርተ ዓመታት አልፈዋል፡፡

በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን

ቀደም ሲል እንደገለፅነው ፋሺስት ኢጣሊያ ሙስሊሞች የሐጅ ጉዞ እንዲያደርጉ ያበረታታ ነበር፡፡ በገንዘብም በመደጎም ይልክ ነበር፡፡ በ1933 ለሐጅ ወደ መካ የተጓዙት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 11 ብቻ ሲሆን ከ1934-1935 የሄዱት 29፣ ከ1935-1936 ደግሞ 7 ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ነገር ግን በ1937 ይህ ቁጥር ወደ 1,700 አድጓል፡፡ ሁሉም ደግሞ በኢጣሊያ መንግሥት ድጎማ የሄዱ ነበሩ፡፡[1] ሳዑዲ አረብያ ለሐጅ የሚሄዱትን ኢትዮጵያውያን በወሃቢዝም ፍልስፍና አጥምቃ ወደ አገር ውስጥ በማስረግ ፍልስፍናውን የማስፋፋት ሥራዋን የጀመረችው ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ከመውረሯ በፊት ነበር፡፡ በተለይም ደግሞ ሼኽ ዩሱፍ አብደል ረህማንና ሐጂ ኢብራሂም ሐሰን የተሰኙ ሁለት ሰዎች ለዚህ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለቱም ወደ ሳዑዲ የተጓዙት በ1930ዎቹ መጀመርያ አካባቢ ነበር፡፡ ሼኽ ዩሱፍ በ1939 ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በሐረር ከተማ የወሃቢዝም ትምህርታቸውን ማስተማር የጀመሩ ሲሆን የሐረርን ከተማ የቀድሞ ነፃነት ለመመለስ የከተማይቱን ሙስሊም ሊቃውንት አደራጅተው ፊርማ በማሰባሰብ በወቅቱ የብሪቲሽ የአካባቢው አማካሪ ለነበሩት ለኮሎኔል ዳላስ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ነገር ግን ኮሎኔሉ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርገዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ነበር ሼኽ ዩሱፍ ለረጅም ጊዜ ትግል መሠረት ለመጣል የወሰኑት፡፡ ከዚያም ብሔራዊ እስላማዊ ማሕበር (አል-ጀማዒያ አል-ወኒያ አል-ኢስላሚያ) ወይም አል-ዋታኒ የተሰኘ ማሕበር በማቋቋም መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ የማሕበሩ አባላት በሙሉ ሐረርን “ከኢትዮጵያ ቅኝ” ነፃ በማውጣት አሕመድ ግራኝ ባስቀመጠው ምሳሌነት መሠረት እስላማዊ መንግሥት እንደገና ለማቋቋም ቃል ኪዳን ገቡ፡፡ የሐረርን ሕዝብ በሚገባ ሳያስተምሩ መንግሥትን መጋፈጥ እንደማይቻል ስለተገነዘቡም ዋታኒ እስላማዊ ማሕበር ቀደም ሲል የተሠራውን ትምህርት ቤት በመጠቀም እስላማዊውን ትምህርት በማስተማር ላይ እንዲያተኩር ተወሰነ፡፡ ትምህርት ቤቱም ዘመናዊ መልክ ኖሮት አረብኛና በሐጂ ኢብራሂም ሐሰን አማካይነት ደግሞ የወሃቢዝም ትምህርት እንዲሰጥ ተባለ፡፡ ሐጂ ኢብራሂምም በከፍተኛ ትጋት በየምሽቱ በቤታቸውም ጭምር ይህንን ፍልስፍና ማስተማር ተያያዙ፡፡ የግራኝ ታሪክና ወታደራዊ አካሄድ እንደ አንድ ዋና ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡ ዋታኒ እስላማዊ ማሕበር በሚያዘጋጃቸው ክብረ በዓላት ላይ በአሕመድ ግራኝ ዙርያ የሚያጠነጥኑ ግጥሞችና የውዳሴ መዝሙሮችም ተዘጋጅተው በተማሪዎች ይዘመሩ ነበር፡፡ ሼኽ አብደል ረህማን ደግሞ በአዲስ አበባ ውስጥ በነበራቸው የመጻሕፍት መደብር አማካይነት በአረብኛ የተዘጋጁ የወሃቢያ መጻሕፍትን እያስመጡ ያከፋፍሉ ነበር፡፡ ኋላ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ሆነው የተሾሙት ከበደ ሚካኤል ትምህርት ቤቱን በጎበኙበት ወቅት ለግራኝ የሚዜሙትን መዝሙሮች ትርጉም ከሰሙ በኋላ እንዳይዘመሩ ያገዱ ሲሆን አማርኛም የመማርያ ቋንቋ እንዲሆን ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር፡፡[2]

ሼኽ አብደላህ አል-ሐረሪ

ነገር ግን ከመንግሥት ይልቅ የዋሃቢዝም ዋና ጠላት የነበሩት ሼኽ አብደላህ ኢብን ሙሐመድ ኢብን ዩሱፍ (አብደላህ አል-ሐረሪ) የተሰኙ ሙስሊም ሊቅ ነበሩ፡፡ እኚህ ሰው የአገራችን አብዛኛው ሙስሊም የሚከተለው በአንፃራዊነት ሰላማዊ ሊባል የሚችለው የሱፊ እስልምና ተከታይ ሲሆኑ ከፀረ ሰላም ትምህርቱ በተጨማሪ አሁን በዝርዝር የማናያቸውን የወሃቢዝም አስተምህሮዎች ይቃወሙ ነበር፡፡ ሼክ አብደላህ ከሐረር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ውሏቸውን በመርካቶ አካባቢ በማድረግ ሙስሊሙን ህብረተሰብ በማስተማር ዝነኛ ሆነው ነበር፡፡ ኋላም ወደ ሊባኖስ በማቅናት በመካከለኛው ምስራቅ ትምህርታቸውን በማስፋፋት በዓለም ላይ ዋነኛ ፀረ ወሃቢዝም ለሆነው ዓለም አቀፍ እስላማዊ ማሕበር ሊቀ መንበር ሆነዋል፡፡[3] የኚህን ኢትዮጵያዊ ትምህርት አረቦች “አሕባሽ” በማለት ይጠሩታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሐጂ አብደላህ ከሐበሻ ምድር የመጡ መሆናቸው ነው፡፡ ትምህርቱ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት የኖረውና አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝበ ሙስሊም የሚከተለው የሱፊ እስልምና እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ትምህርቱን የተቀበሉና ከኢትዮጵያዊው የተማሩ ሊቃውንት ስልጠናዎችን ለመስጠት ከሊባኖስ በመጡበት ወቅት ወሃቢዮች “መንግሥት አሕባሽ የሚባል አዲስ ሃይማኖት አመጣብን” በማለት ሁከት መፍጠር ጀመሩ፡፡ እነርሱ ባለ አገር ሆነው የአገሪቱን የሱፊ ሊቃውንት ማሳደድና መግደል ተያያዙ፡፡

ሼኽ አብደላህ በአንድ ወቅት በሐረር ውስጥ በነበረው የወሃቢዮች ትምህርት ቤት ላይ ባስነሱት ተቃውሞ ምክንያት ለእስር ተዳርገው ነበር፡፡ አዲስ አበባ በነበሩበት ጊዜ ሐጂ ኢብራሂም ለአንድ የአረብኛ ጋዜጣ በጻፉት መጣጥፍ ክርስቲያናዊት ኢትዮጵያንና ንጉሡን ማጣጣላቸውን ለመንግሥት መረጃ እንደሰጡም ይነገራል፡፡ በዚህም ምክንያት ሐጂ ኢብራሂምና የትምህርት ቤቱ የወሃቢያ መምህራን ታስረው ለፍርድ የቀረቡ ሲሆን ሐጂ ኢብራሂም ከሐረር ከተማ ወደ ሌላ የኢትዮጵያ ክፍል ሄደው እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል፡፡ እኚህ ሰው አሁን በሕይወት የሉም፡፡ ኋላ ላይ ሼኽ አብደላህ የሐረር ከተማ ሙፍቲ ሆነው በመሾማቸው ምክንያት ወሃቢዮች ድምፃቸውን አጥፍተው ለመኖር የተገደዱበት ሁኔታ ነበር፡፡ የሐረር ወሃብዮች በ1948 “የሶማሌ ወጣቶች ክበብ” ተብሎ በመንግሥት ፈቃድ በተቋቋመው ቡድን ውስጥ እጃቸውን አስገብተው የነበረ ሲሆን የአሕመድ ግራኝ “መንፈስ” እንደገና በመምጣት ከተማይቱ ላይ አንዣቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ይፋ በመሆኑ ጥር 1948 ዓ.ም. 200 የሚሆኑ የክበቡ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ ወጣቶቹ ይቅርታ በመጠየቅ የተፈቱ ሲሆን 81 የሚሆኑ የወሃቢያን እንቅስቃሴ የሚመሩ የዋታኒ ማሕበር አባላት ከተማይቱን በመልቀቅ እንዲበተኑ ተደርጓል፡፡ በዚሁ ዓመት ኢትዮጵያ የኦጋዴን ግዛቷን በማግኘቷ ምክንያት በሐረር ላይ ያላት ሙሉ ቁጥጥር እውን ስለሆነ በ1936 በሐረር ከተማ የተጀመረው በወሃቢዝም የተመራው የእስላማዊ ፖለቲካ መነቃቃት ሊከሽፍ ችሏል፡፡[4] 

በዘመነ ደርግ

የደርግ መንግሥት ባጠቃላይ ሃይማኖትን በተመለከተ ይከተል ከነበረው ፖሊሲ የተነሳ ያን ያህል የጎላ የወሃቢዝም እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ውስጥ ለውስጥ የተሠሩ ሥራዎች እንደነበሩ እሙን ነው፡፡ በ1958 ከየመን በመጣ ስደተኛ የተመሠረተው የአል-አወልያ ትምህርት ቤት በዘመነ ደርግ ጥብቅ በሆነ የመንግሥት ቁጥጥር ስር ነበር፡፡[5] ደርግ ወደ መውደቂያው አካባቢ “የሰርገኛ መጣ…” ዓይነት የፖሊሲ ለውጦችን በማድረጉ ምክንያት ለሳዑዲ እንቅስቃሴዎችም በር ከፍቶ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት የዓለም የሙስሊሞች ሊግ ከእርዳታ ማስተባበርያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን (እማማኮ) ጋር በመተባበር ትምህርት ቤቶችን፣ እጓለ ሙታንንና ክሊኒኮችን ለማቋቋም ስምምነት አደረገ፡፡ መንግሥትና ሊጉ ያላቸው ግንኙነት መጥበቁን ከሚያመለክቱ ተግባራት መካከል አንዱ ሊጉ የሃይማኖትና የአረብኛ ቋንቋ ሥልጠናዎችን እንዲሰጥ መፈቀዱ ነበር፡፡ በ1991 ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት የመጣው የሊጉ ልዑካን ቡድን በወሎ፣ በሐረር፣ በአዲስ አበባና በደብረ ዘይት ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ሥራ ላይ መሆኑን መግለፁ ኢትዮጵያን የማስለም እንቅስቃሴው በአዲስ መልክ መጀመሩን አመላካች ነበር፡፡[6]

በዘመነ ኢህአዴግ

ከ1991 ወዲህ የተደረገውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ በአገራችን ውስጥ የተገኘውን የእምነት ነፃነት ሽፋን በማድረግ ብዙ ጥፋቶች ተፈፅመዋል፡፡ በተለይ የወሃቢዝም ፍልስፍና ተከታዮች ነፃነቱ የሰጣቸውን ክፍተት በመጠቀም የማንይደፍረኛል ፅንፈኛ ትምህርቶችን በማስተማር  ግርምቢጠኛ ባህርያቸው ከልክ አልፎ በሚያሰራጯቸው ጽሑፎችና የድምፅ እንዲሁም የምስል መልዕክቶች ሌሎች ሃይማኖቶችን በነገር በመጎሽመጥ አገሪቱን ሲያምሱ ቆይተዋል፡፡ የተሰጣቸውን የመንግሥት ሥልጣን ለእምነታቸው ማስፋፍያ በመጠቀም ብዙ በደሎችንም የፈፀሙ ባለሥልጣናት ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት ከውጪ አገራት በገፍ በመግባት አገሪቱን ያጥለቀለቁት የጂሃድ ፊልሞችና አክራሪነትን የሚሰብኩ የህትመት ሥራዎች ያስከተሉት ውጤት በገሃድ ታይቷል፡፡ በተለይ ከሳዑዲ አረብያ በሚመጣው የነዳጅ ዶላር የተገነቡት መስጊዶችና እስላማዊ ማዕከላት  አገሪቱን እንደሙጃ ውጠዋታል፡፡ በበጎ አድራጎት ሥም ወደ አገር ውስጥ የገቡ በርካታ እስላማዊ ድርጅቶችም ውስጥ ለውስጥ ጂሃዳውያንን እያሰለጠኑና የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ  አገሪቱን ወዳልተጠበቀ አደጋ መርተዋታል፡፡ የሂደቱ ገደብ አልባነት እንደ አነሳሱ ቢቀጥል ኖሮ  ሊከተል የሚችለውን አደጋ ማሰብ በእጅጉ ይዘገንናል፡፡ አደጋውን ከማስቀረት አንፃር መንግሥት ይበል የሚያሰኙ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ በተለይም የወሃቢዝም ዋነኛ የርቢ ማዕከል የሆነው አል-አወልያ እስላማዊ ትምህርት ቤት ከወሃቢዮች እጅ ወጥቶ ለተገቢው አካል መሰጠቱ ይበል የሚያሰኝ ነበር፡፡ ከአንደኛ ደረጃ ተነስቶ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪቃም ጭምር ግምባር ቀደም እስላማዊ ትምህርት ቤት ለመሆን የበቃው ይህ የፅንፈኞች ማዕከል በአገሪቱ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የተወሰደው እርምጃ ከረፈደ በኋላ ቢሆንም ነገር ግን ከመሸ በኋላ አለመሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡

——————————–

[1] Erlich. Saudi Arabia & Ethiopia; p. 73

[2] Ibid., 80-83

[3] Ibid., 84

[4] Ibid., 85-92

[5] Ibid., 189-190

[6] ኤፍሬም እሸቴ፡፡ አክራሪ እስልምና በኢትዮጵያ፤ 2000፣ ገፅ 142-143

 

እስልምናና ሽብርተኝነት