አስደናቂ ፍቅር
ሙቲዓ አል-ፋዲ
እኔ የቀድሞ ወሃቢ ሙስሊም ስኾን ተወልጄ ያደግሁት በሳዑዲ አረብያ በሚኖር ሙስሊም ቤተሰብ ውስጥ ነበር፡፡ ለሃይማኖቴ ያደርኩና እያንዳንዱን የእስልምና አስተምሕሮ በያንዳንዱ የሕይወቴ ገፅታ ላይ ለመተግበር የምተጋ ፅኑ ሙስሊም ነበርኩ፡፡ እስልምና በምድር ላይ የመጨረሻው እምነት መኾኑን፤ በፈጣሪ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ብቸኛ ሃይማኖትና ወደ ሰማይ የሚወስድ ብቸኛ መንገድ መኾኑን፤ እስልምናን ያልተቀበሉ ወገኖች ወደ ገሃነም እንደሚወርዱና አላህን እንደ አምላካቸው፣ ሙሐመድን ደግሞ እንደ መልእክተኛው ካልተቀበሉት በስተቀር ሥራቸውና አምልኳቸው ሊያድናቸው እንደማይችል፤ ደህንነት በእስልምና በሥራ የሚገኝ መኾኑንና ለአላህ ክብር ሲጋደሉ ከሞቱት ሙስሊሞች በስተቀር ሌሎቹ ዋስትና እንደሌላቸው፤ ሙስሊሞች የሌሎች ሕዝቦች የበላዮች መኾናቸውን፤ ክርስቲያኖችን ጨምሮ ሙስሊም ያልኾኑት በሙሉ ከሃዲያን መኾናቸውን፤ ክርስቶስ ሰው ብቻና በአላህ የተላከ ነቢይ መኾኑን፤ አምላክ ወይንም የፈጣሪ ልጅ አለመኾኑን፤ አለመሰቀሉን፣ በመስቀል ላይ አለመሞቱንና አለመነሳቱን፤ ይልቁኑ ወደ ሰማይ ማረጉንና በመጨረሻው ዘመን እስልምናን ለመመለስ፣ መስቀልን ለመሰባበር፣ ደጃልን ለመግደልና ክርስቲያኖችን ወደ እስልምና ለመመለስ ተመልሶ እንደሚመጣ አምን ነበር፡፡ ነገር ግን ከልጅነቴ ጀምሮ ከተማርኳቸው ትምሕርቶች ኹሉ ይልቅ በልቤ ውስጥ ጠልቆ የገባው አላህን የማያመልኩትን፤ ሙሐመድን የማይከተሉትንና እስልምናን የማይቀበሉትን ክርስቲያኖችና አይሁድን የመሳሰሉትን ወገኖች በሙሉ መጥላት ነበር፡፡ በግልፅ አባባል ለማስቀመጥ የክርስቶስ ጠላት ኾኜ ስኖር ነበር፡፡
ዕድሜዬ 12 ሲኾን የሙስሊሞች ቅዱስ መጽሐፍ የኾነውን ቁርኣንን በከፊል መሸምደድ ችዬ ነበር፡፡ ቁርኣንን መሸምደድ የተወሰኑ ኃጢአቶቼን እንደሚሸፍንልኝ፤ በፍርድ ቀን ከመልካም ሥራዎቼ ጋር እንደሚደመርልኝና በገነት ያለኝን ደረጃ ከፍ እንደሚያደርግ ስለተማርኩኝ ሙሉ በሙሉ የመሸምደድ ግብ ነበረኝ፡፡
በ1980ዎቹ ውስጥ ከኦሳማ ቢንላደን ጎን በመሰለፍ የሶቪየት ሕብረትን ለመዋጋት ከሚጓዙት ወጣቶች ጋር በመሄድ ለአላህ ስም ለመሞት ዝግጁ ኾኜ ነበር፡፡ በአላህ ስም የሚሞቱትን ሙስሊሞች የሚጠብቃቸው ሽልማት እጅግ ከፍ ያለ እንደኾነ አምን ስለነበር ወላጅ እናቴ በብዙ ልመና ባታስቀረኝ ኖሩ ለመሄድ ዝግጁ ነበርኩኝ፡፡ በአላህ መንገድ ለመጋደል በመምረጥ የሞቱት ሙስሊሞች ኃጢአታቸው ኹሉ ተሰርዞላቸው በቀጥታ ወደ ገነት እንደሚገቡና ሌሎች ከሚቀበሉት በእጅጉ የላቀ ሽልማት እንደሚቀበሉ አምን ነበር፡፡
ኾኖም እድሜዬ ጨምሮ አሥራዎቹን ወደ ማገባደጃ አካባቢ ስደርስ የቁርኣንን ንግግር የበለጠ እየተረዳሁ መጣሁ፡፡ አማኝ ያልኾኑትን ወገኖች በተመለከተ ጥላቻን የሚያስተምሩ የቁርኣን ክፍሎች ምንም ረፍት ሊሰጡኝ አልቻሉም፡፡ የጥላቻ መለእክቶቹን ካለመውደዴም በላይ ላጸድቃቸውም ኾነ ልረዳቸው አልቻልኩም ነበር፡፡ ፈጣሪ ፍጥረታቱ ስላልተቀበሉት ብቻ ዝም ብሎ ይጠላቸዋል የሚለው ሐሳብ ሊዋጥልኝ አልቻለም ነበር፡፡ የፈጣሪ ደግነትና ፍቅር ከዚያ የላቀ መኾን እንደሚገባው ማሰብ ጀመርኩኝ፡፡ ነገር ግን እንዲያ ያለውን እምነቴን ለሌሌች ሰዎች መንገር ብዙ ችግሮች ውስጥ እንድገባ የሚያደርግና በደህንነቴ ላይ አደጋን የሚደቅን በመኾኑ (አላህን መጠራጠርና እርሱን መካድ እንዲሁም እስልምናን መልቀቅ በሞት ስለሚያስቀጣ) ለማንም ሳልነግር ቆየሁ፡፡
በሳዑዲ አረብያ ውስጥ የኮሌጅ ትምህርቴን ካጠናቀቅሁኝ በኋላ ወደ ምዕራብ አገራት በመሄድ የመማር ሐሳብ ነበረኝ ነገር ግን ይህ ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ እንድገባ አደረገኝ፡፡ እዚህ አጣብቂኝ ውስጥ እንድገባ ያደረገኝ እስልምና ሙስሊሞች ክርስቲያኖችና አይሁድን ወዳጅ አድርገው እንዳይይዙ መከልከሉና ሙስሊሞች ደግሞ ምዕራባውያንን ክርስቲያኖችና አይሁድ እንደኾኑ ማሰባቸው ነው፡፡ ሙስሊሞች የሚያምኑት ልክ እነርሱ እስልምናን በውርስ ከወላጆቻቸው እንዳገኙት ኹሉ ምዕራባውያንም ደግሞ ክርስትናን በዚያው መንገድ ማግኘታቸውን ነው፡፡
በ1980ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ወደ ምዕራቡ ዓለም የሄድኩ ብኾንም ከክርስቲያኖች ጋር ተግባቦት በመፍጠሬ ሳብያ (ሱራ 5፡51 እና 5፡57 ላይ እንደተመለከተው) ከመልካም ሥራ እንዳልጎድል የሚል ከፍተኛ ፍርሃት አደረብኝ፡፡ ነገር ግን የተሻለውን ዕውቀት ለመቅሰም ወደ ምዕራቡ ዓለም በመጓዝ ከዩኒቨርሲቲዎቻቸው መካከል በአንዱ ውስጥ መማር እንደነበረብኝ አውቅ ነበር፡፡
በዩኒቨርሲቲ የመኖርያ ክፍል ውስጥ ለአንድ ወር ያህል ከኖርኩኝ በኋላ የሄድኩበትን አገር ባሕልና የኑሮ ዘይቤ ማወቅ እንዳለብኝ አመንኩኝ፡፡ በተጨማሪም እንግሊዘኛን በሚገባ የማውቅ ብኾንም ነገር ግን በምዕራባውያን አገራት የሚነገረው የየዕለት ተግባቦት እንግሊዘኛ ብዙ ፈሊጣዊ ንግግሮችን ከመጠቀሙ አኳያ ለመረዳት አስቸጋሪ መኾኑን ተገነዘብኩኝ፡፡ ከዚያ ቀደም ግን እንግሊዘኛ ችግር ይኾንብኛል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ኹኔታ እግዚአብሔር አምላክ ካለሁበት ወጥቼ ወደሚቀጥሉት ደረጃዎች እንድሸጋገር ለኔ ያዘጋጀውን ዕቅድ የማስፈጸምያ መንገድ ነበር፡፡
በወቅቱ ከሌሎች አገራት የመጡ ተማሪዎች የአገሩን ባሕል እንዲያውቁና የእንግሊዘኛ ችግራቸውን እንዲቀርፉ ለማስቻል የታለመ ተማሪዎችን ከምዕራባውያን ቤሰቦች ጋር የሚያቆራኝ መርሃ ግብር መኖሩን ሰማሁ፡፡
ያ ተቋም ግን ክርስቲያናዊ ተቋም መኾኑን አላውቅም ነበር፡፡ ያንን ባውቅ ኖሮ በምንም ተዓምር ከእነርሱ ጋር አልቀላቀልም ነበር፡፡ ነገር ግን ተመዘገብኩኝ፡፡ ያ ውሳኔዬ ማንነቴን የቀየረና የሕይወቴን አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ የለወጠ ውሳኔ ኾነ፡፡
ለዚያ መርሃ ግብር ከተመዘገብኩኝ ከሁለት ሳምንታት በኋላ የኾኑ ወጣት ቤተሰቦች ወደኔ በመምጣት በሚያስፈልገኝ ነገር ኹሉ ሊረዱኝ የተመደቡት እነርሱ መኾናቸውን አስታወቁኝ፡፡ ለሚቀጥሉት ሰባት ወራት እኒያ ቤተሰብ ከዚያ ቀደም አስቤው በማላውቀው የፍቅር መጠን ወደዱኝ፡፡ እንደዚያ ያለ ፍቅር አግኝቼ አላውቅም ነበር፡፡ በሙስሊም ወገኖቼም ዘንድ አላየሁም፡፡ በዙርያቸው ካሉት ኹሉ ለየት የሚያደርጋቸው የሰላም ድባብ ነበራቸው፡፡ በዙርያዬ የነበሩት በሙሉ ክርስቲያኖች ከኾኑ ይህ ቤተሰብ ግን ስለምን ተለየ? ስለዚህ ይህ ቤተሰብ ክርስቲያን ሊኾን አይችልም ብዬ አሰብኩኝ፡፡
በዚያው ዓመት ማገባደጃ አካባቢ ቤተሰቡ የምስጋና ጊዜ ስለነበራቸው በቤታቸው እራት ጋበዙኝ፡፡ ክርስቲያኖች መኾናቸውን ያወቅሁት በዚያን ዕለት ነበር፤ ምክንያቱም ሲጸልዩ ጸሎታቸውን አዳምጬ ነበርና፡፡ ያንን ባወቅሁበት ቅፅበት ድንጋጤ አደረብኝ፡፡ ክርስቲያኖች በሃይማኖቴ ከተነገረኝ በተጻራሪ እንደዚያ የፍቅር ሰዎች ይኾናሉ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ እኒያ ቤተሰብ የወንጌልን መልእክት በአንደበታቸው አልነገሩኝም ነበር ነገር ግን ክርስቶስን በምግባራቸውና በኑሮ ዘይቤያቸው አሳዩኝ፡፡ (ጸጥ ያለ ምስክርነት ነበር)፡፡ በዚያች ዕለት ስለ እምነቴና ስለምከተለው ትምህርት ትልቅ ጥርጣሬ አድሮብኝ ከቤታቸው ወጣሁ፡፡ በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ እንዲህ ያለውን ታላቅ ለውጥ ያመጣውን የክርስቶስን ትምህርት ለማወቅ ክርስትናን ማጥናት እንዳለብኝም ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁኝ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የሚታይ ሰላምና ፍስሐ፤ ከዚያ ቀደም አይቼውና አስቤው የማላውቀውን ከውሳጣቸው የሚፈልቅ አንጸባራቂ ብርሃን ለማወቅ ወሰንኩኝ፡፡
ከስድስት ዓመታት በኋላ ከኮሌጅ ተመርቄ ስወጣ በአካባቢው የሚገኝ የሥራ ተቋራጭ ውስጥ ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩኝ፡፡ እዚያም እውነተኛ የክርስትና ሕይወት የሚኖር አንድ ግሩም ክርስቲያን አገኘሁኝ! በእምነቱ፣ በኑሮው፣ በደስታው፣ በሰላሙና ከውስጡ በሚወጣው ብርሃን በእጅጉ ተደመምኩኝ፡፡ በዙርያው ከሚገኙት ሰዎች ኹሉ ለየት ያለ ሰው ነበር፡፡ ለክርስቶስ ልደት እራት በቤቱ በጋበዘኝ ዕለት ባለቤቱና ልጆቹም ጭምር ልክ እንደ እርሱ መኾናቸውን ተገነዘብኩኝ፡፡
የመጀመርያው ዘር በልቤ ውስጥ እንዲዘራ ካደረጉት በኮሌጅ ሳለሁ ካገኘኋቸው ቤተሰቦች ጋር ተመሳሳይ ነበሩ፡፡ ጉጉቴ ስለበረታ በዙርያው ከሚገኙት ሰዎች ለምን ለየት ሊል እንደቻለ ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ከዚያም የሕይወት ምስክርነቱን በከፊል ካወጋኝ በኋላ ዳግመኛ የተወለደ ክርስቲያን መኾኑን አመለከተኝ፡፡ (በወቅቱ ግን ትርጉሙ እምብዛም አልገባኝም ነበር፡፡) ክርስቶስን አዳኙና የሕይወቱ ጌታ አድርጎ በመቀበሉ ምክንያት የግል ልፋቱ ሳይታከልበት አሁን የኾነውን እንደኾነ ነገረኝ፡፡ በሕይወቱ ላይ እያየሁት የነበርኩት መልካም ፍሬ የእግዚአብሔር መንፈስ ሥራ ውጤት መኾኑን አመለከተኝ፡፡ እንዳለፈው ቤተሰብ ኹሉ ወንጌልን በቀጥታ ባይነግረኝም ኢየሱስ የሰላሙና የፍቅሩ ምንጭ መኾኑ ግልፅ ነበር፡፡
የሰዎችን ሕይወት እንዲህ የመቀየር አቅም ያለው የክርስቶስ ፍቅር ልቤ ውስጥ ገባ፡፡ የነቢያት መደምደሚያና የአላህ ተወዳጅ እንደኾነ ከማምነው ከኔ ነቢይ በእጅጉ የላቀ ኃይል ነበረ፡፡ ለሃይማኖቴ ያደርኩ ሰው ብኾንም ከነዚህ ሰዎች ጋር የሚነጻጸር ሰላም ግን አልነበረኝም፡፡ በራሴ ማፈርና መሸማቀቅ ጀመርኩኝ፡፡ በውስጤ የሚገኘውን ጥፋት የሚያሳዩኝ መስታወት ነበሩ፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጌታ በብዙ የሕይወት ፈተናዎች ውስጥ እንዳልፍ አደረገኝ፡፡ በነዚህ ፈተናዎችም ምክንያት የበለጠ እርሱን የማወቅ ፍላጎት አደረብኝ፡፡ ምክንያቱም እኔ የማመልከው አምላክ የትም ሊገኝ እንደማይችል ግልፅ ኾኖልኝ ነበርና፡፡
2000 ዓ.ም. መጀመርያ ላይ ወደ ቤተክርስቲያን ለመኼድ ወሰንኩኝ፡፡ (ይህ እንግዲህ የእስልምና እምነቴ ያስተማረኝን በሙሉ የሚጻረር ነው፡፡ ሙስሊሞች ወደ ቤተክርስቲያን መኼድ አይፈቀድላቸውም ምክንያቱም እንዲያ ማድረግ ገነትን ሊያሳጣ የሚችል ከባድ ጥፋት ነውና፡፡) ለስድት ወራት ያህል በቤተክርስቲያን የዮሐንስን ወንጌል ካጠናሁ በኋላ ክርስቶስ ማን መኾኑን ተረዳሁ፡፡ ቀስ በቀስም አምላክነቱ እየተገለጠልኝ መጣ፡፡ የደህንነትም መልእክት እየገባኝ መጣ፡፡ ምን ያህል ደካማ ሰው እንደሆንኩና ደህንነት ምን ያህል እንደሚያስፈልገኝ ተረዳሁ፡፡
በመጨረሻም ጥርጣሬዬ ኹሉ ተወግዶልኝ ክርስቶስን አምኜ የሕይወቴ ጌታ አድርጌ ተቀበልኩ፡፡ የክርስቶስና የክርስትና ተቃዋሚ ከመኾን ዳግም ልደትን ያገኘ ክርስቲያን ኾኜ ጌታና አዳኝ የኾነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ከማገልገል ወደ ኋላ የማይል ቆራጥ ክርስቲያን ሆንኩኝ፡፡
ክርስትናን በተቀበልኩ በጥቂት ወራት ውስጥ ውድ ከኾነው ጌታዬ ጋር የግል ሕብረት ማድረግ ምን እንደሚመስል አወቅሁኝ፡፡ በሕይወቴ ውስጥም እርሱን ለማወቅ ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ ተደገፍኩኝ፡፡ በዚህ ጊዜም ሐልዎቱንና በሕይወቴ ውስጥ ያደረገውን መልካም ሥራ መካድ በማልችልበት ኹኔታ አስደናቂ ክብሩ በአስገራሚ መንገዶች በሕይወቴ ውስጥ ገልጧል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሕይወቴ ሙሉ በሙሉ ስለተለወጠ ከዚያ ቀደም የነበርኩትን ሰው አይደለሁም፡፡ ትዕቢተኛ፣ በገዛ ጽድቁ የሚመካና ኩራተኛ ሰው መኾኔ ቀርቷል፡፡ በዙርያዬ የሚገኙ ሰዎች በግልፅ ማየት እስኪችሉ ድረስ ልቤ መልካም በኾነ ልብ ተለውጦ አዲስ ፍጥረት ኾኛለሁ፡፡ ነገሩ ኹሉ ልክ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ እግዚአብሔር በመምጣት የእርሱን ጌትነት ስለተቀበሉት ሰዎች እንደሚናገረው ነው፡-
“በትእዛዜም ይሄዱ ዘንድ ፍርዴንም ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ፥ በውስጣቸውም አዲስ መንፈስ እሰጣለሁ፥ ከሥጋቸውም ውስጥ የድንጋዩን ልብ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።” – ሕዝቅኤል 11፡19-20
ከዛሬ 2500 ዓመታት በፊት በዚህ ጥቅስ ውስጥ የተባለው ነገር በኔና ጌታን በተከተሉት ሰዎች ኹሉም ውስጥ ሲፈጸም ማየት ምንኛ አስደናቂ ነው፡፡ ልክ እኔ እንዳስተዋልኩት ኹሉ በጌታ የሚያምኑ አማኞች አንድ ልብና አንድ መንፈስ አላቸው፤ ልባቸውም በኔ እንደኾነው ኹሉ ድንጋይ ከመኾን ለስላሳ ወደመኾን በእግዚአብሔር ኃይል ይቀየራል፡፡ ይህ ልምምድ አንዳንዶች እንደሚሉት ስሜታዊ በመኾን ምክንያት የሚፈጠር ጊዜያዊ ለውጥ ሳይኾን እውነተኛና ተጨባጭ ለውጥ ስለመኾኑ ለኔ በቂ ማስረጃ ነው፡፡
የወንጌል መልእክት ክርስቶስን ስፈልግ በነበርኩባቸው ዘመናት እንዳልተነገረኝና ወደ ክርስቶስ እስከመጣሁበት ጊዜ ድረስ ሙሉ በሙሉ አለመስማቴን ቀደም ሲል መግለጼን አስታውሱ፡፡ ክርስቶስን የወደድኩበት ፍቅር የዚያን ያህል ጥልቅ ነበር፡፡ ሕይወቴ የተለወጠው ሁለት ቤተሰቦች በጌታ በታዘዙት መሠረት ፍቅርን ስላሳዩኝ ነበር፡-
ማቴዎስ 5፡14-16 “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።”
ቀለል ባለ የፍቅር ተግባር ውዱ ጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስ ማወቅ ቻልኩኝ፡፡ በእነርሱ ፍቅር አማካይነት የሰማዩ አባታችን ከበረ፤ ወደፊትም ይከብራል፡፡ ብዙ ጊዜ ፍቅር ለኛ የተሰጠ ታላቁ ትዕዛዝ መኾኑን የሚናገረውን ቀለል ያለ የወንጌል መልእክት እንዘነጋለን፡፡ መልእክቱ ክርስትና ሳይኾን ክርስቶስ መኾኑን፤ በዙርያችን ለሚገኙት ወገኖች መልእክቱን የማድረሻ መንገዶች እኛ መኾናችንን፤ እንዲሁም ይህ መልእክትና ውክልና በዙርያችን ኾነው በሚመለከቱን ሰዎች ሕይወት ላይ ልክ በኔ እንደኾነው ምን ያህል ለውጥን እንደሚያመጣ እንዘነጋለን፡፡
ክርስቶስን ካመንኩበት ጊዜ ጀምሮ መታወሬ ቀርቶ እውነትን ማየት የሚችል ሰው ሆኛለሁ፡፡ ሙስሊም ኾኜ ዕድሜ ልኬን የኖርኩበትን የሐሰት ዓለም ተረድቻለሁ፡፡ እስልምና የሚያስተምረውን የሐሰት ትምህርት፤ ተወዳጅ የኾነው ሙስሊሙ ሕዝቤ አሁንም ድረስ የሚኖርበትንና የሚያምነውን ሐሰት ይበልጥ ተገንዝቤያለሁ፡፡ እነዚህ ውሸቶች ሙሐመድ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል የሚለውን ይጨምራሉ፡፡ ነገር ግን እኔ መጽሐፍ ቅዱስን መርምሬ ሙሐመድ በፍጹም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳልተጠቀሰ አረጋግጫለሁ፡፡ ሌላው ውሸት በቁርኣን ውስጥ ሳይንሳዊ ተዓምራት ይገኛሉ የሚለው ነው፡፡ ይህም ማጭበርበርያ ብቻ መኾኑን አረጋግጫለሁ፡፡ ከነዚህ ተዓምራት ተብዬዎች መካከል አንዱ እንኳ የሳይንስ ሽታ ያለው የለም፤ አከተመ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟል የሚል ሌላ ውሸትም አለ፡፡ ቁርኣን ግን መጽሐፍ ቅዱስ መበረዙን በአንድም ቦታ እንደማይናገር አረጋግጫለሁ፡፡ ይልቁኑ ቁርኣን ከአምላክ ዘንድ ስለመኾኑ ለማረጋገጫነት መጽሐፍ ቅዱስንና የመጽሐፉን ሰዎች በዋቢነት ይጠራል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከተበረዘ ቁርኣን እንዴት ኾኖ ነው መጽሐፍ ቅዱስንና የመጽሐፉን ሰዎች ለምስክርነት የሚጠራው? መጽሐፍ ቅዱስ ስላልተበረዘ ትምሕርቶቹ እውነት ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ጌታ ኢየሱስ እኔን ከኃጢአትና ከሰይጣን እስራት ለመፍታት ወደ ምድር የመጣ አምላክ መኾኑን ይናገራል፡፡ በኔ ፋንታ ስለ ኃጢአቴ በመስቀል ላይ ለመሞት እንደመጣና የዘላለምን ሕይወትና የኃጢአቴን ስርየት ዋስትና ሊሰጠኝ ከሰማይ እንደወረደ ይናገራል፡፡ ኢየሱስ እንዲህ አለ፡-
“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” – ዮሐንስ 3፡16
አሜን፡፡
ውድ ወዳጆቼ፤ በሕይወታችሁ ውስጥ ሕያው አምላክ የኾነውን ክርስቶስን እንደ ጌታና አዳኛችሁ በማመን ለመቀበል እስከ ዛሬ ድረስ ያልወሰናችሁ ከኾናችሁ፤ ዛሬውኑ ይህንን ማድረግ ትችሉ ዘንድ እጸልይላችኋለሁ፡፡ አንዴ ይህንን ካደረጋችሁ የሕይወታችሁን አቅጣጫ የሚቀይር ጉዞ ትጀምራላችሁ፡፡ ነገር ግን ይህንን የመቀበያ ብቸኛው መንገድ አሁኑኑ ወደ ክርስቶስ መቅረብ ነው፡፡ ምክንያቱም ሕይወት አጭር ናትና፡፡ በቀጣዩ ሰከንድ በኛ ላይ የሚኾነው ምን እንደኾነ አናውቅም፡፡
ጥያቄና አስተያየት ካላችሁ ልታገኙኝ ትችላላችሁ፡፡
የሰላም ጌታ እናንተንና የናንተ የኾኑትን ኹሉ ይባርክ፡፡
ሙቲዓ አል-ፋዲ
የትርጉም ምንጭ፡ Amazing Love