ከእስልምና ወደ ክርስትና ፈታኝ ጉዞ
ዶ/ር ማርክ ገብርኤል (ሙስጠፋ)
በአል-አዝሃር ግራ መጋባት
ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት ዝነኞቹ የግብፅ ፒራሚዶች በሚገኙባት ጊዛ በተባለች የግብፅ ከተማ ውስጥ የሚገኝ መስጊድ ኢማም ነበርኩኝ፡፡ (የመስጊድ ኢማም ሥልጣን አንድ መጋቢ በቤተክርስቲያን ውስጥ ካለው ደረጃ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡) አርብ ከቀኑ ስድስት ሰዓት እስከ ሰባት ሰዓት ድረስ የሳምንቱን የስብከት መልዕክት ማስተላለፍንና ሌሎች ኃላፊነቶችን እወጣ ነበር፡፡
አንድ አርብ ቀን የመለዕክቴ ርዕስ ጂሃድ የሚል ነበር፡፡ በፊቴ የተቀመጡትን ሁለት መቶ ስድሳ የሚያክሉ ሰዎችን እንዲህ በማለት ነገርኳቸው፡
በእስልምና ጂሃድ ማለት እስላማዊ የሆነን ሀገርና እስልምናን ከጠላት ጥቃቶች መከላከል ነው፡፡ እስልምና የሰላም ሃይማኖት ስለሆነ የሚዋጋው የሚዋጉትን ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ከሃዲያን፣ አረማውያን፣ ጠማሞች፣ ክርስቲያኖችና አላህን አሳዛኝ የሆኑት አይሁዶች ሰላማዊ በሆነው በእስልምናና በነቢዩ ከመቅናታቸው የተነሳ እስልምና በሰይፍና በሽብር እንደተስፋፋ ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ከሃዲያን፣ የእስልምና ከሳሾች የሆኑት ሰዎች ለአላህ ቃል ዕውቅናን ይነፍጋሉ፡፡
ቀጠል በማድረግም የሚከተለውን የቁርአን ቃል ጠቀስኩኝ፡
ያቺንም አላህ ያወገዛትን ነፍስ ያለ ሕግ አትግደሉ፡፡ የተበደለም ኾኖ የተገደለ ሰው ለዘመዱ (በገዳዩ ላይ) በእርግጥ ስልጣንን አድርገናል፡፡ (ሱራ 17፡33)
እነዚህን ቃላት በተናገርኩበት ጊዜ በዓለም ላይ ከሁሉም የተሻለ ተቀባይነት ካለው እድሜ ጠገብ ከሆነው በግብፅ የካይሮ ከተማ ከሚገኘው የአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ ገና ተመርቄ መውጣቴ ነበር፡፡ የአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለእስልምና መንፈሳዊ የበላይ ጠባቂ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥም ስማር በነበርኩባቸው ዓመታትም በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በዚህ መስጊድ ውስጥ ኢማም ሆኜ አገለግል ነበር፡፡
በዚያን ዕለት ስለ ጂሃድ የሰበክሁት የግብፅን መንግሥት ፍልስፍና በሚያንጸባርቅ መንገድ ነበር፡፡ የአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ባለው እስልምና ላይ በማተኮር ከግብፅ መንግሥት አመለካከት ጋር የሚጋጩ ትምህርቶችን ገሸሽ ያደርግ ነበር፡፡
እነርሱ ያስተማሩኝን እያስተማርኩ ያለሁ ቢሆንም ነገር ግን በውስጤ ስለ እስልምና እውነት ግራ ተጋብቼ ነበር፡፡ በአል-አዝሃር ያለኝን ሥራና ደረጃ ማስጠበቅ ካለብኝ ግን አመለካከቴን ለራሴ ብቻ መያዝ ግድ ይለኛል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከአል-አዝሃር አጀንዳ የተለየ አቋም የነበራቸው ሰዎች የደረሰባቸውን ጠንቅቄ አውቅ ነበር፡፡ በቀጥታ የሚባረሩ ሲሆን በሀገሪቱ ውስት በሚገኝ በማንኛውም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ማስተማር እንዳይችሉ እግድ ይጣልባቸው ነበር፡፡
በመስጊድና በአል-አዝሃር ውስጥ የማስተምረው ነገር ገና የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ ሳለሁ ሙሉ በሙሉ በሸመደድኩት ቁርአን ውስጥ የማየው እንዳልሆነ ይገባኝ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ግራ ያጋባኝ ደግሞ የፍቅር፣ የቸርነትና የይቅርታ እስልምናን እንድሰብክ የተነገረኝ መሆኑ ነው፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ እውነተኛውን እስልምና እንዲተገብሩ የሚጠበቅባቸው አጥባቂ ሙስሊሞች አብያተ ክርስቲያናትን በቦምብ ያጋዩ ነበር፤ ክርስቲያኖችንም ይገድሉ ነበር፡፡
በወቅቱ በግብፅ ውስጥ የጂሃድ እንቅስቃሴ ተጋግሎ ነበር፡፡ በክርስቲያኖች ላይ የሚፈፀሙ የቦምብ ጥቃት ዘገባዎችም የተለመዱ ነበሩ፡፡ ይህ ተግባርም የየዕለት ኑሮ አካል ከመሆኑ የተነሳ አንድ ጊዜ በአውቶብስ ስሄድ ሳለሁኝ ቦምብ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲፈነዳ ሰምቼ ነበር፡፡ አሻግሬም ስመለከትም በግማሽ ማይል ርቀት ቦታ ላይ ጢስ ወደላይ ሲጉተለተል ማየት ችዬ ነበር፡፡
በእስልምና ፅኑ በሆነ ቤተ ሰብ ውስጥ ያደግሁኝ ሲሆን የእስልምናንም ታሪክ አጥንቼ ነበር፡፡ በየትኛውም የፅንፈኛ ሙስሊሞች እንቅስቃሴ ውስጥ አልተሳተፍኩም ነገር ግን ከጓደኞቼ መካከል አንዱ ክርስቲያኖችን በመጨፍጨፍ በሚታወቅ እስላማዊ ቡድን ውስጥ አባል ነበር፡፡ ምፀታዊው ነገር የኬሚስትሪ ተማሪ የነበረ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነበር እምነቱን አጥብቆ የያዘው፡፡ የሆነው ሆኖ ጂሃድ ውስጥ በንቃት ይሳተፍ ነበር፡፡ አንድ ቀን እንዲህ በማለት ጠየቅሁት፡- “አብሮ አደጎቻችን የሆኑትን ጎረቤቶቻችንንና የሀገራችንን ሰዎች የምትገድለው ስለምንድነው?”
በጣም ተናደደ፤ ከጥያቄዬም የተነሳ በጣም ተገረመ፡፡ “ከሁሉም አስቀድሞ እናንተ ሙስሊሞች ይህንን ጉዳይ ማወቅ ነበረባችሁ፡፡ ክርስቲያኖች የእስልማናን ጥሪ አይቀበሉም፤ እምነታቸውን ደግሞ መለማመድ ይችሉ ዘንድ ጂዝያን ለመክፈል ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ ስለዚህ ያላቸው ብቸኛው አማራጭ የእስልምና ሕግ ሰይፍ ብቻ ነው፡፡”
እውነትን ፍለጋ
ከእርሱ ጋር ካደረግሁት ንግግር የተነሳ እርሱ የተናጋረውን የሚቃረን ነገር አገኛለሁ በሚል ተስፋ በቁርአንና በእስላማዊ ሕጎች መጻሕፍት ላይ ትኩረቴን አደረግሁኝ፡፡ ያነበብኩትን እውነታ ግን መለወጥ አልተቻለኝም፡፡
እንደ ሙስሊም ያለኝ አማራጭ ሁለት ብቻ መሆኑን ተገነዘብኩኝ፡-
- “ክርስትና የተነሳውን” እስልምና መከተሌን መቀጠል እችላለሁኝ – የሰላም፣ የፍቅር፣ የይቅርታና የርህራሄ እስልምና – ከግብፅ መንግሥት፣ ፖለቲካና ባሕል ጋር አብሮ እንዲሄድ ተለክቶ የተሰፋውን እስልምና በመከተል ስራዬንና ደረጃዬን መጠበቅ እችላለሁ፡፡
- የእስላማዊ እንቅስቃሴ አባል በመሆን በቁርአንና በመሐመድ አስተምሕሮ መሰረት እስልምናን መከተል እችላለሁኝ፡፡ መሐመድ እንዲህ ብሎ ነበር፡ “ከአንድ ነገር ጋር እተዋችኋለሁ [ቁርአን]፡፡ የተውኩላችሁን ነገር አጥብቃችሁ ከያዛችሁ ለዘለዓለም በተሳሳተ መንገድ አትሄዱም፡፡”
ብዙ ጊዜ ለራሴ እንዲህ በማለት ስተገብር የነበርኩትን እስላማዊ አስተሳሰብ አመክንዮአዊ ለማድረግ እሞክር ነበር፣ አንተ ያን ያህል ርቀህ የሄድክ አይደለህም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በቁርአን ውስጥ ስለ ፍቅር፣ ሰላም፣ ይቅርታና ምህረት የሚናገሩ ብዙ ጥቅሶች አሉ፡፡ ስለ ጂሃድና ሙስሊም ያልሆኑትን ሰዎች ስለመግደል የሚናገሩትን ጥቅሶች ብቻ ችላ ማለት ነው የሚጠበቅብህ፡፡
ጂሃድንና ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎችን መግደልን ለማስወገድ ወደ ሁሉም ዓይነት የቁርአን ፍታቴ ሄድኩኝ ነገር ግን ለድርጊቱ ድጋፍ የሚሰጡ ነገሮችን ማግኘቴን ቀጠልኩኝ፡፡ ሙስሊሞች በከሃዲያን (እስልምናን በማይቀበሉት ሰዎች) ላይና እስልምናን በመተው ወደ ኋላ በሚመለሱት ሰዎች ላይ ጂሃድን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው ሊቃውንት ይስማማሉ፡፡ ነገር ግን የጂሃድ ጥቅሶች ከሰዎች ጋር በሰላም ስለመኖር ከሚናገሩት ከሌሎች ጥቅሶች ጋር አብረው አይሄዱም፡፡
በቁርአን ውስጥ የሚገኙት ተቃርኖዎች በሙሉ ለእምነቴ ችግርን መፍጠር ጀመሩ፡፡ የመጀመርያ ዲግሪዬን ለማግኘት አራት ዓመታትን አጥፍቼአለሁኝ፤ ስድስት ሺህ ተማሪዎችን ከያዘ የትምህርት ክፍል ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቅቄአለሁኝ፡፡ ከዚያም የማስተርስ ዲግሪዬን ለመያዝ አራት ዓመታትና የዶክትሬት ዲግሪዬን ለመያዝ ደግሞ ሦስት ዓመታት ነበሩ፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ እስልምናን ለማጥናት ነበር፡፡ ትምህርቶቹንም እንደዚሁ አውቃቸዋለሁ፡፡
አንድ ቦታ ላይ አልኮል ተከልክሏል ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ተፈቅዷል (ሱራ 5፡90-91 ከሱራ 47፡15 ጋር ያነፃፅሩ)፡፡ በአንድ ቦታ ላይ ቁርአን ክርስቲያኖች እውነተኛውን አንዱን አምላክ የሚያመልኩ በጣም ጥሩ ሰዎች እንደሆኑና ከእነርሱም ጋር መወዳጀት እንደሚቻል ናገራል (ሱራ 2፡62፣ 3፡113-114)፡፡ ነገር ግን ደግሞ ክርስቲያኖች መለወጥ እንደሚኖርባቸው፣ ግብርን መክፈል እንዳለባቸውና ይህ ካልሆነ ግን በሰይፍ መገደል እንዳለባቸው ይናገራል (ሱራ 9፡29)፡፡
ምሑራኑ ለነዚህ ሁሉ ሥነ-መለኮታዊ ምላሽ አላቸው ነገር ግን ከሃሊ ኩሉና ሃያል የሆነው አላህ ለምን እጅግ ከራሱ ጋር እንደሚጋጭ ወይንም ደግሞ ለምን እጅግ አቋሙን እንደሚቀያይር ይደንቀኝ ነበር፡፡
የእስልምና ነቢይ የሆነው መሐመድ እንኳ እምነቱን ይለማመድ የነበረው ቁርአንን በሚቃረን መንገድ ነበር፡፡ ቁርአን እንደሚናገረው መሐመድ የተላከው የፈጣሪን ምህረት ለዓለም ለማሳየት ነው፡፡ ነገር ግን ወታደራዊ አምባገነን በመሆን ጥቃትን ይፈፅም፣ ይገድልና ለግዛቱ የሚሆን የዝርፍያ ገንዘብን ይወስድ ነበር፡፡ ይህ ምህረትን ሊያሳይ የሚችለው እንዴት ሆኖ ነው?
በቁርአን ውስጥ የተገለጠው አምላክ፣ አላህ አፍቃሪ አባት አይደለም፡፡ ሰዎችን በተሳሳተ መንገድ መምራት ይፈልጋል (ሱራ 6፡39፣ 126)፡፡ በእርሱ ወደ ተሳሳተ መንገድ የተመሩትን አይረዳቸውም (ሱራ 30፡29)፡፡ ገሃነምንም ለመሙላት ይጠቀምባቸዋል (ሱራ 32፡13)፡፡
እስልምና በሴቶች ላይ፣ ሙስሊም ባልሆኑት ላይ፣ በክርስቲያኖች ላይና በተለይም ደግሞ በአይሁዶች ላይ አድሎን በማድረግ የተሞላ ነው፡፡ ጥላቻ የሃይማኖቱ አካል ነው፡፡ የእኔ ልዩ የጥናት መስክ የሆነው የእስልምና ታሪክ “የደም ወንዝ” በመባል ብቻ ነው ሊገለፅ የሚችለው፡፡
አደገኛ ጥያቄዎች
በመጨረሻም በዩኒቨርሲቲ ካሉት ተማሪዎቼ ጋር እምነቱንና ቁርአንን ጥያቄ ውስጥ የማስገባት ነጥብ ላይ ደረስኩኝ፡፡ አንዳንዶቹ የሽብርተኛ ቡድኖች አባላት ስለነበሩ በቁጣ ተሞሉ፡፡ “እስልምናን ልትወነጅል አትችልም፡፡ ምን ነካህ? ልታስተምረን ይገባሃል፡፡ ከእስልና ጋር መስማማት አለብህ” ይሉኝ ነበር፡፡
ዩኒቨርሲቲው ስለ ጉዳዩ ስለሰማ ታህሳስ 1991 ለስብሰባ ተጠራሁኝ፡፡ የስብሰባውን ጭብጥ ለማስረዳት ያህል እኔ በልቤ ውስጥ የነበረውን ነገር ነገርኳቸው፡ “ቁርአን ከሰማይ ወይንም ከአላህ ዘንድ የመጣ ነው ብዬ ለመናገር ከእንግዲህ ወዲህ ይከብደኛል፡፡ ይህ የእውነተኛው አምላክ መገለጥ ሊሆን አይችልም፡፡”
በነርሱ አመለካከት እነዚህ ታላቅ የክህደት ቃላት ነበሩ፡፡ በፊቴ ላይ ተፉብኝ፡፡ አንድ ሰው እንዲህ በማለት ሰደበኝ “አንተ ከሃዲ! አንተ ዲቃላ!” ዩኒቨርሲቲው እኔን ከሥራ በማባረር የግብፅን ህቡዕ ፖሊስ ጠራ፡፡
ህቡዕ ፖሊሶች አፍነው ወሰዱኝ
ቀጥሎ ምን እንደተከሰተ ለማወቅ ቤተ ሰቦቼ እንዴት እንደኖሩ ምስሉን ማግኘት ይኖርባችኋል፡፡ አባቴ የሦስት ፎቆች ርዝማኔ ያለው ትልቅ መኖርያ ቤት ነበረው፡፡ ወላጆቼ፣ አራት ያገቡ ወንድሞቼ ከነ ቤተሰቦቻቸው፣ ያላገባ ወንድሜና እኔን ጨምሮ መላው ቤተሰቦቼ በዚህ ቤት ውስጥ እንኖር ነበር፡፡ ባለትዳር እህቴ ብቻ ነበረች ከባሏ ጋር መኖር ስላለባት ሌላ ቦታ ትኖር የነበረው፡፡
ቤቱ በብዙ አፓርትመንቶች የተከፈለ ስለነበር በምቾት ነበር ስንኖር የነበረው፡፡ በመጀመርያው ደረጃ ላይ የወላጆቼ አፓርትመንትና እኔ ከመንድሜ ጋር ተጋርቼ የምኖርበት አፓርትመንት ነበሩ፡፡ ከእኛ በላይ በሚገኙት ደረጃዎች ላይ ደግሞ ሌሎቹ ወንድሞቼ ይኖሩ ነበር፡፡
ዩኒቨርሲቲው እኔን ባባረረበት ዕለት ማለዳ ዘጠኝ ሰዓት ላይ አባቴ የቤታችን በር ሲንኳኳ ሰማ፡፡ ከአስራ አምስት እስከ ሃያ የሚገመቱ የሩሲያ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎችን የታጠቁ ሰዎች ወደ ውስጥ ተንጋግተው ገቡ፡፡ የደንብ ልብስ ሳይሆን ሲቪል ነበር የለበሱት፡፡ ደረጃዎችን እየሮጡ ወደ ላይ በመውጣት ሰዎችን እየቀሰቀሱ እኔን ይፈልጉኝ ነበር፡፡ እንደዚያ በዝተው ወደ ውስጥ የገቡበት ምክንያት እኔን ከማግኘታቸው በፊት ሮጬ እንዳላመልጥ በማሰብ ይመስለኛል፡፡
ከመካከላቸው አንዱ በተኛሁበት አልጋዬ ላይ እኔን ከማግኘቱ በፊት ሁሉም እቤት ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ሰዎቹ እየጎተቱ ሲወስዱኝ ወላጆቼ፣ ወንድሞቼ፣ ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው በሙሉ ያለቅሱ ነበር፡፡ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ሁሉ የተፈጠረውን ግርግር ሰምተው ነበር፡፡
እስር ቤት ወደሚመስል ቦታ ተወስጄ በአንዲት ክፍል ውስጥ እንድገባ ተደረግሁኝ፡፡ ሲነጋም ቤተ ሰቦቼ የደረሰብኝን ነገር ለማጣራት ሞከሩ፡፡ በቀጥታም ወደ ፖሊስ ጣብያ በመሄድ “ልጃችን የት ነው?” በማለት ጠየቁ፡፡ ነገር ግን እኔ ያለሁበትን ማወቅ የቻለ ሰው አልተገኘም፡፡
እኔ በግብፅ ህቡዕ ፖሊስ እጅ ነበርኩኝ፡፡
የግብፅ ወኅኒ
ከግብፅ ህቡዕ ፖሊስ ጋር ጊዜን ማሳለፍ የአሜሪካን እስር ቤት ከመጎብኘት የተለየ ነው፡፡ የሽብር ተግባርን በመፈጸም ከተከሰሱ ሁለት አክራሪ ሙስሊሞች ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ አስገቡኝ፡፡ አንዱ ፍልስጥኤማዊ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ግብፃዊ ነበር፡፡
ለሦስት ቀናት ያህል እህልም ሆነ ውኀ አልተሰጠኝም ነበር፡፡
በየዕለቱ ግብፃዊው ሰው “ለምን እዚህ መጣህ?” በማለት ይጠይቀኝ ነበር፡፡ እኔም እስልምናን መጠራጠሬን ካወቀ ይገድለኛል ብዬ ስለፈራሁኝ ለመመለስ ፍቃደኛ አልሆንኩለትም፡፡ በሦስተኛው ቀን ላይ ግን በአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ መምህር መሆኔንና በጊዛ መስጊድ ደግሞ ኢማም መሆኑን አወጋሁት፡፡ ወድያውኑ ውኀ በፕላስቲክና ጠያቂዎቹ ያመጡለትን ፋላፌል (ከሽምብራ የሚሰራ የመካከለኛው ምስራቅ የባሕል ምግብ) እንዲሁም ቂጣ ሰጠኝ፤ ነገር ግን ምንም ነገር እንዳይሰጠኝ ፖሊሶች አስጠንቅቀውት እንደነበር ነገረኝ፡፡
በሦስተኛው ቀን ምርመራው ተጀመረ፡፡ ለሚቀጥሉት አራት ቀናት የህቡዕ ፖሊስ ግብ እኔን እስልምናን መልቀቄን ማሳመንና ያም ደግሞ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ማውጣጣት ነበር፡፡
ምርመራው የተጀመረው ትልቅ ጠረጴዛ ባለበት ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ እኔና መርማሪው በጠረጴዛው ወዲያና ወዲህ በትይዩ ተቀመጥን፡፡ ከእኔ በስተጀርባ ደግሞ ሁለት ወይም ሦስት ፖሊሶች ነበሩ፡፡
እኔ ወንጌል እንደተመሰከረልኝና ወደ ክርስትና እንደተለወጥኩኝ እርግጠኞች ስለነበሩ፡፡ “ያናገርከው መጋቢ ማን ነበር? ወደ የትኛው ቤት ክርስቲያን ነበር ስትሄድ የነበረው? ለምንድነው እስልምናን የካድከው?” በማለት በተደጋጋሚ ይጠይቀኝ ነበር፡፡
ብዙ ጥያቄዎችን ጠየቀኝ፡፡ አንድ ጊዜ መልስ ለመስጠት ብዙ አቅማማሁ፡፡ ከጀርባዬ የነበሩትን ሰዎች ጠቀሳቸው፡፡ እጄን በመጠምዘዝ ጠረጴዛው ላይ አጣብቀው ያዙኝ፡፡ መርማሪዬ በእጁ ላይ ይዞት የነበረውን የተለኮሰ ሲጋራ እጄ ላይ ተረኮሰው፡፡ እስከ አሁን ድረስ ይህ ጠባሳ በእጄ ላይ አለ፡፡ ተመሳሳይ ነገር ስላደረገብኝ በከንፈሬ ላይም ጠባሳ አለብኝ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሲናደድ ሲጋራውን ይጠቀም ነበር፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ፖሊሶቹ ፊቴ ላይ ይመቱኝ ነበር፡፡
ምርመራው በቀጠለ ቁጥር ተፅዕኖውም ከፍ እያለ መጣ፡፡ አንድ ጊዜ የእሳት መቆስቆሻ ብረት ወደ ክፍሉ ይዘው መጡ፡፡ በውስጤ ለምን ይሆን? በማለት ተደነቅሁኝ፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ መርማሪው መናገር ሲጀምር ለምን እንደሆነ ገባኝ፡፡ መቆስቆሻው ግሎ ቀይ ከሆነ በኋላ አንዱ ፖሊስ በግራ እጄ ስጋ ውስጥ ሰደደው፡፡
እኔ መለወጤን እንድናዘዝ ነበር የፈለጉት ነገር ግን እንዲህ አልኳቸው፡ “እኔ እስልምናን አልካድኩም፡፡ የማምነውን ብቻ ነው የተናገርኩት፡፡ እኔ የትምህርት ሰው ነኝ፡፡ እኔ አሳቢ ነኝ፡፡ የእስልምናን የትኛውንም ርዕሰ ጉዳይ የመወያየት መብት አለኝ፡፡ ይህ ሥራዬና የየትኛውም የትምህርት ሕይወት አካል ነው፡፡ እስልምናን ለመተው አልሜ እንኳ አላውቅም፡፡ ደሜ ነው፣ ባሕሌ ነው፣ ቋንቋዬ ነው፣ ቤተሰቤ ነው፣ ሕይወቴም ነው፡፡ ስለተናገርኳችሁ ነገር እስልምናን ትተሃል በማለት የምትወነጅሉኝ ከሆነ ከእስልምና አውጡኝ፡፡ ከእስልምና ውጪ ብሆን ቅር አይለኝም፡፡”
ግርፋቱ
መልሴ እነርሱ ሊሰሙት የፈለጉትን ዓይነት አልነበረም፡፡ የብረት አልጋ ወደ ነበረበት ክፍል ተወሰድኩኝ፡፡ እግሮቼን በአልጋው እግሮች ላይ በማሰር ወፈር ያሉ ገምባሌዎችን አጠለቁልኝ፡፡
አንዱ ፖሊስ አራት ጫማ ያህል የሚረዝም ጥቁር አለንጋ ይዞ ነበር፣ ይገርፈኝም ጀመር፡፡ ሌላው ፖሊስ ትራስ በእጁ በመያዝ በአልጋው ፊት ከአጠገቤ ቆመ፡፡ እኔ ስጮኽ ድምፄ እስኪጠፋ ድረስ ትራሱን ፊቴ ላይ አጥብቆ ይይዝ ነበር፡፡ እኔ ጩኸቴን ባለማቆሜ ሁለተኛው ፖሊስ ተጨማሪ ትራስ ፊቴ ላይ ለማድረግ መጣ፡፡
ስገረፍ ሳለሁኝም እራሴን ሳትኩኝ ነገር ግን ስነቃ አሁንም ድረስ ፖሊሱ እግሮቼን ይገርፍ ነበር፡፡ ከዚያም ግርፋቱን ጋብ በማድረግ ፈቱኝ፤ አንዱ ፖሊስም “ተነስና ቁም” በማለት አዘዘኝ፡፡ መጀመርያ ላይ አልቻልኩኝም ነበር ነገር ግን እኔ እስክቆም ድረስ አለንጋውን በማንሳት ጀርባዬን ይገርፈኝ ነበር፡፡
ከዚያም ረጅም መተላለፍያ በማሳየት “እሩጥ” አለኝ፡፡ አሁንም መሮጥ ሲያቅተኝ መተላለፊያውን ሮጬ ወደታች እስክወርድ ድረስ ጀርባዬን ይገርፈኝ ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ስደርስ ሌላ ፖሊስ ቆሞ ይጠብቀኝ ነበር፡፡ ወደ መጣሁበት በሩጫ እስክመለስ ድረስ እርሱም ይገርፈኝ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ በሩጫ አመላለሱኝ፡፡
ኋላ ላይ ለምን ያንን እንዳደረጉ ገባኝ፡፡ ሩጫው እግሬ እንዳያብጥ የታሰበ ነበር፡፡ ገምባሌዎቹ የተደረጉበት ምክንያት ደግሞ ከግርፋቱ የተነሳ እግሬ ላይ ምልክት እንዳይኖር ነበር፡፡ ትራሶቹ ደግሞ ማንም ስጮኽ ድምፄን እንዳይሰማ የታሰበ ይመስለኛል፡፡
ከዚያም ከመሬት ከፍ ያለ አነስተኛ የመዋኛ ገንዳ ወደሚመስል ነገር ተወሰድኩኝ፡፡ ቀዝቃዛ በሆነ በረዷማ ውሃ የተሞላ ነበር፡፡ አለንጋውን የያዘው ፖሊስ “ግባ” አለኝ፤ እኔም ገባሁኝ፡፡ በጣም ቀዝቃዛ ከመሆኑ የተነሳ ለመውጣት እፍጨረጨር ነበር ነገር ግን ለመውጣት በሞከርኩኝ ቁጥር እየገረፈ ይመልሰኝ ነበር፡፡
ዝቅተኛ የደም ስኳር ስለነበረብኝ ራሴን ለመሳት ጊዜ አልፈጀብኝም ነበር፡፡ ስነቃ ከነእርጥብ ልብሴ መጀመርያ እግሮቼን የተገረፍኩበት አልጋ ላይ ተኝቼ ነበር፡፡
አንድ ሌሊት በጭለማ ውስጥ
አንድ ምሽት ከሕንፃው በስተጀርባ ተወሰድኩኝ፡፡ ምንም መስኮትና በር የሌላት አነስተኛ የግንብ ክፍል ተመለከትኩኝ፡፡ የነበራት ክፍተት በጣርያዋ በኩል ያለው የብርሃን መግቢያ ነበር፡፡ መሰላል በማምጣት ወደ ላይ እንድወጣ ካደረጉ በኋላ “ግባ” የሚል ትዕዛዝ ሰጡኝ፡፡ ጠርዙ ላይ ተቀምጬ እግሮቼን ክፍተቱ መሃል ሳደርግ ውኀ ነካሁ፡፡ የሆነ ነገርም ውኃው ላይ እየዋኘ እንደሆነ ማየት እችል ነበር፡፡ ይህ መቀበርያዬ ነው፤ በቃ ዛሬ ሊገድሉኝ ነው በማለት አሰብኩኝ፡፡
ወደ ክፍተቱ ውስጥ ስገባ ውኀው ሰውነቴን በመሸፈን ወደ ላይ ሲወጣ ተሰማኝ፡፡ ከዚያም በእግሬ ጠንካራ መሬት ስነካ ገረመኝ፡፡ ውኀው እስከ ትከሻዬ ድረስ ብቻ ነበር የደረሰው፡፡ ከዚያም ሲዋኙ ያየኋቸው አይጦች በፊቴና በጭንቅላቴ ላይ ሁሉ መርመስመስ ጀመሩ፡፡ አይጦቹ ለረጅም ጊዜ ምግብ አልተሰጣቸውም ነበር፡፡ መርማሪዎቼ ተንኮለኞች ነበሩ፡፡ “ይህ ሰው ሙስሊም አሳቢ ነው ስለዚህም አይጦች ጭንቅላቱን እንዲበሉት እናደርጋለን” ብለው ነበር፡፡
የብርሃን መግቢያውን ከዘጉ በኋላ የመጀመርያውን ደቂቃ በታላቅ ፍርሃት ነበር ያሳለፍኩት፡፡ ሌሊቱን በሙሉ እዚያ በመተው ጠዋት ላይ በሕይወት መኖሬን ለማረጋገጥ ተመልሰው መጡ፡፡ የብርሃን መግቢያው ተከፍቶ ብርሃን ሳይ ለመትረፌና በሕይወት ለመኖሬ ተስፋን ፈነጠቀልኝ፡፡
ሌሊቱን በሙሉ አንድም አይጥ ሳይነክሰኝ አደርኩኝ፡፡ ጭንቅላቴ ላይ በመውጣት ፀጉሬ ውስጥ ገብተው ነበር፣ ጆሮዬንም ሲነካኩ ነበር፡፡ አንዲት አይጥ ትከሻዬ ላይ ቆማ ነበር፡፡ አፋቸው ፊቴን ሲነካካ ይሰማኝ ነበር ነገር ግን የመሳም ያህል ነበር፡፡ ጥርስ የሚባል ነገር አልተሰማኝም ነበር፡፡ አይጦቹ በሚገርም ሁኔታ ታማኞች ሆነውልኝ ነበር፡፡
ዛሬ እንኳ አይጥ ሳይ የአክብሮት ስሜት ይሰማኛል፡፡ አይጦቹ እንደዛ ዓይነት ጠባይ ለምን እንዳሳዩ አሁንም ድረስ ሊገባኝ አልቻለም፡፡
ከውድ ጓደኛዬ ጋር ተገናኘሁ
ምርመራው ገና አላለቀም ነበር፡፡ በኋላም ፖሊሶቹ ወደ አንዲት ጠባብ ክፍል በር በመውሰድ “አንድ በጣም የሚወድህና ሊያይህ የሚፈልግ ሰው አለ” አሉኝ፡፡
“ማነው እርሱ?” በማለት ጠየቅኋቸው፡፡ ከቤተሰቦቼ መካከል አንዱ ወይንም ሊያየኝና ሊያስፈታኝ የመጣ ወዳጄ ሊሆን እንደሚችል አሰብኩኝ፡፡
“አንተ አታውቀውም እርሱ ግን ያውቅሃል” በማለት መለሱልኝ፡፡ የክፍሉን በር ሲከፍቱ ትልቅ ውሻ አየሁኝ፡፡ በክፍሉ ውስጥ ሌላ ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ሁለት ሰዎች እኔን ወደ ውስጥ ገፍትረው በማስገባት በሩን ዘግተውብኝ ሄዱ፡፡
ይህ ልቤ የጮኸበት የመጀመርያው ጊዜ ነበር፡፡ በልቤ ውስጥ ወደ ፈጣሪዬ ጮኽኩኝ፡፡ አንተ አባቴ ነህ አምላኬም ነህ፡፡ አንተ ትጠብቀኛለህ፡፡ በነዚህ ክፉዎች እጅ እንዴት ትተወኛለህ? እነዚህ ሰዎች ምን ሊያደርጉብኝ እየሞከሩ እንደሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን አንተ ከእኔ ጋር እንደምትሆን አውቃለሁ፡፡ አንድ ቀንም አይሃለሁ፣ ከአንተም ጋር እገናኛለሁ፡፡
ወደ ባዶ ክፍሉ መሃል ላይ በመሄድ እግሬን በማጠላለፍ ቀስ ብዬ ወለሉ ላይ ተቀመጥኩኝ፡፡ ውሻው በመምጣት ከፊት ለፊቴ ተቀመጠ፡፡ ይህ ውሻ ትክ ብሎ ሲመለከተኝ ደቂቃዎች አለፉ፡፡ ዐይኖቹ በተደጋጋሚ ከላይ ወደ ታች ሲንቀሳቀሱ አይ ነበር፡፡ ገና ወዳላወቅሁት አምላክ በልቤ ውስጥ መጸለይ ጀመርኩኝ፡፡
የሆነ ነገር ሊበላ እንዳለ እንስሳ ውሻው በመነሳት ዙርያዬን ይዞር ጀመር፡፡ ከዚያም በስተቀኜ በኩል በመምጣት ጆሮዬን በምላሱ መላስ ጀመረ፡፡ በስተቀኜ በመቀመጥ እዚያው ቆየ፡፡ በጣም ደክሞኝ ነበር፡፡ እርሱ እዚያ በተቀመጠ ጊዜ ወድያውኑ እንቅልፍ ይዞኝ ሄደ፡፡
ስነቃ ውሻው በቤቱ ጥግ ላይ ነበር፡፡ ደህና አደርክ? እንደማለት ወደ እኔ ሮጦ መጣ፡፡ የቀኝ ጆሮዬን ደግሞ በመላስ አሁንም በስተቀኜ ተቀመጠ፡፡
ፖሊሶቹ በሩን ሲከፍቱ ውሻው ከአጠገቤ ተቀምጦ ስጸልይ ተመለከቱኝ፡፡ ከመካከላቸው አንዱም “ይህ ሰውዬ ሰው መሆኑን ማመን አልችልም፡፡ ይህ ሰውዬ ዲያብሎስ ነው፤ ሰይጣን ነው፡፡” ሌላኛው ደግሞ “እኔ እንደዚያ አላምንም፡፡ ከዚህ ሰውዬ በስተጀርባ ቆሞ እየጠበቀው ያለ የማይታይ ኃይል አለ” በማለት መለሰ፡፡
“የትኛው ኃይል? ይህ ሰው ከሃዲ ነው፡፡ ይህ ሰው የአላህ ተቃዋሚ ስለሆነ የሰይጣን ኃይል መሆን አለበት፡፡”
የሆነ ሰው ጥበቃ ሲያደርግልኝ ነበር
ወደ ክፍሌ መልሰው ወሰዱኝ፡፡ እኔ እዝያ ባልነበርኩበት ጊዜ ክፍሌን ይጋራ የነበረው ሰው “ለምንድነው ይህንን ሰው የምታሰቃዩት?” በማለት አንዱን ፖሊስ ጠይቆት ነበር፡፡
“እስልምናን እየካደ ስለሆነ ነው” በማለት መለሱለት፡፡ ያም የክፍል ተጋሪዬን ቁጣ እንዲነድበት አደረገ፡፡ ወደ ክፍሉ ተመልሼ በገባሁበት ጊዜ ሊገድለኝ ዝግጁ ነበር፡፡ እኔ በክፍሉ ውስጥ ገና ከአስራ አምስት እስከ ሃያ ደቂቃ ሲሆነኝ አንድ ፖሊስ የዝውውር ወረቀት ይዞ በመምጣት ወስዶት ሄደ፡፡
እንዲህም ብዬ ራሴን ጠየቅሁት፡ ምንድነው እየሆነ ያለው? ምን ዓይነትስ ኃይል ነው እየጠበቀኝ ያለው? በወቅቱ መልሱ ምን እንደሆነ አላውቅም ነበር፡፡
ስለ እርሱ ብዙም በመጨነቅ ጊዜ አላጠፋሁም፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የእኔም የዝውውር ወረቀት መጣ፡፡ በደቡባዊ ካይሮ ወደሚገኝ መደበኛ ወኅኒ ቤትም ተወሰድኩኝ፡፡
በዚህ ጊዜ መርማሪዎቼ የሰው ፍጥረቶች መሆናቸውን ማመን ከብዶኝ ነበር፡፡ እስልምናን ስለተጠራጠርኩኝ ብቻ ነበር የተያዝኩት፡፡ አሁን ግን እምነቴ በትክክል ተናግቷል፡፡ ወደ ሌላ ወኅኒ ቤት እየተዛወርኩኝ ነበር፡፡
ቀጣዩን ሳምንት በደቡባዊ ካይሮ በሚገኝ ወኅኒ ቤት ውስጥ አሳለፍኩኝ፡፡ በንፅፅር የተሻለ ነፃነት ያለው ጊዜ ነበር፡፡ ከአክራሪ እስልምና ጋር የማይስማማ የእስረኞች ጠባቂ እግዚአብሔር ላከልኝ፡፡
በዚህ ሁሉ ጊዜ ቤተሰቦቼ ያለሁበትን ለማወቅ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ በግብፅ ፓርላማ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የነበረው የእናቴ ወንድም ከባሕር ማዶ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ ግን አልተሳካላቸውም ነበር፡፡ እናቴ እያለቀሰች ደውላ እንዲህ አለችው፡ “ለሁለት ሳምንታት ያህል ልጃችን ያለበትን አናውቅም፡፡ ተለይቶናል፡፡” አጎቴ አስፈላጊ የሆኑት ግንኙነቶች ሁሉ ነበሩት፡፡ እኔ ከተጠለፍኩኝ ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ ይፈታ የሚል የትዕዛዝ ወረቀት ይዞ በመምጣት ወደ ቤት ይዞኝ ሄደ፡፡
በኋላም ፖሊስ ለአባቴ የሚከተለውን ሪፖርት ሰጠ፡
ልጅህ እስልምናን መልቀቁን የሚገልፅ የፋክስ መልዕክት ከአል-አዝሃር ደርሶን ነበር፡፡ ነገር ግን ከአስራ አምስት ቀናት ምርመራ በኋላ ይህንን የሚደግፍ ምንም ማስረጃ አላገኘንም፡፡
አባቴ ይህንን በመስማቱ እፎይታ ተሰማው፡፡ ከወንድሞቼና እህቶቼ መካከል በዩኒቨርሲቲ እስልምናን ያጠናሁት እኔ ብቻ ስሆን እርሱም በእኔ ይኮራ ነበር፡፡ እኔ እስልምናን እንደምለቅ በፍፁም አስቦ ስለማያውቅ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያሉት ሰዎች በእኔ ምሑርነት እንደሚቀኑ በማሰብ ሁኔታውን ሁሉ ከዝያ ጋር አያያዘ፡፡
“እኛ አንፈልጋቸውም” በማለት በእርሱ ፋብሪካ ውስጥ የሽያጭ ኃላፊ ሆኜ ወዲያውኑ ሥራ እንድጀምር ጠየቀኝ፡፡ የቆዳ ጃኬቶችና የወንዶችን እንዲሁም የሴቶችን ልብስ የሚያመርት የተሳካለት ንግድ ነበረው፡፡
አንድ ዓመት ያለ እምነት
ለአንድ ዓመት ምንም እምነት ሳይኖረኝ አሳለፍኩኝ፡፡ ወደ እርሱ የምጸልየው፣ የምጠራው ወይንም የምኖርለት አምላክ አልነበረኝም፡፡ ቸርና ፃድቅ የሆነ አምላክ መኖሩን አውቃለሁ ነገር ግን እርሱ ማን እንደሆነ አላውቅም ነበር፡፡ እርሱ የሙስሊሞች፣ የክርስቲያኖች ወይንም ደግሞ የአይሁዶች አምላክ ነውን? እንደ ሒንዱዎች ላም ዓይነት የሆነ እንስሳ ነውን? እንዴት ላገኘው እንደምችል ምንም የማውቀው ነገር አልነበረኝም፡፡
አንድ ሙስሊም እስልምና እውነት አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ከደረሰ በኋላ የሚቀየርበትን ሌላ ኃይማኖት ካላገኘ በሕይወቱ ውስጥ እጅግ አስቸጋሪው ጊዜ እንደሚሆንበት መረዳት ይኖርባችኋል፡፡ እምነት በመካከለኛው ምስራቅ ሰው ሥጋና ደም ውስጥ የሰረፀ ነገር ነው፡፡ አምላኩን ሳያውቅ መኖር አይታየውም፡፡
ዓመቱን በሙሉ በመንፈሴ ውስጥ የነበረውን ህመም ውጫዊው አካሌ ይገልጠው ነበር፡፡ የሚያስፈልገኝ ቁሳዊ ነገር ሁሉ ቢኖረኝም የእውነተኛውን አምላክ ማንነት ለማወቅ ያለ እረፍት አስብ ስለነበር አካሌ በመድከም እጅግ ዝሎ ነበር፡፡ በማያቋርጥ የራስ ምታትም እሰቃይ ነበር፡፡ ዘመዳችን ወደነበረ አንድ ዶክተር ዘንድ ሄጄ ነበር፡፡ አዕምሮዬን ቢመረምረኝም ነገር ግን ምንም ችግር ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ሊረዱኝ የሚችሉ የተወሰኑ የሚዋጡ መድኃኒቶችን አዘዘልኝ፡፡
የተራራው ስብከት
የራስ ምታቱ ቶሎ እንደሚለቀኝ ስላሰብኩኝ አነስተኛ መጠን ያላቸውን መድኃኒቶች ለመግዛት በሳምንት አንድ ጊዜ ወይንም ሁለት ጊዜ በቅርበት ወዳለ የመድኃኒት መደብር መሄድ ጀመርኩኝ፡፡ የተወሰነ ጊዜ ከተመላለስኩኝ በኋላ ፋርማሲስቷ “በሕይወትህ ውስጥ ምን እየሆነ ነው?” በማለት ጠየቀችኝ፡፡
“ምንም ነገር እየሆነ አይደለም፡፡ ችግሬ አንድና አንድ ነው፤ እርሱም ያለ አምላክ መኖሬ ነው፡፡ አምላኬ ማን እንደሆነ አላውቅም፡፡ እኔንም ሆነ አፅናፈ ዓለሙን የፈጠረው ማን እንደሆነ አላውቅም፡፡” በማለት መለስኩላት፡፡
እርሷም “ነገር ግን እኮ አንተ በጣም በተከበረ እስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፕሮፌሰር ነበርክ፡፡ ቤተሰብህም በሕብረተሰቡ ውስጥ በጣም የተከበረ ነው” በማለት መለሰችልኝ፡፡
“ልክ ነሽ እርሱስ እውነት ነው” በማለት መለስኩላት፡፡ “ነገር ግን በአስተምህሯቸው ውስጥ ውሸትን አገኘሁበት፡፡ ቤቴና ቤተሰቦቼ በእውነት መሠረት ላይ እንደተመሠረቱ ከእንግዲህ በኋላ ማሰብ አልችልም፡፡ ዘወትር በእስልምና ውሸቶች ውስጥ ተጀቡኜ እኖር ነበር፡፡ አሁን ግን እርቃኔን እንደቀረሁኝ ይሰማኛል፡፡ በልቤ ውስጥ ያለውን ባዶነት እንዴት አድርጌ ነው መሙላት የምችለው? እባክሽኝ እርጂኝ፡፡”
“እሺ፣ ዛሬ እነዚህን ክኒኖችና ይህንን መጽሐፍ – መጽሐፍ ቅዱስን እሰጥሃለሁ፡፡ ከዚህ መጽሐፍ የሆነ ነገር ከማንበብህ በፊት ምንም መድኃኒት እንደማትውጥ እባክህን ቃል ግባልኝ” አለችኝ፡፡
መጽሐፉን ወደ ቤቴ በመውሰድ በነሲብ አንድ ቦታ ላይ ከፈትኩኝ፡፡ ዐይኖቼ ማቴዎስ 5፡38 ላይ አረፉ፡
“ዐይን ስለ ዐይን ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት።”
ሰውነቴ በሙሉ መንቀጥቀጥ ጀመረ፡፡ ቁርአንን እድሜዬን በሙሉ ሳጠናው ነበር ነገር ግን እንዲህ ያሉ ኃይል ያላቸውን ቃላት አንድም እንኳ አግኝቼ አላውቅም፡፡ ከጌታ ኢየሱስ ጋር ፊት ለፊት ተገናኘሁ፡፡
ከጊዜ መዘውር ውጪ ሆንኩኝ፡፡ ከኮረብታ በላይ ባለ ደመና ላይ ተቀምጬ የአፅናፈ ዓለም ታላቁ መምህር ከፊት ለፊቴ በመሆን ስለ ሰማይ ሚስጥርና ስለ እግዚአህሔር ልብ እየነገረኝ እንደሆነ ተሰማኝ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን በቀላሉ ለዓመታት ካጠናሁት ከቁርአን ጋር ማነፃፀር እችል ስለነበር እውነተኛውን አምላክ እንደተገናኘሁት ጥርጥር አልነበረኝም፡፡ በቀጣዩ ቀን የመጀመርያ ሰዓታት ላይ አሁንም ድረስ ሳነብ ነበር፤ አመሻሽ አካባቢ ላይም ልቤን ለኢየሱስ ሰጠሁኝ፡፡
ሽምቅ
ኢየሱስን መቀበሌን ለፋርማሲስቷና ለባለቤቷ ብቻ ነበር የተናገርኩት ነገር ግን በግብፅ አንድ ሰው እስልምናን ከተወ ክርስቲያን እንደሆነ ስለሚታሰብ መገደል አለበት ይባላል፡፡ በዚህ ምክንያት አክራሪዎች ሸምቀው እንዲጠብቁኝና እንዲገድሉኝ ሁለት ሰዎችን ልከውብኝ ነበር፡፡
ይህም የሆነው ጓደኛዬ ጋር ቆይቼ ወደ ቤቴ ስመለስ ነበር፡፡ በጊዛ ውስጥ የአስራ አምስት ወይንም የሃያ ደቂቃ የእግር መንገድ ቢሆን ነበር፡፡ ቲርሳኤ ጎዳና በሚባለው ላይ ቤቴ አካባቢ ስደርስ ነበር ሁለት ሰዎችን የግሮሰሪ በር ላይ ቆመው ያየሁት፡፡ ባሕላዊ የሆኑትን ረጃጅም ነጫጭ ቀሚሶችን ለብሰው ነበር፤ ጢማቸውም የረዘመና በራሶቻቸው ላይም ጠምጥመው ነበር፡፡ ገበያተኞች ብቻ እንደሆኑ አስቤ ነበር፡፡ ጉዳት ያደርሱብኛል ብዬ አልጠረጠርኩኝም ነበር፡፡
ሱቁ ጋር ስደርስ አስቁመውኝ ድንገት ሳንጃዎችን በመምዘዝ እኔን ለመውጋት መሰንዘር ጀመሩ፡፡ ምንም መሣርያ አልያዝኩኝም ነበር፤ ቀኑም ሞቃት ስለነበር ቲ-ሸርትና ቁምጣ ብቻ ነበር የለበስኩት፡፡ በእጄም ራሴን መከላከል ጀመርኩኝ፡፡ ሳንጃዎቹ በተደጋጋሚ እኔ ላይ በማረፍ ደረቴን ቆራረጡኝ፡፡
ሌሎች ሰዎች በመንገድ ላይ ነበሩ ነገር ግን የረዳኝ አልነበረም፡፡ ተሰብስበው ብቻ ይመለከቱ ነበር፡፡ በነዚያ ዘመናት ይህ የተለመደ ነበር፡፡ የእጅ ድብድብ ቢሆን ኖሮ ሰዎች ጣልቃ ይገቡ ነበር ነገር ግን በስለት ሲሆን ማንም አይጠጋም፡፡ አንድ ሰው ሽጉጥ ቢመዝ ደግሞ በአካባቢው መገኘት አይፈልጉም፡፡
የመጀርያው ጥቃት ፈፃሚ ልቤን ለመውጋት ነበር ሲሞክር የነበረው፡፡ አንድ ጊዜ ሊወጋኝ ምንም አልቀረውም ነበር ነገር ግን ዘወር በማለት ተረፍኩኝ፡፡ በአምስት ኢንች ያህል ስቶ ትከሻዬን አገኘኝ፡፡ ሳንጃውን መዝዞ ሲያወጣ ወደ ታች ተመልክቼ ያየሁትን የደም ፈሳሽ አስታውሳለሁኝ፡፡
መሬት ላይ ወድቄ እንደ ኳስ እየተንከባለልኩኝ ራሴን ለመከላከል ስጥር ነበር፡፡ ከዚያም ሌላኛው ጥቃት ፈፃሚ ሆዴ ላይ ሊወጋኝ ሞከረ ነገር ግን ስለቱ ቦታውን ስቶ የፊት ጭኔ ላይ ወጋኝ፡፡
በዚህ ጊዜ ብዙ ደም ስለፈሰሰኝ ራሴን እየሳትኩ መጣሁ፡፡ ሁለት ፖሊሶች በሞተር ሳይክል ደርሰው አጥቂዎቼ ሮጠው እስኪሸሹ ድረስ ምንም ተስፋ አልነበረኝም፡፡
ወደ ሆስፒታል ተወስጄ እርዳታ ተደረገልኝ፡፡ ሆስፒታል እያለሁም ለምን ጥቃት እንደተፈፀመብኝ ፖሊስ ጠይቆኝ እንደማላውቅ ተናገርኩኝ፡፡
አሁንም አባቴ እኔ እስልናን መተዌን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን መካዱን ቀጥሏል፡፡ ይህንን ማሰብ እጅግ ተስኖት ነበር፡፡
አባቴ እውነቱን አወቀ
ለአባቴ መስራቴን ቀጥያለሁኝ፤ ስለ አዲሱ እምነቴም መናገር አልፈለኩም ነበር፡፡ በእርግጥ በ1994 ዓ.ም. የንግድ ዕድሎችን እንድቃኝለት ወደ ደቡብ አፍሪካ ልኮኝ ነበር፡፡ እዚያም ሳለሁኝ ከሕንድ ከመጣ ክርስቲያን ቤተሰብ ጋር ሦስት ቀናትን አሳልፌ ነበር፡፡ ስንለያይም ትንሽዬ መስቀል ያለውን የአንገት ሀብል ሰጥተውኝ ነበር፡፡ ይህች ትንሽ መስቀል በሕይወቴ የአቅጣጫ ለውጥ ምልክት ሆነች፡፡
ከአንድ ሳምንት ትንሽ ካለፈ በኋላ አባቴ በአንገቴ ላይ ያለውን ሀብል አስተዋለ፡፡ በእስልምና ደግሞ በአንገታቸው ላይ ጌጥ ማድረግ የሚችሉት ሴቶች ብቻ ስለሆኑ በጣም ተናደደ፡፡ “ለምንድነው ይህንን ሰንሰለት ያደረከው?” በማለትም ጠየቀኝ፡፡
ምላሴ የሚከተሉትን ቃላት በራሱ ጊዜ የተናገረ ይመስል ነበር፡ “አባዬ ይህ ሰንሰለት አይደለም፡፡ ይህ መስቀል ነው፡፡ ለእኔ፣ ላንተና ለሁሉም ሰው በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ በመስቀል ላይ የሞተውን ኢየሱስን ይወክላል፡፡ ኢየሱስን እንደ አዳኜና ጌታዬ አድርጌ ተቀብየዋለሁ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛችሁ ትቀበሉት ዘንድ ላንተም ሆነ ለተቀሩት ቤተሰቦቼ እጸልያለሁኝ፡፡”
መጀመርያ አባቴ እዚያው እመንገድ ላይ ራሱን ሳተ፡፡ የተወሰኑት ወንድሞቼ በፍጥነት የደረሱለት ሲሆን እናቴ በፍርሃት ታለቅስ ነበር፡፡ የአባቴን ፊት በውኀ ሲያጥቡት ሳሉ እዚያው አብሬያቸው ነበርኩኝ፡፡ ሲነቃም አምርሮ ተቆጥቶ ስለነበር መናገር እንኳ ተስኖት ነበር ነገር ግን ዝም ብሎ ወደ እኔ ጣቱን ቀስሮ ያመለክት ነበር፡፡ በታላቅ ቁጣ በተሞላ ድምፅ “ልጅሽ ሃይማኖቱን ለውጧል፡፡ ዛሬ እርሱን መግደል አለብኝ!” በማለት አምባረቀ፡፡
አባቴ በሚሄድበት ቦታ ሁሉ በቆዳ የተሸፈነ ሽጉጥ በብብቱ ስር ይዞ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ (በግብፅ ውስጥ የሚኖሩ አብዛኞቹ ባለጠጎች ሽጉጥ ይይዛሉ፡፡) ሽጉጡን በማውጣ አነጣጠረብኝ፡፡ መንገዱን ይዤ ወደ ታች መሮጥ ጀመርኩኝ፡፡ ጥግ ይዤም ሳለሁ ጥይቶች እያፏጩ በአናቴ ላይ ሲያልፉ እሰማ ነበር፡፡ ሕይወቴን ለማትረፍ መሮጤን ቀጠልኩኝ፡፡
ቤቴን እስከወዲያኛው ተሰናበትኩ
በግማሽ ማይል ርቀት ወደሚገኘው የእህቴ ቤት ሮጬ ደረስኩ፡፡ እህቴ በአባቴ ቤት የሚገኙትን ልብሶቼን፣ ፓስፖርቴንና ሌሎች ዶክመንቶቼን በማምጣት እንድትተባበረኝ ጠየቅኋት፡፡ የተፈጠረውን ነገር ማወቅ ስለፈለገች ጠየቀችኝ፤ እኔም “አባዬ ሊገድለኝ ይፈልጋል” በማለት ነገርኳት፡፡ ለምን እንደሆነም ጠየቀችኝ፤ እኔም “አላውቅም፡፡ እርሱን አባዬን ጠይቂው” በማለት መለስኩላት፡፡
ስሮጥ ሳለሁ ወዴት እንደሆነ አባቴ በትክክል አውቋል፤ ምክንያቱም እኔና እህቴ እንቀራረብ ነበር፤ ቤቷም ደግሞ ቅርብ ነበር፡፡ አባቴ ወደ እህቴ ቤቴ መጣ፤ እኔና እህቴም ስንነጋገር ደረሰ፡፡ እምባው በፊቱ ላይ እየፈሰሰ በሩን መደብደብ ጀመረ፤ እንዲህም ይል ነበር፡ “ልጄ እባክሽን በሩን ክፈቺ፡፡” ከዚያም እንዲህ እያለ ጩኸ፡ “ወንድምሽ ሃይማኖቱን ቀይሯል! እስልምናን ትቷል፡፡ አሁኑኑ እርሱን መግደል አለብኝ!”
እህቴ በሩን በመክፈት ልታረጋጋው ሞከረች፡፡ “አባዬ እዚህ የለም፡፡ ምናልባትም ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምን ወደ ቤት ሄደህ አታርፍም፤ ከዚያም እንደ ቤተሰብ ስለዚህ ጉዳይ ልናወራ እንችላለን፡፡”
እህቴ ራርታልኝ ከወላጆቼ ቤት ቁሳቁሶቼን ሰብስባ አመጣችልኝ፡፡ እርሷና እናቴ የተወሰነ ገንዘብ ስለሰጡኝ ነሐሴ 28/1994 አመሻሽ ላይ መኪናዬ ውስጥ ገብቼ እየነዳሁ ሄድኩኝ፡፡
ለሦስት ወራት ያህል በሰሜናዊ ግብፅ፣ ሊብያ፣ ቻድና ካሜሩን ለመጓዝ ስታገል ነበር፡፡ በመጨረሻም ኮንጎ ላይ ቆም አልኩኝ፡፡ በዚያን ጊዜ ወባ ይዞኝ ነበር፡፡ እንዲመረምረኝ ግብፃዊ ዶክተር አገኙ፡፡ እኔም ጠዋት ላይ እንደምሞት ስለተናገረ በኮንጎ ከሚገኘው የግብፅ ኤምባሲ የሬሳ ሳጥን ለማግኘትና ወደ ሃገር ቤትም ሊልኩኝ ሁኔታዎችን አመቻቹ፡፡
ለእነርሱ አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ በበነጋው ነቃሁኝ፡፡ ከአምስት ቀናት በኋላ ሆስፒታሉን ለቅቄ በመውጣት በሁሉም ቦታ ኢየሱስ የደረገልኝን ለሰዎች መንገር ጀመርኩኝ፡፡
ጉዞ ወደ ደቡብ አፍሪካ
አባቴ ሽጉጥ ከመዘዘብኝ በኋላ የትውልድ ሀገሬን ጥያት ኮበለልኩኝ፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ መሄድ እንዳለብኝ ጌታ ኢየሱስ አመለከተኝ፡፡ እዚያም ሳለሁ አሮጌ በሆነው ሙስሊም ማንነቴ ላይ ድልን መቀዳጀት እችል ዘንድ እውነተኛ ወንድሞችንና እህቶችንም ላከልኝ፡፡ ዩዝ ዊዝ ኤሚሽን ከሚባል ቡድን ጋር ለስድስት ወር ያህል ወደ ደቀ መዝሙርነት ትምህርት ቤት ሊልኩኝ ወሰኑ፡፡ እዚያም ድሉን ተቀዳጀሁ፤ በኢየሱስ ክርስቶስ የተፈጠረውን በውስጤ ያለውንም አዲሱን ሰው መለማመድ ጀመርኩኝ፡፡
በክርስትና እምነት ከፀናሁ በኋላ ከሙስሊም ወንድሞቼ ጋር የምሥራቹን መካፈል ጀመርኩኝ፡፡ በደርባን፣ ደቡብ አፍሪካ ጌታ ወደ አንድ ግብፃዊ ሙስሊም ወንድም መራኝ፡፡ ወደ ክርስቶስ የመጣ ሲሆን በአንድ ሳምንት ውስጥ ሕንዳዊት ሙስሊም ባለቤቱም ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀበለች፡፡
ለአንድ ወር ያህል በእንግሊዘኛ ተናጋሪ ደቡብ አፍሪካውያን ሙስሊሞች መካከል ስሠራ ያስተረጉምልኝ ነበር፡፡ ሰባት ሙስሊሞች ተለወጡ፣ ይህም ደግሞ ታላቅ ድል ነበር፡፡ የዚህም ወሬ አንድ ሊባኖሳዊ ሚስዮናዊ ዘንድ ደረሰ፡፡ የእርሱ ድርጅት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙትን ሙስሊሞች መድረስ ይችል ዘንድ ከእስልምና የተለወጠ ሰው በመምጣት እንዲረዳው ለአራት አመታት ያህል ይጸልይ እንደነበር ተናግሮ ነበር፡፡ በዚህ ሚስዮናዊ በኩል ነበር ለመጀመርያ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መናገር የቻልኩት፡፡ እኔ ስናገር የነበረው በአረብኛ ሲሆን ይህ ሚስዮናዊም ያስተረጉምልኝ ነበር፡፡
በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ለመናገር ብዙ እድሎችን አግኝቼ ነበር፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ ሙስሊም ማሕበረሰቦችን የመድረስ መሻት ነበረን፡፡ ይህንን ለማድረግ በጆሃንስበርግ ውስጥ ይኖር የነበረ አብዱልቃድር የሚባል ሙስሊም መሪና እኔ የምንከራከርበት መድረክ እንዲዘጋጅ አደረግን፡፡ በስቴትስማን ሆቴል ውስጥ የተገናኘን ሲሆን ወደ ሁለት መቶ ሃምሳ የሚሆኑ ሙስሊሞችም ተገኝተው ነበር፡፡ ይህ የሆነው ለሃይማኖት ቅድሚያ በሚሰጥበት በረመዳን ወር ውስጥ ነበር፡፡
እያገባደድን ሳለን አንድ ሰው ሲጮኽ ሰማሁኝ፡፡ አንድ ሙስሊም ሰው ትልቅ ቢለዋ እያወዛወዘ እንዲህ በማለት እየጮኸ ወደ አዳራሹ ውስጥ በሩጫ መጣ፡ “ግብፃዊው ውሻ ወዴት አለ? ግብፃዊው ከሃዲ ወዴት ነው? በዚህ ምሽት ገድዬው ደሙን እጠጣለሁ፡፡” በእስልምና ሕግ የተከለከለ ቢሆንም ነገር ግን ለድፍረት አልኮል እንደተጎነጨ ግልፅ ነበር፡፡ ሕዝቡን በማለፍ ቢለዋውን ይዞ ወደ እኔ መጣ፡፡ ሚስዮናዊው በመካከላችን በመግባት ቢለዋውን ሊቀማው ይሞክር ነበር፡፡
ከዝያም ከሕዝቡ መካከል ስምንት ሰዎች ወደ እኛ መጡ፡፡ የዚህ ሰው ወገኖች ናቸው የሚል ፍርሃት ነበረኝ፡፡ ነገር ግን በዚያ ፋንታ ሰውየውን በመያዝ ቢለዋውን ተቀበሉት፡፡ ከዚያም በቡጢና በርግጫ ይሉት ጀመር፡፡ ከዚያም አንስተው ከሆቴሉ ውጪ ወረወሩት፡፡
ወደ መሰብሰብያ አዳራሹ ተመልሰው በገቡ ጊዜ ከእኔ ጋር ሲከራከር የነበረውን ሙስሊም መሪ እንዲህ አሉት፡ “እኛ እስልምናን በመተው ኢየሱስ ክርስቶስን ልንቀበል ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህንን ሰው ታድጎታል እርሱም እውነተኛውን አምላክ እያገለገለ ነው፡፡”
በዚህ ጊዜ ሕዝቡ በቁጣ ተሞልቶ ነበር፡፡ እነዚህ ስምት ሰዎች እኛን ከሕዝቡ ለመጠበቅ ከበቡን፡፡ ልክ ከሆቴሉ ሮጠን ስንወጣ ሳለን እኔን በትከሻቸው ላይ ተሸክመው ወደ ላይ አነሱኝ፡፡ ሚስዮናዊው ከኛ ጎን ይሮጥ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ መኪናው ጋር መድረስ የቻልን ሲሆን ሚስዮናዊው የመኪናውን በር ከፍቶ እስኪገባ ድረስ መኪነዋን በመክበብ ይከላከሉ ነበር፡፡ ከዝያም ውስጥ በመግባት በፍጥነት እየነዳን ለማምለጥ ቻልን፡፡
በዝያን ዕለት ወደ ክርስቶስ የመጡት ስምንቱ ሰዎች ጉዳት ሳይደርስባቸው ከሕዝቡ ማምለጥ ችለዋል፡፡ ከአልጄርያ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሥራ ፍለጋ የመጡ ሙስሊሞች ነበሩ፡፡ ሚስዮናዊውና እኔ በየሳምንቱ እያገኘናቸው ደቀ መዛሙርት አደረግናቸው፡፡ አብዛኞቻቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እንዲገቡ የረዳናቸው ሲሆን ከነርሱ መካከል አንዱ በፕሪቶርያ የሙስሊም ሕፃናት አገልጋይ በመሆን እየሠራ ይገኛል፡፡
ክርክሩ ከተደረገ ከብዙ ቀናት በኋላ አስቤዛ ልሸምት ወደ ግሮሰሪ እሄድኩ ሳለሁ ሁለት ሰዎች መንገድ ላይ በድንገት አስቁመውኝ በቢለዋ ጥቃት አደረሱብኝ፡፡ ጭንቅላቴ ላይ የመሰንተቅ ጉዳት ስለደረሰብኝ ወደ አልቤርቶን ሆስፒታል ተወስጄ እዝያም ለማገገም ለሦስት ቀናት ያህል ቆየሁኝ፡፡ ሰዎቹ አልጄርያውያን በመሆናቸው ለተደረገው ውይይት የበቀል እርምጃ መሆኑ ግልፅ ነበር፡፡
የደቡብ አፍሪካ የመገናኛ ብዙኀን እየደረሰብኝ ስላለው ስደት መዘገብ ጀመሩ፡፡ ይህ የመገናኛ ብዙኀን ሽፋን በመላው ሃገሪቱ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያንት ውስጥ ምስክርነቴን እንዳካፍል በሮችን ከፈተልኝ፡፡ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከሁለት ሺህ ጊዜ በላይ ንግግሮችን አድርጌአለሁ፡፡ ይህ በመላው ዓለም የሚገኙትን ቦታዎች የሚያጠቃልል ሲሆን በተለይም ደግሞ እስከ 1999 ዓ.ም. የኖርኩባትን ደቡብ አፍሪካን ይመለከታል፡፡
ምርኮኞችን አርነት ማውጣት
ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ በእስልምና እስራት ውስጥ ላሉት ሙስሊሞች ልቤ ማልቀስን አላቆመም፡፡ በወንጌል ነፃ ልናወጣቸው ግድ ይለናል፡፡ ውድ አነባቢያን እናንተ በዚህ ተልዕኮ ውስጥ ይህንን ሚና ከሚጫወቱት ሰዎች መካከል እንደሆናችሁ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡ ሙስሊሞችን በእግዚአብሔር ፍቅር እንወዳቸዋለን፡፡ በባርነት እስራት ውስጥ ያስቀመጣቸውን እስልምናን እንቃወማለን ሕዝቡን ግን እንወዳለን፡፡ በፍቅሩ ወንጌል ደርሰን ፍላጎታቸውን ለመንካት ተነሳሽነቱ ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡
እስልምና 1.3 ቢሊዮን ተከታዮች ያሉት ከዓለም ሁለተኛው ትልቁ ሃይማኖት ነው፡፡ አንድ አምስተኛ የሚሆነው የሰው ልጅ እስልምናን ይከተላል፡፡ በመዋለድና በሚለወጡ ሰዎች ምክንያት በፍጥነት በመስፋፋት በዓለም ላይ ቀዳሚውን ደረጃ ይይዛል፡፡ በተመሳሳይ ጊዜም ክርስትና የዓለም ትልቁ ኃይማኖት መሆኑንም አስታውሱ (2 ቢሊዮን ተከታዮች አሉት)፡፡ ይህ የሙስሊሙ ዓለም በወንጌል ሊደረስ እንደሚችል በራስ መተማመንን ሊሰጠን ይገባል፡፡
እግዚአብሔር እስልምና በዚህ ሁኔታ በመቀጠል ሙስሊም ሕዝቦችን በማሳት ለዘለዓለም ከእርሱ አንዲለያቸው አይፈቅድም፡፡ እግዚአብሔር ሁሉ ወደ ንስሃ እንዲደርሱ እንጂ ማንም ሰው እንዲጠፋ አይፈልግም (2ጴጥ 3፡9)፡፡
ሙስሊሞች በእስልምና የማታለል መንፈስ ስለተሰላቹ እውነትን ተርበዋል፡፡ ሙስሊሞች ፍቅርን፣ ይቅርታንና ምህረትን ይጠማሉ፡፡ ሙስሊሞች ወደ ደም ማፍሰስና ወደ ጥላቻ የሚመራው ሃይማኖታዊ ጂሃድ እነርሱ እንደጠበቁት ስላልሆነላቸው በዚህ ዓለም ላይ ሰላምን እየፈለጉ ይገኛሉ፡፡ ሴቶች በሚደርስባቸው ስደትና የመብት ገፈፋ ተስፋ ቆርጠዋል፡፡ ሙስሊሞች ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረትን ይሻሉ፡፡
ሕይወት እንደ ኢየሱስ ተከታይ
ኢየሱስን ካመንኩኝ አስር ዓመታት አለፉ፡፡ እርሱ ወደ ራሱ ጠርቶኝ ከእርሱ ጋር ግላዊ ሕብረት እንዲኖረኝ ዕድልን ሰጠኝ፡፡ እስልምና ያንን ሊሰጠኝ አልቻለም ነበር፡፡
ጥዬአቸው ለመጣኋቸው ሙስሊም ወገኖቼ ጌታ ኢየሱስ ከእስልምና ጨለማ እንዲያወጣቸው በመጠየቅ ማልቀስን አቁሜ አላውቅም፡፡ የዚህን መጽሐፍ ገፆች በገለጣችሁ ቁጥር ይህ ጨለማ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ ወደ መረዳት ትመጣላችሁ፡፡ በአላህ ሥም ሁሉንም ዓይነት ክፋቶች የሚፈፅሙትን አሸባሪዎች የሚፈጥረው እስልምና ነው፡፡
አሁን መላው ዓለም እስልምና ምን እንደሚያስተምር ለመረዳት ይፈልጋል፡፡ በጣም ብዙ የሆነ የተሳሳተ መረጃ በመገናኛ ብዙኃንና በኢንተርኔት ተሰራጭቷል፡፡ የእኔ ግብ እነዚህ ሰዎች እያደረጉ ያሉትን ነገር ለምን እንደሚያደርጉ መረዳት ትችሉ ዘንድ እናንተን መርዳት ነው፡፡
ነገር ግን ለቁጣ ላነሳሳችሁ አልሻም፡፡ እንድታምኑ ግን ላነሳሳችሁ እፈልጋለሁ – ለእስልምና ውድቀትና በስሩ ላሉት ምርኮኞች በኢየሱስ ስም ነፃ መውጣት በእምነት እንድትንቀሳቀሱ እሻለሁ፡፡
ዶ/ር ማርክ ገብርኤል (ሙስጠፋ)
————————-
ይህ ምስክርነት Mark Gebriel; Islam and Terrorism; the Truth about ISIS, the Middle East and Islamic Jihad; 2015 ላይ የተተረጎመ ነው፡፡ ምስክርነቱ በመጽሐፉ ምዕራፍ አንድ፣ ምዕራፍ ሁለትና ምዕራፍ ሃያ አምስት ላይ የሚገኝ ሲሆን የደራሲውን መጽሐፍ በግዢ አማዞን ድረገፅ ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡