እውነተኛውን አዳኜን አወቅሁት! ባለታሪኩ፡- ወንድም ሰዒድ

እውነተኛውን አዳኜን አወቅሁት!

ባለታሪኩ፡– ወንድም ሰዒድ

ሰዒድ እባላለሁ፡፡ ተወልጄ ያደግሁት በአርሲ ዞን ውስጥ በምትገኝ አነስተኛ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ቤተሰቦቼ የባሕላዊ እስልምና እምነት ተከታዮች ሲሆኑ የኔም አስተዳደግ በዚሁ መልኩ ነበር፡፡ ነገር ግን ራሴን ወደማወቅ እድሜ ስደርስ ቁርኣንን በመቅራትና ሌሎች የእስልምና ትምህርቶችን  በመማር ጠንካራ ሙስሊም ለመሆን ከፍተኛ ጥረት አድርጌአለሁ፡፡ እንደኔ ሙስሊም የነበረው ታላቅ ወንድሜ ለሥራ ጉዳይ ራቅ ወዳለ ስፍራ ከሄደ በኋላ የክርስትናን እምነት ተቀብሎ ተመለሰ፡፡ ቤት ውስጥ አብረን በምንሆንበት ሰዓት ስለ መሲሁ ስለ ኢየሱስና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሲነግረን አንድ ሌላ ወንድሜ ብዙም ተቃውሞ ሳያቀርብ ይሰማው የነበረ ሲሆን እኔ ግን አጥብቄ እቃወመው ነበር፤ ሐሳቡንም ላለማስተናገድ ቆራጥ አቋም ያዝኩኝ፡፡ ታላቅ ወንድሜ መጽሐፍ ቅዱስን እቤት ውስጥ በሚያነብበት ሰዓት እኔ ደግሞ ከፊት ለፊቱ ተቀምጬ ቁርኣን ስቀራ ነገሩን ለሚታዘብ ሰው ፉክክር የገጠምን ይመስል ነበር፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሌላኛው ወንድሜ ከታላቁ ወንድማችን ጋር ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ የንስሃ ጸሎት ማድረጉን ሳውቅ ከልቤ አዘንኩኝ፡፡ አላህ ወንድሞቼን ከተያያዙት የስህተት ጎዳና ወደ ትክክለኛው የኢስላም መንገድ እንዲመልስልኝም ተማፀንኩት፡፡ እራሴን ችዬ መኖር የምችልበት እድሜ ላይ ባለመሆኔ ምክንያት “ካፊር” ከሆኑት ወንድሞቼ ተለይቼ መኖር ቢቸግረኝም ነገር ግን እንደ ነጂስ (ርኩስ) ቆጥሬያቸው እነርሱ በሚበሉበት ማዕድ አብሬያቸው ላልበላ በመወሰን ለብቻዬ መመገብ ጀመርኩኝ፡፡ በዚህ ወቅት የእነርሱ ወደ ክርስትና መግባት እኔን ይበልጥ ጠንካራ ሙስሊም እንድሆን አደረገኝ፡፡ የእስልምናንም ስርኣቶች ይበልጥ አጥብቄ በመያዝ ጥሩ ሙስሊም ለመሆን ከፍተኛ ጥረት አደርግ ነበር፡፡

ታላቅ ወንድሜ ስለ መሲሁ ስለ ኢየሱስ ትምህርቶችና ስለ መስቀል ላይ ሥራው ሲነግረኝ ብዙ ጥያቄዎች ይፈጠሩብኝ ነበር፡፡ የመሲሁ የኢየሱስ ትምህርቶችና የሙሐመድ ትምህርቶች ብዙ ልዩነቶች እንዳሏቸውና እንደሚጋጩም ተረዳሁ፡፡ ወንድሜ ደጋግሞ ይነግረኝ ከነበረው የመሲሁ ትምህርቶች መካከል ያስገርመኝ የነበረው ጠላቶቻችንን ስለመውደድና ክፉ ለሚያደርጉብን ሰዎች መልካም ስለማድረግ የሚናገረው ነበር፡፡ የሰው ቃል ብቻ እንደሆነ በማስበው መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ አይነት ወርቃማ መመርያ መኖሩ ያስደንቀኝ ነበር፡፡ አል-መሲህ ዒሳ እንደ እኛው ምግብ ይበላ የነበረ ሰው እንጂ በፍጹም አምላክ ሊሆን አይችልም ብዬ አጥብቄ አምን ስለነበር “እንዴት ሰውን አምላክ ነው ብላችሁ ታመልካላችሁ?” ብዬ እከራከር ነበር፡፡ “አንድ ሰው ደግሞ የሚድነው በገዛ ሥራው እንጂ በሌላ ሰው ሞት እንዴት ሊሆን ይችላል?” ብዬም እጠይቅ ነበር፡፡ እነዚህ ጥያቄዎቼም ምላሽ እንደሌላቸው አስብ ነበር፡፡ ዛሬ ግን እነዚህ ጥያቅዎች በሙሉ ተመልሰውኝ እኔም በተራዬ ቀድሞ በነበርኩበት ጭለማ ውስጥ ላሉ ወገኖቼ ጥያቄዎቸቻቸውን በመመለስ የመሲሁን ብርሃን እያበራሁላቸው እገኛለሁ፡፡ አምላክ የሆነው ኢየሱስ ሥጋ ለብሶ ወደምድር የመጣውና በመስቀል ላይ የሞተው እንደ እኔ ዓይነቱን ተስፋ የለሽ ኃጢዓተኛ ለማዳን መሆኑ ገብቶኛል፡፡

ከጊዜ በኋላ እነዚህ ክርስቲያኖች የተባሉ ሰዎች የሚፈፅሙትን ነገር የማወቅ ጉጉት ስላደረብኝ አንድ ቀን ለምን እነርሱ ወደሚሰበሰቡበት ሥፍራ ሄጄ አልመለከትም የሚል ሐሳብ ተከሰተልኝ፡፡ ነገር ግን የራሴው ሐሳብ መልሶ እኔኑ አስደነገጠኝ፡፡ ወንድሜ ወደ ቤተክርስቲያን አብሬው እንድሄድና እንድመለከት ደጋግሞ ቢጋብዘኝም ውስጤ እየፈለገ ነገር ግን አብሬው የመሄድ ድፍረት ማግኘት ተስኖኝ ለብዙ ቀናት ቆየሁ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ ቀን ማለዳ ያለኝን ድፍረት በሙሉ አሰባስቤ እኔው ራሴ ወደ ቤተክርስቲያን ይዞኝ እንዲሄድ ጠየቅሁት፡፡ ወንድሜም በሁኔታዬ እየተገረመ በደስታ ይዞኝ ሄደ፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን ለመሄድ የወሰንኩበት ምክንያት እስልምናን ትቼ ክርስቲያን ለመሆን በማሰብ አልነበረም፡፡ ያንን ማድረግ በህልሜም በውኔም አስቤው አላውቅም ነበር፡፡ ትዝ ይለኛል እንዲያውም አንድ ቀን አንዲት ክርስቲያን የነበረች ወጣት ልጅ “ሰዒድ አንድ ቀን ክርስቲያን መሆኑ አይቀርም” ብላ ስትናገር በመስማቴ ሳብያ እጅግ በጣም ተናድጄ ይህንን ያለችውን ልጅ በቁጣ ቃል ተናግሬያታለሁ፡፡ ለኔ ከእስልምና ውጪ ሌላ ሃይማኖት አይታየኝም ነበር፡፡ ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ወደ ቤተክርስቲያን ያቀናሁት የማየት ጉጉት ስላደረብኝ ብቻ እንጂ በፍጹም የክርስትናን ትምህርት ለመቀበል ተዘጋጅቼ አልነበረም፡፡ በእምነቴ የመፅናት አቋሜን በልቤ ይዤ ፈራ ተባ እያልኩኝ ወደ ጸሎት ቤቱ ወንድሜን ተከትየው ገባሁ፡፡ ጸሎት ተጸለየ ፤ መዝሙርም ተዘመረ፡፡  እነዚህ ክርስቲያኖች ሲጸልዩና ሲዘምሩ አምነውበትና ራሳቸውን ሰጥተው እንደሆነ ስረዳ በመደነቅ “ሰው ሐሰት ለሆነ ነገር እንዴት እንደዚህ ራሱን አሳልፎ ይሰጣል?”  ብዬ ለራሴ አሰብኩኝ፡፡

በዚያን ዕለት የነበረው ትምህርት በእግዚአብሔር ዘንድ የሰው ልጅ ያለውን ታላቅ ዋጋ የተመለከተ ነበር፡፡ ሰባኪው ሲሰብክ በጣም ደስተኛ ሆኖ ነበር፡፡ ሕዝቡም በደስታ ይሰማዋል፡፡ እዚያ ስፍራ ላይ የነበረው ሰው ሁሉ ፊቱ በፈገግታ የተሞላ  መስሎ ታየኝ፡፡ በጣም በመገረምም “እንዴት እንደዚህ ነፃና ደስተኞች ሊሆኑ ቻሉ?” ብዬም ራሴን ጠየቅሁ፡፡ ለሰላት ወደ መስጊድ እሄድ በነበረበት ሰዓት  ደስተኛ ፊት አላይም ነበር፡፡ እኔም ከስግደት መልስ ወደ ቤቴ ስሄድ አንድም ቀን ደስተኛ ሆኜ አላውቅም ነበር፡፡ እዚህ ጋር ሁሉም ሰው እንዲረዳልኝ የምፈልገው ነገር  ቢኖር አሁን ይህንን እተናገርኩ ያለሁት እስልምናን ስለተውኩኝ ሳይሆን በወቅቱ ይሰማኝ የነበረው እውነተኛ ስሜት ይኸው ስለነበረ ነው፡፡ ያንን ወቅት ከአሁኑ ሁኔታዬ ጋር ሳነፃፅር  “ሰላምን እተውላችኋለሁ ሰላሜንም እሰጣችሁዋለሁ፡፡ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም” በማለት መሲሁ ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ ይለኛል፡፡ አዎን፣ በእስልምና ውስጥ እውነተኛ ሰላም እንደሌለ አይቻለሁ፡፡ እውለተኛውን ሰላም ግን ከመሲሁ ከኢየሱስ  እግሮች ስር  አግኝቼአለሁ፡፡

እንግዲህ ስለ ክርስትናና ስለመጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ የማወቅ ጉጉት ስላደረብኝ ወደ ቤተክርስቲያን ደጋግሜ መሄዴን  ተያያዝኩት፡፡ በየ እሁዱም ከኋላ ወንበር ላይ ሆኜ ክርስቲያኖች የሚያደርጉትን በማየትና ትምህርታቸውን  በመስማት ወደ ቤቴ እመለስ ነበር፡፡  የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከቁርኣን ትምህርት ይልቅ ኃይል ያለው፣ በፍቅር የተሞላና ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚመራ መሆኑን እየተረዳሁ ስመጣ ውስጤ በፍርሃት ራደ፡፡ እስልምናን ለቅቄ በጣም እቃወመው የነበረውን የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ለመቀበል ጉዞ መጀመሬን ማመን ተሳነኝ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ በልቤ ውስጥ በተተከለው የእስልምና ትምህርት ላይ የነበረኝ ጠንካራ እምነት እንዲህ በፍጥነት ይናጋል ብዬ አስቤውም አልሜውም አላውቅም ነበር፡፡ ከብዙ ውስጣዊ ትግል በኋላ ጥቅምት 6 ቀን 1997 ዓ.ም. መሲሁ ኢየሱስን ለመከተከል ወስኜ ብዙ ሕዝብ በነበረት ጉባኤ ከሌሎች መሰሎቼ ጋር ወደፊት በመውጣት የንስሐ ጸሎት ጸለይኩኝ፡፡ ተቅበዝባዥ የነበረችውም ነፍሴም እውነተኛውን አዳኟን ስላወቀች ሰላምና እረፍትን  አገኘች፡፡ ለእኔ ዛሬ መሲሁ ኢየሱስ የምወደው የቅርብ ወዳጄ ሆኗል፡፡ የሰው ቃል  ብቻ እንደሆነ አስብ የነበረው መጽሐፍ ቅዱስም እውነተኛ የሕይወት ቃል መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ከእስልምና ወደ ክርስትና የነበረው ጉዞዬ እጅግ በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ ሁሉንም ነገር አሁን ላይ ቆሜ ሳስበው ይገርመገኛል፤ ከአዕምሮዬም በላይ ይሆንብኛል፡፡

በሕይወቴ በጣም የሚያሳዝነኝ አንድ ነገር ቢኖር ወላጅ አባቴ እኔ ያገኘሁትን ዘለዓለማዊ ሕይወት የሆነውን መሲሁ ኢየሱስን ሳያገኝ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ነው፡፡ ወላጅ እናቴን ጨምሮ ሁለቱ ወንድሞቼና ሦስቱ እህቶቼ፣ በአጠቃላይ መላው ቤተሰቤ በአሁኑ ሰዓት የመሲሁ የኢየሱስ ተከታዮች መሆናቸው ለእኔ ከምንም በላይ ደስታን እየሰጠኝ ይገኛል፡፡ ለሙስሊም ወገኖቼ ማስተላለፍ የምፈልገው መልእክት  ቢኖር  ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ የዘለዓለም ሕይወት አለመኖሩን ነው፡፡ ሰው መዳን የሚችለው መሲሁ ኢየሱስ ለእርሱ ኃጢአት ሲል እንደሞተና ከሞት እንደተነሳ ማመን ሲችል ብቻ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ብቸኛው የመታረቂያ መንገድ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ መሆኑን ተረድታችሁ፤ እርሱን ወደማወቅና ወደ ማመን ትመጡ ዘንድ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ፡፡ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በግላችሁ በማጥናት እውነቱ የቱ ጋር እንዳለ ትገነዘቡ ዘንድም አበረታታችኋለሁ፡፡ መሲሁ ኢየሱስን በማመን የዘለዓለምን ሕይወት ትወርሱ ዘንድና እኔ ያገኘሁትን የልብ ደስታ እናንተም ትካፈሉ ዘንድ ምኞቴና የዘወትር ጸሎቴ ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ይባርካችሁ!

ወንድማችሁ ሰዒድ ነኝ፡፡

ምስክርነቶች