በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚነሱ ተቃውሞዎችና ምላሾቻቸው

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚነሱ ተቃውሞዎችና ምላሾቻቸው

በመግቢያችን ላይ እንዳልነው በዚህች ዓለም ላይ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ተቃውሞዎችንና ትችቶችን ያስተናገደ መጽሐፍ የለም ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ በተለይም ደግሞ ከዘመነ አብርሆት (Enlightenment) በኋላ የተነሱ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በማጣጣልና በመተቸት ብዙ ጽሑፎችን ጽፈዋል፤ ብዙ ንግግሮችንም አድርገዋል፡፡ በዚያን ዘመን ብቅ ያለው የለዘብተኛ ሥነ መለኮት አስተምሕሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኙ አንኳር አስተምሕሮዎች የራሱን አማራጭ ትንታኔዎች በማዘጋጀት የክርስትናን መሠረት ለማናጋት በከፍተኛ ትጋት  ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በዘመናችን የሚገኙ አምላክ የለሾችና የሌሎች ሃይማኖታዊ ቡድኖች ምሑራን የለዘብተኛ ሥነ መለኮት አቀንቃኞችን ትምህርቶች በመቀበል ያስተጋባሉ፡፡

ዛሬ በተለያዩ መጽሐፍቶችና የኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ አውታሮች ተሰራጭተው የምናያቸው የተለያዩ የመሟገቻ ሐሳቦች ቅርፃቸው ቢለዋወጥ እንጂ ከጥንት ጀምሮ የነበሩና በቤተ ክርስቲያን አባቶች ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ምላሽ የተሰጠባቸው ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላቸውን ጥያቄ በነፃነት መጠየቃቸው ያስደስተናል፡፡ ጥያቄዎችንም በፍቅርና በአክብሮት መመለስ ኃላፊነታችን መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን እነዚህን ጥያቄዎች ከሚጠይቁ ወገኖቻችን መካከል አብዛኞቹ ፍላጎታቸው መልስ ማግኘት ሳይሆን ክርክር መሆኑ ነው፡፡ ለዚህ ነው እልፍ ጊዜ የተመለሰን ጥያቄ በሌላ ጊዜ ምንም ማሻሻያ ሳያደርጉለት መልሰው የሚጠይቁት፡፡ ከነዚህ ወገኖች ጋር የሚደረገው ውይይት ፍሬ አልባና አድካሚ ቢመስልም ነገር ግን መልስ ለመስጠት አንታክትም፡፡ ይህንን የምናደርግበት ምክንያቱ እውነትን በቅን ልብ የሚፈልጉ ሰዎች በእነዚህ የተሳሳቱ መረጃዎች እንዳይታለሉ ለመርዳት ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟልን?

በመጽሐፍ ቅዱስ ተኣማኒነት ላይ የሚነሳው የተለመደ ተቃውሞ መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟል የሚል መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህንን ስሞታ በተደጋጋሚ የሚያሰሙት ደግሞ ሙስሊም ወገኖቻችን ናቸው፡፡ ከቁርአን አስተምህሮና ከቀደሙት ሙስሊሞች እምነት ጋር የማይስማማ ቢሆንም አብዛኞቹ የዘመናችን ሙስሊሞች ስለ ነቢዩ መሐመድ የተተነበዩትን ትንቢቶች ለማስወገድና ለማድበስበስ አይሁድና ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን በርዘውታል የሚል አቋም አላቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚነሱ “ግጭቶች” እና “ሳይንሳዊ ስህተቶችን” የመሳሰሉ ውንጀላዎች በሙሉ የዚህኛው ውንጀላ ንዑሳን ክፍሎች ናቸው፡፡ ዓላማቸውም መጽሐፍ ቅዱስ “መበረዙን” ማረጋገጥ ነው፡፡ ለዚህ መሠረተ ቢስ ውንጀላ የሰጠነውን የማያዳግም ምላሽ ያንብቡ፡-

በዚህኛው ጽሑፋችን በዚህ ርዕስ ስር የሚነሱትን ንዑሳን ተቃውሞዎችን እንመልከታለን፡፡

  1. “መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በእርሱ ይጣረሳል”

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ስህተት አልባ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በውስጡ አስቸጋሪ የሆኑ ነገሮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን አባት የሆነው ቅዱስ አውጉስጢኖስ እንደተናገረው “በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በሚገኝ ግልጽ ግጭት ምክንያት ግራ የምንጋባ ከሆነ የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ተሳስቷል በማለት መናገር ትክክል አይደለም፡፡ ነገር ግን የእጅ ጽሑፉ ችግር አለበት ወይንም ደግሞ ትርጓሜው የተሳሳተ ነው፤ አለበለዚያም ደግሞ በትክክል አልተረዳችሁትም ማለት ነው፡፡”[1] በሌላ አባባል ስህተቶቹ የሚገኙት በቃለ እግዚአብሔር ውስጥ ሳይሆን በሰዎች የተሳሳተ መረዳት ውስጥ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ጽሑፋችን የቅዱሳት መጻሕፍት ግጭቶች ናቸው ተብለው የሚቀርቡትን ነጥቦች አንድ በአንድ የማየት ዓላማ የለንም፡፡ ነገር ግን ለእነዚህ ጥያቄዎች ጠቅለል ባለ ሁኔታ የሚከተሉትን መልሶች እንሰጣለን፡፡

  1. መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ ቢሆንም እንደ ማንኛውም መጽሐፍ፣ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ደግሞ ሲጻፍ ዘመን፣ ቦታና የተደራሲያኑን አውድ ባገናዘበ ሁኔታ ነው፡፡ ስለዚህ እንደየአስፈላጊነቱ አንድ ክስተት በሙሉ፣ በከፊል ወይንም ደግሞ ከተለየ የዕይታ ፅንፍ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ምንባቦች በትክክል ከተረዳናቸው እርስ በእርሳቸው በመገጣጠም ጥሩ ስብጥርን የሚፈጥሩ እንጂ እርስ በእርሳቸው የማይጋጩ መሆናቸውን መረዳት እንችላለን፡፡
  2. ተቃዋሚዎች ብዙ ጊዜ ከፊል ዘገባ የተሳሳተ ዘገባ ነው ወደሚል ድምዳሜ ፈጥነው ይደርሳሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ትክክል አይደለም፡፡ ይህ ትክክል ቢሆን ኖሮ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከተላለፉት መረጃዎች መካከል አብዛኞቹ ስህተት በሆኑ ነበር፣ ምክንያቱም ሙሉ የሆኑ መረጃዎችን ያለምንም መሸራረፍ ለማስተላለፍ የሚበቃ ጊዜና ቦታ የለምና፡፡ ብዙ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ታሪክ በተለያዩ አገላለጾች ወይንም ደግም ከተለየ የዕይታ ጽንፍ ያቀርባል፡፡ ስለዚህ ግልጠተ መለኮት የተለያዩ አገላለጾችን ያካትታል ማለት ነው፡፡ አራቱ ወንጌላት ተመሳሳይ የሆኑ ታሪኮችን ለተለያዩ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች ያቀርባሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም ተመሳሳይ የሆኑ ንግግሮችን በተለያዩ ቃላት ያቀርባሉ፡፡ ይህ የሚያመለክተው ጸሐፊያኑ ለተደራሲያኖቻቸው አስፈላጊ እንደሆኑ ያሰቧቸውን ነገሮች ብቻ ሊገነዘቧቸው በሚችሏቸው መንገዶች ያስተላልፉ እንደነበር ነው፡፡
  3. በሌላ መንገድ ስንመለከት ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ትምህርቶቹን ያስተላለፈው በአረማይክ ቋንቋ ሲሆን ነገር ግን ወንጌላት የተጻፉት በግሪክ ቋንቋ ነው፤ ስለዚህ ወንጌላት ኢየሱስ በአረማይክ ቋንቋ ያስተማራቸው ትምህርቶች የግሪክ ቋንቋ ትርጓሜዎች ናቸው ማለት ነው፡፡ እንደ ሙስሊሞች ደረቅ (Mechanical) የመገለጥ ፅንሰ ሐሳብ አመለካከት ካልተከተልን በስተቀር የተለያዩ ሰዎች ንግግሮችን ከአንዱ ቋንቋ ወደ ሌላው ቋንቋ ሲተረጉሙ ሙሉ በሙሉ በአንድ መንገድ ብቻ እንዲተረጉሙ መጠበቅ የማይቻል ነው፡፡
  4. አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ደግሞ ለመረዳት አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ችግሮቹ የሚፈጠሩት ክፍሎቹ ግልጽ ስላልሆኑና ከሌሎች ክፍሎች ጋር የሚጣረስ ትምህርት የሚያስተምሩ ስለሚመስሉ ነው፡፡ እነዚህን ግልጽ ያልሆኑ ክፍሎች ግልጽ በሆኑት ክፍሎች ብርሃን መመልከት ከተሳሳቱ ድምዳሜዎች እንድንድን ይረዳናል፡፡
  5. ሌላው የተቃዋሚዎች ችግር ግጭት ማለት በራሱ ምን ማለት እንደሆነ በትክክል አለማወቃቸው ነው፡፡ በሥነ አመክንዮ ውስጥ የግጭት አልባነት ሕግ (The Law of Non Contradiction) የተሰኘው የመጀመርያው ሕግ አንድ ነገር በአንድ ጊዜና በአንድ መንገድ የተለያዩ ሁለት ነገሮችን መሆን አይችልም የሚል ነው፡፡ ይህ ማለት አንድ ነገር በአንድ ጊዜና በሁለት መንገዶች፣ በሁለት የተለያዩ ጊዜያትና በአንድ መንገድ ወይንም ደግሞ በሁለት የተለያዩ ጊዜያትና በሁለት የተለያዩ መንገዶች ሁለት የተለያዩ ነገሮችን ሆኖ ቢገኝ አመክንዮታዊ ተቃርኖን አይፈጥርም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሁለት ሐሳቦች እርስ በርሳቸው ይጣረሳሉ ብለን ከመደምደማችን በፊት እነዚህ ነገሮች የሚያመለክቱት አንድ መንገድና ሁለት የተለያዩ ጊዜያትን ነውን? ሁለት መንገዶችንና አንድ ጊዜን ነውን? ሁለት የተለያዩ ጊዜያትንና ሁለት የተለያዩ መንገዶችን ነውን? በማለት መጠየቅ ያስፈልገናል፡፡

ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው “እገሊት ልጄ ናት” ብሎ ቢናገርና በሌላ ጊዜ ደግሞ ያችኑ ልጅ በመጥቀስ “እገሊት ልጄ አይደለችም” ብሎ ቢናገር በመጀመርያ ዕይታ የሚጣረስ ቢመስልም ነገር ግን ለነዚህ ንግግሮች አማራጭ ትርጉም ይኖር እንደሆን ሳንመረምር ንግግሮቹን በተቃርኖነት መፈረጅ አይኖርብንም፡፡ ምናልባት ልጁ እንደሆነች የተናገረበት ምክንያት አሳዳጊ አባቷ ስለሆነ ሊሆን ይችላል፡፡ ልጁ እንዳልሆነች የተናገረበት ምክንያት ደግሞ የአብራኩ ክፋይ እንዳልሆነች ለመናገር ፈልጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ጥቅሶች ይጋጫሉ ብለን ከመደምደማችን በፊት አመክንዮታዊ የማስታረቂያ መንገዶች ይኖሩ እንደሆን ማየት ተገቢ ነው፡፡

ይህንን ነጥብ ለማብራራት ያህል አንድ ምሳሌ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንስጥ፡፡ ኢየሱስ አጥምቋል ወይንስ አላጠመቀም? የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ በዮሐንስ 3፡22 መሠረት አጥምቋል “ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር።” ነገር ግን በዮሐንስ 4፡1-4 መሠረት አላጠመቀም “እንግዲህ ኢየሱስ ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት ያደርጋል ያጠምቅማል ማለትን ፈሪሳውያን እንደ ሰሙ ጌታ ባወቀ ጊዜ፥ ይሁዳን ትቶ ወደ ገሊላ ደግሞ ሄደ፤ ዳሩ ግን ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ ራሱ አላጠመቀም።”

ይህ በመጀመርያ ዕይታ ግልፅ ግጭት ቢመስልም ነገር ግን ጸሐፊው ለማለት የፈለገውን ነገር ለመረዳት ብንሞክር መልሱ በጣም ቀላል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለምሳሌ “አቶ እገሌ ቤት ሠራ” በማለት ብንናገር የቤቱ ባለቤት እርሱ መሆኑን ለማመልከት እንጂ ምሰሶና ማገሩን የሠራው ሙያተኛ እርሱ ነው ለማለት ተፈልጎ ላይሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የቤቱ ባለቤት በመሆኑ ምክንያት ቤቱን ሠርቷል እንላለን ነገር ግን ምሰሶና ማገሩን ከመምታት አንፃር ከሆነ ቤቱን የሠራው አናፂው እንጂ ባለቤቱ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በመጀመርያው ጥቅስ ውስጥ ኢየሱስ አጠመቀ የተባለበት ምክንያት የጥምቀቱ ባለቤት እርሱ ስለ ሆነና ሐዋርያት ደግሞ አገልጋዮች ብቻ በመሆናቸው ምክንት ሲሆን በሁለተኛው ጥቅስ ውስጥ ያጠመቁት ደቀ መዛሙርቱ እንጂ እርሱ አለመሆኑ የተነገረበት ምክንያት ደግሞ የጥምቀቱን ሂደት፣ ማለትም ሰዎችን በውሃ ውስጥ የማጥመቁን ተግባር የፈፀሙት ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ ራሱ ያለመሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ ስለዚህ በነዚህ ጥቅሶች መካከል ምንም ዓይነት ግጭት የለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ ተብለው የሚነገሩ አብዛኞቹ ግጭቶች በዚህ መልኩ ካሰብን በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው፡፡

  1. ሌላው ደግሞ በትርጉም ችግሮች ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭት የሚመስሉ ሐሳቦች መኖራቸውን መረዳት ያስፈልገናል፡፡ በአማርኛ ሲነበቡ ግጭት የሚመስሉ ነገር ግን ወደ ዋናዎቹ ቋንቋዎች በመሄድ ቁልፍ የሆኑትን ቃላት ትርጉሞች ስንመለከት ግልፅ የሚሆኑና በቀላሉ የሚፈቱ ችግሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል እግዚአብሔር ይጸጸታል ወይንስ አይጸጸትም? የሚለውን በተደጋጋሚ የሚነሳን ጥያቄ እንመልከት፡-

ይጸጸታል፡ “እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ።” ዘፍጥረት 6፡6 “እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ሳኦልን ስላነገሠ ተጸጸተ።” 1ሳሙኤል 15፡35

አይጸጸትም፡ “የእስራኤል ኃይል እንደ ሰው የሚጸጸት አይደለምና አይዋሽም አይጸጸትምም አለው።” 1ሳሙኤል 15፡29

መጽሐፍ ቅዱስ በነዚህ ቦታዎች ላይ የተጠቀመው የእብራይስጥ ቃል “ናኻም” የሚል ሲሆን በተለያዩ አውዶች ውስጥ የተለያዩ ትርጉሞች አሉት፡፡ እንደየአገባቡ፡- ማዘን፣ መጸጸት፣ ራስን ማበረታታት፣ (ለሠሩት ስህተት ራስን) መቅጣት፣ (ራስን) ማፅናናት፣ መዝናናት የሚሉና ሌሎች ትርጉሞችም አሉት፡፡ ስለዚህ በመጀመርያዎቹ ጥቅሶች ውስጥ እግዚአብሔር ተጸጸተ ተብሎ የተተረጎመው ማዘኑን ለመግለጽ ሲሆን አይጸጸትም የተባለው ደግሞ እግዚአብሔር የሠራው ሥራ ትክክል አለመሆኑን በማሰብ እንደ ሰው እንደማይጸጸት ለመግለጽ ነው፡፡ New International Version የኢንግሊዘኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በመጀመርያዎቹ ጥቅሶች ውስጥ “Grievd” የሚል ቃል የተጠቀመ ሲሆን የልብ ሐዘንን ያመለክታል፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ግድ የማይለው ስሜት አልባ ስላልሆነ የምናደርጋቸው ነገሮች ሊያስደስቱት ወይንም ደግሞ ሊያሳዝኑት ይችላሉ፡፡

ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ስናጠቃልልም ማሳሰብ የምንፈልገው ነገር ቢኖር ቅድመ ግንዛቤዎቻችን ካሳደሩብን ተፅዕኖ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ በትክክል መረዳት የሚያስችለንን በጎ ህሊና እንዳናጣ መጠንቀቅ ያስፈልገናል የሚል ነው፡፡

  1. “መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንሳዊ ስህተቶች አሉበት”

ክርስቲያኖች ሳይንሳዊ ምርምሮችን የሚያበረታቱ ቢሆኑም ነገር ግን ሳይንስን ለቃለ እግዚአብሔር እንደ መለኪያ መስፈርት አይቆጥሩትም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የተቀበልነው በሳይንስ መዝነን እውነት መሆኑን ስላረጋገጥን ሳይሆን መለኮታዊ ኃይሉ በሕይወታችን ውስጥ ሲሠራ ስላየን ነው፡፡ ሳይንስ በየጊዜው እንደ መለዋወጡ መጠን ሙሉ ፍፅምና የለውም፤ ስለዚህ ዘላለማዊውን እውነት ለመለካት እንደ መደበኛ መመዘኛ መስፈርት ሊቀርብ ይገባዋል የሚል እምነት የለንም፡፡ ከሳይንሳዊ እውነታዎች ጋር በጣም የሚስማሙ ብዙ ጥቅሶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ቢሆኑም ነገር ግን ሙስሊሞች የሃይማኖት መጽሐፋቸው እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ጥቅሶችን ከልክ በላይ እየለጠጡ እንደሚተነትኑት ዓይነት አካሄዶችን አናበረታታም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንሳዊ ስህተቶች እንዳሉበት የሚናገሩ ሰዎች ብዙ ጊዜ ከሚፍፅሟቸው ስህተቶች መካከል የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፡- መላምቶችንና የተረጋገጡ ሳይንሳዊ እውነታዎችን ያለመለየት፤ ክስተታዊና ሳይንሳዊ ንግግሮችን ያለመለየት፣ መጽሐፍ ቅዱስ የማይለውን ነገር ማስባል፣ ተምሳሌታዊ ንግግሮችን እንደ ቀጥተኛ ንግግሮች መቁጠር፣ ወዘተ. ይገኙበታል፡፡ እነዚህን አንድ በአንድ እንደሚከተለው እናያለን፡-

  • መላምቶችንና የተረጋገጡ ሳይንሳዊ እውነታዎችን ያለመለየት

መላምቶች (Theories) እውነት የመሆናቸው ሁኔታ ከፍተኛ ቢሆንም ነገር ግን ሙሉ በሙሉ እውነት ናቸው ተብለው የተደመደሙ አይደሉም፡፡ የሳይንስ ሊቃውንት ስለተለያዩ ጉዳዮች ባላቸው መረጃዎች ላይ ተመሥርተው እውነት የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆኑ ያመኑባቸውን መላምቶች ያቀርባሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የዩኒቨርስን አጀማመር በተመለከተ የተለያዩ መላምቶች ቢኖሩም ይበልጥ ተቀባይነት ያለው ግን ቢግ ባንግ (ታላቁ ፍንዳታ) በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ የቢግ ባንግ መላምት መቶ በመቶ የተረጋገጠ እውነታ ሳይሆን ነገር ግን በተነፃፃሪነት እውነት የመሆኑ ዕድል ከፍተኛ እንደሆነ በብዙ ሳይንቲስቶች ዘንድ የሚታመንበት ነው፡፡ ከተረጋገጠ ሳይንሳዊ እውነታ ጋር የሚጋጭ አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሌለ መሆኑን ብናውቅም ነገር ግን እውነታነታቸው መቶ በመቶ እስካልተረጋገጠ ድረስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይስማሙ ሳይንሳዊ መላምቶች መኖራቸው የሚያሳስበን ጉዳይ አይሆንም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ጋር እንደሚጋጭ የሚያምኑ ወገኖች በሳይንሳዊ መላምቶች እና በተረጋገጡ እውነታዎች መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ሰው የሚያስብ ፍጥረት ሆኖ በእግዚአብሔር አምሳል እንደ ተፈጠረ የሚናገር ሆኖ ሳለ ነገር ግን ሳይንቲስቶች ሰው ከዝንጀሮ መሰል እንስሳ በዝግመተ ለውጥ የመጣ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህ መቶ በመቶ የተረጋገጠ እውነታ ሳይሆን ነገር ግን ካሉት መረጃዎች በመነሳት ሰዎች ያቀነባበሩት ማላምት ነው፤ ስለዚህ ከንደነዚህ ዓይነት መላምቶች በመነሳት መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት እንደሆነ መናገር አንችልም፡፡ እነዚህ ትወራዎች በየጊዜው የሚሻሻሉና የሚለዋወጡ መሆናቸው በራሱ መቶ በመቶ እንዳንተማመንባቸው ያደርገናል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በኢትዮጵያ ውስጥ የተገኘው “አርዲፒቲከስ ራሚደስ” ተብሎ የተሰየመው ቅሪተ አካል እስከ አሁን ድረስ ያለውን የሰው ዝግመተ ለውጥ መላምት ውድቅ ሊያደርገው እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል፡፡

ሌላው በጣም አስገራሚው ነገር አንዳንድ በሳይንስ የሚነገሩ ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፉት ነገሮች ይልቅ ትልቅ እምነትን የሚጠይቁ መሆናቸው ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን አፅናፈ ዓለም ያለምንም ምክንያት ከምንም ነገር ወደ መኖር እንደ መጣ በብዙ ሳይንቲስቶች ዘንድ መታመኑ ነው፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ቁስና ኃይል ከአንዱ ዓይነት ወደሌላው ቢለዋወጡ እንጂ ሊፈጠሩም ሊጠፉም እንደማይችሉ ይናገራሉ፡፡ ይህ እርስ በርሱ ግጭትን ከመፍጠሩ ሌላ አፅናፈ ዓለም ያለ ምንም ምክንያት ከምንም ነገር ወደ መኖር እንደመጣ የሚናገረው ሐሳብ ከጊዜና ከስፍራ ውጪ መኖር የሚችል መለኮታዊ ኃይል አፅናፈ ዓለምን ወደ መኖር እንዳመጣው ከሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይልቅ ብዙ እምነትን የሚፈልግ ነው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ሳይንሳዊ መላምቶች መጽሐፍ ቅዱስን ስህተት ነው ሊያስብሉት አይችሉም፡፡

  • ክስተታዊና ሳይንሳዊ ንግግሮችን ያለመለየት

ዕለት ዕለት የምንጠቀማቸው ብዙ ንግግሮች ክስተታዊ (phenomenal) እንጂ ሳይንሳዊ ንግግሮች አይደሉም፡፡ ለምሳሌ ያህል የሳይንስ ምሑራንን ጨምሮ በዓለም ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ፀሐይ  “ወጣች” “ገባች” የሚሉትን ዓይነት ንግግሮች ይጠቀማሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ንግግሮች ከሳይንስ አኳያ ሲታዩ ትክክል አይደሉም፡፡ ፀሐይ የወጣችና የገባች የሚመስለን ለኛ እንጂ እንደ እውነቱ ከሆነ በራሷ ዛብያ ላይ በመዞር የተለያዩ ገፆቿን ወደ ፀሐይ የምታዟዙረው መሬናት፡፡ ነገር ግን እንደዚህ አይነት ክስተታዊ ንግግሮች ሳይንሳዊ ስላልሆኑ በስህተትነት አይፈረጁም ወይንም ደግሞ ከዕለት ተዕለት የመግባቢያ ንግግራችን ውጪ አይደረጉም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ብዙ ንግግሮች ሳይንሳዊ ከመሆን ይልቅ ክስተታዊ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ለምሳሌ በመጽሐፈ ኢያሱ 10፡12-13 ላይ እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎ እናነባለን፡-

እግዚአብሔርም በእስራኤል ልጆች እጅ አሞራውያንን አሳልፎ በሰጠ ቀን ኢያሱ እግዚአብሔርን ተናገረ በእስራኤልም ፊት እንዲህ አለ፦ በገባዖን ላይ ፀሐይ ትቁም፥ በኤሎንም ሸለቆ ጨረቃ፡፡ ሕዝቡም ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይ ቆመ፥ ጨረቃም ዘገየ። ይህስ በያሻር መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ፀሐይም በሰማይ መካከል ዘገየ፥ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለም።”

ትክክለኛውን ሳይንሳዊ ትንታኔ ብንጠቀም የቆመችው መሬት እንጂ ፀሐይ አይደለችም፡፡ ነገር ግን በዘመናችን እንዳሉት ብዙ ንግግሮች ሁሉ ይህም ክስተታዊ ንግግር በመሆኑ እንደ ሳይንሳዊ ስህተት ሊቆጠር አይገባውም፡፡ በዚህ ዘመንም ቢሆን ፀሐይ ለመግባት ብትዘገይ ክስተቱን የሚመሰክር የዐይን እማኝ “ፀሐይ ቆመች” ይላል እንጂ “መሬት ቆመች” አይልም፡፡

ሌላው ብዙ ጊዜ በተቃዋሚዎች እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንሳዊ ስህተት ተደርጎ የሚቀርበው የፀሐይና የጨረቃን ብርሃን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት 1፡16 ላይ የሚናገረው ቃል ነው፡-

እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ” ይላል፡፡

የጨረቃ ብርሃን የራሷ እንዳልሆነና ከፀሐይ ተቀብላ የምታንፀባርቀው እንደሆነ በሳይንስ የተረጋገጠ እውነታ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ ይህም ቃል እንደ ሌላው ሁሉ ክስተታዊ እንጂ ሳይንሳዊ አለመሆኑን እንረዳለን፡፡ በዓለም ላይ የሚገኝ የትኛውም ሰው በዕለት ተዕለት የመግባቢያ ንግግሩ ውስጥ “ጨረቃ ከፀሐይ ተቀብላ የምታንፀባርቀው ብርሃን” ከማለት ይልቅ  “የጨረቃ ብርሃን” በማለቱ ሳብያ የሳይንስ ዕውቀት እንደጎደለው እንደማይቆጠር ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስም ጨረቃን “ብርሃን” ብሎ መጥራቱ እንደስህተት ሊቆጠር አይገባውም፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ መጽሐፍ ቅዱስ የጨረቃ ብርሃን ከፀሐይ የመጣ መሆኑን የሚናገር ይመስላል፡፡ ለምሳሌ፡-

የሰማይም ከዋክብትና ሠራዊቱ ብርሃናቸውን አይሰጡም፥ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ትጨልማለች፥ ጨረቃም በብርሃኑ አያበራም።” (ኢሳይያስ 13፡10)

ባጠፋሁህም ጊዜ ሰማዮችን እሸፍናለሁ፥ ከዋክብቶችንም አጨልማለሁ ፀሐዩንም በደመና እሸፍናለሁ ጨረቃም ብርሃኑን አይሰጥም።” (ሕቅኤል 32፡7)

በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም” (ማርቆስ 13፡24)፡፡

በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የፀሐይ መጨለምና የጨረቃ ብርሃኗን ያለመስጠት እንደ ሳብያና ውጤት ነው የተቀመጠው፡፡ የነዚህን ዓረፍተ ነገሮች አወቃቀር ስናጤን የጨረቃ ብርሃኗን ያለመስጠት ምክንያቱ የፀሐይ መሸፈንና መጨለም እንደሆነ በሚያሳይ መልኩ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

እዚህ ጋር ሊሰመርበት የሚገባው ነጥብ ቢኖር በክስተታዊ ንግግሮች ምክንያት የትኛውም ማሕበረሰብ ሳይንሳዊ እውቀት የጎደለው እንደሆነ እንደማይታሰብ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስም እንደዚህ ዓይነት ንግግሮችን በመጠቀሙ ምክንያት ሳይንሳዊ ስህተት እንዳለበት በመቆጠር ሊነቀፍ እንደማይገባው ነው፡፡

  • መጽሐፍ ቅዱስ የማይለውን ነገር ማስባል

አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንሳዊ ስህተት እንዳለበት ለማሳየት የራሳቸውን ሐሳብ በመጨመር ሲያነቡትና የማይለውን ሲያስብሉት እናያለን፡፡ ለምሳሌ ያህል ቀስተ ደመና የፀሐይ ጨረር በውሃ ፍንጥቅጣቂ ወይንም እንፋሎት ውስጥ ሲያልፍ የሚፈጠር ነገር ነው፡፡ ስለዚህ የፀሐይ ብርሃንና ውሃ ባሉበት ዘመን ሁሉ ሊኖር የሚችል በመሆኑ በኖኅ ዘመን የተፈጠረ ሊሆን አይችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት 8፡12-17 ድረስ እንዲህ ይላለል፡-

እግዚአብሔርም አለ፦ በእኔና በእናንተ መካከል፥ ከእናንተም ጋር ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል፥ ለዘላለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው ቀስቴን በደመና አድርጌአለሁ፥ የቃል ኪዳኑም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል።  በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቲቱ በደመናው ትታያለች፡፡ በእኔና በእናንተ መካከል፥ ሕያው ነፍስ ባለውም ሥጋ ሁሉ መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ ሥጋ ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም። ቀስቲቱም በደመና ትሆናለች በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ያለውን የዘላለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ። እግዚአብሔርም ኖኅን፦ በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው ሁሉ መካከል ያቆምሁት የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው አለው።”

ብዙ ሰዎች ከዚህ ጥቅስ በመነሳት መጽሐፍ ቅዱስ ቀስተ ደመና በኖህ ዘመን እንደ ተፈጠረ እንደሚያስተምር ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን በዚህ ጥቅስ ውስጥ በፊት የነበረው ቀስተ ደመና ልዩ ትርጉም ማግኘቱን እንጂ ከዚያ በኋላ መፈጠሩን የሚያሳይ ነገር የለም፡፡

  • ፈሊጣዊ ንግግሮችን፣ ግነቶችንና ተለዋጭ ዘይቤዎችን የመሳሰሉ የንግግር ዓይነቶችን ቃል በቃል መተርጎም

መጽሐፍ ቅዱስ እንደማንኛውም የሥነ ጽሑፍ ዓይነት የተለያዩ የንግግር ዘይቤዎችን ይጠቀማል፡፡ ከነዚህም መካከል ፈሊጣዊ ንግግሮች (idioms)፣ ግነቶች (hyperboles) እና ተለዋጭ ዘይቤዎች (metaphores) ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን የንግግር ዓይነቶች እንደ ቀጥተኛ ንግግሮች የምንወስዳቸው ከሆነ ለስህተት እንዳረጋለን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱ ፈሊጣዊ ንግግሮች በቀጥታ ተወስደው እንደ ስህተት ከተቆጠሩት መካከል አንዱ የሚከተለው ነው፡-

እግዚአብሔር አምላክም እባቡን አለው፦ ይህን ስላደረግህ ከእንስሳት ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ትሆናለህ በሆድህም ትሄዳለህ፥ አፈርንም በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ትበላለህ” ዘፍጥረት 3፡14፡፡

እባቦች አፈር አይበሉም ነገር ግን በአካባቢያቸው የሚገኘውን ሁኔታ ለማወቅ አፈር በምላሳቸው ይቀምሳሉ፡፡ አፈር መብላት ውርደትና ሽንፈትን ለማመልከት የሚነገር የእብራይስጥ ፈሊጣዊ አነጋገር መሆኑን ከተገነዘብን ደግሞ ይህ ጥቅስ ይበልጥ ትርጉም ይሰጠናል፡፡ ለምሳሌ ያህል መዝሙር 72፡29፣ ኢሳይያስ 49፡23፣ ሚክያስ 7፡17 ያንብቡ፡፡ የእባብ “አፈር መብላት” ለሰዎች ውድቀት ምክንያት በመሆኑ ሳብያ እግዚአብሔር እንዳዋረደው የሚያሳይ የእብራውያን ፈሊጣዊ ንግግር ነው፡፡

ግነታዊ ዘይቤዎችን ካለማወቅ የተነሳ አንዳንዶች ዳንኤል 4፡10-11 ላይ የሚገኘውን ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ዝርግ እንደሆነች እንደሚያስተምር ለማስረዳት ይጠቀማሉ፡፡ ክፍሉ እንዲህ ይነበባል፡-

የራሴ ራእይ በአልጋዬ ላይ ይህ ነበረ እነሆ፥ በምድር መካከል ዛፍ አየሁ፥ ቁመቱም እጅግ ረጅም ነበረ። ዛፉም ትልቅ ሆነ፥ በረታም፥ ቁመቱም እስከ ሰማይ ደረሰ፥ መልኩም እስከ ምድር ሁሉ ዳርቻ ድረስ ታየ።”

ይህ ጥቅስ ሳይንሳዊ ስህተት እንዳለበት የሚናገሩ ወገኖች ዛፉ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ መታየት የሚችለው ምድር ዝርግ ከሆነች ብቻ ስለሆነ ይህ ጥቅስ የዝርግ ምድርን ጽንሰ ሀሳብ የሚያንጸፀባርቅ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን በመጀመርያ ደረጃ ይህ ክፍል ናቡ ከደነፆር የተባለ የባቢሎን ንጉሥ ያየውን ህልም የሚተርክ ነው፡፡ በህልም የሚታይ ብዙ ነገር ከተጨባጩ ዓለም ጋር የማይገጥም መሆኑን ከራሳችን ልምድ በመነሳት ማወቅ እንችላለን፡፡ ይህ ህልም እግዚአብሔር ለአረማዊው ንጉሥ በራሱ መረዳት መጠን ያሳየው ሲሆን የዛፉ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ መታየትና ጫፉ ሰማይን መንካት የግዛቱን ስፋት ለማሳየት የተነገረ ግነታዊ ዘይቤ ነው፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ምድር ዳርቻ፣ የዓለም ጫፍ፣ የዓለም ማዕዘናት፣ ወዘተ. የተነገሩ ሐሳቦች ምድር ዝርግ መሆኗን የሚናገሩ ሳይሆኑ መላዋን ዓለም ለማመልከት የተነገሩ ዘይቤዎች መሆናቸው መታወቅ አለበት፡፡

አንዳንድ ሰዎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ዝርግ ክብ (የእንጀራ ምጣድ መሳይ) መሆኗን እንደሚናገርና ይህም ደግሞ ሌላ ሳይንሳዊ ስህተት መሆኑን ሲናገሩ እንሰማለን፡፡ ለምሳሌ ያህል፡-

ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬ ነበርሁ፥ በቀላያት ፊት ክበብን በደነገገ ጊዜ(ምሳሌ 8፡27)

እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀመጣል፥ በእርስዋም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው እንደ ድንኳንም ለመኖርያ የሚዘረጋቸው…” (ኢሳይያስ 40፡26)፡፡

በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ “ክበብ” ለሚለው ቃል የገባው የእብራይስጥ አቻ “ኸውግ” የሚል ሲሆን እንደ ብዙዎቹ የጥንት ቋንቋዎች ሁሉ እብራይስጥም በዚያ ዘመን ለዝርግ ክብና ለሉላዊ ክብ (ኳስ መሰል ክብ) የተለያዩ ቃላት ስላልነበሩት ይህ ቃል እንደየአውዱ አገባብ ሁለቱንም ለማመልከት ያገለግል ነበር፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ ቃል (ኢዮብ 22፡14)ን ጨምሮ ሦስት ጊዜ ብቻ የተጠቀሰ ሲሆን በነዚህ ጊዜያት ዝርግ ክብን ለማመልከት ስለመዋሉ ምንም ፍንጭ የለም፡፡ ከዚህ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ የምድርን ትክክለኛ ቅርጽ በማመላከት ረገድ ቀዳሚው ጥንታዊ ሰነድ እንደሆነ ብንናገር የተሳሳትን አንሆንም፡፡ ይህ እንግዲህ አርስጣጣሊስ (አርስቶትል) የተባለው ግሪካዊ ፈላስፋ ምድር ሉላዊ ክብ መሆኗን ከመናገሩ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት መሆኑ ነው፡፡ ክርስቶፈር ኮሎምበስ የተባለውን የመካከለኛው ክፍለ ዘመን አሳሽ ጉዞውን እንዲያደርግ ያነሳሳው መጽሐፍ ቅዱስ እንደነበር ይነገራል፡፡[2]

ሳይንስ ከሚናገረው በተፃራሪ መጽሐፍ ቅዱስ ምድር በአንድ ቦታ ጸንታ የቆመች መሆኗን እንደሚያስተምር ለማሳየት ብዙ ጊዜ ከሚነሱት ጥቅሶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-

“…የምድር መሠረቶች የእግዚአብሔር ናቸውና፥ በእነርሱ ላይም ዓለምን አደረገ።” (1ሳሙኤል 2፡8)

“ምድርን ከስፍራው ያናውጣታል፥ ምሰሶችዋም ይንቀጠቀጣሉ።” (ኢዮብ 9፡6)

“ምድርና በእርስዋ ውስጥ የሚኖሩት ሁሉ ቀለጡ፥ እኔም ምሰሶችዋን አጠናሁ።” (መዝሙር 75፡3) 

የሰማይ አዕማድ ይንቀጠቀጣሉ፥ ከተግሣጹም የተነሣ ይደነግጣሉ።” (ኢዮብ 26፡11)

እነዚህን የመሳሰሉ ጥቅሶች ተለዋጭ ዘይቤዎች (metaphores) እና ግነቶች የሚንፀባረቁባቸው ሲሆኑ ቃል በቃል ሊተረጎሙ አይገባቸውም፡፡ ነገር ግን ስለ ምድር መሠረቶች የሚናገሩትን ጥቅሶች ቃል በቃል ብንተረጉም እንኳ “ኤሬትዝ” የሚለው የእብራይስጥ ቃል ምድርን በሞላ ለማመልከት ብቻ ሳይሆን የተወሰነ የየብስ ክፍልን ለማመልከትም ጭምር መዋል መቻሉን ከግምት ውስጥ ብናስገባ የምድር መሠረቶች የተባሉት ምድር የተሰራችባቸው ቁሶች ወይንም ደግሞ ክፍለ ዓለማት የተመሠረቱባቸው ጠንካራ የምድር ክፍሎች (continental blocks) እንደሆኑ ልንናገር እንችላለን፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ምድር በባዶ ህዋ ላይ (ከበታችዋ ምንም ነገር ሳይኖር) መንጠልጠሏን እንዲህ በማለት ይናገራል፡-

ሰሜንን በባዶ ስፍራ ላይ ይዘረጋል፥ ምድሪቱንም በታችዋ አንዳች አልባ ያንጠለጥላል” ኢዮብ 26፡7፡፡

ይህ በዚያ ዘመን የማይታወቅ አስገራሚ ሳይንሳዊ እውነታን የያዘ ዓረፍተ ነገር ነው፡፡

ሰዎች ባለማወቅም ይሁን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጣጣል ካላቸው እኩይ ፍላጎት የተነሳ የተለያዩ የመከራከርያ ነጥቦችን ቢያቀርቡም ነገር ግን እየተነዙ የሚገኙት ክሶች ሁሉ ሀሰት ስለመሆናቸው ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በአንጻሩ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ ሳይንሳዊ እውነታዎች ጋር በእጅጉ የተስማማ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ክፍሎችን ማግኘት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ያህል ሳይንቲስቶች የውኃን ዑደት ከማወቃቸው ከብዙ ዓመታት በፊት በሚከተሉት ጥቅሶች ውስጥ በግልጽ እንደሚታየው መጽሐፍ ቅዱሳችን ሦስቱንም የውኃ ዑደት ደረጃዎች በሚገባ አስቀምጧል፡-

አዳራሹን በሰማይ የሠራ፥ ጠፈሩንም በምድር ላይ የመሠረተ፥ የባሕርንም ውኃ ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሰው እርሱ ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው።” (አሞፅ 9፡6)

“የውኃውን ነጠብጣብ ወደ ላይ ይስባል፥ ዝናብም ከጉም ይንጠባጠባል፤ ደመናት ያዘንባሉ፥ በሰዎችም ላይ በብዙ ያንጠባጥባሉ።” (ኢዮብ 36፡27-28)፡፡

እነዚህን የሚመስሉ ብዙ ሳይንሳዊ ጥቅሶችን መጥቀስ ብንችልም ነገር ግን ሰዎች እነዚህን አይተው በመደነቅ ወደ ክርስትና እንዲመጡ ፍላጎታችን አይደለም፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች የቀረቡት መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንሳዊ ስህተቶች እንዳሉበት የሚለፍፉ ወገኖች የሚያስተላልፉት መረጃ ምን ያህል ከእውነት የራቀ መሆኑን ለማሳየት ብቻ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን እነዚህን በሚመስሉ ማስረጃዎች ለማረገገጥ አይደለም፡፡ እኛ ከነዚህ ይልቅ አሳማኝ የሆኑ ሌሎች ማስረጃዎች ስላሉን እነዚህን የመሳሰሉ ነጥቦችን መጠቀም አያሻንም፡፡ ስለዚህ ክርስቲያን ወገኖች ሙስሊሞ ቅዱሳት መጻሕፍቶቻቸው እውነተኛ የፈጣሪ ቃል መሆናቸውን ለማሳየት ጥቀሶችን ያለአግባብ በመጠምዘዝ ሳይንሳዊ ንግግሮችን ለመፍጠር የሚጠቀሟቸውን አካኼዶች እንዳይለማመዱ በመምከር ይህንን ርዕስ እናጠቃልላለን፡፡

  1. “መጽሐፍ ቅዱስ የግልበጣ ስህተቶች አሉበት”

የግልበጣ ስህተቶች ማለት ጥንታውያን ጽሑፎች ከብራና ወደ ብራና በሚገለበጡበት ወቅት የሚፈጠሩ የፊደል ግድፈቶችን የመሳሰሉ ስህተቶች ማለት ነው፡፡ በጥንት ዘመን የጽሕፈትና የኮፒ ማሽኖች ስላልነበሩ መጻሕፍት ይገለበጡ የነበሩት ልዩ ክህሎት በነበራቸው የጽሑፍ ባለሙያዎች ነበር፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች በሚገለብጡበት ሰዓት ፊደላትን መግደፍ፣ ቃላትን መዝለል፣ ቦታ ማቀያየርና የመሳሰሉትን ስህተቶች ይሠራሉ፡፡ የሃይማኖት መጻሕፍትን ጨምሮ የትኛውም ጥንታዊ ሰነድ ከንደነዚህ ዓይነት ችግሮች የፀዳ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች ሥልጣን ከርሱ በፊትም ሆነ በኋላ ከተጻፉት ጽሑፎች ሁሉ የላቀ በመሆኑ የግልበጣ ስህተቶች ተዓማኒነቱን አጠራጣሪ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ በአንዱ ብራና ውስጥ የተዘለለ ወይንም ደግሞ የተገደፈ ክፍል ቢኖር በሌሎች ብራናዎች ውስጥ ተስተካክሎ ይገኛል ወይንም ደግሞ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በመነሳት ትክክለኛውን አጻጻፍ ማወቅ ይቻላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ ከተባሉት የግልበጣ ስህተቶች መካከል አብዛኞቹ እዚህ ግቡ የሚባሉ ካለመሆናቸው የተነሳ ሊተረጎሙ እንኳ የማይችሉ ናቸው፡፡ የከፉ የሚባሉቱ ደግሞ እንደ ስምና ቁጥር ስህተቶች ያሉ ዋናውን መልዕክት ሊነኩ የማይችሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል በቀድሞ የአማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም (1954 እትም) 2ነገሥት 8፡26 አካዝያስ በነገሠ ጊዜ እድሜው 22 ዓመት እንደነበር ሲገልፅ 2ዜና 22፡2 ግን 42 ዓመቱ እንደነበር ይናገራል፡፡ የእጅ ጽሑፎችን ስንመለከት የእብራይስጡ 42 ሲል የሱርስትና አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ቅጆች 22 እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ከዚህም በመነሳት የጥንታውያን መዛግብት ምሑራን ትክክለኛው 22 እንደሆነና 42 የሚለው የግልበጣ ስህተት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ (አዲሱ መደበኛ ትርጉም 2ዜና 22፡2 የግርጌ ማስታወሻ ይመልከቱ)፡፡ እንደነዚህ ባሉ ጥቃቅን ችግሮች ምክንያት የትኛውም ጥንታዊ ሰነድ ተዓማኒነት እንደሚጎለው አይታሰብም፡፡ በዘርፉ እውቀት ያላቸው ምሑራን እነዚህን ችግሮች እንደ አሳሳቢ ችግሮች አይቆጥሯቸውም ነገር ግን ስለጉዳዩ እውቀት የሌለው ሕዝብ ግራ ሊጋባ ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ተዓማኒ እንዳልሆነ ለማሳየት የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ የሚገኙ ተቃዋሚዎች የሚነዙት የተጋነነ ፕሮፓጋንዳ ሲታከልበት ደግሞ ውዥንብሩ ይብሳል፡፡ ዶ/ር ባርት አህርማንን (Bart Ehrman) የመሳሰሉ ለክርስትና ጥላቻ ያላቸው ምሑራን በጥንታውያኔ መዛግብት ጥናት ዘርፍ ያላቸውን እውቅናና የሚድያ ሽፋን በመጠቀም ለገንዘብ ትርፍ በማሰብ ይህንን ጉዳይ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሲያውሉትና የዋሁን ሕዝብ ሲያወናብዱ እናያለን፡፡ ሙስሊም ጸሐፍት ደግሞ ፕሮፓጋንዳውን እንዳለ በመቅዳት ያስተላልፉታል፡፡ እነዚህ ወገኖች ለሚሰሟቸው ሰዎች የማይነግሩት አንድ እውነት ቢኖር የእነርሱ መጽሐፍ የከፋ ችግር እንዳለበት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የሙስሊሞች ቅዱስ መጽሐፍ የሆነውን ቁርአንን ብንወስድ የመጀመርያዎቹ ቅጂዎች ብዙ መለያየቶችና ግጭቶች ስለነበሩባቸው ዑሥማን የተባለ ኻሊፋ (የሙስሊሞች መሪ) በአራት ሊቃውንት አማካይነት እርማት ተደርጎ አንድ መደበኛ ቅጂ እንዲዘጋጅ ካደረገ በኋላ የበፊቶቹ ቅጂዎች እንዲቃጠሉ እንዳደረገ በጥንታውያን የእስልምና የታሪክ ድርሳናት ውስጥ ተጽፎ የተቀመጠ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት የተገኙ የተለያዩ የቁርአን የእጅ ጽሑፎች ብዙ የግልበጣ ስህተቶችና እርማቶች እንዳሏቸው ታውቋል፡፡[3] በተለይም ደግሞ ጀርመናዊው የጥንታውያን የአረብኛ ጽሑፎችና የቁርአን ፓሌኦግራፊ ሊቅ ዶ/ር ገርድ-ሩዲጀር ፑዊን (Gerd-Ruediger Puin) እና የሥራ ባልደረባቸው ግራፍ ቮን ቦሥመር (Graf Von Bothmer) ምርምር እያደረጉባቸው የሚገኙት “የሰነዓ የእጅ ጽሑፎች” በመባል የሚታወቁት የቁርአን ቅጂዎች ብዙ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች እንዳሉባቸው የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የየመን መንግሥት ምዕራባውያን ምሑራን እነዚህን መዛግብት እንዳያጠኑ ከጊዜ በኋላ ቢከለክልም ነገር ግን ጀርመናውያኑ ሊቃውንት ከ35,000 በላይ የሚሆኑ ፎቶግራፎችን በማይክሮ ፊልም አስቀድመው ስለወሰዱ የየመን መንግሥት ጽሑፎቹን ለመደበቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ የዚህ ጥናት ሙሉ ውጤትም በቅርብ ቀን ይጠበቃል፡፡

ነገር ግን የጥንት ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን እንኳንስ ሊያቃጥሉ ይቅርና ሊያቃጥሏቸው ለሚፈልጉ ሰዎች አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ ሞትን በመምረጥ ብዙዎቹ ሰማዕታት ሆነዋል፡፡ ክርስቲያን አባቶች ጥንታውያን የመጽሐፍ ቅዱስ የእጅ ጽሑፎች የግልበጣ ስህተቶች ቢኖሩባቸውም እንኳ ከማቃጠል ይልቅ በክብር ያስቀምጧቸው ነበር፡፡ ይህም ደግሞ ትክክለኛውን አነባበብ በመመርመር ማወቅ እንድንችል ረድቶናል፡፡ ስለቁርአን የግልበጣ ስህተቶች ያነሳንበት ምክንያት ሙስሊም ወገኖቻችን ጸሐፍታቸው መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ የሚጠቅሷቸው አንዳንድ ችግሮች የቁርአንም ችግሮች መሆናቸውን እንዲያውቁና ሁለቱንም መጻሕፍት በአንድ ሚዛን መመዘን እንዲጀምሩ ለማሳሰብ ነው፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የግልበጣ ስህተቶች የተለያዩ የእጅ ጽሑፎችን ጎን ለጎን በማስተያየት ትክክለኛዎቹ ምንባቦቻቸው ሊታወቁ የሚችሉ ናቸው፡፡ የመጀመርያው መልዕክት በነዚህ ምንባቦች ውስጥ የተጠበቀ ስለሆነ በእውነቱ ከሆነ መሰል ችግሮች ሊያሳስቡን የሚገቡ አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር እነዚህ ችግሮች እንዳይከሰቱ የማድረግ ኃይል ቢኖረውም ነገር ግን ቅዱስ ቃሉ በተፈጥሯዊ መንገድ ተጠብቆ እንዲኖር መርጧል፡፡

  1. “መጽሐፍ ቅዱስ ያልተፈጸሙ ትንቢቶች አሉበት”

መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ቃለ እግዚአብሔር መሆኑን የማይቀበሉ ሰዎች ከሚጠቅሷቸው ነጥቦች መካከል “ያልተፈጸሙ ትንቢቶች” ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ወገኖች እንደሚፈጸሙ የተነገሩ ነገር ግን ጊዜ ያለፈባቸው ትንቢቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ እንደ ሌሎቹ ውንጀላዎች ሁሉ እነዚህም ደግሞ እውነት አለመሆናቸውን የሚያረጋግጡ ምላሾቻችንን እንደሚከተለው እናቀርባን፡፡ አሁንም ዓላማችን ለያንዳንዱ ውንጀላ ምላሽ መስጠት ሳይሆን ዋና ዋና የተባሉትን ብቻ ለናሙናነት በመጥቀስ ለሚነሱት ተቃውሞዎች ሁሉ በቂ ምላሽ እንዳለን ማሳየት ነው፡፡

ብዙ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት የሚከተሉት ትንቢቶች የክርስቶስን ምጽዓት በተመለከተ የተነገሩ ሲሆኑ ነገር ግን ሳይፈጸሙ የቀሩ ናቸው፡-  

“በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም።” ማቴዎስ 10፡23

“እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።” ማቴዎስ 16፡28

“እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።” ማቴዎስ 24፡34

እነዚህን የመሳሰሉ ጥቅሶችን በመጥቀስ መጽሐፍ ቅዱስ የተሳሳቱ ትንቢቶች እንዳሉበት የሚናገሩ ሰዎች ያልተረዱት አንድ ነገር ቢኖር የክርስቶስ መምጣት ሁል ጊዜ የመጨረሻ ምጽዓቱን ብቻ የሚያመለክት አለመሆኑን ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሚልኪያስ 7፡1-4 እና ሉቃስ 7፡16 ስለ እግዚአብሔር መምጣት ይናገራሉ፤ ነገር ግን ስለሚታይ አካላዊ መምጣት አይደለም፡፡ አዲስ ኪዳናችን በብዙ ቦታዎች ላይ ስለ ክርስቶስ መምጣት ሲናገር አካላዊ ምጽዓቱን ብቻ ሳይሆን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመኖር በመንፈስ መምጣቱን የሚያመለክቱ ክፍሎች አሉት፡፡ ለምሳሌ ያህል፡-

ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ።” (ዮሐንስ 14፡18)

ይህ የመንፈስ ቅዱስን መውረድ ወይንም ደግሞ የክርስቶስን ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ መታየት የሚያመለክት ነው፡፡

ኢየሱስም መለሰ አለውም። የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን።” (ዮሐንስ 14፡23)

ይህ “መምጣት” ተፈጻሚ የሆነው መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ነበር፤ ምንያቱም የእግዚአብሔር መንፈስ የክርስቶስ መንፈስ ነውና፡-

እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም። ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፥ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። ገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያሥነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያሥነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል። (ሮሜ 8፡9-11) እንዲሁም 2ቆሮንቶስ 13፡5 ያንብቡ፡፡

“ምጽዓት” የሚለው ቃል በተጨማሪም አመጸኛ የሆነችዋን ቤተ ክርስቲያን ለመቅጣት በማይታይ ሁኔታ የሚሆነውን የክርስቶስን መምጣት ሊያመለክት ይችላል፡፡ (ራዕይ 2፡5፣ 2፡16፣ 3፡3)

እነዚህን ነጥቦች በልባችን ይዘን እስኪ አሁን ደግሞ ያልተፈጸሙ ትንቢቶች እንደሆኑ በአንዳንድ ሰዎች የተፈረጁትን ከላይ የተቀመጡትን ጥቅሶች እንመልከት፡፡

ማቴዎስ 10፡23 ላይ የተጠቀሰው መምጣት ደቀ መዛሙርቱ ተልዕኳቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከአገልግሎት መልስ ጌታ ኢየሱስ ወደ እነርሱ እንደሚጣ የሚያመለክት እንደሆነ በማቴዎስ 11፡1 እና በማርቆስ 6፡30 ላይ የተጻፈውን ሐሳብ በማንበብ መረዳት እንችላለን፡፡ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የአገልግሎት መመርያዎችን ከሰጠ በኋላ ወደ ገሊላ ለመሄድ እንደተለያቸውና በመጨረሻም ደቀመዛሙርቱ ያደረጉትን ሁሉ እንደዘገቡለት እናያለን፡፡ ስለዚህ ይህ ቃል ስለመጨረሻው ምጽዓት የሚናገር አይደለም፡፡

ማቴዎስ 16፡28 የክርስቶስን መለኮታዊ ክብር መገለጥ የሚያመለክት እንደሆነ ማርቆስ 9፡1 ላይ ያለውን ተጓዳኝ ምንባብ አንብበን መረዳት እንችላለን፡፡

እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ስትመጣ እስኪያዩ ድረስ፥ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ አላቸው።” (ማርቆስ 9፡1)

ይህ ቃል ከስድስት ቀናት በኋላ እንደተፈጸመ በማቴዎስ 17፡1-3 ላይ እንዲህ ተጽፎ እናነባለን፡-

ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። ፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው…”

2ጴጥሮስ 1፡16-18 ላይ የተጻፈው ቃልም ይህንኑ የሚረጋግጥ ነው፡-

የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ። ከገናናው ክብር በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን።

በተጨማሪም ይህ ትንቢት በበዓለ ሃምሳ ዕለት የክርስቶስ መንግሥት በምድር ላይ በሚታይ ሁኔታ መመሥረቱን የሚመለክት ሊሆንም ይችላል (የሐዋርያት ሥራ 2፣ 22፡16-18 ያንብቡ)፡፡

ማቴዎስ 24፡34 ደግሞ በሁለት የተለያዩ መንገዶች ሊመለስ ይችላል፡፡ የመጀመርያው “ይህ ትውልድ” የሚለው ሐረግ በግሪኩ  (ጌኔዎስ) የሚል ሲሆን “ሕዝብ” ወይም “ዘር” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡[4] በዚህም መሠረት የክርስቶስ ዳግም ምጽዓት እስኪሆን ድረስ የአይሁድ ሕዝብ ወይም ዘር ከምድረ ገጽ እንደማይጠፋ ለማመልከት የተነገረ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛው መልስ ደግሞ ክርስቶስ እየተናገረ የነበረው እርሱን እየሰማ ስለነበረው ትውልድ ሳይሆን የምጽዓቱ ምልክቶች ሲፈጸሙ ስለሚያየው ትውልድ ነው የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ትውልድ የተባለው በወቅቱ እርሱን ሲሰማ የነበረው ትውልድ ሳይሆን በምጽዓቱ ምልክት ዘመን የሚኖረው ትውልድ ሊሆን ይችላል፡፡

ስለ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት የሚናገር ያልተፈጸመ ትንቢት እንደሆነ በአንዳንዶች የሚጠቀስ ሌላ ቃል ራዕይ 1፡7 ላይ ይገኛል፡-

እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን።”

እዚህ ጋር የሚነሳው ተቃውሞ ክርስቶስን የወጋው ትውልድ ካለፈ ቆይቷል የሚል ነው፡፡ የዚህ መልስ በጣም ቀላል ነው፡፡ አባቶቹ የሠሩትን ጥፋት የሚደግፍ ትውልድ በአባቶቹ ኃጢዓት ስለሚጠየቅ በዚህ ስፍራ ላይ “የወጉት” የሚለው በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቶስን የሰቀሉትን አይሁድ ብቻ ሳይን ክርስቶስን ያልተቀበሉትን አይሁድ በሙሉ ያጠቃልላል፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ ክርስቶስን መካድ እርሱን ዳግመኛ እንደመስቀል እንደሚቆጠር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡-

አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው፤ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና።” (ዕብራውያን 6፡4-6)

በዚህ ጥቅስ መሠረት “የወጉት” የሚለው ቃል ክርስቶስን የካደን ማንኛውንም ሰው ያጠቃልላል ማለት ነው፡፡


ማጣቀሻዎች

[1] Geisler, Norman L. When Critics Ask, Introduction ይመልከቱ።

[2] http://hbu.edu/HBU/media/HBU/publications/bia_newsletter/vol-3_issue1_10-05bia.pdf 

[3] በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት “ድብቁ እውነት ሲገለጥ” በሚል ርዕስ በሳሂህ ኢማን የተጻፈውን መጽሐፍ ታነቡ ዘንድ እንጠቁማችኋለን፡፡

[4] Greek Dictionary Of The New Testament by James Strong, S.T.D., LL.D ይመልከቱ

መጽሐፍ ቅዱስ ተዓማኒ ቃለ እግዚአብሔር ነውን? ማውጫ