የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ማስረጃዎች

ታሪካዊ ማስረጃዎች

ቀደም ሲል እንደገለፅነው መጽሐፍ ቅዱስ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያሳይ መጽሐፍ በመሆኑ መለኮታዊ ትዕዛዛትን ብቻ ሳይሆን በዘመናት መካከል የሰው ልጆች ለእግዚአብሔር የሰጡትንም ምላሽ እንዲሁም ደግሞ እግዚአብሔር በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ እንዴት እንደሠራ የሚናገሩ ትራኬዎችንም በውስጡ አካቷል፡፡ አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሰዎችንና የቦታዎችን ስሞች እንዲሁም ዘመናትንና ክስተቶችን ያወሳሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ይዘቶች ከመብዛታቸው አንፃር መጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ መጽሐፍ እንደሆነ ብንናገር ከእውነት የራቅን አንሆንም፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት 2,930 ስለሚያህሉ ሰዎች የሚናገር ሲሆን 1,551 የሚሆኑ ቦታዎችን ይጠቅሳል፡፡ በይሁዶ-ወክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት ታሪኮች በሌሎች ሃይማኖታዊ መጻሕፍትና ጥንታዊ ታሪኮች ውስጥ ከሚገኙ ታሪኮች የተለዩ የሚያደርጓቸው ገፅታዎች አሏቸው፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ለታሪክ ከፍተኛ ግምት በነበራቸው ሰዎች በጥንቃቄ የተጻፉ ናቸው

አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ተዓማኒ የታሪክ ምንጭ ለመቀበል ይቸገራሉ ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች እንደ ሌሎቹ ጥንታውያን ታሪኮች በግብታዊነት የተጻፉ ስላልሆኑ በሃቀኝነታቸው ላይ መቶ በመቶ ልንተማመን እንችላለን፡፡ ዴቪድ ሼንክ የተባሉ ክርስቲያን ምሑር እንደሚከተለው ጽፈዋል፡

“…የብሉይ ኪዳን ታሪካዊ ዘገባዎች የተዋቀሩት በየትኛውም ስፍራ የሚገኝ ማንኛውም ማህበረሰብ ለትክክለኛ ታሪካዊ ዘገባ ፍላጎት በማያሳይበት ዘመን ነበር፡፡ ታሪክ ትርጉም አልባ የድግግሞሽ መዘውር መሆኑን ያምኑ ስለነበር አብዛኞቹ ባህሎች ትኩረት አይሰጡትም ነበር፡፡ የቻይና ነገስታትን የመሳሰሉ ዘገባዎችን የከተቡ ጥቂቶችም ቢሆኑ የሆነ ነገር ለማረጋገጥ በማሰብ እንጂ ለትክክለኛነቱ ደንታ አልነበራቸውም፡፡ ለምሳሌ ቻይናውያን ታሪኮቻቸውን የጻፉት በጥሩ ነገስታት ዘመን ሁሉም ነገር በጣም መልካም በሆነ ሁኔታ እንደተጓዘ እና በክፉ ነገስታት ዘመን ደግሞ በተቃራኒው እንደሆነ ለማረጋገጥ ነበር፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የታሪክ ዘገባዎች ይለያሉ፡፡ ታሪኮቹ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተገለጡ ነው የሚመጡት፡፡ እውነታነት (realism) የዘገባዎቹ መለያ ነው፡፡ መልካሞቹ እንደተመዘገቡ ሁሉ ክፉዎቹም ተመዝግበዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ተወዳጁ ንጉስ ዳዊት በዝሙት ውስጥ ገብቶ ነበር፤ እንዲሁም ደግሞ የሴቲቱን ባል ለማስገደል ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡ ባለፈው ምዕተ ዓመት ውሰጥ ሥነ  ቁፋሮ የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባዎች ትክክለኛነት መርምሯል፡፡ አሁን በሕይወት የሌሉት የሃያኛው ክፍለ-ዘመን ታላቅ የሥነ  ቁፋሮ ምሑር ዊልያም አልብራይት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ከጥንታዊ ታሪኮች መካከል ብቻኛው ትክክለኛ ታሪክ መሆኑን ተገንዝበዋለ፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ለምንድነው ለታሪክ ትክክለኛነት ይህንን ያህል ትኩረት የሚሰጡት? በትክክል እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ እንደሚሰራና ራሱን እንደሚገልጥ እርግጠኞች ከመሆናቸው የተነሳ ነው፤ እናም ታሪካቸው ትርጉም አለው፡፡ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝቦች ያንን እርግጠኛነት በጣም አጥብቀው ይዘዋል፡፡ ታሪካቸውንም በከፍተኛ ጥንቃቄ መዝግበዋል፡፡”[1]

ዶ/ር ዴቪድ በመጽሐፋቸው ውስጥ በትክክል እንዳስቀመጡት የጥንት እስራኤላውያን ለታሪክ የነበራቸው ግንዛቤ በዙርያቸው ከሚገኙ ሕዝቦች ሁሉ በጣም የተለየ ነበር፡፡ እነርሱ ታሪክን ይመለከቱ የነበሩት ፃድቅ፣ እውነተኛና አዕማሬ ኩሉ ከሆነው ከአምላካቸው አንፃር እንጂ በዘፈቀደ እንደሚሰረዝና እንደሚደለዝ ትረጉም አልባ ድግግሞሽ አልነበረም፡፡ ስለራሱ ክፋትና በታሪኩ ውስጥ ስለተከሰቱ አሳፋሪ ድርጊቶች በመጻፍ ለትውዶች የሚያስተላልፍና የራሱን ገመና ለዓለም የሚገልጥ ሕዝብ ለታሪክ ሃቀኝነት የሚሰጠው ክብደት ከፍ ያለ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከሌሎች የሃይማኖት መጻሕፍት አንጻር እንኳ መጽሐፍ ቅዱስን ብንመረምር ከእነርሱ በተለየ ሁኔታ በውስጡ የሚገኙ ታሪኮች እውነታነትን የተላበሱ መሆናቸውን መገንዘብ እንችላለን፡፡ እንደሌሎች መጻሕፍት በጎ በጎውን ብቻ በመጻፍ ቅዱሳን የተባሉትን ሰዎች ምንም ድካም እንደሌለባቸው ልዩ ፍጡራን በመሳል አያሞካሽም፡፡

በዓለም ላይ የሚገኝ የትኛውም ሃይማኖታዊ መጽሐፍ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሃቀኝነትን የተላበሱና እውነት መሆናቸው በተጨባጭ ማስረጃዎች ሊረጋገጡ የሚችሉ ጥንታዊ ታሪኮችን ሊያስነብበን አይችልም፡፡ በሌሎች መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ጥንታዊ ታሪኮች የሐቀኝነት ለዛ የሚጎድላቸውና አፈታሪኮች መሆናቸውን የሚያሳብቁ ይዘቶች አሏቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በጣም የተለየ ነው፡፡ ታሪኮቹ ስሜትን ከመግዛት አልፈው በሐቀኝነት ለዛቸው አዕምሯችንን የሚማርኩ ናቸው፡፡

 በ20ው ክፍለ ዘመን ከኖሩ ታላላቅ የሥነ ጽሑፍ ምሑራን መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ሲ. ኤስ. ሌዊስ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ወደ ክርስትና የመጡ ሰው ነበሩ፡፡ እኝህ  በካምባሪጅ ዩኒቨርቲ የመካከለኛው ዘመን እና የዘመነ ህዳሴ (ሬኔሳንስ) ጽሑፎች ምርምር ዋና ተጠሪ የነበሩ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን ሥነ ጽሑፋዊ ይዘት ከመረመሩ በኋላ የሚከተለውን ተናግረው ነበር፡-

“በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ግጥሞችን፣ የፍቅር ታሪኮችን፣ አቡ ቀለምሲሳዊ ጽሑፎችን፣ አፈ ታሪኮችን እና ተረታ ተረቶችን ሳነብ ነበር፡፡ ምን እንደሚመስሉም አውቃለሁ፡፡ አንዳቸውም ይህንን [ወንጌላትን] እንደማይመስሉ አውቃለሁ፡፡”[2]

ኖርማን ጌይዝለር የተባሉ ክርስቲያን አቃቤ እምነት የሚከተለውን ይሉናል፡-

የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በዐይን ምስክሮችና በወቅቱ በነበሩ ሰዎች የሕይወት ዘመን ነበር የታዩት፡፡ ሉቃስ የተጻፈው ከሐዋርያት ሥራ ቀደም ብሎ በ60 ዓ.ም.፣ ከኢየሱስ ሞት በኋላ 27 ዓመታትን ብቻ በመዘግየት ነበር፡፡ 1ቆሮንቶስ ከኢየሱስ ሞት 22 ወይንም 23 ዓመታትን ብቻ በመዘግየት በ 55 ወይንም 56 ዓ.ም. ነበር የተጻፈው፡፡ እንዲያውም ለውጥ አራማጅ የአዲስ ኪዳን ምሑር የሆኑት ጆን ኤ. ቲ. ሮቢንሰን መሠረታዊ የወንጌል መዛግብትን ከ40 እስከ 60 ዓ.ም. መካከል ያስቀምጧቸዋል፡፡ ትረካው ውሸት መሆኑን ለማጋለጥ የሚችሉ የዓይን እማኞች ከመኖራቸው የተነሳ አፈ ታሪክ መፈጠር የሚችልበት ጊዜ ወይንም መንገድ አልነበረም፡፡”[3]

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች የታሪክ ተመራማሪዎችን ፈተናዎች የማለፍ ብቃት አላቸው

እስካሁን ድረስ በታሪክ ተመራማሪዎች ተጠንቶ ስህተት መሆኑ የተረጋገጠ አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የለም፡፡ ከዚህ ቀደም በዚህ ሁኔታ የተፈረጁ አንዳንድ ክፍሎችም ቢሆኑ ጊዜያቸውን ጠብቀው ትክክለኛነታቸው ተረጋግጧል፡፡ ለምሳሌ ያህል ወንጌላዊው ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ 18፡12 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ በአካባቢው በነበረበት ዘመን ጋልዮስ የተባለ ሰው የአካይያ አገረገዥ እንደነበር ጽፏል፡፡ ነገር ግን ይህንን የሚያሳይ ምንም ዓይነት መረጃ ባለመገኘቱ ብዙ ምሑራን በዚያ ዘመን እንዲህ አይነት ማዕረግ ለሰዎች መሰጠቱን እንኳ ይጠራጠሩ ነበር፡፡ ነገር ግን በ1905 ዓ.ም. የዶክትሬት ትምህርቱን ሲያጠና የነበረ አንድ ፈረንሳዊ ዴልፊ ከምትባል የግሪክ ከተማ የተሰበሰቡ ጥንታዊ ቅርጻ ቅርጾችን ሲያስስ ሳለ ከብዙ ጽሑፎች መካከል አንድ ላይ ሲገጣጠሙ የሮም ንረጉሥ ከነበረው ከቀላውዴዎስ ቄሣር የተጻፈ ትርጉም የሚሰጥ ደብዳቤ መፍጠር የሚችሉ ቁርጥራጮችን አገኘ፡፡ ይህ ደብዳቤ ተጽፎ የነበረው ለአካይያ አገረ ገዥ ለጋሊዮስ ነበር፡፡ ይህ ደብዳቤ በ52 ዓ.ም. የተጻፈ መሆኑ ስለተረጋገጠ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ከተማ የሄደበትን ትክክለኛ ጊዜ ለማወቅ አስችሏል፡፡ ይህንን በተመለከተ ጄይ ስሚዝ የተባሉ ክርስቲያን አቃቤ እምነት እንዲህ በማለት ጽፈዋል፡-

“…በሐዋርያት ሥራ 18፡12 ላይ ጋልዮስ የተባለ ሃገረ ገዥ ተጠቅሷል፡፡ ነገር ግን የታሪክ ተማራማሪዎች እንደተናገሩት የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ጸሐፌ ታሪክ የሆነው ፕሊኒ  ጋልዮስ ሃገረ ገዥ መሆኑን አልጻፈም ምክያቱም ሃገረ ገዥ የሚለው ማዕረግ እስከ አንደኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ አልመጣም ነበርና፡፡ ስለዚህ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከፕሊኒ በኋላ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን ተጽፎ ነገር ግን የመጀመርይቱ ቤተ ክርስቲያን በነበረችበት ዘመን የተጻፈ የሚያስመስል ስለሆነ ስህተት መሆን አለበት ብለው ነበር፡፡ ይህ የሆነው ግን የዴልፊ ቅርጻ ቅርጾች እስከተገኙበት ጊዜ ድረስ ብቻ ነበር፡፡ ይህም ጋልዮስ በ52 ዓ.ም. ለአንድ ዓመት ያህል አገረ ገዥ እንደነበር ይጠቅሳል፡፡ ይህ የሚያረጋግጠው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እውነት መሆኑን ብቻ ሳይሆን እንደዚህ በጣም ትክክል ለመሆን የሐዋርያት ሥራ ጸሐፊ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን የዐይን ምስክር መሆን እንዳለበትም ጭምር ነው፡፡”[4]

ሰር ዊልያም ራምሰይ የተባሉ እንግሊዛዊ የታሪክ ምሑር የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ተዓማኒነት እንደሌላቸው የሚያምኑ ሰው ነበሩ፡፡ በተለይም ደግሞ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሁለተኛው ክፍለ ዘመን ፈጠራ እንደሆነ አጥብቀው ያምኑ ነበር፡፡ ነገር ግን እኚህ ምሑር በትንሹ ኢስያ (Asia Minor) ውስጥ የተለያዩ የሥነ ቁፋሮ ግኝቶችን ሲመረምሩ ሳሉ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው የሚገኙ ብዙ ነገሮች እውነት መሆናቸውን የሚያረጋግጡ የትየለሌ ማስረጃዎችን አገኙ፡፡ እኚህ ምሑር ሉቃስ መጽሐፉን የጻፈው በመጀመርያው ምዕተ ዓመት (ሐዋርያት በነበሩበት ዘመን) መሆኑን ብቻ ሳይሆን ሉቃስ ከታላላቅ  የታሪክ ጸሐፊዎች መካከል መመደብ እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡[5]

በመንጌላት ውስጥ የሚገኙት የኢየሱስ ታሪኮች በዓለማውያን እና ክርስቲያን ባልሆኑ ሰዎች በተጻፉ መዛግብት የተረጋገጡ ናቸው

ቀደም ሲል የመጽሐፍ ቅዱስ ማዕከላዊ ትኩረት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን መግለፃችን ይታወሳል፤ ስለዚህ በማስከተል በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኘው የኢየሱስ ሕይወት ትረካ እውነት መሆኑን የሚያረጋግጡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ የሚገኙ መስረጃዎችን አጠር አድርገን በመመልከት ይህንን ርዕስ እንቋጫለን፡፡

ኢየሱስ በኖረበት ዘመን አካባቢ የነበሩ የተለያዩ የታሪክ ጸሐፊያን ስለ እርሱ ሕይወት ጽፈዋል፡፡ የምንጠቅሳቸው ጸሐፊያን ክርስቲያኖች ያልነበሩ ሲሆኑ የሚሰጧቸው መረጃዎች በምሑራን ዘንድ ክብደት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡

  1. ካይውስ ፕሊኒውስ ሴኩንዱስ ወይንም ደግሞ ፕሊኒ ትንሹ በመባል የሚታወቀው በ62 ዓ.ም. ጣሊያን ሚላን አካባቢ የተወለደው ጸሐፌ ታሪክ በንጉሥ ትራጃን ዘመነ መንግሥት በአሁኗ ቱርክ ውስጥ የሚገኙ የሮም ግዛቶችን ያስተዳድር ነበር፡፡ ይህ ሰው ያሳድዳቸው ስለ ነበሩ ክርስቲያኖች ከንጉሡ ትዕዛዝን ለመቀበል በጻፈው ደብዳቤ ውስጥ እንዲህ የሚል ቃል አስፍሮ ነበር፡- “ክርስቲያኖች ስለመሆናቸው በቀጥታ ጠየቅኋቸው… በእምቢተኝነት የፀኑትን ውሳኔ አስተላለፍኩባቸው… ክርስቲያኖች መሆናቸውን የካዱቱ… ያንተን ምስልና የአማልክቶችን ምስል አመለኩ ክርስቶስንም ተሳደቡ፡፡ በተወሰነ ቀን ከንጋት በፊት ይሰበሰቡና ለአምላካቸው ለክርስቶስ ይዘምራሉ… እውነቱን ማወቅ አስፈላጊ ሆኖ ስለታየኝ ዲያቆናት በመባል የሚጠሩ ሁለት ሴት አገልጋዮችን በማሰቃየት ያገኘሁት አስቀያሚ የሆነ ያልተጨበጠ እምነትን ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህ ምርመራውን በማቆም ለአደጋ የተጋለጡትን ሰዎች በተመለከተ… አንተን ለማማከር ተጣደፍኩኝ፡፡ ከሁሉም እድሜ፣ የኑሮ ደረጃ እና ከሁለቱም ፆታዎች የሆኑ ብዙ ሰዎች ለአደጋ ተጋልጠዋልና፡፡”[6]

በዚህ ደብደቤ ውስጥ ፕሊኒ ብዙ ክርስቲያኖች ለክርስቶስ ነፍሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት ዝግጁዎች እንደነበሩ ይመሰክራል፤ የጥንቶቹም ክርስቲያኖች ክርስቶስን ያመልኩት እንደነበር ይናገራል፡፡ ይህ ኢየሱስ አምላክ ነው የሚለው ትምህርት ከኒቂያ ጉባኤ በኋላ እንደመጣ በማስመሰል የሚናገሩትን ሰዎች የተሳሳተ ውንጀላ ውድቅ የሚያደርግ ማስረጃ ነው፡፡

  1. ሮማዊ ባለ ስልጣን እና ጸሐፌ ታሪክ የነበረው ታሲተስ ክርስቶስን እና ክርቲያኖችን በተመለከተ እንደሚከተለው ጽፏል፡-“ጉርምርምታውን ለማስቆም ኔሮ ክርስቲያኖች በመባል በሚጠሩ በነውረኛ ስራቸው በሚታወቁት አንዳነድ ሰዎች ላይ ወንጀሉን በማላከክ በከባድ ቅጣቶች እንዲቀጡ አደረገ፡፡ ይህንን ስም ያስገኘው ክርስቶስ; ጢባሪዮስ ቄሣር ንጉሥ በነበረበት ዘመን ወኪል አስተዳዳሪ በነበረው በጳንጢዮስ ጲላጦስ ትእዛዝ ተገድሏል፡፡ ይህ መርዛማ አምልኮት ለጊዜው በቁጥጥር ስር ቢውልም ነገር ግን ይህ ክፋት በተጀመረባት በይሁዳ ብቻ ሳይሆን ከዓለም ዙርያ ሁሉ ቆሻሻና አስቀያሚ የሆኑ አስተሳሰቦች ሁሉ በሚጠራቀሙባት በሮምም ውስጥ እንደ ወረርሺኝ ተስፋፍቷል፡፡”[7]

ታሲተስ የጻፈው ታሪክ አውዱ የአዕምሮ መታወክ ችግር የነበረበት ንጉሥ ኔሮ የሮም ከተማ እንድትቃጠል ትዕዛዝ የሰጠው ራሱ ሆኖ ሳለ ወንጀሉን በክርስቲያኖች ላይ እንዳላከከ የሚናገር ነው፡፡ ከአጻጻፉ እንደምንረዳው የአረማውያን አማልክትን ባለማምለካቸው የተነሳ ታሲተስ ክርስቲያኖችን የሚጠላ እና ክፉ ስሞችን የሰጣቸው ቢሆንም ነገር ግን ክርስቶስን በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን የሚያረጋግጡ ነጥቦችን ጠቅሷል፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንደተናገረው ክርስቶስ በጢባርዮስ ቄሣር ዘመን የይሁዳ ገዢ በነበረው በጲላጦስ ትዕዛዝ መገደሉ እና ክርስቲያኖች ስያሜያቸውን ከእርሱ ማግኘታቸው የታሪክ እውነታ ነው ማለት ነው፡፡ ታሲተስ ክርስቲያኖችን የሚጠላ ሰው እንደ መሆኑ መጠን ክርስቶስ መሰቀሉን የሚናገረው የክርስቲያኖች እምነት አንደንዶች እንደሚሉት የፈጠራ ታሪክ ቢሆን ኖሮ እነርሱን ከማጋለጥ ይልቅ እነርሱን ሊደግፍ የሚችል ነገር በውሸት ወይንም በስህተት እንደማይጽፍ ግልፅ ነው፡፡ ይህ በወቅቱ በነበሩ ሕዝቦች ዘንድ የክርስቶስ ስቅለት በጣም የሚታወቅ ታሪካዊ ክስተት መሆኑን ያሳል፡፡

  1. ጆሲፈስ ፍላቪየስ (ዮሴፍ ወልደ ኮሪዮን) በመባል የሚታወቀው የአይሁድ እና የሮም ታሪክ ጸሐፊ በ93-94 ዓ.ም. በጻፋቸው ሁለት መጽሐፍቱ ውስጥ ክርስቶስን ጠቅሶታል፡፡ “ስለዚህ [ሐናንያ] ዳኞችን በመሰብሰብ ክርስቶስ ብለው የሚጠሩት የኢየሱስ ወንድም የሆነውን ያዕቆብን ከሌሎች ጋር በፊታቸው አቀረበ፡፡ በሕግ ጥሰት ከከሰሳቸው በኋላም በድንጋይ እንዲወገሩ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡” (Antiquities XX 9:1)

ይህ ዘገባ የኢየሱስ ወንድም የሆነውን የሐዋርያው ያዕቆብን አሟሟት የሚናገር በመሆኑ ኢየሱስ በምድር ላይ በትክክል መኖሩን የሚያሳዩ ክርስቲያናዊ ያልሆኑ መዛግብት እንዲጠቀሱላቸው ለሚፈልጉ ወገኖች ትልቅ መልስ ነው፡፡ አዲስ ኪዳንም ደግሞ ኢየሱስ ያዕቆብ የተባለ የሥጋ ወንድም እንደነበረው መናገሩ ትክክል መሆኑን ይመሰክራል፡፡ የጌታ ወንድም የሆነው የያዕቆብ አሟሟት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ባለመጠቀሱ ጆሲፈስ ታሪኩን ያሰፈረው ከአዲስ ኪዳን በመቅዳት አለመሆኑን ስለሚያመለክት በብዙ ምሑራን ዘንድ ክብደት እንዲሰጠው አድርጓል፡፡ ጆሲፈስ ስለ ኢየሱስ የጻፈው ሌላው አስደናቂ መረጃ የሚከተለው ነው፡-

“በዚህ ጊዜ ሰው ብሎ እርሱን መጥራት ተገቢ ከሆነ ኢየሱስ የተባለ ጥበበኛ ሰው ነበር፤ የድንቅ ሥራዎች አድራጊ፣ እውነትን በደስታ የሚቀበሉ አይነት ሰዎች መምህርም ነበር፡፡ ከአይሁድ እና ከአሕዛብ ብዙዎችን ወደ ራሱ ሳበ፡፡ እርሱም ክርስቶስ ነበረ፣ እናም ጲላጦስ ከኛው መካከል ታላላቆች የሆኑቱ በሰጡት አስተያየት እንዲሰቀል ፈረደበት፡፡ በሶስተኛው ቀን ሕያው ሆኖ ስለታያቸው መጀመርያ የወደዱት አልከዱትም ነበር፡፡ ይህም መለኮታዊ መልዕክተኞች የሆኑ ነቢያት እነዚህንና ሌሎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ትንቢቶችን ስለ እርሱ እንደተናገሩት ነው፡፡ ከእርሱ ስያሜውን ያገኘው ነገደ ክርስቲያን እስከ ዛሬ ድረስ ከምድረ ገፅ አልጠፋም፡፡”[8]

  1. የባቢሎናውያን ታልሙድ የጥንት አይሁዳውያን ሕግጋት፣ ትምህርቶች እና ታሪኮች ስብስብ ነው፡፡ የአይሁድን ትምህርት በመደገፍ የኢየሱስን መለኮታዊነት የሚክድ ቢሆንም ነገር ግን ስቅለቱን በተመለከተ የሚሰጠን ጠቃሚ መረጃ አለ፡፡ “በፋሲካ ዋዜማ ዬሹዋ (ኢየሱስ) ተሰቀለ፡፡ ከመገደሉ በፊት 40 ቀናት ቀደም ብሎ አዋጅ ነጋሪ በመውጣት ‘አስማትን በመለማመድ እስራኤልን ወደ ክህደት ስለመራ ይወገራል፡፡ እርሱን በመደገፍ የሆነ ነገር መናገር የሚችል ፊት ለፊት ይውጣና ስለ እርሱ ይሟገት’ በማለት ጮኾ ነበር፡፡ እርሱን የሚደግፍ ምንም ነገር ባለመቅረቡ በፋሲካ ዋዜማ ተሰቀለ፡፡”

ከላይ ባነበብነው የታልሙድ ዘገባ መሠረት የአይሁድ የቀደመ ሐሳብ ኢየሱስን በሕጋቸው መሠረት በድንጋይ በመውገር መግደል ቢሆንም ነገር ግን እነርሱ እንዳሰቡት ሳይሆን ኢየሱስ በሮማውያን ልማድ መሠረት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞቷል፡፡ ይህም በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተተነበየው ነው፡፡ ይህ ዘገባ ኢየሱስ ልዕለ ተፈጥሯዊ የሆኑ ተዓምራትን ማድረጉን እና በአይሁድ ፋሲካ ዋዜማ መሰቀሉን የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ አስደናቂ ማስረጃ ነው፡፡

  1. የኢስጦኢኮች ፈላስፋ የሆነው ሶርያዊው ማራ በር-ሴራፒዮን (ማራ ወልደ ሴራፒዮን) በእስር ቤት ውስጥ ሆኖ የሚከተለውን ደብዳቤ ለልጁ ጽፎ ነበር፡- “ሶቅራጥስን በመግደል የአቴንስ ሰዎች ምን አተረፉ? ድርቅና ወረርሽኝ ለሰሩት ወንጀል እንደ መቀጣጫ መጣባቸው፡፡ የሳሞስ ሰዎች ፓይታጎረስን በማቃጠላቸው ምን አተረፉ? በቅጽበት መሬታቸው በአሸዋ ተሸፈነ፡፡ አይሁድ ጥበበኛ ንጉሣቸውን በመግደላቸው ምን አተረፉ? ልክ ከዚያ በኋላ መንግሥታቸው አከተመለት፡፡ አምላክ ለነዚህ ሦስት ሰዎች በትክክለኛ ፍረድ ተበቀለለላቸው፡፡ አቴናውያን በረሃብ ሞቱ፡፡ ሳሞሳውያን በባህር ሰጠሙ፡፡ አይሁድ ተፍረክርከው ከምድራቸው ላይ በመባረር ሙሉ በሙሉ ተበትነው ኖሩ፡፡ ነገር ግን ሶቅራጥስ መሞቱ ለበጎ አልሆነም፡፡ በፕላቶ ትምህርት ኖሯልና፡፡ ፓይታጎረስ መሞቱ ለበጎ አልሆነም፡፡ በሄራ ሐውልት ውስጥ ኖሯልና፡፡ ጥበበኛውም ንጉሥ መሞቱ ለበጎ አልሆነም፡፡ ራሱ ባስተማረው ትምህርት ኖሯልና፡፡”

ምንም እንኳ ክርስቶስን በስም ባይጠቅሰውም ጲላጦስ ፊት ቀርቦ በነበረበት ወቅት ከተመሰረቱበት ክሶች መካከል ‹ራሱን የአይሁድ ንጉስ አደረገ› የሚለው አንዱ በመሆኑ ይህ ፈላስፋ ጥበበኛ ንጉሥ ብሎ የጠራው እርሱን መሆኑ ምንም አያጠራጥርም፡፡ ሮማዊው ጄነራል ታይታስ (ቲቶ) ኢየሩሳሌምን የደመሰሰው እና አይሁድ የተበተኑት በ70 ዓ.ም. (ክርስቶስ ከተሰቀለ ከ37 ዓመታት በኋላ) ነበር፡፡ ማራ ወልደ ሴራፕዮን የኖረው በመጀመርያው ክፍለ ዘመን እንደመሆኑ መጠን ይህ የእርሱ ጽሑፍ መጽሐፍ ቅዱስ የሚተርከው የክርቶስ ሕይወት እውነት ስለመሆኑ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡

  1. ወደ ክርስቶስ የሚያመለክት ሌላው አስደናቂ የታሪክ መረጃ በ55 ዓ.ም. አካባቢ እንደተጻፈ ምሑራን ይናገራሉ፡፡ ታሉስ የተባለ ሮማዊ የታሪክ ጸሐፊ በክርስቶስ ስቅለት ወቅት በምድር ላይ ስለወደቀው ጨለማ ጽፎ የነበረ ሲሆን ነገር ግን በእርሱ የተጻፈው ቀዳሚ ሰነድ በመጥፋቱ የተነሳ ያለን መረጃ ጁሊየስ አፍሪካኑስ የተባለ ክርስቲያን የታሪክ ጸሐፊ (160-240 ዓ.ም.) የእርሱን ጽሑፍ በመጥቀስ የጻፈው ነው፡፡ አፍሪካኑስ እንዲህ በማለት ጽፏል፡- “በሦስተኛው የትረካ (መጽሐፉ) ታሉስ ይህንን ጨለማ የፀሐይ ግርዶሽ በማለት ይጠራዋል፤ ይህ ለኔ ስህተት መስሎ ይታየኛል፡፡”

ጁሊየስ አፍሪካኑስ የታሉስን ጽሑፍ የጠቀሰው ክርስቶስ የተሰቀለው ሙሉ ጨረቃ በምትታይበት በፋሲካ ዋዜማ በመሆኑና በሙሉ ጨረቃ ጊዜ ደግሞ የፀሐይ ግርዶሽ የማይከሰት በመሆኑ በክርስቶስ ስቅለት ወቅት በምድር ላይ የወደቀው ጨለማ የፀሐይ ግርዶሽ እንደነበረ ታሉስ በመጽሐፉ ውስጥ ማስፈሩ ትክክል እንዳልሆነ በሚገልጽበት ክፍል ነው፡፡[9]

ከላይ የጠቀስናቸው ታሪካዊ መረጃዎች ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ምሳሌዎች መጽሐፍ ቅዱሳችን ከታሪካዊ ዘገባ አንጻር ተኣማኒና ሃቀኛ ስለመሆኑ ማሳያዎች ናቸው፡፡


ማጣቀሻዎች

[1] Shenk, David W. Journeys of the Muslim Nation and the Christian Church, Exploring the Mission of Two Communities; Herald Press Scotdalle, 2003, p. 103

[2] Lewis,  C. S. Christian Reflection; Grand Rapids: Eerdmans, 1967, 157-55, cited in Norman L. Geisler and Abdul Saleeb, Answering Islam: The Crescent in the Light of the Cross, second ed., Grand Rapids: Baker Books, 2002, p. 244

[3] Geisler, Norman L. Encyclopedia of Christian Apologetics; Grand Rapids: Baker Books, 1999, p. 711 PDF

[4] Smith, Jay. The Bible in the British Museum and the British Library, a Tour of the British Museum and the Brtish Library; p. 17

[5] Ramsay, Sir William. Saint Paul the Traveller and the Roman Citizen; New York: G. P. Putnam’s Sons, 1896

[6] Ipistulae, Vol X, No. 96

[7] Annals of Imperial Rome, XV 44

[8] Antiquitie XVIII, 3:2

[9] Van Voorst, Robert E. Jesus Outside the New Testament, An Introduction to the Ancient Evidence; Wm. Β. Eerdmans Publishing, Grand Rapids, Michigan, 2000, p. 20

መጽሐፍ ቅዱስ ተዓማኒ ቃለ እግዚአብሔር ነውን? ዋናው ማውጫ

መጽሐፍ ቅዱስ