መጽሐፍ ቅዱስ ተዓማኒ ቃለ እግዚአብሔር ነውን? ምዕራፍ ፩ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ዓይነት መጽሐፍ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ዓይነት መጽሐፍ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ሰዎች፣ በተለያዩ ዘመናትና በተለያዩ ቦታዎች የተጻፉ በቁጥር 66 የሚያክሉ የተለያየ ርዝማኔ ያላቸውን መጻሕፍት በውስጡ ይዟል፡፡ ሁለት ታላላቅ ክፍሎች ሲኖሩት እነዚህም ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን በመባል ይታወቃሉ፡፡ ብሉይ ኪዳን በዋናነት እግዚአብሔር  ከሕዝበ እስራኤል ጋር ስላደረገው ቃል ኪዳን ይናገራል፡፡ የተለያዩ ሕዝቦች ታሪኮች በውስጡ የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ታሪኮች የተጻፉት ህዝቦቹ ከእስራኤል ጋር ከነበራቸው ግንኙነት አኳያ ነው፡፡  አዲስ ኪዳን ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመኑ ክርስቲያኖች የተጻፈ ሲሆን ቤተክርስቲያን በመባል ስለምትታወቅ ማሕበረሰብ ይናገራል፡፡ የመጀመርያውን ምዕተ ዓመት የታሪክ ዘመን ይሸፍናል እንዲሁም ስለመጨረሻው ዘመን ይተነብያል፡፡ ብሉይ ኪዳን 39 አዲስ ኪዳን ደግሞ 27 መጻሕፍትን በውስጣቸው ይዘዋል፡፡

የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት በእብራይስጥ ቋንቋ ሲሆን በአራማይክ ቋንቋ የተጻፉ ጥቂት ክፍሎችም በውስጡ ይገኛሉ፡፡ አዲስ ኪዳን የተጻፈው “ኮይኔ” ወይም “የአሌክሳንደርያ ዘዬ” በመባል በሚታወቅ የግሪክ ቋንቋ ዘዬ ነው፡፡ ይህ የግሪክ ቋንቋ ዘዬ አዲስ ኪዳን በተጻፈበት ዘመን የሜድትራንያን አካባቢ ሕዝቦች መግባብያ (Linguafranka) ነበር፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው ክፍለ ዘመን የተተረጎመው የሰብዓ ሊቃናት የብሉይ ኪዳን ትርጓሜ (Septuagent) ይህንኑ የግሪክ ቋንቋ ዘዬ የተከተለ ነበር፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ 1,189 ምእራፎችና 31,103 ቁጥሮች አሉት፡፡ የቁጥሮቹ ብዛት በተለያዩ ትርጉሞች ውስጥ በትንሽ መጠን ከዚህ ከፍ ወይም ዝቅ የሚልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ እነዚህ አከፋፈሎች በቀዳሚያን ጽሑፎች ውስጥ የማይገኙ ቢሆኑም ነገር ግን በመካከለኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ የኖሩ አይሁድና ክርስቲያን ሊቃውንት መጽሐፉን በቀላሉ ለማንበብ እንዲያመች በማሰብ በዚህ መልኩ ከፋፍለውታል፡፡

እ.ኤ.አ. በ 1227 ዓ.ም. የካንተር በሪ ሊቀ ጳጳስ የነበረው እስቴፈን ላንግተን ለመጀመርያ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በምዕራፎች ከፋፈለ፡፡ በ 1382 ዓ.ም. የታተመው የዊክሊፍ የእንግሊዘኛ ትርጓሜ ይህንን አከፋፈል በመከተል በምዕራፎች የተከፋፈለ የመጀመርያው መጽሐፍ ቅዱስ ለመሆን በቃ፡፡ በ 1448 ዓ.ም. አይዛክ ናታን ቤን ካላኒመስ የተሰኘ አይሁዳዊ ረቢ ብሉይ ኪዳንን በቁጥር የከፋፈለ ሲሆን በ 1555 ዓ.ም. ደግሞ ሮበርት ኤስቲን (እስቴፋነስ) የተባለ ሰው አዲስ ኪዳንን በቁጥር ከፋፍሏል፡፡[1] እነሆ የነዚህ ሰዎች መልካም ጥረት ዛሬ በእጃችን የሚገኙትን የመጽሐፍ ቅዱስ ኮፒዎች በቀላሉ ተነባቢ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በማን፣ መቼና የት ተጻፈ?

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የጻፉት መጽሐፍ እንደሆነ ክርስቲያኖች ያምናሉ፡፡ እነዚህ ጸሐፊያን በተለያዩ ቦታዎችና ዘመናት የኖሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ እድሜያቸው፣ ዕውቀታቸው፣ ሥራቸው እንዲሁም በማሕብረሰባቸው ውስጥ የነበራቸው ደረጃ የተለያየ ነበር፡፡ ከጸሐፍቱ መካከል አብዛኞቹ ስሞቻቸው  ከጻፏቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር ተያይዘው ተጠቅሰዋል፡፡

በፍጥሞ ደሴት ላይ የሚገኝ የቅዱስ ዮሐንስ ገዳም፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ ራዕዩን ያየው እና መጽሐፉን የጻፈው በዚህ ቦታ ነበር፡፡

የፎት ምንጭ፡ Oxford Bible Atlas, Fourth Edition

መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ለመጠናቀቅ 1,500 ዓመታት ያህል ፈጅቷል፡፡ የመጀመርያው ጽሑፍ የተከተበው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1400 ዓ.ዓ. አካባቢ እንደሆነና የመጨረሻው ክፍል ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ90 ዓ.ም. አካባቢ እንደተጻፈ በአብዛኞቹ ምሑራን ዘንድ ይታመናል፡፡

የዚህ እድሜ ጠገብ መጽሐፍ ልዩ ልዩ ክፍሎች በተለያዩ ሦስት አህጉራት፣ ማለትም በኢስያ፣ አውሮፓና አፍሪካ ውስጥ ተጽፈዋል፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት

ይህ ታላቅ መጽሐፍ ተጽፎ ለመጠናቀቅ 1500 ዓመታትን የፈጀ፣ ከ40 በላይ ጸሐፊያንን ያሳተፈና በተለያዩ ብዙ ቦታዎች የተጻፈ ቢሆንም በሚያስደንቅ ሁኔታ ማዕከላዊ መልዕክቱ አንድ ነው፤ እርሱም እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያዘጋጀው የዘለዓለም ሕይወት ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን  ለእግዚአብሔር ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር መምጣት ቅድመ ዝግጅት ሲሆን አዲስ ኪዳን ደግሞ የእርሱን መምጣት እውን መሆን የሚያበስር ነው፡፡

ብሉይ ኪዳን የፍጥረትን አጀማመርና የጥፋትን ውሃ ከተረከ በኋላ እግዚአብሔር አብራም የተሰኘ የመስጴጦምያ (Mesopotamia) ሰው ስለመጥራቱና ከዚህም ሰው እስራኤል የተባለ ሕዝብ ስለመገኘቱ ይተርክልናል፡፡ የአብራም መጠራት መሲሁ ኢየሱስ ወደ ምድር ይመጣ ዘንድ የመጀመርያው ዝግጅት ነበር፡፡ በዘፍጥረት 26፡2 ላይ እግዚአብሔር “የምድርም አህዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ” የሚል ቃል ኪዳን ለአብራም ገብቶለት ነበር፡፡ ይህ ቃል ኪዳን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንደተፈጸመ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ተናግሯል (ገላትያ 3፡16)፡፡

የተቀረው የብሉይ ኪዳን ክፍል በአብዛኛው የሚያተኩረው እግዚአብሔር ከሕዝበ እስራኤል ጋር በነበረው ግንኙነት እንዲሁም ስለመሲሁ መምጣትና ስለሌሎች ብዙ ጉዳዮች በተተነበዩ የነቢያት ትንቢቶች ላይ ነው፡፡

አዲስ ኪዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት፣ በትምህርቶቹ እንዲሁም ከእርገቱ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ባደረጓቸው ነገሮችና ባስተማሯቸው ትምህርቶች ላይ ያተኩራል፡፡ ጠቅለል ባለ ሁኔታ የአዲስ ኪዳን መልዕክት ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ የመጣ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ማስተማሩን፣ ማንነቱን የሚያረጋግጡ ብዙ ተዓምራትን ማድረጉን፣ መከራን መቀበሉን፣ ስለ ሰው ልጆች ኃጢዓት ሲል በመስቀል ላይ መሞቱን፣ መቀበሩን፣ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን መነሳቱን፣ ለደቀ መዛሙርቱ መታየቱን፣ ወደ ሰማይ ማረጉን፣ ለሁሉም እንደየሥራው ሊከፍል ወደ ምድር ተመልሶ እንደሚመጣ፣ ደቀ መዛሙርቱ ደግሞ ለነዚህ ነገሮች ምስክሮች መሆናቸውንና የዘለዓለም ሕይወት የሚገኘው በእርሱ በማመን ብቻ መሆኑን የሚናገር ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ዓይነት የሥነ  ጽሑፍ ስልት የተከተለ መጽሐፍ አይደለም፡፡ ሕግ፣ ትረካ፣ ቅኔ፣ ትንቢት፣ መልዕክት፣ አቡ ቀለምሲስ፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ዘርፈ ብዙ የሥነ  ጽሑፍ ዓይነቶች በውስጡ ይገኛሉ፡፡

የመገለጥ ትርጉም

የተለያዩ ኃይማኖቶች ስለመገለጥ የየራሳቸው የሆነ አመለካከት አላቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሙስሊሞች ቅዱስ ቁርኣን “የተገለጠበትን” ሁኔታ ተንዚል ወይም ናዚል በማለት ይጠሩታል፡፡ ተንዚል ማለት “ከላይ የወረደ መገለጥ” ማለት ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ የነበረው ክርስቲያናዊ አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ ከላይ የወረደ መገለጥ ነው የሚል ሳይሆን የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት (በመመራት) የጻፉት ቃል ነው የሚል ነው፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ሰዎቹ የነበራቸውን እውቀት፣ ባህልና ቋንቋ እንዲጠቀሙ መንፈስ ቅዱስ ፈቅዷል፡፡

ክርስቲያኖች የሚያምኑት ከላይ የወረደው የእግዚአብሔር መገለጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ መሆኑን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በሰው ልጆች ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ የተገለጠ በጽሑፍ የቀረበ ግልጠተ-መለኮት ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ንግግር ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆች ለእግዚአብሔር ሐሳብ የሰጡትንም ምላሽ በውስጡ አካቷል፡፡ ይህም ማለት መጽሐፍ ቅዱስ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በውስጡ የያዘ መጽሐፍ ነው ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው በተለያዩ ዘመናት የተደረጉ የሰው ልጆች ታሪኮች በውስጡ የሚገኙት፡፡

በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ “የእግዚአብሔር ቃል” (ሎጎስ) ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ይህም እግዚአብሔር በሙላት ራሱን የገለጠው በእርሱ በኩል መሆኑን ያሳያል፡፡

“በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።” ዮሐንስ 1፡1-3

እግዚአብሔር ዓለማትን የፈጠረበት ሕያውና ዘላለማዊ ቃሉ ሰው ሆኖ በመምጣት ከሰው ልጆች ጋር በምድር ላይ ኖረ፤ የእግዚአብሔርንም ማንነት በሙላት ገለጠ፡፡ ይህ መገለጥ ተሠግዎ (Incarnation) በመባል ይታወቃል፡፡ ተሠግዎ ማለት “ሥጋ መሆን” ማለት ነው፡፡

“ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን፡፡” ዮሐንስ 1፡14

ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ቃል በመሆኑ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ መግለጥ ይችላል፡፡ እርሱ የእግዚአብሔር የመጨረሻው ታላቅ መገለጥ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታዎች ላይ ይናገራል (ቆላስይስ 2፡9 ጢሞቴዎስ 3:16 ቆላስይስ 1፡15-16 ዮሐንስ 14፡7-10)

ከመሲሁ ስሞች መካከል አንዱ “አማኑኤል” የሚል ሲሆን ትርጓሜውም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ማለት ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ኢየሱስ ከመወለዱ ከ700 ዓመታት በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ የሚል ትንቢት ተናግሮ ነበር ፡-

“ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” ኢሳይያስ 7፡14

ክርስትና እግዚአብሔር ከንግግር ባለፈ መንገድ ራሱን ለሰው ልጆች እንደገለጠ ያስተምራል፡፡ ይህም አንድያ ልጁን ወደ ምድር በመላክ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ቃል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በማይለካ ፍቅር፣ በማይለካ ፅድቅ፣ በማይለካ ቅድስና፣ በማይለካ እውነተኛነትና በማይለካ ይቅር ባይነት የእግዚአብሔርን ማንነት በትክክል አሳይቶናል፡፡ በእርሱም በኩል እግዚአብሔርን አይተነዋል፡፡ በስሙ የሚያምኑ ሰዎች የእርሱን ማንነት በሕይወታቸው ውስጥ እውን ሆኖ ያገኙታል፡፡ የክርስትና አስደናቂና አስደሳቹ ገጽታም ይህ ነው፡፡ 

የቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና

ተቃዋሚዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ተዓማኒነት አጠራጣሪ ለማድረግ ብዙ ጊዜ የሚጠቅሱት በውስጡ የሚገኙትን መጻሕፍት ዝርዝር በተመለከተ በክርስቲያኖች መካከል የሚገኘውን ልዩነት ነው፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስን ቀኖና በተመለከተ በተለያዩ የክርስትና ቤተ እምነቶች መካከል ልዩነት መኖሩ የታወቀ ነው፡፡ የወንጌላውን አብያተ ክርስቲያናት ቀኖና 66 መጻሕፍትን የያዘ ሲሆን የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን 73፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ 81 መጻሕፍትን የያዙ ናቸው፡፡ በስድሳ ስድስቱ መጻሕፍት ዙርያ በነዚህ የክርስትና ቤተ እማነቶች መካከል ስምምነት ያለ ሲሆን ልዩነቱ የተፈጠረው አፖክሪፋ በመባል በሚታወቁት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዙርያ ነው፡፡

ቀኖና የሚለው ቃል “ካኖን” ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጓሜውም “የመለክያ ብትር” ወይም “ደንብ” ማለት ነው፡፡ ይህ ቃል እስትንፋሰ-መለኮት መሆናቸው የሚታመንባቸውን የቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝር ያመለክታል፡፡ ቀኖናን በተመለከተ በሰፊው የሚናፈሱ የተሳሳቱ አመለካከቶች ከመኖራቸው አንፃር እነዚህን ውዥንብሮች ለማጥራት አንድ መሠረታዊ እውነት መጠቀስ ይኖርበታል፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያን የቀኖና ውጤት እንጂ የቀኖና እናት አለመሆኗ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሠረት የሐዋርያትና የነቢያት ትምህርት በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን አባቶች “ይህኛው ቀኖና ነው ያኛው ደግሞ ቀኖና አይደለም” በማለት ሲለዩ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበትን መሠረት በማጤን እንጂ ለቤተ ክርስቲያን መሠረት እያጣሉላት አልነበረም ማለት ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደተባለው ቅዱሳን አባቶች የነቢያትና የሐዋርት ምንጭ ያላቸውንና የቤተ ክርስቲያን መሠረት የሆኑትን መጻሕፍት በመለየት አስታወቁ እንጂ አዲስ ነገር አልፈጠሩም፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የቀኖና ልጅ እንጂ የቀኖና እናት አይደለችም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቀኖና አገልጋይ እንጂ የቀኖና የበላይ አይደለችም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቀኖና ምስክር እንጂ የቀኖና ወሳኝ አይደለችም፡፡ የቀኖና ወሳኙ እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር በመንፈሱ ምሪት በተጻፉት ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የራሱን “አሻራ” በማስቀመጥ ቀኖናን ወስኗል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ድርሻም ይህ “አሻራ” ያረፈባቸውን መጻሕፍት መለየት ነው፡፡[1]

በስድሳ ስድስቱ መጻሕፍት ዙርያ በክርስትና ቤተ እማነቶች መካከል ስምምነት ያለ ሲሆን ልዩነቱ የተፈጠረው አፖክሪፋ በመባል በሚታወቁት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዙርያ ነው፡፡ አፖክሪፋ ማለት የተሰወረ ወይም አጠራጣሪ ማለት ሲሆን እነዚህን መጻሕፍት እንደ እስትንፋሰ መለኮት የሚቀበሏቸው ወገኖች ዲዩትሮካኖኒካል (ሁለተኛ ቀኖና) በማለት መጥራትን ይመርጣሉ፡፡ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን መጻሕፍት እንደማይጠቅሙ ወይንም ደግሞ በውስጣቸው ምንም እውነት እንዳልያዙ አይቆጥሯቸውም፡፡ ይልቁኑ በነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ብዙ ጠቃሚ እውነቶች እንዳሉና ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ጎን ለጎን ለተጨማሪ እውቀት መነበብ እንሚገባቸው ያምናሉ ነገር ግን በሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ደረጃ ላይ አያስቀምጧቸውም፡፡ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ፡፡ ከነዚህ መካከል አራቱ የሚከተሉት ናቸው፡-

  1. የአፖክሪፋ መጻሕፍት ነቢያት በነበሩበት ዘመን ሳይሆን በዝምታ ዘመን የተጻፉ ናቸው፡፡ በነቢዩ ሚልኪያስና በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል የነበረው የ400 ዓመታት ጊዜ “የዝምታ ዘመን” በመባል ይታወቃል፡፡ በነዝያ ዘመናት የተከናወኑ ልናውቃቸው የሚገቡ ታሪኮች ቢኖሩም ነገር ግን እግዚአብሔር የሚናገራቸው ነቢያት ስላልነበሩ በወቅቱ የተጻፉት ጽሑፎች ሁሉ የሰው ስራዎች እንጂ እስትንፋሰ መለኮት ሊሆኑ አይችሉም፡፡
  2. እነዚህ መጻሕፍት ወደ ክርስቲያን ቀኖና የተጨመሩት በቀደሙት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ዘመን ሳይሆን በመካከለኛው ዘመን ነበር፡፡ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶች እነዚህን መጻሕፍት የጠቀሷቸው ቢሆንም መንፈሳዊ እሴት እንዳሏቸው ጠቃሚ መጻሕፍት እንጂ እንደ ስልጣናዊ ቃለ እግዚአብሔር አልነበረም፡፡ በ382 ዓ.ም. በሮም የተደረገውን የመሳሰሉ የአፖክሪፋ መጻሕፍት ቀኖናዊ መሆናቸውን የሚናገሩ ጉባኤዎች አካባቢያዊና የተወሰኑ ሰዎች ድምዳሜ እንጂ ቤተ ክርስቲያንን የሚወክሉ አይደሉም፡፡ እንዲያውም ኦሪጎን፣ የኢየሩሳሌሙ ቄርሎስ፣ አትናቴዎስ እና ጀሮምን የመሳሰሉ ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች አፖክሪፋን ተቃውመዋል፡፡[2] መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ላቲን ቋንቋ የተረጎሙት ቅዱስ ጀሮም እነዚህን መጻሕፍት አፖክሪፋ (የተሰወሩ ወይንም አጠራጣሪ) የሚል ስያሜ በመስጠት ከስድሳ ስድስቱ መጻሕፍት በመለየት ተርጉመዋቸዋል፡፡ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እነዚህን መጻሕፍት በቀኖናነት ያጸደቀችው የተሓድሶ (Reformation) እንቅስቃሴ አንዳንድ አስተምህሮዎችዋን መገዳደር በጀመረበት ዘመን (በ1546 ዓ.ም.) “የትረንት ጉባኤ” በመባል በሚታወቅ የቤተክርስቲያኒቱ ጉባኤ ላይ ሲሆን ለነዚህ አስተምህሮዎች ድጋፍ ሊሰጡ የሚችሉ ሐሳቦች በአፖክሪፋ ውስጥ እንደሚገኙ ስላመነች ቤተ ክርስቲያኒቱን ለሁለት የከፈለውን እንቅስቃሴ ለመቋቋም እንዲጠቅሟት በማለም ነበር፡፡ ነገር ግን በዚያን ዘመንም ቢሆን ካርዲናል ካጄታንን የመሳሰሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት የሪፎርሜሽን እንቅስቃሴን ይቃወሙ የነበሩ ቢሆኑም ነገር ግን የአፖክሪፋ መጻሕፍትን ወደ ቀኖና መጨመር ተቃውመው እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ብትሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እነዚህን መጻሕፍት በሰላሳ ዘጠኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እና በአዲስ ኪዳን መካከል የተለየ ቦታ በመስጠት ዲዩትሮካኖኒካል (ሁለተኛ የቀኖና መጻሕፍት) የሚል ስያሜ በመስጠት እንዲታተሙ ታደርግ ነበር፡፡ ነገር ግን በ2000 ዓ.ም. በታተመው የሰማንያ አሐዱ እትም ላይ እነዚህን የአፖክሪፋ መጻሕፍት ከሌሎች የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጋር በመቀላቀል እንዲታተሙ ተደርጓል፡፡
  3. ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን መጽሐፍት እንደ ቃለ እግዚአብሔር የማይቀበሉበት ሌላው ምክንያት ደግሞ እነዚህ መጻሕፍት በአይሁድ ቀኖና ውስጥ የማይገኙ መሆናቸው ነው፡፡ በ90 ዓ.ም. ዮሐናን ቤን ዛካይ በተባለ ረቢ መሪነት በጃምኒያ በተደረገ የአይሁድ ሊቃውንት ጉባኤ ላይ በአይሁድ ታሪክ ውስጥ በቀኖናነት ተቀባይነት እንደነበራቸው ተረጋግጠው እስትንፋሰ መለኮት መሆናቸው ዕውቅና የተሰጣቸው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሰላሳ ዘጠኙ ብቻ ነበሩ፡፡ የጉባኤው አላማ ቀኖናን ማጽደቅ ሳይሆን የትኞቹ መጻሕፍት በቀኖናነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ እንደነበሩ ለይቶ ዕውቅና መስጠት እንደ ነበር ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የአይሁድ መምህር የነበረው የእስክንድርያው ፋይሎ (20 ዓ.ዓ. – 40 ዓ.ም.) ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚቻልበት ሁኔታ ከሁሉም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የጠቀሰ ሲሆን ከአፖክሪፋ ግን አንድም ጊዜ አልጠቀሰም፡፡ የአይሁድ ጸሐፌ ታሪክ የነበረው ጆሲፈስ ፍላቪየስ (ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን) (30 ዓ.ም. – 100 ዓ.ም.) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት 22 ብቻ መሆናቸውን በመጥቀስ የአፖክሪፋን መጻሕፍ ውድቅ አድርጓቸዋል፡፡ አይሁድ አንዳንድ መጻሕፍትን እንደ አንድ መጽሐፍ ስለሚቆጥሯቸው እንጂ እነዚህ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ቆጠራ መሠረት 39 ከሆኑት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተለዩ አይደሉም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሮሜ 3፡1-2 ላይ እንደጻፈው እግዚአብሔር ብሉይ ኪዳንን በአደራ የሰጠው ለአይሁድ ሕዝብ ነው፡-

እንግዲህ የአይሁዳዊ ብልጫው ምንድር ነውወይስ የመገረዝ ጥቅሙ ምንድር ነውበሁሉ ነገር ብዙ ነው፡፡ አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃላት አደራ ተሰጡአቸው፡፡” 

ስለዚህ አይሁድ የትኞቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከእግዚአብሔር እንደሆኑና እንዳልሆኑ ለይተው ያውቃሉ፡፡ የአይሁድ ሕዝብ ቅዱሳት መጻሕፍትን በታላቅ አክብሮትና በጥንቃቄ ይዘው እንደቆዩ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ የጥንቃቄያቸውን ብዛት ለመረዳት እስኪ ተከታዮቹን እውነታዎች ተመልከቱ፡-

  • የጽሑፍ ሥራው ከመጀመሩ በፊት በእድሜ የሁሉ ታላቅ የሆነ ረቢ ተነስቶ በመቆም አንድ ፊደል እንኳ መቀነስ ወይንም ደግሞ መጨመር ለጥፋት እንደሚዳርጋቸው ጸሐፍቱን ያስጠነቅቃል፡፡
  • ጸሐፍቱ ሥራቸውን እየሠሩ ሳሉ ንጉሥ እንኳ ቢገባ ስህተት ላለመስራት የጀመሩትን ገፅ እስኪጨርሱ ድረስ ቀና ብለው ማናገር እንደ ሌለባቸው ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል፡፡
  • ብሉይ ኪዳን የሚጻፍበት ብራና ከንፁህ እንስሳት ቆዳ በአይሁዳዊ እጅ ብቻ መዘጋጀት አለበት፡፡
  • እያንዳንዱ ወርድ ከ 48 በታች እና ከ 60 በላይ መስመሮች ሊኖሩት አይገባም፡፡
  • ቀለሙ ጥቁር ብቻ መሆን አለበት፣ በተለየ ሁኔታም ይዘጋጃል፡፡
  • ከትውስታ የሚጻፍ ምንም ዓይነት ቃል ወይንም ፊደል መኖር የለበትም፡፡ ጸሐፊው ተኣማኒ የሆነ ኮፒ ከፊት ለፊቱ ማስቀመጥ አለበት፣ ከመጻፉ በፊትም ከፍ ባለ ድምፅ በትክክል ሊያነበው ይገባል፡፡
  • ጸሐፊው ከመጻፉ በፊት አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ መጻፍያውን መወልወል አለበት፡፡
  • ጸሐፊው ያሕዌ የሚለውን የእግዚአብሔርን ስም ከመጻፉ በፊት መላ ሰውነቱን መታጠብ አለበት፡፡
  • ጸሐፊው ያሕዌ የሚለውን የእግዚአብሔርን ስም ለመጻፍ አዲስ ብዕር ይጠቀማል፡፡ ያሕዌ የሚለውን ስም የጻፈበትን ብዕር ሌላ ቃል ለመጻፍ አይጠቀምበትም፡፡
  • በአንድ ገፅ ላይ የሚፈጠር አንድ ስህተት ገፁን በሙሉ ያበላሸዋል፡፡ በአንድ ገፅ ላይ ሦስት ስህተቶች ከተገኙ ብራናው በሙሉ ከጥቅም ውጪ ይሆናል፡፡
  • እያንዳንዱ ቃል እና እያንዳንዱ ፊደል ተቆጥሮ ተመዝግቧል፡፡[3]

ስለዚህ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የብሉይ ኪዳንን ቀኖና በተመለከተ እግዚአብሔር ታማኝ አድርጎ ቆጥሮ ቃሉን በአደራ ከሰጣቸውና እንዲህ ባለ ጥንቃቄና አክብሮት የእግዚአብሔርን ቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲያስተላልፉ ከኖሩት ሕዝቦች ጋር ይስማማሉ፡፡

  1. ጌታችን ኢየሱስ ዕውቅናን የሰጠው ለአይሁድ ቀኖና ብቻ ነበር፡፡ በጌታ ዘመን ብሉይ ኪዳን ሕግ፣ ነቢያት እና መዝሙራት በመባል ለሦስት ተከፍሎ ነበር (ሉቃስ 24፡44)፡፡ በነዚህ ሦስቱ ክፍሎች ውስጥ የአፖክሪፋ መጻሕፍት አልነበሩም፡፡ በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ “ከአቤል ደም እስከ ዘካርያስ ደም” በማለት ብሉይ ኪዳን ከአቤል ጀምሮ እስከ ዘካርያስ ዘመን ድረስ የሚገኘውን የታሪክ ዘመን እንደሚሸፍን አመላክቷል (ማቴ 23፡35፣ ሉቃ 11፡51)፡፡ ይህም ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ መጨረሻዎቹ ነቢያት ድረስ የሚገኘው ዘመን ነው፡፡ ነቢዩ ዘካርያስ እና ነቢዩ ሚልኪያስ በአንድ ዘመን የኖሩ ሲሆኑ ከእነርሱ በኋላ እስከ ክርስቶስ ዘመን ድረስ የነበረው ዘመን የዝምታ ዘመን በመባል ይታወቃል፡፡ በይሁዳ መልዕክት ቁጥር 14-15 ላይ ከአፖክሪፋ መጻሕፍት መካከል አንዱ የሆነው መጽሐፈ ሄኖክ መጠቀሱ መጽሐፉ ትምህርት ሰጪ የሆነን መልዕክት በውስጡ የያዘ መሆኑን የሚያመለክት እንጂ መጽሐፉ ሙሉ በሙሉ እውነት መሆኑን የሚያመለክት አይደለም፡፡ የጌታ ሐዋርያት ለተደራሲያኖቻቸው ትምህርት ሊሰጡ የሚችሉ የግሪክ ጽሑፎችንና ሌሎች የአይሁድ መጻሕፍትን እንኳ ሲጠቅሱ እንመለከታለን፡፡ ይህ ጽሑፎቹን እስትንፋሰ መለኮት አያደርጋቸውም፡፡

ማጠቃለያ

የአፖክሪፋ መጻሕፍት ቀኖና መሆን አለመሆናቸው የክርስትናን ዋና ዋና አስተምህሮዎች በምንም መልኩ የሚነካ አይደለም፡፡ የተቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መቀየራቸውንም አያሳይም፡፡ የአፖክሪፋ መጻሕፍት ከቀኖና መቆጠራቸው በመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ መልዕክት ላይ የሚጨምረውም ሆነ የሚቀንሰው ምንም ነገር የለም፡፡ በየትኛውም ቤተ እምነት ቀኖና የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ ያነበበ ሰው መሠረታዊ የሆኑ የክርስትና አስተምህሮዎችን በተሟላ ሁኔታ ያገኛል፡፡ የአፖክሪፋን መጻሕፍት እንደ ቃለ እግዚአብሔር የማይቆጥሩ አብያተ ክርስቲያናትም ቢሆኑ እነዚህን መጻሕፍት ሙሉ በሙሉ ውድቅ የማያደርጉ ሲሆን መንፈሳዊ ትምህርቶችን እንደያዙ አስተማሪ መጻሕፍት ይቀበሏቸዋል፤ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጎን ለጎን ለተጨማሪ ዕውቀት ያጠኗቸዋል፡፡ ሙስሊም ወገኖች ራሳቸው “ሐዲስ ቁድሲ” በማለት የሚጠሯቸው የሐዲስ ክፍሎች እንደ ቁርኣን ሁሉ የአላህ ቃል ናቸው ወይስ አይደሉም? በሚለው ላይ ስምምነት የላቸውም፡፡ ክርስቲያኖች በአፖክሪፋ መጻሕፍት ዙርያ ያላቸውን ልዩነት በዚሁ መንገድ መረዳት ያስፈልጋል፡፡


ማጣቀሻዎች

[1] በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት Norman Geisler, Baker Encyclopeadea of Christian Apologetics pp. 80 – 85 ያንብቡ፡፡

[2] Ibid., p. 33-34

[3] Paul Roost. Proofs that the Bible is the word of almighty God, Book 147, pp. 30, Evangelical Bible College of Western Australia

[1] http://www.biblegateway.com/blog/2014/05/bible-trival-where-do-verse-and-chapter-number-come-from/

http://www.gotquestions.org/divided-Bible-chapters-verses.html

መጽሐፍ ቅዱስ ተዓማኒ ቃለ እግዚአብሔር ነውን? ዋናው ማውጫ