ዶክሜንተሪ ሃይፖቴሲስ እና የሙስሊም ሰባኪያን ስህተት

ዶክሜንተሪ ሃይፖቴሲስ እና የሙስሊም ሰባኪያን ስህተት

አብዛኞቹ የሙስሊም ሰባኪያን ሙግቶች ከለዘብተኛ የሥነ መለኮት ሊቃውንት ምንጮች የተቃረሙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሰባኪያን ሙግቶቹ ለክርስትናም ሆነ ለእስልምና የጋራ የሆኑ አመለካከቶችን በመካድ ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ባለማስተዋል ኮርጀው የሚያቀርቡ ሲሆን በሒደቱም የገዛ ሃይማኖታቸውን ውድቅ ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ በብዙ ጽሑፎቻቸው ውስጥ ከሚደጋግሟቸው ሙግቶች መካከል አንዱ “ዶክሜንተሪ ሃይፖቴሲስ” የተሰኘው ነው፡፡

ዶክሜንተሪ ሃይፖቴሲስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይዘትና የአጻጻፍ ስልቶች በመነሳት የደራሲያኑን ማንነት እንዲሁም የተጻፉበትን ዘመን ለመገመት የሚሞክር የጥናት ዘዴ ሲሆን ለዚህ የጥናት ስልት ፈር ቀዳጅ በመባል የሚታወቀው ጀርመናዊው ሊቅ ጁሊየስ ወልሃውሰን ነው (1844-1918 ዓ.ም.)፡፡ የዚህ መላ ምት ዋና ትኩረት የኦሪትን ተዓምራዊ ይዘትና የሙሴን ጸሐፊነት ማጣጣል ሲሆን መሠረቱም የእስራኤላውያን የአሓዳዊነት እምነት በዝግመተ ለውጥ ከመድብለ አማልክታዊነት ወደ አሓዳዊነት ያደገ ነው የሚል ነው፡፡ በወልሃውሰን ግምት መሠረት አምስቱ ብሔረ ኦሪት አራት ምንጮች ያሏቸው ሲሆን ያሕዌያዊ፣ ኤሎሂማዊ፣ ዘዳግማዊና ካህናዊ (Jehovist, Elohist, Deuteronomist, Priestly) በማለት ሰይሟቸዋል፡፡ በአጭሩ J-E-D-P በመባል የሚታወቁ ሲሆን እንደየ ቅደም ተከተላቸው የዘጠነኛው፣ የስምንተኛው፣ የስድስተኛውና የአምስተኛው ዓ.ዓ. ምንጮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምቱን አስቀምጧል፡፡ (Norman Geislere: Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 1391)

ክርስቲያኖች ይህንን መላምት ለምንድነው የማይቀበሉት?

  1. መላምቱ በታሪክና በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ውድቅ ነው፡፡ የጥንት አይሁድ፣ ለምሳሌ ያህል የአንደኛው ክፍለ ዘመን ሊቃውንት የነበሩት ፋይሎና ጆሲፈስ (ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን) የአምስቱ ብሔረ ኦሪት ጸሐፊ ሙሴ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም መጻሕፍቱ በሙሴ የተጻፉ መሆናቸውን ይመሰክራል፡፡ ከአምስቱ መጻሕፍት አራቱ፣ ማለትም ዘጸአት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኁልቁና ዘዳግም በሙሴ የተጻፉ መሆናቸውን መጻሕፍቱ ራሳቸው ይመሰክራሉ (ዘጸ. 24፡4፣ ሌዋ. 1፡1፣ 4፡1፣ 5፡14፣ ዘኁ. 1፡1፣ 33፣2፣ ዘዳ. 1፡1፣ 4፡44፣ 29፡1)፡፡ መጽሐፈ ኢያሱን ጨምሮ ሌሎች የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትም ይህንኑ ምስክርነት ያረጋግጣሉ ( ኢያ. 1፡7፣ መሳ. 3፡4፣ 1ነገ. 2፡3፣ 2ነገ 14፡6፣ ዕዝ. 3፡2፣ ነህ. 1፡7፣ መዝ. 103፡7፣ ዳን. 9፡11፣ ሚል. 4፡4)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ ከእነዚህ መጻሕፍት ከመጥቀሳቸውም ባለፈ በሙሴ የተጻፉ ስለመሆናቸው ተናግረዋል (ማቴ. 4፡7-10፣ 8፡4፣ ማር. 7፡10፣ 12፡26፣ ሉቃ. 20፡28፣ 24፡44፣ ዮሐ. 7፡19፣ ሐ.ሥ. 3፡22፣ 28፡23፣ ሮሜ 10፡19፣ 1ቆሮ 9፡9፣ ዕብ. 9፡19-20)፡፡ ስለዚህ የታሪክና የቅዱት መጻሕፍት ምስክርነቶች መላ ምቱን ውድቅ ያደርጉታል፤ ተዓማኒነታቸውንም ለመጠራጠር የሚያበቃ ምክንያት የለም፡፡
  2. J-E-D-P የጽሑፍም ሆነ የአርኪዎሎጂ ድጋፍ የሌለው መላ ምት ነው፡፡ አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት በተለያዩ ዘመናትና በተለያዩ ቦታዎች የተጻፉ መሆናቸውን የሚያሳይ ምንም ዓይነት የጽሑፍም ሆነ የአርኪዎሎጂ ማስረጃ የለም፡፡
  3. ጁሊየስ ወልሃውሰን የእስራኤላውያን የአሓዳዊነት እምነት በዝግመተ ለውጥ ከመድብለ አማልክታዊነት ወደ አሓዳዊነት ያደገ ነው ብሎ ያስቀመጠውን የመላምቱን መነሻ ውድቅ የሚያደርጉ የአርኪዎሎጂ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ስለዚህ የአሓዳዊነት ይዘት ያላቸው መጻሕፍት በሙሴ ዘመን ሊኖሩ እንደማይችሉ መናገር ከአርኪዎሎጂ ማስረጃ ጋር መላተም ነው፡፡ (, 1392)
  4. የመላምቱ “ማስረጃ” እንደሆነ የተነገረው በመጻሕፍቱ ውስጥ የሚገኘው የአጻጻፍ ልዩነት በቀላሉ ሊብራራ የሚችልና ውኀ የማይቋጥር ነው፡፡ የመላምቱ ፈር ቀዳጅ የነበረው ወልሃውሰን “ከያሕዌያዊ ምንጭ የተገኙ” ብሎ የፈረጃቸው ክፍሎች “ኤሎሂም” ከሚለው ይልቅ “ያሕዌ” የሚለውን የእግዚአብሔርን የተፀውዖ ስም የሚጠቀሙ ሲሆን “ከኤሎሂማዊ ምንጭ የተገኙ” ያላቸው ደግሞ “ኤሎሂም” የሚለውን የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ዘፍጥረት 1 ኤሎሂምን የሚጠቀም ሲሆን 2 ደግሞ ያሕዌን ይጠቀማል፡፡ እንዲህ እያለ የመጽሐፉን የተለያዩ ክፍሎች “ከያሕዌያዊና ከኤሎሂማዊ ምንጮች የተገኙ” በማለት ከፋፍሏቸዋል፡፡ ነገር ግን ሁለቱ ስሞች ያላቸውን አገባብ ስንመለከት ኤሎሂም የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት፣ ያሕዌ ደግሞ እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ሕብረት ማድረጉንና የሰዎች አምላክ መሆኑን በሚያሳዩ ክፍሎች ውስጥ ጥቅም ላይ ውለው እንመለከታለን፡፡ ስለዚህ ሙሴ ሁለቱን ስሞች በተለያየ አገባብ መጠቀሙ የተለያዩ መልእክቶችን ከማስተላለፍ አንፃር በዓላማ ያደረገው እንጂ ተቺዎች እንደሚሉት እነዚያ ክፍሎች ከተለያዩ ምንጮች ስለተቀዱ አይደለም፡፡ “ያሕዌ” በተጠቀሰባቸው የዘፍጥረት አብዛኞቹ ክፍሎች ውስጥ “ኤሎሂም” የሚለው ተደራቢ ሆኖ “ያሕዌ-ኤሎሂም” ተብሎ ተጠቅሶ መገኘቱም የትወራውን መሠረተ ቢስነት የሚያረጋግጥ ሌላ ማስረጃ ነው፡፡ ካህናዊ ሕግጋትና ሌሎች ሕግጋት ልዩነት ስላላቸው የአጻጻፍ ልዩነቶቹን መነሻ በማድረግ “ካህናዊና ዘዳግማዊ ምንጮች” ብሎ ያስቀመጠው ግምትም የሚያስኬድ አይደለም፡፡ እጅግ ደካማ ነው፡፡

ሙስሊሞች ይህንን መላ ምት መቀበላቸው ምን ችግር ያስከትላል?

  1. ከቁርኣንና ከሐዲስ መጻሕፍት ጋር ይጋጫል፡፡ የሙሴ ተውራት በሙሐመድ ዘመን በአይሁድና በክርስቲያኖች እንጅ እንደነበረ ቁርኣንና እስላማዊ ሐዲሳት ይመሰክራሉ (ሱራ 2፡40-41፣ 2፡89፣ 2፡91፣ 2፡101፣ 10፡94፣ 7፡169፣ 2፡44፣ 2፡113፣ 2፡121፣ 3፡93፣ 3፡113፣ 5፡66፣ 5፡68፣ 5፡43-44፣ 5፡65፣ 2፡4፣ Sunan Abu Dawud, Book 38, Number 4434)፡፡ በታሪክ የታወቀው ተውራት (ቶራህ) የዶክሜንተሪ ሃይፖቴሲስ አቀንቃኞች እየተቿቸው የሚገኙት የአምስቱ መጻሕፍት ስብስብ በመሆኑ ሙስሊሞች ይህንን መላምት ከተቀበሉ የገዛ እምነታቸውን ውድቅ አደረጉ ማለት ነው፡፡
  2. የመላምቱ ዋልታና ማገር “የእስራኤላውያን አሓዳዊነት በዝግመተ ለውጥ ከመድብለ አማልክታዊነት የተገኘ በመሆኑ የሙሴን ያህል ዕድሜ የለውም” የሚል ነው (Geisler, pp. 1390-91)፡፡ ነገር ግን ከአብርሃም ጀምሮ፣ ልጁ ይስሓቅና የይስሐቅ ልጅ ያዕቆብ እንዲሁም ከእርሱ የተገኙት አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች አንዱን አምላክ ያመልኩ እንደበር ሙስሊሞች ስለሚያምኑ ሊያስኬዳቸው አይችልም፡፡ መላምቱን መቀበል አብረሃምና ነገዶቹ አንዱን አምላክ አያውቁትም ማለት ይሆናልና፡፡
  3. የመላምቱ ዋና ዓላማ እግዚአብሔር አምላክ በሙሴ በኩል የሠራቸውን ተዓምራትና እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ያደረጉትን ጉዞ ማጣጣል በመሆኑ ሙስሊሞች ይህንን መላምት ከተቀበሉ እነዚህን እውነታዎች ሊክዱ ነው፡፡ እነዚህን እውነታዎች መካድ ደግሞ ቁርኣንን መካድ ነው (ሱራ 28፡30-32፣ 26፡61-68)፡፡
  4. አንድ ሰው የቁርኣንንም ክፍሎች በዚህ መንገድ ከፋፍሎ ተመሳሳይ መላምት መፍጠር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ረብ የሚለው የፈጣሪ ስም በ 11 የቁርኣን ሱራዎች ውስጥ አይገኝም (24፣ 48፣ 49፣ 58፣ 61፣ 62፣ 77፣ 88፣ 95፣ 104፣ 112)፡፡ እንዲሁም አላህ የሚለው ስም በ 18 ሱራዎች ውስጥ አይገኝም (54፣ 55፣ 56፣ 68፣ 75፣ 78፣ 83፣ 89፣ 92፣ 93፣ 94፣ 99፣ 100፣ 105፣ 106፣ 108፣ 113፣ 114)፡፡ ስለዚህ ረብ ያልተጠቀሰባቸውን፣ አላህ ያልተጠቀሰባቸውን እንዲሁም ረብና አላህ ተቀላቅለው የተጠቀሱባቸውን ሱራዎች ይዘን ከሦስት የተለያዩ ምንጮች የተቀዱ ናቸው ልንል እንችላለን፡፡ ዶክሜንተሪ ሃይፖቴሲስ ማለት በአጭሩ ይህ ነው፡፡ ሙስሊም ወገኖች ቁርኣንን በተመለከተ እንዲህ ያለውን ግምታዊ አመለካከት የማይቀበሉ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን ፈጥነው ተቀብለው የሚያስተጋቡበት ምክንያት ምን ይሆን?

 

መጽሐፍ ቅዱስ