ኢንጂል ተበርዟልን? ስለ አዲስ ኪዳን እውነቱን ለማወቅ ያደረኩት ፍለጋ 

ኢንጂል ተበርዟልን?

ስለ አዲስ ኪዳን እውነቱን ለማወቅ ያደረኩት ፍለጋ                    

ፉአድ መስሪ

በኢቡክ መልክ www.fouadmasri.com ላይ ይገኛል፡፡

ውድ አንባቢ

ፈጣሪ ይመስገን! አልሐምዱሊላህ!

ይህንን መጽሐፍ እንድጽፍ ኃይልን የሰጠኝ ፈጣሪ ነው፡፡ የዒሳ አልመሲህ መጽሐፍ በሆነው በቅዱስ ኢንጂል ላይ ያደረኩትን ይህንን ጥናት ለናንተ አቀርባለሁ፡፡ እግዚአብሔር አልኢንጂልን የላከልን ፈቃዱን ትዕዛዛቱን በማወቅ የእምነትን ሕይወት እንድንኖር ነው፡፡ በፈጣሪ (ሱበሃነ ወተዓላ) በማመን መኖር ታላቅ ሕይወት ነው፡፡ እምነት በዚህ ምድር ላይ ስኬታማ የሚያደርገንና ትርጉ የሚሰጠን ነዳጅ ነው፡፡ ከዚህም በመነሳት ይህንን መጽሐፍ ለኛ ኡማ አበረክታለሁ። በችግር ውስጥ ላለው ዓለማችን በረከት ይሁን፡፡

አብደላህ (የአላህ አገልጋይ)

ፉአድ መስሪ

ምዕራፍ 1

መግቢያ

“ኢንጂል ተበርዟል” ሲባል ሰምታችሁ ይሆናል፡፡ ምናልባት እናንተም ተናግራችሁት ይሆናል፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ ባሳለፍኳቸው ዘመናት አስተማሪዎቼና ተማሪ ጓደኞቼ ኢንጂልን ሲያጣጥሉ መስማት የተለመደ ነበር፡፡ ክርስቲያኖች ስለቀየሩት በዘመናት መካከል ትክክለኛ ይዘቱን አጥቷል ይላሉ፡፡

የሃይስኩል ተማሪ ሳለሁ ከማል የተባለ ጓደኛዬ ክርስቲያኖች ኢንጂልን ስለለወጡት ላነበው እንደማይገባ ነግሮኝ ነበር፡፡

ከማልን “ወንጌልን አንብበህ ታውቃለህን?” ብዬ ጠየኩት፡፡

“አላውቅም” በማለት መለሰልኝ፡፡

“ካላነበብከው ታድያ እንደተበረዘ እንዴት አወክ?” ብዬ ጠየኩት፡፡

“አያቴና አጎቴ ነግረውኛል” በማለት መለሰልኝ፡፡

ጉዳዩን ሳጣራ ኢንጂል እንደተበረዘ የተናገሩት እርሱ የጠቀሳቸው ዘመዶቹም መጽሐፉን እንዳላነበቡት ተረዳሁ፡፡

ወንጌል በአስተማሪዎቼና በጓደኞቼ ለምን እንደተናቀ፣ እንደተደበቀና እንደነውር እንደተቆጠረ እንዳጠና ያነሳሳኝ ይህ ሁኔታ ነበር፡፡

አስገራሚው ነገር ሙስሊሞች ወንጌልን አግኝተው የማንበብና የማመን ግዴታ እንዳለባቸው መረዳት መቻሌ ነው፡፡ ክርስቲያኖችም የመናገር ግዴታ አለባቸው፡፡ ጓደኞቼ ወንጌልን እንደ መጥፎ ዜና የሚቆጥሩት ሲሆኔ ክርስቲያኖች ግን እንደ መልካም ዜና እንደሚቆጥሩት ማወቅ ችያለሁ፡፡

የፈጣሪ መልእክት

ኢንጂል የኢየሱስ መጽሐፍ የአረብኛ ስያሜ ነው፡፡ የመጽሐፉ የመጀመርያው ስያሜ የሆነው ኢዋንጌሊዮን የሚለው የግሪከኛ ቃል መልካም ዜና የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ በአረብኛ መጽሐፉ ኢንጂል ተብሏል፡፡

ኢንጂል ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚከተሉት ሰዎች የተሰጠ የፈጣሪ መልእክት ነው፡፡ ኢንጂል እያንዳንዱን የክርስቲያን ሕይወትና እምነት ይመራል፡፡

ኢንጂል ሙስሊሞች ሊያምኗቸው፣ ሊከተሏቸውና ሊታዘዟቸው ከሚገቡ አራት መጻሕፍት መካከል አንዱ መሆኑን ኢማሞች ያስተምራሉ፡፡ እንደርሱ ከሆነ በብዙ እስላማዊ የመጻሕፍት መደብር ውስጥ ኢንጂልን ለምን አናገኘውም? ሙስሊሞች በኢንጂል ማመን ካለባቸው አንዳንድ እስላማዊ መንግሥታት ዜጎቻቸው እንዳያነቡት ስለምን ይከለክላሉ?

የከማል አጎት እንደተናገረው ኢንጂል ተለውጦ ይሆን? ራሴን ጠየኩት፡፡

ሙስሊሞች ቁርአን አል-ከሪምን ጨምሮ ፈጣሪ ለሰው ልጆች የላካቸውን አል-ተውራት (የሙሴ መጽሐፍ)፣ አዝ-ዘቡር (የዳዊት መጽሐፍ)፣ እንዲሁም አል-ኢንጂል (የኢየሱስ መጽሐፍ) ማመን ይጠበቅባቸዋል፡፡

አንድ ሰው እንዲህ አለኝ “ሙስሊሞች እነዚህን ሁሉ መጻሕፍት ማክበር ይጠበቅባቸዋል ነገር ግን ቁርአንን ብቻ እንከተላለን”፡፡ ኢንጂል በብዙ ሙስሊም አገራት ውስጥ የማይገኝበት ምክንያት የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች እንደተበረዘ በማመናቸው ምክንያት ነው፡፡  ታህሪፍ የተሰኘ አይሁድና ክርስቲያኖች ቅዱሳት መጻሕፍታቸውን በርዘውታል የሚል አስተሳሰብን ይከተላሉ፡፡

የተለመደው ማብራርያ የሚከተለው ነው፡-

  1. አል-ተውራት (የሙሴ መጽሐፍ) ስለተበረዘ ፈጣሪ አዝ-ዘቡር (የዳዊትን መጽሐፍ) ላከ፡፡
  2. አዝ-ዘቡር ሲበረዝ ፈጣሪ ኢንጂልን ላከ፡፡
  3. በመጨረሻም አል-ኢንጂል ሲበረዝ ፈጣሪ አል-ቁርአን ከሪምን ላከ፡፡
  4. ቁርአን የፈጣሪ ቃል ስለሆነ ሊበረዝ አይችልም፡፡

ይህ ኢ-አመክንዮአዊ አስተሳሰብ ነበር ስለ ኢንጂል እንዳናውቅ የተከለከልነው ምን እንደሆነ እንድመረምር ያነሳሳኝ፡፡ ኢንጂል በእውነት ተበርዟልን? ክርስቲያኖች ኢንጂልን ለውጠውታልን?

ኢንጂልን በማጥናት በግሌ ብረዛውን ለማጋለጥ ተነሳሳሁ፡፡ ለራሴ እንዲህ አልኩት፡- እውነታዎቹን ሳልመረምር ለምን በማሕበረሰቤ ትውፊት ላይ ብቻ እመሠረታለሁ? አብዛኞቹ ኢንጂልን አላነበቡትም ነገር ግን ያጣጥሉታል፡፡ ብዙዎች ምድር ክብ መሆኗን እውነታዎችን በማጥናት ከማረጋገጣቸው በፊት ዝርግ እንደሆነች አስበው ነበር፡፡ ነገሮች ብዙ ጊዜ መስለው ከሚታዩን የተለዩ ናቸው፡፡

በማስከተል የሚገኘው ለፈጣሪ የተገዙ ሰዎች በሚጠይቁት ወሳኝ ጥያቄ ላይ ያደረኩት ጥናት ጭማቂ ነው፤ ኢንጂል ተበርዟልን?

ምዕራፍ 2

የቁርአን ምስክርነት

ቁርአን ስለ ኢንጂል ምን ይላል?

አል-ኢንጂል ከፈጣሪ ዘንድ የተላከ ነው

(ቁርአን 3፡2-4)

ሙስሊሞች ኢንጂልን ማንበብና ማመን ይኖርባቸዋል

(ቁርአን 2፡136

(ቁርአን 57፡27)

(ቁርአን 5፡68)

ፈጣሪ ቃሉን ይጠብቃል

(ቁርአን 2፡148)

ብዙ ኢማሞች ቀደም ሲል ከተጠቀሱት የቁርአን ጥቅሶች  በተቃራኒ እንደሚያስተምሩ ስደርስበት በጣም ተገረምኩኝ፡፡ እንዲህ ይላሉ፡- አል-ተውራት (የሙሴ መጽሐፍ) ስለተበረዘ ፈጣሪ አዝ-ዘቡር (የዳዊትን መጽሐፍ) ላከ፡፡ አዝ-ዘቡር ሲበረዝ ፈጣሪ ኢንጂልን ላከ፡፡ በመጨረሻም አል-ኢንጂል ሲበረዝ ፈጣሪ አል-ቁርአን ከሪምን ላከ፡፡ ቁርአን የፈጣሪ ቃል ስለሆነ ሊበረዝ አይችልም፡፡

ነገር ግን የእስልምና ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው ቁርአን እንዲህ ያለ ነገር አይናገርም፡፡

ምዕራፍ 3

ፈጣሪ እውነተኛ ይሁን

ኢንጂል ስለ ራሱ ምን ይላል?

ቁርአን የኢንጂልን አስፈላጊነት ይጠቁማል ነገር ግን ኢንጂል ስለ ራሱ አስፈላጊነት የሚናገረውን መመልከት ወሳኝ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለአይሁድ፣ ለክርስቲያኖችና ለመላው የሰው ልጆች በኢንጂል ውስጥ ያስቀመጠውን ምክር ስሙ፡-

ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ምንጫቸው እግዚአብሔር ነው

“የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” (2ጢሞቴዎስ 3፡16-17)

“ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።” (2ጴጥሮስ 1፡20-21)

የእግዚአብሔር ቃል ፀንቶ በመኖር ይፈፀማል

“እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ።” (ማቴዎስ 5፡17-18)

“ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም።” (ማቴዎስ 24፡35)

የእግዚአብሔር ቃል ፀንቶ የሚኖርና ሕይወት ሰጪ ነው

“ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ።” (1ጴጥሮስ 1፡23)

እግዚአብሔር ቃሉን ይጠብቃል

“በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የትንቢት ቃል ለሚሰማ ሁሉ እኔ እመሰክራለሁ፤ ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል፤ ማንምም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል፥ በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ዕድሉን ያጎድልበታል።” (ራዕይ 22፡18-19)

እግዚአብሔር ቃሉን እንደሚጠብቅ የሚናገረው ኢንጂል ብቻ ሳይሆን ዘቡርና ተውራትም ጭምር ናቸው፡፡

ከተውራት

“ከእነርሱ ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ይህ ነው ይላል እግዚአብሔር፤ በአንተ ላይ ያለው መንፈሴ በአፍህም ውስጥ ያደረግሁት ቃሌ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ ከአፍህ ከዘርህም አፍ ከዘር ዘርህም አፍ አያልፍም፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡” (ኢሳይያስ 59፡21)

በእርግጥ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ቃል ካለመታዘዝና ከመለወጥ ይልቅ ሞታቸውን ይመርጣሉ፡፡

ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ ተከታዮቹ ከቦታ ወደ ቦታ በመዞር እርሱ የሰው ልጆች ሁሉ አዳኝ እንደሆነ ያውጁ ነበር፡፡ የአይሁድ መሪዎች ቃላቸውን አልተቀበሉም፤ ሮማውያንና አረማውያን ነገሥታትም የኢየሱስ ተከታዮች በሚሰብኩት ስብከት ያላግጡ ነበር፡፡

በክርስትና የመጀመርያዎቹ ሦስት መቶ ዓመታት ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት ይጨፈጨፉ፣ ይጠቁና ይሠቃዩ ነበር፡፡ ሰላማዊያንና ንፁሃን ሰዎች ሆነው ሳሉ ክርስቶስ እንደ ዓለም አዳን በማመናቸው ብቻ ፍትሃዊ ያልሆነ ግፍ ይፈፀምባቸው ነበር፡፡ በብዙ ሁኔታዎች እነዚህ የክርስትና እምነት ሰማዕታት አሳዳጆቻቸው ክርስትናን እንዲቀበሉ ምክንያት ሆነው ነበር፡፡

የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ቃል እውነት እንደሆነ ያምኑ ነበር፤ ካለፉት ጥቅሶች በመነሳት እግዚአብሔር ሃያል የሆነ የአፅናፈ ዓለም ፈጣሪ በመሆኑ ኢንጂልን ለመጠበቅ የገባውን ቃል የመጠበቅ ኃይል እንዳለው ያምኑ ነበር፡፡

ምዕራፍ 4

ከሃያሉ ፈጣሪ በላይ ኃይል ያለው የለም

ሥነ መለኮታዊ ምርመራ

በፈጣሪ እንሚያምን ሙዕሚን የፈጣሪ ቃል በሰዎች መለወጥ መቻሉ ሊገባኝ ያልቻለ ጉዳይ ነበር፡፡ ፈጣሪ ኢንጂልን ከገለጠ እርሱን የመጠበቅ ኃላፊነት የእርሱ አይደለምን? ብዬ ራሴን ጠይቄያለሁ፡፡ እግዚአብሔር የአፅናፈ ዓለም ፈጣሪ መሆኑን እናውቃለን፤ ጸሐይ፣ ከዋክብት፣ ጨረቃ፣ ሁሉም በእርሱ ተፈጥረዋል፡፡ እርሱ ሰዎችን፣ አእምሯቸውንና ዕውቀታቸውን ፈጥሯል፡፡ እግዚአብሔር ልብን የሚመረምር የሼኮችንና የዜጎችን፣ የነጋዴዎችንና የእረኞችን፣ የሳይንቲስቶችንና የአርቲስቶችን የልብ ሐሳብ የሚያውቅ አምላከ ነው፡፡ የእርሱ ዕውቀት የጊዜ ክፍሎችንና ዘመናትን ተሻጋሪ ነው፡፡ ያለፈውን፣ የአሁኑንና መፃዒውን የሚያውቅ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ነው!

ሰዎች ከፈጣሪ ይልቅ ሃያላን ናቸውን

ፈጣሪ ቃሉን ለሰው ልጆች ከገለጠና የሰው ልጆች ቃሉን መበረዝ ከቻሉ ያ የሰው ልጆችን ከፈጣሪ በላይ ሃያላን አያደርጋቸውምን? የማይሆን ነው!

የፈጣሪ ቃልና መልእክት እንደተበረዘ ካመንኩኝ ሃያሉ ፈጣሪ (ሱብሃነ ወተዓላ) ሳይሆን እንደ እኔ ያለ ተራ ሰው የሁሉም ነገር መለኪያ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ፈጣሪ ኢንጂልን የላከው ሰዎች እውነት እንዲበራላቸው ነው፤ ኢየሱስም እውነት ነፃ እንደሚያወጣን ተናግሯል፡፡ ሰዎች ከፈጣሪያቸው ይልቅ በምንም ተዓምር ብርቱዎች አይደሉም! ኢንጂል የፈጣሪ ቃል በመሆኑ በፍፁም ሊበርዙት አይችሉም፡፡

ኢየሱስ ስለ ፈጣሪ ቃል የነበረው እሳቤ 

በእስልምና መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጣሪ ተወዳጅ ነቢይ ነው (ሐቢብ አላህ)፡፡

በእርግጥ እርሱ ከፍጥረት በፊት ዓለምን ይዋጅ ዘንድ (አል ፋዲ) የተመረጠ ነው (ሙስጠፋ አላህ)፡፡

በኢንጂል ውስጥ ኢየሱስ በቢሸረት ማርቁስ  ምዕራፍ 13 አያ 31 ላይ እንዲህ አለ፡- “ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም፡፡”

በተጨማሪም በ 2ጢሞቴዎስ 3፡16 ላይ ኢንጂል ሁሉም ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር መንፈስ እንዳለባቸው ይናገራል፡፡ እርሱ ነው የገለጣቸው ስለዚህ የእርሱ ናቸው፡፡

ኢንጂል ከየት እንደመጣ በግልፅ ይናገራል፡- “ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።” (2ጴጥሮስ 1፡20-21)

ፈጣሪን እንመን ሰውን እንጠራጠር

በሃያሉ ፈጣሪ ላይ ያለኝ እምነት ኢንጂል እንደተበረዘ የሚናገሩትን እነዚያን የሃይማኖት መምህራን እንድጠራጠር አድርጎኛል፡፡ አስቶጉፉሩላህ! የፈጣሪ ቃል እኔን በመሳሰሉ ፍጡራን ሰዎች ከመበረዝ የረቀ ነው፡፡

ኢንጂል እንደተበረዘ በተናገሩ ቁጥር ፈጣሪን እየተሳደቡ ነው፡፡ ፈጣሪ ኢንጂልን የላከ ሲሆን በሁሉም ላይ ሥልጣን አለው፤ ኢንጂልን በሰው ልጆች ሁሉ ላይ መስካሪ ይሆን ዘንድ ይጠብቀዋል፡፡

ፈጣሪ ፍትሃዊ ነው፤ ሰዎች ለኢንጂል መልእክት በሰጡት ምላሽ ላይ ተመሥርቶ ፍትሃዊ የሆነ ፍርድ ይሰጥ ዘንድ ቃሉን ይጠብቃል፡፡

ማንም ሊያበላሸው አይችልም፡፡ ፈጣሪ ሊጠብቀው ቃል ገብቷል፡፡ ማንም ሰው ደግሞ ከፈጣሪ በላይ ሃያል አደለም፡፡

ምዕራፍ 5

ምናባዊ አስተሳሰብና እውነታ

ሥነ አመክንዮአዊ ምርመራ

እውነት ሐሰትን ድል ነስታ ትቆማለች! እግዚአብሔር ለእርሱና ለተስፋዎቹ ባለን አክብሮት ላይ ብቻ ተመሥርተን ሳይሆን አመክንዮና የማሰብ ችሎታችንን በመጠቀም ጭምር እውነትን እንድናውቅ ይፈልጋል፡፡

እኛ የሰው ልጆች መረጃዎችን በምንሰበስብበት፣ በምናብላላበት፣ ድምዳሜ ላይ በምንደርስበትና ለሌሎች በምናስተላልፍበት መንገድ ከሌሎች ፍጡራን እንለያለን፡፡ የማሰብ ችሎታችን እውነትን የሚፃረር አይደለም፤ ይልቁኑ ያረጋግጠዋል፡፡ እግዚአብሔር ማሰብ የሚችል አእምሮ ከሰጠኝ የቃሉን እውነት መሆን ለማረጋገጥ ይህንኑ የማሰብ ችሎታዬን መጠቀም ይችላል፡፡

ከዚህ ሐሳብ በመነሳት የኢንጂልን መበረዝ ከአመክንዮ አንፃር ልመረምር ተነሳሁ፡፡ ምናልባት ፈጣሪ እኔ ያሰብኩትን ያህል ኃይል የሌለው ይሆን? (አስቶጉፍሩላህ)፡፡

ተከታዮቹ ወሳኝ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው የጥናቴ ውጤቶች ናቸው፡፡ ፈጣሪ ቃሉ የሆነውን ኢንጂልን የመጠበቅ ችሎታውን በመጠራጠሬ አስቀድሜ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡

ሰባት ወሳኝ ጥያቄዎች

1.                           ኢንጂልን ማን ለወጠው?

ኢንጂል ይለወጥ ዘንድ ይህንን ሴራና ተንኮል የሚፈፅሙ ሰዎች በታሪክ ውስጥ መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡

ከፈጣሪ ዘንድ የተላከውን መገለጥ ለመለወጥ አልሞ ጊዜውንና ጉልበቱን ይህንን ለመሰለ ተግባር የሚያውል ሰው ማን ነው? በፈጣሪና በክርስቲያኖች ላይ ክህደትን በመፈፀም ኢንጂልን የሚበርዝ ሰው ምን ዓይነት ነው?

ይህ ብረዛ በእግዚአብሔር ፍትሃዊ ፍርድና በክርስቶስ አዳኝነት በሚያምን ክርስቲያን ተፈፅሞ ይሆን? ወይንስ ይህንን ተግባር የፈፀመው አረማዊ ወይንም አይሁድ ቀናተኛ ይሆን?

እንዲህ ያለ ከሃዲ ኖሮ ቢሆን ኖሮ በኢንጂል ላይ የጨመረውንና የቀነሰውን ይህንን ሰው ታሪክ ባጋለጠው ነበር፡፡

2.                           ኢንጂል ስለምን ነበር የተለወጠው?

እንዲህ ያለ ሰው ኢንጂልን ስለምን ይለውጣል? ኢንጂል የፈጣሪን መኖር የሚገልጥና ፈጣሪ ለዓለም ያለውን ውብ ዕቅድ የያዘ መጽሐፍ ከሆነ አንድ ሰው ያንን የመሰለ መገለጥ ለመለወጥ ምን ያነሳሳዋል?

ኢንጂል ተለውጦ ቢሆን ኖሮ ፈጣሪ ጥንታዊያኑ ክርስቲያኖች ለስድስት መቶ ዓመታት ያህል የእርሱን ፈቃድ ባለማወቅ እንዲኖሩ ስለምን ፈቀደ? (ኢንጂል ተበረዘ በተባለበት ጊዜና በእስልምናው ነቢይ መምጣት መካከል ላለው ዘመን)፡፡ ሰዎች የፈጣሪን ፈቃድ ለማወቅ ሁሌም ፍለጋ እንዳደረጉ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ አስተሳሰብ ዋጋ ማሳጣት ለምን አስፈለገ?

3.                           ኢንጂል የት ሀገር ነበር የተለወጠው?

በየትኛው ከተማ ወይንም በየትኛው ቦታ ነበር ኢንጂል የተለወጠው? ብረዛው የተፈፀመው በፖለቲካ ወይንስ በሃይማኖት ማዕከል? ኢንጂል ስጋት የሆነባቸው የትኞቹ መንግሥታት ናቸው?

ሮም፣ ቢዛንቲን፣ ኢየሩሳሌም፣ እነዚህ ሁሉ ከተሞች የሃይማኖት ማዕከላት ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁሉ ከፈጣሪ በላይ ኃይል ኖሯቸው ይሆን? ኦሪጂናል ኢንጂልን አግኝተን ተበረዘ ከተባለው ጋር ማነፃፀር እንችል ይሆን?

4.                           ኢንጂል መች ነበር የተለወጠው?

በታሪክ በየትኛው ዘመን ነበር ኢንጂል የተለወጠው? በክርስትና ትውፊት መሠረት ክርስቶስ የተሰቀለው 30ኛ ዓመቱ አካባቢ ሲሆን ክስተቱ በ 29 ዓ.ም. እስከ 33 ዓ.ም. መካከል ነበር፡፡

ከክርስቶስ በኋላ ለሦስት መቶ ዓመታት ያህል ክርስቲያኖች ክፉኛ ይሰደዱ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ቁልፍ ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል፡፡

5.                           የኢንጂል ብረዛ የተፈፀመው ከመሐመድ መምጣት በፊት ነው ወይንስ በኋላ?

ነቢዩ ሙሐመድ ሙስሊሞች ሁሉ ኢንጂልን እንዲያነቡ ስላዘዙ የተበረዘው ከእሳቸው ዘመን በኋላ መሆን አለበት፡፡ የተበረዘ መጽሐፍ እንድናነብ ስለምን ያዝዙን ነበር?

በሌላ ወገን ደግሞ ኢንጂል በእሳቸው ዘመን ወይንም ከእሳቸው ዘመን በፊት ተበርዞ ቢሆን ኖሮ ያንን በነገሩን ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ተበርዞ እንደሆን በታሪክ የኋሊት በመሄድ ማግኘት ይኖርብናል፡፡

6.                           የትኞቹ ክፍሎች ናቸው የተበረዙት?

ብዙ ኢማሞች ኢንጂል መበረዙን ይናገራሉ ነገር ግን የትኞቹ የኢንጂል ክፍሎች እንደተበረዙ ሊነግሩኝ አልቻሉም፡፡

ብረዛው የከፋ በመሆኑ ሁሉንም የኢንጂል ክፍሎች ለውጦ ይሆን? ከሆነ የወንጌልን መልእክት በማንበብ የሚገኝ ጥቅም ይኖራልን? ሁሉም ተበርዞ ከሆነ ቁርአን በእርሱ እንድናምንና እንድናነበው ስለምን ይናገራል?

ምናልባት የተወሰነ የኢንጂል ክፍል ብቻ ተለውጦ ይሆናል፡፡ እንደርሱ ከሆነ እውነቱን ከስህተት መለየት የምችለው እንዴት ነው? ፈጣሪ የተወሰነውን ክፍል ጠብቆ የተቀረውን መጠበቅ ተስኖት ይሆን?

7.                           ኦሪጅናል ጽሑፉ የት ነው የሚገኘው?

ይህ ለኔ ቁልፍ ጥያቄ ነበር፡፡ ሁሉም አሓዳውያን ሃይማኖታት የናዝሬቱ ኢየሱስን መምጣት ያረጋግጣሉ፡፡ ስለዚህ እውነተኛው ኢንጂል የት ነው የሚገኘው? ፈጣሪን እንደሚፈራ ሰው የፈጣሪን ትዕዛዝ በማክበር ኢንጂልን አግኝቼ ማጥናትና ማክበር ይኖርብኛል፡፡ ዋናው ኢንጂል ከጠፋ ፈጣሪዬን ታዝዤ ኢንጂልን ማንበብ የምችለው እንዴት ነው? ፈጣሪ እንዲህ ያለውን ውጥንቅጥ ይፈቅዳልን?

ፈጣሪ ኢየሱስንና ኢንጂልን ለሰው ልጆች በትውልዶች ሁሉ ብርሃን እንዲሆኑ ስለላካቸው ሃይማኖታዊ ግዴታዬን ለመወጣት ኦሪጅናሉን ኢንጂል አግኝቼ ማንበብ ይኖርብኛል፡፡

የመጨረሻው መገለጥ

አንድ በተደጋጋሚ የሰማሁት ሙግት ትኩረትን ይስባል፡፡ አንዳንድ ሙስሊም ሊቃውንት እስልምና ኋላ ላይ የመጣ ሃይማኖት በመሆኑ በኢንጂል ውስጥ የሚገኙትን ስህተቶችና ስለ ፈጣሪ የሚያቀርባቸውን የተሳሳቱ አመለካከቶች እንዳረመ ይናገራሉ፡፡

ይህንን ሐሳብ ለመደገፍ የሚጠቀሰው የቁርአን ጥቅስ 16፡101-102 ላይ የሚገኘው ነው፡፡

የቁርአን መልእክት መጨረሻ ላይ የመጣ ቢሆንም መልእክቱ አረማውያንን ወደ አንዱ እውነተኛ አምላክ ይጠራ ከነበረው ከአብርሃም መልእክት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

ቁርአን ለሙሐመድ በተሰጠበት ጊዜ አንዱን አምላክ የሚያመልኩ ሰዎች ለሙሴ በተሰጠው ቃል (ተውራት)፣ ለዳዊት በተሰጠው ቃል (ዘቡር) እና ለዒሳ በተሰጠው ቃል (ኢንጂል) ተመርተዋል፡፡

ነቢዩ አብርሃም (ኢብራሂም) የቤተሰቦቹን ጣዖታት በመተው ወደ አንዱና እውነተኛው አምላክ በመመለስ የመጀመርያው ነበር፡፡ ቤተሰቦቹን ከአረማውያን ምድር ፈጣሪ ወዳሳየው ምድር መርቶ ነበር፡፡

ለሙሴ (ሙሳ)፣ ለዳዊት (ዳውድ) እና ለኢየሱስ (ዒሳ) የተሰጡት መልእክቶች ግን ለተለዩ አድማጮች የተሰጡ ነበሩ – አንዱንና እውነተኛውን አምላክ ለሚያመልኩ ሰዎች፡፡ ስለዚህ በተውራት፣ ዘቡርና ኢንጂል ውስጥ የሚገኘው የፈጣሪ መልእክት በአሓዳዊነት መልእክት ላይ የተገነባ ሲሆን የበለጠ ጥልቅ የሆኑ ነገረ መለኮታዊ ፅንሰ ሐሳቦችን፣ ስለ ፈጣሪ ይበልጥ የጠለቁ መረዳቶችንና ለኑሮ ተግባራዊ የሆኑ መመርያዎችን የያዘ ነው፡፡

የፈጣሪ መገለጥ ወደ ድምዳሜ የመጣቸው የፈጣሪ ቃል በሆነው በኢየሱስ (ዒሳ ኢብን መርየም) ነው፡፡ የእርሱ መልእክት ሀገር፣ ዘርና ቋንቋ ሳይለይ ለሁሉም የሰው ልጆች የመጣ ነው፡፡

“እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 29፡19-20)

 “እላችኋለሁም፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፡፡” (ማቴዎስ 8፡11)

“አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።” (ገላቲያ 3፡28)

ቁርአን የቀደሙትን መገለጦች እንደተካ አልተናገረም

በአንፃሩ ቁርአን አሓዳዊነትን በመካድ መድብለ አማልክትን ወደሚከተሉት አረቦች የመጣ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ አል-ጀህሊያ ወይንም የድንቁርና ዘመን በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ለአረብ ሰዎች እንደ ማንቂያ የመጣ መልእክት ነበር፡፡ ለዚህ ነው ቁርአን ቋንቋው አረብኛ የሆነው ለአረቦች እንዲገባቸው በማለም እንደሆነ የሚናገረው፡-

(አዝ-ዙክሩፍ 43፡3)

በተጫማሪም ቁርአን መልእክቱ የቀደሙትን መለእክቶች እንደሚያረጋግጥ በተደጋጋሚ ይናገራል፤ የቀደሙትን መልእክቶች እንደተካ አይናገርም፡፡

(አል-ማዒዳህ 5፡48)

የፈጣሪን ቃላት መለወጥ?

አንዳንድ ሙስሊሞች ክርስቲያኖች የፈጣሪን ቃል እንደለወጡት ለማመልከት ተከታዩን የቁርአን ጥቅስ ይጠቅሳሉ፡-

(አል-በቀራ 2፡146)

(አል-ኢምራን 3፡71)

(አል-በቀራ 2፡159)

ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች የፈጣሪን ቃል ስለለወጡ ሰዎች ሳይሆን ስለደበቁት ግለሰቦች የሚናገሩ ናቸው፡፡ ፈጣሪ ከሰዎች ይልቅ ሃያል ነው፡፡ ሰዎች ቃሉን ለመደበቅ ቢሞክሩም የእርሱ እውነት ውሸትን ድል ነስታ ትቆማለች፡፡

እውነትን መፍራት

ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ጥናት ሳደርግ በማሕበረሰቤ ውስጥ የሚገኙት የሃይማኖት መሪዎች በእጅጉ ዕውቀት የጎደላቸው መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡ ጥያቄዎችን የሚፈሩ ይመስላሉ፡፡ እነዚህን ሐሳቦች መወያየት ክልክል ነው፡፡ ጥያቄዎችን መጠየቅ ስጀምር ከሃይማኖቴ እንዳፈነገጥኩ ነበር የተቆጠርኩት፡፡ ለምንድነው ኢንጂልን የማላነበው? ብዬ ራሴን ጠየኩት፡፡

አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ብረዛውን ዘመናትን፣ ክስተቶችንና ቦታዎችን በመጥቀስ ለማረጋገጥ ሲሞክሩ ሰምቻለሁ ነገር ግን ብሒሎቻቸውን በጥልቀት ሳጠና ስለ ኢየሱስ ሕይወትና ስለ ኢንጂል እንዲሁም ስለ ክርስትና ታሪክ የነበራቸውን የዕውቀት ጉድለት ማስተዋል ችያለሁ፡፡

ጓደኞቼ እውነትን ለመፈለግ አደርግ የነበረውን ጥረት ይቃወሙ ነበር፡፡ ከዲስ  ኪዳንን ለምን እንደማጠና በተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቦብኝ ለጥቃት ተዳርጌያለሁ፡፡

ይህ ሁሉ ተቃውሞ ለምን? ኢንጂልን በመመልከት ጥሩ አማኝ ለመሆን ጥረት እያደረኩ ብቻ ነበር፡፡ አመክንዮአቸው ከባሕርያቸው የከፋ ነበር፡፡ ፈጣሪያቸውን የሚጠሙ ሳይሆኑ ደም የሚጠሙ ነበሩ፡፡

በዚህ ጊዜ ጥናቴ የአዲስ ኪዳንን ታሪካዊ ማስረጃና ክርስቲያኖች ለምን እንደሚከተሉት ወደ መመርመር መራኝ፡፡

ምዕራፍ 6

የእጅ ጽሑፎች ይናገራሉ

ታሪካዊ ምርመራ

መልስ ለማግኘት ያደረኩት ጥረት የአዲስ ኪዳንን ታሪካዊ ዳራና የእጅ ጽሑፎች ወደማጥናት መራኝ፡፡

ኢንጂል በክርስቲያኖች ዘንድ በእጅጉ እንደሚከበር ማወቅ ቻልኩኝ፡፡ ከብረዛ እርሱን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ የኢንጂል ታሪክ በሦስት ታሪካዊ ክፍሎች ሊከፈል ይችላል፡፡

. የዐይን ምስክሮች ደረጃ

. የስደት ደረጃ

. የትርጉም ደረጃ

ሀ. የዐይን ምስክሮች ደረጃ (0-100 ዓ.ም.)

ኢየሱስ ተዓምራዊ በሆነ ሁኔታ ከድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ ልደቱ ኢሳይያስን በመሳሰሉት ነቢያት አስቀድሞ ተነግሮ ነበር፡፡

ከድንግል ስለመወለዱ አስቀድሞ ተነግሯል

(ኢሳይያስ 7፡14)

የሚወለድበት ከተማ አስቀድሞ ተነግሯል

(ሚክያስ 5፡2)

ቀድም ሲል በተጠቀሱት ጥቅሶች ውስጥ እንደተመለከታችሁት የነቢዩ ዒሳ (ኢየሱስ የማርያም ልጅ) ልደት በመቶዎች ከሚቆጠሩት ዓመታት በፊት አስቀድሞ ተነግሯል፡፡ መሲሁ ሰዎችን ወደ ፈጣሪ እውነት ለመምራት እንደሚመጣ ተውራት በግልፅ ይናገራል፡፡

(ዮሐንስ 1፡41)

ይህ ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበትና የብዙ አማኞች መሪ ነበር፡፡ ሙታንን አስነስቷል የታመሙትን ፈውሷል፡፡ የእርሱ ትምህርትና ቃላት በአል ኢንጂል ውስጥ ተመስዝግበዋል፡፡

አል ኢንጂል የሚለው ቃል ኢዋንጌሊዮን የሚለውን የግሪክ ስያሜ ተክቶ የገባ የአረብኛ ቃል ነው፡፡ ኢየሱስና ተከታዮቹ የሮማ ኢምፓየር መግባቢያ የነበረውን ኮይኔ ግሪክ ይናገሩ ነበር፡፡ በተጨማሪም ምሑራን የተስማሙበት ነገር ቢኖር ኢየሱስ ኮይኔ ግሪክ፣ አረማክና እብራይስጥ ይናገር እንደነበር ነው፡፡

የእጅ ጽሑፎች

በአሁ ወቅት የየትኛውንም ሃይማኖት ኦሪጅናል ጽሑፍ ያገኘ ሰው የለም፡፡ የቁርአን አል ከሪም ኦሪጅናል ጽሑፍ ኮፒ የለንም፡፡ የኡሥማን ቅጂም ቢሆን የለንም፡፡

እንደዚሁም የተውራት፣ ዘቡርና ኢንጂል ኦሪጅናል ጽሑፎች በእጃችን አይገኙም፡፡ ነገር ግን ኮፒ በማድረግ ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላለፍናቸው ኮፒዎች አሉን፡፡

ሊቃውንት ኢንጂል ለሰው ልጆች ብርሃን እንዲሆን የተላከ የፈጣሪ ቃል በመሆኑ በእጅ በመገልበጥ ሲጽፉ በታላቅ ጥንቃቄ ነበር፡፡

(ራዕይ 22፡18-19)

በኢንጂል ውስጥ ለሚገኙት ክስተቶች የዐይን ምስክሮች

የኢየሱስን ልደት፣ ሞትና ትንሣኤ የተመለከቱ የዐይን መስክሮች ባሉበት ሁኔታ የኢየሱስን አስተምህሮም ሆነ ባሕርይ በተሳሳተ መንገድ ማቅረብ ተቀባይነትን ሊያገኝ አይችልም፡፡ እነዚህ ሰዎች እውነቱን ያውቃሉ፡፡

(ሉቃስ 1፡1-3)

(2ጴጥሮስ 1፡16)

እነዚህ የዐይን ምስክሮች የተመለከቱትን ነገር በትክክል ስለመዘገባቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን፡፡ እነርሱ የጻፉት በጥርጣሬ ሊታይ አይችልም፤ ተሳስተው ቢሆን ኖሮ ክስተቶቹን የተመለከቱ ሌሎች ሰዎች ባረሟቸው ነበር፡፡

በተመሳሳይ፤ የክርስቶስ ተከታዮች ከመጀመርያው ጀምሮ ቃሉን በተሳሳተ መንገድ ጽፈውት ቢሆን ኖሮ ኢንጂልና ክርስትና  ገና ከጅምሩ ባልኖሩም ነበር፡፡

ፈጣሪ ኢንጂልን እንደላከ የምናምን ከሆነ፤ አስቀድሞ በትክክል እንዲጻፍና እንዲገለበጥ ማረጋገጡንም ማመን ያስፈልገናል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ሰዎች በውስጡ በተጻፈው ነገር ሊፈረድባቸው ባልቻለም ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ፍርድ ትክክለኛና ፍትሃዊ ይሆን ዘንድ የእርሱ መገለጥ ትክክለኛና ከስህተት የጸዳ ሊሆን ይገባዋል፡፡

በዐይን ምስክሮች ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን ለመበረዝ የሚያስችል ሁኔታ አልነበረም ምክንያቱም የዐይን ምስክሮች በሕይወት ነበሩና፡፡ በሕይወት የነበሩና ታሪኩን የሚያውቁ ሰዎች – አማኞች ቢሆኑም ባይሆኑም – በታሪኩ ላይ የተደረገ ለውጥ ቢኖር ኖሮ በተቃወሙ ነበር፡፡

ለምሳሌ ያህል ጆን ኤፍ ኬኔዲ እንዳልተገደለ ወይንም ማርቲን ሉተር ኪንክ “ህልም አለኝ” የሚለውን ታዋቂ ንግግሩን አለማድረጉን ወይንም የአሜሪካ ጠፈርተኞች ጨረቃን አለመርገጣቸውን ብጽፍ፤ ሰዎች የተሳሳተ ታሪክ መጻፌን በመግለፅ ይቃወማሉ፡፡

የጆን ኤፍ ኬኔዲን መገደል የተመለከቱ፣ የኪንግን ንግግር የሰሙ እንዲሁም ጨረቃን የረገጡት ምስክሮች አሁንም ድረስ አሉ፡፡ ከ50 እስከ 100 ዓመታት ባሉት መካከል ሰዎች መጽሐፌን ሊገዙ ይችላሉ ነገር ግን የዐይን ምስክሮች በሕይወት እስካሉ ድረስ ዋና ዋና ታሪካዊ ክስተቶችን መካድም ሆነ መፍጠር አይቻለኝም፡፡

በኢንጂል ውስጥ የሚገኙትም ዋና ዋና ክስተቶች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በዐይን ምስክሮች ዘመን ታሪካዊ ክስተቶችን አጨቃጫቂ ሊያደርግ የሚችል የለም፡፡

የዐይን ምስክሮች በሕይወት ኖረው የአዲስኪዳንን ተዓማኒነት ከመመስከራቸውም በተጨማሪ ሌሎች ሁለት እውነታዎች የአዲስ ኪዳንን ተዓማኒነት ያረጋግጣሉ፡፡ እነርሱም ሰማዕታትና የክርስቶስ ትንሣኤ ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡

1.                           ራሱ ለፈጠረው ውሸት ሰማዕት የሚሆን የለም

ብዙ ጊዜ ሰዎች ለግል ጥቅም ሲሉ ወይንም አሳፋሪ ገጠመኞቻቸውን ለመደበቅ ሲሉ ሊዋሹ ይችላሉ፡፡ የነቢዩ ኢየሱስ ብዙ ተከታዮች ኢየሱስ ከሞት የተነሣ መሲሁ መሆኑን በመመስከር ሰማዕታት ሆነዋል፡፡

2.                           ኢየሱስ በመቃብር ውስጥ መቅረቱን የሚያመለክት ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም

ክርስቶስን ይቃወሙት የነበሩት የዓይን ምስክሮች ትንሣኤውን ውድቅ ለማድረግ የኢየሱስን አስክሬን ከመቃብሩ በማውጣት ማሳየት ይችሉ ነበር፡፡ ማድረግ ቢችሉ ኖሮ ያንን ማድረጋቸው ግድ ነበር!

የኢንጂል ሁኔታ ይህንን ይመስላል፡፡ የዓይን ምስክሮች ደረጃ ከኢየሱ ልደት አንስቶ 100 ዓ.ም. ላይ ይጠናቀቃል፡፡ የኢየሱን ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ የተመለከተ የዐይን ምስክር ከ100 ዓ.ም. በኋላ ሊኖር አይችልም፡፡ የዓይን ምስክሮች ማሕበረሰብ የኢየሱስ ተከታዮች ሆኑም አልሆኑም በ100 ዓ.ም. ላይ ሞተው አልቀዋል፡፡

የመጨረሻው የዐይን ምስክ 100 ዓ.ም. አካባቢ ከሞተ በኋላ የፈጣሪን ቃል የመለወጥ የመጀመርያው አጋጣሚ ይፈጠር ነበር፡፡ አንድ ከሃዲ የፈጣሪን ቃል መለወጥ ቢፈልግ ዕድል ያገኛል፡፡

ለ. የስደት ደረጃ (100 ዓ.ም. – 325 ዓ.ም.)

በዚህ ደረጃ ክርስቲያኖች በየቦታው ይሰደዱ ነበር፡፡ የአይሁድ መሪዎች በየቦታው ጥቃት ይፈፅሙባቸውና ይገድሏቸው ነበር፡፡ ሮማውያ በመድብለ አማልክቶቻቸው ስለማያምኑ እንደ አምላክ የለሾች ይቆጥሯቸው ነበር፡፡ ሮማውያን እንደ ስጋት ይቆጥሯቸው ስለነበር በየቦታው እንገደሉና ከነመጻሕፍታቸው እንዲቃጠሉ አዘዙ፡፡

በዚህ የስደት ዘመን ለውጦች በኢንጂል ላይ መፈፀማቸው የማይሆን ነበር፡፡ በዚህ ወቅት የአዲስ ኪዳንን ተዓማኒነት የሚያረጋጡት አራቱ ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፡-

  1. የእጅ ጽሑፎች
  2. በአበው ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሱት ጥቅሶች
  3. ቀዳሚያን ትርጉሞች
  4. የቤተክርስቲያን አበው

እያንዳንዱን ማስረጃ አንድ በአንድ እንመልከት

1.                            የእጅ ጽሑፎች

የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በፓፒረስ ላይ በእጅ ይገለበጡ ነበር፡፡ ፓፒረስ በምድረ ግብፅ የሚበቅል እፅዋት ነበር፡፡ ግብፃውያን ወረቀትን ከፓፒሪ በፈጠሩ ጊዜ ሒሮግሊፊክስ ለመጻፍ የተለያዩ ቀለማት ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር፡፡

አጭር ታሪክ

ፎኒሻኖች የግብፃውያንን ግኝት በመቅዳት ፊደላትን ተጠቅመው በመጻሕፍት መልክ ዕውቀትን ለሌላው ዓለም ያሸጋግሩ ነበር፡፡ ቀዳሚያን ክርስቲያኖች የእጅ ጽሑፎች ሲያረጁ ወይንም አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ሲመሠረቱ ኢንጂልን በእጅ ይገለብጡ ነበር፡፡ የመጨረሻው ደቀ መዝሙር ወደ ፍጥሞ ደሴት በግዞት ተወስዶ ከሞተ በኋላ ክርስቲያኖች የኢንጂልን ጽሑፎች በታደሰ ስሜት በመገልበጥ ለአብያተ ክርስቲያናት ያሰራጩ ነበር፡፡

የክርስቲያን ማሕበረሰብ አብዛኞቹ አባላት አጠቃላዩን አዲስ ኪዳን ኮፒ የማዘጋጀት አቅም አልነበራቸውም፡፡ ከዚህ የተነሳ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ገሚስ ቅጂዎች በመዘጋጀት ይሰራጩና ክርስቲያኖች ይቀባበሏቸው ነበር፡፡

ሌሎች የገሚስ የእጅ ጽሑፎች ዓይነቶች በክርስቲያኖች ቤቶችና በአብያተ ክርስቲያናት ፍርስራሾች ውስጥ የተገኙት ናቸው፡፡  እነዚህ ገሚስ ቅጂዎች የተገመሱት በዕድሜ ወይንም በአደጋ ምክንያት እንጂ መጀመርያ እንደርሱ ስለነበሩ አይደለም፡፡

ከ100 – 325 ዓ.ም. መካከል የሚገኙት ገሚስ ቅጂዎች አጠቃላይ የኢንጂል መጻሕፍት፣ የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ዘገባዎች፣ የኢየሱስ ልዩ መሆን ዘገባዎችና የቤዛነት ሞቱን የሚገልፁ ናቸው፡፡

2.                           የቤተክርስቲያን ጥቅሶች (ሌክሽነሪዎች)

የቤተክርስቲያን ሌክሽነሪዎች መገኘት የአዲስ ኪዳንን ተዓማኒነት ከሚያረጋግጡ ታላላቅ ማስረጃዎች መካከል አንዱ ቢሆንም ጥልቅ ጥናቶች ካልተደረጉባቸው ጉዳዮችና በአነስተኛ ሁታ ጥቅም ላይ ከዋሉት ሙግቶች መካከል አንዱ ነው፡፡

ሌክሽነሪዎች ለቤተክርስቲያን ዓመት እያንዳንዱ ቀን የተመደቡትን ጥቅሶች የያዙ ጽሑፎች ናቸው፡፡ ከዚህ የተነሳ ለአጥብያ አብያተ ክርስቲያናት በጣም ወሳኝ ነበሩ፡፡

ብዙ ክርስቲያኖች የኢንጂል የግል ኮፒ ስላልነበራቸው በእግዚአብሔር ቃል ዕውቀት ለማደግ እነዚህን የአገልግሎት መጻሕፍት ይጠቀሙ ነበር፡፡

አሁን የሚወቁት ሌክሽነሪዎች ኮፒ 2,300 ያህል ሆኗል፡፡ በተጨማሪም 3,200 የሚሆኑ ተከታታይነት ያላቸው ሌክሽሪዎች በመገኘት በዚያን ዘመን አዲስ ኪዳን በስፋት ስለመነበቡና በታማኝነት ስለመተላለፉ ምስክር ሆነዋል፡፡

3.                           ቀዳሚያን ትርጉሞች

የአዲስ ኪዳንን ተዓማነት ለማረጋገጥ ወደ ሜድትራንያን ቋንቋዎች የተተረጎሙ የተሟሉ የአዲስ ኪዳን ትርጉሞች ወሳኝ ናቸው፡፡ ከነዚህ መካከል አንዱ ፔሺታ በመባል የሚታወቀው የአዲስ ኪዳን የሢርያክ ትርጉም ይገኝበታል፡፡ እንዲህ ያሉ ትርጉሞች የግሪክን ኦሪጅናል ጽሑፍ ይዘት ትክክለኛነት ለመገምገም እንደገና ወደ ግሪክ ሊተረጎሙ ይችላሉ፡፡

4.                           የቤተክርስቲያን አበው

የክርስቶስ ሐዋርያት ተከታዮች የነበረው የክርስቲያን ማሕበረሰብ መሪዎች የቤተክርስቲያን አበው በመባል ይታወቃሉ፡፡ የሁለተኛው ትውልድ ደቀ መዛሙርት ብላችሁ ልትጠሯቸውም ትችላላችሁ፡፡

በአሳቃቂ ስደት ውስጥ በማለፍ ማሕበረሰቦቻቸውን በክርስቶስ ባለው እምነት መምራት ችለዋል፡፡ በሜድትራንያን ባሕር የተለያዩ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ ቢሆንም የተለያዩ ደብዳቤዎችንና ስብከቶችን በመጻጻፍ እርስ በርሳቸው ይገናኙ ነበር፡፡ የእነርሱ ጽሑፎች ከቀዳሚው የተሟላ የአዲስ ኪዳን ጽሑፍ (ኮዴክስ ሲናይቲከስ) ጋር ለማነፃፀርና ለማጥናት እንችል ዘንድ ዛሬም ድረስ ተጠብቀውልናል፡፡

በእነዚህ ደብዳቤዎችና ስብከቶች ውስጥ የተጠቀሱት ጥቅሶች ከዛሬው ጽሑፍ ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማሉ፡፡

ሐ. የትርጉም ደረጃ (ከ325 ዓ.ም. እስከ አሁን)

ክርስና በአውሮፓና በኢስያ ውስጥ እየተስፋፋ ሲመጣ ኢንጂል በተዓማኒነት ይተረጎም ነበር፡፡ ኢንጂል በሌሎች ቋንቋዎች ሲዘጋጅ ተርጓሚዎቹ ከዋናዎቹ የእጅ ጽሑፎች ጋር ያላቸውን ስምምነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር፡፡

ሁሉም ቅጂዎች ወይንም የሌሎች ቋንቋዎች ትርጉሞች ከተከታዮቹ ቀዳሚያን ትርጉሞች ላይ የተዘጋጁ ናቸው፡-

  1. ኮዴክስ ሲናይቲከስ
  2. ኮዴክስ ቫቲካነስ
  3. ኮዴክስ አሌክሳንድሪነስ

ቅጂዎች

አንዳንዶች እንደሚናገሩት ብዙ የሆኑት የኢንጂል ቅጂዎች ለብረዛ አጋልጠውታል፡፡ ቅጂ ማለት ትርጉም ማለት ነው፡፡ ታዋቂ የሆኑት ሙስሊም ተከራካሪዎች የኢንጂል ቅጂ ማለት የአንድ ታሪክ የተለየ ቅጂ ማለት እንደሆነ ሲናገሩ የቋንቋ እጥረት እንዳለባቸው እያሳዩ ነው፡፡

አንዳንድ በክርስትና መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የጠለቀ ዕውቀት እንዳላቸው የሚናገሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ቋንቋዎች የሆኑት የግሪክና የእብራይስጥ ቋንቋ መሠረታዊ ዕውቀት እንኳ የሌላቸው ናቸው፡፡

አንድ በአረብኛ ምንም ሥልጠና የሌለው ሰው የቁርአን ሊቅ እንደሆነ ቢናገር ቂልነት እንደሚሆን ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስም ሊቅ ለመሆን ቋንቋዎቹን (እብራይስጥና ኮይኔ ግሪክ) ማጥናት አስፈላጊ ነው፡፡

ታሪክ ይናገራል

ታሪክ ምን ይነግረናል? ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ አንስቶ እስከዚህ ዘመን ድረስ የሚገኘውን የክርስትና ታሪክ ስንመለከት የእግዚአብሔርን ቅዱስ ቃል ለመጠበቅ ያልተቋረጠ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉን እንመለከታለን፡፡

ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን የዐይን ምስክሮች ዘገባዎች አንስቶ ስደተኛ በሆኑት ክርስቲያኖች መካከል እስከተላኩት ደብዳቤዎች ድረስ፤ ከዚያም ቀጥሎ ከ325 ዓ.ም. ጀምረው የሚገኙት ትርጉሞች መልእክት እያስተላለፉልን ነው፡፡ የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ የተጻፉትን የኢየሱስ መልእክቶች በታማኝነት እያስተላለፉን ነው፡፡

“ኢየሱስም የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ አለ” (ማርቆስ 4፡9)

ምዕራፍ 7

የዚህ ሁሉ ትርጉም ምንድነው?

በዚህ ጥናት ኢንጂል ተበርዟል የሚለውን የጓደኞቼን መሠረት የለሽ ሐሳብ ለመረዳት ሞክሬያለሁ፡፡ ያገኘሁት ነገር ኢንጂል በፈጣሪ ተጠብቆ መቆየቱን ብቻ ሳይሆን እንዳምነውና ሕይወቴን በእርሱ ላይ እንድመሠርት አድርጎኛል፡፡

ዛሬ የሚገኙት ኁልቁ መሣፍርት የሌላቸው ማስረጃዎች ለኛ ከመናገር አልፈው እየጮኹ ነው! ማስረጃዎቹ የኢንጂልን እውነተኛነትና ንፅህና ያረጋግጣሉ፡፡ ዛሬ በእጃችን የያዝነው መጽሐፍ በኢየሱስ ተከታዮች ሲታመን የነበረው ያው ታሪክ ነው፡፡ በዚያ እምነት በመፅናት ኖረው ሞተዋል፡፡

ከአመክንዮ አንፃር አንድ ሰው እንጂል ተበርዟል ከማለቱ  በፊት ወሳኝ ጥያቄዎችን መመለስ እንደሚገባው ተመልክተናል፡-

  • ኢንጂል መች ነበር የተበረዘው?
  • ማነው እንዲህ ያለ ተግባር የሚፈፅመው?
  • አንድ ሰው ኢንጂልን እንዲለውጥ ምን ያነሳሳዋል?

በተጓደኝ፣ ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው እምነታቸው የውሸት መሆኑን እያወቁ ለውሸት ይሞታሉ ማለት የማይታሰብ ነው፡፡

ኢንጂል እንደረተበረዘ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች ስለ መነሻውና መልእክቱ ያላቸው ግንዛቤ የተሳሳተ ነው፡፡ ብሒላቸው በጥናትም ሆነ በአምክንዮአዊ ማስረጃ የተደገፈ አይደለም፡፡ ካለማወቃቸው የተነሳ ብዙዎችን ከእውነተኛ መንገድ ወደተሳሳተ መንገድ መርተዋል፡፡ ለፈጣሪ እንከራከራለን በሚል መነሻ ቃሉ የሆነውን ኢንጂልን መጠበቅ መቻሉን በመካድ ተገቢውን ክብር ነፍገውታል!

በመጨረሻም ቃሉን ጠባቂና ፍትሃዊ የሆነውን ሃያሉን ፈጣሪ ማመን ይቻል ዘንድ ይህ ፈጣሪያችን ቃሉ የሆነውን ኢየሱስን እንደላከልን ማመን ግድ ይላል፡፡ ለሰው ልጆች መመርያ ብርሃን ይሆን ዘንድ (ሊሁዳ አል-ዓለሚን) ኢንጂል በፈጣሪያችን እንደተጠበቀ ማመን አስፈላጊ ነው፡፡

ሃያሉ ፈጣሪ ይህንን ጥናት ተጠቅሞ በእርሱና ቤዛችን በሆነው በመሲሁ ኢየሱስ ማመን እችል ዘንድ ረድቶኛል፡፡ ዛሬ ተከታዩን ጸሎት በመጸለይ ወደ ኢየሱስ ቤተሰብ ትቀላቀሉ ዘንድ እጋብዛችኋለሁ፡፡ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ መኖር ትችሉ ዘንድ ኃይልን ይሰጣችኋል፡፡

ጸሎት በየትኛውም ቦታ ሆናችሁ ከሃያሉ ፈጣሪያችሁ ጋር የምትነጋገሩበት መንገድ ነው፡፡

ሁሉን ቻዩ አምላኬ ሆይ፣ አንተ ምሕረትን የተሞላህ አምላክ ነህ፡፡ ከኃጢአቴና ራስን ከማፅደቅ አመለካከቴ ንስሐ እገባለሁ፡፡ ባንተና ቃልህ በሆነው በመሲሁ ኢየሱስ አምናለሁ፡፡ እስከ መጨረሻዋ እስትነፋሴ ድረስ ያንተን ትምህርት ለመከተል ቃል እገባለሁ፡፡

አሜን፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ