በእጃችን የሚገኙት ብሉይና አዲስ ኪዳናት በሙሐመድ ዘመን በአይሁዶችና በክርስቲያኖች እጅ ነበሩ፤ ቁርኣንም ይመሰክርላቸዋል

በእጃችን የሚገኙት ብሉይና አዲስ ኪዳናት በሙሐመድ ዘመን በአይሁዶችና በክርስቲያኖች እጅ ነበሩ፤ ቁርኣንም ይመሰክርላቸዋል

ይህ ጽሑፍ ميزان الحق ሚዛኑል ሃቅ (የእውነት ሚዛን) በሚል ርዕስ ሲ.ጂ ፋንደር በተሰኙ ሊቅ ከ100 ዓመታት በፊት ከተጻፈ መጽሐፍ ላይ የተተረጎመ ነው፡፡

በዚህ ምዕራፍ ዓላማችን በአይሁዶችና በክርስቲያኖች እጅ የሚገኙት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትና አሁን በክርስቲያኖች እጅ የሚገኙት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በሙሐመድ ዘመን የነበሩት መሆናቸውን፤ በምን ያህል መጠን የተበረዙ (محرّقة) ወይንም የተለወጡ ስለመሆናቸው የሚያትተውን ጥያቄ መመልከት ነው፡፡ ማስረጃውን ከመመርመራችን በፊት በሙስሊም ሀገራት የሚገኙት ያልተማሩ ሰዎች ትክክል ናቸው እንበልና እናስብ፡፡ ስለዚህም (1) አሁን ያሉት ቅዱሳት መጻሕፍት በሙሐመድ ዘመን የነበሩት አይደሉም፣ ወይንም ደግሞ (2) ሊነበቡ እስከማይችሉ ድረስ ተበርዘዋል፡፡ ይህ እውነት ከሆነ የሰው ልጆች እጣ ፈንታ እጅግ አስከፊ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ ፈቃዱ ሁሉ የእግዚአብሔርም ቃል (كلام الله) እንደማይለወጥ ለአዕምሯችን ግልጽ ነውና፡፡ ያ ቃል ደግሞ ቁርኣን ራሱ እንደሚያስተምረው በነቢያት ተነግሯል፤ ሙስሊሞችም ደግሞ እንዲያምኑበት ታዘዋል (ሱራ 2፡130፣ 3፡78)፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ቃል ግን ከሰዎች መካከል ሙሉ በሙሉ ደብዛው የጠፋ ከሆነ ወይንም ደግሞ ተኣማኒነቱን ሙሉ በሙሉ እስኪያጣ ድረስ የተበረዘ ከሆነ የሰው ልጆች ሁሉ ምንኛ በሰቆቃ ውስጥ ገብተዋል! ቁርኣንም ደግሞ የርሱ ጠባቂ مُهَيْمِن የመሆኑ ተልዕኮ ምንኛ ከሽፏል! ስለዚህ የቁርኣን ባሕርይ ምንድነው? እነርሱ እንደሚያምኑት በእግዚአብሔር የተሰጠውን ተልዕኮ መወጣት የማይችል ከሆነ ሙስሊሞችም ደግሞ ሊያምኑት የሚችሉት እንዴት ነው?

ነገር ግን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁንና የእግዚአብሔር ቃል አልጠፋም ወይንም ደግሞ አልተበረዘም፡፡ እግዚአብሔር ጠባቂው ነውና፡፡ እውነት ፈላጊ የሆነውን ሙስሊም መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ማወቅ ይችል ዘንድ ቁርኣን እንኳ ያግዘዋል፡፡

እኛ ክርስቲያኖች ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ቁርኣን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገራቸውን ነገሮች ስለምንቀበል መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰነዘር የትኛውም ጥቃት እርሱን “በሚያረጋግጠው”ና “በሚጠብቀው” በቁርኣን ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በመሆኑ የገዛ ራሳቸውን ክቡር መጽሐፍ የሚጎዳ መሆኑን ካላስተዋሉ ከአንዳንድ ሙስሊሞች ቁርኣንን ጭምር እንከላከላለን፡፡ ለምሳሌ ያህል የዴልሂ ነዋሪ የሆኑት ሼክ ሐጂ ራህመቱሏህ በ1270 ዓ.ስ. (ዓመተ ስደት) በታተመው ኢስሐሩል ሃቅ (إظهار الْحقّ) በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ የዴልሂ ዑላማዎች እንዲህ የሚል ፋቱዋ እንዳወጡ ይናገራሉ፡- “አሁን አዲስ ኪዳን በመባል የሚታወቀው የመጽሐፍቶች ስብስብ በእኛ ዘንድ ተቀባይነት የለውም፤ ይህም በቁርኣን ውስጥ የተጠቀሰው ኢንጂል አይደለም ነገር ግን ከዚህ በተጻራሪ በኛ አመለካከት መሠረት ኢንጂል የሚለው ቃል በኢየሱስ ላይ የወረደውን ያመለክታል፡፡” ራህመቱሏህ ራሳቸው አሉታዊ ከሆነ ግንዛቤያቸው የተነሳ በተመሳሳይ ስህተት ውስጥ ገብተዋል፣ እንዲህ ይላሉና፡- “ኦሪጅናል ቶራህ እንዲሁም ኦሪጅናል ኢንጂል ከሙሐመድ ተልዕኮ በፊት ጠፍተዋል፤ አሁን ተርፈው ያሉት እውነተኛና ሐሰተኛ ዘገባን ከያዙ ከሁለት እርስ በርሳቸው ከተቆራኙ መጽሐፍት የተገኙ በመሆናቸው እስከ ነቢዩ መምጫ ጊዜ ድረስ በትክክለኛ ይዘታቸው ነበሩ ነገር ግን ከዚያ በኋላ ሐሰት (التّحريف) ተቀላቀለባቸው አንልም፡፡” በየትኛውም መንገድ እኝህ ጸሐፊ ስለ “ኦሪጅናል ቶራህ” ሲናገሩ ስለ ኦሪጅናል የእጅ ጽሑፍ እየተናገሩ አይደለም ምክንያቱም የቁርኣን የመጀመርያ የእጅ ጽሑፎች በተመሳሳይ ሁኔታ ጠፍተዋልና፡፡ ያለ ጥርጥር እየተናገሩ ያሉት ስለ እጅ ጽሑፎቹ እውነተኛና ትክክለኛ ይዘት ነው፡፡ ሆኖም ግን ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ በኛ ዘመን በሕንድ ውስጥ የሚገኙ የተማሩ ሙስሊሞች ሁላቸውም ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ እንደሚቀበሉት የሳቸው ንግግር ስህተት ነው፡፡ በጥንት ዘመን በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙርያ የነበረውን አለማወቅና ስህተት ቀለል አድርጎ ለማየት በተወሰነ ደረጃ ምክንያት ነበረ፤ አሁን ግን ምንም አይነት ምክንያት የለም፡፡

ራህመቱሏህ ቤተ መቅደሱ በ587 ቅ.ክ. በናቡ ከደነፆር በወደመ ጊዜ ቶራህ ሙሉ በሙሉ መጥፋቱን መሃይማን እንዲያምኑ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህንንም ለማረጋገጥ አንደንዶች ሁለተኛ ዕዝራ በሌሎች ደግሞ አራተኛ ዕዝራ ተብሎ የተሰየመውን የተጭበረበረ መጽሐፍ በመጥቀስ ዕዝራ (عُزيَر) የፈጠራ መጽሐፍ በመጻፍ እውነተኛና ትክክለኛ የሙሴ መጽሐፍ መሆኑን እንደተናገረ ሙስሊሞች እንዲያምኑ ጥረዋል፡፡ ነገር ግን ሼኹ ወደጠቀሱት ረብ የለሽ ወደሆነው መጽሐፍ ሄደን ስንመለከት የሼኹን አባባል የሚደግፍ ምንም ነገር አናገኝም፡፡ ከዚህ በተጻራሪ ግን መጽሐፉ የሚነግረን (ም. 15, 21, 22) ዕዝራ ጸሐፊውን እንዲህ ብሎ እንዲጽፍ እንዳዘዘው ነው፡- “በሕግህ ውስጥ የተጻፈው ከመጀመርያው ጀምሮ በዓለም ውስጥ የተደረገው ሁሉ…”፤ ይህ ማለት በዚህ ዘገባ መሠረት ዕዝራ የቶራህ ሐፊዝ (በቃሉ የሸመደደ) እንደነበረና ለጸሐፊው ቶራን በቃሉ ሲያነብለት ሐሰተኛ የሆነ መገለጥ ፈጥሮ እየተናገረ አልነበረም፡፡ ባይዛዊ በሱራ 9፡30 ላይ ሲያትት ሙሉ በሙሉ ተአማኒነት የሌለው ቢሆንም ነገር ግን ይህንን ማብራርያ የሚደግፍና የሼክ ራህመቱሏን የሚቃረን አፈ ታሪክ ያቀርባል፡፡ ባይዘዊ እንደሚለው አይሁዶች “ከናቡ ከደነፆር ጭፍጨፋ የተነሳ ቶራን የሚያውቅ አንድም ሰው በመካከላቸው አልቀረም ነበር ነገር ግን እርሱ (ዕዝራ) እግዚአብሔር ከ100 ዓመታት በኋላ ወደ ሞር ሲመልሰው ቶራን በቃሉ አነበበላቸው (املى) እነርሱም በርሱ ተደነቁ፡፡” በዚያ ሁኔታ መደነቃቸው አያስገርምም ነገር ግን አንድ ሰው ይህንን አፈ ታሪክ ማመኑ ያስገርማል፡፡ ሁለተኛ (ወይንም አራተኛ) ዕዝራ ራሱ እንደዚህ ተዓማኒነት የሌለው ምንም ነገር አይነግረንም፡፡ ነገር ግን መጽሐፉም ሆነ ባይዛዊ ዕዝራ የተጭበረበረ ቶራህ ደራሲ ሳይሆን ሐፊዝ መሆኑን ይነግሩናል፡፡ በሁለተኛ ዕዝራ ውስጥ የተጻፈው አፈ ታሪክ እውነት ከሆነ በቃላቸው የሸመደዱትና ለሌሎች የሚያስጠኑ ሰዎች ስላሉ ቁርኣን ሁሉም ኮፒዎቹ ቢቃጠሉ ሊጠፋ እንደማይችል ሁሉ ዕዝራ በቃሉ ስለሚያውቀውና ለሌሎች ስላነበበላቸው ቶራም ሊጠፋ አይችልም፡፡ ሼኽ ራህመቱሏህ እንዳሰቡት ይህ የቶራን መውደም አያረጋግጥም፡፡ ነገር ግን ማንም ምሁር ሁለተኛ (ወይንም አራተኛ) ዕዝራን እንደማይቀበል መጥቀስ አስፈላጊ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም ቀደምት ክፍሎቹ በ81ና 96 ዓ.ም. መካከል የተጻፈ ሲሆን ኋለኛ ክፍሎቹ ደግሞ ቢያንስ ከ263 ዓ.ም. በኋላ ነው፡፡ ዕዝራ ግን የኖረው አምስተኛው ክ.ዘ. ቅ.ክ. ነበር፡፡ (2ዕዝራ 2፡47፣ 7፡28-29ና የመሳሰሉት የሚያመለክቱት መጽሐፉ የተጻፈው ከክርስቶስ ልደት በፊት ሳይሆን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነው፡፡) መጽሐፉ በአይሁዶች ተቀባይነትን አላገኘም፡፡ በሦስተኛው የክርስቲያኖች ክፍለ ዘመን አንዳንድ እብራይስጥን የማያውቁ ሰዎች በቀላሉ የሚታለሉ ሞኞች ቢሆኑም አይሁዶች በመጽሐፉ ውስጥ የተጻፉትን አፈታሪኮች ተቀባይነት በመንፈግ ረገድ ከሌሎች ምሁራን ጋር ይስማማሉ፡፡ እንግዲህ አሁን ቶራህና ሌሎች የአይሁድ ጥንታውያን ቅዱሳት መጻሕፍት በናቡ ከደነፆር ዘመን እንዳልወደሙ ማሳየት ይገባናል፡፡ መቅደሱ በባቢሎናውያን ከወደመ ከ100 ዓመታት በኋላ እንኳ በዕዝራ ዘመን እንደነበረ ማሳየት ከቻልን ይህ ግልፅ ሆናል፡፡ ማስረጃ ማምጣት አስቸጋሪ አደለም ምክንቱም በአይሁዶችና በክርስቲያኖች ቀኖና ውስጥ በሚገኘው በትክክለኛው የዕዝራ መጽሐፍ ውስጥ ዕዝራ “በሙሴ ሕግ ፈጣን ጸሐፊ ነበረ” (ዕዝራ 7፡6 ከነህምያ 8 ጋር ያነጻጽሩ) እንዲሁም ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሰ ጊዜ የእግዚአብሔር ህግ (ቶራህ) በዕዝራ እጅ ነበር (ዕዝ 7፡14)፡፡ ስለዚህ ቶራህ በናቡከደነፆር ዘመን እንዳልወደመ ግልጽ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ ምስክርነት በቂ ነው ነገር ግን ብቸኛው አይደለም፡፡ በሁለተኛው የክርስቲያን ክፍለ ዘመን እንደተጻፈ በሚነገርለት ፒርኬ አብሆሳ (بِرقَىْ آبهَوْت) በሚል ርዕስ በተጻፈ የእብራይስጥ ጽሑፍ ውስጥ እንዲህ ይላል፡ “ሙሴ[1] ቶራን ከሲና ተቀበሎ ለኢያሱ አስተላለፈ፣ ኢያሱ ደግሞ ለሽማግሌዎች፣[2] ሽማግሌዎች ደግሞ ለነቢያት፣ ነቢያት ደግሞ ለታላቁ የምኩራብ ሰዎች አስተላለፉት፡፡” ታላቁ ምኩራብ የተባለው በዕዝራ የተደራጀ የምሁራን ስብስብ እንደነበር ይነገራል፡፡ ዋና ተልዕኳቸውም ቶራን መጠበቅና ማስተማር ነበር፡፡ ታልሙድ ስለ እነርሱ እንደሚናገረው ከባቢሎን ምርኮ በኋላ “የታላቁ ምኩራብ ሰዎች የከበረውን (ቶራን) ወደ ተገቢ ቦታ ው መልሰውታል፡፡” ከዚሁ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ፒርኬ አብሆት[3] እንዲህ ይላል፡ “ሦስት ነገሮችን ይናገሩ ነበር፡ ‹ፍርድ በምትሰጡበት ሰዓት ተጠንቀቁ፣ በተቻላችሁ መጠን ብዙ ደቀ መዛሙርት ይኑራችሁ እንዲሁም ለቶራህ አጥር ስሩ፡፡›” ይህ የመጨረሻው አባባል የሚያመለክተው ቶራን ከምንም ዓይነት ችግር ወይንም ብረዛ መጠበቅን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚደረገው በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው፡፡ አይሁዶች ያደረጉትን ያህል ጥንቃቄ ለቅዱስ መጽሐፉ ያደረገ ሕዝብ በዓለም ላይ አይገኝም፡፡ በቶራህ ውስጥ ያሉትን ቃላትና ፊደላት ብዛት እንኳ መዝግበው አስቀምጠዋል፡፡ ቀደም ሲል በጠቀስንው ፒርኬ አብሆት ውስጥ የሚገኝ አንድ ምንባብ አይሁዶች ለቶራህ የሰጡት ቦታ ምን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ ይናገራል፡፡ እንዲህ ይላል፡- “ጻድቁ ስምዖን[4] ከታላቁ ምኩራብ ትሩፋን መካከል አንዱ ነበር፡፡ እንዲህ በማለት ይናገር ነበር ‹ዓለም ጸንታ የቆመችው በሦስት ነገሮች ላይ ነው – ቶራህ፣ አምልኮና መልካም ሥራ ናቸው›፡፡” አይሁድ ቶራን በኦሪጅናል እብራይስጥና አረማይክ ከትውልድ ወደ ትውልድ በትልቅ ጥንቃቄና አክብሮት አስተላልፈዋል፡፡

ለዚህ አንዱ ማረጋገጫ በተለያዩ የብሉይ ኪዳን ክፍሎች ውስጥ የዘይቤ ልዩነቶች መታየታቸው ነው፡፡ ይህም ደግም የሚያመለክተው የአንድ ሰውና የአንድ ዘመን ሥራ አለመሆኑን ነው፡፡ በተጨማሪም ተመሳሳይ ታሪክ ባላቸው ተለያዩ ምንባቦች መካከልና ብዙም መንፈሳዊ ጠቀሜታ በሌላቸው አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግልጽ ግጭት የሚመስሉ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ግጭት ያልሆኑ ነገሮች ይታያሉ፡፡ ይህ የሚያመለክተው አይሁዶች እነዚህን ግጭት የሚመስሉ ነገሮችን ለማስወገድ ምንባቡን የመቀየር ምንም ዓይነት ሙከራ አለማድረጋቸውን ነው፡፡ የዚህ ሐሳብ ጥንካሬ ከቁርኣን በተወሰደ ስዕላዊ መገለጫ ግልጽ ሊሆን ይችላል፡፡፡ ሱራ ዐሊ ዒምራን 3፡48 ላይ ፈጣሪ እንዲህ እንዳለ ተነግሮናል፡ “ዒሳ ሆይ! እኔ ወሳጂህ ወደ እኔም አንሺህ ነኝ፡፡ ከነዚያም ከካዱት ሰዎች አጥሪህ ነኝ እነዚያንም የተከተሉህን እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ ከነዚያ ከካዱት በላይ አድራጊ ነኝ፡፡” እንዲሁም በሱራ አል ኒሳ 4፡157 ላይ ስለ ዒሳ ሲናገር አንዲህ ይላል፡ “ከመጽሐፉም ሰዎች ከመሞቱ በፊት በእርሱ (በዒሳ) በእርግጥ የሚያምን እንጅ (አንድም) የለም፡፡ በትንሣኤም ቀን በነሱ ላይ መስካሪ ይኾናል፡፡” ሁለተኛው ተውላጠ ስም ወደ ክርስቶስ ያመለክት እንደሆን አንዳንድ ጥርጣሬዎች አሉ ነገር ግን በሱራ 18 ላይ የርሱ ሞት በመጠቀሱ ላይ ምንም ዓይነት ጥርታሬ የለም፡፡ ሱራ መርየም ቁ. 34 ላይ እንዲህ እንዳለ ተነግሯል፡ “ሰላም በኔ ላይ ነው በተወለድኩ ቀን፣ በምሞትበትም ቀን እንደገና ሕው ሆኜ በምቀሰቀስበትም ቀን፡፡” ነገር ግን በ ሱራ 4፡156 ላይ አይሁዶች እርሱን መግደላቸውን ይክዳል፡ “አልገደሉትም አልሰቀሉትምም፡፡” በመጀመርያው ዕይታ አንባቢው በዚህ ቦታ ላይ ተቃርኖ መኖሩን በአዕምሮው ውስጥ ይስላል፡፡ በአንዱ ቦታ ላይ የክርስቶስን ሞት ሲናገር በሌላው ስፍራ ላይ ደግሞ የሚክድ ሊመስለው ይችላል፡፡ የዚህ ግልፅ ግጭት በቁርኣን ውስጥ መኖር ሙስሊሞች ምንባቡን እንዳልለወጡት ያሳያል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ግጭት የሚመስሉ ይዘቶችም እንደዚሁ ናቸው፡፡ መኖራቸው በራሱ ምንባቡን በመለወጥ እነርሱን “የማስታረቅ” ሥራ ላለመሰራቱ ማረጋገጫ ነው፡፡

አንዳንድ ሙስሊም ጸሐፍት ትክክለኛ ተቃርኖዎች በብሉ ኪዳን ውስጥ መኖራቸውን የሚናገሩ ረጃጅም ዝርዝሮችን ጽፈዋል፡፡ ተቃርኖዎቹ ልክ ከላይ የጠቀስናቸውን የቁርኣን ጥቅሶች የሚመሳስሉ ናቸው፡፡ በብዙ ሁኔታዎች ተቃርኖዎቹ ጥንቁቅ በሆኑ ተማሪዎች በቀላሉ የሚታረቁ ናቸው፡፡ በሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ ችግሮቹ የሚመነጩት የሆኔታዎቹን ሙሉ ምስል ካለማወቃችን የተነሳ ነው፡፡ ነገር ግን የነዚህ ግጭት መሰል ይዘቶች መኖር የሚያረጋግጠው ነገር ቢኖር አይሁዶች ለቅዱስ መጽሐፋቸው ካላቸው አክብሮት የተነሳ የእግዚአብሔርን እውነት ከማግኘት ይልቅ የራሳቸውን ከንቱ ጉብዝና ለማሳየት ለሚሹ ደካማና መጥሌ አስተሳሰብ ላላቸው ተቃዋሚዎች እንቅፋት የሚሆኑትን አሰናካይ ነገሮች ለማስወገድ ምንም ዓይነት ጥረት አለማድረጋቸውን ነው፡፡ የሰው ልጅ በእኩለ ቀን እንኳ ዐይኑን ጨፍኖ እግዚአብሔር የሰጠውን ብርሃን አለማየት ይችላል፡፡ በጨለማ ውስጥ ለመጓዝ የሚሻ ሰው ደግሞ በተሳሳተ ጎዳና ከመሄድ ሊከለክለው የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡

አሁን ያሉት ብሉይና አዲስ ኪዳናት በሙሐመድ ዘመን “በመጽሐፉ ሰዎች” እጅ የሚገኙትና ቁርኣን የሚመሰክርላቸው እንደሆኑ የሚያሳየውን ማረጋገጫችንን እስኪ እናቅርብ፡፡

የአይሁድ ቀኖናን የፈጠሩት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዝርዝር አሉን፡፡ እነዚህ ዝርዝሮች ከሙሐመድ ዘመን በእጅጉ የሚቀድሙ ሲሆኑ አሁን በእብራይስጥ ብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኙትን መጻሕፍት ሁሉ ይዟል፡፡

የአይሁድ ጸሐፌ ታሪክ የሆነው ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን[5] በ90 ዓ.ም. እንዲህ በማለት ጽፏል፡- “በኛ ዘንድ የተከፋፈሉና እርስ በርሳቸው የሚጋጩ መጻሕፍት የሉም ነገር ግን የሁሉንም ዘመናት ታሪክ የያዙና መለኮታዊ መሆናቸው በትክክል የታመነባቸው ሃያ ሁለት መጻሕፍት አሉ፡፡ ከነዚህ መካከል አምስቱ[6] የሙሴ ናቸው፡፡ ህግንንና እስከ ሞቱ ድረስ ያለውን የሰው ዘር ተያያዥ ታሪክ የያዙ ናቸው፡፡ ይህ ጊዜ 3,000 ዓመታት ለመሙላት ጥቂት ብቻ ይቀረዋል፡፡ ከሙሴ ሞት ጀምሮ እስከ ፋርስ ንጉሥ አርጤክስስ ድረስ ከሙሴ በኋላ የነበሩ ነቢያት በአስራ ሦስት[7] መጻሕፍት ውስጥ በነርሱ ዘመን የተፈጸመውን ጽፈዋል፡፡ የተቀሩት አራቱ[8] መጻሕፍት ዝማሬዎችንና ግብረ ገባዊ መመርያዎችን የያዙ ናቸው፡፡”

በ90 ዓ.ም. የተደረገው የጃምኒያ ጉባኤ ተመሳሳይ የሆነ ቀኖናን ያቀርባል፡፡ በ363 ዓ.ም. የተደረገው የሎዶቅያ ጉባኤም ሃያ ሁለት መጻሕፍት ብሉይ ኪዳንን እንደፈጠሩ ይጠቅሳል፡፡ በቅርብ ጊዜ ቀለል ለማድረግ ከነዚህ መጻሕፍት መካከል አንዳንዶቹ የተለያየ ክፍል ችንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው ሁኔታ ይህ የተደረገው መች እንደሆነ በትክክል መናገር እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ያህል በ916 ዓ.ም. በእብራይስጥ በተጻፈው በሴይንት ፔቲስበርግ ኮዴክስ ውስጥ አስራ ሁለቱም[9] ደቂቃን ነቢያት በአንድ መጽሐፍ ውስጥ ተጠቃለዋል፡፡ መጽሐፍቱ እንደ ምዕራፍ የተከፋፈሉ ሲሆኑ የሁሉም ቁጥሮች ግን ተቆጥሮ አንድ ድምር ውጤት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሳሙኤል፣ ነገሥትና ዜና ሁለት ሁለት ቦታ የተከፈሉት፤ ዕዝራና ነህምያ ሁለት መጻሕፍት የተደረጉት ለመጀመርያ ጊዜ በ1516 እና 1517 በታተመው የእብራይስጥ ዕትም ነበር፡፡

ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን እንደነገረን ከሆነ[10] ለሃያ ሁለቱ መጻሕፍት እኩል ተቀባይነት ያላገኙ ሌሎች መጻሕፍት ወደ ግሪክ ቋንቋ ተተርጉመዋል፡፡ ስለዚህ አይሁዶች እንደ ቀኖና ከተቀበሏቸውና በእብራይስጥ ቋንቋ ካቆዩአቻው በተጓዳኝ  የግሪክ ሰብዓ ሊቃናት ቅጂ ከክርስቶስ ልደት በፊት የተጻፈ ቢሆንም በአይሁዶች እንደ ቀኖና ተቀባይነት ያላገኙ ሌሎች መጻሕፍትን ይዟል፡፡ ስለዚህ እነዚህ የብሉይ ኪዳን አካል ተደርገው አይቆጠሩም፡፡ ብሉይ ኪዳን ከእብራይስጥ ወደ ግሪክ በ285-247 ዓ.ዓ. መካከል ፕቶለሚ ወይንም ደግሞ በቅፅል ስሙ ፍላዴልፊየስ በተባለው ንጉስ ፍላጎት መሠረት እንደተተረጎመ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ አንዳንዶቹ ከዚያ ይዘገያል በማለት ይናገራሉ (250-200 ዓ.ዓ.) ነገር ግን ያ ብዙም ጠቃሚ አይደለም፡፡ የተቀሩት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ኋላ ላይ ተተርጉመዋል ነገር ግን ሁሉም ከክርስቶስ ልደት በእጅጉ በመቅደም ነበር፡፡ ይህ ሰብቱጀንት (ወይንም ከተረጎሙት ሊቃውንት ብዛት በመነሳት የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም) የተሰኘው እኛ ምናውቀው ቀደምት የብሉይ ኪዳን ትርጉም ነው፡፡

አሁን በእጃችን የሚገኘው ብሉይ ኪዳን በሙሐመድ ዘመንና ከርሱ በፊት ከነበረው ጋር ፍጹም አንድ መሆኑን ምን ያህል እርግጠኞች እንደሆንን ለማሳየት ሌሎች የብሉይ ኪዳን ቅጂዎችን ወደ መጥቀስ እናልፋለን፡፡

በ130 ዓ.ም. አቂላ በተባለ ሰው የግሪክ ቅጂ የተዘጋጀ ሲሆን በ218 ዓ.ም. ሲማቹስ በተባለ ሳምራዊ ሌላ ቅጂ ተጠናቀቀ፡፡ ኢጣላ ወይንም ቀደምት የላቲን ቅጂ በሁለተኛው የክርስቲያን ክፍለ ዘመን ሥራ ላይ ዋለ፡፡ ከሰብቱጀንት የተተረጎመ ነበር፡፡ ቩልጌት የተባለው በጀሮም የተዘጋጀው የብሉይ ኪዳን ትርጉም በ405 ዓ.ም. ተጠናቀቀ፡፡ ከእብራይስጡ በቀጥታ የተተረጎመ ነበር፡፡

ወደ ሦርያ ትርጉም በጣም ቀደም ብሎ ነበር የተጀመረው፡፡ የኤዴሳው ያዕቆብ እንደተናገረው በክርስቶስ ዘመን አካባቢ አንድ ትርጉም ለኤዴሳው ንጉሥ ለአብጋር ተዘጋጅቶለት ነበር፡፡ ፔሺታ (بشِطّا) በመባል የሚታወቀው የብሉይ ኪዳን የሦርያንኛ ቅጂ መጀመርያ እንደተጠቀሰ የሚታመነው በሁለተኛው ክፍለ ዘመን በሰርዴሱ ሜሊቶ እንደሆነ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ በሦስተኛው ክፍለ ዘመን ነው ይላሉ፡፡ የፊሎሴኖች የሦርያንኛ ቅጂ ፖሊካርፕ በተባለ ተርጓሚ በ508 ነበር የተዘጋጀው፡፡ በ616 ዓ.ም. ደግሞ በሄራክሊያው ቶማስ (حرقل) ተከልሷል፡፡ ስለዚህ ሌሎች ሁሉም የሦርያንኛ ቅጂዎች ከሙሐመድ በፊት የተጀመሩ ሲሆኑ ይኸኛው ግን በርሱ ዘመን የተዘጋጀ ነው፡፡

ከሂጅራ በፊት የሙሐመድ ተከታዮች ከመካ ተሰደው ወደ አቢሲንያ በመጡ ጊዜ እዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች በኢትዮጵያንኛ የተጻፈ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳንን ሲያነቡ አገኟቸው፡፡ ይኸኛው ቅጂ በጣም የቆየ ከመሆኑ የተነሳ ለአብሲናውያን እንኳ ለመረዳት የሚከብድ ነበር፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ በአራተኛው ክፍለ ዘመን ከሰብዓ ሊቃናት ቅጂ ስለተተረጎመ ነው፡፡

ኡመር ግብፅን አሸንፎ በያዘ ጊዜ በአብዛኛው ክርስቲያን የሆኑ ማህበረሰቦችን አገኘ፡፡ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉምን ቢያንስ ወደ ሦስት ያክል የራሳቸው ቋንቋ (ኮፕቲክ) ዘዬ ተርጉመው ነበር፡፡ እነዚህም የቡኻርኛ (بُحَيْرِي)፣ ሳዒዲኛ (صَعِيدي)ና ቡሽሙርኛ (بُشْمُورِي) ዘዬዎች በመባል ይታወቃሉ፡፡ አንዳንዶች ቀደምትነት ያላቸው እንደሆኑ የሚታሰቡ ቢሆንም ነገር ግን በሦስተኛና አራተኛ ክፍለ ዘመን ውስጥ የተዘጋጁ ሳይሆኑ አልቀረም፡፡

የተወሰኑ የብሉይ ኪዳን ትጉሞች ከሦርያንኛ ወደ አርመን ቋንቋ በ411 ዓ.ም. ተተርጉመው ነበር፡፡ ሌላ ትርጉምም ከሰብዓ ሊቃናት ቅጂ ወደ አርመንኛ በ436 ተሠርቶ ነበር፡፡ ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ ደግሞ የጆርጂያንኛ ትርጉም ከአርመንኛ ላይ ተሠርቶ ነበር፡፡ ይህም ከሂጅራ በጣም ቀደም ብሎ ነበር፡፡

ወደ አውሮፓ ደግሞ ስንመለስ በ381 ወይንም ደግሞ በ383 ዓ.ም. የሞተ ኡልፊያስ የተባለ የጎቲክ ጳጳስ በ360 ዓ.ም. ለራሱ ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ጎቲክ ቋንቋ ተርጉሞ ነበር፡፡

ከሰብዓ ሊቃናት ትርጉምና ከአቂላስ ቅጂ በተረፈ እነዚህ ሁሉ ትርጉሞች የተዘጋጁት በክርስቲያኖች ነበር፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ እብራይስጥ መናገር ባቆሙበት ወቅት አይሁዶች አብዛኛውን ብሉይ ኪዳን ከእብራይስጥ ወደ አረማይክ ተርጉመው ነበር፡፡ የኦንኬሎስ ቶራህ ቅጂ በ150ና በ200 ዓ.ም. መካከል ነበር የተዘጋጀው፡፡ ዮናታን ቤን ኡዝኤል የነቢያትን መጽሐፍት በ322 ዓ.ም. ነበር የተረጎመው፡፡ ከነዚህም በተጨማሪ ከሂጅራ በፊት ምናልባትም በስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተዘጋጀው የኢየሩሳሌም ተርጉም ይገኛል፡፡

ቀደም ብለው በነበሩት ዘመናት ሳምራውያን የአይሁዶች ቀንደኛ ጠላቶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ሳምራውያን ሙሴ ከጻፈው ቶራህ ውጪ ያሉትን የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች ለመቀበል እንቢ ብለው ነበር፡፡ እርሱን ግን ይቀበላሉ ያከብሩትማል፡፡ የእብራይስጥ ቶራህ ቅጂ መች እጃቸው ውስጥ እንደገባ በርግጠኝነት ማወቅ አይቻለንም፡፡ አንዳንዶች የ70 ዓመቱ የአይሁድ ምርኮ ከጀመረ በኋላ እንደሆነ ይገምታሉ፡፡[11] አንዳንዶች ደግሞ የሊቀ ካህኑ ኤልያሻብ ልጅ የሆነው ምናሴ ወደ ሰማርያ እንዳመጣው ይገምታሉ፡፡ የሰንበላጥን ልጅ አግብቶ ነበር (ነህ 13፡28)፤ በነህምያ ከኢየሩሳሌም ስለተባረረ ሌላ ቤተ ወቅደስ በገሪዛን ተራራ ላይ በ409 ዓ.ዓ. ሰርቶ ነበር፡፡ የሳምራውያን ፔንታቱክ አሁን ይገኛል፡፡ ይህም በእብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈ ሲሆን አይሁዶች ከሚጠቀሙት ፊደላት በተለዩ ፊደላት የተጻፈ ነው፡፡

እነዚህን ሁሉ የተለያዩ እማኞች ስንመረምርና አሁን በእጃችን የሚገኘው ብሉይ ኪዳን በሙሐመድ ዘመን የነበረው መሆን አለመሆኑን እንዲነግሩን ስንጠይቃቸው ሁሉም በአንድ ድምፅ “አዎን” በማለት ይመልሱልናል፡፡ ልክ በቁርኣንና በሌሎች ጥንታዊ ጽሑፎች ውስጥ እንደሚገኙት ሁሉ ልዩነት ያላቸው አነባበቦች መኖራቸው እርግጥ ነው፡፡ እንደተመለከትነውም የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም አዘጋጆች ከእብራይስጥ ቀኖናዊ መጻሕፍት በተጨማሪ ሌሎች ስልጣን የሌላቸው መጻሕፍት እንዲዘዋወሩ መፍቀዳቸውም እርግጥ ነው፡፡ ነገር ግን በቀኖና ውስጥ ከሚገኙት መካከል አንዱንም እንኳ አልጣሉም ነበር፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስናቸውን የብሉ ኪዳን ቅጂዎች ስንመለከት በውስጣቸው በሚገኙ የንባብ ልዩነቶች የተነሳ የተለወጠ አንድም አስተምህሮ የለም፡፡ ከዚህ መረጃ በመነሳትም አሁን በእጃችን የሚገኘው ብሉይ ኪዳን በሙሐመድ ዘመን የነበረውና ቁርኣንም የሚመሰክርለት እንደሆነ ማየት እንችላለን፡፡

ወደ አዲስ ኪዳንም በመምጣት በዚህ ስም እየተጠራ ያለው ጥራዝ በሙሐመድ ዘመን የነበረው መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልገናል፡፡ ይህንን በተመለከተ በምሑራን መካከል ቅንጣት ታህል እንኳ ጥርጣሬ የለም፡፡

የቅርብ ጊዜ ምርመራዎች እንዳሳዩት በክርስቶስ የሕይወት ዘመን እንኳ አንዳንድ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ትምህርቱና ስለ ስራው አጫጭር ማስታወሻዎችን ይይዙ ነበር፡፡ እነዚህም በማርቆስ ወንጌል ውስጥ የሚገኙ ብዙ ቁጥሮችና በማቴዎስና በሉቃስ ውስጥ የተጠቃለሉት እንደሆኑ ሊታሰቡ ይችላሉ፡፡ በርግጥ የስቅለቱ፣ የመቀበሩና የትንሣኤው ትረካዎች እርሱ ወደ ሰማይ እስኪያርግ ድረስ ሊጻፉ አይችሉም፡፡ ጌታችንን ያዩትና ከርሱም ጋር የተነጋገሩ ብዙ ሰዎች ባሉበት ዘመን (1ቆሮ 15፡6) ሰዎችን ለማስረዳት መጻሕፍት መጻፍ አያስፈልግም ነበር፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩን በሕይወት ካሉ ምስክሮች መስማት ይችላሉና (ሐዋ 1፡21-22)፡፡ እነዚህም ምሰክሮች መስቀለኛ ጥያቄዎችን ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ መጽሐፍ ግን ሊጠየቅ አይችልም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የትንሣኤው ጌታ ደቀ መዛሙርቱን ወንጌልን እንዲሰብኩ ነበር ያዘዛቸው፡፡ በመጀመርያው እንዲጽፉ አልነበረም ያዘዛቸው፡፡ የቅዱስ ጳውሎስን መልዕክት ስናነብ ወንጌል (بشارة) ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማየት እንችላለን፡፡ የመጀመርዎቹ መልዕክቶች (1ና 2 ተሰሎንቄ) ከክርስቶስ እርገት በኋላ 22 ወይንም 23 ዓመታትን ብቻ ዘግይተው የተጻፉ ነበሩ፡፡ በነዚህና በሌሎች የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክቶች ውስጥ ከሚገኙት ጋር አንድ የሆኑ አስተምህሮዎችን ዛሬም እየተከተልን እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡

የመጀመርያዎቹ የክርስቲያን ትውልዶች መሞት ሲጀምሩ ቀጥለው ለነበሩት ትውልዶች ወንጌላት እንዲጻፉ የእግዚአብሔር መንፈስ ምሪትን ሰጠ፡፡ የቅዱስ ማርቆስ ወንጌል ኢየሩሳሌም በ70 ዓ.ም. ከመውደቋ በፊት ተጽፎ ተጠናቀቀ፡፡ ምናልባት በ65ና 66 ዓ.ም. መካከል በሮም ከተማ ሊሆን ይችላል፡፡ ማርቆስ የሐዋርትና ቀደምት ደቀ መዛሙርት ወዳጅ ብቻም አልነበረም በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁሌም የሚታወቀው የቅዱስ ጴጥሮስ አስተርጓሚ እንደነበር ነው፡፡ በማርቆስ ወንጌል ውስጥ የሚገኙት መረጃዎች ከቅዱስ ጴጥሮስ የተገኙ ናቸው ማለት ነው፡፡ በርግጥ መለኮታዊ ምሪት ያንን መረጃ አልለወጠውም ነገር ግን ክርስቶስ የተናገረውን ነገር በማሳሰብ (ዮሃ 14፡26፣ 15፡26)ና ከስህተት በመጠበቅ ጴጥሮስና ማርቆስ ምን መጻፍ እናዳለባቸውና ምን መጻፍ እንደሌለባቸው መርቷቸዋል፡፡ የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልም ከ70 ዓ.ም. በፊት ነበር የተጻፈው፡፡ የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ደግሞ በ60ና 70 ዓ.ም. መካከል ነበር፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ደግሞ ተወዳጁ ደቀ መዝሙር አዛውንት በነበረ ጊዜ በ90ና 100 ዓ.ም. መካከል ነበር የጠጻፈው፡፡ ስለዚህ ሁለት በሐዋርያት የተጻፉ (ማቴዎስና ዮሐንስ) አንድ በተመረጠ የሐዋርያት ወዳጅ በነበረ ሰው (በማርቆስ) የተጻፈና አራተኛ በቅዱስ ጳውሎስ ወዳጅ በሉቃስ የተጻፈ አራት ወንጌላት አሉን ማለት ነው፡፡ ሉቃስ እያንዳንዱን ጥቃቅን ነገር ከዐይን ምስክሮች በጥንቃቄ እንደመረመረ ይነግረናል (ሉቃ 1፡3&4)፡፡ በመጀመርያዎቹ ሁለት ምዕራፎች ውስጥ የተመዘገቡት ነገሮች ከድንግል ማርያም ከራሷ አንደበት እንደሰማ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

ይህ ሁሉ ነገር ግልጠተ መለኮት አይደለም የሚል ተቃውሞ ይመጣ ይሆናል፡፡ ይህ ሙስሊሞች ቁርኣን ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በሰሌዳ ላይ እንደተጻፈና በ“ኃይል ሌሊት” ወደ ታችኛው ሰማይ ወርዶ[12] እንደየ አስፈላጊነቱ በመልአኩ ገብርኤል አማካይነት በሙሐመድ ላይ እንደተነበበ ከሚያምኑት ታሪክ የተለየ ነው፡፡ እንደርሱ ዓይነቱ መገለጥ በኛ በክርስቲያኖች ዕይታ የማይፈለግና ቁርኣንን በተመለከተም እውነት መሆኑ ሊረጋገጥ የማይችል ነው፡፡ ይህም ደግሞ “የቁርኣን የመጀመርያ ምንጮች”[13] በሚለው መጽሐፍ ውስጥ እንደተመለከተው ነው፡፡ አንድ መጽሐፍ በሰማይ ተጽፎ ወደ ምድር የመጣ ቢሆን እንኳ ይህ እውነት መሆኑ ሊረጋገጥ እንደማይችል ልቦና ያላቸው ሰዎች ሁሉ የሚረዱት እውነታ ነው፡፡ ነገር ግን በክርስቲያኖች የመገለጥ ግንዛቤ መሠረት መለኮታዊ መገለጥ ለሰዎች ምሪት በጽሑፍ እንዲሰፍር በማድረግ ሂደት ውስጥ መልእክቱ የእግዚአብሔር ሲሆን ቃላቱ የጸሐያኑ ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር የነቢያቱን እጅ ብቻ ሳይሆን አዕምሯቸውን፣ ትውስታቸውን፣ ዕውቀታቸውንና መንፈሳቸውን ተጠቅሟል (ዮሃ 16፡13 ይመልቱ)፡፡

እዚህ ጋር እውነትን በሚፈልጉበት ወቅት በሙስሊም ወንድሞቻችን ፊት የተቀመጠውን ችግር ማብራራት ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት “አሁን በክርስቲያኖች እጅ የሚገኘው ኢንጂል ለኢየሱስ የወረደለት ሊሆን አይችልም ምክንያቱም አሁን ያሉት አራት የተለያዩ አንጂሎች (اناجيل) እንጂ አንድ እንጂል አይደለም፡፡ እንዲሁም እነዚህ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ዘግይተው የተጻፉ ናቸው፡፡” እንግዲህ ለዚህ ክርክር መልስ መስጠት አያስቸግርም፡፡ ይህ ክርክር ሚዛን የሚደፋ ከሆነ ኢንጂልን ብቻ ሳይሆን ቁርኣንንም ጭምር የሚጎዳ ይሆናል ምክንያቱም በሚሽካቱል መሰቢህና[14] በሌሎች እስላማዊ ጽሑፎች ላይ እንደምናነበው ቁርኣን እስከ ሙሐመድ ሞት ድረስ ተሰብስቦ በአንድ ጥራዝ አልተቀመጠም ነበርና፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ አንድ ወንጌል ብቻ ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም ወንጌል የሚለው ቃል አሁን የመጽሐፍ ስም ሆኖ ቢያገለግልም ነገር ግን ትርጉሙ “የምሥራች” ማለት ነውና፡፡ ሙስሊሞች ይህንን ብዙ ጊዜ አያስተውሉም፡፡ “ኢንጂል”ευαγγελιον የሚለው የግሪክ ቃል የአረብኛ አቻ ሲሆን (الِبشارة) የሚለውን ያመለክታል፡፡ በተለያዩ መንገዶች ቢነገርም እንኳ ይህ የምሥራች፣ ይህ የእግዚአብሔር ፍቅር መልእክት አንድ ነው፡፡ በአንድ ግለሰብ ምስክርነት ብቻ ሳይሆን በአራት የተለያዩ ሰዎች ምስክርነትም ተረጋግጧል፡፡ አሁንም ደግመን አንድ ወንጌል ብቻ እንዳለ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡ በኦሪጅናሉ የግሪክ ቋንቋ “ወንጌል እንደ ቅዱስ ማቴዎስ” “ወንጌል እንደ ቅዱስ ማርቆስ” ወዘተ. ስለሚል የመጽሐፍቱ ስያሜ ይህንን ያመለክታል፡፡ አጠርና ቀለል እንዲል ስለተፈለገ ብቻ ነው “የማቴዎስ ወንጌል” ወዘተ. የምንለው፡፡ እያንዳንዱ የወንጌል ጸሐፊ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ስር በመሆን በራሱ ሁኔታ ጽፏል፡፡ ነገር ግን መልዕእክቱ ተመሳሳይና አንድ ነው፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደሚናገረው ልክ ከዕርገት በኋላ ይህ ወንጌል በየሀገሩ በክርስቲያኖች ተሰብኳል፡፡ ነገር ግን በመጀመርያ በክርስቶስ በራሱ ነበር የተሰበከው (ማር 1፡15፣ 13፡10፣ ሉቃ 20፡1)፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ ለክርስቶስ ለራሱ “የወረደለት” መሆን አለበት ምንያቱም እርሱ ራሱ “እኔ የምናገረውን አብ እንደ ነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ” በማለት ተናግሯልና (ዮሃ 12፡50፣ ከዮሃ 8፡28ና 12፡49 ጋር ያነጻፅሩ)፡፡

በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቃለሉትን መጽሐፍት በተመለከተ ምንም ስልጣን የሌላቸውና መለኮታዊ ያልሆኑ መጽሐፍት ሾልከው እንዳይገቡ ለመከላከል በሂደት ከብዙ ምርመራ በኋላ ቀኖናዊ ወደመሆን እንደመጡ ማንም ምሑር የሚያውቀው ነው፡፡ አንዳንድ መልእክቶች የግል ደብዳቤዎች ከመሆናቸው የተነሳ (1እና2 ጢሞቴዎስ፣ ቲቶ፣ ፊልሞና፣ 2እና3 ዮሐንስ) ይህ ምርመራ የተወሰነ ጊዜ ወስዶ ነበር፡፡ የተቀሩት ደግሞ ለነጠላ አብያተ ክርስቲያናት የተላኩ ነበሩ፡፡ ነገር ግን እስካሁን ተጠብቀው ካሉት የቀደሙት ክርስቲያኖች ጽሑፎች እንደምንረዳው አራቱም ወንጌላት በ70ና 130 ዓ.ም. መካከል ሥልጣናዊ መሆናቸው ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፡፡ ከ170 ዓ.ም. የሆነ ቁርጥራጭ ጽሑፍ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ከፊል ዝርዝር ይዟል፡፡ የሙራቶራውያን ቀኖና በመባልም ይታወቃል፡፡ ይህ ጽሑፍ ቁርጥራጭ ቢሆንም ነገር ግን ከያዕቆብ፣ 2ጴጥሮስና ዕብራውን መልዕክታት በተረፈ ሁሉም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት መኖራቸውን ይናገራል፡፡ ነገር ግን ይህ ዝርዝር ሙሉ ቢሆን ኖሮ ያለጥርጥር እነዚህንም ያካትታል ምክንያም ብዙ ጊዜ በጥንታዊ ሰነዶች ውስጥ ተጠቅሶ ከማናገኘው ከ2ጴጥሮስ ውጪ ሁሉም መጻሕፍ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን በተጻፈ ጽሑፍ ውስጥ ተጠቅሰው እናያለንና፡፡ በዚያ ዘመን መጽሐፍት ውድ መሆናቸውንና ክርስቲያኖችም ደግሞ ድሆች መሆናቸውን ከግምት ውስጥ ብናስገባ፤ በብራና ላይ ልክ በዚያ ዘመን እንደነበረው በትልልቅ የግሪክ ፊደላት ቢጻፉ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የብራና ጥቅልሎችን ሳይሆን መለስተኛ ቤተ መጻሕፍትን ይፈጥሩ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ ሁሉንም መጻሕፍት በተለያዩ ቦታዎች በአንድነት በማግኘታችን ልንደነቅ እንችላለን፡፡ በ363 ዓ.ም. በተደረገው የሎዶቂያ ጉባኤ ላይ ከዚህ ቀደም እንደተመለከትነው ሃያ ሁለቱ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከመጠቀሳቸው ሌላ ከዮሐንስ ራዕይ በተረፈ ዛሬ የምናውቃቸው የአዲስ ኪዳን መጻሕፍ ሁሉ ተጠቅሰዋል፡፡ ስለዚህ በወቅቱ የኋለኛውን በተመለከተ አንዳንድ ጥርጣሬዎች መኖራቸውን እናያለን፡፡ አንዳንድ አብያተ ከርስቲያናት ሲቀበሉት ሌሎቹ ደግሞ እዚያ ውሳኔ ላይ አልደረሱም ነበር፡፡ ኋላ ላይ ግን ተቀብለውታል፡፡ በ397 የተደረገው የካርቴጅ ጉባኤ አሁን ያሉትን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ ዝርዝር ይሰጣል፡፡ እንዲህ የሚሉ ቃላትንም ይዟል፡ “እነዚህ መጽሐፍት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መነበብ እንዳለባቸው ከአባቶቻችን ተቀብለናል፡፡”

በጉባኤዎች ከተዘጋጁት ከነዚህ ዝርዝሮች በተጨማሪ ታዋቂ በሆኑ የተወሰኑ ክርስቲያን ጸሐፍት ጽሑፎች ውስጥ የገዛ ምርመራዎቻቸው እነዚህ በሐዋርትና በቀደሙት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የተጻፉ እንደሆኑ እንዲቀበሉ ያደረጓቸውን የመጻሕፍት ዝርዝሮች እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ ያህል በ253 ዓ.ም. የሞተው ኦሪጎን ሁሉንም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍታችንን ጠቅሷቸዋል፡፡ በ315 ዓ.ም. የሞተው አትናቴዎስ እንዲሁ አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ ዘመን የጻፈው ኢዮስቢዮስም ሁሉንም ጠቅሷቸዋል፡፡ ነገር ግን የያዕቆብ ምልዕክት፣ የይሁዳ መልዕክት፣ 2ጴጥሮስ፣ 2እና3 ዮሐንስና የዮሐንስ ራዕይ ትክክለኛ መሆን አለመሆናቸው ላይ በአንዳንዶች ዘንድ ጥርጣሬ መኖሩንም ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል እንዳልነው ጥንቃቄን የተሞላ ዕይታ እነዚህ መጻሕፍት የአዲስ ኪዳን ቀኖና አካል እንዲሆኑ በቤተ ክርስቲያን እንዲታመን አድርጓል፡፡

ስለዚህ በመጀመርያዎቹ አራት ክፍለ ዘመናት ሁሉም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት መኖራቸውን በተመለከተ ከፓለስታይን፣ ሦርያ፣ ቆጵሮስ፣ ትንሹ ኢስያ፣ እስክንድሪያ፣ ሰሜን አፍሪካና ኢጣልያ ምስክሮች አሉን ማለት ነው፡፡

ከዚህም በመነሳት አሁን በክርስቲያኖች እጅ የሚገኘው አዲስ ኪዳን በሙሐመድ ዘመን በአረብያ፣ ሦርያ፣ ግብፅ፣ አቢሲንያ ይኖሩ በነበሩ ክርስቲያኖች እጅና ከርሱ ጋር ግንኙነት በነበራቸው ሌሎች ሕዝቦች እጅ እንደነበር ግልፅ ነው፡፡

ስለዚህ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን በሙሐመድ ዘመን እንደነበሩ ማረጋገጥ ችለናል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህን ስሞች ይዘው የሚገኙ እነዚህ መጻሕፍት በዚያ ዘምን ከነበሩት ጋር በይዘት አንድ ስለመሆናቸው ገና አላረጋገጥንም፡፡ ምናልባት ቀደም ብለው የነበሩት መጻሕፍት በመጥፋት አሁን ያሉት ስሞቻቸው ብቻ የሚመሳሰል ሆኖ ተጭበርብረው የተጻፉ ይሆንን? አንድ ሙስሊም “አሁን በእጅህ ባለው ቁርኣን ውስጥ ተጽፎ የሚገኘው ሱራ አል በቀራ በኡመር ዘመን ተመሳሳይ ስም ከነበረው ጋር በይዘት አንድ መሆኑን በምን ታውቃለህ?” ተብሎ ቢጠየቅ እስኪ አስቡት፡፡ ቅዱስ መጽሐፋችንን በተመለከተ ተመሳሳይ ጥያቄ መጠየቃችን ምን ያህል የማይረባ ጥያቄ መሆኑን ይረዳ ሆናል፡፡ ነገር ግን ሁሉንም ዓይነት ማመካኛዎችንና ጥርጣሬዎችን ለማስወገድ ምላሽ እንሰጥበታለን፡፡

አሁን በእጃችን የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ በሙሐመድ ዘመን ከነበረው ጋር አንድ መሆኑን የሚያሳየው የመጀመርያው ማስረጃ ከርሱ ዘመን በፊት የነበሩ እጅግ ብዙ የብሉይና አዲስ ኪዳናት የእጅ ጽሑፎች ዛሬም በእጃችን መገኘታቸው ነው፡፡ ቀጥለን እንደምናሳየው ይህ ከአዲስ ኪዳን የግሪክ ጽሑፎችና የብሉይ ኪዳን የግሪክ ትርጓሜዎች አንጻር እውነት ነው፡፡

የእብራይስጥ የብሉይ ኪዳን ጽሑፎችን በተመለከተ አሁን ያለን የእጅ ጽሑፍ ዐሥርቱን ትዕዛዛትና የእብራይስጥ የእምነት መግለጫን የያዘው (ዘጸ 20፡2-17ና ዘዳ 6፡4-9) ከአራት ዓመታት በፊት በግብጽ የተገኘው ፓፒረስ ብቻ ነው፡፡[15] ይህም የተጻፈው በ220 ዓ.ም.ና በ250 ዓ.ም. መካከል ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ከሂጅራ በፊት ብዙ ዘመናት የሚቀድም ነው፡፡

ከሁሉም ቀዳሚ የሆነው ትልቅ መጠን ያለው የእጅ ጽሑፍ “ኦሪዬንታል ቁጥር 4445” በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ በብሪቲሽ ቤተ መዘክር ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በ820ና 850 ዓ.ም. የተጻፈ ነው፡፡ ሁለተኛው ቀዳሚ ደግሞ “የቅዱስ ፒተርስበርግ ኮዴክስ” በመባል የሚታወቀው በ916 ዓ.ም. እንደተጻፈ የሚገልጽ ጽሑፍ ያለው የእጅ ጽሑፍ ነው፡፡ ነገር ግን እነኚህ በጣም ቀደምት ከሆነ የእጅ ጽሑፍ ላይ የተገለበጡ ናቸው፡፡ የሁለቱንም መኖር ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህም “ሴፈር ሂሌሊ”ና “ሴፈር ሙጋህ” በመባል ይታወቃሉ፡፡ በ1500 ዓ.ም. አካባቢ የጸፈው ዛኩት (زَكّوت) የተባለ አይሁዳዊ የዜና መዋዕል ጸሐፊ “ሴፈር ሂሌሊ” በ597 ዓ.ም. እንደተጻፈ ይናገራል፡፡ እርሱ ራሱ የቀዳሚና ተከታይ ነቢያትን የያዘውን ክፍሉን እንዳየ ይናገራል፡፡ ይህም ማለት መጽሐፈ ኢያሱ፣ መሳፍንት፣ 1እና2 ሳሙኤል፣ 1እና2 ነገሥት፣ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ሆሴዕ፣ ኢዩኤል፣ አሞፅ፣ አብድዩ፣ ዮናስ፣ ሚክያስ፣ ናሆም፣ ዕንባቆም፣ ሰፎንያስ፣ ሐጌ፣ ዘካርያስና ሚልክያስ ናቸው፡፡ “ሴፈር ሙጋህ”ም የዚያኑ ያክል እድሜ ያለው ሊሆን ይችላል፡፡ ቢያንስ ከሁለቱ አንዱ የእጅ ጽሑፍ በሙሐመድ ዘመን ነበረ፡፡ በነርሱ ላይ ከተሰጡት የአይሁድ ሕታቴዎች በመነሳት አሁን ካለው የእብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ መጽሐፍቶችን መያዛቸውን ማወቅ ይቻላል፡፡ የኋለኞቹ የእብራይስጥ የእጅ ጽሑፎች ብዛት በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡

ቀዳሚ የሆኑት የእጅ ጽሑፎች ምን እንደተደረጉ ቢጠየቅ መልሱ ሊሆን የሚችለው በምኩራብ ውስጥ ለዘመናት ተነበው ካረጁ በኋላ አይሁድ በግምጃ ቤት ውስጥ የማስቀመጥ ልማድ ነበራቸው የሚል ነው፡፡ ከጊዜ በኋላ አንድ ታዋቂ ረቢ ሲሞት ያረጀውን የእጅ ጽሑፍ ከርሱ ጋር የመቅበር ልማድ ነበር፡፡

የሰብዓ ሊቃናት የግሪክ ቅጂን ስንመለከት ደግሞ ቁጥራቸው በዛ ያለ የእጅ ጽሑፎች አሉን፡፡ እነዚህም ደግሞ ከሂጅራ በፊት ብዙ ዘመናትን በመቅደም የተጻፉ ሲሆኑ በሙሐመድም ዘመን ይዘዋወሩ ነበር፡፡ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም መኖሩ በራሱ የትርጉም ምንጭ የሆነው የእብራይስጥ ጽሑፍ መኖሩን ያረጋግጣል፡፡ ዋና ዋና የሆኑትን እንጠቅሳለን፡

  1. ኮዴክስ ሲናይቲከስ (السّفر الْسّينايُ) – በአራተኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ወይንም ደግሞ በአምስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ የተጻፈ ነው፡፡
  2. ኮዴክስ ቫቲካነስ (الواطيقاني) – በአራተኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ምናልባትም በክፍለ ዘመኑ መጀመርያ አካባቢ ላይ የጠጻፈ ነው፡፡
  3. ኮዴክስ አሌክሳንድሪነስ (الإْسكندري) – በአምስተኛው ክፍለ ዘመን መካከል ወይንም መጨረሻ አካባቢ ላይ የተጻፈ ነው፡፡
  4. ኮዴክስ ኮቶኒያነስ (القُطّوني) – የዘፍጥረት መጽሐፍ ሲሆን በአምስተኛው ወይንም ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ የተጻፈ ነው፡፡
  5. ኮዴክስ አምብሮሲያነስ (الاّمبروسياني) – በአምስተኛው ክፍለ ዘመን የመጀመርያው አጋማሽ አካባቢ የተጻፈ ነው፡፡

እነዚህ ሁሉ የግሪክ ብሉይ ኪዳን የእጅ ጽሑፎች በሙሐመድ ዘመን ነበሩ፡፡ ማንኛውም ምሑር ቁርኣን የሚመሰክርላቸው ቶራህ፣ ዘቡርና የነቢያት መጻሕፍት ይዘት ምን እንደሆነ ማወቅ ከፈለገ እነዚህ የእጅ ጽሑፎች የተቀመጡባቸውን ቤተ መጻሕፍት መጎብኘት ብቻ ነው የሚጠበቅበት፡፡ በመላው ክርስቲያን ሊቃውንት እጅ የሚገኙት የኛ የግሪክ ብሉይ ኪዳን ኮፒዎች የታተሙት በነዚህ ጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ በሚገኘው ንባብ መሰረት ነው፡፡ የእብራይስጥ የእጅ ጽሑፎችን ስናነጻፅር በያንዳንዱ አስተምህሮ ላይ ይስማማሉ፡፡ የንባብ ጥቃቅን ልዩነቶች ይታያሉ፡፡ በአንዳንድ ቦታዎችም ላይ አስቸጋሪ ቃላትን የግሪክ ተርጓሚዎች በተሳሳተ መንገድ የተረጎሙበት ሁኔታ አለ፡፡ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም በዘፍጥረት 5ና 11 ላይ የሚገኙትን የአባቶች እድሜ በተመለከተ ከእብራይስጡ በተወሰነ መልኩ ይለያል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ልዩነቶች ኃይማኖታችንን በአስተምህሮም ሆነ በልምምድ ተፅዕኖ የሚያሳድሩበት ቅንጣት ታህል መንገድ የለም፡፡

የግሪክ አዲስ ኪዳንን በተመለከተም በጣም ጥንታዊ የሆኑ የእጅ ጽሑፎች አሉን፡፡ ይህ በብራና ላይ እንጂ በወረቀት ላይ ስላልሆነ ሼኽ ራህመቱላህ የተናገሩት[16] “ወረቀትን ወይንም ፊደልን ለ1400 ዓመታት ጠብቆ ማቆየት የማይታሰብ ነው” የሚለው ዓይነት ንግግር ምንም ቦታ የለውም፡፡ ነገር ግን በግብጽ ከ1800 ዓመታት በላይ እድሜ ያላቸውን በፓፒረስ ላይ የተጻፉ ጽሑፎች መገኘታቸውን ምሑራን በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ብዙ የብሉይ ኪዳን የግሪክ ትርጉሞች ኦሪጅናሉን የግሪክ አዲስ ኪዳን ይዘዋል፡፡ 1. አንደኛው ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኮዴክስ ሲናይቲከስ ሲሆን በቅዱስ ፒተርስበርግ ኢምፔርያል ለይብረሪ ውስጥ ተቀምጧል፡፡ 2. ሁለተኛው በሮም ቫቲካን ላይብረሪ ውስጥ የሚገኘው ኮዴክስ ቫቲከነስ ነው፡፡ 3. ሦስተኛው በለንደን ብሪቲሽ ላይብረሪ ውስጥ የሚገኘው ኮዴክስ አሌክሳንድሪነስ ነው፡፡ 4. በ1907 ምናልባትም ከአራተኛው ክፍለ ዘመን የሆኑ ነገር ግን ከስድስተኛው ክፍለ ዘመን ያነሰ እድሜ የሌላቸው አራት የግሪክ ጥንታዊያን የእጅ ጽሑፎች በአኽሚም ትይዩ በሶሃግ አካባቢ በሚገኝ የግብጽ ገዳም ውስጥ ተገኝተዋል፡፡ የመጀመርያው ክፍል ዘዳግምና መጽሐፈ ኢያሱን የያዘ ሲሆን ሁለተኛው ክፍል መዝሙረ ዳዊትን፣ በሦስተኛው ውስጥ አራቱን ወንጌላት፣ በአራተኛው ውስጥ የቅዱስ ጳውሎስን መልእክታት ቁርጥራጭ ይዟል፡፡ 5. አምስተኛው በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተጠብቆ የሚገኘው ኮዴክስ ቢዛዬ (السِفّر الْبِيزاَيُ) ሲሆን በስድስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ አካባቢ ነበር የተጻፈው፡፡ 6. ስድስተኛው ኮዴክስ ኤፍራይም (السِّفر الإفرْايُمي) ሲሆን በአምስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ አካባቢ የተጻፈ ነው፡፡ በፈረንሳይ ናሽናል ላይብረሪ ውስጥ ተቀምጦ ይገኛል፡፡

ከነዚህ ትልልቅ የእጅ ጽሑፎች በተጓዳኝ ልዩ ልዩ የአዲስ ኪዳን ክፍሎችን የያዙ ትንንሽ ጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች በየመጽሐፍት ቤቶቻችን አሉን፡፡ ከነዚህ ሁሉ ቀዳሚው በግብጽ ሀገር ውስጥ በሚገኝ የኦክዚርሂንከስ ፍርስራሽ ውስጥ ነበር፡፡ ይህም የሚገኘው ከካይሮ ከተማ 120 ኪሎ ሜትር ወደ ደቡብ ባህናሳህ በመባል በምትጠራው መንድር አካባቢ ነው፡፡ ለዚህም ነው የኦክዚርሂንከስ (بهنسيّة) ፓፒሪ የሚል ስያሜ የተሰጠው፡፡ በ200ና 300 ዓ.ም. መካከል የተጻፈ ሲሆን ይህ ማለት ከሙሐመድ ልደት በፊት 370-270 ዓመታትን በመቅደም ማለት ነው፡፡ የዮሐንስን ወንጌል የመጀመርያውንና ሃያኛውን ምዕራፎች ይዟል፡፡ እነዚህ በቅርብ የተገኙት ጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች ከኛ የምልከታ ነጥብ አንፃር ያላቸው ዋጋ በቃላት ሊገለፅ የማይችል ነው ምክንያቱም በቅርቡ ተቆፍረው እስከወጡበት ጊዜ ድረስ ከጊዜ በኋላ በሙስሊሞች በተወረሩባቸው በረሃዎች ውስጥ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዘመናት ተቀብረው የኖሩ ናቸውና፡፡ ከሰዎች ሁሉ የመጨረሻ ቂል የሆነው ሰው እንኳ ቁርኣን “ከወረደ” በኋላ ተጭበርብረው የተጻፉ ናቸው ወይንም ደግሞ “ተበርዘዋል”(محرّقة) በማለት ሊናገር አይችልም፡፡

የግሪክ አዲስ ኪዳን ከፊል ወይንም ሙሉ 3,899 የሚያህሉ ጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች አሉን፡፡ ተማሪዎች የት እንደተቀመጡ ማወቅ ይችሉ ዘንድ እነዚህ ሁሉ በጥንቃቄ ተመርምረው ዝርዝር ተዘጋጅቶላቸው ተቀምጠዋል፡፡ ገና ዝርዝር ያልተዘጋጀላቸው ከ2000 እስከ 3000 የሚገመቱ ደግሞ አሉ፡፡

እስከ አሁን ድረስ ስለ ግሪክ አዲስ ኪዳን እያወራን የነበርን ብንሆንም ነገር ግን ከሙሐመድ ዘመን እጅግ የሚቀድሙ የሌሎች ቋንቋ ትርጉሞች መኖራቸውን ሳንጠቅስ አናልፍም፡፡ ለምሳሌ ያህል ፔሺታ (بِشطّا) በመባል የሚታወቀው የሦርያ ትርጉም ቢያንስ አስር አለን፡፡ እነዚህ በአምስተኛው ክፍለ ዘመን የተገለበጡ ሲሆኑ ሌሎች ሠላሳ ደግሞ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተገለበጡ ናቸው፡፡

ስለ ብሉይ ኪዳን ስናወራ ያነሳናቸው ቅጂዎች ቋንቋዎቹ እጅግ ጥንታዊ ከመሆናቸው የተነሳ በዚህ ዘመን እንደ አፍ መፍቻ ቋንቋው የሚናገራቸው ማንም የለም፡፡ ወደ እንደዚህ ዓይነቶቹ በጣም ጥንታዊ ቋንቋዎች በከፊልም ሆነ በሙሉ የተተረጎሙ በርካታ የአዲስ ኪዳን ቅጂዎች አሉ፡፡ ከነዚህ መካከል በጣም ጠቃሚ የሆኑትን የተወሰኑትን እንጠቅሳለን፡፡ ከሚከተሉት መካከል ከአንዱ በስተቀር የተተረጎሙት ከሙሐመድ በፊት ሲሆን ይህ አንዱ ራሱ ከሂጅራ በፊት የተተረጎመ ነው፡፡

በተለይ በሁለተኛውና ሦስተኛው ክፍለ ዘመን የተዘጋጀውን የፔሺታ ቅጂን ጨምሮ ብዙ የሦርያ ቅጂዎች አሉን፡፡ የፊሎዜናውያን ሦርያንኛ የተዘጋጀው በ508 ዓ.ም. ሲሆን በሄራክሊያው ቶማስ (حرقل)በ616 ዓ.ም. ተከልሷል፡፡ ከነዚህ በተጓዳኝ ሁለቱ የኩረቶኒያውያንና የሲና ሦርያንኛ በመባል የሚታወቁትን ጨምሮ ብዙ የሦርያንኛ ቅጂዎች አሉ፡፡ በ110 ዓ.ም. ታሺያን የተባለ ሰው የአራቱን ወንጌላት ሕብር ማዘጋጀቱ ቀደምት የሆነ የሦርያንኛ ትርጉም መኖሩን ያረጋግጣል፡፡ ይህ ሥራ በላቲንና በአርመንኛ ጥቂት ልዩነት ያለው ሲሆን አሁን በእጃችን ይገኛል፡፡ የዚህ “ዲያቴሳሮን” በመባል የሚታወቀው ሥራ የአረብኛ ትርጉም በ1043 ዓ.ም. በሞተው ኢብኑ ጣቢብ (ابْن الطّبيب) በተባለ ሰው ተዘጋጅቷል፡፡ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት መካከል አንዱ የኢየሱስ አፍ መፍቻ ቋንቋ በሆነው በፓለስታይን ውስጥ በሚነገር የሦርያንኛ ቋንቋ ከግሪክ የተተረጎመው የአዲስ ኪዳን ቅጂ ቁርጥራጭ መገኘት ነው፡፡ ይህ ቅጂ የተዘጋጀው በአራተኛው ክፍለ ዘመን ምናልባትም ከዚያ ቀደም ብሎ ነው፡፡ ከርሱ የተረፈውን የያዘው ጥንታዊ የእጅ ጽሑፍ “ኮዴክስ ክሊማሲ ሬስክሪፕተስ” (سِفر كليماكوس) በመባል ይታወቃል፡፡ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈ ሲሆን የተወሰነ የአራቱን ወንጌላት ክፍል፣ የሐዋርያት ሥራና የቅዱስ ጳውሎስን መልእክቶች የያዘ ነው፡፡

ቀደም ብለው በነበሩት ዘመናት እጅግ ብዙ የአዲስ ኪዳን ትርሞች በላቲን ቋንቋ ተዘጋጅተው ነበር፡፡ እነዚህም ደግሞ በአውጉስጢኖስና በጀሮም ጽሑፎች ውስጥ ተጠቅሰዋል፡፡ የኋለኛው እንደሚነግረን ከሆነ በአንዳንድ ሁኔታዎች ከነዚህ ትርሞች መካል አንዳንዶቹ ትክክል አልነበሩም ምክንያቱም አንዳንድ ዕውቀት የጎደላቸው ሰዎች ለራሳቸው ዓላማ ሲሉ አዘጋጅተዋቸዋልና፡፡ ከነዚህ መካከል ምርጡ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን የተዘጋጀው ኢጣላ ወይንም ደግሞ ቀደምት የላቲን ቅጂ የሚባለው ነው፡፡ በተሻለ ሁኔታ ትክክል የሆነ ትርጉም አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ በ383ና 385 ዓ.ም. መካከል ጀሮም አዲስ ኪዳንን ወደዚህ ቋንቋ ተርጉሞ ነበር፡፡ የዚህ ትርጉም ቢያንስ 8,000 ጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች አሉን፡፡ የቩልጌት (التّرجمة العاميّة) ላቲን ቅጂ በመባል ይታወቃል፡፡ ከነዚህ የእጅ ጽሑፎች መካከል አንዳንዶቹ ከአራተኛው፣ አምስተኛውና ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የሆኑ ናቸው፡፡ ከሙሐመድ ዘመን በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ላቲን መተርጎሙ ብቻ ሳይሆን የዚህ ትጉም የእጅ ጽሑፎች በሙሐመድ ዘመን እንኳ እድሜ ጠገብት መሆናቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡

ቀደም ሲል እንዳልነው በጥንት ዘመን የብሉይ ኪዳን ትርጉም በሦስት የኮፕቲክ (ቅብጥ) ዘዬዎች ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ አዲስ ኪዳንም እንዲያው ነው፡፡ የቡሃይሪኛ (البُحَيْرِي) ቅጂ በአራተኛውና አምስተኛው ክፍለ ዘመን መካል የተዘጋጀ ነበር፡፡ የሳዒዲኛውም (الصَعِيدي) በተመሳሳይ ዘመን፡፡ ሦስተኛው ወይንም ደግሞ የቡሽሙርኛው (الصَعِيدي) ዘዬ በሦስት ንዑስ ዘዬዎች ይከፈላል፡፡ እነርሱም ፈዩሚኛ (الفيومي) ታህታይ ሳዒዲኛና አክሚሚኛ (الاخميمي) ናቸው፡፡ የሳዒዲኛው ቅጂ ምናልባትም ከሁሉም ቀዳሚው ነው፡፡ እድሜ ጠገቡ የኮፕቲክ አዲስ ኪዳን ከአራተኛውና አምስተኛው ክፍለ ዘመን የሆነ ነው፡፡

የጎቲክ ቅጂ የተዘጋጀው በ360 ዓ.ም. አካባቢ ነበር፡፡ አሁን ያለው የእጅ ጽሑፍ ደግሞ በአምስተኛው ወይንም ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተዘጋጀ ነው፡፡

በተለያዩ ቋንቋዎች ከተጻፉት የእጅ ጽሑፎች በተጨማሪ በእጃችን የሚገኙት ብሉና አዲስ ኪዳናት በሙሐመድ ዘመንና ከዚያ በፊት የነበሩ መሆናቸውን የሚረጋግጥ ሌላ ማስረጃም አለን፡፡ ይህም ማስረጃ በቀደሙት ክርስቲያኖች ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት ጥቅሶች ናቸው፡፡ ጽሑፎቻቸው አንዳንዶቹ በግሪክ፣ አንዳንዶቹ በላቲን፣ አንዳንዶቹ በሦርያንኛ፣ አንዳንዶቹ በቅጵጥና ሌሎቹ ደግሞ በአርመንኛ ናቸው፡፡ ልክ በአረብኛ፣ ፋርስኛ፣ ኡርዱ፣ ቱርክኛና ሌሎች ቋንቋዎች በጻፉ ሙስሊም ጸሐፊያን ጽሑፎች ውስጥ የቁርኣን ጥቅሶች እንደሚገኙ ሁሉ በጣም ብዙ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችም በነዚህ ክርስቲያኖች ጽሑፎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ሁሉም የቁርኣን ኮፒ ቢጠፋብን አብዛኛውን ክፍል ወይንም ሁሉንም ከነዚህ ጽሑፎች መልሰን መጻፍ እንችላለን፡፡ ልክ እንደዚሁ አዲስ ኪዳን ሙሉ በሙሉ ቢወድም ከሙሐመድ ዘመን በፊት ከነዚህ የመጀመርያዎቹ ጥቂት ክፍለ ዘመናት ከተጻፉ ጽሑፎች ሙሉ በሙሉ መልሰን ልንጽፈው እንችላለን፡፡ ጥቂት ጥቅሶችም ሴልሰስ፣ ፖርፊሪና ጁሊያን ከሃዲውን በመሳሰሉ አሕዛቦች ተጠቅሰዋል፡፡ ከቀጥተኛ ጥቅሶች በተጨማሪም ሁሉም ክርስቲያን ጸሐፍት የክርስቶስን ስቅለት፣ ትንሣኤና እርገቱን የመሳሰሉ በወንጌላት ውስጥ የሰፈሩትን የክርስቶስ ቅደም ተከተላዊ ሕይወት ታሪኮች ጠንቅቀው ያውቁ ነበር፡፡ ይህ ቀደም ሲል ከጠቀስነው ማስረጃ የተለየ ሲሆን ተጨማሪ ድጋፍ ነው፡፡

በተጨማሪም በሮም ከተማ ስር በሚገኘው ካታኮምብ በመባል በሚታወቀው ዋሻ ውስጥ የሁለተኛው፣ ሦስተኛውና አራተኛው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች መቃብሮች ተገኝተዋል፡፡ በነዚህ መቃብሮች ላይ የሚገኙት ጽሑፎችና ስዕሎች በዚያ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ዛሬ በእጃችን በሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አስተምህሮዎችን ይከተሉ እንደነበሩ ያረጋግጣሉ፡፡

ከሙሐመድ በፊት በጣም ቀደም ብሎ ክርስቲያኖችና አይሁዶች ግልጠተ መለኮት የሆኑትን የቅዱሳት መጻሕፍ ዝርዝር ቀኖና ማስቀመጣቸውና እነዚህም መጻሕፍት ዛሬ በዝውውር ውስጥ በሚገኙትና ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች በተተረጎሙ ብሉይና አዲስ ኪዳናት ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ከጥርጣሬ በጸዳ ሁኔታ ተረጋግጧል ማለት  ነው፡፡

ስለዚህ ቁርኣን ሙሐመድን “በመጽሐፉ” ውስጥ የሚገኙ ትምህርቶችን በተመለከተ “የመጽሐፉን ሰዎች” እንዲጠይቅ ሲነግረው አሁን የክርስቲያኖችና የአይሁዶች ቅዱሳት መጻሕፍት ከሆኑት ብሉይና አዲስ ኪዳናት የተለየ መጽሐፍ ሊሆን አይችልም፡፡ በመጀመርያው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው ቁርኣን ቀኖናዊ መጻሕፍትን ቶራህ፣ ዘቡር፣ ነቢያትና ኢንጂል በማለት ይከፍላቸዋል እንዲሁም ጥቅሶችን ከነርሱ ውስጥ ይጠቅሳል፡፡ ቁርኣን መጽሐፍ ቅዱስን የፈጣሪ ቃል (كلام الله)፣ የፈጣሪ መጽሐፍ፣ የፉርቃን መጽሐፍ (فرقان) ወይን መለክያ፣ ዚኪር (ذِكر) ወይንም አስታዋሽ  በማለት በመጥራት ትልልቅ የማዕረጋት መጠርዎችን ይሰጠዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የማያከብሩትን ሰዎች በሚመጣው ዓለም አስፈሪ ቅጣት እንደሚደርስባቸው ቁርኣን ያስጠነቅቃል (ሱራ 11፡72)፡፡ ቁርኣን ይህንን መጽሐፍ ለማረጋገጥ (ሱራ 3፡2)ና ለመጠበቅ  (ሱራ 3፡5) እንደተላከ በግልፅ ይናገራል፡፡ ሙስሊሞችም ልክ በቁርኣን እንደሚያምኑት ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስም እንዲያምኑ ታዘዋል (ሱራ 2፡130፣ 3፡78)፡፡

ስለዚህ አሁን በአይሁዶችና በክርስቲያኖች እጅ የሚገኙት ብሉይና አዲስ ኪዳናት በሙሐመድ ዘመን የነበሩና ቁርኣን የሚመሰክርላቸው መሆኑ ስለተረጋገጠ ሙስሊሞች ሁሉ “አብርሆት የሚሰጠውን” “የፈጣሪን መጽሐፍ” (ሱራ 35፡23) መረዳት ይችሉ ዘንድ እንዲረዳቸው እንዲሁም “ልባም ለሆኑ ሰዎች የሚሰጠውን ምሪትና ግሳፄ” ያገኙ ዘንድ ቸር ወደሆነው አምላክ ከልባቸው መጸለይ ያስፈልጋቸዋል፡፡[17]

[1] Pirqey Abhoth, i. I.

[2] Those mentioned in Joshua xxiv. 31.

[3]  Pirqey Abhoth, i. I.

[4] Pirqey Abhoth i. 2.

5 Against Apion, Bk. I, chap. viii

[6] ዘፍጥረት፣ ዘጸአት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኁልቁ፣ ዘዳግም፡፡

[7] ኢያሱ፣ መሳፍንትና ሩት፣ ሳሙኤል፣ ነገስት፣ ዜና መዋዕል፣ እዝራና ነህምያ፣ አስቴር፣ ኢዮብ፣ አስራ ሁለት አነስተኛ ነቢያት፣ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ እና ሰቆቃወ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ዳንኤል፡፡

[8] መዝሙር፣ ምሳሌ፣ መክብብ፣ መኃልየ መኃልይ፡፡

[9] ሆሴዕ፣ ኢዩኤል፣ አሞፅ፣ አብድዩ፣ ዮናስ፣ ሚክያስ፣ ናሆም፣ ዕንባቆም፣ ሶፎንያስ፣ ሐጌ፣ ዘካርያስ፣ ምልክያስ፡፡

[10] Antiquities of the Jews, Bk. xii, cap. 2: Against Apion, ii. 4.

[11] በ536 ዓ.ዓ. ነበር የተጠናቀቀው

[12] For various theories about the “Descent” of the Qur’an, see the Kashfu’z Zunun, vol. ii, p. 340, printed at Constantinople, A.H. 1310

[13] In Arabic called مصادر الإسلام; in Persian ينابيع الإسلام; in Urdu also it bears this latter name.

[14] Mishkat, pp. 185 sqq.

[15] ይህ የካርል ፋንደር መጽሐፍ የተጻፈው ከረጅም ዘመናት በፊት በመሆኑ በ1947 ዓ.ም. በቁምራን ስለተገኙት የብሉይ ኪዳን ጽሑፎች በዚያን ዘመን የሚታወቅ ነገር አልነበረም፡፡ በሙት ባሕር አካባቢ በሚገኘው በዚህ ቦታ ከመጽሐፈ አስቴር በተረፈ በእብራይስጥ፣ በግሪክ እና በአረማይክ የተጻፉ ሁሉም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ተገኝተዋል፡፡ የተጻፉት ደግሞ በ250 ዓ.ዓ. እና በ68 ዓ.ም. መካከል ነበር፡፡

[16] ان بقاء الْقرطاس والْحرف على الف واربع مأية او ازيد مستبعد عادةً‫.

Izharu’l Haqq, p. 245 of vol. i

[17] هُودىَّ وَذِكْرىَ لأِولِي الأْلبَابِ‫ ሱራ 11፡56