ተውራትና ኢንጅል መጽሐፍ ቅዱስ ናቸውን?

ተውራትና ኢንጅል መጽሐፍ ቅዱስ ናቸውን?

አንዳንድ ሙስሊም ሰባኪያን ተውራት ለነቢዩ ሙሴ፣ ኢንጅል ደግሞ ለኢየሱስ የተሰጡ መጻሕፍት በመሆናቸው በዚህ ዘመን በሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሉም የሚል ሙግት ያቀርባሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ቁርአን የጠቀሳቸው ተውራትና ኢንጅል ለሙሴና ለኢየሱስ የተሰጡ መጻሕፍት እንጂ በሌሎች ነቢያትና በኢየሱስ ሐዋርያት የተጻፉ ባለመሆናቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሊገኙ አይችሉም ይላሉ፡፡ ይህ ሙግት በደካማ አመክንዮ ላይ የተመሠረተ፣ ከታሪክ፣ ከቁርአንና ከእስላማዊ  ትውፊቶች ጋር የሚጣረስ ልፍስፍስ ሙግት ነው፡፡

ይህንን ሙግት በጥልቀት ከማጤናችን በፊት ኢንጅልና ተውራትን በተመለከተ ክርስቲያናዊውን አቋም ግልፅ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ 

(በነገራችን ላይ ቁርአን ዒሳ ኢንጅል የተሰኘ መጽሐፍ ከአላህ እንደወረደለት ቢናገርም ለሙሴ ግን መጽሐፍ እንደወረደለት እንጂ ተውራት የተሰኘ መጽሐፍ እንደወረደለት አይናገርም፡፡ በአማርኛ ትርጉም በቅንፍ የተጨመሩት በአረብኛ ቁርአን ውስጥ አይገኙም፡፡)

ተውራት ለሚለው የአረብኛ ቃል መነሻ የሆነው በነጠላ “ቶራህ”፣ በብዙ ቁጥር ደግሞ “ቶሮት”  የሚለው የእብራይስጥ ቃል ትርጉሙ ሕግ ወይም ሕግጋት ማለት ሲሆን አምስቱን የሙሴ መጻሕፍትንም ሆነ አጠቃላዩን ብሉይ ኪዳንን ለማመልከት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡

በክርስቶስ ዘመን የነበሩት አይሁድ ብሉይ ኪዳንን ለሦስት በመክፈል ሕግ፣ ነቢያትና መዝሙራት በማለት ይጠሩ ነበር፡፡ ጌታ ኢየሱስም ለዚህ አከፋፈል ዕውቅናን ሰጥቷል፡-

“እርሱም፦ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው።” (ሉቃስ 24፡44)

የሙሴ ሕግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ ሕግ (ቶራህ) ተብሎ ተጠርቷል፡፡

“በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ምድር ሙሴ እንዲህ ብሎ ይህችን ሕግ (ቶራህ) ይገልጥ ጀመር።” (ዘዳግም 1፡5)

“ነገር ግን ጽና፥ እጅግ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ (ቶራህ) ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። የዚህ ሕግ መጽሐፍ (ሴፌር ቶራህ) ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም።” (ኢያሱ 1፡7-8)

“በርታ ሰውም ሁን፤ የምታደርገውንና የምትሄድበትን ሁሉ ታከናውን ዘንድ፥ በሙሴ ሕግ (ቶራህ) እንደ ተጻፈ ሥርዓቱንና ትእዛዛቱን ፍርዱንና ምስክሩንም ትጠብቅ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ፥ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ።” (1ነገሥት 2፡3)

“ለእስራኤል ሁሉ ሥርዓትንና ፍርድን አድርጌ በኮሬብ ያዘዝሁትን የባሪያዬን የሙሴን ሕግ (ቶራህ) አስቡ።” (ሚልክያስ 4፡4)

ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት “ቶራህ” የሚለው ቃል አምላካዊ ሕግጋትን በሙሉ የሚገልፅ ቃል ሆኖ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ከሙሴ መጻሕፍት ውጪ የሚገኙትን ቅዱሳት መጻሕፍት “ሕግ” ወይም “ቶራህ” በማለት ጠርቷል፡-

“ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ እኔ፦ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን?…” (ዮሐንስ 10፡34)

በዚህ ቦታ ጌታ ኢየሱስ የጠቀሰው መዝሙረ ዳዊትን ቢሆንም “ሕግ” ብሎታል፡፡ ይህም ቃሉ በሙሴ መጻሕፍት ብቻ ያልተወሰነና ሕገ እግዚአብሔርን በሞላ የሚያሳይ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ቃሉ በሌሎች ነቢያት በኩል የተሰጡ መለኮታዊ ትዕዛዛትን እንደሚያካትት የሚያሳዩ ጥቅሶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ፡-

“እናንተ የሰዶም አለቆች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ፥ የአምላካችንን ሕግ አድምጡ። የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል? ይላል እግዚአብሔር፤ የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፤ የበሬና የበግ ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም።” (ኢሳይያስ 1፡10-11)

ሕግ ከጽዮን የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው፦ ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ።” (ኢሳይያስ 2፡3)

“ከሠሩትም ሥራ ሁሉ የተነሣ ቢያፍሩ፥ የቤቱን መልክና ምሳሌውን መውጫውንም መግቢያውንም ሥርዓቱንም ሕጉንም ሁሉ አስታውቃቸው፤ ሥርዓቱንና ሕጉን ሁሉ ይጠብቁ ዘንድ ያደርጉትም ዘንድ በፊታቸው ጻፈው። የቤቱ ሕግ ይህ ነው፤ በተራራው ራስ ላይ ዳርቻው ሁሉ በዙሪያው ከሁሉ ይልቅ የተቀደስ ይሆናል። እነሆ፥ የቤቱ ሕግ ይህ ነው። የመሠዊያውም ልክ በክንድ ይህ ነው፥ ክንዱም ክንድ ተጋት ነው። የመሠረቱም ቁመቱ አንድ ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፥ አንድ ስንዝርም ክፈፍ ዳር ዳሩን በዙሪያው አለ የመሠዊያው መሠረት እንዲሁ ነው።” (ሕዝቅኤል 43፡11-13)

“እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ልብ አድርግ ስለ እግዚአብሔርም ቤት ሥርዓትና ሕግ ሁሉ የምናገርህን ሁሉ በዓይንህ ተመልከት በጆሮህም ስማ፤ የቤቱንም መግቢያ የመቅደሱንም መውጫ ሁሉ ልብ አድርግ።” (ሕዝቅኤል 44፡5)

ከላይ በተጠቀሱት ጥቅሶች ውስጥ “ሕግ” የተባለው እግዚአብሔር በነቢያቱ በኩል ያስተላለፈው ቃል መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ “ቶራህ” የሚለው ቃል በሙሴ ሕግ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን መለኮታዊ ሕግጋትን በሙሉ የሚያጠቃልል ነው፡፡

ኢንጅል የሚለው የአረብኛ ቃል በግሪክ “ኢዋንጌሊዮን” ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜው መልካም ዜና ወይንም የምሥራች ማለት ነው፡፡ የአረብኛው ቃል ከሦርያ አነባበብ የተወሰደ መሆኑን ሊቃውንት ይናገራሉ (Arthur Jeffery, The Foreign Vocabulary of the Quran, pp. 71-72)፡፡

እስልምና ኢየሱስ ወንጌል የተባለ መጽሐፍ ከአላህ ዘንድ እንደተቀበለ ቢያስተምርም ለዚህ ድጋፍ የሚሰጥ የመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የታሪክ ማስረጃ የለም፡፡ ልክ እንደ “ቶራህ” ሁሉ ይህም ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ጥቅም ላይ ውሏል፡-

“የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ።” (ማርቆስ 1፡1)

“ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና፦ ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ እያለ ወደ ገሊላ መጣ።” (ማርቆስ 1፡14-15)

“ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24፡14)

“እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል።” (ማቴዎስ 26፡13)

“ፊልጶስም አፉን ከፈተ፥ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት።” (የሐዋርያት ሥራ 8፡35)

“ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ጳውሎስ በነቢያቱ አፍ በቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ለሰጠው ለእግዚአብሔር ወንጌል ተለየ። ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።” (ሮሜ 1፡1-3)

ከላይ በተጠቀሱት ጥቅሶች መሠረት የወንጌል ምንጭ እግዚአብሔር ነው፤ ወንጌሉ ደግሞ ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ይህ ወንጌል መጀመርያ በኢየሱስ በራሱ የተሰበከ ሲሆን ሐዋርያቱ በእርሱ ትዕዛዝ መሠረት ለአይሁድም ሆነ ለአሕዛብ ሰብከዋል፤ በመጽሐፍ የሰፈረውም ይኸው ወንጌል ነው፡፡

አራቱ ወንጌላት ብለን የምንጠራቸው የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በተለያዩ አራት ሰዎች የተጻፈ አንዱ ወንጌል እንጂ የተለያዩ ወንጌላት አይደሉም፡፡ ለዚህ ነው በመግቢያቸው ላይ “ወንጌል ማቴዎስ እንደጻፈው፣ ወንጌል ማርቆስ እንደጻፈው፣ ወንጌል ሉቃስ እንደጻፈው፣ ወንጌል ዮሐንስ እንደጻፈው” የሚል ርዕስ የተሰጣቸው፡፡ አንዱ ወንጌል ነው በተለያዩ ሰዎች የተጻፈው፡፡ “ለዒሳ የተሰጠ ኢንጅል የተሰኘ መጽሐፍ አለ” የሚለው እስላማዊ አስተምሕሮ መሠረተ ቢስ ፈጠራ ነው፡፡

ይህን ካልን ዘንዳ ቁርአን የጠቀሳቸው ተውራትና ኢንጅል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሉም የሚለው የሙስሊም ሰባኪያን ሙግት እስከ ምን እንደሚያስኬዳቸው እንመለከታለን፡፡ ይህ ሙግት በተከታዮቹ 4 ምክንያቶች ተቀባይነት የለውም፡-

  1. በደካማ አመክንዮ ላይ የተመሠረተ ነው

ይህ ሙግት “ቁርአን እውነተኛ መለኮታዊ መገለጥ ነው” በሚል ያልተረጋገጠ ቅድመ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡ ቁርአን ተውራትና ኢንጂል የተሰኙ መጻሕፍትን ቢጠቅስም “የመጽሐፉ ባለቤቶች” ተብለው በቁርአን የተጠቀሱት አይሁድና ክርስቲያኖች ቶራህና ወንጌል ብለው የሚጠሯቸው መጻሕፍት በቁርአን ውስጥ ከተጠቀሱት ተውራትና ኢንጅል ጋር አይመሳሰሉም፡፡ ነገር ግን አለመመሳሰላቸው ተውራትና ኢንጅል የሉም ወይንም በቁርአን የተጠቀሱት ተውራትና ኢንጅል በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ የሚገኙት አይደሉም ወደሚል ድምዳሜ አይመራም፡፡ ምክንያታዊውና ቀላሉ ምላሽ የቁርአን ጸሐፊ ስለ ተውራትና ኢንጅል የነበረው ግንዛቤ ስህተት ነበር የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ኃይለ ሥላሴ የተሰኙ የኢትዮጵያ ንጉሥ ቁመታቸው ረዥም፣ አፍንጫቸው ጎራዳ፣ የቆዳ ቀለማቸው ነጭ፣ ወዘተ. እያለ ኃይለ ሥላሴን ቢገልጻቸው፤ በታሪክ የሚታወቁት ኃይለ ሥላሴ ቁመታቸው አጠር ያለ፣ አፍንጫቸው ሰልካካ፣ የቆዳ ቀለማቸውም የቀይ ዳማ በመሆኑ ታሪክ የሚያውቃቸው ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ትክክለኛው አይደሉም ወይም ሰውየው የጠቀሳቸው ኃይለ ሥላሴ ሌላ ናቸው ማለት ቂልነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የሚታወቁት ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ አንድ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ብቻ ናቸው፡፡ ትክክለኛው ድምዳሜ ኃይለ ሥላሴን ለመግለፅ የሞከረው ሰው ቀባዥሯል የሚል ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ በታሪክ የሚታወቁት ተውራትና ኢንጅል በክርስቲያኖችና በአይሁድ እጅ የሚገኙት በመሆናቸው የቁርአን ጸሐፊ ተውራትና ኢንጅልን የገለጸበት መንገድ ስህተት ነው፡፡ ስለዚህ የቁርአን ጸሐፊ ስህተት አለመሥራቱ እስካልተረጋገጠና በቁርአን የተጠቀሱትን ተውራትና ኢንጅል የሚመስሉ መጻሕፍት በታሪክ ስለመኖራቸው ማስረጃ እስካልቀረበ ድረስ በታሪክ የታወቁትን ቶራህና ወንጌል ህልውናቸውን መካድ በየትኛውም የአመክንዮ ሕግ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ይህ ወደ ሁለተኛው ነጥባችን ይወስደናል፡፡

  1. ከታሪካዊ ማስረጃዎች ጋር ይጣረሳል

ቶራህና ወንጌልን የሚጠቅሱት የታሪክ ማስረጃዎችና የአርኪዎሎጂ ውጤቶች በሙሉ እንደሚያመለክቱት ለህልውናቸው ማስረጃ ያላቸውና ከሙሴና ከኢየሱስ ዘመን ተያይዘው የመጡት ብቸኛ ቶራህና ወንጌል በክርስቲያኖች እጅ በሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ናቸው፡፡ ቁርአን የገለጻቸው ዓይነት ተውራትና ኢንጅል ምንም ዓይነት ታካዊም ሆነ የአርኪዎሎጂ ማስረጃ የላቸውም! በዓለማውያንም ሆነ በአማኝ የነገረ መለኮት ሊቃውንት ምስክርነት መሠረት ብቸኛ ተውራትና ወንጌል አይሁድና ክርስቲያኖች የተቀበሏቸው ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ስለ እምነታቸው ዕውቀት ያላቸው ሙስሊም ሊቃውንት ተውራት በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኙት የሙሴ መጻሕፍትና[1] ኢንጅል ደግሞ አዲስ ኪዳን መሆናቸውን[2] አምነው የተቀበሉት፡፡ እነዚህ ሊቃውንት ተውራትና ኢንጅል ተበርዘው እንጂ ዛሬ በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ ከሚገኙት መጻሕፍት የተለዩ አይደሉም ይላሉ፡፡ ይህ የብረዛ ክስ በራሱ ማስረጃ አልባ አሉባልታ ቢሆንም ተውራትና ኢንጅል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሉም ከሚለው አመለካከት የተሻለ ትርጉም ይሰጣል፡፡ ተውራትና ኢንጅል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት አይደሉም የሚለው አመለካከት የረባ ዕውቀት በሌላቸውና እስልምናን ከትችት ለመከላከል የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ በሚገኙት ሙስሊም አቃቤ እምነታቸውያን ዘንድ ብቻ የሚቀነቀን ሲሆን በማስከተል እንደምንመለከተው በቁርአንም ሆነ በእስላማዊ ትውፊቶች ምንም ዓይነት ድጋፍ የሌለው ለአቅመ ውይይት እንኳ የማይበቃ ሙግት ነው፡፡

  1. ከቁርአን ጋር ይጣረሳል

በቁርአን መሠረት ተውራትና ኢንጅል በመሐመድ ዘመን በነበሩት አይሁድና ክርስቲያኖች እጅ የነበሩ ሲሆን የቁርአን ጸሐፊ የነዚህን መጻሕፍት ሐቀኝነት በማረጋገጥ አይሁድና ክርስቲያኖች እንዲጠቀሙባቸው ያበረታታቸዋል፡፡ ማስረጃዎቹን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡-

ሀ. መጽሐፉ በመሐመድ ዘመን በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ ነበር፡-

“የእስራኤል ልጆች ሆይ! ያችን በናንተ ላይ የለገስኳትን ጸጋዬን አስታውሱ፡፡ በቃል ኪዳኔም ሙሉ፤ በቃል ኪዳናችሁ እሞላለሁና፤ እኔንም ብቻ ፍሩ፡፡ ከናንተ ጋር ያለውን (መጽሐፍ) የሚያረጋግጥ ሆኖ ባወረድኩትም (ቁርኣን) እመኑ፡፡ በርሱም የመጀመሪያ ከሓዲ አትሁኑ፡፡ በአንቀጾቼም ጥቂትን ዋጋ አትለውጡ፡፡ እኔንም ብቻ ተጠንቀቁ፡፡” (ሱራ 2፡40-41)

ከነሱም ጋር ያለውን (መጽሐፍ) አረጋጋጭ የኾነ መጽሐፍ ከአላህ ዘንድ በመጣላቸው ጊዜ (ከመምጣቱ) በፊት በነዚያ በካዱት ላይ ይረዱበት የነበሩ ሲኾኑ ያወቁት ነገር በመጣላቸው ጊዜ በርሱ ካዱ፡፡ የአላህም ርግማን በከሓዲዎች ላይ ይኹን፡፡” (ሱራ 2፡89)

“አላህም ባወረደው (ሁሉ) ለእነርሱ «እመኑ» በተባሉ ጊዜ «በኛ ላይ በተወረደው (መጽሐፍ ብቻ) እናምናለን» ይላሉ፡፡ ከርሱ ኋላ ባለው (ቁርአን) እርሱ ከነሱ ጋር ላለው (መጽሐፍ) አረጋጋጭ እውተኛ ሲኾን ይክዳሉ፡፡ «አማኞች ከኾናችሁ ከአሁን በፊት የአላህን ነቢያት ለምን ገደላችሁ?» በላቸው፡፡” (ሱራ 2፡91)

እነርሱ ጋርም ላለው (መጽሐፍ) አረጋጋጭ የኾነ መልክተኛ ከአላህ ዘንድ በመጣላቸው ጊዜ ከነዚያ መጽሐፍን ከተሰጡት ከፊሉ እነርሱ እንደማያውቁ ኾነው የአላህን መጽሐፍ ከጀርባዎቻቸው ኋላ ጣሉ፡፡” (የላም ምዕራፍ 2፡101) በተጨማሪም 3:81; 4:47; 5:43; 16:43-44; 21:7 ይመልከቱ፡፡

ለ. መሐመድና አድማጮቹ መጽሐፉን የሚያነቡትን እንዲጠይቁ አላህ አዟቸዋል

“ወደ አንተም ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን እነዚያን ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ፡፡ እውነቱ ከጌታህ ዘንድ በእርግጥ መጥቶልሃል፡፡ ከተጠራጣሪዎቹም አትሁን፡፡” (ሱራ 10፡94)

“ከአንተም በፊት ወደእነሱ የምናወርድላቸው የኾነን ሰዎችን እንጂ ሌላን አላክንም፡፡ የማታውቁም ብትኾኑ የመጽሐፉን ባለቤቶች ጠይቁ፡፡” (ሱራ 21፡7)

ሐ. አይሁድና ክርስቲያኖች መጽሐፉን የማንበብ ዕድል ነበራቸው፡-

“ከኋላቸውም፡- መጽሐፉን የወረሱ መጥፎ ምትኮች ተተኩ፡፡ የዚህን የቅርቡን ጠፊ ጥቅም ይይዛሉ፡፡ ብጤውም ጥቅም ቢመጣላቸው የሚይዙት ሲኾኑ « (በሠራነው)፡- ለኛ ምሕረት ይደረግልናል» ይላሉ፡፡ በአላህ ላይ ከእውነት በቀር እንዳይናገሩ በእነርሱ ላይ የመጽሐፉ ቃል ኪዳን አልተያዘባቸውምን? በእርሱ ውስጥ ያለውንም አላነበቡምን? የመጨረሻይቱም አገር ለእነዚያ ጌታቸውን ለሚፈሩት በላጭ ናት፡፡ አታውቁምን?” (ሱራ 7፡169)

እናንተ መጽሐፉን የምታነቡ ሆናችሁ ሰዎችን በበጎ ሥራ ታዛላችሁን? ነፍሶቻችሁንም ትረሳላችሁን? (የሥራችሁን መጥፎነት) አታውቁምን?” (2፡44) “Do you order righteousness of the people and fnetet yourselves while you recite the Scripture? Then will you not reason?”

እነርሱ መጽሐፉን የሚያነቡ ሲኾኑ አይሁዶች፡- ክርስቲያኖች በምንም ላይ አይደሉም አሉ፡፡ ክርስቲያኖችም፡- አይሁዶች በምንም ላይ አይደሉም አሉ፡፡ እንደዚሁ እነዚያ የማያውቁት (አጋሪዎች) የንግግራቸውን ብጤ አሉ፡፡ አላህም በዚያ በርሱ ይለያዩበት በነበሩት ነገር በትንሣኤ ቀን በመካከላቸው ይፈርዳል፡፡” (2፡113)

“እነዚያ መጽሐፉን የሰጠናቸው ተገቢ ንባቡን ያነቡታል፡፡ እነዚያ በርሱ ያምናሉ፤ በርሱም የሚክዱ እነዚያ እነርሱ ከሳሪዎቹ ናቸው፡፡” (ሱራ 2፡121)

“ተውራት ከመወረድዋ በፊት እስራኤል በራሱ ላይ እርም ካደረገው ነገር በስተቀር ምግብ ሁሉ ለእስራኤል ልጆች የተፈቀደ ነበር፡፡ እውነተኞችም እንደኾናችሁ ተውራትን አምጡ አንብቡዋትም በላቸው፡፡” (ሱራ 3፡93)

“(የመጽሐፉ ሰዎች ሁሉ) እኩል አይደሉም፡፡ ከመጽሐፉ ሰዎች ቀጥ ያሉ በሌሊት ሰዓቶች እነርሱ የሚሰግዱ ኾነው የአላህን አንቀጾች የሚያነቡ ሕዝቦች አሉ፡፡” (ሱራ 3፡113)

መ. አይሁድና ክርስቲያኖች የተሰጣቸውን መጽሐፍ መታዘዝ ይኖርባቸዋል፡-

እነርሱም ተውራትንና ኢንጂልን ከጌታቸውም ወደእነሱ የተወረደውን መጽሐፍ ባቋቋሙ (በሠሩበት) ኖሮ ከበላያቸውና ከእግሮቻቸው ሥር በተመገቡ ነበር፡፡ ከእነሱ ውስጥ ትክክለኞች ሕዝቦች አልሉ፡፡ ከእነሱም ብዙዎቹ የሚሠሩት ነገር ከፋ!” (ሱራ 5፡66)

“«እናንተ የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! ተውራትንና ኢንጂልን ከጌታችሁም ወደእናንተ የተወረደውን እስከምታቆሙ (እስከምትሠሩባቸው) ድረስ በምንም ላይ አይደላችሁም» በላቸው፡፡ ከጌታህም ወደ አንተ የተወረደው ቁርኣን ከእነሱ ብዙዎቹን ትዕቢትንና ክህደትን በእርግጥ ይጨምርባቸዋል፡፡ በከሓዲያን ሕዝቦችም ላይ አትዘን፡፡” (ሱራ 5፡68)

ሠ. በመካከላቸው ያለውን ሙግት መፍታት ያለባቸው በቁርአን ሳይሆን በመጽሐፋቸው ነው፡-

እነርሱም ዘንድ ተውራት እያለች በውስጧ የአላህ ፍርድ ያለባት ስትኾን እንዴት ያስፈርዱሃል! ከዚያም ከዚህ በኋላ እንዴት ይሸሻሉ! እነዚያም በፍጹም ምእምናን አይደሉም፡፡ እኛ ተውራትን በውስጥዋ መምሪያና ብርሃን ያለባት ስትኾን አወረድን፡፡ እነዚያ ትዕዛዝን የተቀበሉት ነቢያት በእነዚያ አይሁዳውያን በኾኑት ላይ በርሷ ይፈርዳሉ፡፡ ሊቃውንቱና ዐዋቂዎቹም ከአላህ መጽሐፍ እንዲጠብቁ በተደረጉትና በርሱም ላይ መስካሪዎች በኾኑት (ይፈርዳሉ)፡፡ ሰዎችንም አትፍሩ፡፡ ፍሩኝም፡፡ በአንቀጾቼም አነስተኛን ዋጋ አትለውጡ፡፡ አላህም ባወረደው ነገር ያልፈረደ ሰው እነዚያ ከሓዲዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡” (ሱራ 5፡43-44)

የኢንጂልም ባለቤቶች በውስጡ አላህ ባወረደው ሕግ ይፍረዱ፡፡ አላህም ባወረደው የማይፈርድ ሰው እነዚያ አመጸኞች እነርሱ ናቸው፡፡” (ሱራ 5፡47)

ረ. አይሁድና ክርስቲያኖች ተውራትንና ኢንጂልን ከታዘዙ ይባረካሉ፡-

እነርሱም ተውራትንና ኢንጂልን ከጌታቸውም ወደእነሱ የተወረደውን መጽሐፍ ባቋቋሙ (በሠሩበት) ኖሮ ከበላያቸውና ከእግሮቻቸው ሥር በተመገቡ ነበር፡፡ ከእነሱ ውስጥ ትክክለኞች ሕዝቦች አልሉ፡፡ ከእነሱም ብዙዎቹ የሚሠሩት ነገር ከፋ!” (ሱራ 5፡65)

ሰ. ሙስሊሞች በቀደሙት መገለጦች ማመን ይጠበቅባቸዋል፡-

“ለእነዚያም ወደ አንተ በተወረደውና ከአንተ በፊትም በተወረደው የሚያምኑ በመጨረሻይቱም (ዓለም) እነርሱ የሚያረጋግጡ ለኾኑት (መሪ ነው)፡፡” (ሱራ 2፡4)

“«በአላህና ወደኛ በተወረደው (ቁርኣን) ወደ ኢብራሂምም ወደ ኢስማዒልና ወደ ኢስሐቅም ወደ ያዕቁብና ወደ ነገዶቹም በተወረደው በዚያም ሙሳና ዒሳ በተሰጡት በዚያም ነቢያት ሁሉ ከጌታቸው በተሰጡት ከነርሱ በአንድም መካከል የማንለይ ስንኾን አመንን፤ እኛም ለርሱ (ለአላህ) ታዛዦች ነን» በሉ፡፡” (ሱራ 2፡136)

“መልክተኛው ከጌታው ወደ ርሱ በተወረደው አመነ፡፡ ምእምኖቹም (እንደዚሁ)፡፡ ሁሉም በአላህ፣ በመላዕክቱም፣ በመጻሕፍቱም፣ በመልክተኞቹም ከመልክተኞቹ «በአንድም መካከል አንለይም» (የሚሉ ሲኾኑ) አመኑ፡፡ «ሰማን፤ ታዘዝንም፡፡ ጌታችን ሆይ! ምሕረትህን (እንሻለን)፡፡ መመለሻም ወዳንተ ብቻ ነው» አሉም፡፡” (ሱራ 2፡285)

“«በአላህ አመንን፡፡ በእኛ ላይ በተወረደውም (በቁርኣን)፣ በኢብራሂምና በኢስማዒልም፣ በኢስሓቅም፣ በያዕቆብም፣ በነገዶችም ላይ በተወረደው፤ ለሙሳና ለዒሳም ለነቢያትም ሁሉ ከጌታቸው በተሰጠው (አመንን)፡፡ ከእነርሱ መካከል አንድንም አንለይም፡፡ እኛ ለእርሱ ታዛዦች ነን» በል፡፡” (ሱራ 3፡84)፣ በተጨማሪም 3፡119; 4:136; 5:59; 28:49; 29:46

ከላይ እንዳየነው በቁርአን መሠረት ተውራትና ኢንጅል በመሐመድ ዘመን በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ ነበሩ፤ መሐመድና አድማጮቻቸው የመጽሐፉን አንባቢዎች እንዲጠይቁ አላህ አዟቸዋል፤ አይሁድና ክርስቲያኖች መጽሐፉን የማንበብ ዕድል ነበራቸው፤ አይሁድና ክርስቲያኖች የተሰጣቸውን መጽሐፍ መታዘዝ እንደሚኖርባቸው ተነግሯል፤ በመካከላቸው ያለውን ሙግት እንኳ ለመፍታት የገዛ መጽሐፋቸው በቂ ስለሆነ ቁርአን አያስፈልጋቸውም፤ መጽሐፋቸውን ከታዘዙ እንደሚባረኩ ተነግሯል፤ ሙስሊሞች በቀደሙት መገለጦች ማመን እንደሚጠበቅባቸው ተነግሯል፡፡ በመሐመድ ዘመን በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ የነበሩት ተውራትና ኢንጅል ዛሬ በክርስቲያኖች እጅ ከሚገኙት የተለዩ እንዳልሆኑ የታወቀና የተረጋገጠ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩት የእጅ ጽሑፎች ምስክሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ በቁርአን የተጠቀሱት ተውራትና ኢንጅል ዛሬ በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ የሚገኙት አይደሉም የሚለው የአንዳንድ ሙስሊም ሰባኪያን ሙግት መሠረት የለሽና ተስፋ የመቁረጥ ሙግት ነው፡፡

  1. ከእስላማዊ ትውፊቶች ጋር ይጣረሳል

ከስድስቱ የሐዲስ ስብስቦች መካከል አንዱ የሆነው ሱናን አቡ ዳውድ እንዲህ በማለት ይህንን ሙግት ውድቅ ያደርጋል፡-

“… ለአላህ መልእክተኛ (ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁንና) ወንበር አመጡላቸው፤ ተቀመጡበትም፡፡ ከዚያም ተውራትን አምጡልኝ አሉ፤ አመጡላቸውም፡፡ ከዚያ ከወንበሩ ላይ ተነስተው ተውራትን አስቀመጡና እንዲህ አሉ፡- በአንተ እና አንተን በገለጠው አምላክ አምናለሁ፡፡ Sunan Abu Dawud, Book 38 (Kitab al Hudud, i.e. Prescribed Punishments), Number 4434

ኢብን ከሢር የተሰኘው ስመ ጥር የቁርአን ተንታኝ ደግሞ አላህ ስላዘዛቸው መሐመድ ይህንን ማድረጋቸውን ይናገራል፡፡ (Tafsir Ibn Kathir (Abridged) Volume 3, Parts 6, 7 & 8)

“…ካብ ተውራትን በማንበብ ‹‹ነቢዩ የተናገሩት እውነት ነው›› አለ፡፡ (Sunan Abu Dawud Book 3, No. 1041)

ተውራት የሚባል መጽሐፍ በመሐመድ ዘመን በአይሁድ እጅ ከነበረ ህልውናን ለሚክዱት የዘመናችን ሙስሊሞች ትልቅ ችግር ነው፡፡

“ኸዲጃ ነቢዩን ወደ አጎቷ ልጅ ወደ ወረቃ ወሰደችው… እርሱም ከእስልምና ዘመን በፊት ክርስቲያን የሆነ ሲሆን የእብራይስጥ ጽሑፎችን ይጽፍ ነበር፡፡ አላህ እንዲጽፍ በፈቀደለት መጠን ወንጌልን በእብራይስጥ ይጽፍ ነበር፡፡” (Sahih Al-Bukhari Vol 1, Book 1, No 3)

“ወረቃ ከእስልምና ዘመን በፊት ክርስቲያን የሆነ ሲሆን አላህ እንዲጽፍ በፈቀደለት መጠን ወንጌልን በአረብኛ ይጽፍ ነበር፡፡” (Sahih Al-Bukhari Vol 6, Book 60, Number 478)

በሌላ ዘገባ መሠረት ወረቃ ወንጌላትን (ወንጌላት የሚለው በብዙ ቁጥር መሆኑን ልብ ይሏል) በአረብኛ ቋንቋ ያነብ ነበር፡፡ (Sahih Al-Bukhari Vol 4, Book 55, Number 605)

በቁርአን የተጠቀሰው ኢንጅል በክርስቲያኖች እጅ የሚገኝ ካልሆነ ክርስቲያን የነበረው ወረቃ በአላህ ፈቃድ ሲጽፍና ሲያነብብ የነበረው ምን ነበር?

ማጠቃለያ

በታሪክ የሚታወቁት ተውራትና ኢንጅል በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ የሚገኙት ብቻ በመሆናቸው በቁርአን የተጠቀሱት ተውራትና ኢንጂል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኙም የሚለው የአንዳንድ ሙስሊም ሰባኪያን ሙግት ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም፤ ታሪክንና እስላማዊ መጻሕፍትን ከሚያውቅ ሰውም የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ይህንን አመለካከት የሚያቀነቅኑ ወገኖች ተውራትና ኢንጂል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት የተለዩ ስለመሆናቸው ማስረጃ ስጡ ቢባሉ ቅንጣት ታክል የታሪክ፣ የአርኪዎሎጂም ሆነ የእስላማዊ ቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃ ሊያቀርቡ አይችሉም፡፡ ሙግታቸውም ቁርአንን ከገባበት አጣብቂኝ ለማውጣት የተፈጠረ ፈጣን ምላሽ (ad-hoc) እንጂ በሙስሊምም ሆነ ሙስሊም ባልሆኑት ሊቃውንት ዘንድ ተቀባይነት ያለው በጥናት ላይ የተመሠረተ ምላሽ አይደለም፡፡

እነዚህ ወገኖች ይህንን ልፍስፍስ ሙግት የፈጠሩት ቁርአን የገለፃቸው ተውራትና ኢንጂል በክርስቲያኖች እጅ ከሚገኙት ጋር ባለመመሳሰላቸውና  መልእክታቸውም ከቁርአን ጋር ባለመጣጣሙ ነው፡፡ በቁርአን የተገለጹት መጻሕፍት ተበርዘው እንጂ አሁን በክርስቲያኖች እጅ ከሚገኙት ጋር አንድ ናቸው የሚለውን የተለመደ እስላማዊ ሙግት አለመቀበላቸው የብረዛ ክስ በቁርአንም ሆነ በእስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ ድጋፍ የሌለው በመሆኑ ይመስላል፡፡ በተጨማሪም ቁርአን የአላህ ቃል እንደማይለወጥ መናገሩ ይህንን ሙግት ለመምረጣቸው ሌላው ምክንያት ሊሆን ይችላል፡-

  • “የአላህን ንግግሮች ለዋጭ የለም” 6፡34
  • “ለቃላቱ ለዋጭ የለም” 6፡115
  • “የአላህ ቃል መለወጥ የላትም” 10፡64
  • “ለቃላቱ ለዋጭ የላቸውም” 18፡27
  • “ለአላህ ድንጋጌ ፈጽሞ መለወጥን አታገኝም” 33፡62

ከሐዲሳትና ከቀዳሚያን ተፍሲሮች እንደምንረዳው የጥንት ሙስሊሞች አላህ ያወረዳቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ፈጽሞ እንደማይለወጡና ማንም ሊለውጣቸው እንደማይችል አጥብቀው ያምኑ ነበር፡፡ ለምሳሌ የሚከተለውን የኢብን ከሢር ተፍሲር ተመልከቱ፡-

“… አል ቡኻሪ እንደዘገበው ኢብን አባስ እንዲህ ብሏል፤ ‹የዚህ አያ ትርጉም የሚከተለው ነው፡- … ከአላህ ፍጥረታት መካከል ማንም የአላህን ቃላት ከመጻሕፍቱ ውስጥ ማስወገድ አይችልም፡፡ ግልፅ ትርጉማቸውን ያጣምማሉ ማለት ነው፡፡› ወሃብ ኢብን ሙነቢህ እንዲህ አለ ተውራት እና ኢንጂል ልክ አላህ በገለጣቸው ሁኔታ ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡ ከውስጣቸው አንድም ፊደል አልተወገደም፡፡ ነገር ግን ሰዎች ራሳቸው በጻፏቸው መጻሕፍት ላይ ተሞርኩዘው በመጨመርና ውሸት በሆነ አተረጓጎም ሌሎችን ያሳስታሉ፡፡” … “የአላህ መጻሕፍት ግን እስከ አሁን ተጠብቀው ይገኛሉ፤ ሊለወጡም አይችሉም፡፡ (Tafsir Ibn Kathir – Abridged, Volume 2, Parts 3, 4 & 5, Surat Al-Baqarah, Verse 253, to Surat An-Nisa, verse 147, First Edition: March 2000, p. 196)

እዚሁ ተፍሲፍ የግርጌ ማስታወሻ ላይ እንዲህ የሚል እናገኛለን፡-

“ቃሉን ያጣምማሉ ማለት ትርጉሙን ይለውጣሉ ወይም ያጣምማሉ ማለት ነው፡፡ ከየትኞቹም የአላህ መጻሕፍት ውስጥ አንድ ቃል እንኳመለወጥ የሚችል የለም፡፡ ይህ ማለት በተሳሳተ መንገድ ይተረጉማሉ ማለት ነው፡፡”

የሆነው ሆኖ ተውራትና እንጂል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኙም የሚለው ሙግትም ሆነ ተበርዘዋል የሚለው ክስ በአመክንዮ፣ በታሪክ፣ በቁርአንም ሆነ በእስላማዊ ትውፊቶች ፊት የሚቆሙበት ወገብ የላቸውም፡፡ ቶራህና ወንጌል በእጃችን ይገኛሉ፤ ለቃሉ ታማኝና ቃሉን አክባሪ የሆነው አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር እንዲጠፉና እንዲበረዙ አልፈቀደም፡፡

ሙስሊም ወገኖች ሆይ! በሰባተኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈውን የፈጠራ ጽሑፍ ከስህተቱ ለማዳን ስትሉ የፈጣሪ ቅዱስ ቃል ጠፍቷል፣ ተበርዟል፣ ወዘተ. እያላችሁ በፈጣሪያችሁ ላይ ክህደትን ስለምን ትናገራላችሁ? ከዚህ ሁሉ ግራ መጋባትና የክህደት ኃጢአት የፈጠራ ጽሑፍ የሆነውን ቁርአንን በመተው ወደ እውነተኛው የፈጣሪ ቃል ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መመለስ አይሻላችሁምን? እግዚአብሔር አምላክ ልቦና ይስጠን! አሜን!

—————–

[1] The Torah is the Jewish holy book, believed to have been revealed to Moses on Mount Sinai. The written Torah consists of the first five books of the Hebrew Bible (known to Christians as the Old Testament): Genesis, Exodus, Leviticus, Numbers, and Deuteronomy… The Torah is mentioned explicitly 18 times in the Quran, in addition to a number of indirect references. On the basis of statements in the Quran, Muslims agree that it is the holy book of the Jews revealed to Moses on Mount Sinai, and that it is why they consider Jews to be people oF the book (for example, Q 5:44, 68). (Juan E. Campo. Encyclopedia of Islam, p. 671)

[2] The Quran and Muslims refer to the entire New Testament as the Gospel, not just the first four books of that section of the Bible. The Quran could be interpreted as suggesting that the Gospel is a sacred text that God revealed to Jesus, as he revealed the Torah to Moses and the Quran to Muhammad. This relationship with other sacred scriptures is evidenced by the fact that nine of the 12 times the Gospel is mentioned in the Quran, it occurs in relation to the Torah (Arabic: al-tawrat), the Jewish sacred text. However, Muslims have also maintained that the Torah and the Gospel, as Jews and Christians have received them, contain errors and omissions, while the entire Quran is absolutely perfect and complete. (Ibid., pp. 265-266)

ለተጨማሪ ንባብ

መጽሐፍ ቅዱስ