ክርስቲያኖች ለምንድነው በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑት?

ክርስቲያኖች ለምንድነው በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑት?

በመንፈሳዊነት ረገድ በግላቸው ትርጉም የሚሰጥ ሆኖ ከማግኘታቸው በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ተኣማኒ በሆነ መንገድ ተጠብቆ መቆየቱን ለማመን ክርስቲያኖች በቂ የሆኑ ታሪካዊ ምክንያቶች አሏቸው፡፡

አንደኛ፥ አዲስ ኪዳን ከብሉይ ኪዳን ትምህርት ጋር በመስማማት በእርሱ ላይ ራሱን ይመሠርታል፡፡ ብሉይ ኪዳን ስለ መሲሁ የተነገሩና በወንጌላትና በተቀሩት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ በተዘገበው ሁኔታ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ የተፈጸሙ በርካታ ትንቢቶች አሉት፡፡ ወሳኝ ከሆኑት መካከል አንዱ ኢየሱስ ከመወለዱ ከ700 ዓመታት በፊት ለነቢዩ ኢሳይያስ የተገለጠውና የመሲሁን አገልግሎት ዓላማ የሚገልጠው የሚከተለው ክፍል ነው (53:4-6)፡-

በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ።

በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል ያለው የመገለጥ ተከታታይነት ብቸኛው መስፈርት አይደለም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ አስተላለፍ እጅግ ከፍተኛ ለሆነ ውጪያዊና እንዲያውም በጥላቻ የተሞላ ምርመራ የተጋለጠ ሆኗል፡፡ ሐንስ ኩንግ የተባሉ የሮማ ካቶሊክ የሥነ-መለኮት ምሑር የሚከተለውን ብለዋል:-

በዘመናዊው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሒስ የተደረሰበትና ለ300 ዓመታት በተደረገ ጥንቃቄ በተሞላ ምሑራዊ ሥራ የተወከለው ጥንቁቅ የሆነው ምሑራዊ ውጤት በሰው ልጆች ከተደረሰባቸው ከፍተኛ የሆኑ የዕውቀት ደረጃዎች መካከል እንደሚመደብ ብዙኀኑ ሕዝብ አያውቅም፡፡ ከዓለም ታላላቅ ሃይመኖቶች መካከል ከይሁዶ-ወክርስቲያን ትውፊት ውጪ ያለ የትኛውም ሃይማኖት የራሱን መሠረቶችና የራሱን ታሪክ በጣም ጥልቀት ባለውና ወሳኝ በሆነ መንገድ መርምሯልን? አንዳቸውም እንኳ ይህንን ወደማድረግ አልተጠጉም፡፡ በዓለም የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ በጣም የተጠና ግንባር ቀደሙ መጽሐፍ ነው፡፡ (Hans Küng, Judaism: The Religious Situation of Our Time. London: SCM Press Ltd, 1992, 24)

ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱን ትችት በጽናት መቋቋም እንደሚችል አሳይቷል፤ በአንጻሩም ጥብቅ የሆነው ጥናትም በሥነ-ቁፋሮ ማስረጃ፣ በንባብ ሂስና (Textual Criticism) በታሪካዊ ማስረጃ ለትክክለኛነቱ ድጋፍ ሰጥቷል፡፡

ቅዱስ መጽሐፉ እንዲተችበት የሚፈልግ ማንም ባይኖርም እኛ ክርስቲያኖች ግን ቅዱስ መጽሐፋችን ዘመናዊ በሆነውና ጥንቃቄን በተሞላው ምሑራዊ መንገድ መመርመር እንዳለበት ተቀብለናል፡፡ እውነት መሆኑንና ለዓለማችን በቂ መሆኑን ሙሉ በሆነ ምሑራዊና መንፈሳዊ አመኔታ አረጋግጠን እምነታችንን ለኛ ዘመን ማቅረብ የምንችለው እንዲህ ዓይነቱን ምርመራ ማለፍ ሲችል ነው፡፡

ሦስተኛው ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍት ከኦሪጅናል ጽሑፎቻቸው ትርጉም ባለው ሁኔታ ልዩነት እንዲኖራቸው በሚያስችል መልኩ አልተበረዙም የሚል ነው፡፡ ይህ መከሰቱን የሚለፍፉት እስላማዊ እሳቤዎች በታሪካዊ ማስረጃ የተደገፉ አይደሉም፡፡ ይልቁኑ በሁሉም ማስረጃዎች ሙሉ ዕይታ ላይ ያልተመሰረቱ ሥነ-መለኮታዊ ክርክሮች ናቸው፡፡ ዳቪንቺ ኮድና የባርት ኤህርማንን የመሳሰሉት መጻሕፍት ይህንን አያረጋግጡም፡፡ እጅግ በጣም ትንሽ የሆነ ተዓማኒነት ባለው ማስረጃ ላይና እጅግ የበዛ ግምት ላይ በመመሥረት የተለየ የንባቡን ታሪክ ያቀርባሉ፡፡

አንድ የመጨረሻ ዘርፍ ደግሞ የክርስትና ታሪካዊ አነሳስ ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞቱንና ከሙታን መነሳቱን የኢየሱስ ሐዋርትና ደቀ መዛሙርት አጥብቀው ከማመናቸው የተለየ ለክርስትና መነሳትና በቀጣይነት መኖር በቂ ሊሆን የሚችል ታሪካዊ ምክንያት የለም፡፡ የክርስቶስ የሥርየት ሞትና ትንሣኤ ባይኖር ኖሮ ክርስትና የይሁዲ የተሓድሶ እንቅስቃሴ ብቻ በመሆን በይሁዲ ውስጥ ይቀር ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ታሪኮች ስለተከሰቱና ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ለሐዋርያቱ በመታየት ቀጥለው ለነበሩት አስርተ ዓመታት ስለመራቸው ክርስትና ተወልዶ ዓለም አቀፋዊ አስፈላጊነትና ተዓማኒነት እንዳለው የሚናገር የተለየ ሃይማኖት ለመሆን በቅቷል፡፡

በመጽሐፍ ውስጥ በተከታታይ የተቀመጠው መለኮታዊ መገለጥ ቢያንስ ከታሪክ አኳያ ትክክልና ድጋፍ ያለው መሆን አለበት፡፡ እግዚአብሔር በጊዜና በቦታ የተከናወኑትን ሥራዎቹን ያለ በቂ ምስክርነት እንዳልተወ ክርስቲያኖች ያምናሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን መስፈርት ያሟላል፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙት አራቱ ወንጌላት ስለ ኢየሱስና እርሱ ስለኖረበት ዘመን ትክክለኛ የሆነ ምስል ያቀርባሉ፡፡ ትክክለኛ የሆኑትን ቃሎቹን፣ ትምህርቶቹንና ስለ አምላክነቱ የተናገራቸውን ነገሮች በዝርዝር ያስነብባሉ፡፡ ከሞት በተነሳው ክርስቶስ ላይ እምነታቸውን ያደረጉ ሚሊዮኖች ይቅርታንና ከኃጢኣት መንጻትን በመስጠት በሕወታቸው ውስጥ ሊያመጣው የሚችለውን ለውጥ ተለማምደዋል፡፡ ማንኛውም ሕግ ወይንም የሰው ጥረት ሊያመጣው ከሚችለው በላይ የሆኑ ለውጦችን በሕይወታችን ውስጥ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ክርስትና ሕልውናው የተረጋገጠውና በሚያስገርም ሁኔታ በዘመናችን እየተስፋፋ የሚገኘው ከስቅለትና ከትንሣኤ ታሪካዊ ክስተትና በዘመናት ሁሉ መካከል ክርስቲያኖች እየተቀበሉ ካሉት ቀጣይነት ካለው የኃጢአት ሥርየት ልምምድ የተነሳ ብቻ ነው፡፡

የትርጉም ምንጭ፡ Keith E. Small, Holy Books Have a History, 2010, p. 91

 

መጽሐፍ ቅዱስ