ኢየሱስ የምፅዓቱን ዕለት እንደማያውቅ ስለምን ተናገረ?

ኢየሱስ የምፅዓቱን ዕለት እንደማያውቅ ስለምን ተናገረ?

ማርቆስ 13፡32 ላይ “ነገር ግን ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ከአብ በቀር ፣ የሰማይ መላእክትም ፣ወልድም ቢሆን ፣ ማንም አያውቅም” እንደተባለው ስለ ትንሣኤ ኢየሱስንም ጨምሮ ማንም ከአብ በቀር የሚያውቅ እንደሌለ ተገልጿል፡፡ ክርስቲያኖች እንደሚሉት ኢየሱስ ከአብ እኩል ከሆነ እንዴት የትንሣኤን ጊዜ ማወቅ ተሳነው? ኢየሱስ ሁሉንም የማያውቅ ከሆነ እንዴት አምላክ ነው ልንል እንደፍራለን? አንዳንድ ክርስቲያኖች “ወልድ ሰው ስለሆነ ነው የማያውቀው ” ይላሉ፡፡ ግና ሰው ብቻ ነውን? ኢየሱስ ወደ ምድር ሳይመጣ በፊትና ወደ ሰማይ ካረገ በኃላ “ወልድ ” አይባልምን? ታድያ ጥቅሱ “ወልድም ቢሆን” እንጂ “ምድር ሳለ፣ ሥጋ በለበሰ ጊዜ” አይል?

ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት እስኪ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሁሉን አዋቂነት የሚናገረውን እንመልከት፡-

ሁሉን እንድታውቅ ማንምም ሊጠይቅህ እንዳትፈልግ አሁን እናውቃለን፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን አሉት፡፡ ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ አሁን ታምናላችሁን?” ዮሐንስ 16፡30-31

“ሦስተኛ፦ ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው፡፡ ኢየሱስም፦ በጎቼን አሰማራ፡፡” ዮሐንስ 21፡17

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ልብ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ይናገራል (1ነገሥት 8፡39)፡፡ የሰዎችን ልብና ኩላሊት በመመርመር እንደየሥራቸው መስጠት የእግዚአብሔር ሥልጣን መሆኑን ያስገነዝባል፡-  

እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኵላሊትንም እፈትናለሁ፡፡” (ኤርምያስ 17፡10)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያንን የሚያደርገው እርሱ መሆኑን ተናግሯል፡-

“አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ፡፡” ራዕይ 2፡23፡፡ (በተጨማሪም ማቴዎስ 9፡3-4፣ ሉቃስ 9፡46-47፣ ዮሐንስ 6፡60-66፣ 1ቆሮንቶስ 4፡5፣ ማርቆስ 2፡5-12)፡፡

ታድያ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎች ብዙ ቦታዎች ኢየሱስ መለኮታዊ ዕውቀት እንዳለው ቅዱሱ መጽሐፍ ካረጋገጠ ስለ ምፅዓቱ እንደማያውቅ ስለምን ተነገረ? ደጋግመን እንደገለፅነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም አምላክ የመሆኑን ያህል ፍፁም ሰው ነው፡፡ በሰውነቱ በጊዜና በቦታ የተገደበ እንደነበረ ሁሉ እውቀቱም የተገደበ ነበር፡፡ እንዲያ ባይሆን ኖሮ ፍፁም ሰው ሊሆን ባልቻለም ነበር፡፡ ፍፁም ሰውነቱ ደግሞ በቤዝዎት አገልግሎቱ ውስጥ በእጅጉ ወሳኝ ነው፤ ምክንያቱም በሁሉም ረገድ እኛን መወከል ያስፈልገዋልና፡፡ ነገር ግን በመለኮቱ ዘለዓለማዊ፣ ምሉዕ በኩላሄና አዕማሬ ኩሉ ነው፡፡  ይህንን ምላሽ ጸሐፊው ጥቅሱ ወልድ ስለሚልና ሥጋ በለበሰ ጊዜ ስለማይል እንደማያስኬድ ለመሞገት ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን ወልድ የሚለው ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ የሆነውን አንዱን ኢየሱስን ስለሚያመለክት መጽሐፍ ቅዱስ የተገደበውን የወልድን ገፅታ ሲነግረን ስለ ሰብኣዊ ባሕርዩ እየተናገረ እንዳለ ሊገባን ያስፈልጋል፡፡ የተገደበ መሆኑን መናገሩ ብቻ ሰብኣዊ ባሕርዩን የተመለከተ መሆኑን ግልፅ ስለሚያደርግ ሌላ ማብራርያ መጨመር አያሻም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በቅን ልብ እውነትን ለሚፈልጉ ሰዎች እንጂ እንደ ጠያቂው ፀጉር ለሚሰነጥቁ ሐያሲያን አይደለም፡፡

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ

መሲሁ ኢየሱስ