ለቃላቱ ለዋጭ የላቸውም!
ለአቡ ሀይደር ስህተት የተሰጠ መልስ
ሙስሊም ወገኖቻችን በሁሉም ነቢያትና በሁሉም ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያምኑ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን የሙሐመድ ትምህርት ከነቢያት ትምህርት ጋር ስለሚጋጭ ሙሐመድ መሳሳቱን ከማመን ይልቅ ከፈጣሪ ዘንድ የሆኑት ቅዱሳት መጻሕፍት በቀድሞ ይዘታቸው እንደሌሉና እንደተበረዙ ማመንን መርጠዋል፡፡ ሆኖም ቁርኣን የፈጣሪ ቃል በባሕርዩ እንደማይለወጥና ማንም ሊለውጠው እንደማይችል መናገሩ የቀደሙት ቅዱሳት መጻሕፍት ተለውጠዋል የሚለውን እምነታቸውን ውድቅ የሚያደርግ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖባቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት እነዚህን የቁርኣን ጥቅሶች የቀደሙትን ቅዱሳት መጻሕፍት በማያመለክቱበት መንገድ ሲተረጉሙ እየታዘብን ነው፡፡ ይህ ትርጓሜ ምን ያህል አሳማኝ ነው? በዚህ ምላሻችን ኡስታዝ ሳዲቅ ሙሐመድ (አቡ ሀይደር) ለክርስቲያኖች ምላሽ በሚል ያዘጋጀውን ጽሑፍ እንፈትሻለን፡፡ አቡ ሀይደርና መሰሎቹ ቅዱስ የሆነው ቃለ እግዚአብሔር እንደተለዋወጠና እንደተበላሸ በማስመሰል የሚናገሩት መለኮታዊ ልዕልናን የሚያንኳስስ የክህደት ንግግር ምን ያህል እንደሚያራምዳቸው እናያለን፡፡ እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-
አቡ ሀይደር
የአላህን ቃላት ለዋጭ የላቸውም!
በአቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
” وَلَقَدْ كُذِّبَتْ رُسُلٌ مِنْ قَبْلِكَ فَصَبَرُوا عَلَى مَا كُذِّبُوا وَأُوذُوا حَتَّى أَتَاهُمْ نَصْرُنَا وَلَا مُبَدِّلَ لِكَلِمَاتِ اللَّهِ وَلَقَدْ جَاءَكَ مِنْ نَبَإِ الْمُرْسَلِينَ ” سورة الأنعام 34
“ከበፊትህም መልክተኞች በእርግጥ ተስተባበሉ፡፡ በተስተባበሉበትም ነገርና በተሰቃዩት ላይ እርዳታችን እስከመጣላቸው ድረስ ታገሱ፡፡ የአላህንም ንግግሮች ለዋጭ የለም፡፡ ከመልክተኞቹም ወሬ (የምትረጋጋበት) በእርግጥ መጣልህ፡፡” (ሱረቱል አንዓም 6፡34)፡፡
” وَاتْلُ مَا أُوحِيَ إِلَيْكَ مِنْ كِتَابِ رَبِّكَ لَا مُبَدِّلَ لِكَلِمَاتِهِ وَلَنْ تَجِدَ مِنْ دُونِهِ مُلْتَحَدًا ” سورة الكهف 27
“ከጌታህም መጽሐፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፡፡ ለቃላቶቹ ለዋጭ የላቸውም፡፡ ከእርሱም በቀር መጠጊያን በፍጹም አታገኝም፡፡” (ሱረቱል ከህፍ 18፡27)፡፡
በነዚህ ሁለት የቅዱስ ቁርኣን ጥቅሶች መሠረት ‹‹የአላህን ቃላት ለዋጭ የለም›› ተብሎ ተነግሯልና፡ ተውራትና ኢንጂልም የአላህ ቃላት ናቸውና አልተለወጡም ማለት እንችላለን፡፡ እናንተ ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟል ስትሉ ከዚህ የቅዱስ ቁርኣን ሀሳብ ጋር አትጋጩም ወይ? የሚል ጥያቄ ከካፊሮች በኩል ቀርቧል፡፡ እኛም ለጥያቄዎቹ የሚኖረን መጠነኛ ምላሽ እንደሚከተለው ይቀርባል ኢንሻአላህ፡-
1ኛ/ ጥቅላዊ ምላሽ፡-
የአላህ ቃል ተብሎ ሲጠቀስ ‹‹ቃል›› የሚለው ኃይለ-ቃል ሁለት ነገራትን እንደሚያቅፍ በቅድሚያ ማወቁ ለመልሱ አጋዥ ይኾናል፡፡ የመጀመሪያው ‹‹ከሊማቱላህ አል-ከውኒያህ›› ሲኾን፡ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹ከሊማቱላህ አሽ-ሸርዒያህ›› የተሰኘው ነው፡፡
‹‹ከሊማቱላህ አል-ከውኒያህ›› ማለት፡- አላህ አስቀድሞ ከጥንቱ የወሰነውና የፈረደው የውሳኔ ቃል፣ ለነቢያቱና አማኝ ባሪያዎቹ መልካም የተስፋ ቃል-ኪዳንን የገባላቸው ቃል፣ በከሀዲያንና አመጸኞች ላይ በቁጣውና በጀሀነም እሳት የዛተባቸው፡ የማስፈራራሪያ ቃል ማለት ነው፡፡ ይህንን ቃል(ውሳኔ) ማንም ፍጥረት ለመሻር፣ ለመለወጥ፣ ለማስቀየር አይችልም፡ አቅሙም የለውም፡፡
መልስ
ሙስሊሙ ሰባኪ ፈጣሪ ለነቢያቱና አማኝ ባሪያዎቹ የገባላቸውን መልካም የተስፋ ቃል ኪዳን እንዲሁም በከሃዲያንና አመጸኞች ላይ በቁጣውና በገሃነም እሳት የዛተባቸውን የማስፈራሪያ ቃል ማንም መለወጥ እንደማይችል ከነገረን በኋላ በጽሑፍ የሰፈረው ቃል ሊለወጥ እንደሚችል ሊያሳምነን መፈለጉ በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ ለመሆኑ እነዚህን የተስፋና የማስፈራሪያ ቃላት የምናገኘው የት ነው? በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ አይደለምን? ቅዱሳት መጻሕፍቱ ከተለወጡ ስለ እነዚህ የተስፋ ቃል ኪዳኖችና ማስፈራርያዎች ማወቅ የምንችለው፤ ከነ ጭራሹስ ስለ ተስፋ ቃል ኪዳኖችና የማስፈራርያ ዛቻዎች መናገር የምንችለው እንዴት ነው? እነዚህን የተስፋ ቃል ኪዳኖችና የማስፈራርያ ዛቻዎች የያዙት ቅዱሳት መጻሕፍት ከተለወጡ ተስፋዎቹና ማስፈራሪያዎቹ ምን እንደሆኑ እንዲሁም ለምንና እንዴት እንደተሰጡ ማወቅ የምንችልበት መንገድ ስለማይኖር ለሰው ልጆች ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ተስፋ የሚያደርጉት ምንም ነገር አይኖራቸውም፡፡ ክፉ ሰዎችም የፈጣሪን ማስጠንቀቂያዎች ስለማያውቁ ሊፈሩና ሊጠነቀቁ አይችሉም፡፡ ተስፋዎቹና ማስፈራርያዎቹ ከሰው ልጆች አንጻር ፋይዳ የሚኖራቸው እነርሱን የያዙት ቅዱሳት መጻሕፍት በትክክል ከተጠበቁ ብቻ ነው፡፡ ሙስሊም ሰባኪያን በአመክንዮ የማሰብ አቅማቸው ደካማ ነው ስንል በምክንያት ነው፡፡
አቡ ሀይደር
‹‹ከሊማቱላህ አሽ-ሸርዒያህ›› ማለት ደግሞ፡- ጌታ አላህ በነቢያቱና በመልክተኞቹ አማካኝነት፡ ለባሪያዎቹ የሕይወት መመሪያ ይኾን ዘንድ ያወረዳቸው መለኮታዊ መጽሐፍቱ ማለት ነው፡፡ እነዚህ መለኮታዊ መጽሐፍት የአላህ ቃል ይባላሉ፡፡ ቃሉም ኾነ መልእክቱ የርሱ በመኾናቸው፡፡ እነዚህን ‹የአላህ ቃል› የተሰኙ መለኮታዊ መጽሐፍት፡ በውስጣቸው ያለውን የህግ አንቀጾች፡ አላህ እራሱ በሌላ የህግ አንቀጽ በመተካት የፈለገውን ሊሽረውና ሊሰርዘው ይችላል (ሱረቱል በቀራህ 2፡106፣ ሱረቱ-ነሕል16፡101)፡፡ እንዲሁም መጽሐፍቶቹን ለመጠበቅ (ልክ እንደ ቁርኣን) ቃል ካልገባላቸው ሰዎችም እነዚህ መጻሕፍት ላይ እጃቸውን በማስገባት፡ መጨመርና መቀነስ፣ መሰረዝና መደለዝ ይችላሉ ማለት ነው፡፡
መልስ
አንደኛ፡- “አላህ” ቁርኣንን ብቻ ነጥሎ እንደሚጠብቅና ሌላውን እንደማይጠብቅ የተናገረበት አንድም ጥቅስ በቁርኣን ውስጥ አይገኝም፡፡ ሙስሊሞች ለጥበቃ ቃል የተገባለት ቁርኣን ብቻ እንደሆነ ለማስመሰል አሳስተው የተረጎሙት አንድ ጥቅስ ይገኛል፤ እርሱን በግርጌ ማስታወሻ ዳሰነወል፡፡[1] ሁለተኛ፡- በዚህ ቦታ አላህ ቃሉ እንደማይለወጥ “የተናገረው” ጥቅላዊ በሆነ መንገድ እንጂ እንዲህ ባለ መንገድ በመሸንሸን አይደለም፡፡ አላህ መለዋወጥ የቃሉ ባሕርይ እንዳልሆነ ጥቅላዊ በሆነ መንገድ ተናገረ እንጂ “የተስፋና የማስፈራርያ ቃሌ አይለወጥም፣ ለሰው ልጆች የሰጠሁት የመመርያ ቃሌ ይለወጣል” ወይም “ቁርአኔ አይለወጥም ሌሎች መጻሕፍቴ ይለወጣሉ” ብሎ የተናገረበት ጥቅስ በቁርኣን ውስጥ አይገኝም፡፡ የቁርኣን የሽረት አስተምህሮ የአላህ ቃል እንደማይለወጥ ከሚናገሩት ጥቅሶች ጋር ግጭት የሚፈጥር ሌላ ችግር ነው፡፡
አቡ ሀይደር
ከዚህ ገለጻ በመነሳት፡- ‹ወገኖቻችን› የአላህ ቃላት እንደማይለወጥ ያቀረቧቸው ጥቅሶች፡ አላህ አስቀድሞ ለባሪዎቹ ቃል የገባላቸውን፣ በከሀዲያን ላይ ደግሞ የዛተባቸውን የውሳኔ ቃሉን ለማመልከት፣ ወይንም ደግሞ ለዓለማት ሕዝቦች የሕይወት መመሪያ ይኾን ዘንድ የተወረደውን የመጨረሻውን መለኮታዊ መጽሐፍ ቅዱስ ቁርኣንን ለመግለጽ ካልኾነ በስተቀር፡ እነሱ ዘንድ ያለውን ‹መጽሐፍ ቅዱስ›ን በፍጹም ሊገልጽ አይችልም፡፡ ይህንንም በደንብ ለማሳየት በዚህ ዙሪያ የተነገሩ የቁርኣን ክፍሎችን በጠቅላላ በዝርዝር እናቀርባቸዋለን ኢንሻአላህ፡፡
ሀ. ሱረቱል አንዓም 6፡34፡-
” وَلَقَدْ كُذِّبَتْ رُسُلٌ مِنْ قَبْلِكَ فَصَبَرُوا عَلَى مَا كُذِّبُوا وَأُوذُوا حَتَّى أَتَاهُمْ نَصْرُنَا وَلَا مُبَدِّلَ لِكَلِمَاتِ اللَّهِ وَلَقَدْ جَاءَكَ مِنْ نَبَإِ الْمُرْسَلِينَ ” سورة الأنعام 34
“ከበፊትህም መልክተኞች በእርግጥ ተስተባበሉ፡፡ በተስተባበሉበትም ነገርና በተሰቃዩት ላይ እርዳታችን እስከመጣላቸው ድረስ ታገሱ፡፡ የአላህንም ንግግሮች ለዋጭ የለም፡፡ ከመልክተኞቹም ወሬ (የምትረጋጋበት) በእርግጥ መጣልህ፡፡” (ሱረቱል አንዓም 6፡34)፡፡
ይህ አንቀጽ እያናገረ ያለው ነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነው፡፡ ቃሉም፡- ለሳቸው በወገኖቻቸው በኩል በሚደርስባቸው ማስተባበልና ክህደት ሀዘን እንዳይሰማቸው ማጽናኛን እየሰጠ ነው፡፡ ይህ ነቢያትን የማሰቃየትና የማስተባበል ተግባር ከሳቸው በፊት በነበሩት ነቢያትም ላይ የተፈጸመ ነገር መኾኑን በማውሳት፡ አዲስ እንዳልኾነ በመግለጽና፡ እነዚያም ነቢያት የአላህ እርዳታ (በጠላት ላይ ድልን መጎናጸፍ) እስኪመጣላቸው ድረስ በደረሰባቸው ችግር እንደታገሱ በመግለጽ፡ እሳቸውም እንዲታገሱ ያስተምራል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ‹‹የአላህንም ንግግሮች ለዋጭ የለም፡፡›› በማለት የተናገረው፡፡ ይህም አላህ ነቢያቱንና አማኝ ባሪያዎቹን እንደሚረዳና የበላይ እንደሚያደርግ ከጥንቱኑ ቃል የገባለት ጉዳይ በመኾኑ፡ ይህን ቃል ማንም ሊለውጠው እንደማይችል ተናገረ፡፡ ታዲያ ይህ ቃል በምን መልኩ ነው ከቀደምት መለኮታዊ መጽሐፍት ጋር የሚገናኘውና፡ እነሱም እንደማይለወጡ የሚያሳየው?
‹‹የአላህንም ንግግሮች ለዋጭ የለም›› የሚለውን ሀሳብ የቅዱስ ቁርኣን ተንታኞች (ሙፈሲሮች) በጠቅላላ በአንድ ድምጽ ‹አላህ የወሰነውን መለኮታዊ ውሳኔና ፍርድ፣ ለአማኝ ባሪያዎቹ የገባላቸውን የተስፋ ቃል-ኪዳን ማለት እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ከነዚህም መካከል፡-
ሀ/ ኢማሙል ቁርጡቢይ (አል-ጃሚዑ ሊአሕካሚል-ቁርኣን).
ለ/ ኢማሙል በገዊይ (መዓሊሙ-ተንዚል ፊ-ተፍሲር ወት-ተእዊል).
ሐ/ ጀላሉዲን አስ-ሲዩጢይ (ተፍሲሩል-ጀላለይን).
መ/ አል-ሓፊዝ ኢብኑ ከሢር (ተፍሲር አል-ቁርኣኒል ዐዚም).
ሠ/ አል-ኢማም አሽ-ሸውካኒይ (ፈትሑል ቀዲር)›
መልስ
ቀደም ሲል እንዳልነው የሰው ልጆች ፈጣሪ ለአገልጋዮቹ ቃል መግባቱን ያወቁት በቅዱሳት መጻሕፍት አማካይነት በመሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍቱ ተለውጠዋል እያልን ስለ ተስፋ ቃሎቹ መናገር የምንችልበት ሁኔታ የለም፡፡ የተስፋ ቃሎቹ የቅዱሳት መጻሕፍቱ አካል በመሆናቸው ቅዱሳት መጻሕፍቱ ከተለወጡ ፈጣሪ ቃል መግባቱን አንዲሁም ቃል የገባው ንግግሩ ራሱ ላለመለወጡ ዋስትና መስጠቱን ማወቅ የምንችልበት መንገድ የለም፡፡ ፈጣሪ ለሰው ልጆች የሚናገርበት አስተማማኝ መንገድ ቅዱሳት መጻሕፍት በመሆናቸው ቅዱሳት መጻሕፍቱ ሊለወጡ እንደሚችሉ እየተናገርን ስለ ተስፋው አለመለወጥ መናገር ትርጉም አይሰጥም፡፡ የተስፋ ቃሎቹ ለአገልጋዮቹ መሰጠታቸውንም ሆነ የተሰጡት የተስፋ ቃሎች የማይለወጡ መሆናቸውን የማወቂያ አስተማማኝ መንገድ የሆነው በጽሑፍ የሰፈረው ቃሉ ተዓማኒነቱ ዋስትና የሌለው ከሆነ ሁሉም ነገር ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ ብዙዎቹ ጥንታውያን ሙስሊም ሊቃውንት የጥቅሶቹን የምንባብ አውድ ከማስረዳት በዘለለ እንደ ዘመናችን ሙስሊም ሰባኪያን ፈጣሪ በጽሑፍ ለሰፈረው ቃሉ ጥበቃ ማድረጉን አይክዱም፡፡ ይህንን በማስከተል በምንሰጣቸው ምላሾች እንመለከታለን፡፡
አቡ ሀይደር
ለ. ሱረቱል አንዓም 6፡115፡-
” وَتَمَّتْ كَلِمَتُ رَبِّكَ صِدْقًا وَعَدْلًا لَا مُبَدِّلَ لِكَلِمَاتِهِ وَهُوَ السَّمِيعُ الْعَلِيمُ ” سورة الأنعام 115
“የጌታህም ቃላት እውነተኛና ትክክለኛ ስትኾን ተፈጸመች፡፡ ለቃላቱ ለዋጭ የለም፡፡ እርሱም ሰሚው ዐዋቂው ነው፡፡” (ሱረቱል አንዓም 6፡115)፡፡
ይህም አንቀጽ ከላይኛው ጋር መልእክቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁለቱም በአንድ ሱራ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ መልእክቱንም የቁርኣን ሙፈሲሮች በሁለት ጎን ነው ያዩት፡፡ እሱም፡-
‹‹የጌታህም ቃላት›› የሚለውን ቁርኣን በሚለው ይገልጹትና ሲያብራሩት፡- ቁርኣን በትምሕርቶቹና በዜናዎቹ ፍጹም እውነተኛ፡ እንዲሁም በፍርዱና በውሳኔው ፍጹም ትክክል የኾነ ማለት ነው ይላሉ፡፡
‹‹የጌታህም ቃላት›› የሚለውን የአላህን መለኮታዊ ውሳኔ በማለት በሌላ ጎኑ ይተረጉሙትና ደግሞ ሲያብራሩት፡- አላህ በነቢያት በኩል በገባው ቃል መሰረት እውነትን የበላይ በማድረግ፡ ሀሰትን ደግሞ በማንኮታኮት የተስፋ ቃሉን ሞላልን/ፈጸመልን፡፡ ትክክለኛ ፍርዱንም ፈጸመልን ማለት ነው ብለዋል፡፡ በሁለቱም መልኩ ብናየው መልእክቱ ጤናማ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ ‹‹የአላህን ቃላት›› የሚለውን ግን ወደ ቀደምት መለኮታዊ መጻሕፍት በመውሰድ የተረጎመው የለም፡፡ ይልቁኑ ‹ፈትሑል በያን› በተሰኘው ተፍሲር ላይ ‹‹የጌታህም ቃላት›› ሚለውን ቁርኣን በሚለው ከፈታው በኋላ ሲያብራራው እንዲህ ይላል፡- ‹‹በተውራትና በኢንጂል ላይ የሰው እጅ እንደገባበት ሁሉ፡ ማንም ሰው በቁርኣን ላይ እጁን እንዳያስገባበት በኃይሉ በመጠበቅ እውነተኛና ትክክለኛ አደረገው›› ይላሉ፡፡
መልስ
አቡ ሀይደር ለራሱ አመለካከት የሚመቸውን ትርጓሜ ብቻ መርጦ በመውሰድ ሌሎቹን ሲክድ እንመለከታለን፡፡ ይህ አንድም አለማወቅ ሲከፋም ሆነ ብሎ አንባቢን ማሳሳት ነው፡፡ አጥ-ጠበሪ ይህ ቃል አላህ በመጻሕፍቱ ውስጥ የተናገረውን ቃል የተመለከተ መሆኑን ተናግሯል፡-
“None can change His words”, He is saying that there is no one who could change what He has informed in His books about anything which is bound to happen during it’s time or has been postponed. It all happens as Allah says it would. (Ibn Jarir al-Tabari, Jami’ al-bayan fi ta’wil al-Qur’an, Commentary on Surah 6:115)
ትርጉም፡-
“ለቃላቱ ለዋጭ የለም”፤ በጊዜውም ሆነ በቀጠሮ እንደሚፈፀም የተወሰነው በመጻሕፈቱ ውስጥ የተነገረውን የትኛውንም ነገር መለወጥ የሚችል እንደሌለ እየተናገረ ነው፡፡ አላህ እንደተናገረው እንደዚያው ይፈጸማል፡፡”
ከዚህ ማብራርያ ሁለት ነገሮችን እንረዳለን፤ አንደኛ “በመጻሕፈቱ ውስጥ” የሚለው አባባል በአንድ መጽሐፍ በቁርኣን ብቻ ያልተወሰነ መሆኑን የሚነግረን ሲሆን ሁለተኛ እንደማይለወጥ ቃል የተገባው በአንደበት የተነገረው ብቻ ሳይሆን በጽሑፍ የሰፈረውንም እንደሚያጠቃልል ያስረዳናል፡፡ ጥቅሱ እየተናገረ ያለው በመጽሐፍቱ ውስጥ ስለተገባው ቃል ከሆነ መጽሐፍቱ በተለወጡበት ሁኔታ የተስፋ ቃሎቹ እውነተኛ የፈጣሪ ቃሎች ይሁኑ ወይም የሰው ፈጠራዎች ማወቅ የሚቻልበት መንገድ የለምና፡፡
አጥ-ጠበሪ በሌላ ቦታ ይህንን ጥቅስ ሲያብራራ እንዲህ በማለት በአይሁድና በክርስቲያኖች እጅ የሚገኙ መጻሕፍትን የተመለከተ መሆኑን ጽፏል፡-
The word of God meant in this verse is the Quran. This word is complete in truth and justice. Nothing can change Allah’s word which he revealed in his BOOKS. The liars cannot add or delete from Allah’s BOOKS. This is referring without a doubt to the Jews and Christians because they are the people of the books which were revealed to their prophets. Allah is revealing that the words they (the people of the book) are corrupting were not revealed by Allah, since Allah’s word cannot be changed or substituted. (Tafsir al-Tabari ምንጭ )
ትርጉም፡-
“በዚህ ቦታ የአምላክ ቃል የተባለው ቁርኣን ነው፡፡ ይህ ቃል በእውነትና በፍትህ የተሟላ ነው፡፡ በመጻሕፍቱ ውስጥ የተገለጠውን የአላህ ቃል መለወጥ የሚችል የለም፡፡ ሐሰተኞች በአላህ መጻሕፍት ላይ መጨመርም ሆነ መቀነስ አይቻላቸውም፡፡ ይህ ያለ ጥርጥር አይሁድንና ክርስቲያኖችን የተመለከተ ነው ምክንያቱም ለነቢያቶቻቸው የተገለጡት የመጻሕፍቱ ባለቤቶች ናቸውና፡፡ አላህ እየተናገረ ያለው እነርሱ (መጻሕፍቱ ባለቤቶች) እየበረዙ ያሉት በአላህ የተገለጡ አይደሉም ምክንያቱም የአላህ ቃል ሊለወጥና በሌላ ሊተካ አይችልምና፡፡”
በአጥ-ጠበሪ መሠረት ጥቅሱ ስለ ቁርኣን ቢናገርም በቁርኣን ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ለአይሁድና ለክርስቲያኖች የተገለጡትንም መጻሕፍት በመርህ ደረጃ ያጠቃልላል፡፡ በአጥ-ጠበሪ መሠረት የአላህ ቃል ሊለወጥና ሊተካ ስለማይችል አይሁድና ክርስቲያኖች ሌሎች መለኮታዊ ያልሆኑ ቃላትን ይለዋውጡ እንደሆን እንጂ በአላህ ለነቢያት የተገለጡትን መጻሕፍት መበረዝ አይቻላቸውም፡፡ እንደ እስልምና ቁርኣን የአላህ ቃል ቢሆንም የአላህ ቃል በሙሉ ቁርኣን ብቻ ባለመሆኑ የአጥ-ጠበሪ ሐሳብ በጣም ትክክል ነው፡፡ ቁርኣን የማይለወጥበት ምክንያት የአላህ ቃል በመሆኑ ነው ከተባለ ያለመለወጥ ባሕርይ በቁርኣን የተወሰነ አይደለም ማለት ነው፡፡
አቡ ሀይደር
ሐ. ሱረቱ ዩኑስ 10፡62-64፡-
” أَلَا إِنَّ أَوْلِيَاءَ اللَّهِ لَا خَوْفٌ عَلَيْهِمْ وَلَا هُمْ يَحْزَنُونَ * الَّذِينَ آمَنُوا وَكَانُوا يَتَّقُونَ * لَهُمُ الْبُشْرَى فِي الْحَيَاةِ الدُّنْيَا وَفِي الْآخِرَةِ لَا تَبْدِيلَ لِكَلِمَاتِ اللَّهِ ذَلِكَ هُوَ الْفَوْزُ الْعَظِيمُ ” سورة يونس 64-62
“ንቁ! የአላህ ወዳጆች በእነሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነሱም አያዝኑም፡፡ (እነሱም) እነዚያ ያመኑትና ይፈሩት የነበሩ ናቸው፡፡ ለእነሱ በቅርቢቱ ሕይወትም በመጨረሻይቱም ብስራት አላቸው፤ የአላህ ቃላት መለወጥ የላትም፤ ይህ እርሱ ታላቅ ዕድል ነው፡፡” (ሱረቱ ዩኑስ 10፡62-64)፡፡
እውነተኛ የአላህ ወዳጆች ማለት፡- በጌታቸው አላህ ያመኑ ኾነው የትም ስፍራ ላይ ቢኾኑ፡ ይህን ጌታቸውን በንግግራቸውም ኾነ በተግባራቸው እንዲሁም በልቦናቸው ሚፈሩት ናቸው፡፡ እነዚህ አማኝ ባሪያዎች፡ ከሞት በኋላ ምን ይገጥመናል የሚል ስጋትም ኾነ፡ ባሳለፉት ምድራዊ ሕይወት ትካዜ አይገጥማቸውም፡፡ እንደውም ገና በቅርቢቱ (ምድራዊ) ሕይወታቸው፡ በህልም አማካኝነት ወይም ሊሞቱ ሲሉ መልካም ብስራት፣ በመጨረሻው ዓለም ደግሞ ጀነት አለላቸው፡፡ ይህ አላህ ለነሱ የገባው ቃል-ኪዳን ነውና፡ የአላህ ቃል ደግሞ በፍጹም አትለወጥም ነው፡፡
የቅዱስ ቁርኣን ተርጓሚዎች ‹‹የአላህ ቃላት›› የሚለውን ከአንቀጹ ላይና ታች ያሉ ተያያዥ ሀሳቦች ጋር በማገናኘት የፈቱት ‹‹የአላህን የተስፋ ቃል-ኪዳን›› በሚለው ነው፡፡
መልስ
የዚህን ምላሽ ቀደም ሲል ተመልክተናል፡፡ የፈጣሪ የተስፋ ቃል እንደማይለወጥ እየተናገርን ፈጣሪ የተስፋ ቃሉን የሰጠበትና ያ የተስፋ ቃሉ የማይለወጥ መሆኑን ያረጋገጠበት የመረጃ ምንጭ ተለውጧል ማለት አመክንዮአዊ ተፋልሶ ነው፡፡
አቡ ሀይደር
መ. ሱረቱል ከህፍ 18፡27፡-
” وَاتْلُ مَا أُوحِيَ إِلَيْكَ مِنْ كِتَابِ رَبِّكَ لَا مُبَدِّلَ لِكَلِمَاتِهِ وَلَنْ تَجِدَ مِنْ دُونِهِ مُلْتَحَدًا ” سورة الكهف 27
“ከጌታህም መጽሐፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፤ ለቃላቶቹ ለዋጭ የላቸውም፤ ከርሱም በቀር መጠጊያን በፍጹም አታገኝም።” (ሱረቱል ከህፍ 18፡27)፡፡
ይህ አንቀጽ እየተናገረ ያለው ስለ ቁርኣን ነው፡፡ ‹‹ከጌታህም መጽሐፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ›› በማለት የሚያናግረው ነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነው፡፡ ወደሳቸው የወረደው መጽሐፍ ደግሞ ‹ቅዱስ ቁርኣን› ነው፡፡ ይህን መጽሐፍ እንዲያነቡ ካዘዛቸው በኋላ፡ ‹‹ለቃላቶቹ ለዋጭ የለውም›› በማለት፡ ይህ ቁርኣን ማንም ሰው ሊለውጠው እንደማይችል ተናገረ ማለት ነው፡፡ የቁርኣኑ ተርጓሚዎችም አቋም ይህ ነው ወላሁ አዕለም፡፡
መልስ
የሙስሊሙ ሰባኪ ድምዳሜ ከአመክንዮ እና ከቀደምት ሙስሊም ሊቃውንት አመለካከት አኳያ በእጅጉ የተሳሳተ ነው፡፡ ከአመክንዮ አኳያ ስንመለከት ጥቅሱ ስለ ቁርኣን ብቻ ሳይሆን ስለ አላህ ቃል ሁሉ እንደሚናገር መገንዘብ እንችላለን፡፡ “ከጌታህም መጽሐፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፤ ለቃላቶቹ ለዋጭ የላቸውም” ሲል የቁርኣንን “ያለመለወጥ” ምስጢር እየነገረን ነው፤ እርሱም የአላህን ቃል የሚለውጥ ስለሌለ ቁርኣን አይለወጥም የሚል ነው፡፡ ሐሳቡን በሲሎጂዝም ብንደረድር የሚከተለውን ይመስላል፡-
- የአላህን ቃላት የሚለውጥ የለም፡፡
- ቁርኣን የአላህ ቃል ነው፡፡
- ስለዚህ ቁርኣንን የሚለውጥ የለም፡፡
በእስልምና መሠረት ቁርኣን “የአላህ ቃል” እንጂ የአላህ ቃል ሁሉ ቁርኣን ስላልሆነ ቁርኣን “ለዋጭ የላቸውም” ከተባለላቸው የአላህ ቃላት መካከል አንዱ እንጂ ከአላህ ቃላት መካከል እርሱ ብቻ ተለይቶ የማይለወጥ ሌላው ግን የሚለወጥ አይደለም፡፡ የቁርኣን አለመለወጥ የአላህ ቃል ሊለወጥ አይችልም በሚለው መርህ ላይ የተመሠረተ እስከ ሆነ ድረስ መርሁን በቁርኣን ብቻ መወሰን ተቀባይነት የለውም፡፡ ይህ አመለካከት የታላላቅ ሙስሊም ሊቃውንት ነው፡፡
ከሰለፊስቶች ሊቃውንት መካከል ግንባር ቀደም የሆነው ኢብን ቀይም አል-ጀውዚያ ሱራ 6፡115 ላይ የሚገኘውን የአላህ ቃል እንደማይለወጥ የሚናገረውን ጥቅስ ሲያብራራ ጥቅሱ በቁርኣን ያልተወሰነና ቶራህ እና ወንጌልም ጭምር በትክክል የተጠበቁ ስለመሆናቸው ማስረጃ እንደሚሰጥ የሚያምኑ ሙስሊም ሊቃውንት መኖራቸውን ጠቅሷል፡፡ ዋቢ ካደረጋቸው መካከልም ኢማም አል-ቡኻሪ እና አር-ራዚ ይገኙበታል፡፡ ሙሐመድ ራሱ የቀደሙት መጻሕፍት አለመበረዛቸውን መመስከሩን ለማሳየት በአቡ ዳውድ ውስጥ የሚገኘውን ተከታዩን ሐዲስ ጠቅሷል፡-
“… ለአላህ መልእክተኛ (ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁንና) ወንበር አመጡላቸው፤ ተቀመጡበትም፡፡ ከዚያም ተውራት አምጡልኝ አሉ፤ አመጡላቸውም፡፡ ከዚያ ከወንበሩ ላይ ተነስተው ተውራትን አስቀመጡና እንዲህ አሉ፡– በአንተ እና አንተን በገለጠው አምላክ አምናለሁ፡፡” Sunan Abu Dawud, Book 38 (Kitab al Hudud, i.e. Prescribed Punishments), Number 4434
ኢብን አል-ቀይም ይህንን ሐዲስ ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ ሲል ይደመድማል፡-
“ሊቃውንቱ እንደሚሉት ቶራህ የተበረዘ ቢሆን ኖሮ ወንበሩ ላይ አያስቀምጡትም ነበር፤ ደግሞም ‹በአንተና አንተን በገለጠው አምናለሁ› ብለው አይናገሩም ነበር፡፡” (Ibn Qayyim al-Jawziyyah, Ighathat Al Lahfan, Volume 2, p. 351)
ሙሐመድ ራሱ እንዲህ ባለ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስን ካከበረ የዘመናችን ሙስሊሞች ነቢያቸውን ለማስዋሸት የሚደክሙት ለምንድነው? መልሱ ቀላልና ግልፅ ነው፡፡ ነቢያቸው ለቅዱሳት መጻሕፍት የሰጠውን ምስክርነት ከተቀበሉ ከእነዚሁ መጻሕፍት ጋር የሚጋጩ የቁርኣን ትምህርቶችን ለመጣል ሊገደዱ ነው፡፡ ሙሐመድ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ይዘታቸውን የሚያውቅ ሰው ስላልነበረ እንዲሁ በደፈናው ተቀብሎ መሰከረላቸው፡፡ የዘመናችን ሙስሊሞች ደግሞ የቅዱሳት መጻሕፍትን ይዘት ስለተረዱ የነቢያቸውን ምስክርነት እንዳይቀበሉ የቁርኣንን ትምህርት ውድቅ ማድረግ ሆኖባቸው ተቸግረዋል፡፡ የሙሐመድ ምስክርነት ትክክል ከሆነ የሙሐመድ ትምህርት ስህተት ይሆናል፡፡ የሙሐመድ ትምህርት ትክክል ከሆነ የሙሐመድ ምስክርነት ስህተት ይሆናል፡፡ በሁለቱም መንገዶች ሙሐመድ ሐሰተኛ ነቢይ፣ እስልምናም የሐሰት ሃይማኖት ነው፡፡
አቡ ሀይደር
ሀሳቡን ጠቅለል ለማድረግ፡- ከላይ ባየናቸው አራት የቅዱስ ቁርኣን አንቀጾች ውስጥ ‹‹የአላህ ቃላት›› ተብሎ የተጠቀሰው፡ አላህ አስቀድሞ የወሰነውና የፈረደው መለኮታዊ ቃሉን፣ ለነቢያቱና ለአማኝ ባሪያዎቹ የገባላቸውን መልካም የተስፋ ቃል-ኪዳኑን፣ በከሀዲንና በአመጸኞች ላይ የተዛተባቸውን የቅጣት ቃሉን የሚገልጽ ነው፡፡ በተጨማሪም ለሰው ልጆች የሕይወት መመሪያ ይኾን ዘንድ በነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ አለይሂ ወሰለም) በኩል የተወረደውን ቅዱስ ቁርኣን የሚገልጽ ነው እንጂ፡ ስለ ቀደምት መለኮታዊ መጽሐፍት የሚናገር አይደለም የሚለውን ድምዳሜ መያዝ እንችላለን ማለት ነው፡፡
መልስ
ይህንን ድምዳሜ መያዝ እንደማንችል ከላይ ተመልክተናል፡፡ ድምዳሜውን ለመያዝ አመክንዮ፣ የሙስሊም ሊቃውንት ትርጓሜና የሙሐመድ የራሱ ምስክርነት እንደማይፈቅዱ በበቂ ማስረጃ ዓይተናል፡፡ ሙስሊሙ ሰባኪ የጥቅሶቹን አመክንዮአዊ ምልከታ ባለማገናዘብ፣ ከሊቃውንቱ መካከል የሚመቹትን ብቻ በመምረጥ እንዲሁም የሙሐመድን ምስክርነት ችላ በማለት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ችሏል፡፡
አቡ ሀይደር
እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ፡- ቀደምት መለኮታዊ መጽሐፍት (ተውራት. ዘቡር. ኢንጂልና የነቢያት መጻሕፍት) የአላህ ቃል አይደሉም ወይ? የሚል ከኾነም፡ መልሱ፡- አዎን የአላህ ቃል ናቸው! ብለን እንመልሳለን፡፡ ጥያቄውም ይቀጥልና፡- እነዚያ መጻሕፍትም የአላህ ቃል ከኾኑ፡ ለምን እነሱንም ‹‹የአላህ ቃላት መልለወጥ የላትም›› የሚለው ውስጥ አብረው አልተካተቱም? ካሉን ደግሞ ምላሻችን እንደሚከተለው ይቀርባል፡-
1ኛ/ የቅዱስ ቁርኣንን ሀሳብ ለመረዳት አንደኛው መንገድ ሲያቅ (ኮንቴክስት) ማየትና ከግምት ማስገባት ነው፡፡ የአንቀጹን መልእክት ከላይና ከታች ከተጠቀሱት ጋር በማመሳከር ስለምን እየተነገረ እንደኾነ መረዳት ይቻላል፡፡ የቅዱስ ቁርኣን የተፍሲር ሊቃውንትም በጉዳዩ ላይ የሰጡትን ትንተና ማየቱ ለመረዳት የበለጠ ያግዛል፡፡ ከዚህ በመነሳት በአራቱም አንቀጾች ላይ ያሉትን ሀሳቦች ወደ ላይ ወደ ታች ብትመለከቱ፡ እንዲሁም የተፍሲር ሊቃውንትን ሀሳብ ብትመለከቱ፡ ስለ ቀደምት መለኮታዊ መጻሕፍት የሚያወራ ነገር አታገኙም፡፡ ስለዚህ እኛም ከሊቃውንቱ ሀሳብ የወጣ ነገር አይኖረንም ማለት ነው፡፡
መልስ
አቡ ሀይደርን የመሳሰሉት የዳዋ አስፋፊዎች ስለ አውድ ሲናገሩ ከመስማት በላይ አስገራሚ ነገር የለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ከአውድ ገንጥለው እየጠቀሱ ለማጋጨት የሚሞክሩ፣ ቁርአናቸውን ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር ለማስማማትና ትንቢታዊ እንዲሆን ለማድረግ ሲቆነጣጥሩትና ሲያፍተለትሉት ውለው የሚያድሩ ሙስሊም ሰባኪያን ስለ አውድ ይጨነቃሉ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነው፡፡ ይህ ሙስሊም ሰባኪ ይህንን ጽሑፍ ከመቋጨቱ በፊት የገዛ ቁርአኑን ጥቅስ ከአውድ በመገንጠል መጽሐፍ ቅዱስ የተረዘ እንደሆነ እንደሚናገር ለማስመሰል ሲሞክር መታዘባችን ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡
ከላይ እንደተመለከትነው አጥ-ጠበሪ፣ አል-ቡኻሪ እና አር-ራዚን የመሳሰሉት ታላላቅ ሙስሊም ሊቃውንት ጥቅሶቹን በቁርኣን ብቻ ወስነው አልዘጉም፡፡ በጥቅሶቹ ውስጥ የሚገኘው “የፈጣሪ ቃል አይለወጥም” የሚለው መርህ ሁሉንም ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያጠቃልል ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ ሙስሊሙ ሰባኪ “ከሊቃውንቱ ሐሳብ የወጣ ነገር አይኖረንም” ሲል ምን ማለቱ ነው? የገዛ ሊቃውንቱ በጉዳዩ ላይ ወጥ አመለካከት እንደሌላቸው ስለማያውቅ ነው ወይስ አውቆ ለማወናበድ?
ሌላው መገንዘብ ያለብን ነገር የሊቃውንት አቋም ምንም ይሁን ምን መቀበል የሚኖርብን ምክንያታዊና አሳማኝ እስከ ሆነ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ሊቃውንትም እንደ እኛው ሰዎች በመሆናቸው የሃይማኖታቸውን ደካማ ጎን ለመሸፈን ወይም እውነት መስሏቸው በመሳሳት ትክክል ያልሆነ አቋም ሊያራምዱ ይችላሉ፡፡ እግዚአብሔር አእምሮ የሰጠን እንድናመዛዝንና እንድናገናዝብ እንጂ በጭፍን እንድንነዳ አይደለም፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ግለሰብ ምንም ያህል የሊህቅና ደረጃ ቢኖረው ሐሳቡን ከመቀበላችን በፊት “ለምን?” ብለን መጠየቅ ተፈጥሯዊ መብታችን ነው፤ ደግሞም ከስህተት ለመዳን አስፈላጊ ነው፡፡ አንድን ሐሳብ በምክንያትና በማስረጃ ሳይሆን “እገሌ ተናግሮታል” ብሎ መቀበል “Argumentum ad Verecundiam” (Appeal to Authority) የተሰኘ የሥነ አመክንዮ ተፋልሶ ነው፡፡
አቡ ሀይደር
2ኛ/ ከቅዱስ ቁርኣን በፊት የነበሩት ቀደምት መለኮታዊ መጻሕፍት፡ ለዘልዓለሙ ተጠብቀው እንዲቆዩ አምላካዊ ዋስትና አልተሰጣቸውም፡፡ የመጽሐፍቶቹም ኾነ የነቢያቱ ተልእኮ በጊዜና በቦታ የተገደበ እንጂ ዘላለማዊና ዘውታሪ አልነበረም፡፡ ከነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በፊት የነበረ መልክተኛ የሚላከው ለሕዝቦቹ እንጂ፡ ለዓለማት አልነበረም፡፡ መልእክቱም ተልእኮውም በሕዝቦቹ ላይ ብቻ የተገደበ ነበር፡፡ ደግሞም ነቢይ በሞተ ቁጥር፡ ወዲያውኑ ሌላ ነቢይ በማስነሳት ይተካላቸው ስለነበር፡ ትምሕርቱ ቢጠፋ እንኳ ያ ከኋላ የተነሳው ነቢይ ያድስላቸው ነበር ማለት ነው፡፡
መልስ
በየትኛው የመረጃ ምንጭ መሠረት ነው “ቀደምት መለኮታዊ መጻሕፍት ለዘለዓለሙ ተጠብቀው እንዲቆዩ አምላካዊ ዋስትና ያልተሰጣቸው”? መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል የማያልፍና ዘላለማዊ መሆኑን ይናገራል፡-
“ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፥ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።” (ኢሳይያስ 40፡8)
“ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።” (ማቴዎስ 21፡33)
“በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤” (ራእይ 14፥6)
“አቤቱ፥ ቃልህ በሰማይ ለዘላለም ይኖራል። እውነትህ ለልጅ ልጅ ናት ምድርን መሠረትሃት እርስዋም ትኖራለች። ሁሉም ባሪያዎችህ ናቸውና ቀኑ በትእዛዝህ ይኖራል። ሕግህ ተድላዬ ባይሆን፥ ቀድሞ በጐስቍልናዬ በጠፋሁ ነበር። በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና ፍርድህን ለዘላለም አልረሳም።” (መዝሙር 119፡89-93)
“ከእነርሱ ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ይህ ነው ይላል እግዚአብሔር፤ በአንተ ላይ ያለው መንፈሴ በአፍህም ውስጥ ያደረግሁት ቃሌ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ ከአፍህ ከዘርህም አፍ ከዘር ዘርህም አፍ አያልፍም፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡” (ኢሳይያስ 59፡21)
እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ።” (ማቴዎስ 5፡18)
እነዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት የማይለወጠውንና የማይሻረውን የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ቃል ስለያዙ በንግግርም ሆነ በጽሑፍ ደረጃ ሳይለወጡ እንደሚኖሩ ይናገራሉ፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍቱ ስለ ራሳቸው እንዲህ ያለ ምስክርነት በሚሰጡበት ሁኔታ ሙስሊሙ ሰባኪ “ከቁርኣን በፊት የነበሩት ቀደምት መለኮታዊ መጻሕፍት ለዘለዓለሙ ተጠብቀው እንዲቆዩ አምላካዊ ዋስትና አልተሰጣቸውም” ብሎ ማለቱ የከፋ እብለት ነው፡፡ አስተውሎት ያለው ሰው መለኮታዊ የሆነ ማንኛውም ነገር ከብክለትና ብልሽት የጸዳ መሆኑን ይገነዘባል፡፡ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን አንድ አረብ ነጋዴ ወደ ዋሻ ገብቶ በመውጣት ተገለጠልኝ ያለው ከነቢያትና ከሐዋርያት መልእክት ጋር የሚጋጭ ቅዠት እውነት እንዲሆን መለኮታዊ መጻሕፍት እንደ ተራ የሰው ቃል የግድ መበላሸትና መለወጥ አለባቸው ብሎ መሟገት በፈጣሪ ላይ መሣለቅ ነው!
የነቢያትና የክርስቶስን የተልዕኮ አድማስ በተመለከተ እስልምና እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ አቋሞች ናቸው ያሉት፡፡ በአንድ ወገን ሁሉም ነቢያት ለሕዝባቸው ብቻ እንደተላኩና ሙሐመድ ደግሞ ለመላው ዓለም እንደተላከ የሚናገር ሲሆን (Sahih al-Bukhari, Volume 1, Book 7, Number 331) በሌላ ወገን ደግሞ ከሕዝባቸው ውጪ ለሚገኙ ለሌሎች ሕዝቦች፣ አልፎም ለመለው ዓለም የተላኩ መልእክተኞች እንዳሉ ይናገራል፡፡ ለምሳሌ ያህል ሙሴ የእስራኤል ነቢይ ቢሆንም ወደ ፈርዖንና ወደ ግብፃውያን ተልኳል (ሱራ10፡75-83፣ 14፡4-6፣ 11፡96-99፣ 73፡15-16)፡፡ ሙሴ ወደ ግብፃውያን የተላከበት አኳኋን ሙሐመድ ወደ ራሱ ሕዝቦች ከተላከበት ሁኔታጋር እንደሚመሳሰል ሱራ 73፡15-16 ላይ ተነግሯል፤ ስለዚህ ከተልዕኮ ዓይነት አኳያ የሚቀርብ ሙግት ውድቅ ነው፡፡ ሙሴ በምድረ ግብፅ ያደገ ቢሆንም ግብፃውያን የሙሴ ሕዝብ መሆናቸው በቁርኣን ውስጥ አልተነገረም፡፡ ቁርኣን በሙሴ ሕዝብና በግብፃውያን መካከል ግልፅ ልዩነት ያስቀምጣል (ሱራ 7:127-128፣ 26:52-66፣ 40:28, 45-46፣ 43:52-55) ስለዚህ ሙሴ የራሱ ወገን ወዳልሆነ ሕዝብ ስለተላከ በግብፅ ምድር ማደጉ ከግብፃውያን ወገን አያደርገውም፡፡ ወደ ሌሎች ሕዝቦች የተላከ ሌላኛው እስራኤላዊ ነቢይ ዮናስ ነው፡፡ ዮናስ እስራኤላዊ ቢሆንም ወደ ኢራቅ ሀገር ወደ ነነዌ ሕዝቦች ተልኳል (ሱራ10:98፣ 35:147-148)፡፡ በተጨማሪም በቁርኣን መሠረት የክርስቶስ ተልዕኮ ዓለም አቀፋዊ ነው፡-
“ያችንም ብልቷን የጠበቀቺውን በርሷም ውስጥ ከመንፈሳችን የነፋንባትን እርሷንም ልጅዋንም (እንደዚሁ) ለዓለማት ተዓምር ያደረግናትን (መርየምን አስታውስ)፡፡” (ሱራ 21፡91)
ይህ የቁርኣን ጥቅሰ ማርያምና ልጇ ለዓለማት ተዓምር መሆናቸውን ይናገራል፡፡ ዓለም አቀፋዊ አስፈላጊነት የሌለው አካል ለመላው ዓለም ምልክት ሊሆን እንዴት ይችላል? እስላማዊ መጻሕፍት ይህንን ሐቅ በማጠናከር ክርስቶስ ሐዋርያቱን ወደ መላው ዓለም መላኩን ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ቀዳሚውን የሙሐመድ ግለ ታሪክ የመዘገበው ኢብን ኢስሐቅ የክርስቶስ ሐዋርያት የተላኩባቸውን ሕዝቦች ቋንቋዎች ሁሉ ተዓምራዊ በሆነ መንገድ እየተናገሩ ማስተማራቸውን፣ ጳውሎስና ጴጥሮስን በስም በመጥቀስ ወደ ሮም እንደተላኩ እንዲሁም በርቶሎሜዎስ ወደ አረብያ እንደተላከ ጽፏል (The Life of Muhammad: A Translation of Ibn Ishaq’s Sirat Rasul Allah, by Alfred Guillaume, p. 653)፡፡ አል-ጃላላይን እና ኢብን አባስ በተፍሲራቸው ወደ አንፆኪያ ስለተላኩ ሦስት የክርስቶስ መልእክተኞች ጽፈዋል https://quranx.com/Tafsirs/36.13 ፡፡ ኢብን ከሢር ደግሞ ሦስቱ መልእክተኞች ስምዖን፣ ዮሐንስና ጳውሎስ መሆናቸውን ጠቅሷል (Tafsir Ibn Kathir (Abridged), Volume 8, Surat Yasin (36) Verse 14 to 15)፡፡ አጥ-ጠበሪም በተመሳሳይ ጳውሎስና ጴጥሮስ ወደ ሮም፣ ቶማስ ወደ ባቢሎን፣ ዮሐንስ ወደ ኤፌሶን፣ በርቶሎሜዎስ ወደ ሂጃዝ፣ ስምዖን ወደ ሰሜን አፍሪካ እንደተላኩ ጽፏል (Tabari, History, Volume IV, p. 123)፡፡ እነዚህ ዘገባዎች ከመጽሐፍ ቅዱስና ከክርስትና ታሪኮች ጋር ይስማማሉ ስለዚህ ዓለም አቀፋዊ ድንበሮችን ተሻግረው ወደ ሌሎች ሕዝቦች የተላኩ መልእክተኞች መኖራቸውን ቁርኣንና ሌሎች እስላማዊ ምንጮች እስከተናገሩ ድረስ ቅዱሳት መጻሕፍትን በአንድ ሕዝብ መወሰን አይቻልም፡፡ ቁርኣንና ሐዲስን ስንመለከት ሙሐመድ ከአሕዛብ ወገን የሆኑና ክርስቲያኖች የሆኑ ሕዝቦችን “የኢንጂል ሰዎች” “የመጽሐፉ ሰዎች” በማለት የክርስቶስ ተከታዮች መሆናቸውን ዕውቅና በመስጠት ይጠቅሳቸዋል፡፡ ክርስቶስ ለአይሁድ ብቻ ቢሆን ኖሮ አላህ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑት ተከታዮቹ ዕውቅናን ባልሰጠ ነበር፡፡ እስልምና ይህንን ውስጣዊ ግጭቱን ባላስታረቀበት ሁኔታ ሙስሊሙ ሰባኪ ቅዱሳት መጻሕፍት በተወሰኑ ሕዝቦች የተገደቡ መሆናቸውን መናገሩ ተቀባይነት የለውም፡፡
አቡ ሀይደር
ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐሌሂ ወሰለም) ግን የተላኩት በየትኛውም ዘመንም ኾነ በየትኛውም ስፍራ ለሚኖር የሰው ዘር በጠቅላላ በመኾኑ (4፡79፣ 7፡158፣ 21፡107፣ 34፡28) ቁርኣንም የወረደው እንደዛው ለዓለማት ሕዝቦች የሕይወት መመሪያ እንዲሆን ስለኾነ (6፡90፣ 25፡1፣ 68፡52) ትንሳኤ/ቂያማ እስኪመጣና እስኪከሰት ድረስ ጌታ አላህ ‹‹እኔው እንዳወረድኩት እኔው እጠብቀዋለሁ›› በማለት ቃል ገባለት (ሱረቱል-ሒጅር 15፡9)፡፡
መልስ
የሙሐመድ መልእክት አረቦችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በቁርኣን ውስጥ እንደተገለጸው ሙሐመድ ብዙ ጊዜ ራሱን ለአረቦች ብቻ የተላከ መልእክተኛ አድርጎ ይቆጥር የነበረ ሲሆን በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ዓለም አቀፋዊ አስፈላጊነት እንዳለው ተናግሯል፡፡ የቁርኣንን ይዘት ስንመለከት አረቦችን በተመለከቱ ጉዳዮች የተሞላ ከመሆኑም በላይ አረብኛ መሆኑና ሌላ ቋንቋ አለመሆኑ አረቦችን ለመጥቀም እንደሆነ ይናገራል፡፡ በሌላ ወገን አዲስ ኪዳንን ስንመለከት ከሉቃስ በስተቀር ጸሐፊያኑ አይሁድ ቢሆኑም የክርስቶስን መልእክት በዘመኑ በነበረው ዓለም አቀፍ ቋንቋ በኮይኔ ግሪክ ነበር ሲጽፉ የነበሩት፡፡ በበዓለ ሃምሳ ዕለት በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው የተለያዩ የዓለም ቋንቋዎችን መናገራቸው ተልዕኳቸው ዓለም አቀፋዊ መሆኑን ያሳያል (የሐዋርያት ሥራ 2)፡፡ በአንፃሩ ግን የሙሐመድ መልእክት በአንድ ቋንቋ የተገደበ መሆኑና በሌላ ቋንቋ “አለመውረዱ” አረቦችን ለመጥቀም መሆኑን ቁርኣን ይናገራል፡–
“አንቀጾቹ የተብራሩ የኾነ መጽሐፍ ነው፡፡ ዐረብኛ ቁርኣን ሲኾን ለሚያውቁ ሕዝቦች (የተብራራ) ነው፡፡” (ሱራ 41፡3)
በዚህ ጥቅስ ውስጥ በቅንፍ (የተብራራ) የሚለው በዋናው አረብኛ ውስጥ የሌለ ሲሆን “ዐረብኛ ቁርኣን ሲኾን ለሚያውቁ ሕዝቦች ነው” በማለት መጽሐፉ አረብኛ ለሚያውቁ ሕዝቦች መሆኑን ይገልጻል፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸው ጥቅሶች አሉ፡-
“እኛ (ፍቹን) ታውቁ ዘንድ ዐረብኛ ቁርኣን ሲሆን በእርግጥ አወረድነው፡፡” (ሱራ 12፡2)
“እኛ ታውቁ ዘንድ ዐረብኛ ቁርኣን አደረግነው፡፡” (ሱራ 43፡3)
እነዚህ ጥቅሶች ቁርኣን አረቦችን ታሳቢ ያደረገ መጽሐፍ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ሙሐመድም ከእርሱ በፊት የነበሩት መልእክተኞች ወደ ገዛ ሕዝባቸው እንደተላኩት ሁሉ እርሱም የአረቦች መልእክተኛ መሆኑን በተደገጋጋሚ ተናግሯል፡-
“እንደዚሁም የከተሞች እናት የኾነችውን (የመካን ሰዎች) በአካባቢዋ ያሉትንም ልታስፈራራ የመሰብሰቢያውንም ቀን በእርሱ ጥርጣሬ የሌለበት ሲኾን ልታስጠነቅቅ ዐረብኛ የኾነን ቁርኣን ወደ አንተ አወረድን፡፡ (ከእነርሱም) ከፊሉ በገነት ውሰጥ ከፊሉም በእሳት ውስጥ ነው፡፡” (ሱራ 42፡7)
“«አላህ (አወረደው)» በላቸው፡፡ ከዚያም በውሸታቸው ውስጥ የሚጫወቱ ሲኾኑ ተዋቸው፡፡ ይህም ያወረድነው የኾነ ብሩክ ያንንም በፊቱ የነበረውን (መጽሐፍ) አረጋጋጭ መጽሐፍ ነው፡፡ የከተሞችን እናት (መካን) እና በዙሪያዋ ያሉትንም ሰዎች ልታስጠነቅቅበት (አወረድነው)፡፡ እነዚያም በመጨረሻይቱ ዓለም የሚያምኑት እነርሱ በሶላታቸው ላይ የሚጠባበቁ ሲኾኑ በርሱ ያምናሉ፡፡” (ሱራ 6፡92)
“እነዚያም የካዱት በእርሱ ላይ ከጌታው ተዓምር ለምን አልተወረደለትም ይላሉ፡፡ አንተ አስፈራሪ ብቻ ነህ፡፡ ለሕዝብም ሁሉ መሪ አላቸው፡፡” (ሱራ 13፡7)
“እርሱ ያ በመሃይሞቹ ውስጥ አንቀጾቹን (ቁርኣንን) በእነርሱ ላይ የሚያነብላቸው፣ (ከማጋራት) የሚያጠራቸውም፣ መጽሐፍንና ጥበብን የሚያስተምራቸውም የኾነን መልክተኛ (ሙሐመድን) ከእነርሱው ውስጥ የላከ ነው፡፡ እነርሱም ከእርሱ በፊት በግልጽ ስሕተት ውስጥ ነበሩ፡፡” (ሱራ 62፡2)
ከላይ የሚገኙት ጥቅሶች ሙሐመድ በመካና በዙርያዋ ላሉት አረብኛ ተናጋሪ ሕዝቦች የተላከ መሆኑን፤ ቋንቋውም ሆነ መልእክቱ እነርሱን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በሌሎች ቦታዎች ግን ለሰው ልጆች የተላከ መልእክተኛ መሆኑን ተናግሯል (ሱራ 34፡28፣ 25፡1)፡፡
ስናጠቃልል የሙሐመድ መልእክትም ሆነ ቋንቋው አረቦችን ብቻ ታሳቢ ያደረገ ቢሆንም ራሱን ዓለም አቀፋዊ አስፈላጊነት ያለው መልእክተኛ አድርጎ አቅርቧል፡፡ የክርስቶስን ሐዋርያት ስንመለከት ግን መልእክታቸውም ሆነ ቋንቋቸው ዓለም አቀፋዊ ነበር፡፡ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ተጽፈው በተጠናቀቁ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች በመተርጎም ለብዙ የዓለም ሕዝቦች ተዳርሰዋል፡፡
አቡ ሀይደር
ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐሌሂ ወሰለም) የነቢያት መደምደሚያ በመኾናቸውና ከሳቸው በኋላ ከአላህ ዘንድ የሚላክ ነቢይ ባለመኖሩ ሰበብ፡ አላህ የኢስላምን መልእክት እስከመጨረሻው ዘመን ማብቂያ ድረስ ሊጠብቀው ቃል ገባ፡፡ ቃል በገባለት መሰረትም፡ ዲኑ እስካሁን ሳይበረዝና ሳይደለዝ አልለ ማለት ነው፡፡ ቀደምት መጻሕፍት ግን ምንም በውስጣቸው የአላህ ቃላት ቢኖሩም የሰው ሀሳብና ስህተቶችንም አብረው አቅፈዋል፡፡ ስለዚህ ‹‹መልለወጥ የላትም›› የሚለው ውስጥ መካተት የሚችለው ቁርኣን ነው፡፡
መልስ
ሙስሊም ፕሮፓጋንዲስቶች ከሚያወሩት በተጻራሪ ቁርኣን ብዙ መለዋወጦችን ያስተናገደ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህንን ከእስላማዊ ምንጮች እንዲሁም ከእጅ ጽሑፎች መረዳት ይቻላል፡፡ ተከታዮቹን ጽሑፎች ይመልከቱ፡-
- ቁርኣን በትክክል ተጠብቋልን?
- የቁርኣን መበረዝ በጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች ላይ የተደረገ አዲስ ጥናት
- የኡሥማን ቁርኣንን የማረም ሒደት ከጥርጣሬ የፀዳ ነበርን?
- ቁርኣን አንድ ነውን?
- አወዛጋቢው የሐፍስ ቁርኣን አመራረጥ
- ከቁርኣን ውስጥ የጠፉ 213 አንቀጾች!
- የሐፍሷ ቢንት ዑመር “ኦሪጅናል” ቁርኣን ለምን ተቃጠለ?
ቁርኣን ሰዎች ሲሰርዙትና ሲደልዙት የኖሩት መጽሐፍ ሆኖ ሳለ አላህ እስከመጨረሻው ዘመን ማብቂያ ድረስ ሊጠብቀው ቃል እንደገባ መናገር የሚቻለው እንዴት ነው?
ይህ ሙስሊም ሰባኪ “የአላህ ቃል መለወጥ የላትም” የሚለውን ቃል ከእስልምና የሽረት አስተምህሮ ጋር እንዴት እንደሚያስታርቅ ቢነግረን ጥሩ ነው፡፡ አላህ ቃሉ በባሕርዩ እንደማይለወጥ አስቀድሞ ስላስታወቀን በሽረትም ሆነ በማንኛውም መንገድ ቢለወጥ አለመለወጥ የቃሉ ባሕርይ እንደሆነ የሚናገረው የቁርኣን ጥቅስ ሐሰት ሊሆን ነው፡፡ “የአላህ ቃል መለወጥ የላትም” (10፡64)፡፡ “አይለወጥም” ሲል ትኩረቱ በለዋጩ ማንነት ላይ ሳይሆን በቃሉ ባሕርይ ላይ በመሆኑ አላህ ቃሉን መለዋወጡ ግጭትን ይፈጥራል፡፡
አቡ ሀይደር
3ኛ/ በብዙ የቅዱስ ቁርኣን ክፍሎች ላይ ቀደምት መለኮታዊ መጽሐፍት የሰው እጅ እንደገባባቸውና እንደተበረዙ ተገልጾአል፡፡ ከዚህ በመነሳትም ‹‹የአላህ ቃላት መልለወጥ የላትም›› የሚለውን ለቀደምት መለኮታዊ መጻሕፍት መተርጎሙ የሚያስኬድ አይደለም ማለት ነው፡፡ ከነዚህም የቁርኣን ክፍሎች ውስጥ አንዱ እንዲህ ይላል፡-
” فَوَيْلٌ لِلَّذِينَ يَكْتُبُونَ الْكِتَابَ بِأَيْدِيهِمْ ثُمَّ يَقُولُون
َ هَذَا مِنْ عِنْدِ اللَّهِ لِيَشْتَرُوا بِهِ ثَمَنًا قَلِيلًا فَوَيْلٌ لَهُمْ مِمَّا كَتَبَتْ أَيْدِيهِمْ وَوَيْلٌ لَهُمْ مِمَّا يَكْسِبُونَ ” سورة البقرة 79
“ለነዚያም መጽሐፉን በእጆቻቸው ለሚጽፉና ከዚያም በርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «ይህ ከአላህ ዘንድ ነው» ለሚሉ ወዮላቸው፡፡ ለነርሱም ከዚያ እጆቻቸው ከጻፉት ወዮላቸው፡፡ ለነሱም ከዚያ ከሚያፈሩት (ኃጢኣት) ወዮላቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡79)፡፡
በዚህ የቅዱስ ቁርኣን አንቀጽ ላይ ታዋቂው የቁርኣን ተንታኝና ሊቅ የኾነው ታላቁ ሶሓቢይ ዐብዱላህ ኢብኑ ዐብባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዲህ ይላል፡-
عَنْ عَبْدِ اللَّهِ بْنِ عَبَّاسٍ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُمَا، قَالَ: ” يَا مَعْشَرَ المُسْلِمِينَ، كَيْفَ تَسْأَلُونَ أَهْلَ الكِتَابِ، وَكِتَابُكُمُ الَّذِي أُنْزِلَ عَلَى نَبِيِّهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ أَحْدَثُ الأَخْبَارِ بِاللَّهِ، تَقْرَءُونَهُ لَمْ يُشَبْ، وَقَدْ حَدَّثَكُمُ اللَّهُ أَنَّ أَهْلَ الكِتَابِ بَدَّلُوا مَا كَتَبَ اللَّهُ وَغَيَّرُوا بِأَيْدِيهِمُ الكِتَابَ، فَقَالُوا: هُوَ مِنْ عِنْدِ اللَّهِ لِيَشْتَرُوا بِهِ ثَمَنًا قَلِيلًا، أَفَلاَ يَنْهَاكُمْ مَا جَاءَكُمْ مِنَ العِلْمِ عَنْ مُسَاءَلَتِهِمْ، وَلاَ وَاللَّهِ مَا رَأَيْنَا مِنْهُمْ رَجُلًا قَطُّ يَسْأَلُكُمْ عَنِ الَّذِي أُنْزِلَ عَلَيْكُمْ ” رواه البخاري 2685.7522.7523
ዐብዱላህ ኢብኑ-ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዲህ ይላል፡- “እናንተ ሙስሊሞች ሆይ! በነቢዩ ላይ የተወረደላችሁ መጽሐፍ (ቁርኣን) ከአላህ ዘንድ የመጣ አዲስ (ያላረጀ) ሆኖ ሳለ፡ እናንተም ያልተበረዘና የሰው እጅ ያልገባበት ሆኖ እያነበባችሁት፡ የመጽሐፉን ሰዎች (አይሁዶችና ክርስቲያኖች) እንዴት ትጠይቃላችሁ? አላህም (በቁርኣኑ) የመጽሐፉ ሰዎች መጽሐፉን በእጃቸው እንደበረዙትና እንደቀየሩት፣ ከዛም የተበረዘውን ጥቂትን ምድራዊ ዋጋ ለመሸመት፡ ይህ ከአላህ ዘንድ የመጣ ነው እንዳሉ ነግሯቹኋል፡፡ እንግዲያውስ ወደናንተ የመጣላችሁ ዕውቀት እነሱን ከመጠየቅ አይከለክላችሁምን? በአላህ ይሁንብኝ! ከነሱ ውስጥ አንድም ሰው ወደናንተ ስለወረደው ሲጠይቁአችሁ በፍጹም አላየንም (ታዲያ እናንተ እነሱን እንዴት ትጠይቃላችሁ?)” (ቡኻሪይ 2685፣ 7522፣ 7523)፡፡
መልስ
በሌላ ጽሑፍ በስፋት እንዳተትነው ከኢብን ዐባስ ጋር የተያያዘው ሐዲስ የቁርኣንን ጥቅስ የተረጎመበት መንገድ ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ ትክክል ነው ከተባለ ቁርኣን በሱረቱ ዩኑስ 10፡94 ላይ “ወደ አንተም ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን እነዚያን ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ…” ብሎ በሌላ ቦታ ላይ ደግሞ “መጽሐፋቸው የተበረዘ ነው” የሚል ከሆነ እርስ በርሱ ይጋጫል ማለት ነው፡፡ በርግጥ የጥቅሱን አውድ የምንመለከት ከሆነ ኢብን ዐባስ መሳሳቱ ግልፅ ይሆንልናል፡፡ ሐዲሱ የሚጠቅሰው የቁርኣን ክፍል እንዲህ ይነበባል፡-
“(አይሁዶች) ከነሱ የኾኑ ጭፍሮች የአላህን ቃል የሚሰሙና ከዚያም ከተረዱት በኋላ እነርሱ እያወቁ የሚለውጡት ሲኾኑ ለናንተ ማመናቸውን ትከጅላላችሁን? እነዚያንም ያመኑትን ባገኙ ጊዜ «አምነናል» ይላሉ፡፡ ከፊላቸውም ወደ ከፊሉ ባገለለ «ጊዜ አላህ በናንተ ላይ በገለጸላቸሁ ነገር እጌታችሁ ዘንድ በርሱ እንዲከራከሩዋችሁ ትነግሩዋቸዋላችሁን? አታውቁምን?» ይላሉ፡፡ አላህ የሚደብቁትንና የሚገልጹትን የሚያውቅ መኾኑን አያውቁምን? ከነሱም መጽሐፉን የማያውቁ መሃይማናን አሉ፡፡ ግን ከንቱ ምኞቶችን (ይመኛሉ)፤ እነርሱም የሚጠራጠሩ እንጂ ሌላ አይደሉም፡፡ ለነዚያም መጽሐፉን በእጆቻቸው ለሚጽፉና ከዚያም በርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «ይህ ከአላህ ዘንድ ነው» ለሚሉ ወዮላቸው፡፡ ለነርሱም ከዚያ እጆቻቸው ከጻፉት ወዮላቸው፡፡ ለነሱም ከዚያ ከሚያፈሩት (ኃጢኣት) ወዮላቸው፡፡” (አል-በቀራ 2፡175-179)
የጥቅሱ አውድ እንደሚናገረው እነዚህ ወገኖች ከአይሁድ ወገን የሆኑ የተወሰኑ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የተወሰኑ ሰዎች ሙስሊሞችን ሲያገኙ እስልምናን የተቀበሉ ይመስላሉ ነገር ግን እውነተኛ አማኞች አይደሉም፡፡ ከእነርሱ ወገን የሆኑ መጽሐፉን የማያውቁ መሃይማን ደግሞ አሉ፡፡ ከአውዱ እንደሚታየው ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ መጽሐፉን በእጆቻቸው የሚጽፉትና ከአላህ ዘንድ እንደሆነ የሚናገሩት እነዚህ ሐሰተኛ ወገኖች ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ትክክለኛውን መጽሐፍ አያውቁትም ነገር ግን ሌላ መጽሐፍ በእጃቸው በመጻፍ ይሸጣሉ፡፡ በዚህ ስፍራ መጽሐፍ ሻጮቹ ክርስቲያኖች አይደሉም፤ አይሁድ ናቸው፡፡ ከአይሁድም ሁሉም አይሁድ አይደሉም፤ የተወሰኑት ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ እስልምናን የተቀበሉ የሚያስመስሉ ነገር ግን ከልባቸው ያላመኑ ናቸው፡፡ ይህንን ተግባር የሚፈፅሙት ደግሞ ሁሉም ሳይሆኑ ከእነርሱ መካከል የተወሰኑ መሃይማን ናቸው፡፡ የሚጽፉት መጽሐፍ ምን እንደሆነ ባይገለጽም መጽሐፍ ቅዱስ ሊሆን አይችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ኮፒዎች የተሰራጨና በሊቃውንቱ እጅ የሚገኝ በመሆኑ ምክንያት ጥቂት አይሁድ ለዚያውም እስልምናን እንደተቀበሉ የሚናገሩ ለሙሐመድ ቅርበት የነበራቸው ወገኖች ሊለውጡት የሚችሉት አይደለም፡፡ ስለዚህ አቡ-ሃይደር የጠቀሰው የኢብን ዐባስ ትርጓሜ የጥቅሱን አውድ የሳተ ነው፡፡ የተሳሳተ ሐሳብ በማንም ተነገረ በማን ስህተት እስከሆነ ድረስ ስህተት ነው፡፡
ይህንን አባባል ከኢብን ዐባስ እንደተላለፈ አድርጎ ያቀረበው አል-ቡኻሪ በሌላ ሐዲስ ደግሞ ይህንን የሚጣረስ ከኢብን ዐባስ የተላለፈ ሌላ ሐሳብ ያቀርብልናል፡፡ ዕውቁ ሙፈሲር ኢብን ከሢር እንዲህ ጠቅሶታል፡-
“… አል ቡኻሪ እንደዘገበው ኢብን አባስ እንዲህ ብሏል፤ ‹የዚህ አያ ትርጉም የሚከተለው ነው፡- … ከአላህ ፍጥረታት መካከል ማንም የአላህን ቃላት ከመጻሕፍቱ ውስጥ ማስወገድ አይችልም፡፡ ግልፅ ትርጉማቸውን ያጣምማሉ ማለት ነው፡፡› ወሃብ ኢብን ሙነቢህ እንዲህ አለ “ተውራት እና ኢንጂል ልክ አላህ በገለጣቸው ሁኔታ ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡ ከውስጣቸው አንድም ፊደል አልተወገደም፡፡ ነገር ግን ሰዎች ራሳቸው በጻፏቸው መጻሕፍት ላይ ተሞርኩዘው በመጨመርና ውሸት በሆነ አተረጓጎም ሌሎችን ያሳስታሉ፡፡” … “የአላህ መጻሕፍት ግን እስከ አሁን ተጠብቀው ይገኛሉ፤ ሊለወጡም አይችሉም፡፡” (Tafsir Ibn Kathir – Abridged, Volume 2, Parts 3, 4 & 5, Surat Al-Baqarah, Verse 253, to Surat An-Nisa, verse 147, First Edition: March 2000, p. 196)
እዚሁ ተፍሲር የግርጌ ማስታወሻ ላይ እንዲህ የሚል እናገኛለን፡-
“ቃሉን ያጣምማሉ ማለት ትርጉሙን ይለውጣሉ ወይም ያጣምማሉ ማለት ነው፡፡ ከየትኛውም የአላህ መጻሕፍት ውስጥ አንድ ቃል እንኳ መለወጥ የሚችል የለም፡፡ ይህ ማለት በተሳሳተ መንገድ ይተረጉማሉ ማለት ነው፡፡”
ስለዚህ የቱ ነው ትክክል? ሙስሊሞች ባይወዱትም ትክክለኛው ትርጓሜ የኋለኛው ነው፡፡ ሙሐመድ አንድ ጊዜም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ መበረዙን ተናግሮ አያውቅም፡፡ ይልቅስ ሥልጣኑን ተቀብሎ አክብሮት ይሰጠው ነበር፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስነውን የሱናን አቡዳውድ ሐዲስ ደግመን እናንብበው፡-
“… ለአላህ መልእክተኛ (ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁንና) ወንበር አመጡላቸው፤ ተቀመጡበትም፡፡ ከዚያም ተውራት አምጡልኝ አሉ፤ አመጡላቸውም፡፡ ከዚያ ከወንበሩ ላይ ተነስተው ተውራትን አስቀመጡና እንዲህ አሉ፡– በአንተ እና አንተን በገለጠው አምላክ አምናለሁ፡፡” Sunan Abu Dawud, Book 38 (Kitab al Hudud, i.e. Prescribed Punishments), Number 4434
ኢብን ከሢር ደግሞ አላህ ስላዘዘው ሙሐመድ ይህንን ማድረጉን ይናገራል፡፡ (Tafsir Ibn Kathir (Abridged) Volume 3, Parts 6, 7 & 8)
ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስ እንደተበረዘ ሲናገሩ ከገዛ ነቢያቸው በላይ ራሳቸውን አዋቂ እያደረጉ ነው፡፡
አቡ ሀይደር
4ኛ/ ወገኖቻችን እንደሚሉት ‹‹የአላህ ቃላት መለወጥ የልላትም›› የሚለው እነሱ ዘንድ ያለውን መጽሐፍ ‹መጽሐፍ ቅዱስ›ንም የሚጨምር ከኾነ፡ እንግዲያውስ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ለምን አንድ ወጥ አልኾነም? ለምን ሁላችሁም የምትይዙት አንድ አይነት አልኾነም? የአንደኛው ግሩፕ በውስጡ 66 መጻሕፍት ያሉት፣ የሌላኛው ደግሞ 73 መጻሕፍትን በውስጡ የያዘ፣ ሶስተኛው ደግሞ 81 መጻሕፍትን ያቀፈ መጽሐፍ ለምን ኾነ? ይህ በራሱ ለመጽሐፉ መለወጥ በቂ ማስረጃ አይሆንምን? በማለት ልንጠይቃችሁ እንወዳለን፡፡
መልስ
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ከመስጠታችን በፊት ጥያቄው አመክንዮአዊ ተፋልሶ እንዳለበት ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ቁርኣን የአላህ ቃል እንደማይለወጥ ከተናገረና መጽሐፍ ቅዱስ የአላህ ቃል መሆኑን ከመሰከረ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ የእውነት ተለውጦ ከሆነ ምክንያታዊ ድምዳሜ ሊሆን የሚችለው ቁርኣን የአላህ ቃል እንደማይለወጥ መናገሩ ወይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ የአላህ ቃል መሆኑን መመስከሩ ስህተት ነው የሚል ነው፡፡ ከሁለት አንዱ የግድ ስህተት ነው፤ በሁለቱም መንገዶች ደግሞ እስልምና ሐሰት ይሆናል፡፡ ምክንዮውን የማይገነዘቡ ወገኖች ካሉ እሰኪ በቀላል መንገድ እናስቀምጠው፡-
- በቁርኣን መሠረት የአላህ ቃል አይለወጥም፡፡
- ቁርኣን መጽሐፍ ቅዱስ የአላህ ቃል መሆኑን ይመሰክራል፡፡
- መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጧል፡፡
- ስለዚህ ቁርኣን የአላህ ቃል እንደማይለወጥ መናገሩ ስህተት ነው፡፡
ወይም ደግሞ፡-
- በቁርኣን መሠረት የአላህ ቃል አይለወጥም፡፡
- ቁርኣን መጽሐፍ ቅዱስ የአላህ ቃል መሆኑን ይመሰክራል፡፡
- መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጧል፡፡
- ስለዚህ ቁርኣን መጽሐፍ ቅዱስ የአላህ ቃል መሆኑን መመስከሩ ስህተት ነው፡፡
ሙስሊም ሰባኪያን መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጧል የሚሉ ከሆነ ጥያቄ ማንሳት ያለባቸው የአላህ ቃል እንደማይለወጥ በተናገረው በገዛ ቁርአናቸው ላይ ነው፡፡
ለጥያቄው መልስ ስንሰጥ፤ የቀኖና ልዩነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መካተት ያለባቸው መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው? በሚለው ጥያቄ ዙርያ የተፈጠረ ልዩነት እንጂ የተካተቱት መጻሐፍት መለወጣቸውን ለማሳየት ሊቀርብ የሚችል ሙግት አይደለም፡፡ እውነት ነው አብያተ ክርስቲያናት የተለያዩ ቀኖናዎች አሏቸው፡፡ ነገር ግን የአፖክሪፋ መጻሕፍት ቀኖና መሆን አለመሆናቸው የክርስትናን ዋና ዋና አስተምህሮዎች በምንም መልኩ የሚነካ አይደለም፡፡ የተቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መቀየራቸውንም አያሳይም፡፡ ይህ ጉዳይ እንደ ከባድ ችግር የሚቆጠር ከሆነ በመጀመርያዎቹ የእስልምና ዘመናት የተለያዩ የቁርኣን ቅጂዎች እንደነበሩ ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡ የኡበይ ቢን ከዕብ ቁርኣን 116፣ የአብደላህ ኢብን መስዑድ 111፣ የኡሥማን 114 ሱራዎች ነበሯቸው፡፡ ልዩነቱ ኡሥማን አንዱን ቀኖና ብቻ መርጦ ሌሎቹን ሕገ ወጥ ማድረጉና ክርስቲያኖች ግን ያንን ማድረግ አለመቻላቸው ነው፡፡ በዚህ ዘመን እንኳ ሐፍስ፣ ዋርሽ፣ አል ዱሪ፣ ቃሉን፣ ወዘተ. የተሰኙ ብዙ ልዩነቶችን የሚያሳዩ ከ 24 ያልተናነሱ የአረብኛ የቁርኣን ንባቦች ይገኛሉ፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሚጠቀሙት የሐፍስ ቁርኣን በ1924 የግብፅ ካይሮ ኦፊሴላዊ ቁርኣን ተደርጎ የታወጀ ሲሆን ዓለም አቀፋዊ እንዲሆን የተደረገው በ1985 ዓ.ም. በሳዑዲው ንጉሥ ፈሐድ አማካይነት ነበር፡፡ በወቅቱም አንድ ዓይነት ሳይሆን ወደ አምስት ዓይነት የሚሆኑ የሐፍስ ቁርአኖች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ለማወቅ እዚህ ጋ እና እዚህ ጋ ጠቅ ያድርጉ፡፡
የሙስሊሞች የቀኖና ችግር በቁርኣን ብቻ የተገደበ ሳይሆን ሐዲስንም ይጨምራል፡፡ የሐዲስ መጻሕፍት ሃይማኖታዊና ሌሎች ጉዳዮችን ለመወሰን የሚያስችሉ የሙሐመድ ቅንጭብጫቢ ታሪኮችና ንግግሮች ሲሆኑ በእስልምና በጣም ወሳኝ ናቸው፡፡ የሐዲስ መጻሕፍት የእስልምና ቀኖና አካል ናቸው፡፡ ሆኖም የትኛው ሐዲስ መካተት እንዳለበት በሙስሊሞች መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ትልቅ አለመግባባት አለ፡፡ ሱኒና ሺኣ የተለያዩ ሐዲሳት ያሏቸው ሲሆን ጭራሹኑ ሐዲስን የማይቀበሉ ሙስሊሞችም አሉ፡፡ ስለዚህ የእስልምና ቀኖና እስከ ዛሬ ድረስ ያልተዘጋና ተለዋዋጭ ነው፡፡ በተጨማሪም “ሐዲስ ቁድሲ” ከተባሉት የአላህ ቃሎች እንደሆኑ ከሚታመኑት የሐዲስ ክፍሎች ትክክለኞቹ የትኞቹ ናቸው? በሚለው ላይ ሙስሊሞች ስምምነት የላቸውም፡፡ የሺኣ ሙስሊሞች ከአል-ቡኻሪና ከሙስሊም ሐዲሳት ውስጥ የተሰበሰቡትን የአላህ ቃሎች የተባሉትን ብዙዎቹን ሐዲስ ቁድሲ ሐሰተኛ ቃሎች እንደሆኑ ነው የሚያምኑት። ሱኒዎችም ከሺኣ ምንጮች የተሰበሰቡ ብዙ “ሐዲስ ቁድሲዎችን” አይቀበሉም፡፡ ሁለቱም አንጃዎች የሚጋሯቸው “ሐዲስ ቁድሲዎች” ቢኖሩም አንዳቸው ብቻ ተቀብለው ሌላኛቸው የማይቀበሏቸው ብዙ አሉ፡፡ ሙስሊሞች በራሳቸው ቀኖና እስከ ዛሬ ስላልተስማሙ ነገሮችን ማጋነን ማቆም ያስፈልጋቸዋል፡፡
በቅርቡ በማሕበራዊ ሚድያዎች ላይ አሰራጭቼ መልስ ያላገኘሁለትን ጥያቄ እዚህ ጋ በማምጣት ምላሼን እቋጫለሁ፡፡
ያልተለመዱ ቁርአኖች መኖራቸውን ያውቃሉ?
ብዙ ሙስሊሞች ቁርኣን አንድ ዓይነት ብቻ መሆኑን ነው የሚያውቁት፡፡ ሻል ያለ ዕውቀት ያላቸው ቂርኣት በሚል አከፋፈል ሰባት ዓይነት ቁርኣኖች መኖራቸውን ያውቃሉ ነገር ግን ልዩነቶቹ የአጻጻፍ እንጂ የትርጉም እንዳልሆነ ያምናሉ፡፡ ጥሩ ዕውቀት ያላቸው ደግሞ ልዩነቱቹ የአጻጻፍ ብቻ ሳይሆን የትርጉምም መሆኑን ይገነዘባሉ፤ በቂርኣት አከፋፈልም ቁርኣን በሰባት ያልተወሰነና አሥር ዓይነት መሆኑን፤ አሥሩ ደግሞ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ቁርአኖችን በውስጣቸው መያዛቸውን፤ ሁለት ሁለት የተባሉትም አንዳንዶች የተለያዩ ዓይነት ቁርአኖችን በውስጣቸው መያዛቸውን ያውቃሉ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በሙስሊም ሊቃውንት ዘንድ “ያልተለመዱ” ተብለው የተገለሉ ብዙም የማይወራላቸው ቁርአኖች መኖራቸውን የሚያውቁት ጥቂቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ቁርአኖች በቁጥር አራት ሲሆኑ መጠርያቸውም፡- ኢብን ሙሐይሲን፣ አል-ያዚዲ፣ አል-ሐሰን እና አል-ዓመሽ ይሰኛሉ፡፡ ኢማም አንነወዊ እና ሌሎች ሙስሊም ሊቃውንት “ያልተለመዱ” በተባሉት በነዚህ ንባቦች መሠረት ቁርኣንን ማነብነብ የተወገዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ስለ እነዚህ ቁርአኖች የተወሰኑ መረጃዎችን ቀጥሎ በተቀመጠው ታዋቂ የፋትዋ ድረ-ገፅ ላይ ማግኘት ይቻላል፡-
ስለ እነዚህ አራት ዓይነት ቁርአኖች ያለን መረጃ የዘገባ ሰንሰለታቸው (ኢስናድ) በብዙ አስተላላፊዎች የተረጋገጠ (ሙተወቲር) ሳይሆን ባለ አንድ የዘገባ ሰንሰለት (አሓድ) ነው በሚል በሙስሊም ሊቃውንት መወገዛቸውን ነው፡፡ አሥሩ ቂርኣት እርስ በርሳቸው አንደማይስማሙት ሁሉ እነዚህም ቁርኣኖች ከአሥሩ ጋር የሚስማሙ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ለሙስሊም ወገኖቻችን ያለን ጥያቄ፡- እነዚህ ቁርኣኖች የተበረዙ ወይም ሰው ሠራሽ ከሆኑ በቁርኣን ጥበቃ ላይ ጥያቄ ለማንሳት አንገደድም ወይ? ምናልባት ከእነዚህ ቁርኣኖች መካከል አንዱ ትክክለኛ ሊሆን የመቻል ዕድል እንደሌውና በጊዜ ብዛት ትክክለኛነቱ አለመደብዘዙን በምን እርግጠኛ መሆን ይቻላል? የሙስሊም ሊቃውንት ሐሳብ ትክክል ከሆነና እነዚህ ቁርአኖች ሰው ሠራሽ ከሆኑ “እርሱን የሚመስል መጽሐፍ ማንም መፍጠር እንደማይችል” የሚናገሩት የቁርኣን አናቅፅ ምን ሊሆኑ ነው? የጥንት ሙስሊሞች ከቀርአን(ኖች) ጋር በጣም የሚመሳሰሉ ነገር ግን እውነተኛ ቁርኣን(ኖች) ያልሆኑ መጻሕፍትን ጽፈዋልና! ሙስሊም ወገኖች ቁርአናችሁ እንዲህ ያለ ገፅታ ያለው መጽሐፍ የመሆኑ እውነታ ከልጅነታችሁ ሲነገራችሁ ከነበረው የቁርኣን ፍፁማዊ አንድነት ትርክት አኳያ እንዴት ታዩታላችሁ?
[1] ሙስሊም ወገኖቻችን አላህ ቁርኣንን እንደሚጠብቅ ቃል ስለገባ ሊበረዝ አይችልም፤ ሌሎች መጻሕፍትን ለመጠበቅ ቃል ስላልገባ ሊበረዙ ይችላሉ በማለት ይናገራሉ። ለማስረጃነትም ተከታዩን ጥቅስ ይጠቅሳሉ:-
إِنَّا نَحْنُ نَزَّلْنَا الذِّكْرَ وَإِنَّا لَهُ لَحَافِظُونَ
“እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፡፡ እኛም ለእርሱ ጠባቂዎቹ ነን፡፡” (ሱራ 15:9)
ነገር ግን በጥቅሱ ውስጥ “ቁርኣንን” የሚለው ቃል የአማርኛ የተሳሳተ ትርጉም መሆኑንና በአረብኛው ውስጥ እንደማይገኝ አያውቁም። الذِّكْرَ (አዝዚክረ) የሚለው ቃል “አስታዋሽ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን (ዝክር ከሚለው የግዕዝ ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው) ቁርኣንን ብቻ ሳይሆን “አላህ ያወረዳቸውን” ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ያጠቃልላል። ይህንንም ከተከታዮቹ የቁርኣን ጥቅሶች መረዳት ይቻላል:- ሱራ 16:43፣ 21:7፣ 21:48፣ 21:105፣ 40:53-54። በነዚህ ሁሉ ጥቅሶች ውስጥ የቀደሙት ቅዱሳት መጻሕፍት “ዚክር” በሚል ተመሳሳይ የአረብኛ ቃል ተጠቅሰዋል። የአማርኛ ተርጓሚዎች ሱራ 15:9ን “ቁርኣን” በማለት በቦታው ላይ ባልተጠቀሰ ቃል መተርጎማቸው ስህተት ነው። ቁርኣንን ለማመልከት የገባ ቃል አድርገው ቢቆጥሩት እንኳ በቦታው ላይ ባልተጠቀሰ ቃል መተርጎም ትክክል አይደለም።
ሙስሊም ወገኖቻችን የጥቅሱ አውድ ለሙሐመድ የወረደለትን ዚክር ወይም ቁርኣን ብቻ የሚያመለክት እንጂ የቀደሙትን ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያጠቃልል አይደለም የሚል ሙግት ያቀርባሉ፡፡ ለዚህም መነሻቸው ሱራ 15፡6 ላይ ለሙሐመድ አዝዚክር እንደወረደለት መነገሩ ነው፡- “«አንተ ያ በእርሱ ላይ ቁርኣን (አዝዚክሩ) የተወረደለት ሆይ! አንተ በእርግጥ ዕብድ ነህ» አሉም፡፡” ነገር ግን ቁጥር 9 ላይ “አዝዚክር” ለሙሐመድ ብቻ “የተገለጠውን” በሚያመለክት መንገድ “ላንተ የተገለጠውን አዝዚክር” ወይም “ይኸኛውን አዝዚክር” በማለት በቁርኣን ብቻ ወስኖ አላስቀመጠም፡፡ ከላይ ቁጥር 6 ላይ ለሙሐመድ የተገለጠውን አዝዚክር ስለጠቀሰ ቁጥር 9 ላይ የግድ ተመሳሳይ ሐሳብ እንዲይዝ የሚያስገድድ ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ምዕራፍ ወደ ፊት አልፈን ብንመለከት በአንድ ቁጥር ልዩነት ውስጥ ይኸው ቃል ሁለት መጻሕፍትን ለማመልከት ውሏል፡- “ከአንተም በፊት ወደእነሱ ወሕይን (ራእይን) የምናወርድላቸውን ሰዎችን እንጂ ሌላን አልላክንም፡፡ የማታውቁም ብትኾኑ የዕውቀትን (አዝዚክሪ) ባለቤቶች ጠይቁ፡፡ በግልጽ ማስረጃዎችና በመጻሕፍት (ላክናቸው)፡፡ ወደ አንተም ለሰዎች ወደእነሱ የተወረደውን (ፍች) ልትገልጽላቸውና ያስተነትኑም ዘንድ ቁርኣንን (አዝዚክረ) አወረድን” (ሱራ 16፡43-44)፡፡ ከዚህ ክፍል እንደምንመለከተው በተከታታይ ቁጥሮች ውስጥ አንዱ ቃል ሁለት መጻሕፍትን ለማመልከት ውሏል፡፡ ስለዚህ ምዕራፍ 15 ላይ አንዱ ቃል በሦስት ቁጥሮች ልዩነት የግድ አንድ ነገር ብቻ ማሳየት አለበት ማለት የሚያስኬድ አይደለም፡፡ በሌላ ቦታ እንዲሁ ይኸው ቃል ለሙሐመድ የተገለጠለትና የቀደሙት መጻሕፍት አንድ መሆናቸውን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል፡- … ይህ (ቁርኣን) እኔ ዘንድ ያለው ሕዝብ መገሰጫ (ዚክሩ) ከእኔ በፊትም የነበሩት ሕዝቦች መገሰጫ (ዚክሩ) ነው» በላቸው …” (21፡24)፡፡ በዚህ ጥቅስ መሠረት ለሙሐመድ የተገለጠው ዚክር ከዚያ ቀደም ለነበሩት ሕዝቦች ከተሰጠው ዚክር ጋር በአንድነት ተቆጥሯል፡፡ እዚህ አንቀፅ ውስጥ ዚክር የተባሉት ቶራህ እና ወንጌል መሆናቸውን አል-ጃለላይን በተፍሲራቸው ጽፈዋል https://quranx.com/Tafsir/Jalal/21.24 ፡፡ ስለዚህ ሱራ 15፡9 “አዝዚክር” በቁርኣን ብቻ የተወሰነ ሳይሆን አጠቃላዩን መለኮታዊ መገለጥ የሚያመለክት ነው፡፡
ሙስሊም ወገኖች ቃሉን በቁርኣን ብቻ ለመወሰን የሚቀርቡት ሌላው ምክንያት በብዜት ሳይሆን በነጠላ “አዝዚክር” መባሉ ነው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ጥቅሶች አንጻር ስንመለከት ይህ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ሱራ 16፡43 ላይ ቶራህ እና ወንጌል ሁለት መጻሕፍት ሆነው ሳሉ “አዝዚክሩ” ተብለው በነጠላ ተጠቅሰዋል፡፡ ሱራ 21፡24 ላይ እንዲሁ ለሙሐመድ “የተገለጠው” ከቀደሙት መገለጦች ጋር አንድ ተደርጎ “ዚክሩ” በሚል ነጠላ ቃል ተገልጿል፡፡ በእስልምና መሠረት ለሰው ልጆች የተሰጡት መጻሕፍት ሁሉ ከሰማይ ከ “ለውህ አል-ማህፉዝ” (የተጠበቀ ሰሌዳ) ተከፋፍለው የመጡ የአንድ መጽሐፍ አካል ናቸው፤ ስለዚህ ሱራ 15፡9 ላይ “አዝዚክር” ተብሎ በነጠላ ቃል የተቀመጠው አጠቃላዩን መለኮታዊ መገለጥ ለማመልከት ነው፡፡
ስናጠቃልል “አላህ” በቁርኣን ውስጥ ቁርኣንን ብቻ ነጥሎ እንደሚጠብቅና ሌሎቹን መጻሕፍት እንደማይጠብቅ የተናገረበት ጥቅስ የለም፡፡
ለተጨማሪ ንባብ
- እስላም እና ክርስትና – ንጽጽራዊ አቀራረብ ለዶ/ር ሙሐመድ ዓሊ አልኹሊ የተሰጠ ምላሽ
- መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ!
- ተውራትና ኢንጅል መጽሐፍ ቅዱስ ናቸውን?
- እስላማዊ አጣብቂኝ :- መጽሐፍ ቅዱስ ከተበረዘ ቁርኣን ዋሽቷል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ካልተበረዘ ቁርኣን የፈጣሪ መጽሐፍ አይደለም!
- ኢንጂል ተበርዟልን?
- በእጃችን የሚገኙት ብሉይና አዲስ ኪዳናት በሙሐመድ ዘመን በአይሁዶችና በክርስቲያኖች እጅ ነበሩ፤ ቁርኣንም ይመሰክርላቸዋል