አድሃ በኢንጂል፤ ፈጣሪ ያዘጋጀው ትክክለኛ የመዳን መንገድ 

አድሃ በኢንጂል

ፈጣሪ ያዘጋጀው ትክክለኛ የመዳን መንገድ 

ፉአድ መስሪ

በኢ-ቡክ መልክ www.fouadmasri.com  ላይ ይገኛል

በመላው ዓለም የሚገኙት ሙስሊሞች በየዓመቱ የአል-አድሃን በኣል ያከብራሉ፡፡ ይህ በኣል በሙስሊሞች የጨረቃ አቆጣጠር መሠረት ዙል ሒጃ በመባል በሚታወቀው ወር 10ኛ ቀን ላይ ይውላል፡፡

አድሃ የሚለው ቃል ዳሂያ ወይንም መሥዋዕት ከሚለው የአረብኛ ሥረወ ቃል የተገኘ ነው፡፡ የአል-አድሃ በኣል የመሥዋት በኣል ወይንም ታላቁ በኣል፣ ዒድ አል ከቢር በመባል ይታወቃል፡፡ በቱርክ ዓለም ውስጥ የአድሃ በኣል ቁርባኒ በመባል ይታወቃል፡፡

በአል-አድሃ በኣል ዕለት ሙስሊሞች ፈጣሪ የአብርሃምን ልጅ የዋጀበትን ክስተት ለማስታወስ በግ ይሠዋሉ፡፡ ይህ ክስተት በቁርአን ውስጥ ሱራ 37፡99-111 ላይ ተዘግቧል፡፡

የአይሁድ ሃይማኖት ተከታዮችም እግዚአብሔር የአብርሃምን ልጅ በበግ የዋጀበትን ይህንን ክስተት ያምናሉ፡፡ አብርሃም ልጁን ሊሠዋ ሲል የእግዚአብሔር ቅዱስ መልአክ አስቆመው፡፡ አብርሃምም ቀንዱ በዕፀ ሳቤቅ የታሰረ በግ ተመለከተ፡፡ በጉን በመውሰድ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው፡፡ የዚህ ታሪክ ሙሉ ዘገባ በተውራት ውስጥ ዘፍጥረት 22፡1-19 ላይ ይገኛል፡፡

የአይሁድ ሃይማኖት ይህንን ክስተት እንደ በኣል ባያስብም በነቢዩ ሙሴ በተሰጣቸው የፋሲካ በኣል ውስጥ ተመሳሳይ ሐሳብ ይገኛል፡፡ አይሁድ እግዚአብሔር የበኩር ልጆቻቸውን እንዳይሞቱ ከግብፃውያን የለየበትን በኣል ያከብራሉ፡፡ የሞት መልአክ በበራቸው መቃን ላይ የበጉን ደም የቀቡትን የበኩር ልጆቻቸውን ሳይጎዳ ያልፋቸው ነበር፡፡ ፋሲካ በተውራት ውስጥ ዘጸአት 12፡1-14 ላይ ተመዝግቧል፡፡

የክርስቲያን አድሃ ወዴት አለ?

ክርስቲያኖች በአይሁድ ፋሲካም ሆነ በአድሃ (የአብርሃም ልጅ በበግ የተዋጀበትን ክስተት) የሚያምኑ ቢሆኑም እንደ በኣል ሲያከብሯቸው የማይታየው ለምንድነው? የክርስቲያን ፋሲካና አድሃ አለን? ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት አዲስ ኪዳንን በማጥናት የእግዚአብሔርን ባሕርይና ለሰው ልጆች ያዘጋጀውን ዕቅድ መመልከት ያስፈልገናል፡፡

የኢንጂል አስተምሕሮ

1.       እግዚአብሔር ፍቅር ነው

እግዚአብሔር አፅናፈ ዓለምን የፈጠረ ሲሆን ከፍጥረቱ ጋር ሕብረት ማድረግ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ሕብረት በማድረግ ይደሰታል፡፡ የፍጥረቱ ቁንጮዎች ሲሆኑ አእምሮና ፈቃድ የተሰጣቸው ብቸኛ ፍጥረታት ናቸውና፡፡

ኢንጂል እንዲህ ይላል፡-

 “እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል።” (1ዮሐንስ 4፡16)

በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።(ዮሐንስ 3፡16)

እግዚአብሔር ከሰው ልጆች ጋር ሕብረት ማድረግ የሚፈልግ ከሆነ ዓለማችን ከእግዚአብሔር የራቀችው ለምን ይሆን? ሰዎች ከእግዚአብሔር የተለዩ እንደሆኑ ስለምን ይሰማቸዋል? የእግዚአብሔርን ፍቅር እንዳናጣጥም ትልቅ ባሕር የከፈለን ይመስላል፡፡

2.       እግዚአብሔር ቅዱስ ነው

እግዚአብሔር ቅዱስና ጻድቅ ሲሆን ሰዎች ግን ኃጢአተኞች ናቸው፡፡ በሁሉም ቦታ የሰዎችን ኃጢአተኝነት እናያለን፡፡ ተግባሮቻቸው የኃጢአት በሽታ ምልክቶች ናቸው፡፡ ኃጢአት በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ ነው፡፡

ሁሉም የሰው ልጆች ኃጢአትን ሠርተዋል፡፡ ኃጢአት የእግዚአብሔርን መንገድ ከመምረጥ ይልቅ የገዛ ራሳችንን መንገድ መምረጥ ነው፡፡ ሁሉም የሰው ልጆች የእግዚአብሔርን ሕግ ከመከተል ይልቅ በገዛ መንገዳቸው ነጉደዋል፡፡ኢንጂል ኃጢአት ብሎ የሚጠራው ይህንን አለመታዘዝነው፡፡

ሁላችንም በሃያሉ ፈጣሪያችን ላይ ኃጢአትን የሠራን ቢሆንም ወንጀላችንን ማስወገድ አይቻንም፡፡ ጻድቅ የሆነው እግዚአብሔር ቅዱስ በመሆኑ ኃጢአተኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር ሕብረት የለውም፡፡

ኢንጂል ሁሉም ሰዎች በቅዱሱ እግዚአብሔር ላይ ኃጢአት መሥራታቸውን ይናገራል፡-

“ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል።” (ሮሜ 3፡10-12)

“ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” (ሮሜ 3፡23)

አፍቃሪና ቅዱስ ከሆነው ፈጣሪያችን የለየን ኃጢአት መሆኑን ኢንጂል ይናገራል። የእግዚአብሔር ቅድስና ኃጢአትን ይቃወማል። የእግዚአብሔር ቅዱስ የሆነ ባሕርይ ኃጢአትን መቀበል አይችልም። ስለዚህ ሰውና እግዚአብሔር ኃጢአት በተባለ ትልቅ ባሕር ተለያይተዋል።

ይህ ከእግዚአብሔር መለየት መንፈሳዊ ሞትን ያስከትላል።

ኢንጂል እንዲህ ይላል፦

“የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው።” (ሮሜ 6:23)

የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው ነገር ግን ሌላኛውን ሃጢአተኛ ሞቶ ሊዋጅ የሚችል ሃጢአተኛ የለም። ይህ ደግሞ በቅዱሱ እግዚአብሔርና በሰዎች መካከል ትልቅ ባሕር ሆኖዋል።

አምፖል የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያስፈልገው ሁሉ ሰዎችም እግዚአብሔር ያስፈልጋቸዋል፡፡ አምፖል ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል የሞተ፣ ሕይወት አልባና ዓላማ የለሽ ነው፡፡ ኃጢአት እኛን ከእግዚአብሔር በመለየት በመንፈስ ሙታን፣ ሕይወት አልባና ዓላማ የለሽ እንድንሆን አድርጎናል።

3.       እግዚአብሔር ፍትሃዊ ነው

የእግዚአብሔር ፍትሃዊ ባሕርይ ኃጢአትን እንዲቀጣና እንዲያጠፋ ያስገድደዋል። በሃያሉ ፈጣሪያችን ላይ ኃጢአትን ስለሠራን ቅጣቱ ሞት ነው። አንድ ኃጢአተኛ የኃጢአት ዕዳው እስኪከፈል ድረስ እግዚአብሔር ይቅር ሊለው አይችልም። ፆምና ድኾችን መርዳትን የመሳሰሉት መልካም ሥራዎች የእግዚአብሔርን ችሮታ በማስገኘት ዕዳችንን መክፈል አይችሉም። በጣም መልካም የምንለው ተግባር እንኳ የእግዚአብሔርን ፍፁማዊ ቅድስናና ፍትህ ሊስተካከል አይችልም። ስለዚህ ከኛ መካከል ምርጥ የምንለው ሰው እንኳ ፍፁም የሆነውን ፈጣሪያችንን ለማስደሰት የማይበቃ በመሆኑ ኃጢአተኛ ነውና ቅጣት ይገባዋል።

ወንጀለኛ ወንጀለኛን ሊዋጅ አይችልም። በቀላል አባባል፤ ከሰው ልጆች መካከል ኃጢአት የሌለበትና ከእግዚአብሔ ጸጋ ያልጎደለ ማንም የለም። የእግዚአብሔር ፍትሃዊ ባሕርይ ይህ ታላቅ ዕዳ ሳይከፈል ይቅር እንዲባል አይፈቅድም። የገዛ መንገዳችንን በመምረጥ የእግዚአብሔርን ተዕዛዛት ስለተላለፍን ቅጣታችንን መክፈል ይኖርብናል። ያ ቅጣት ደግሞ ከፈጣሪያችን መለየት ነው።

4.       እግዚአብሔር መሓሪ ነው

የእግዚአብሔር ምሕረት ለዚህ ችግር ምላሽ ይሰጠናል። እግዚአብሔር ፍጥረቱ ከሆንነው ከእኛ ጋር ሕብረት ማድረግ ቢፈልግም የኃጢአት ባሕር ግን ለይቶናል።

ባሕሩን ተሻግሮ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የሚችለው ጻድቅ የሆነ ሰው ብቻ ነው። ነገር ግን ሁሉም ሰው ኃጢአት መሥራቱንና አለመብቃቱን ቀደም ሲል አረጋግጠናል!

ሁሉም ሰው፤ ከኢየሱስ በስተቀር። ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ በሆነው እግዚአብሔርና  ኃጢአተኛ በሆኑት የሰው ልጆች መካከል የሚገኝ ድልድይ መሆኑን ኢንጂል ያስተምራል።

ለምን ኢየሱስ ብቻ? ለምን ሌላ ሰው አልሆነም?

ተዓምራዊ ልደት

ኢንጂል እንደሚያስተምረው ኢየሱሰ ሰው የሆነ አባት የሌለውና በመንፈስ ቅዱስ ሃይል የተጸነሰ ነው። ከድንግል የተወለደ ብቸኛው ሰው ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በሰው ፈቃድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ የተከናወነ ነበር።

ኢየሱስ ክርስቶስ በተዓምራዊ ልደቱ ለየት ያለ ነበር። ከድንግል የተወለደ መሪ ወይንም ነቢይ የለም። ሁሉም ነቢያት ሰዎች ብቻ መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣ ቃል፣ ከሊመት አላህ ነው። ይህንን ተዓምር የሠራው የእግዚአብሔር ሃይል ነው።

“መልአኩም እንዲህ አላት፦ ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። ማርያምም መልአኩን፦ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፥ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። ማርያምም፦ እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ።” (ሉቃስ 1:30-37)

ተዓምራዊ የሆነ ሕይወት

ኢየሱስ ክርስቶስ የቅድስናና የቅንነትን ሕይወት ኖረ። በሕይወት ዘመኑ በሙሉ ለእግዚአብሔር ሕግ ታዛዥ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ከማንም በተለየ ሁኔታ ያስተማረ ሲሆን በሰዎች ላይ የነበሩትን ድካሞችና ህመሞች ሁሉ ፈወሰ። ከልደቱ አንስቶ ኃጢአት የሌለበትና በምድር ላይ ከኖሩት መምህራን ሁሉ የላቀው ነው።

“ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር። ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ አጋንንትም ያደሩባቸውን በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፥ ፈወሳቸውም። ከገሊላም ከአሥሩ ከተማም ከኢየሩሳሌምም ከይሁዳም ከዮርዳኖስም ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።” (ማቴዎስ 4:23-25)

ተዓምራዊ አሟሟት

ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው ጥሩ አስተማሪ ወይንም ፈዋሽ ብቻ ለመሆን ሳይሆን የእግዚአብሔር መሥዋዕት ለመሆን ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ከልደቱ አንስቶ ጻድቅና ኃጢአት የሌለበት በመሆኑ ሞቱ ብቻ የኃጢአትን ቅጣት ሊከፍል ይችላል። የሰው ልጆችን ከውድቀት ሊያድን ነው የመጣው። ሁሉም በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአትን መሥራታቸውንና ደህንነት እንደሚያስፈልጋቸው ኢንጂል በግልፅ ይናገራል። ደህንነት ማለት እኛ መክፈል የማንችለውን ዕዳ ሌላ ሰው ስለከፈለልን በእግዚአብሔር ይቅርታን ማግኘት ማለት ነው።

ብቸኛ ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ መክፈል የማንችለውን ዕዳ ከፈለልን። የሰው ልጆች በኃጢአት ሙታን ነበሩ። ኃጢአት እኛንና እግዚአብሔርን የለየ ባሕር ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ የሆነ መሥዋዕት በመሆን ለሰው ዘር በሙሉ ሞቷል። አብርሃም በልጁ ፋንታ በግ እንደሰዋው ሁሉ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ሞትም የሰው ልጆችን የኃጢአት ዕዳ ከፍሏል።

የአብርሃም ልጅ ነፃ ይሆን ዘንድ በጉ ሞተ። ልክ እንደዚሁ እኛ ነፃ እንሆን ዘንድ ኢየሱስ ሞተ። እግዚአብሔር የአብርሃምን ልጅ በበግ እንደዋጀው ሁሉ ዓለምንም በኢየሱስ ክርስቶስ ዋጅቷል።

ሙስሊሞች በዒድ አል-አድሃ ዕለት እንዲሁም እስራኤላውያን ከግብጽ መውጣታቸውን አስመልክቶ በግ እንደሚሰውት ሁሉ፣ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ እኛ ፍጹም መሥዋዕት አደረገው።

ኢየሱስ እውነተኛው አድሃ ሆነ። የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እርሱ ነው። መጥምቁ ዮሐንስ (ነቢዩ ያህያ) ኢየሱስን ባየ ጊዜ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፦

“እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።” (ዮሐንስ 1:29)

እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእርሱ በለየን ባሕር ላይ ድልድይን ሠራ።

“ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው።” (2ቆሮንቶስ 5:18)

የኃጢአት ዕዳ ስለተከፈለ የእግዚአብሔር ፍትህ ረካ። የሰው ልጆች ቤዛን ስላገኙ የእግዚአብሔር ምህረት ተፈፀመ።

ተዓምራዊ ትንሣኤ

ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ይኖረን ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢአት ዕዳችንን ከፈለ።

ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቅ በመሆኑ ሞት የሚገባው አልነበረም። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ደህንነት መሥዋዕት ይሆን ዘንድ ሥጋ በመሆን የመጣ የእግዚአብሔር ቃል ነው።

አስቀድሞ በተተነበየው መሠረት ከርስቶስ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነስቷል። የክርስቶስ ትንሣኤ መስዋዕትነቱ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን አረጋገጠ።

እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ፦ መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ…” (1ቆሮንቶስ 15:3-6)

በመላው ዓለም የሚገኙት ክርስቲያኖች አድሃንና ፋሲካን የከርስቶስን ስቅለትና ትንሣኤ አስመልክተው በአንድ ላይ እንደ ታላቅ በኣል ያከብሩታል። ይህም በአማርኛ ፋሲካ፣ በእንግሊዘኛ ኢስተር፣ በአረብኛ ደግሞ ዒድ አል-ቂያማ በመባል ይታወቃል። ይህ አድሃና ፋሲካ የተገናኙበትና የተፈፀሙበት ነው!

እነዚህ ሁለቱ ክስተቶች ትክክለኛውን ቤዛነት መረዳት እንችል ዘንድ እግዚአብሔር የተጠቀማቸው ተምሳሌቶች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የበጎችና የሌሎች እንስሳት መሥዋዕት ሃጢአታችንን ማንፃት አይችልም። ጽድቃችንም ፍፁም ከሆነው የእግዚአብሔር ጽድቅ ጋር ሲስተያይ እንደ ቆሻሻ ጨርቅ ነው። በኛ ላይ የነበረውን ታላቅ የእግዚአብሔር ዕዳ መክፈል የሚችል ማንም የለም።

ደስ የሚያሰኘው የምሥራች ግን እግዚአብሔር የዓለምን ኃጢአት ያስወግድ ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስን መላኩ ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ የኛ እውነተኛው አድሃ ነው!

አንድ ወዳጄ ለሥራ ወደ ሩቅ ሀገር በሄደበት ሰዓት ቤቱን እንድጠብቅለት በአደራ ሰጥቶኝ እኔ ግን ድንገት የቤቱን ቁሳቁስ ሰበርኩ እንበል። ነገር ግን እርሱ ከመመለሱ በፊት መኪናውን አጠብኩለት። ይህ የተሰበረውን ዕቃ ለመተካት የሚያስችለውን ወጪ ይሸፍናልን? አይሸፍንም!

ጓደኛዬ መኪናውን ስላጠብኩለት የሰበርኩትን ንብረት ይቅር እንዲለኝ ብጠይቀው ትክክል ይሆናልን? አይሆንም!

ጓደኛዬ ይቅር ቢለኝ እንኳ አዲስ ዕቃዎችን ለመግዛት ገንዘቡን መክፈል ያስፈልገዋል። ልክ እንደዚሁ የኛ መልካም ሥራ ከእግዚአብሔር ጽድቅ ጋር ሲስተያይ በቂ አይደለም። የኛ መልካም ሥራዎች ኃጢአታችንን ማስወገድ አይችሉም ምክንያቱም መልካም መሥራትና ሁሉንም የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት መጠበቅ ይኖርብናልና።

ኃጢአታችን የእግዚአብሔርን ጽድቅ የሚፃረር ነው፤ ብቃት ያለው የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ብቻ ነው። የኃጢአታችንን ዕዳ በመክፈል ልዩነቱን ማስወገድ የሚችለው የክርስቲያን አድሃ ብቻ ነው።

የክርስቲያን አድሃ ለሁሉም ሰው የተዘጋጀ ነው። ምክንያቱም ክርስቶስ ሁሉንም የሰው ዘር ሊያድን መጥቷልና። በክርስቶስ በኩል ተሻግረን ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ማድረግ እንዲሁም ፍቅሩንና ማዳኑን ማጣጣም እንችላለን።

5.       እግዚአብሔር ይቅር ባይ ነው

እግዚአብሔር ለኃጢአት የሚሆን አድሃ ማዘጋጀቱን ማወቅ ብቻ በቂ አይደለም። እያንዳንዳችን ይህንን አድሃ በግልና በትህትና ልንቀበል ያስፈልገናል።

የእግዚአብሔርን ይቅርታ በሕይወታችን ውስጥ የምናገኘው በሚከተለው መንገድ ነው። የእግዚአብሔርን ፍቅርና ይቅርታ በሕይወታችን ውስጥ ለመለማመድ ከኃጢአታችን ንስሐ ገብተን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ጌታና አዳኝ በሕይወታችን ውስጥ ልንቀበል ይገባናል።

ንስሐ ከኃጢአተኛ መንገዳችን በመመለስ በክርስቶስ የመስቀል ሥራ (የክርስቲያን አድሃ) በኩል የተገኘውን የእግዚአብሔርን የይቅርታ ስጦታ መቀበል ነው።

ኢንጂል እንዲህ ይላል፦

“በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለንና ከአመፃም ሁሉ ሊያናፃን የታመነና ጻድቅ ነው።” (1ዮሐንስ 1:9)

  • እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ብንናዘዝ ይቅር የሚለን ክርስቶስ ዕዳችንን ስለከፈለ ነው።
  • ፍጹም የሆነው የእግዚአብሔር ፍትሃዊ ባሕርይ ቅጣትን ይጠይቃል።
  • የእግዚአብሔር ምህረት በክርስቲያን አድሃ ውስጥ ታይቷል።
  • የእግዚአብሔር ፍትህ ስለረካ ይቅርታ ተሰጥቷል።
  • ክርስቶስ ዕዳችንን ስለከፈለ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞች ይቅርታን ያገኛሉ።

ኃጢአት በሁሉም የሰው ልጆች ልብ ውስጥ ይገኛል። የሰው ልጆች “የልብ ቅያሬ” ያስፈልጋቸዋል። ይህም ደግሞ ኃጢአተኛን ወደ ጻድቅ ሰው ይለውጣል። ኢንጂል እንዲህ ይላል፦

“የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።” (ሮሜ 6:23)

የክርስቲያን አድሃ ከመንፈሳዊ ሞት በማውጣት የዘላለምን ሕይወት ሰጥቶናል። የእግዚአብሔር የዘላለም ሕይወት ስጦታ የክርስቶስን መሥዋዕትነት በመቀበል ይገኛል። የክርስቶስን መሥዋዕትነት የምንቀበለው በእምነት ነው።

የክርስቶስ መሥዋዕትነት ነፃ ቢሆንም በገንዘብ የሚተመን ግን አይደለም። በእምነት ልንቀበለው ይገባል። ከዚህ ያለፈ እርሱን ለማግኘት በራሳችን የምንሠራው ምንም ነገር የለም።

“ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።” (ኤፌሶን 2:8-9)

የእግዚአብሔርን ስጦታ ማጣጣም የምንችለው ስንቀበለው ነው። ክርስቶስንና የመሥዋዕትነት ሥራውን መቀበል የምንችለው ልባችንን ሙሉ በሙሉ በመስጠት ነው።

“ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።” (ዮሐንስ 1:12-13)

ክርስቶስ ወደ ሕይወታችን በመግባት ከኃጢአት ሊያንጻንና ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን የተበላሸ ሕብረት ሊያስተካክል ይፈልጋል። ክርስቶስ ጌታችንና አዳኛችን ሊሆን ይፈልጋል። ኢየሱስ ኢንጂል ውስጥ እንዲህ አለ፦

“እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ። ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ።” (ራዕይ 3:20)፟

ጸሎት ለእግዚአብሔር መናገር ማለት ነው። በየትኛውም ቦታ ሆነን በየትኛውም ሰዓት ለእግዚአብሔር መናገር እንችላለን። የክርስቶስን መሥዋዕትነት (የክርስቲያን አድሃ) ለመቀበል ወደ እግዚአብሔር እንጸልያለን፤ ደህንነት መቀበላችንንም በእምነት እናውቃለን።

እንዲህ ብላችሁ ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ትችላላችሁ፦

ጌታ ሆይ ለኔ ስላለህ ፍቅር አመሰግንሃለሁ። ከክርስቶስ መሥዋዕትነት የተነሳ ይቅርታህን እጠይቃለሁ። የሕይወቴን በር በመክፈት ክርስቶስን እንደ ጌታዬና አዳኜ እቀበላለሁ። አዲስ ሰው አድርገኝ። የዘላለምን ሕይወት ስለሰጠኸኝ አመሰግንሃለሁ። በኢየሱስ ስም፤ አሜን።

ይህንን ጸሎት በመጸለይ ክርስቶስ ወደ ሕይወታችሁ እንዲገባ፣ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲል እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር ያላችሁን ሕብረት እንዲያድስ ጠይቁት። በእውነት ከልባችሁ ሆናችሁ ክርስቶስ ወደ ሕይወታችሁ እንዲመጣ ከጠየቃችሁት ወደ ሕይወታችሁ እንደመጣ እርግጠኞች ሁኑ።

የእግዚአብሔር ተስፋዎች እውነት እንደሆኑ ማወቅ ወሳኝ ነው። ራዕይ 3:20 ላይ ክርስቶስ እንዲህ አለ፦

“እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ። ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ።”

የሕይወታችሁን ደጅ በመክፈት ክርስቶስ እንደ ጌታና አዳኝ እንዲገባ ብትጠይቁት አያታልላችሁም። ክርስቶስ ታማኝ ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ ለቃሉ ታማኝ መሆኑን ኢንጂል ይናገራል፦

“በእኔ ብትኖሩ፣ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ጠይቁ ይሆንላችሁማል።” (ዮሐንስ 15:7)

“አልተውህም አልጥልህም።” (ዕብራውያን 13:5)

“ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናም ዛሬም እስከ ለዘላለምም ያው ነው።” (ዕብራውያን 13:8)

“ያመንሁትን አውቃለሁና፤ የሰጠሁትንም አደራ እሰከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ።” (2ጢሞቴዎስ 1:12)

“በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈፅመው ይህን ተረድቼአለሁና።” (ፊልጵስዩስ 1:6)

የመዳን መንገድ

መሲሁ ኢየሱስ