የደህንነትን ማረጋገጫ መረዳት (ክፍል 1)

መግቢያ

ለረጅም ጉዞ ከመውጣቴ በፊት የሚያስፈልገኝን ነገር ሁሉ መያዜን ለማረጋገጥ ዙርያ ገባውን እቃኛለሁ፡፡ የገንዘብ ቦርሳዬን ይዣለሁን? ለነዳጅና ለምግብ በቂ ገንዘብ አለኝ? የአውሮፕላን ቲኬቴን ይዣለሁን? የሆቴሎች አድራሻ የተጻፈበትን ወረቀት ይዣለሁን? እነዚህን ሁሉ ቁሳቁሶች መኪና ውስጥ መጨመሬን ባውቅም ለመጨረሻ ጊዜ መኖራቸውን አረጋግጣለሁ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንድ አስፈላጊ ነገር ከረሳሁ ወደምፈልገው ቦታ መድረስ ስለማልችል ነው፡፡

ልክ እንደዚሁ ክርስቶስን ለመከተል ከወሰንኩ በኋላ ሁሉንም ነገር በትክክል መፈፀሜን ለማረጋገጥ ዞር ብዬ ማየት ያስፈልገኛል፡፡ አንድን የደህንነት ወሳኝ ገፅታ በትክክል ካልተረዳሁ መድረስ ወደምፈልገው ቦታ (ሰማይ) መድረስ እንደማልችል አውቃለሁ፡፡ ይህ የደህንነት ልምምድ ወሳኝ በመሆኑ አንዳንድ ሰዎች “በትክክል አድርጌዋለሁ ወይ?” ብለው መጠየቃቸው አያስገርምም፡፡ እግዚአብሔር ልጁ ዕዳችንን ይከፍል ዘንድ በመላክ የድርሻውን እንደተወጣ እናውቃለን፡፡ የኛ ስጋት የእርሱን ስጦታ ለመቀበል የድርሻችንን በትክክል አልተወጣን ይሆናል የሚል ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ ይህንን ጉዳይ የተመለከተ ነው፡፡

እግዚአብሔር ያደረገልንን መረዳት

መጀመርያ መረዳትና ማመን የሚገቡን የተወሰኑ ነገሮች አሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ይላሉ፡- “እምነትህን አጥብቀህ እስከያዝክ ድረስ ምንም ብታምን ልዩነት የለውም፡፡” ነገር ግን ሂትለር “ደካሞችን” በመግደል “ምርጥ” የሆነውን የአርያን ዘር ዓለምን እንዲቆጣጠር በማድረግ የሰው ልጆችን እየጠቀመ እንደሆነ አስቦ ነበር፡፡ ኦሳማ ቢን ላደን እርሱ የሚያምነውን የማያምኑትን ሰዎች እንዲገድል አላህ እንዳዘዘው ያምን ነበር፡፡ ሂትለርና ቢንላደን ያመኑበትን ነገር አጥብቀው የያዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን የተሳሳተ እምነት ወደተሳሳተ ተግባር ይመራል፡፡ ትክክለኛውን እምነት መያዝ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ለመዳን ምን ማመን አለብን?

መጥፎ ዜና፡- እኛ ኃጢአተኞች ነን፡፡ ይህ ኃጢአት ደግሞ ከእግዚአብሔር ይለያል፡፡ ከኃጢአት የተነሳ ከእግዚአብሔር ጋር በራሳችን ጥረት ሕብረት ሊኖረን አይችልም፡፡

ለምሳሌ ያህል ሒሳብ እየተማራችሁ ነው እንበል፡፡ መምህራችሁ “አሁን እነዚህን የስሌቶች ቀመሮች ማወቅ ይጠበቅባችኋል፡፡ ለዚህ ፈጣን ፈተና የማለፍያ ነጥቡ መቶ ከመቶ ማምጣት ነው” አለ፡፡ ነገር ግን እየተፈተንክ እያለህ አንዳንድ ቀመሮችን መሳሳትህን ተረዳህ፡፡ ከዚህ በኋላ ሁሉንም ጥያቄዎች መመለስ ብትችል እንኳ ፈተናውን ማለፍ ትችላለህን? አትችልም፡፡ ምክንያቱም የማለፍያ ነጥቡ 100% ነውና፡፡ አንዴ ከተሳሳትክ ከዚህ በኋላ የፈለከውን ያህል ጥያቄ ብትመልስ 100% ልታገኝ አትችልም፡፡ ትወድቃለህ፡፡

ልክ አንዱን ጥያቄ ከተሳሳትን በኋላ ያንን የሒሳብ ፈተና ማለፍ እንደማንችል ሁሉ አንዴ ኃጢአት ከሠራን (የእግዚአብሔርን ፍፁማዊ መመዘኛ ካላሟላን) ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት አንችልም፡፡ ፍፅምና የጎደላቸው ሰዎች ፍፁም ወደሆነው ሰማይ በራሳቸው ችሎታ ሊገቡ አይችሉም፡፡ ማመን የሚገባን ቀዳሚው ነገር ይህ ነው፡፡

መልካሙ ዜና፡- እግዚአብሔር አምላክ ራሳችንን ማዳን እንደማንችል ስለሚያውቅ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ያድነን ዘንድ ላከልን፡፡ ኢየሱስ ለአባቱ በመታዘዝ ፍፁም እንከን የለሽ ሕይወት ኖረ፡፡ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ስለ ራሱ ኃጢአት አልነበረም የሞተው ነገር ግን ስለኛ ኃጢአት ነበር፡፡ እኛ መክፈል የነበረብንን የቅጣት ዕዳ እርሱ ከፈለልን፡፡

“ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፡፡” (1ጴጥ. 3፡18)

“ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል፡፡” (ሮሜ 8፡10)

ባለፈው ዓመት ቀጣሪዎችህ ተቋማቸውን ለሸሪኮቻቸው ጥሩ ለማስመሰል ሐሰተኛ የሆነ ትርፍ የጻፉበትን ሰንድ አገኘህ እንበል፡፡ ይህንን መረጃ አደባባይ የማውጣት የህሊና ግዴታ እንዳለብህ ብታውቅም ነገር ግን ከሥራ ተባረህ ቤተሰብህን አደጋ ላይ ላለመጣል ብለህ ዝምታን መረጥክ፡፡ አሁን መረጃውን በመደበቅህ ምክንያት የወንጀሉ ተባባሪ ሆነህ ተከሰህ ፍርድቤት ዳኛ ፊት ቆመሃል፡፡ ዳኛው 100,000 ብር መክፈል አለብህ፤ አለበለዚያ ለ10 ዓመት ትታሰራለህ የሚል ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ 100,000 ብር እንደሌለህ ነገርከው፡፡ እርሱም እንደ ፍትሃዊ ዳኛ ወንጀለኛ መሆንህን አረጋገጠብህ፡፡

ዳኛው ያንተን ጭንቀትና የልጆችህን ጭንቀት በማየት  አዘነ፡፡ ከዚያም እርሱ ብቻ ማየት የሚችለውን ጽሑፍ ጻፈ፡፡ ለፍርድ ቤቱ ተላላኪ አቀበለው፤ እርሱም ላንተ ሰጠው፡፡ ወረቀቱ ዕዳህን በሙሉ የሚከፍል በዳኛው እጅ 100,000 ብር የተጻፈበት ቼክ መሆኑን ስታውቅ በድንጋጤ ክው አልክ፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ “ጸጋ” ብሎ የሚጠራው እርሱን ነው፡፡ እግዚአብሔር ዕዳህን ከፍሎልሃል፡፡ ስለሚገባህ ሳይሆን ከታላቅ ፍቅሩ የተነሳ፡፡ እግዚአብሔር ዕዳችንን በልጁ ሞት መክፈሉ ምንኛ አስደናቂ ነው!

ነገር ግን እግዚአብሔር ይህንን ስጦታ መስጠቱ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ መልካሙ ዳኛ የሰጠህን ቼክ አለመቀበል ትችላለህ፡፡ የእግዚአብሔርን ጸጋ የምንቀበለው እንዴት ነው? በእግዚአብሔር ማመንና ኢየሱስ እንደሞተልን ማመን በቂ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ሰይጣን እንኳ በእግዚአብሔር ያምናል (ያዕ. 2፡19)፡፡ ይቅርታውን በንስሐና በእምነት መቀበል ይኖርብናል፡፡ እስኪ እነዚህን አንድ በአንድ እንመልከት፡፡

እግዚአብሔር ምላሽ እንድንሰጥ በሚፈልግበት መንገድ ምላሽ መስጠት

ከኃጢአታችን ንስሐ መግባት፡- ንስሐ ለመጥፎው ዜና የምንሰጠው ምላሽ ነው፤ ኃጢአተኞች መሆናችንንና በእግዚአብሔር ላይ ማመፃችንን በማወቅ የምንሰጠው ምላሽ፡፡ የንስሐ ቀለል ያለ ትርጉም “ለመመለስ ፈቃደኛ መሆን” የሚል ነው፡፡ እዚህ ጋ ግራ እንዳይገባችሁ! ራሳችንን ስንቀይር እግዚአብሔር ያድነናል እያልን አይደለም፡፡ እርሱ በሥራ የሚገኝ መዳን ነው የሚሆነው! በተጓዳኝ እግዚአብሔር እስኪያድሰንና አዲስን ሕይወት እንድንኖር አቅምን እስኪሰጠን ድረስ የረባ ለውጥ ልናደርግ አንችልም፡፡ ለራሳችን ከመገዛት ለእግዚአብሔር ወደ መገዛት የልቦና ለውጥ እናደርጋለን ማለት ነው፡፡ ንስሐ ስንገባ ለእግዚአብሔር “ለመለወጥ ፈቃደኛ ነኝ! ከኃጢአቴ በመመለስ ላገለግልህ እፈልጋለሁ!” ብለን እየነገርነው ነው፡፡

“ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር፡፡” (ማቴ. 4፡17)

በኢየሱስ ማመን፡- በኢየሱስ ማመን ለሰማነው የምሥራች ወይም መልካም ዜና የምንሰጠው ምላሽ ነው፡፡

“ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም፡፡” (ኤፊ 2፡8-9)

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡” (ዮሐ. 3፡16)

ዝም ብለን በአእምሯችን “ኢየሱስ መኖሩን፣ ተዓምራትን ማድረጉንና ከሙታን መነሳቱን አምናለሁ” ብሎ መናገር አይደለም፡፡ በኢየሱስ ማመን ማለት እምነታችንን ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ መጣል ማለት ነው፡፡ ሰዎች እስፖርት በመሥራት እንደሚያምኑ ሲናገሩ እስፖርት የሚባል ነገር በዓለም ላይ የሆነ ቦታ አለ ብለው ማመናቸው አይደለም፡፡ እስፖርት ጠቃሚ መሆኑን ተቀብለው ለመሥራት ፈቃደኞች ናቸው ማለት ነው፡፡ አንዲት ሴት በኮካ አምናለሁ ብትል ኮካ ኮላ መኖሩን በሐሳቧ ከማመን ያለፈ ነገር ውስጧ አለ ማለት ነው፡፡ እንደ አዝናኝ መጠጥ ሙሉ በሙሉ ስለምትቀበለው ለመጠጣት ፈቃደኛ ናት ማለት ነው፡፡

በተመሳሳይ በኢየሱስ ማመን እርሱ መኖሩን በአእምሮ ከመቀበል ያለፈ ነው፡፡ እንዲያድነን እምነታችንን በእርሱ ላይ መጣል ነው፡፡ ለእርሱ ራሳችንን አሳልፈን መስጠት ነው፡፡ እግዚአብሔር በልጁ በኩል እዳችንን በመክፈል ይቅርታን እንደሰጠን እናምናለን፤ የከፈለንንም ክፍያ እንቀበላለን ማለታችን ነው፡፡ ክርስቶስንም ለመከተል ፍቃደኝነታችንን እየገለፅን ነው፡፡

ሁሉንም በአንድነት ማድረግ

ንስሐና እምነት በሁለት የተለያዩ ነገሮች ላይ ማለትም በኃጢአታችንና በክርስቶስ ላይ የሚያተኩሩ ቢሆንም ሁለቱም አንድ የአእምሮ ተግባር ናቸው፡፡ ከኃጢአታችን በተመለስንበት ቅፅበት ወደ ክርስቶስ እንመለሳለን፡፡ ኢየሱስ እንዳለው፡-

“ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ” (ማር. 1፡15)

በዚህ ትምህርት መጀመርያ ላይ ወደጠቀስነው ወሳኝ ጉዞ እስኪ እንመለስ፡፡ ወደ መዳረሻዬ መድረስ መቻሌን ለማረጋገጥ እንዲህ ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡- “የአውሮፕላን ቲኬቴን ይዣለሁን? በቂ ገንዘብ ይዣለሁን?” በተመሳሳይ መንገድ በእውነት የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንንና ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባታችንን እርግጠኞች መሆን ከፈለግን “በእውነት ከልብ ንስሐ ገብቻለሁን? በኢየሱስ ከልቤ አምኛለሁን?” በማለት ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልገናል፡፡ ያንን አለማድረግህን ካወክ ወይም ያንን ማድረግህን እርግጠኛ ካልሆንክ ውሳኔህን በጸሎት ለእግዚአብሔር በመግለፅ አሁኑኑ አረጋግጥ፡፡ የልብህን ቅንነት እንጂ የምትናገራቸውን ቃላት አይመለከትም፡፡ ተከታዩ የተጻፈ ጸሎት በልብህ ውስጥ ያለውን መሻት የሚገልፅልህ ከሆነ አሁኑኑ በእግዚአብሔር ፊት ለምን አትጸልይም?

“እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ በራሴ መንገድ በመሄዴ ተጸጽቻለሁ፡፡ ይቅር በለኝ፡፡ ከኃጢአቴ እመለሳለሁ፡፡ እንድከተልህ አቅምን ስጠኝ፡፡ በአንተ አምናለሁ፡፡ ከኃጢአቴ ታድነኝ ዘንድም በአንተ እደገፋለሁ፡፡ አዲስ ሰው አድርገህ ወደ መንግሥትህ አግባኝ፡፡ በጣም ስለወደድከኝና ኃጢአቴን ይቅር ስላልከኝ አመሠግንሃለሁ፡፡”

ይህንን ጸሎት ከልብህ ከጸለይክ በእግዚአብሔር ቃል ሥልጣን መሠረት እነግርሃለሁ፤ አንተ ልጁ ሆነሃል፤ መዳረሻህ ወደ ሆነው ወደ መንግሥተ ሰማያትም በስኬት ጉዞ ጀምረሃል፡፡

እውነታዎችና ስሜቶች

አለቃህ በጣም ስላቃለለህ ባለፈው ምሽት በቂ እንቅልፍ አልተኛህም፡፡ የሚያፅናና ቃል  ፈልገህ ወደ ጸሎት ስብሰባ ሄደሃል፡፡ በዚህ ፋንታ እግዚአብሔር ችግሮቹን ሁሉ እንዴት እንደፈታለት በስሜት ተውጦ የሚናገር ክርስቲያን አጋጠመህ፡፡ “ችግሮቼ ሁሉ አልተቀረፉም” ብለህ አሰብክ፡፡ ከዚያም አንድ አዲስ ክርስቲያን ተነስቶ ክርስቶስን ሲቀበል እንደ ኤሌክትሪክ ያለ ንዝረት በመላው አካሉ እንደተሰራጨ አስገራሚ ምስክርነት ሰጠ፡፡ “በዳንኩበት ሰዓት ምንም የተለየ ስሜት አልተሰማኝም” ብለህ አሰብክ፡፡ ከዚያም ክርስቲያን መሆንህን እንኳ መጠራጠር ጀመርክ፡፡

በዚህ ጊዜ ስሜቶችህን ቦታ ልታሲዛቸው ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡” (ዮሐ. 3፡16) “ሁል ጊዜ ጥሩ ስሜት የሚሰማቸው” አላለም፡፡ “ልክ ሲያምኑ ድንገተኛ የሆነ ስሜት የሚሰማቸው” አላለም፡፡ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ” ነው ያለው፡፡

ስለዚህ በእውነት አምኜ ንስሐ ከገባሁ እና ካልዳንኩ ይህ ስለ እግዚአብሔር ምን ይነግረናል? (ሐሰተኛ ልንለው ነው! እርሱ ደግሞ ከዋሸ ምን ተስፋ ይኖረናል!) ስለዚህ ምንም ይሰማን ምን ንስሐ የገቡትና ያመኑት ሰዎች መዳን እንደ እግዚአብሔር ተስፋ ሁሉ እውነትና የጸና ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ ውሸት የማያውቀው እውነተኛና ታማኝ ነውና፡፡