የእስላማዊ ባንክ አሉታዊ ገፅታዎች
ይዘት
መግቢያ
እስላማዊ ፋይናንስ ምንድነው?
የእስላማዊ ፋይናንስ ችግሮች
- ወለድን መከልከል ዘመናዊ የአክራሪዎች የቁርአን ትርጓሜ ነው
- በእስላማዊ ፋይናንስ ወለድ የለም የሚለው አባባል አታላይ ነው
- እስላማዊ ፋይናንስ በፅንፈኛ እስላማውያን የሚቀነቀንና ከእነርሱ ጋር የተቆራኘ ሥርዓት ነው
- እስላማዊ ፋይናንስ የተለየና ተፎካካሪ የፋይናንስ ሥርዓትን ለመዘርጋት ያለመ ነው
- እስላማዊ ፋይናንስ ኢ-ዲሞክራሲያዊ፣ አድሏዊና አክራሪ ለሆነው የሸሪኣ ሕግ ዕውቅናን ይሰጣል
- በአንዳንድ ሁኔታዎች ዘካት ይከፈላል – ወዴት ይሆን የሚሄደው?
- እስላማዊ ባንኮች ግልፀኝነት ስለሚጎድላቸው ለሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ማጭበርበር የተጋለጡ ናቸው
- በእስላማዊ ፋይናንስ አጠቃቀም ምክንያት የሚፈጠረውን አለመግባባት የሚዳኘው ማን ነው?
- እስላማዊ ፋይናንስ ሙስሊሞችን ለችግር ይዳርጋል
- እስላማዊ ፋይናንስ በአብዛኞቹ ሙስሊሞች ዘንድ ድጋፍ የለውም
ማጠቃለያ
መግቢያ
ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ሰባት ሺሕ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ሙስሊም ባለአክሲዮኖች 350 ሚሊዮን ብር ገደማ በሆነ ካፒታል ለማቋቋም ያሰቡት ዘምዘም የተሰኘ እስላማዊ ባንክ በምሥረታ ላይ እያለ መፍረሱ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ግንቦት 14/2011 በሚሊንየም አዳራሽ በነበረው የኢፍጣር ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ምኒስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ እስላማዊ ባንክ በኢትዮጵያ እንዲከፈት የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል ሲገቡ ታይተዋል፡፡ ባንኩ እውን ይሆን ዘንድ የተወሰኑ ሙስሊሞች ጥያቄ ሲያቀርቡና ግፊት ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን የመንግስትም ሆኑ የግል ባንኮች “ከወለድ ነፃ” የተሰኙ መስኮቶችን በመክፈት ለዚህ ጥያቄ ምላሽ መስጠታቸው ይታወቃል፡፡ ዳሩ ግን አንዳንድ ሙስሊም ወገኖች በዚህ የረኩ አይመስልም፡፡ በእስላማዊ ሕግ የሚመራ፣ ሙስሊሞችን ነጥሎ የሚያስተናግድ፣ “እስላማዊ” የሚል ታፔላ የለጠፈ የተለየ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲዘረጋላቸው መጠየቃቸውን ቀጥለዋል፤ ከመንግሥት ዘንድም አዎንታዊ ምላሽ የተሰጣቸው ይመስላል፡፡ የእስላማዊ ባንክ ዓላማ ከወለድ ነፃ የሆነ ብድር መስጠት ከሆነና ለዚህም የሚሆኑ መስኮቶች በየባንኮቹ ውስጥ ተከፍተው ሳሉ ሌላ የተለየ ባንክ ማቋቋም ማስፈለጉ በብዙ ሰዎች ዘንድ ጥያቄን ፈጥሯል፡፡ ለዚህም ስንል በብሪቲሽ ክርስቲያን ኮንሰርን የተዘጋጀውን ስለ እስላማዊ ባንክ ምንነትና አሠራር እንዲሁም የፋይናንስ ሥርዓቱን በማወክ በማሕበረሰቡ ላይ የሚያስከትለውን ችግር የሚዳስሰውን ይህንን ጠቃሚ ጽሑፍ ለአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በሚስማማ መንገድ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡
በ2014 (እ.ኤ.አ) ብሪታንያ እስላማዊ ቦንድ ለገበያ በማቅረብ ሙስሊም ካልሆኑት አገራት የመጀመርያዋ ሆነች፡፡ ይህ ቦንድ እንግሊዝን “የምዕራቡ ዓለም እስላማዊ ፋይናንስ ማዕከል” ለማድረግ ታልሞ የተዘጋጀ ነበር፡፡[1] መንግሥትም ለአሥር ዓመታት ያህል እስላማዊውን የፋይናንስ ሥርዓት በማበረታታት ስኬትን አስመዝግቧል፡፡[2] ዛሬ በአገረ እንግሊዝ ከሃያ በላይ እስላማዊ ባንኮች የሚገኙ ሲሆን ይህ ቁጥር በዩናይትድ እስቴትስ ውስጥ ከሚገኙት እጥፍ ያህል ነው፡፡ የዓለም አቀፉ እስላማዊ የፋይናንስ ሥርዓት በ2014 ዓ.ም. ሁለት ትሪሊየን ያህል ዶላር ያንቀሳቅስ እንደነበር የተነገረ ሲሆን በ2018 ወደ ሦስት ትሪሊየን እንዳደገ ተገምቷል፡፡[3] ሲቲዩኬ የተሰኘ ተቋም ባስቀመጠው ግምት መሠረት እስላማዊው የፋይናንስ ሥርዓት በአገረ እንግሊዝ 100,000 ያህል ደንበኞች አሉት፡፡ እንግሊዝ በመጀመርያም ሆነ በሁለተኛ የድግሪ መርሃ ግብሮች እስላማዊውን የፋይናንስ ሥርዓት በሚከታተሉት ተማሪዎች ብዛት ከምዕራቡ ዓለም ቀዳሚዋ ናት፡፡
ብዙ ሰዎች ይህንን ሁኔታ እንደ ጥሩ የገበያ አጋጣሚ ሊቆጥሩት ይችላሉ ነገር ግን ችግር ያስከትል ይሆን? ይህ የፋይናንስ ሥርዓት መዘዙ ብዙ ነው ነገር ግን በዚህ ጽሑፍ የተወሰኑትን ብቻ እናያለን፡፡
እስላማዊ ፋይናንስ ምንድነው?
እስላማዊ ፋይናንስ ወይንም ሸሪኣዊ ፋይናንስ በእስላማዊ ሕግ ሁሉም ዓይነት ወለዶች ክልክል (ሐራም) ናቸው በሚል እሳቤ ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ገንዘብ ዋጋን የመተመኛ መሣርያ ብቻ እንጂ በራሱ ዋጋ ያለው ኃብት ተደርጎ ስለማይታሰብ ከተጠቃሚ ወለድን መቀበል ኢ-ፍትሃዊ ተደርጎ ይታመናል፡፡ ከወለድ ይልቅ በአበዳሪና በተበዳሪ መካከል ጉዳትንና ጥቅምን የመጋራት ሁኔታ የሚመቻች ሲሆን ከወለዱ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ነገር ግን “ትርፍ” ተብሎ የተሰየመ ክፍያ ለአበዳሪው ይከፈላል፡፡ ወለድን ለማስቀረት የተለያዩ ስልታዊ የገንዘብ ልውውጦች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ እስላማዊው ፋይናንስ በሸሪኣ ሕግ ክልክል በሆኑ እንደ ቁማር፣ መጠጥ፣ የአሣማ ሥጋና በመሳሰሉት ላይ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስን ይከለክላል፡፡ የተለመዱት የፋይናንስ ሥርዓቶችም ወለድ ስለሚያስከፍሉ ክልክል ናቸው፡፡ የፋይናንስ ሥርዓቱ ከሸሪኣ ሕግ ጋር መስማማት አለመስማማቱን የሚቆጣጠር ከሙስሊም ሊቃውንት የተዋቀረ የሸሪኣ አማካሪ ቦርድ ይሰየምለታል፡፡
የእስላማዊ ፋይናንስ ችግሮች
1. ወለድን መከልከል ዘመናዊ የአክራሪዎች የቁርአን ትርጓሜ ነው
በዘመናት ሁሉ ሙስሊሞች ገንዘብን በወለድ ሲበደሩም ሆነ ሲያበድሩ መኖራቸው የታሪክ ሃቅ ነው፡፡[4] ወለድ በቁርአን ውስጥ ተከልክሏል የሚለው ዘመንኛ የፅንፈኞች ትርጓሜ ነው፡፡ ቲሙር ከራን የተሰኙ ዕውቅ ሊቅ እንዳስቀመጡት “አስተምሕሮው ጥንታዊ ነው የሚለው ተረት መሠረተ ቢስ ነው… የእስላማዊው ምጣኔ ሐብት ፅንሰ ሐሳብ በራሱ የሃያኛው ክፍለ ዘመን ውጤት ነው፡፡”[5] ሙስሊም ሊቅ የሆኑት ማሕሙድ ኧል-ገማል እንደጻፉት ደግሞ “እስላማዊው ፋይናንስ በ1970ዎቹ ውስጥ የተጠነሰሰ ነው፡፡”[6] ፓትሪክ ሱኬዶ እዲህ ሲሉ ያብራራሉ፡- “ከወለድ ነፃ የሚለው እስላማዊ የምጣኔ ኃብት ሥርዓት የተጠነሰሰው ጀመዓት አል-ኢስላሚ የተሰኘውን ፅንፈኛ የፓኪስታን ቡድን በመሠረተው አቡል ዓላ መውዱዲ በተሰኘ ሰው ነው፡፡”[7]
ወለድን መከልከል አስፈላጊ ስለመሆን አለመሆኑ እየተደረገ ያለው ክርክር በሁለት ቁርአናዊ ጥቅሶች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የመጀመርያው ሱራ 3፡130 ነው፡-
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ አራጣን የተነባበሩ እጥፎች ሲሆኑ፥ አትብሉ፤ ትድኑም ዘንድ አላህን ፍሩ።”
በዚህ ቦታ “አራጣ” ተብሎ የተተረጎመው የአረብኛ ቃል “ሪባ” የሚል ነው፡፡ ጥቅሱ “የተነባበሩ እጥፎች” ስለሚል አላግባብ የሆነ ተደራራቢ አራጣ ለማለት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ረቁይብ ዘማን እንደተናገሩት፡- “ሪባ ለሚለው ቃል ብቸኛው ቁርአናዊ ትርጓሜ ይህ ነው፡፡”[8] ሁለተኛው ጥቅስ ሱራ 2፡275-79 ላይ ይገኛል፡-
“እነዚያ አራጣን የሚበሉ ያ ሰይጣን ከመንካቱ የተነሳ የሚጥለው ሰው (ከአውድቁ) እንደሚነሳ ብጤ እንጅ (ከመቃብራቸው) አይነሱም፡፡ ይህ እነርሱ መሸጥ የአራጣ ብጤ ብቻ ነው በማለታቸው ነው፡፡ ግን መሸጥን አላህ ፈቅዷል፡፡ አራጣንም እርም አድርጓል፡፡ ከጌታውም ግሳጼ የመጣለትና የተከለከለ ሰው ለርሱ (ከመከልከሉ በፊት) ያለፈው አለው፡፡ ነገሩም ወደ አላህ ነው፤ (አራጣን ወደ መብላት) የተመለሰም ሰው እነዚያ የእሳት ጓዶች ናቸው፡፡ እነርሱ በውስጧ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡ አላህ አራጣን (በረከቱን) ያጠፋል፡፡ ምጽዋቶችንም ያፋፋል፡፡ አላህም ኃጢአተኛ ከሓዲን ሁሉ አይወድም፡፡ እነዚያ ያመኑ፡፡ መልካም ሥራዎችንም የሠሩ፡፡ ሶላትንም ያስተካከሉ፡፡ ዘካንም የሰጡ ለነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው፡፡ በእነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም እነርሱም አያዝኑም፡፡ እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ፍሩ፡፡ ከአራጣም የቀረውን ተዉ፡፡ አማኞች እንደኾናችሁ (ተጠንቀቁ)፡፡(የታዘዛችሁትን) ባትሠሩም ከአላህና ከመልክተኛው በኾነች ጦር (መወጋታችሁን) ዕወቁ፡፡ ብትጸጸቱም ለእናንተ የገንዘቦቻችሁ ዋናዎች አሏችሁ፡፡ አትበድሉም አትበደሉምም፡፡”
አንዳንድ የእንግሊዘኛ ትርጉሞች “አራጣ” (Usury) ከሚለው ቃል ይልቅ “ወለድ” (Interest) በማለት መተርጎምን ቢመርጡም የአረብኛው ቃል ግን ያው “ሪባ” የሚለው አራጣን አመልካች የሆነው ቃል ነው፡፡ ረቁይብ ዘማን ሁሉም ጥንታውያን ሙስሊም ሐታቾች ሪባ የሚለውን ቃል “ወለድ” ሳይሆን “አራጣ” ብለው መረዳታቸውን ብዙ ማስረጃዎችን በማጣቀስ አሳይተዋል፡፡[9] “ወለድ” ተብሎ እንዲተረጎም መሠረት የሚሆን ምንም ነገር በሐዲስ ውስጥ አለመኖሩንም አረጋግጠዋል፡፡[10] ዘመነኞቹ እስላማውያን ሪባ የሚለውን ቃል “ወለድ” ብለው ለመተርጎም የትኛውንም ጥንታዊ ትውፊት አልተጠቀሙም፡፡ ቃሉን ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ፅንፍ በማስያዝ የተረጎሙ ሲሆን ለዚህ ትርጓሜያቸው ደግሞ አንዳች የተጨበጠ መሠረት አላስቀመጡም፡፡ ምዕራባውያንና የአገራችን የፋይናንስ ተቋማት ይህንን ትርጓሜ እንደ ብቸኛና ትክክለኛ ትርጓሜ የተቀበሉ ሲሆን የሸሪኣ ሕግ ሁሉንም ዓይነት ወለድ ይከለክላል ከሚለው ዘመንኛ የፅንፈኞች አመለካከት ጋር ተስማምተዋል፡፡ አልፎ ተርፎም የእንግሊዝ መንግሥት እንዲህ ብሏል፡- “ወለድን (ሪባ) መቀበል በሸሪኣ መርሆች መሠረት በጥብቅ ተከልክሏል፡፡ ይህም የሆነው ገንዘብ በራሱ ዋጋ ያለው ነገር ባለመሆኑ ለገንዘብ ክፍያ መከፈል ስለሌለበት ነው፡፡”[11] መንግሥታት በሪባ ላይ ትንተና ለመስጠት የሊቃውንትን ደረጃ የተቀዳጁት ከመቼ ጀምሮ ነው? ዘመንኛውን ፅንፈኛ ትርጓሜ የተቀበሉትስ ለምን ይሆን? ይህንን የሪባ መረዳት በማቀንቀናቸው ምክንያት ፅንፈኛና አክራሪ የሆነን የቁርአን ትርጓሜ እያበረታቱ ነው፡፡
2. በእስላማዊ ፋይናንስ ወለድ የለም የሚለው አባባል አታላይ ነው
የእስልምና ፋይናንስ ምርቶች ለገበያ የሚቀርቡት እንደ ወለድ አልባ ምርቶች ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን አጠቃላይ የመሸጫ ዋጋቸው ከወለድ ጋር በእጅጉ ይቀራረባል፡፡ ይህ እንደ አጋጣሚ የተፈጠረ አይደለም፡፡ ስለ ሥርዓቱ ጥያቄን የሚያጭር ሆን ተብሎ የተደረገ ማታለል ነው፡፡ ቲሙር ከራን እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ፡- “የእስላማዊ ባንክ የተለመደ የብድር አሰጣጥ የሆነው ሙራባሃ ጥንታውያን ሕግጋትን ያቀፈ ነው፡፡ ከወለድ ነፃ የሆኑ ብዙ የገንዘብ ልውውጦችን ያካተተ ሲሆን በድምር ውጤታቸው ከወለድ ጋር የሚመጣጠን ገቢን ለአበዳሪው ያስገኛሉ፡፡”[12]
ብዙ ሙስሊሞች ይህንን በተመለከተ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ ከራን የተሰኙት ጸሐፊ ኹርሺድ አሕመድ የተሰኙትን ፓኪስታናዊ ሊቅ በመጥቀስ እንዲህ ብለዋል፡- “የፓኪስታንን ኢኮኖሚ በማስለም ረገድ ከፍተኛ ሚና በተጫወቱት ኮሚሽኖች ውስጥ ቁልፍ ሥልጣን የነበራቸውና ዕውቅ ጸሐፊ የሆኑት አሕመድ የአገራቸው እስላማዊ ባንኮች 99 ከመቶ የሚሆን ንግድ በወለድ ላይ የተመሠረተ መሆኑን በመግለፅ በአደባባይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡”[13]
ሙሐመድ ሰሊም የዚህ ሥርዓት ሌላው ተቃዋሚ ናቸው፡፡ “Islamic Banking – a $300 Billion Deception” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ሲሉ አስፍረዋል፡-
“ዋነኛ የገንዘብ ማንሸራሸርያ ስልታቸው በሆነው በሙራባሃ የገንዘብ ልውውጥ ውስጥ በግዢና በሽያጭ ዋጋዎች መካከል ያለው ልዩነት የሚሰላው ከወለድ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ሲሆን እርሱም ገንዘብ በጊዜ ውስጥ ባለው ዋጋ ነው፡፡ የበለጠ ግልፅ በሆነ መንገድ ለማስቀመጥ ያህል፣ እስላማዊ ባንኮች 95% በሆነው የገንዘብ ልውውጣቸው ውስጥ ወለድን የሚያስከፍሉ ሲሆን በእስላማዊ ካባ የተሸፈነ ነው፡፡ በተለያዩ ሽፍንፍን ዘዴዎች ወለድን ማስከፈላቸው ምርቶችን ለማድበስበስ የታለመ ሲሆን እስላማዊ ባንኮች በማጭበርበርና በማታለል አለመታመንን ያበረታታሉ፡፡ በአላህ ፊት የከፋው ኃጢአት የትኛው ነው? በግልፅ ወለድን ማስከፈል ወይንስ በማጭበርበር ተግባራት ውስጥ ተሳታፊ መሆን?”[14]
ኧል-ገማልም ይህንን ማጭበርበር የተቃወሙ ሌላኛው ሙስሊም ናቸው፡፡ ፎርቹን በተሰኘ መጽሔት ውስጥ የሚገኝን እንዲህ የሚል አስተያየት ጠቅሰዋል፡- “ውጤቱ በብዙ መንገድ ከወለድ ጋር ይመሳሰላል፤ አንዳንዶች እንደሚሉት ሙራባሃ በስሱ የተሸፈነ የወለድ ዓይነት ነው፤ እስላማዊ ባንኮች የሚያስከፍሉት ክፍያ አሁን ካለው የወለድ መጠን ጋር በእጅጉ ተቀራራቢ ነው፡፡ ነገር ግን የባንክ ኃላፊዎች ፈጣሪ አምላክ የዚህ ተዋናይ መሆኑን ይነግሩናል፡፡”[15] ሱኩክ የተሰኘውን “ከወለድ ነፃ” የቦንድ ሽያጭ በተመለከተ ሪውተርስ የዜና ምንጭ “4 በመቶ ዓመታዊ ትርፍ” እንደሚከፈልበት የዘገበውንም ይጠቅሳሉ፡፡[16]
ሌላ ቦታ እንዲህ በማለት ይሞግታሉ፡-
“እስላማዊ ሕግጋትን ወይንም የፋይናንስ ሥርዓትን የተመለከቱ ከሞላ ጎደል ሁሉም ጽሑፎች እስላማዊው ሕግ (ሸሪኣ) ወለድን እንደሚከለክል ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ውስጥ የነበሩትን የእስላማዊ ፋይናንስ አገልግሎት ሰጪዎችን ተግባራት የተመለከትን እንደሆን ይህ አባባል ምንታዌ መሆኑ ግልፅ ይሆንልናል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ አብዛኞቹ እስላማዊ የፋይናንስ ልውውጦች የተመላሽ ገንዘብን መጠን ወይንም የካፒታል ዋጋን የሚያሰሉት LIBOR በተሰኘው የወለድ መጠን መለኪያ ሲሆን ማንኛውም የቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ተማሪ በወለድ ላይ የተመሠረተ የዕዳ ፋይናንስ መሆኑን በቀላሉ መናገር ይችላል፡፡”[17]
ምዕራባውያንና የአገራችን መሪዎች በአታላይነት ላይ የተመሠረተን የፋይናንስ ሥርዓት የሚያበረታቱት ለምን ይሆን? እስላማዊ ፋይናንስ “ከወለድ ነፃ” በሚል ካባ የተሸፈነ ወለድን የሚያስከፍል የፋይናንስ ሥርዓት መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡
3. እስላማዊ ፋይናንስ በፅንፈኛ እስላማውያን የሚቀነቀንና ከእነርሱ ጋር የተቆራኘ ሥርዓት ነው
ሼኽ ታቂ ዑስማኒ ለሸሪኣ ፋይናንስ ዓለም አቀፋዊ መደበኛ መስፈርትን ለማስቀመጥ አልሞ ለሚንቀሳቀሰው Accounting and Auditing Organisation for Islamic Financial Institutions (AAOIFI) ለተሰኘ ተቋም የቦርድ ሊቀ መንበር ነው፡፡[18] በተጨማሪም የብዙ ባንኮች የሸሪኣ አማካሪ ሲሆን የብዙ እስላማዊና እስላማዊ ያልሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ሊቀ መንበርም ነው፡፡[19]
“Islam and Modernism” በሚል ርዕስ የተጻፈው መጽሐፉ ወደ እንግሊዘኛ የተተረጎመ ሲሆን[20] ወሳኝ ይዘቶቹ ኦን ላይን ይገኛሉ፡፡[21] በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እስልምና በነፃነት በሚሰበክባቸው እንግሊዝን በመሳሰሉት አገራት ውስጥ ጂሃድን ማወጅ አስፈላጊ ስለ መሆን አለመሆኑ ያብራራል፡፡ ቁርአንን በመጥቀስም እንዲህ ሲል መልስ ይሰጣል፡- “ከሃዲያን ተዋርደው ወይንም ተሸንፈው የጂዝያ ግብርን እስኪከፍሉ ድረስ ግድያ መቀጠል አለበት፡፡”[22] ጂዝያ በእስላማዊ ግዛት ውስጥ በሚገኙት ሙስሊም ባልሆኑት ወገኖች ላይ የሚጫን አዋራጅ የግብር ዓይነት ነው፡፡ እንዲህ ሲል ማብራራቱን ይቀጥላል፡- “የግድያ ዓላማው እስልምናን የመስበክ ፈቃድና ነፃነትን ማግኘት ቢሆን ኖሮ ‹‹እስልምናን መስበክ እስኪፈቅዱ ድረስ›› ብሎ በተናገረ ነበር፡፡”
ከአንዳንድ እስላማዊ ካልሆኑ ድርጅቶች መሪነት እንዲነሳ ቢደረግም ይህ ሰው ግን አሁንም ድረስ በብዙ የአማካሪ ቦርዶች ላይ በመሪነት ተቀምጧል፤ የሸሪኣ ፋይናንስንም በተመለከተ ግንባር ቀደም ሊቅ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ ይህ ሰው እንዲህ ያለ ፅንፈኛ አመለካከት ይዞ በሌሎች ኃላፊነቶች ላይ እንዲቀመጥ መደረጉ ድርጅቶቹ አመለካከቱን ስላላወቁ መሆኑ የማይመስል ነው፡፡ ፓትሪክ ሱኬዶ በአገረ እንግሊዝ የሚገኙት የሸሪኣ አማካሪ ቦርድ አባላት ከፅንፈኛ ቡድኖች ጋር ያላቸውን ግንኙነት “Understanding Shari’a Finance” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ በዝርዝር አስፍረዋል፡፡[23] የማክኮርሚክ ተቋም ሪፖርት የሸሪኣ አማካሪ ቦርድ አባላት ከፅንፈኛ ቡድኖች ጋር ያላቸውን ግንኙነትና አንዳንዴም ሽብርተኝነትን በመደገፍ የተናገሯቸውን ንግግሮች በስፋትና በዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡[24]
የቀድሞው የማሌዥያ ጠቅላይ ምኒስትር ሙሐመድ መሐሢር ኖቬምበር 2002 በኩዋላላምፑር በተደረገ የባንኮች ስብሰባ ላይ እንዲህ ብለው ነበር፡- “ይህንን ባርነት (የምዕራባውያንን) ለማስወገድ ዓለም አቀፋዊ የባንክ ሥርዓትን መዘርጋት ወሳኝ ጂሃድ ነው፡፡”[25] በኢትዮጵያ ውስጥም ቢሆን እስላማዊ የፋይናንስ ሥርዓቶችን ከመደገፋችንና ከማበረታታችን በፊት ፅንፈኛ ሙስሊሞች ይህንን የፋይናንስ ሥርዓት ለመዘርጋት እንዲህ መስገብገባቸውና እረፍት ማጣታቸው ለምን እንደሆነ ልንጠይቅ ይገባናል፡፡ ይህ ሁኔታ ጉዳዩን በእጅጉ አሳሳቢና አስፈሪ ያደርገዋል፡፡
4. እስላማዊ ፋይናንስ የተለየና ተፎካካሪ የፋይናንስ ሥርዓትን ለመዘርጋት ያለመ ነው
አክራሪ ሙስሊሞች ሙሉ በሙሉ አዲስ ፅንሰ ሐሳብ በሆነው እስላማዊ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች የመሆናቸው ጉዳይ ከግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ይገባዋል፡፡ ዓላማቸው ሆነ ብለው ተፎካካሪ የፋይናንስ ሥርዓትን መፍጠር ነው፡፡ እስላማዊው ፋይናንስ ሙስሊሞች ከሌሎች ማሕበረ ሰቦች ጋር እንዳይቀላቀሉና እንዳይሰባጠሩ በማድረግ ያገለግላል፡፡ ሙስሊሞች የመደበኛውን ፋይናንስ ምርቶች መጠቀም እንደማይፈቀድላቸው ይነገራቸዋል፡፡ የፋይናንስ ተቋማት ሙስሊሞችን ብቻ ከሌሎች ነጥለው የሚያገለግሉ ገበያዎችን እንዲፈጥሩ ይነገራቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሙስሊሞችን ከዋናው የኢኮኖሚ ሥርዓት በመነጠል በቀጥታ በሙስሊም ሊቃውን ተፅዕኖ ስር በሚገኝ ተፎካካሪ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲጠቀሙ ያስገድዳቸዋል፡፡
ቲሙር ከራን እንዲህ ይላሉ፡-
“የእስላማዊ ኢኮኖሚክስ ትክክለኛ ዓላማ የኢኮኖሚ መሻሻል ሳይሆን ዓለም አቀፋዊውን የባሕል ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚያስችል የተለየ እስላማዊ ማንነት መፍጠር ነው፡፡ ሙስሊም ማሕበረሰቦች በተለየ የኢኮኖሚ መርሆች በመተዳደር ተነጥለው መኖር ይችላሉ የሚለውን ቅዠት በማቀጣጠል ‹‹እስላማዊ አክራሪነት›› የተሰኘው ዓለም አቀፋዊ እስላማዊ ንቅናቄ የሚያራምደውን አቋም የሚደግፍ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የሙስሊሞች ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በሌሎች ቦታዎች እየተተገበሩ ለሚገኙት መርሆች ተገዢ ነው፡፡”[26]
በተጨማሪም እስላማዊ የምጣኔ ኃብት ሥርዓትን “ሥልጣኔን የመቋቋምያ መሣርያ” በማለት የገለጹት ሲሆን “‹የሥልጣኔዎች ግጭት› የሚለው ፅንሰ ሐሳብ እስላማዊ የምጣኔ ኃብት ሥርዓት ሲጠነሰስ ጀምሮ ቀስቃሽ ምክንያት ሆኖ በዋናነት እንደሚታይ” ያብራራሉ፡፡[27] ሮበርት እስፔንሰር የተሰኙ ጸሐፊ ብዙ ሙስሊሞች ለአይ አር ኤስ፣ ለማስተር ካርድና ለመሳሰሉት የክሬዲት ካርድ ሰጪ ተቋማት መከፈል ያለባቸውን ወለዶች በተሳካ ሁኔታ ሳይከፍሉ መቅረታቸውን ማስረጃዎችን በመጥቀስ አሳይተዋል፡፡[28] ይህ እንግዲህ እስላማዊ ፋይናንስ ሙስሊሞች ምን ያህል ራሳቸውን በማግለል ሥልጣኔን እንዲቃወሙ እንደሚያደርጋቸው ያሳያል፡፡ ማይክል ናዚር አሊ የተሰኙ ጸሐፊ ደግሞ ሸሪኣዊ ሕግን በተከተለ ፋይናንስ ለተመረቱት ምርቶች ከተለመደው የፋይናንስ ሥርዓት ፈንድ ማምጣት ይቻል እንደሆን ይጠይቃሉ፡፡ መልሱ አሉታዊ በመሆኑ “በሸሪኣ በተፈቀዱት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ብቻ የሚሳተፉ ራሳቸውን የቻሉ ተቋማትን መመሥረት የግድ ያስፈልጋል” ይላሉ፡፡[29]
ሙሉ በሙሉ ‹ከወለድ ነፃ› የሆነ እስላማዊ ኢኮኖሚ በመጨረሻ ከአጠቃላዩ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ የተነጠለ ወደመሆን ይሄዳል፡፡ ውጤቱም ተፎካካሪ የኢኮኖሚ ሥርዓት ነው፡፡ በሙስሊሞች ቁጥጥር ስር ይገባና ሙስሊም ባልሆኑ ሰዎች ላይ አድልዎን የሚፈፅም ይሆናል፡፡ ምዕራባውያንና የአገራችን የፋይናንስ ተቋማት ይህንን አግላይና ጨቋኝ የሆነ የፋይናንስ ሥርዓት በማበረታታት ከልክ በላይ እየተሞኙ ነው፡፡
5. እስላማዊ ፋይናንስ ኢ-ዲሞክራሲያዊ፣ አድሏዊና አክራሪ ለሆነው የሸሪኣ ሕግ ዕውቅናን ይሰጣል
እስላማዊ ፋይናንስ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ተፎካካሪ የሆነን የፋይናንስ ሥርዓት ከመፍጠሩ ጋር ተያይዞ ለሸሪኣ ሕግ ዕውቅናን በመስጠት ተቀባይነት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ውስጥ የሚሳተፉት አክራሪ እስላማውያን ቁልፍ ዓላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱት የሸሪኣ ፋይናንስን በማበረታታት ለአጠቃላዩ የሸሪኣ ሕግ ተግባራዊነት መንገድ መክፈትን ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ዕውቅ ሊቅ የሆኑት ቲሙር ከራን እንዲህ በማለት ያስቀምጣሉ፡- “በአንድ ዘርፍ የማስለም ሒደት በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ መሆኑ በሌሎች ዘርፎች የማስለም ሒደት ተግባራዊ እንዲሆን መንገድ ይከፍታል፡፡ ስለዚህ በእስልምና ስም የሚደረግ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለአጠቃላዩ የእስላማውያን አጀንዳ ድጋፍ በመስጠት ሌላ መዘዝ ያስከትላል፡፡”[30] ሰዎች የሸሪኣ ፋይናንስን አንዴ ከተቀበሉ በሌሎቹ የሸሪኣ ገፅታዎች ላይ ትችት መሰንዘር ያዳግታቸዋል፡፡ የሸሪኣ ሕግን በፋይናንስ ሥርዓታችን ውስጥ እንዲካተት ማድረጋችን በቤተሰብ ሕግ ውስጥ መካተቱን መቃወም እንዳንችል አቅማችንን ይሰልባል፡፡ ሁሉም ዘርፎች እርስ በርሳቸው የተሰባጠሩ በመሆናቸው በኢኮኖሚው ላይ ሸሪኣ ተግባራዊ ከሆነ ሌሎች ዘርፎችንም ይነካል፡፡ የሸሪኣ ፋይናንስ በፍጥነት የኢኮኖሚው አካል በመሆን የመንግሥት ብድሮችና የሥራ ፈጠራዎች በእርሱ ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ የሸሪኣ ሕግ በባሕርዩ በሴቶችና ሙስሊም ባልሆኑት ወገኖች ላይ አድልዎ እንዲፈፀም የሚያደርግ ሕግ ነው፡፡ የሸሪኣ ፋይናንስ በቀጥታ በዚህ መንገድ አድልዎን ባይፈፅም እንኳ አድልዎን ለሚፈፅም ሥርዓት በር ከፋች መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ በባሕላችን ላይ ሸሪኣዊ ሕግጋት ተፈፃሚ እንዲሆኑ መንገድ ለሚጠርግ ለማንኛውም ነገር ቦታ መስጠት ኋላ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡
6. በአንዳንድ ሁኔታዎች ዘካት ይከፈላል – ወዴት ይሆን የሚሄደው?
ዘካትን መክፈል ከእስልምና አዕማዳት መካከል አንዱ ነው፡፡ ከዓመታዊ ገቢ ላይ 2.5% ምፅዋት ማድረግ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ “የነፍስ አባት” እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሼኽ ዩሱፍ አል-ቀረዷዊ ዘካት ለነውጠኛ ጂሃድ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችል ፋትዋ (ድንጋጌ) አውጥተዋል፡፡[31] አንድ ሰው ዘካትን ለዩኒሴፍ መስጠት ይችል እንደሆን በኢንተርኔት ላይ ለጠየቀው ጥያቄ መስጠት እንደማይችል ከተነገረው በኋላ ከቁርአን በመነሳት ዘካትን ለነማን መስጠት እንደሚችል ዝርዝር ቀርቦለታል፡፡ 7ኛው ነጥብ “እስላማዊ ፕሮፓጋንዳ፣ ጂሃድ” የሚል ተካቶበታል፡፡[32] በርግጥ በዚህ መንገድ የሚሰጥ ዘካት ለሽብር ቡድኖች የሚደርስ ትልቁ የገቢ ምንጭ ነው፡፡[33]
ብሪሳርድ የተሰኙ ጸሐፊ ለሽብርተኝነት የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ አስመልክቶ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት “አልቃኢዳ የዘካትን ሥርዓት ተከትሎ በአሥር ዓመታት ውስጥ ከሦስት መቶ እስከ አምስት መቶ ሚሊየን ዶላር ያህል ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ገንዘቡ የተገኘው ከአጠቃላይ የሳዑዲ ዓመታዊ ምርት ሃያ ከመቶውን ከተቆጣጠሩት ባለጠጎችና ባንከሮች ነው፡፡ ገንዘቡም የተላለፈው እስላማዊ ባንኮችን በመጠቀም ሲሆን በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የተለያዩ ካምፓኒዎች አማካይነት ነው፡፡ ለፅንፈኛ ቡድኖች የሚቀርበው የገንዘብ ድጋፍ አሁንም ድረስ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡”[34]
ሴንተር ፎር ሴኪዩሪቲ ፖሊሲ የተሰኘ ተቋም ያዘጋጀው የጥናት ጽሑፍ እንዲህ ሲል ያስቀምጣል፡-
“በዘካት በኩል የሚደረግ የገንዘብ ጂሃድ አዲስ ነገር ሳይሆን ለዘመናት ሲተገበር የኖረ ነው፡፡ በጋዛ የሚገኙት የዘካት ኮሚቴዎች ለሐማስ ፈንድን በማስተላለፍ ረገድ በመሣርያነት ሲያገለግሉ የነበረ ሲሆን በተመሳሳይ በፓኪስታን የሚገኙት ፅንፈኛ የጂሃድ መድረሳዎችም ለአሥርተ ዓመታት በከፊል ከዘካት በሚገኝ ገንዘብ ሲደጎሙ ኖረዋል፡፡ እስላማዊ ፋይናንስን አዲስ የሚያደርገው ነገር ቢኖር ዘካትን መጠነ ሰፊ በሆነ መንገድ መሰብሰብ ማስቻሉና የሚሰበሰበውን ገንዘብ ለማሰባሰብና ለማሰራጨት የሚያስችል የተማከለ አሠራር መዘርጋቱ ነው፡፡ ይህ የተማከለ አሠራር ደግሞ ያለ ጥርጥር ቁርጠኛ በሆኑ እስላማውያን የሚመራ ይሆናል፡፡ እስላማዊ ምርቶችን የሚያቀርቡት ባንኮች እያንዳንዳቸው 2.5% ዘካት የሚያወጡ ሲሆን በ75 አገራት ውስጥ ከሚገኙት 400 ከሚሆኑት በትሪሊየን የሚቆጠር ዶላር ከሚያንቀሳቅሱት ባንኮች የሚዋጣው ገንዘብ መጠን የትየለሌ ነው፡፡”[35]
ስለዚህ እስላማዊ ባንኮች ለሽብር የሚውል ገንዘብ መጠን እንዲያድግ ምክንያት ይሆናሉ፡፡
7. እስላማዊ ባንኮች ግልፀኝነት ስለሚጎድላቸው ለሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ማጭበርበር የተጋለጡ ናቸው
የእስላማዊ ባንኮች አሠራር ውስብስብ መሆኑ በብዙ መንገዶች ለብልሹ አሠራሮች ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡ ኧል-ገማል የተሰኙት ሊቅ እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ፡-
“እስላማዊ ባንኮች በሚያበድሩበት ወቅት ወለድን ለማድበስበስ ሲባል በሸቀጥ ወይንም በንብረት ሽያጭ መልክ የሚቀበሉት ትርፍ የፋይናንስ ወንጀሎችን የሚፈፅሙ ሰዎች ከሚጠቀሙት የማምታታት ስልት ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል፡፡ የፋይናንስ ወንጀል ፈፃሚዎች ተመሳሳይ መንገዶችን የመጠቀም ልምድ ስላላቸው እስላማዊውን የሸሪኣ ፋይናንስ በመጠቀም ወንጀል መፈፀም በእጅጉ ይቀላቸዋል፡፡”[36]
አንድ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) የተዘጋጀ ጽሑፍ “የእስላማዊ ፋይናንስ አሠራር ውስብስብነት ለሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ተጋላጭ የመሆኑ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር አድርጎታል” በማለት ያስጠነቅቃል፡፡[37] በእስላማዊ ፋይናንስ አማካይነት ሊፈጠር የሚችለውን ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ለሽብርተኝነት የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ በተመለከተም የተደረገው ጥናት እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑንም ይጠቁማል፡፡[38] ይህ ለሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ተጋላጭነት መድረሻው በማይታወቀው ዘካት ላይ ታክሎ የሚፈጥረውን አደገኛ ሁኔታ ማሰብ አያዳግትም፡፡
8. በእስላማዊ ፋይናንስ አጠቃቀም ምክንያት የሚፈጠረውን አለመግባባት የሚዳኘው ማን ነው?
የእስላማዊ ፋይናንስ ምርቶች ብዙ ጊዜ በሸሪኣ አማካሪዎች የሚታገዙ ሲሆን እነዚህ አማካሪዎች ምርቱ ከሸሪኣ ሕግ ጋር መስማማት አለመስማማቱን ይወስናሉ፡፡ በምርቶቹ አጠቃቀም ዙርያ አለመግባባት ሲፈጠር አማካሪዎችን ማማከር ግዴታ ስለሚሆን ውጤቱ ሙስሊም ኤክስፐርቶችን የዳኝነት ሥልጣን የሚያጎናፅፍ ይሆናል፡፡[39] ሙስሊም አማካሪዎች ለእስላማዊ ፋይናንስ ምርቶች ምን ዓይነት ፈንድ ተቀባይነት እንዳለው ሲወስኑ አቅራቢዎች ችግር ላይ ሊወድቁ ይችላሉ፡፡
ሕጋዊ ክርክር ቢነሳ ሙስሊም አማካሪዎች ከአገሪቱ ሕግ ይልቅ የሸሪኣ ሕግ ጥቅም ላይ እንዲውል ጥያቄ ሊያቀርቡ ይችላሉ፤ ወይንም ደግሞ በየትኛውም ውሳኔ ላይ ድምፀ ተአቅቦ በማድረግ ደስ ያልተሰኙበትን የትኛውንም የፍርድ ቤት ውሳኔ ሊያደናቅፉ ይችላሉ፡፡ ይህ የአገሪቱን ሕግ የበላይነት በመፈታተን የሸሪኣ ሕግ የበለጠ ጠንካራ ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረውና በሕግ ሥርዓታችን ውስጥ ሰርጎ በመግባት እንዲደላደል ያስችለዋል፡፡ በእስላማዊ ፋይናንስን ምክንያት በሚነሱት አለመግባባቶች ረገድ ሙስሊም ሊቃውንት ያላቸውን ሚና በተመለከተ ብዙ ዓይነት ውስብስብ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡
9. እስላማዊ ፋይናንስ በውስብስብነቱ እንዲሁም ለግብይት በሚጠይቀው ከፍ ያለ ዋጋ ምክንያት ሙስሊሞችን ለችግር ይዳርጋል
ቁርአን ወለድን ይከለክላል ከሚለው የአክራሪዎች ትርጓሜ ጋር ስሙሙ ለማድረግ ሲባል የእስላማዊ ፋይናንስ ምርቶች ከተለመደው የፋይናንስ ሥርዓት ምርቶች ይልቅ ውስብስብ ይሆናሉ፡፡ ይህ ተጨማሪ ውስብስብነት ደግሞ ተጨማሪ ወጪን ይጠይቃል፡፡ ኧል-ገማል እንዲህ ይላሉ፡- “የዘመናችን እስላማዊ ፋይናንስ ለደንበኞቹ የረባ ኢኮኖሚያዊ ዕሴት ባልጨመረበት ሁኔታ እንዲሁ በባዶ ሜዳ የግብይት ዋጋን በማናር የኢኮኖሚ አቅምን ያዳክማል፡፡”[40] ይህ ወጪ በደንበኞች ትከሻ ላይ የሚጫን ሲሆን ወደ ኋላ ይጎትታቸዋል፡፡ ስለዚህ እስላማዊ ፋይናንስ በኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረውን መጓተት ማስቀረት አይቻልም፡፡ ኧል-ገማል እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ፡-
“የዘመናችን የፋይናንስ ሥርዓት ከእስላማዊ ሕግ ጋር እንዲስማማ ለማድረግ ጥረት በሚደረግበት ወቅት በቅድመ ሥልጣኔ ዘመናት የነበሩትን የስምምነት ውል ፎርሞች ስለምንጠቀም ለአላስፈላጊ መጓተት እንዳረጋለን፡፡ ይህ ደግሞ ጥንታዊው የእስልምና የሕግ ሥርዓት በተጠነሰሰበት ወቅት የነበረውን ዋና ዓላማ እንኳ የሚፃረር ይሆናል፡፡”[41]
ኧል-ገማል እየነገሩን ያሉት እስላማዊ የውል ስምምነት ሕግጋት መጀመርያ ሲጠነሰሱ አላስፈላጊ መጓተትን ለማስቀረት ታልመው የነበረ ሆኖ ሳለ አሁን ደግሞ የተሻለ ሥልጣኔ ላይ በመድረሳችን ምክንያት ፈጣን አካሄዶችን መጠቀም ስንችል ጥንታዊ ወደሆነው የተጓተተ አካሄድ መመለሳችን ጥንታዊያን ሕግጋቱ ሲቀረፁ ከነበረው ነገሮችን የማሳለጥ ዓለማ ጋር እንደሚጣረስ ነው፡፡ ሙስሊሞች እስላማዊውን ፋይናንስ መጠቀማቸው ለተጨማሪ ወጪና የጊዜ ብክነት ይዳርጋቸዋል፤ እናም የተለመደውን የፋይናንስ ሥርዓት ከሚጠቀሙት ሰዎች አኳያ ወደ ኋላ ይጎትታቸዋል፡፡
10. እስላማዊ ፋይናንስ በአብዛኞቹ ሙስሊሞች ዘንድ ድጋፍ የለውም
ዘመንኛው የአክራሪዎች እስላማዊ ፋይናንስ ፅንሰ ሐሳን ከመጠንሰሱ በፊት ምንም ዓይነት የተፈላጊነት ጥያቄ አልነበረም፡፡ ሙስሊሞች ለክፍለ ዘመናት የተለመዱትን የፋይናንስ ሥርዓት ምርቶች በደስታ ይጠቀሙ ነበር፡፡ ኧል-ገማል እንደተናገሩት፡- “በእርግጥ እስላማዊ ፋይናንስ በዋናነት በአቅርቦት ላይ የተመሠረተ ኢንደስትሪ ነበር፡፡ በሸሪኣ ዳኝነት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ የሕግ ባለሙያዎች የኢንደስትሪውን ደንበኞች ለማብዛት በተለያዩ ስብሰባዎችና የሕትመት ውጤቶች አማካይነት ተዘዋዋሪ ማስታወቂያዎችን የሚሠሩለት ሲሆን ሙስሊሞች የተለመደውን ፋይናንስ ከመጠቀም እንዲታቀቡ ይጎተጉቷቸዋል፡፡”[42] አብዛኞቹ ሙስሊሞች እስላማዊ ፋይናንስ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ስለሚያስተውሉ በዚህ አታላይና ጎታች የአክራሪዎች ሥርዓት ውስጥ መሳተፍ አይፈልጉም፡፡ ቲሙር ከራን እንዲህ ሲሉ ማስረጃዎችን ይጠቅሳሉ፡- “እስላማዊ ባንኮች ከተለመዱት ባንኮች ጋር ጎን ለጎን ሆነው በሚሠሩባቸው ቦታዎች የሙስሊሞችን ተቀማጭ ገንዘብ የሚጋሩት በሃያ ከመቶ ብቻ ነው፤ በአንዳንድ ሙስሊም አገራት እንዲያውም እስከ አንድ ከመቶ ያህል ዝቅ ብለው ይታያሉ፡፡”[43] ሱኬዶ በበኩላቸው በ2004 ዓ.ም. የተሠራን አንድ ዳሰሳዊ ጥናት በማጣቀስ 75 ከመቶ የሚሆነው የእንግሊዝ ሕዝበ ሙስሊም ለሸሪኣ ፋይናንስ ምንም ግድ ያልነበረውና ጥያቄም ማቅረብ የማይፈልግ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ እንዲያውም 83 ከመቶ የሚሆኑት ሙስሊሞች በሸሪኣ ፋይናንስ አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ አላቸው፤ ከሊቃውንቶቻቸው ጋርም አይስማሙም፡፡[44] በ2013 ዓ.ም. የእንግሊዝ እስላማዊ ባንክ ባደረገው ጥናት መሠረት ሸሪኣ ፋይናንስን እየተጠቀሙ የሚገኙት 36 ከመቶ የሚሆኑት ሙስሊሞች ብቻ ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ እስላማዊ ባንክ በብቸኝነት የሚጠቀሙት 9 ከመቶ ብቻ ናቸው፡፡[45] አብዛኞቹ ሙስሊሞች መደበኛ የፋይናንስ ምርቶችን መጠቀማቸውን መቀጠላቸው ሙስሊሞች የመደበኛ ፋይናንስ ምርቶችን ከመጠቀም እንደተከለከሉና ሸሪኣዊ ባንክ በእጅጉ እንደሚያስፈልጋቸው የሚለፍፉትን አክራሪዎች ሰበካ ውድቅ ያደርጋል፡፡
ማጠቃለያ
እስላማዊ ፋይናንስ በዘመንኛ የአክራሪዎች ቁርአን ትርጓሜ ላይ የተመሠረተ ሲሆን ሆን ብሎ ሌላውን የፋይናንስ ሥርዓት ለማናጋት የታለመ አታላይ ሥርዓት ነው፡፡ ከእስላማዊ ፋይናንስ በስተጀርባ የሚገኘው ሐሳብ ተፎካካሪ የፋይናንስ ሥርዓትን መፍጠርና የአክራሪ እስልምናን ተፅዕኖ በፋይናንሱ ዓለም ማንሰራፋት ነው፡፡ ምዕራባውያንና የአገራችን የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም መንግሥታት ይህ ሥርዓት እንዲያብብ ከመፍቀድም አልፈው እንደ ትክክለኛው የእስልምና ወኪል በመቁጠር ማበረታታቸውና ተቀባይነትን እንዲያገኝ ማገዛቸው አስገራሚ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ያሳዩት ግድ የለሽነትና ሞኝነት የማይታመን ነው፡፡ ብቸኛው መልካም ዜና ከባንኮችና ከመንግሥታት አጋፋሪነት በተጻራሪ አብዛኞቹ ሙስሊሞች ለዚህ ሥርዓት ቦታ አለመስጠታቸው ነው፡፡ እነዚህ ለዘብተኛ ሙስሊሞች በእስላማዊ ፋይናንስ ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ከአክራሪዎች ጋር በመግጠም ራሳቸውንም ሆነ ኢኮኖሚውን እንዲጎዱ ከማበረታታት ይልቅ መደበኛውን የፋይናንስ ሥርዓት እንዲጠቀሙ ማበረታታት ያስፈልገናል፡፡ ትክክለኛውን የእስላማዊ ፋይናንስ ምንነት በመረዳት አታላይ የሆነውን ሥረ መሠረቱን ለማጋለጥ ጊዜው አሁን ነው፡፡ የአገራችንም መሪዎች የጥቂት ጯኺዎችን ድምፅ የብዙሃን ድምፅ በማስመሰል ከማስተጋባት ይልቅ የአብዛኛውን ሕዝበ ሙስሊም የልብ ትርታ ማድመጥ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በመሰል ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ አገሪቱን ለአክራሪዎች አጀንዳ አሳልፎ ከመስጠት በፊትም በጉዳዮቹ ላይ በቂ ዕውቀት ያላቸውን ገለልተኛ ኤክስፐርቶች ማማከር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ዛሬ እንደ ዋዛ የሚገቡት ቃልና የሚወስኑት ውሳኔ ነገ አገሪቱ ልትወጣው የማትችለው ጫና ውስጥ ሊከታት ይችላል፤ በታሪክም ያስወቅሳል፡፡
ጌታ እግዚአብሔር ለመሪዎቻችን ማስተዋልን ይስጣቸው፤ አሜን፡፡
—————
[1] “UK Excellence in Islamic fnance,” (London: UK Trade and Investment, 2014). https://www.gov.uk/government/uploads/system/uploads/attachment_data/fle/367154/UKTI_UK_Excellence_in_Islamic_Finance_Reprint_2014_Spread.pdf
[2] The UK: Leading Western Centre of Islamic fnance,” (London: TheCityUK, 2105). https://www.gov.uk/government/uploads/system/uploads/attachment_data/fle/367154/UKTI_UK_Excellence_in_Islamic_Finance_Reprint_2014_Spread.pdf
[3] Ibid.
[4] Patrick Sookhdeo, Understanding Shari’a Finance: The Muslim Challenge to Western Economics (Isaac Publishing, 2008), 9-12.
[5] Timur Kuran, Islam & Mammon (Princeton University Press, 2006), 83.
[6] Mahmoud El-Gamal, Islamic fnance: Law, Economics, and Practice (Cambridge University Press, 2009), 137.
[7] Sookhdeo, Understanding Shari’a Finance: The Muslim Challenge to Western Economics, 13.
[8] M. Raquibuz Zaman, “Usury (Riba) and the Place of Bank Interest in Islamic Banking and Finance,” International Journal of Banking and Finance 6, no. 1 (2008): 2.
[9] Zaman, “Usury (Riba) and the Place of Bank Interest in Islamic Banking and Finance,” 2-3.
[10] Ibid., 3-6
[11] “UK Excellence in Islamic fnance,” 7.
[12] Kuran, Islam & Mammon, 15
[13] Ibid., 16-17
[14] Muhammad Saleem, Islamic Banking – a $300 Billion Deception (Xlibris, 2005), 68-69.
[15] El-Gamal, Islamic fnance: Law, Economics, and Practice, 2.
[16] Ibid.
[17] “Interest” and the Paradox of Contemporary Islamic Law and Finance,” Fordham International Law Journal (2003): 1.
[18] http://aaoif.com/members-2/?lang=en
[19] Positions held by Hussain Kureshi, 18 August, 2013, http://islamicfnancialsystems1.blogspot.co.uk/2013/08/mufti-taqi-usmani.html
[20] Taqi Usmani, Islam and Modernism, trans. Dr. Mohammed Swaleh Siddiqui (New Delhi, India: Adam Publishers and Distributors, 2006).
[21] http://www.saneworks.us/uploads/application/40.pdf
[22] Usmani, Islam and Modernism, 131.
[23] Sookhdeo, Understanding Shari’a Finance: The Muslim Challenge to Western Economics, 81-88.
[24] “Shariah, Law and ‘Financial Jihad’: How Should America Respond?,” (McCormick Foundation, 2009). http://www.saneworks.us/uploads/application/49.pdf
[25] http://humanevents.com/2005/09/22/fnancial-jihad/
[26] http://news.usc.edu/20744/Conversation-With-Timur-Kuran/
[27] Kuran, Islam & Mammon, 98.
[28] Robert Spencer, Stealth Jihad: How Radical Islam Is Subverting America without Guns or Bombs (Washington: Regnery Publishing, 2008), 185-86.
[29] Michael Nazir-Ali, “Islamic Law, Fundamental Freedoms, and Social Cohesion: Retrospect and Prospect,” in Shari’a in the West, ed. R.J. Ahdar and N. Aroney (Oxford: Oxford University Press, 2010), 83.
[30] Kuran, Islam & Mammon, 62.
[31] http://www.freerepublic.com/focus/news/666056/posts
[32] https://uk.answers.yahoo.com/question/index?qid=20100205104923AAh862S
[33] Sookhdeo, Understanding Shari’a Finance: The Muslim Challenge to Western Economics, 42.
[34] Jean-Charles Brisard, “Terrorism Financing: Roots and Trends of Saudi Terrorism Financing,” (Report prepared for the President of the Security Council, United Nations, 2002), 3.
[35] Alex Alexiev, “Islamic fnance or Financing Islamism?,” (Center for Security Policy, 2007), 12-13.
[36] El-Gamal, Islamic fnance: Law, Economics, and Practice, 176
[37] Nadim Kyriakos-Saad et al., “Islamic fnance and Anti-Money Laundering and Combating the Financing of Terrorism (Aml/Cft),” in IMF Working Paper (2016), 9.
[38] Ibid., 8.
[39] Michael Nazir-Ali, “The Challenges of Islamist Ideology to America’s Founding Principles,” Backgrounder, no. 2430 (2010). http://report.heritage.net/bg2430
[40] El-Gamal, Islamic fnance: Law, Economics, and Practice, 190.
[41] Ibid., xii.
[42] Ibid., 190.
[43] Kuran, Islam & Mammon, 73.
[44] Sookhdeo, Understanding Shari’a Finance: The Muslim Challenge to Western Economics, 78-79.
[45] https://www.alrayanbank.co.uk/useful-info-tools/about-us/latest-news/jan-dec-2014/majority-of-non-muslim-uk-consumers-believe-that-islamic-finance-is-relevant-to-all-faiths/
በፒዲ ኤፍ ለማውረድ እዚህ ጋ ይጫኑ