መንፈስ ቅዱስ

 


‹እስታር ዋርስ› የተሰኘው ፊልም ከተለቀቀ ወዲህ “ያ ኃይል ካንተ ጋር ይሁን” የሚለው በፊልሙ ውስጥ የሚገኘው “ባርኮት” የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህም በሕይወት ፈተናዎች ወቅት አብሮ በመሆን ኃይልን የሚሰጥ ማንነት አልባ የሆነ ኃይል ለማለት ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ብዙ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስን የሚያስቡት እንደዚህ ነው፡፡ ለእነርሱ መንፈስ ቅዱስ ሕይወታቸው ላይ በተወሰነ መንገድ ተፅዕኖ የሚያደርግ ሚስጥራዊ ዓይነት “ኃይል” ብቻ ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ማንነትና አሠራር መተንተን ከባድ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን በቅዱስ መንፈሱ በኩል መረዳ ያለው ጥቅም እርሱን ለማወቅ ከምንከፍለው ዋጋ ጋር ሲስተያይ በጣም ይልቃል፡፡

መንፈስ ቅዱስ ማነው? ይህ የእግዚአብሔር ሌላኛው ስም ብቻ ነውን? ኃይል ነገር? ማንነት አልባ ኃይል? የተነጠለ ማንነት? መንፈስ ቅዱስ ልክ እንደ ሥላሴ ፅንሰ ሐሳብ ሁሉ ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ (በእርግጥ ከሞላ ጎደል ኑፋቄዎች ሁሉ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሲነሳ ግራ ይገባቸዋል፤ አምላክነቱን ይክዳሉ፡፡)

እንደ መታደል ሆኖ የእግዚአብሔርን ፈቃድና እውነት የሚገልጥልን የቃሉ ብርሃን አለን፡፡ በተለይም ስለ መንፈስ ቅዱስ ማንነት ለመረዳት ይህ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በዚህ የታሪክ ዘመን እግዚአብሔር ከሰብዓዊ ሕዋሶቻችን የተሰወረ ነው፡፡  ነገር ግን የማይታይ ቢሆንም ሕልውናው እውን ስለሆነ በጉዳዮቻችን ውስጥ እየገባ ይሰራል፡፡ ነፋስ የማይታይ ቢሆንም ልንገልፀውና ውጤቱን ልንመለከት እንችላለን፡፡ በተመሳሳይ መንገድ መንፈስ ቅዱስን በዓይናችን ማየት ባንችልም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልናየውና በአማኞች ሕይወት ውስጥ የሚሠራውን ሥራ ተመልክተን ልንመሰክር እንችላለን (ዮሐ. 3፡5-8)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስን የሚገልፅበትን መንገድ በማየት እግዚአብሔርን የበለጠ ልናውቀው እንችላለን፡፡ 

የመንፈስ ቅዱስ አምላክነትና ማንነት

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔርም ሆነ ስለ መንግሥቱ ተከታታይና ሰፊ የሆነ መደበኛ ሐተታ እንደማይሰጥ ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በፍጥረቱና በሕዝቡ መካከል የሠራውን ሥራ በሙሉ መዝግቦ የያዘ መጽሐፍ አይደለም፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ በግልፅ ያስተምረናል ነገር ግን ስለ መንፈስ ቅዱስ አምላክነትና አካልነት የሚያስረዳ ሰፊ ሐተታ የለውም፡፡ በዚህ ፋንታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፍት የመንፈስ ቅዱስን አምላክነትና አካል መሆን እንደ ቅድመ ግንዛቤ በመያዝ እግረ መንገዳቸውን ገልፀው ያልፋሉ፡፡

በሥላሴ ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ድርሻ

በብዙ ባሕሎች ውስጥ አንድን ሰው ለመጀመርያ ጊዜ ሲተዋወቁት ስለ ቤተሰቡ መጠየቅ የተለመደ ነው፡፡ የአንድን ሰው ቤተሰብ ስሞች በማወቅ የተዋወቅነው ሰው በማሕበረሰቡ ውስጥ ያለውን ቦታና አውድ የማወቅ ዕድል ይኖረናል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ መንፈስ ቅዱስ ከሌሎች የሥላሴ አካላት ጋር ያለውን ሕብረት በማወቅ የእርሱን ማንነት እንድናውቅ ይረዳናል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ እግዚአብሔር አብ የማቀድን ሥራ በቀዳሚነት እንደሚሠራ ማስተዋል እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር ወልድ የሆነው ኢየሱስ ደግሞ የአብን ዕቅድ ይፈፅማል፡፡ መከራን እንደሚቀበል አገልጋይና ነፃ አውጪ እንደሆነ ንጉሥ ያለው መሲሃዊ አገልግሎቱ የማንነቱ ማዕከላዊ ጉዳይ ነው፡፡ በመጨረሻም የመንፈስ ቅዱስ ድርሻ ዕቅዱ በአማኞች ሕይወት ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡

እነዚህን የሥላሴ ድርሻዎች በደህንነት ሥራ ውስጥ ማየት እንችላለን፡፡ አብ በማቀድ ልጁን ላከ፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በመሞትና ከሞት በመነሳት ዕቅዱን ፈፀመ፡፡ መንፈስ ቅዱስም ሰዎችን ወደ ክርስቶስ በማምጣትና በውስጣቸው በመኖር የደህንነትን ውጤቶች በሕይወታቸው ውስጥ ይተገብራል፡፡

የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶች

አንዳንድ ጊዜ ከሰዎች ጋር ጥሩ ሕብረት ለመፍጠር ተመራጩ መንገድ የሚሠሩትን ሥራ ማወቅ ነው፡፡ ተግባር ከንግግር ይልቅ ይጮኻል የሚለው ብሂል እውነት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ፋንታ ብዙ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ እነዚህንም አገልግሎቶች መመልከት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ለማወቅ ይረዳናል፡፡

መጀመርያ ንስሐ ስንገባና የእግዚአብሔርን የደህንነት ስጦታ ስናምን መንፈስ ቅዱስ ብዙ ትሩፋቶችን ይሰጠናል፡፡ ቲቶ 3፡5 እንዲህ ይላል፡- “እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፡፡” ዮሐ. 3፡3-8 እና ኤፌ. 2፡4-5 ስለዚህ የአዲስ ልደት አገልግሎት ይናገራሉ፡፡ መጀመርያ ደህንነትን ስንቀበል መንፈስ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ መስዋዕትነት ይመሰክርልናል ለእግዚአብሔርም ዓላማ ይለየናል (ዕብ. 10፡13-14)፡፡ በውስጣችን ይኖራል፣ በኛ ፋንታ ይማልዳል፣ መንፈሳዊ ስጦታዎችንም ይሰጠናል (ሮሜ 8፡9፣ ኤፌ. 1፡13-14፣ ሮሜ 8፡26-27፣ 1ቆሮ. 12፡7-11)፡፡ መንፈስ ቅዱስ ደህንነትን ስንቀበል እነዚህን ሥራዎች በኛ ፋንታ ይሠራል፡፡

ሌሎች የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶች ከእርሱ ጋር ስንስማማ ብቻ በአማኞች ሕይወት ውስጥ የሚፈፀሙ ናቸው፡፡ በተገዛንለትና ኃይሉን በተለማመድን ቁጥር መንፈስ ቅዱስ ስለ ኃጢአት እንደሚወቅስና እውነትን እንደሚያስተምረን ዮሐንስ ይናገራል (ዮሐ. 16፡8-11፣ 13-26)፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በፈለግን ቁጥር ፀጋውን በሕይወታችን ውስጥ በመግለጥ ይመራናል፣ ኃይል ያስታጥቀናል፣ ደግሞም ይሞላብናል (ገላ. 5፡16-18፣ ሐዋ. 1፡8፣ ኤፌ. 5፡18)፡፡ ይህም ማለት መንፈስ ቅዱስ እኛን በመቀደስ ሒደት በሕይወታችን ላይ ተፅዕኖ እያመጣ ከኛ ጋር ይራመዳል ማለት ነው (ዕብ. 10፡13-14)፡፡

መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ሕይወት ውስጥ ከመሥራት ባለፈ “ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል” (ዮሐ. 16፡8-11)፡፡ በመጨረሻም መንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ እስትንፋስ ሆኖ ጸሐፊያንን በማነሳሳት ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲጽፉ ነድቷቸዋል (2ጢሞ. 3፡16፣ 2ጴጥ. 1፡20-21)፡፡

መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ሕይወት ውስጥ በመኖሩና በመንፈስ ቅዱስ ሙላት መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡

መንፈስ ቅዱስ በአማኝ ሕይወት ውስጥ መኖር የሚጀምረው ደህንነትን ሲቀበሉ ነው፡፡ ይህም ማለት መንፈስ ቅዱስ ወደ አማኝ ሕይወት ይገባል ማለት ነው (ሐዋ. 2፡38፣ ሮሜ 8፡9፣ 1ቆሮ. 12፡13፣ ኤፌ. 1፡13-14)፡፡ ይህ ከመቅፅበት የሚሆን የአንዴና የመጨረሻ ክስተት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከላይ የተጠቀሰውን ዓላማ ለመፈፀም ማለትም አማኞችን ለቅዱስ ዓላማ ለመለየት በውስጣቸው ይኖራል (ዕብ. 10፡13-14)፣ ያትማቸዋል (ኤፌ. 1፡13-14)፣ ይማልዳል (ሮሜ. 8፡26-27)፣ ስጦታዎችን ይሰጣል (1ቆሮ. 12፡7-11)፣ ወዘተ፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ሙላት የሚከሰተው አማኝ ከዳነ በኋላ ማንነቱንና ፈቃዱን በሙሉ ለእግዚአብሔር ሲሰጥ ነው፡፡ አማኝ ራሱን ሲሰጥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈፀም ይችል ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ኃይልን ይሰጠዋል፡፡ አማኞች ሁሉ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ለመገዛት በየዕለቱ ትግል ስለሚገጥማቸው የመንፈስ ቅዱስም ሙላት በየዕለቱ በመደጋገም መፈፀም ይኖርበታል (ሐዋ. 4፡23-41)፡፡ 

ኤፌ 5፡18 “መንፈስ ይሙላባችሁ…” ይላል፡፡ “ይሙላባችሁ” የሚለው የግሪክ ግሥ የአሁን ጊዜና የማያቋርጥ ሒደትን ስለሚያመለክት “ደግሞ ደጋግሞ መሞላት” የሚል ትርጉም ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ይህ ትዕዛዝ አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ደግመው ደጋግመው እንዲሞሉ ይነግራቸዋል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መሞላትን (በመንፈስ መመላለስን) መረዳት በክርስትና ሕይወት ለማደግ ወሳኝ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ደጋግሞ መሞላትን የተለማመደ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ጥብቅ ቁርኝት ማድረግ፣ ትሁት የሆነ መንፈስና ለመማር ዝግጁ የሆነ ልብ አስፈላጊ መሆኑን ያውቃል፡፡

ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስን ማንነትና በሕይወታችን ውስጥ የሚሠራውን ሥራ እያሰብን በትህትና ማመስገን ያስፈልገናል፡፡ እርሱ በሕይወታችን ውስጥ የሚሠራ፣ እርሱን ለመታዘዝ ጥረት ስናደርግ የሚረዳን ማንነት ያለው አምላክ ነው፡፡ ቃሉን በማንበብና በጸሎት ልንፈልገው ይገባል፡፡ በዕድሜ ዘመናችንም ከእርሱ ጋር በመተባበር መኖር ያስፈልገናል፡፡

ማጠቃለያ

 

አምላካችን እንደ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንዴት ራሱን እንደገለጸ በማጥናት ይበልጥ ልናውቀው እንችላለን፡፡

 የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፍት የመንፈስ ቅዱስን አምላክነትና አካል መሆን እንደ ቅድመ ግንዛቤ በመያዝ እግረ መንገዳቸውን ገልፀው ያልፋሉ፡፡
 መንፈስ ቅዱስ ከሌሎች የሥላሴ አካላት ጋር ያለውን ሕብረት ማወቅ የእርሱን ማንነት እንድናውቅ ይረዳናል፡፡
 መንፈስ ቅዱስም ሰዎችን ወደ ክርስቶስ በማምጣትና በውስጣቸው በመኖር የደህንነትን ውጤቶች በሕይወታቸው ውስጥ ይተገብራል፡፡
 አንዳንድ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶች ከመቅፅበት በአማኝ ሕይወት ውስጥ የሚተገበሩ ናቸው፡፡
 ሌሎች የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶች ከእርሱ ጋር ስንስማማ ብቻ በአማኞች ሕይወት ውስጥ የሚፈፀሙ ናቸው፡፡
 በትህትና እያመሰገንን ከእርሱ ጋር በመተባበር መኖር ያስፈልገናል፡፡

 የመንፈስ ቅዱስ አምላክነት

1. እግዚአብሔር ተብሏል ሐዋ. 5፡3-4፣ 1ቆሮ. 3፡16
2. እግዚአብሔር ባሕርያት እንዳሉት ተነግሯል

ሕይወት ሰጪ፡ ሮሜ 8፡2

እውነት፡ ዮሐ. 16፡13፣ 1ዮሐ. 5፡6

ፍቅር፡ ሮሜ 15፡30

ቅዱስ፡ ኤፌ. 4፡30

ዘላለማዊ፡ ዕብ. 9፡14

ምሉዕ በኩላሄ (በሁሉም ቦታ የሚገኝ)፡ መዝ. 139፡7-10

አእማሬ ኩሉ (ሁሉን አዋቂ)፡ ዮሐ. 14፡26፣ 16፡12-13 

ከሃሊ ኩሉ (ሁሉን ቻይ)፡ ሉቃ. 1፡35፣ ኢዮ. 33፡4፣ ዘካ. 4፡6

 እግዚአብሔር የሚሠራቸውን ሥራዎች እንደሚሠራ ተነግሯል 

መፍጠር፡ ዘፍ. 1፡2፣ ኢዮ. 33፡4

ዳግም ልደት፡ ቲቶ 3፡5

ቅዱሳት መጻሕፍትን መግለጥ፡ 2ጴጥ. 1፡21

ሙታንን ማስነሳት፡ ሮሜ 1፡4

በክርስቶስ ልደት ውስጥ ተሳተፈ፡ ሉቃ. 1፡35

መቀደስ፡ 2ተሰ. 2፡13

1. የመንፈስ ቅዱስ ንግግርና ተግባር የእግዚአብሔር ንግግርና ተግባር መሆናቸው ተነግሯል

ኢሳ. 6፡8-10 ከሐዋ. 28፡25-27 ጋር

ዘጸ. 16፡7 እና መዝ. 95፡8-11 ከዕብ. 3፡7-9 ጋር

ዘፍ. 1፡27 ከኢዮ. 33፡4 ጋር

ኤር. 31፡31-34 ከዕብ. 10፡15-17 ጋር አነፃፅራችሁ ተመልከቱ፡፡

1. መንፈስ ቅዱስ ከሌሎች የሥላሴ አካላት ጋር እኩል ተጠቅሷል

ስለ ጥምቀት ትዕዛዝ፡ ማቴ. 28፡19

በቡራኬ፡ 2ቆሮ. 13፡14

በሰላምታ፡ 1ጴጥ. 1፡2

መንፈስ ቅዱስ አካል ነው (ማንነት አለው)

1. የአካል ባሕርያት እንዳሉት ተገልጿል 

ሀ. ዕውቀት

1ቆሮ. 2፡10-11፡ የእግዚአብሔርን ምስጢር ያውቃል ይመረምራል

ሮሜ 8፡27፡ አሳብ አለው

1ቆሮ. 2፡13፡ ያስተምራል

ለ. ስሜቶች

ኤፌ. 4፡30፡ ያዝናል

ሮሜ 15፡30፡ መውደድ ይችላል             

ሐ. ፈቃድ

1ቆሮ 12፡11፡ የጸጋ ስጦታዎችን ያከፋፍላል

ሐዋ. 16፡6-11፡ ይመራል

ሐዋ. 15፡28፡ ሐሳብ ይሰጣል

1. መንፈስ ቅዱስ ሲጠቀስ ማንነትን አመልካች ተውላጠ ስም ጥቅም ላይ ውሏል

ሀ. ዮሐ. 16፡14፣ 15፡26፣ 16፡7-8፣ 1ቆሮ. 12፡8-11፣ ሮሜ 8፡16፣26፣ ኤፌ. 1፡14

ለ. “መንፈስ” የሚለው የግሪኩ ቃል ፆታ አልባ ቢሆንም ከላይ በተጠቀሱት ጥቆች ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በተባዕታይ ተውላጠ ስም ተወክሏል፡፡

 ማንነት ያለው አካል ብቻ ሊፈፅማቸው የሚችላቸውን ሥራዎች ሠርቷል፡፡ (ከታች የተዘረዘሩትን የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎችን የሚገልፁ ቀደም ሲል የተጠቀሱ ጥቅሶችን ተመልከቱ፡፡)

ይመረምራል፣ ያውቃል፣ ይናገራል፣ ይመሰክራል፣ ይገልጣል፣ ያሳምናል፣ ያስተምራል፣ ያዛል፣ ይሠራል፣ ይንቀሳቀሳል፣ ይረዳል፣ ይመራል፣ ይፈጥራል፣ ዳግም ልደት ይሰጣል፣ ይቀድሳል፣ ያነቃቃል፣ ይማልዳል፣ የቤተ ክርስቲያንን ሥርኣት ይመራል፣ ተዓምራትን ያደርጋል፣ ሙታንን ያስነሳል፣ ያፀድቃል፣ ወደ እውነት ይመራል፣ ሰዎችን ለአገልግሎት ይጠራል፣ ክርስቶስን ያከብራል፣ ወዘተ.፡፡

1. ሌሎች የሚፈፅሙት ድርጊት ይነካዋል

ሀ. ሰዎች ተቃውመውታል፣ ይፈተናል፣ ይሰደባል፣ ያዝናል፣ ሰዎች ይዋሹታል፣ ይታዘዙታል፣ ያከብሩታል፡፡ (እነዚህን የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች የሚገልፁ ቀደም ሲል የተጠቀሱ ጥቅሶችን ተመልከቱ፡፡)

ለ. ማንነት አልባ ኃይል ብቻ ቢሆን ኖሮ ለነዚህ የሰው ድርጊቶች ስሜት ባልኖረው ነበር፡፡