ድንግል ወይንስ ወጣት ሴት? የዐልማህ ትክክለኛ ትርጉም

ድንግል ወይንስ ወጣት ሴት?

የዐልማህ ትክክለኛ ትርጉም

አንዳንድ ሙስሊም ሰባኪያን ኢሳይያስ 7፡14 ላይ “…ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” በሚለው ጥቅስ ውስጥ “ድንግል” ተብሎ የተተረጎመው “ዐልማህ” የሚለው የእብራይስጥ ቃል “ወጣት ሴት” ተብሎ መተርጎም እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ በነዚህ ወገኖች ሙግት መሠረት “ድንግል” ለሚለው ትክክለኛው የእብራይስጥ አቻ “ቤቱላህ” የሚል በመሆኑ ኢሳይያስ 7፡14ን “ድንግል” ብሎ መተርጎም ስህተት ነው፡፡

ይህ ሙግት በተከታዮቹ ምክንያቶች በእጅጉ የተሳሳተ ነው፡፡

  1. በእብራይስጥ መዝገበ ቃላት መሠረት “ዐልማህ” የሚለው የእብራይስጥ ቃል ወጣት ሴትን የሚያመለክት ሲሆን “ድንግል” የሚለው ከቀጥተኛ ትርጉሞቹ መካከል አንዱ ነው፡፡

Strong’s #5959: `almah (pronounced al-maw’)

feminine of 5958; a lass (as veiled or private):–damsel, maid, virgin.

Brown-Driver-Briggs Hebrew Lexicon:

‛almâh

1) virgin, young woman

1a) of marriageable age

1b) maid or newly married

Part of Speech: noun feminine

Relation: from H5958

ምንጭ፡ https://www.bibletools.net/index.cfm/fuseaction/Lexicon.show/ID/H5959/%60almah.htm

ቃሉ “ድንግል” ተብሎ ሊተረጎም የማይችልበት በቂ ምክንያት እስካልቀረበ ድረስ ተርጓሚዎች ከቃሉ ትርጉሞች መካከል አንዱን መርጠው ቢተረጉሙ በስህተትነት መፈረጅ ተቀባይነት የለውም፡፡

  1. በጥቅሱ ውስጥ የሚገኘው “ዐልማህ” የሚለው ቃል በእብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ደናግላንን ለማመልከት በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ድንግል ያልሆነችን ሴት ለማመልከት አንድም ጊዜ ጥቅም ላይ አልዋለም፡፡ ይህንን በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡-

“There is no instance where it can be proved that ‘almâ designates a young woman who is not a virgin. The fact of virginity is obvious in Gen 24:43 where ‘almâ is used of one who was being sought as a bride for Isaac.”

“ዐልማህ ድንግል ያልሆነችን ወጣት ሴት ለማመልከት [በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ] ጥቅም ላይ የዋለበት አንድም አጋጣሚ መኖሩን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ዘፍጥረት 24፡43 ላይ ዐልማህ የሚለው ቃል ለይስሐቅ ሚስት ትሆነው ዘንድ የተመረጠችውን [ርብቃን] ለማመልከት ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ድንግል መሆንዋ ግልፅ ነው፡፡” (R. Laird Harris, et al. Theological Wordbook of the Old Testament, p. 672.)

የአንድ ቃል ትርጉም የሚወሰነው በዲክሺነሪ ትርጉሙ ብቻ ሳይሆን በአንድ መጽሐፍ ውስጥ ጥቅም ላይ በዋለበት መንገድም ጭምር ነው፡፡ በሁሉም አጋጣሚዎች ድንግል ሴቶችን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሎ በዚህ በአንድ አጋጣሚ ግን “ድንግል” ተብሎ ሊተረጎም የማይችልበት አሳማኝ ምክንያት ሊጠቀስ ይገባል፡፡

  1. በእብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ “ቤቱላህ” የሚለው ቃል ድንግል ያልሆነችን ሴት ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ለምሳሌ ያህል ኢዩኤል 1፡8 ላይ ባል ያላት ሴት “ቤቱላህ” ተብላለች፡፡ ኢሳይያስ 47፡1 ላይ የባቢሎን ሴት “ቤቱላህ” (በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ “ድንግል”) ተብላ ብትጠራም እዚያው ምዕራፍ ቁጥር 8-9 ላይ ባል ያላትና ልጆችን የወለደች መሆኗ ተነግሯል፡፡
  2. የዚህ ሙግት አቅራቢዎች “ዐልማህ” የሚለውን ቃል “ድንግል” ብለው የተረጎሙት ክርስቲያኖች እንደሆኑ በማስመሰል ቢናገሩም ቅሉ ይህንን ቃል “ድንግል” ብለው ወደ ግሪክ የተረጎሙት የመጀመርያዎቹ ተርጓሚዎች ከክርስቶስ ልደት በፊት የኖሩት አይሁድ ሊቃውንት ነበሩ፡፡ ሰብዓው ሊቃናት ከክርስቶስ ልደት በፊት 285-244 ዓ.ዓ. መካከል ባዘጋጁት የግሪክ ትርጉም ውስጥ ይህንን ቃል “ፓርቴኖስ” (ድንግል) ብለው ተርጉመውታል፡፡ እነርሱ ምን የተለየ motive ኖሯቸው ይሆን በዚህ መንገድ የተረጎሙት?

ቃሉ ድንግል ተብሎ መተርጎም የለበትም የሚለው ክርክር ከክርስቶስ ልደት በኋላ መነሳቱ በራሱ የሙግቱ አቅራቢዎች የክርስቶስን ከድንግል መወለድ የማጣጣል እኩይ ዓላማ እንዳላቸው ያመለክታል፡፡ ክርስቶስ ከድንግል መወለዱን እናምናለን የሚሉት ሙስሊም ወገኖች ይህንን የረበናተ አይሁድ የክህደት ክርክር መኮረጃቸው በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡

  1. የጌታ ሐዋርያ ማቴዎስ የሰብዓ ሊቃናትን ትርጉም በማረጋገጥ በወንጌሉ ውስጥ ጠቅሶታል (ማቴ. 1፡23)፡፡ ከእርሱ በኋላ የነበሩትም ክርስቲያን ትውልዶች ይህንኑ ትርጉም ተቀብለው ኖረዋል፡፡ ፀረ-ክርስትና አቋም ያላቸው ረበናተ አይሁድና ሙስሊም ሰባኪያን ከክርስቶስ ሐዋርያትና ከክርስቲያን አበው ጋር እኩል ሚዛን ላይ ሊቀመጡ አይችሉም፡፡
  2. በጥቅሱ ውስጥ እንደተገለፀው የአማኑኤል መወለድ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠ ምልክት ወይም ተዓምር ነው (በእብራይስጥ “ኦት” የሚለው ቃል ምልክትን ወይም ተዓምርን አመልካች ነው)፡፡ ወንድ የምታውቅ ሴት ልጅ መውለድዋ ተዓምር ሊባል አይችልም ነገር ግን የድንግል መውለድ ተዓምር ነው፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች “ዐልማህ” የሚለው የእብራይስጥ ቃል “ድንግል” ተብሎ መተርጎሙ ትክክል ነው፡፡ ትንቢቱም በትክክል የጌታችንን ከድንግል መወለድ የሚገልፅ ነው፡፡

 

መሲሁ ኢየሱስ